እግዚአብሔርን መጠበቅ
የፍርድ አምላክ እንደ መሆኑ

ምዕራፍ 21 · 2 ደቂቃ ንባብ

የፍርድ አምላክ እንደ መሆኑ

አሥራ ዘጠነኛ ቀን። እግዚአብሔርን መጠበቅ፦ የፍርድ አምላክ እንደ መሆኑ።

«አቤቱ፥ በፍርድህ መንገድ ጠበቅንህ፤ . . . ፍርድህ በምድር ላይ በሆነ ጊዜ በዓለም የሚኖሩ ጽድቅን ይማራሉና።»—ኢሳይያስ 26:8,9።

«እግዚአብሔር የፍርድ አምላክ ነው፤ እርሱን የሚጠባበቁ ሁሉ ብፁዓን ናቸው።»—ኢሳይያስ 30:18።

እግዚአብሔር የምሕረት አምላክና የፍርድ አምላክ ነው። በአሠራሩ ሁሉ ምሕረትና ፍርድ ዘወትር አብረው ናቸው። በጥፋት ውኃ፥ እስራኤልን ከግብፅ በማዳኑ፥ ከነዓናውያንንም በመገልበጡ ሁልጊዜ በፍርድ መካከል ምሕረትን እናያለን። በገዛ ሕዝቡ ውስጠኛ ክበብ ውስጥም ይህንኑ እናያለን፤ ፍርድ ኃጢአትን ይቀጣል፥ ምሕረት ግን ኃጢአተኛውን ያድናል። ይልቁንም ምሕረት ኃጢአተኛውን የምታድነው በኃጢአቱ ላይ የመጣው ያ ፍርድ ቢኖርም አይደለም፤ በዚያው ፍርድ አማካይነት እንጂ። እግዚአብሔርን ስንጠብቅ ይህን እንዳንረሳ መጠንቀቅ አለብን፤ ስንጠብቅ የፍርድ አምላክ ሆኖ እንዲመጣ መጠባበቅ ይገባናል።

«በፍርድህ መንገድ ጠበቅንህ።» ይህ ቃል በውስጣዊ ልምምዳችን እውነት ሆኖ ይገኛል። ቅድስናን በቅንነት ከናፈቅን፥ ፈጽመን የጌታ እንሆን ዘንድም በቅንነት ከጸለይን፥ ቅዱስ ሀልዎቱ የተሰወረውን ኃጢአት ቀስቅሶ ይገልጠዋል፤ የተፈጥሮአችንን ክፋት፥ ለእግዚአብሔር ሕግ ያለውን ተቃውሞ፥ ያንንም ሕግ ለመፈጸም ያለውን አቅመ ቢስነት አጥብቆ በሚያስረዳን መራራ ወቀሳም እጅግ ዝቅ ያደርገናል። እንዲህ የሚለው ቃል እውነት ይሆናል፦ «የመምጣቱን ቀን መታገሥ የሚችል ማን ነው? እርሱ እንደ አንጥረኛ እሳት ነውና።» «የሚያቀልጥ እሳት እንደሚነድድ ምነው በወረድህ!» እግዚአብሔር በታላቅ ምሕረቱ ነፍስ ክፋቷንና በደሏን እንድትረዳ በማድረግ በነፍስ ውስጥ በኃጢአት ላይ ፍርዱን ይፈጽማል። ብዙዎች ከእነዚህ ፍርዶች ለመሸሽ ይሞክራሉ፤ እግዚአብሔርንና ከኃጢአት መዳንን የምትናፍቅ ነፍስ ግን በትሕትናና በተስፋ ከፍርዶቹ በታች ትሰግዳለች። በነፍስ ጸጥታም እንዲህ ትላለች፦ «አቤቱ፥ ተነሥ፥ ጠላቶችህም ይበተኑ። በፍርድህ መንገድ ጠበቅንህ።»

