እግዚአብሔርን መጠበቅ
ወደ አዲስ ዝማሬ የሚወስደው መንገድ

ምዕራፍ 16 · 3 ደቂቃ ንባብ

ወደ አዲስ ዝማሬ የሚወስደው መንገድ

አሥራ አራተኛ ቀን። እግዚአብሔርን መጠበቅ፦ ወደ አዲስ ዝማሬ የሚወስደው መንገድ።

«እግዚአብሔርን ታግሼ ጠበቅሁት፤ ወደ እኔም ዘንበል አለ፥ ጩኸቴንም ሰማ። . . . በአፌም አዲስ ዝማሬን፥ ለአምላካችን ምስጋናን አኖረ።»—መዝሙር 40:1-3።

ና፥ በትዕግሥት እግዚአብሔርን መጠበቅ የሚያስገኘውን እርግጠኛና ብፁዕ ፍጻሜ ከተሞክሮው የሚናገርን ሰው ምስክርነት አድምጥ። እውነተኛ ትዕግሥት በራሱ ለሚተማመነው ባሕርያችን እጅግ እንግዳ ነው፤ እግዚአብሔርን በመጠበቃችንም ውስጥ ፈጽሞ የማይቀር ነው፤ የእውነተኛ እምነትም ዋና ክፍል ነው፤ ስለዚህ ቃሉ ስለ እርሱ የሚያስተምረንን እንደ ገና ብናሰላስል ተገቢ ነው።

ትዕግሥት ተብሎ የተተረጎመው የእንግሊዝኛ ቃል መከራን ከሚያመለክት የላቲን ቃል የተገኘ ነው። ነጻ ልንወጣ የምንመኘው አንድ ኃይል በግድ የያዘንን ሰው አሳብ ያመለክታል። መጀመሪያ ያለ ፈቃዳችን እንገዛለን፤ መቃወም ከንቱ በሆነ ጊዜ ግን በትዕግሥት መጽናት ከሁሉ የሚበልጥ ጥበብ እንደ ሆነ ተሞክሮ ያስተምረናል። እግዚአብሔርን በመጠበቅ ግን የምንገዛው ስለ ተገደድን ብቻ ሳይሆን በብፁዕ አባታችን እጅ ለመሆን በፍቅርና በደስታ ስለምንፈቅድ መሆኑ ወሰን የሌለው ትልቅ ነገር ነው። ያን ጊዜ ትዕግሥት ከሁሉ የሚበልጥ ብፅዕናችንና ከሁሉ የሚበልጥ ጸጋችን ይሆናል። እግዚአብሔርን ያከብራል፤ በእኛም ላይ ፈቃዱን እንዲያደርግ ጊዜ ይሰጠዋል። በቸርነቱና በታማኝነቱ ላይ ያለን እምነት ከሁሉ የላቀ መግለጫ ነው። እግዚአብሔር ሥራውን እየሠራ እንዳለ በማረጋገጥ ለነፍስ ፍጹም ዕረፍትን ያመጣል። እግዚአብሔር መልካም መስሎ በታየው መንገድና ጊዜ ከእኛ ጋር እንዲሠራ ሙሉ በሙሉ መፍቀዳችንን የሚያሳይ ምልክት ነው። እውነተኛ ትዕግሥት የራሳችንን ፈቃድ በእርሱ ፍጹም ፈቃድ ውስጥ ማጣት ነው።

እግዚአብሔርን በእውነትና በሙላት ለመጠበቅ እንዲህ ያለ ትዕግሥት ያስፈልጋል። እንዲህ ያለው ትዕግሥት በመጠበቅ ትምህርት ቤት የምንማራቸው የመጀመሪያዎቹ ትምህርቶች እድገትና ፍሬ ነው። እግዚአብሔርን በእውነት መጠበቅ ምን ያህል አስቸጋሪ እንደ ሆነ ለብዙዎች እንግዳ ይመስላቸዋል። ነፍስ በራሷ አቅመ ቢስነት ውስጥ ሰጥማ እርሱ ራሱን እስኪገልጥ ድረስ የምትጠብቅበት በእግዚአብሔር ፊት ያለው ታላቅ የነፍስ ጸጥታ፤ እግዚአብሔር መፈለግንም ማድረግንም ካልሠራ በቀር የራሷ ፈቃድ ወይም የራሷ ኃይል አንዳች እንዲሠራ የሚፈራ ጥልቅ ትሕትና፤ እግዚአብሔር ብርሃኑን ካልሰጠ በቀር ምንም ላለመሆንና ምንም ላለማወቅ የሚረካ የዋህነት፤ ቅዱስ ፈቃዱ የሚንቀሳቀስበትና የሚቀርጽበት ዕቃ ብቻ ለመሆን የሚሻ የፈቃድ ፍጹም መሰጠት፦ እነዚህ ሁሉ የፍጹም ትዕግሥት ክፍሎች በአንድ ጊዜ አይገኙም። ነገር ግን ነፍስ ስፍራዋን አጽንታ ስትይዝና ደጋግማ፦ «በእውነት ነፍሴ እግዚአብሔርን ትጠብቃለች፤ መዳኔ ከእርሱ ዘንድ ነውና። እርሱ ብቻ ዓለቴና መድኃኒቴ ነው» ስትል በየልካቸው ይመጣሉ።

ጳውሎስ በተናገራቸው በእነዚህ ቃላት ትዕግሥት እጅግ ልዩ ጸጋ የሚሰጥለት ጸጋ እንደ ሆነ የሚያሳይ ምን ያህል ማስረጃ እንዳለን አስተውለህ ታውቃለህን? «እንደ ክብሩ ጉልበት መጠን በኃይል ሁሉ እየበረታችሁ» — ለምንድር ነው? «ከደስታ ጋር በሁሉ ለመጽናትና ለመታገሥ።» አዎን፥ እግዚአብሔርን በትዕግሥት ሁሉ የምንጠብቅ ከሆንን በእግዚአብሔር ኃይል ሁሉ፥ ያውም እንደ ክብሩ ጉልበት መጠን፥ መበርታት ያስፈልገናል። ሁሉን በፍጹም ትዕግሥት በእጁ እንድንተው የሚያስችለን እግዚአብሔር ሕይወታችንና ኃይላችን ሆኖ ራሱን በእኛ ውስጥ መግለጡ ነው። እንዲህ ያለ ትዕግሥት ስለሌላቸው ተስፋ ለመቁረጥ የሚያዘነብሉ ቢኖሩ አይዞአቸው፤ እግዚአብሔር ራሱ በተሰወረ ኃይሉ የሚያበረታንና የቅዱሳንን ትዕግሥት፥ የክርስቶስን የራሱን ትዕግሥት፥ በእኛ ውስጥ የሚሠራው ደካማና እጅግ ጉድለት ያለበት መጠበቃችንን በምንቀጥልበት ጊዜ ነው።

በብርቱ የተፈተነውን የአንዱን ሰው ድምፅ አድምጥ፦ «እግዚአብሔርን ታግሼ ጠበቅሁት፤ ወደ እኔም ዘንበል አለ፥ ጩኸቴንም ሰማ።» ያለፈበትንም ስማ፦ «ከሚያስፈራ ጕድጓድ ከረግረግም ጭቃ አወጣኝ፤ እግሮቼንም በዓለት ላይ አቆመ፥ አረማመዴንም አጸና። በአፌም አዲስ ዝማሬን፥ ለአምላካችን ምስጋናን አኖረ።» እግዚአብሔርን በትዕግሥት መጠበቅ ብዙ ዋጋ ያስገኛል፤ መዳኑ የተረጋገጠ ነው፤ እግዚአብሔር ራሱ በአፍህ አዲስ ዝማሬን ያኖራል። ነፍስ ሆይ! ትዕግሥት አትጣ፤ መጠበቅ የሚያስቸግርህ በጸሎትና በአምልኮ ልምምድ ቢሆን፥ ወይም የተወሰኑ ልመናዎችህ መልስ በመዘግየቱ ቢሆን፥ ወይም እግዚአብሔር ራሱ በጥልቅ መንፈሳዊ ሕይወት እንዲገለጥልህ ያለው የልብህ ምኞት እስኪፈጸም ቢሆን — አትፍራ፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ዕረፍ፥ በትዕግሥትም ጠብቀው። አንዳንድ ጊዜም ትዕግሥት ስጦታህ እንዳልሆነ ቢሰማህ፥ የእግዚአብሔር ስጦታ መሆኑን አስብ፥ ይህንንም ጸሎት ያዝ (2ኛ ተሰሎንቄ 3:5 የተሻሻለው ትርጉም)፦ «ጌታም … ወደ ክርስቶስም ትዕግሥት ልባችንን ያቅናው።» እግዚአብሔርን ልትጠብቅበት ወደሚገባህ ትዕግሥት እርሱ ራሱ ይመራሃል።

«ነፍሴ ሆይ፥ እግዚአብሔርን ብቻ ጠብቂ!»

ምዕራፍ 16 ተጠናቋል

ወደ አዲስ ዝማሬ የሚወስደው መንገድ

ገጽ 1 / 1 · 3 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል