እግዚአብሔርን መጠበቅ
የበረከቱ እርግጠኝነት

ምዕራፍ 24 · 3 ደቂቃ ንባብ

የበረከቱ እርግጠኝነት

ሃያ ሁለተኛ ቀን። እግዚአብሔርን መጠበቅ፦ የበረከቱ እርግጠኝነት።

«እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ፥ እኔን የሚጠባበቁ እንደማያፍሩ ታውቃለህ።» —ኢሳይያስ 49:23።

«እርሱን የሚጠባበቁ ሁሉ ብፁዓን ናቸው።» —ኢሳይያስ 30:18።

እንዴት ያሉ የተስፋ ቃሎች ናቸው! እርሱን መጠበቅ ፈጽሞ ከንቱ ሊሆን እንደማይችል በሚሰጠን እጅግ ጽኑ ማረጋገጫ እግዚአብሔር ወደ መጠበቅ ሊስበን እንዴት ይሻል! «እኔን የሚጠባበቁ አያፍሩም።» ይህን ብዙ ጊዜ ተለማምደነው ሳለ፥ ይህ የተባረከ መጠበቅ እንደ ሕይወታችን እስትንፋስ ሊሆን ግድ እንደ ሆነና እንደሚችልም—በእግዚአብሔር ሀልዎትና በፍቅሩ ውስጥ የማያቋርጥ ዕረፍት፥ ሥራውን በእኛ ውስጥ ይፈጽም ዘንድ ራሳችንን ለእርሱ ያለማቋረጥ አሳልፎ መስጠት እንደ ሆነ—ለመማር አሁንም እጅግ የዘገየን መሆናችን እንዴት ይገርማል! ልባችን በአዲስ እርግጠኝነት «እርሱን የሚጠባበቁ ብፁዓን ናቸው!» እስኪል ድረስ እንደገና እናድምጥ፥ እናሰላስልም። በስድስተኛው ቀን ትምህርታችን በመዝሙር 25 ጸሎት ውስጥ «አንተን የሚጠባበቁ ሁሉ አያፍሩ» የሚለውን አግኝተናል። ይህ ጸሎት ራሱ ምናልባት እንዲህ እንዳይሆን ምን ያህል እንደምንፈራ ያሳያል። ፍርሃት ሁሉ እስኪወገድ ድረስ፥ እግዚአብሔር የሚናገረውንም ቃል ወደ ሰማይ መልሰን እስክንልክ ድረስ የእግዚአብሔርን መልስ እናድምጥ፤ አዎን፥ ጌታ ሆይ፥ የምትለውን እናምናለን፦ «እኔን የሚጠባበቁ ሁሉ አያፍሩም።» «እርሱን የሚጠባበቁ ሁሉ ብፁዓን ናቸው።»

የእነዚህ የሁለቱ ክፍሎች አውድ የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን በታላቅ ጭንቀት ውስጥ ወደ ነበረችበትና በሰው ዓይን የመዳን ዕድል ወደማይታይበት ዘመን ያመለክተናል። እግዚአብሔር ግን በተስፋ ቃሉ ጣልቃ ይገባል፥ ሁሉን የሚችል ኃይሉንም ለሕዝቡ መዳን ዋስ አድርጎ ይሰጣል። የቤዛነታቸውን ሥራ ራሱ በኃላፊነት እንደ ወሰደ አምላክ ሆኖ ነው እርሱን እንዲጠብቁ የሚጋብዛቸው፥ ማፈርም የማይቻል መሆኑን የሚያረጋግጥላቸው። እኛም ደግሞ በቤተ ክርስቲያን ሁኔታ ውስጥ—በስመ ክርስትናዋና በሥርዓታዊነቷ—ሊገለጽ የማይቻል አሳዛኝ ነገር በበዛበት ዘመን እንኖራለን። እግዚአብሔርን ከምናመሰግንበት ሁሉ መካከል፥ ወዮ፥ ልናለቅስበት የሚገባ ብዙ ነገር አለ! የእግዚአብሔር የተስፋ ቃሎች ባይኖሩ ኖሮ ተስፋ ለመቍረጥ በቂ ምክንያት በኖረን ነበር። ነገር ግን ሕያው አምላክ በተስፋ ቃሎቹ ራሱን ሰጥቶናል፥ ራሱንም ከእኛ ጋር አስሮአል። እርሱን እንድንጠብቅ ይጠራናል። እንደማናፍር ያረጋግጥልናል። ኦ፥ የተስፋ ቃሎቹ ምን ማለት እንደ ሆኑ እርሱ ራሱ እስኪገልጥልን፥ በተስፋ ቃሎቹም ውስጥ ራሱን በተሰወረ ክብሩ እስኪገልጥ ድረስ ልባችን በፊቱ መጠበቅን ቢማር! እርሱን ብቻ ወደ መጠበቅ በማይቋቋም ኃይል እንሳባለን። «ነፍሳችን እግዚአብሔርን ትጠብቃለች፤ እርሱ ረዳታችንና ጋሻችን ነው» የሚሉትን ሰዎች ማኅበር እግዚአብሔር ያብዛ።