እግዚአብሔርን የመጠበቅን የተባረከ ጥበብ ለመማር የሚሻ ማንም ሰው፥ እርሱን ለመጠበቅ የሚያደርገው ሙከራ በመጀመሪያ ኃጢአቱንና ጨለማውን አብዝቶ ብቻ ቢገልጥበት አይደነቅ። ያልተሸነፉ ኃጢአቶች፥ ወይም ክፉ አሳቦች፥ ወይም ታላቅ ጨለማ የእግዚአብሔርን ፊት የሚሰውሩ ቢመስሉ ማንም ተስፋ አይቍረጥ። የምሕረቱ ስጦታና ተሸካሚ በሆነው በገዛ ተወዳጅ ልጁ ላይ በቀራንዮ፥ ምሕረት በፍርድ ውስጥ የተሰወረችና የጠፋች መስላ አልነበረምን? እንግዲህ ተገዛ፤ ለኃጢአትህ ሁሉ ከሚገባው ፍርድ በታች ጠልቀህ ስመጥ፤ ፍርድ መንገድን ያዘጋጃል፥ በሚያስደንቅ ምሕረትም ፈንድቶ ይወጣል። «በፍርድ ትቤዣለህ» ተብሎ ተጽፎአል። ርኅሩኅ ምሕረቱ በፍርድ መካከል ቤዛነቱን በአንተ ውስጥ እየሠራ እንደ ሆነ በማመን እግዚአብሔርን ጠብቅ፤ እርሱን ጠብቅ፥ ይራራልሃል።

ገና ሌላ ትግበራም አለ፤ ሊነገር የማይቻል ክብደት ያለው ትግበራ። እግዚአብሔር በፍርዱ መንገድ ይህችን ምድር እንዲጐበኝ እየተጠባበቅን ነው፤ እርሱን እየጠበቅነው ነን። እንዴት ያለ አሳብ ነው! ስለሚመጡት ስለ እነዚህ ፍርዶች እናውቃለን፤ ክርስቲያን ነን ከሚሉት ወገኖቻችን መካከል በግዴለሽነት የሚኖሩ እልፍ አእላፋት እንዳሉ፥ ለውጥም ካልመጣ በእግዚአብሔር እጅ ሊጠፉ ግድ እንደ ሆነ እናውቃለን። እንግዲህ እግዚአብሔር ምናልባት ይምራቸው እንደ ሆነ እነርሱን ለማስጠንቀቅ፥ እነርሱን ለመለመንና ስለ እነርሱም ለመማለድ የምንችለውን ሁሉ አናደርግምን? የድፍረት ማጣት፥ የቅናት ማጣት፥ የኃይል ማጣት ቢሰማን፥ እግዚአብሔርን የፍርድ አምላክ እንደ መሆኑ ይበልጥ በግልጽና በጽናት መጠበቅ አንጀምርምን? በገዛ ወዳጆቻችን ላይ በሚመጡት ፍርዶች ራሱን እንዲገልጥልን፥ ለእርሱ አዲስ ፍርሃት፥ ለእነርሱም አዲስ ስጋት እንዲያነሣሣን፥ ከዚህ ቀደም ፈጽሞ ባልሆነ መንገድ እንድንናገርና እንድንጸልይም ግድ እንዲለን እንለምነው። በእውነት እግዚአብሔርን መጠበቅ መንፈሳዊ ራስን ማስደሰት እንዲሆን አልታሰበም። ዓላማው እግዚአብሔርና ቅድስናው፥ ክርስቶስና በቀራንዮ የሞተው ፍቅር፥ በሰማይ የሚነድደውና ወደ ምድር የመጣው መንፈስና እሳት እንዲይዙን፥ በፍርዱም መንገድ እግዚአብሔርን እየጠበቅነው ነን በሚለው መልእክት ሰዎችን እንድናስጠነቅቅና እንድናነቃ ነው። ክርስቲያን ሆይ! በፍርድ አምላክ በእውነት እንደምታምን አሳይ።

«ነፍሴ ሆይ፥ እግዚአብሔርን ብቻ ጠብቂ!»

ገጽ 1 / 1 · 2 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል