ምዕራፍ 20 · 2 ደቂቃ ንባብ
ራሱን እንዲገልጥ
አሥራ ስምንተኛ ቀን። እግዚአብሔርን መጠበቅ፦ ራሱን እንዲገልጥ።
«በዚያም ቀን እንዲህ ይባላል፦ እነሆ፥ አምላካችን ይህ ነው፤ እርሱን ጠብቀናል፥ ያድነናልም፤ እግዚአብሔር ይህ ነው፤ እርሱን ጠብቀናል፤ በማዳኑ ደስ ይለናል፤ ሐሴትም እናደርጋለን።»—ኢሳይያስ 25:9።
በዚህ ክፍል ሁለት ውድ አሳቦች አሉን።
አንደኛው፥ ይህ በአንድነት እርሱን ሲጠብቁ የኖሩ የእግዚአብሔር ሕዝብ ቋንቋ መሆኑ ነው፤ ሁለተኛው፥ የመጠበቃቸው ፍሬ እግዚአብሔር ራሱን እንዲህ አድርጎ መግለጡ ነው፤ ስለዚህም በደስታ፦ እነሆ፥ አምላካችን ይህ ነው፤ እግዚአብሔር ይህ ነው ለማለት ቻሉ። በአንድነት የመጠበቅን ኃይልና በረከት ልንማረው ያስፈልገናል።
ሁለት ጊዜ የተደገመውን «እርሱን ጠብቀናል» የሚለውን ልብ በል። በአንድ የመከራ ጊዜ የሕዝቡ ልብ በአንድነት ተሳስቦ ነበር፤ የሰውን ተስፋና እርዳታ ሁሉ ትተው በአንድ ልብ አምላካቸውን ለመጠበቅ ራሳቸውን ሰጥተው ነበር። በአብያተ ክርስቲያኖቻችን፥ በጉባኤዎቻችንና በጸሎት ስብሰባዎቻችን የሚያስፈልገን ይህ አይደለምን? የቤተ ክርስቲያንና የዓለም ችግር ይህን ለመጠየቅ በቂ ታላቅ አይደለምን? በክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ምንም የሰው ጥበብ የማይቋቋማቸው ክፋቶች የሉምን? ቤተ ክርስቲያንን ኃይሏን የሚዘርፉ ሥርዓት አምላኪነትና ምክንያታዊነት፥ መደበኛነትና ዓለማዊነት የሉብንምን? መንፈሳዊ ሕይወቷን የሚያሰጉ የዓለም ትምህርትና ገንዘብ ተድላም የሉብንምን? የቤተ ክርስቲያን ኃይሎች በክርስቲያን አገሮችና በአሕዛብ ዓለም ካሉት የክሕደት፥ የዓመፃና የጕስቍልና ኃይሎች ጋር ለመጋፈጥ ፈጽሞ የማይበቁ አይደሉምን? በእግዚአብሔር የተስፋ ቃልና በመንፈስ ቅዱስ ኃይልስ ችግሩን ሊያሟላና አምላኳ ከእርሷ የሚጠብቀውን ሁሉ እያደረገች እንዳለች የሚያሳርፍ ማረጋገጫ ለቤተ ክርስቲያን ሊሰጣት የሚችል የተዘጋጀ ነገር የለምን? የመንፈሱን ስጦታ ለማግኘት በአንድነት እግዚአብሔርን መጠበቅስ የሚያስፈልገው በረከት መሆኑ በእርግጥ ግልጽ አይደለምን? ልንጠራጠረው አንችልም።
