ምዕራፍ 20 · 2 ደቂቃ ንባብ · 3 ደቂቃ ማዳመጥ
ሴቶች በወንጌል አገልግሎት
ከሠላሳ ዓመት በፊት ስለ ቅድስና ከሚናገር ሰው ጋር የሚራራ ሰው በአብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ማግኘት በጭንቅ ነበር። እኔ ግን በየዋህነቴ የክርስቲያን አገልጋዮች ጉባኤ ጉዳዬን ይረዳል፣ በጽድቅም ይፈርዳል ብዬ አስቤ ነበር። ይሁን እንጂ ተስፋዬ ከሸፈ።
የሰው ሁሉ እጅ በእኛ ላይ፣ የእኛም እጅ በሰው ሁሉ ላይ እንደ ሆነ መሰማት ቀላል ነገር አይደለም፤ በዚያን ጊዜ በእኔ ላይ የሆነውም እንዲሁ ይመስል ነበር፤ ነገር ግን ኢየሱስ ብቻ ከእኛ ጋር ቢሆን ይህ እንዴት የከበረ ነው! በዚህ ጽኑ ፈተና ውስጥ ወደ እግዚአብሔር ዘወትር መቅረብ ይቻለኝ ነበር፤ እርሱም እንደሚሰማኝ በግልጽ አውቅ ነበር፤ ቢሆንም ቀድሞ የነበረኝ የመንፈስ ሙላት ያለኝ አይመስልም ነበር። ኅብረቱ ይበልጥ የቀረበ በነበረ መጠን፣ ከእግዚአብሔር ጥቂት እንኳ ፈቀቅ ማለት የሚያመጣው ሥቃይ ይበልጥ እንደሚብስ እጅግ አጥብቄ ተረዳሁ። ያልተቋረጠ ኅብረት ሊጠበቅ የሚችለው የሚያነጻው ደም ዘወትር በእኛ ላይ ሲደረግ ብቻ ነው።
ማንንም ማሳዘን ባልፈልግም፣ በመንፈስ ቅዱስ በተመራሁበት መጠን ካልሆነ በቀር ማንንም ደስ ማሰኘት አልቻልሁም። ከሰዎች ሁሉ የተሻሉት እንኳ ሊሳሳቱ እንደሚችሉ፣ ብቸኛውም አስተማማኝ መንገድ ድምፁን በመታዘዜ ነቀፋና ስድብ ቢወድቅብኝም በክርስቶስ ላይ መውደቅ እንደ ሆነ ከቀድሞው ሁሉ ይልቅ አየሁ። የሰው አስተያየት በእኔ ዘንድ ምንም ክብደት አልነበረውም፤ ተልእኮዬ ከሰማይ ነበርና፤ ዋጋዬም በልዑል ዘንድ ነበር።
ለመስበክ ያነሣሣኝ ለአጭር ጊዜ የሚቆይ ግፊት ወይም አልፎ አልፎ የሚመጣ ስሜት ነው ብዬ ማመን አልቻልሁም። በበዓለ ኀምሳ ቀን በኢዩኤል 2:28-29 የተጻፈው መጽሐፍ እንደ ተፈጸመ አነባለሁ፤ በዚያን ጊዜ ወንዶች ብቻ ሳይሆኑ ሴቶችም በመንፈስ ቅዱስ እንደ ተሞሉ በእርግጥ አይካድም፤ የተስፋውን ቃል መፈጸም እየጠበቁ በጸሎትና በምልጃ ከተጉት መካከል ሴቶች እንደ ነበሩ በግልጽ ተጽፎአልና። ሴቶችና ወንዶች በአንድነት ተቈጥረዋል፤ ወንጌልን የመስበክ ኃይል በሴቶች ዘንድ ለአጭር ጊዜ የሚቆይና አልፎ አልፎ የሚመጣ ከሆነ፣ በወንዶችም ዘንድ እንዲሁ መሆን አለበት፤ ሴቶች የትንቢትን ስጦታ አጥተው ከሆነ፣ ወንዶችም አጥተዋል።
አንዲት ሴት መለኮታዊ ጥሪ አለኝ ብትልና በዚህም ላይ ተመሥርታ የተሰቀለውን ቤዛ ጉዳይ በሕዝብ ፊት የመሟገት መብት ብትጠይቅ፣ ከሰማይ የተሰጣትን ማረጋገጫ ስታሳይ — ማለትም ተአምር ስትሠራ — ትታመናለች ተብሎ አንዳንድ ጊዜ ይነገረናል። ወንጌልን የመስበክ መብትን ለማረጋገጥ ይህ አስፈላጊ ከሆነ፣ ወንድሞቼ ማረጋገጫቸውን እንዲያሳዩኝ እጠይቃቸዋለሁ፤ አለዚያ የአገልግሎታቸውን ትክክለኛነት ማመን አልችልም።
ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ «…ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና» ሲል ይህን ክርክር ይቋጨዋል። ፊልጶስ ትንቢት የሚናገሩ፣ ማለትም የሚሰብኩ፣ አራት ሴቶች ልጆች ነበሩት። ጳውሎስ አቂላን ብቻ ሳይሆን ጵርስቅላንም «ረዳቱ»፣ ወይም በግሪኩ እንደ ተጻፈ «አብሮ ሠራተኛው» ብሎ ጠርቷታል። ሮሜ 16:3፤ 2ኛ ቆሮንቶስ 8:23፤ ፊልጵስዩስ 2:25፤ 1ኛ ተሰሎንቄ 3:2። በተለመደው (የእንግሊዝኛ) ትርጉማችን ስለ ፌቤን ሲነገር (ሮሜ 16:1) «የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ» ተብሎ የተተረጐመው ያው ቃል ስለ ቲኪቆስ ሲነገር «መጋቢ» ተብሎ ተተርጕሟል። ኤፌሶን 6:21። ጳውሎስ «እንድታግዛቸው እለምንሃለሁ … በወንጌል ከእኔ ጋር አብረው ተጋድለዋልና» ብሎ ስለ ሴቶቹ ሲናገር፣ ሻይ ከማፍሰስ የበለጠ ነገር እንዳደረጉ ማለቱ በእርግጥ ነው። በአንደኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ አሥራ አንድ ጳውሎስ ወንዶችና ሴቶች በሕዝብ ጉባኤ ትንቢት ሲናገሩ ወይም ሲጸልዩ እንዴት መታየት እንዳለባቸው መመሪያ ይሰጣል፤ ትንቢት መናገርንም ለማነጽና ለመምከር ለማጽናናትም መናገር እንደ ሆነ ይገልጸዋል።
ደግሞም የቅዱሳት ሴቶች አካሄድ ለጾታቸው ሌሎች ምሳሌ እንዲሆን በመጽሐፍ ቅዱስ እንደ ተመዘገበ ልጨምር እወዳለሁ። በክርስትናም የመጀመሪያ ዘመናት ብዙ ሴቶች በሰማዕትነት ደስተኞችና ክቡራን ሆኑ። በኋለኞቹም ዘመናት ሴቶች ስለ ጌታ ኢየሱስ ስም ስደትንና ሞትን እንዴት በክብር፣ እንዴትስ በጀግንነት ተቀበሉ!
እነዚህን እውነታዎች ስመለከት፣ ለእኔ ከተደረገው የበለጠ ተአምር ለእነዚያ ሴቶች እንደ ተደረገላቸው ማየት አልቻልሁም።
ተቃውሞ ቢገጥመኝም ለእግዚአብሔር እየሠራሁ ወጣሁ፤ እርሱም ድካሜን ተቀበለው፣ ባረከውም፤ እስከ ዛሬም በሄድሁበት ሁሉ እንዲሁ አድርጓል። በመታዘዝ እስከ ተመላለስሁም ድረስ፣ ሲኦል ቢቈጣና ክፋቱን ቢያፈስስም እንኳ፣ እርሱ እንዲሁ እንደሚያደርግ አውቃለሁ።
ምዕራፍ 20 ተጠናቋል
ሴቶች በወንጌል አገልግሎት