እግዚአብሔርን መጠበቅ
በልብ

ምዕራፍ 11 · 3 ደቂቃ ንባብ

በልብ

ዘጠነኛ ቀን። እግዚአብሔርን መጠበቅ፦ በልብ።

«በርቱ፥ ልባችሁም ይጽና፥

እግዚአብሔርን የምትጠባበቁ ሁላችሁ።»— መዝሙር 31:24። (የተሻሻለው ትርጉም)

ቃሉ ባለፈው ማሰላሰላችን ከነበረው ጋር ይመሳሰላል ማለት ይቻላል። ቢሆንም እግዚአብሔርን መጠበቅ ምን እንደ ሆነ በእውነትና በሙላት ለመማር ለሚሹ ሁሉ እጅግ የሚያስፈልግ አንድ ትምህርት ለማስረገጥ ቃሉን እንደ ገና በደስታ እጠቀምበታለሁ። ትምህርቱ ይህ ነው፦ እግዚአብሔርን መጠበቅ ያለብን በልባችን ነው። «ልባችሁ ይጽና።» መጠበቃችን ሁሉ በልብ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ ነው። የሰው ልቡ እንደ ሆነ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት እንዲሁ ነው። መንፈስ ቅዱስ ልባችንን ካዘጋጀው መጠን አልፈን፣ በዚያ እርሱን ለመጠበቅ ወደ እግዚአብሔር ሀልዎት ቅዱስ ስፍራ ከዚያ በላይ ልንገፋም ልንጠልቅም አንችልም። መልእክቱም «እግዚአብሔርን የምትጠባበቁ ሁላችሁ፥ ልባችሁ ይጽና።» የሚል ነው።

እውነቱ እጅግ ቀላል መስሎ ስለሚታይ አንዳንዶች፦ ይህንን ሁሉም የሚቀበለው አይደለምን? ታዲያ በተለየ ሁኔታ አጥብቆ መናገር ለምን አስፈለገ? ብለው ይጠይቁ ይሆናል። ምክንያቱም እጅግ ብዙ ክርስቲያኖች በአእምሮ ሃይማኖትና በልብ ሃይማኖት መካከል ያለውን ታላቅ ልዩነት አይገነዘቡም፤ ከሁለቱም የመጀመሪያው ከኋለኛው ይልቅ እጅግ በትጋት ይኰተኰታል። ልብ ከአእምሮ እጅግ ወሰን በሌለው መጠን እንደሚበልጥ አያውቁም። የክርስትና ሕይወታችን ድካም ዋና ዋና ምክንያቶች አንዱ መፈለግ ያለበት በዚህ ነው፤ እግዚአብሔርን መጠበቅ ሙሉ በረከቱን የሚያመጣውም ይህ ሲገባን ብቻ ነው።

ምሳሌ 3:5 ሐሳቤን ግልጽ ለማድረግ ይረዳ ይሆናል። በእግዚአብሔር ፍርሃትና ሞገስ ስለሚኖር ሕይወት ሲናገር፦ «በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ» ይላል። በሃይማኖት ሁሉ እነዚህን ሁለት ኃይላት መጠቀም አለብን። አእምሮ ከእግዚአብሔር ቃል እውቀትን መሰብሰብና ልብ ከውስጣዊ ሕይወቱ ጋር የሚመገብበትን ምግብ ማዘጋጀት አለበት። ነገር ግን እዚህ ላይ አስፈሪ አደጋ ይመጣል፤ ይኸውም በራሳችን ማስተዋል መደገፋችንና ስለ መለኮታዊ ነገሮች ባለን ግንዛቤ መታመናችን ነው። ሰዎች በእውነት ከተጠመዱ መንፈሳዊ ሕይወታቸው በራሱ ጊዜ እንደሚጠነክር ያስባሉ። ይህ ግን ፈጽሞ እንዲህ አይደለም። ማስተዋል ከመለኮታዊ ነገሮች ጽንሰ ሐሳቦችና ምስሎች ጋር ይሠራል፤ ነገር ግን ወደ ነፍስ እውነተኛ ሕይወት ሊደርስ አይችልም። ስለዚህም ትእዛዙ፦ «በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ» የሚል ነው። ሰው የሚያምነውና ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኘው በልቡ ነው። እግዚአብሔር መንፈሱን የሰጠው በልብ ውስጥ ነው፤ በዚያ በእኛ ውስጥ የሚሠራ የእግዚአብሔር ሀልዎትና ኃይል ይሆንልን ዘንድ ነው። በሃይማኖታችን ሁሉ የሚታመን፣ የሚወድ፣ የሚሰግድና የሚታዘዝ ልብ ነው። አእምሮዬ መንፈሳዊ ሕይወትን በውስጤ ለመፍጠርም ሆነ ለመጠበቅ ፈጽሞ አቅም የለውም፤ እርሱ በውስጤ ይሠራው ዘንድ ልብ እግዚአብሔርን መጠበቅ አለበት።

ይህ ልክ እንደ ሥጋዊ ሕይወት ነው። አእምሮዬ ምን እንደምበላና እንደምጠጣ፣ ምግቡም እንዴት እንደሚመግበኝ ሊነግረኝ ይችላል። በመብላትና በመመገብ ግን አእምሮዬ አንዳች ሊያደርግ አይችልም፤ ለዚያ ልዩ ዓላማ ሰውነት የራሱ ብልቶች አሉት። እንዲሁም አእምሮ የእግዚአብሔር ቃል የሚለውን ሊነግረኝ ይችላል፤ ነፍስን በሕይወት እንጀራ በመመገብ ረገድ ግን አንዳች ሊያደርግ አይችልም—ይህንን በእግዚአብሔር ላይ ባለው እምነትና መታመን ሊያደርግ የሚችለው ልብ ብቻ ነው። ሰው የምግብንና የእንቅልፍን ባሕርይና ውጤት እያጠና ሊሆን ይችላል፤ መብላት ወይም መተኛት ሲፈልግ ግን ሐሳቡንና ጥናቱን ወደ ጎን ትቶ የመብላትን ወይም የመተኛትን ችሎታ ይጠቀማል። እንዲሁም ክርስቲያን የእግዚአብሔርን ቃል ካጠና ወይም ከሰማ በኋላ ከሐሳቡ ማረፍ፣ በእርሱም አለመታመን፣ ልቡንም በእግዚአብሔር ፊት እንዲከፈትና ከእርሱ ጋር ሕያው ኅብረትን እንዲሻ ማንቃት ሁልጊዜ ያስፈልገዋል።

እንግዲህ እግዚአብሔርን የመጠበቅ ብፅዕና ይህ ነው፤ የሐሳቤንና የጥረቴን ሁሉ አቅመ ቢስነት መናዘዜ፣ በቅዱስ ዝምታ ልቤን በፊቱ ለማስገዛት ራሴን ጸጥ ማድረጌ፣ የራሱንም ሥራ በውስጤ እንዲያድስና እንዲያጸና በእርሱ መታመኔ ነው። የጥቅሳችንም ትምህርት ይኸው ነው፦ «እግዚአብሔርን የምትጠባበቁ ሁላችሁ፥ ልባችሁ ይጽና።» በአእምሮ በማወቅና በልብ በማመን መካከል ያለውን ልዩነት አስታውስ። ግልጽና ብርቱ ሐሳቦች ባሉት ማስተዋልህ ላይ የመደገፍን ፈተና ተጠንቀቅ። እነርሱ የሚረዱህ ልብ ከእግዚአብሔር ማግኘት ያለበትን እንድታውቅ ብቻ ነው፤ በራሳቸው ግን ምስሎችና ጥላዎች ብቻ ናቸው። «እግዚአብሔርን የምትጠባበቁ ሁላችሁ፥ ልባችሁ ይጽና።» እግዚአብሔር ራሱን የሚገልጥበት፣ አንተም እርሱን ልታውቀው የምትችልበት የመንፈሳዊ ባሕርይህ ድንቅ ክፍል አድርገህ ልብህን በፊቱ አቅርብ። ወደ ልብህ ዘልቀህ ማየት ባትችልም እግዚአብሔር በዚያ በቅዱስ መንፈሱ እየሠራ እንደ ሆነ ከሁሉ የላቀ መተማመንን አዳብር። ልብ አንዳንድ ጊዜ በፍጹም ዝምታና ጸጥታ ይጠብቅ፤ በተሰወረው ጥልቀቱ ውስጥ እግዚአብሔር ይሠራል። ይህንን እርግጠኛ ሁን፤ እርሱንም ብቻ ጠብቅ። ልብህን ሁሉ ከስውር እንቅስቃሴዎቹ ጋር ዘወትር በእግዚአብሔር እጅ አስረክብ። እርሱ ልብን ይፈልጋል፤ ይወስደዋልም፤ እንደ እግዚአብሔርም በውስጡ ያድራል። «በርቱ፥ ልባችሁም ይጽና፥ እግዚአብሔርን የምትጠባበቁ ሁላችሁ።»

«ነፍሴ ሆይ፥ እግዚአብሔርን ብቻ ጠብቂ!»

ገጽ 1 / 1 · 3 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል