ምዕራፍ 15 · 2 ደቂቃ ንባብ · 2 ደቂቃ ማዳመጥ
አዲስና ደስ የማያሰኙ መገለጦች
ባሌ የልብ ንጽሕናን ጉዳይ ሁልጊዜ በበጎ ዓይን ይመለከተው ነበር፤ አሁን ግን ይቃወመው ጀመር። በየቀኑ ይበልጥ እያበድሁ እንደ ሆነና ሌሎችንም ወደዚያው እየመራሁ እንደ ሆነ፣ ካላቆምሁም ወደ ቤተ ሰቤ ወይም ወደ እብዶች ቤት እንደሚልከኝ ነገረኝ። አእምሮው በጭፍን አመለካከት እንደ ተያዘ ስለ ተሰማኝ ስለ ልቡ ሁኔታ በቅርበት ጠየቅሁት። ስለ አሳቦቹ አደገኛነትና ስሕተት ከእርሱ ጋር ልከራከር አልሞከርሁም፤ ይልቁንም እግዚአብሔር ነፍሱን በዚያች ሰዓት ቢጠይቀው በጸጋ ያለው ሁኔታው ምን እንደ ሆነ ብቻ ጠየቅሁት። መልስ እንዲሰጠኝ አጥብቄ እስክጠይቀው ድረስ አልመለሰልኝም። ከዚያም፦ «ጁሊያ፣ አንቺ ራስሽን ቅድስት እንደ ሆንሽ እንደምታስቢው እኔ ራሴን ቅዱስ እንደ ሆንሁ ከቶ ማመን የምችል አይመስለኝም» አለ።
እኔም የክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ የማንጻት ኃይል እንዳለው ማመን ቢያቅተው እንኳ፣ በክርስቶስ ቅድስና እንዲያምን አጥብቄ ለመንሁት። ይህን ተስፋ የሚያደርግ ሁሉ እርሱ ንጹሕ እንደ ሆነ ራሱን ያነጻል። አብረን ተንበርክከን ጸለይን፤ ባሌ ጸሎቱን መራ፤ ሲጸልይም በጣም የተነካ ይመስል ነበር። ለእኔ የከበረ ጊዜ ነበር፤ ሆኖም በመካከላችን ሊገለጽ የማይችል አንዳች ነገር ነበር — ጨለማና ረጅም የሆነ ነገር። ወደ እርሱ ስመለከት እነዚህ የገጣሚው ቃላት ወደ እኔ መጡ፦
«እግዚአብሔር ድንቆቹን ሊፈጽም በምሥጢራዊ መንገድ ይሠራል።»
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የባሌን ፊት እንደ ቀድሞው ጥርት ብሎና ግልጽ ሆኖ አይቼው አላውቅም፤ የጨለማው ጥላ ሁልጊዜ በዚያ ነበረና። ይህም ብዙ ጭንቀትና ብዙ ጸሎት አስከተለብኝ። ብዙም ሳይቆይ ለስድስት ወር በባሕር ላይ እንዲሠራ የቀረበለትን ሥራ ተቀበለ፤ የደመወዙን እኩሌታ እኔ እንድቀበል አደረገ። በእንግዶች መካከል ምን ያህል ብቸኛ እንደምሆን በሚገባ እየተረዳሁ፣ ሳልወድ በዚህ ዝግጅት ተስማማሁ። ውድ «ማም» ራይሊ ባትኖር ኖሮ ልቋቋመው ባልቻልሁም ነበር። ትምህርቷና ምሳሌነቷ ለድጋፍ በክርስቶስ ላይ ይበልጥ እንድደገፍ አስተማረኝ። እግዚአብሔር እነዚህን የከበሩ ቃላት ሰጠኝ፦ «በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ።» በእውነት እግዚአብሔር የሁሉን ነገር ፍጻሜ የሚወስን ታላቅ ዳኛ ነው፤ «እርሱ ሕያው ነውና እኔ ደግሞ ሕያው እሆናለሁ።»
ባሌ መርከብ የተሳፈረበት ቀን የብርቱ መከራና የታላቅ ውስጣዊ ፈተና ቀን ነበር። በቅሬታና በክርስቲያናዊ ቻይነት፣ በትዕግሥተኛ ፍቅርም መካከል ያለውን ትክክለኛ መስመር መለየት አስቸጋሪ ሆነብኝ። ሳላስበው ወደ ክፉ እንዳልወድቅ፣ ሁሉንም ነገር ለእግዚአብሔር ክብር ከማዋልም እንዳልከለከል፣ ሁሉን ነገር በየዋህነትና በፍርሃት መንፈስ ለመቀበል የሚያስችል ጥበብ ምንኛ ናፈቅሁ!
በዚህ ደመና በሚመስል ሁኔታ ሥር ሳለሁ የመለኮትን እርዳታ እየለመንሁ መጽሐፍ ቅዱስን ይዤ ወደ እልፍኜ ገባሁ። መጽሐፉን ስከፍት ዓይኖቼ በእነዚህ ቃላት ላይ አረፉ፦ «ፈጣሪሽ ባልሽ ነውና።» ከዚያም የኢሳይያስን አምሳ አራተኛ ምዕራፍ ደጋግሜ አነበብሁ። ከዚያ በፊት ከቶ አይቼው የማላውቅ መሰለኝ። እግዚአብሔርን እያከበርሁ ወጣሁ።
ምዕራፍ 15 ተጠናቋል
አዲስና ደስ የማያሰኙ መገለጦች