በስብሰባዎቻችን እግዚአብሔርን ይበልጥ በግልጽ የመጠበቅ ዓላማ በግል አምልኮ ካለው ጋር እጅግ ተመሳሳይ ይሆናል። ይህም፦ እግዚአብሔር ሁሉን ማድረግ እንዳለበትና እንደሚያደርግም የጠለቀ እምነት፤ ወደ ጥልቅ አቅመ ቢስነታችን ይበልጥ በትሕትናና በጽናት መግባትና በእርሱ ላይ ሙሉ በሙሉና ያለማቋረጥ መደገፍ እንደሚያስፈልገን ማወቅ፤ ዋናው ነገር ለእግዚአብሔር የክብሩንና የኃይሉን ስፍራ መስጠት እንደ ሆነ ሕያው ግንዛቤ፤ እግዚአብሔር እርሱን ለሚጠብቁት በመንፈሱ በኩል የመቀበሉንና የመገኘቱን ምሥጢር፥ ከዚያም በጊዜው የማዳን ኃይሉን መገለጥ እንደሚሰጥ በልበ ሙሉነት መጠባበቅ ማለት ይሆናል። ታላቁ ዓላማ በሚጸልይና በሚያመልክ ጉባኤ ውስጥ ያለውን እያንዳንዱን ሰው የእግዚአብሔር መገኘት ጥልቅ ስሜት ሥር ማምጣት ይሆናል፤ ይኸውም ሲለያዩ እግዚአብሔርን ራሱን እንዳገኙት፥ ልመናቸውን ሁሉ በእርሱ ዘንድ እንደ ተዉ፥ አሁንም እርሱ ማዳኑን እስኪፈጽም በጸጥታ እንደሚጠብቁ እንዲያውቁ ነው።
በጥቅሳችን የተመለከተው ይህ ተሞክሮ ነው። የቃሉ መፈጸም አንዳንድ ጊዜ ሁሉም በአንድነት፦ «እነሆ፥ አምላካችን ይህ ነው፤ እግዚአብሔር ይህ ነው!» ብለው እንዲጮኹ በሚያደርግ እጅግ በሚያስደንቅ የእግዚአብሔር ኃይል ጣልቃ ገብነት ሊሆን ይችላል። እንዲሁም የእግዚአብሔር ሕዝብ በሚጠብቁባቸው ጊዜያት መገኘቱን እጅግ ስለሚገነዘቡ ነፍሳት በቅዱስ ፍርሃት፦ «እነሆ፥ አምላካችን ይህ ነው፤ እግዚአብሔር ይህ ነው!» የሚል ስሜት በሚሰማቸው ጊዜ በመንፈሳዊ ተሞክሮም እኩል እውነት ሊሆን ይችላል። ወዮ፥ በአምልኮ ስብሰባዎቻችን እጅግ የሚጐድለው ይህ ነው። እግዚአብሔርን ለሚፈራ የወንጌል አገልጋይ ሕዝቡን እግዚአብሔርን ወደ መገናኘት ከመምራትና፥ ገና ሳይሰብክ፥ እያንዳንዱን ከእርሱ ጋር ከማገናኘት የሚበልጥ አስቸጋሪ፥ የሚበልጥ ከባድ፥ የሚበልጥም የተባረከ ሥራ የለውም። «እኛ ሁላችን አሁን በእግዚአብሔር ፊት በዚህ አለን» — እነዚህ የቆርኔሌዎስ ቃላት የጴጥሮስ አድማጮች ለመንፈስ ቅዱስ መምጣት እንዴት እንደ ተዘጋጁ ያሳያሉ። በእግዚአብሔር ፊት መጠበቅ፥ እግዚአብሔር እስኪመጣ መጠበቅ፥ በእግዚአብሔርም ላይ ተስፋ አድርጎ መጠበቅ፥ እግዚአብሔር መገኘቱን የሚያሳይበት ብቸኛው ቅድመ ሁኔታ ነው።
እርስ በርሳቸው በአጭር የጸጥታ ጊዜያት እየተረዳዱ እግዚአብሔርን ብቻ ለመጠበቅ በአንድ ዓላማ የተሰበሰቡ፥ እግዚአብሔር ስለ ክፋት፥ ስለ ፈቃዱ፥ ስለ አዲስ የሥራ በሮች ወይም የአሠራር ዘዴዎች ሊገልጠው ላለው ለማንኛውም አዲስ ነገር ልባቸውን የሚከፍቱ የአማኞች ጉባኤ ብዙም ሳይቆይ፦ «እነሆ፥ አምላካችን ይህ ነው፤ እርሱን ጠብቀናል፥ ያድነናልም፤ እግዚአብሔር ይህ ነው፤ እርሱን ጠብቀናል፤ በማዳኑ ደስ ይለናል፤ ሐሴትም እናደርጋለን» ለማለት ምክንያት ያገኛል።
«ነፍሴ ሆይ፥ እግዚአብሔርን ብቻ ጠብቂ!»
ምዕራፍ 20 ተጠናቋል
ራሱን እንዲገልጥ