ምዕራፍ 16 · 2 ደቂቃ ንባብ · 2 ደቂቃ ማዳመጥ
ለረጅም ዘመን የጠፋ ወንድም ተገኘ
ልጆች ስላልነበሩኝ ባሌ ከሄደ በኋላ ብዙ ትርፍ ጊዜ ነበረኝ፤ ስለዚህ ብዙ ድሆችንና የተተዉ ሰዎችን እየጐበኘሁ ስለ አዳኙ ስለ ኢየሱስ አነብላቸውና አነጋግራቸው ነበር። አንድ ቀን መንፈስ የባሕረኞችን ሆስፒታል እንድጐበኝ መራኝ። በአንዱ ክፍል ውስጥ ሳልፍ አንድ ሰው በልጅነት ስሜ (ከማግባቴ በፊት በነበረኝ የቤተ ሰብ ስም) ሲጠራኝ ሰማሁ። ድምፁ ወደ መጣበት አልጋ ስሄድ የሰው አጽም የሚመስል ነገር አየሁ። ትኩር ብዬ ስመለከተው የቤተ ሰባችንን መልክ ማየት ጀመርሁ፤ እኔ ገና ትንሽ ልጅ ሳለሁ ከብዙ ዓመታት በፊት ከቤት የወጣውን ታላቅ ወንድሜን አወቅሁት። ስለ እርሱ ምንም ወሬ ስላልሰማን እንደ ሞተ ቆጥረን አልቅሰንለት ነበር። በደከመ ድምፅ ስለ ተንከራታችና የባሕረኛ ሕይወቱ ነገረኝ፤ «አሁን ደግሞ፣ እኅቴ» አለ፣ «እየሞትሁ ነው።»
ለመሞት ፈቃደኛ እንደ ሆነ — በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም ዝግጁ እንደ ሆነ ጠየቅሁት። «አይደለሁም፣ ኧረ አይደለሁም!» አለ። እንዲጸልይ ለመንሁት። ራሱን እየነቀነቀ «መጸለይ አልችልም፤ ልቤ እጅግ ደንድኗል፤ አእምሮዬም ጨልሟል፣ ግራ ተጋብቷልም» አለ፤ ከዚያም በነፍሱ ጭንቀት «ኦ፣ ያ አስፈሪ የሚነድ ሲኦል! እንዴት አመልጠዋለሁ?» ብሎ ጮኸ።
እንዲጸልይና ኢየሱስ ለሁሉ እንደ ሞተ እንዲያምን አጥብቄ መከርሁት። ስለ እርሱ ጸለይሁ፤ በተቻለኝም መጠን አብሬው ቆየሁ። አንድ ጠዋት ልጠይቀው ስሄድ ሕይወት አልባ አስከሬኑን በሬሳ ማቆያ ክፍል አሳዩኝ። ይህ በእውነት ለእኔ ከባድና የሚያስደነግጥ ጊዜ ነበር።
በወንድሜ አሟሟት ብዙ ተስፋ አልነበረኝም። ነገር ግን ለሁሉ ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት የሚኖር ሊቀ ካህናት አለ፤ እርሱም እንደ ረታ ተስፋ አደርጋለሁ። ጌታ የምድር ሁሉ ፈራጅ ነው፤ ነፍሳትም ሁሉ በእጁ ናቸው፤ መሓሪና ጥበበኛ ቢሆንም በደለኛውን ከቶ ንጹሕ አያደርግም። ሆን ተብሎ የሚደረግ አለማመን ወደ ሰማይ የሚጮኽ ኃጢአት ነው፤ ያለ ቅጣትም አይታለፍም። እግዚአብሔር በጽድቅ ይፈርዳል፤ ኃጢአትንም ሁሉ ይበቀላል። ፍርድ ለሁሉ ይሰጣል — በዚህ ዓለም ወይም በዘላለም። ጌታ ይመስገን! ነፍሴ ሁሉ ተባብራ፣ ጌታ ይመስገን ትላለች!
እግዚአብሔር በታላቅ ምሕረቱ ባሌን በሰላም መለሰልኝ፤ ስለዚህም በታላቅ ምስጋና ሰገድሁ። ጆርጅ መርከቡ ጌታን ለማገልገል መጥፎ ቦታ እንደ ሆነና በብዛት የሚሰማው መሐላና እርግማን እንደ ነበረ ነገረኝ። አንዳንድ ጊዜ ሾልኮ ሄዶ ይጸልይ እንደ ነበረ፣ በአንድ ወቅትም የመርከቡ አዛዥ ሳያስበው ደርሶበት «ሞኝ» ብሎ እንደ ጠራውና ተነሥቶ ወደ ሥራው እንዲሄድ እንዳዘዘው ነገረኝ። ይህ ሁሉ ቢሆንም ባሌ ለሁለተኛ ጉዞ በመርከብ ተቀጠረ። ጌታ ይመስገን! በመለያየታችን ከሚሰማ ሥቃይ ጠበቀኝ። በደስታ «በሁሉ ስፍራ የምትገኝ አምላክ ሆይ! ፈቃድህ ይሁን» ማለት ቻልሁ።
ከቤት በራቅሁበት ዓመት ውስጥ ከወላጆቼና ከወዳጆቼ ደብዳቤዎች በተደጋጋሚ ይመጡልኝ ነበር፤ በያዙትም ብዙ በረከትና የሚያበረታታ ቃል ደስታንና ምስጋናን ሞሉኝ። አሁን ግን ቤተ ሰቤ ከእኔ እጅግ ወደ ራቀችው ወደ ሲልቨር ሌክ ሊዛወሩ መሆኑን የሚገልጽ ደብዳቤ መጣ። እየተንቀጠቀጥሁ ወደ ሰማያዊ አባቴ ሄድሁ፤ እርሱም ወዲያው ጸጋንና ብርታትን ሰጠኝ።
ምዕራፍ 16 ተጠናቋል
ለረጅም ዘመን የጠፋ ወንድም ተገኘ