እግዚአብሔርን ስለ ቤተ ክርስቲያኑና ስለ ሕዝቡ ብለን መጠበቃችን እርሱን መጠበቅ በግል ሕይወታችን ውስጥ ባገኘው ስፍራ ላይ እጅግ የተመሠረተ ይሆናል። አእምሮ እግዚአብሔር ሊያደርግ ቃል ስለ ገባው ነገር ብዙ ጊዜ ውብ ራእይ ሊኖረው ይችላል፥ ከንፈሮችም ስለዚያ በሚያነቃቁ ቃላት ሊናገሩ ይችላሉ፤ እነዚህ ግን በእውነት የእምነታችን ወይም የኃይላችን መለኪያ አይደሉም። አይደለም፤ እግዚአብሔርን በግል ልምምዳችን—በውስጥ ያሉትን ጠላቶች ድል ሲነሣ፥ ሲነግሥና ሲገዛ፥ በውስጠኛው ማንነታችን በቅድስናውና በኃይሉ ራሱን ሲገልጥ—በእውነት የምናውቀው ነው፥ ከእርሱ የምንጠብቀውንና ለባልንጀሮቻችን የምናመጣውን መንፈሳዊ በረከት በእውነት የሚለካው ይኸው ነው። እግዚአብሔርን መጠበቅ ለገዛ ነፍሳችን ምን ያህል ብፅዕና እንደ ሆነ ስናውቅ ነው በዙሪያችን ባለችው ቤተ ክርስቲያን ላይ በሚመጣው በረከት በመተማመን ተስፋ የምናደርገው፤ የምንጠብቀውም ነገር ሁሉ ቁልፍ ቃል እንዲህ ይሆናል፦ እርሱ «እኔን የሚጠባበቁ ሁሉ አያፍሩም» ብሎአል። በእኛ ውስጥ ካደረገው በመነሣት በዙሪያችን ታላላቅ ነገሮችን እንዲያደርግ እንታመነዋለን። «እርሱን የሚጠባበቁ ሁሉ ብፁዓን ናቸው።» አዎን፥ አሁንም በመጠበቅ ውስጥ ብፁዓን ናቸው። ለራሳችንም ሆነ ለሌሎች ተስፋ የተሰጡት በረከቶች ሊዘገዩ ይችላሉ፤ ተስፋ የሰጠውን፥ መለኮታዊውን ባራኪ፥ የሚመጡትን በረከቶች ሕያው ምንጭ የማወቅና የማግኘት ሊነገር የማይቻል ብፅዕና ግን አሁንም የእኛ ነው። እግዚአብሔርን መጠበቅ በራሱ የፍጡር ከሁሉ የላቀ መብት፥ የተቤዠው ልጁም ከሁሉ የላቀ ብፅዕና እንደ ሆነ ይህ እውነት ነፍሳችሁን ፈጽሞ ይያዝ።

የፀሐይ ብርሃን ከቀዝቃዛው መሬት ወደ ላይ ወደሚወጣ ወደ እያንዳንዱ ትንሽ የሣር ቅጠል በብርሃኑና በሙቀቱ፥ በውበቱና በበረከቱ እንደሚገባ፥ እንዲሁ ዘላለማዊው አምላክ «በክርስቶስ ፊት የእግዚአብሔርን የክብሩን እውቀት ብርሃን» በልቡ ያበራ ዘንድ፥ በፍቅሩ ታላቅነትና ርኅራኄ የሚጠብቀውን እያንዳንዱን ልጅ ይገናኛል። እግዚአብሔር ላንተ ሊያደርግ የሚጠብቀውን ልብህ እስኪያውቅ ድረስ እነዚህን ቃላት እንደገና አንብባቸው። በታላቂቱ ፀሐይና በዚያች ትንሽ የሣር ቅጠል መካከል ያለውን ልዩነት ማን ሊለካ ይችላል? ይሁን እንጂ ሣሩ ሊፈልገው ወይም ሊይዘው የሚችለውን የፀሐይ ብርሃን ሁሉ ያገኛል። እግዚአብሔርን በመጠበቅ ውስጥ የእርሱ ታላቅነትና የአንተ ታናሽነት እጅግ በሚያስደንቅ ሁኔታ እንደሚስማሙና እንደሚገናኙ እመን። በባዶነትና በድህነት፥ ፈጽሞም አቅም በማጣት፥ በትሕትናና በየዋህነት፥ ለፈቃዱም ራስን በመስጠት በታላቅ ክብሩ ፊት ብቻ ስገድ፥ ጸጥም በል። እርሱን ስትጠብቅ እግዚአብሔር ይቀርባል። እያንዳንዱን የተስፋ ቃሉን በኃይል የሚፈጽም አምላክ ሆኖ ራሱን ይገልጣል። ልብህም ዘወትር ደጋግሞ ይህን ዝማሬ ያንሣ፦ «እርሱን የሚጠባበቁ ሁሉ ብፁዓን ናቸው።»

«ነፍሴ ሆይ፥ እግዚአብሔርን ብቻ ጠብቂ!»

ገጽ 1 / 1 · 3 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል