አንድነትና ኅብረት
አባሪ

ምዕራፍ 10 · 1 ደቂቃ ንባብ · 2 ደቂቃ ማዳመጥ

አባሪ

የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት

የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት የሚወክሉት እነማንን ነው? የሚል ጥያቄ ብዙ ጊዜ ይጠየቃል።

ሙሽራይቱ እንዳልሆኑ ግልጥ ነው፤ ይሁን እንጂ ከእርሷ እጅግ የራቁ አይደሉም። ሙሽራው በቀትር መንጋውን የት እንደሚያሳርፍ ያውቃሉ፤ ውዱ በእርሱ እየኖረች ስታርፍ እንዳያስነሡአትና እንዳይቀሰቅሱአት በሙሽራው ይማላሉ፤ ሙሽራው በግርማና በክብር ከምድረ በዳ ሲወጣ ትኩረትን ወደ እርሱ ይስባሉ፤ የፍቅር ስጦታዎቻቸው የክብር ሰረገላውን ያስጌጡታል፤ ሙሽራይቱ ውዷን ለማግኘት እርዳታቸውን ትጠይቃቸዋለች፤ ስለ ውበቱ በምትሰጠው በስሜት በተሞላ መግለጫዋም ተነሣሥተው ከእርሷ ጋር ሊፈልጉት ይመኛሉ፤ የሙሽራይቱን ውበት በሰፊው ይገልጣሉ፤ በሌላ በኩል ግን በሙሽራው ማንነት ተጠምደው ከቶ አናገኛቸውም፤ እርሱ ለእነርሱ ሁሉ በሁሉ አይደለም፤ ውጫዊና ምድራዊ ነገሮችን ያስባሉ።

በእውነት ያልዳኑ ቢሆኑ እንኳ ለመዳን እጅግ የቀረቡትን፣ ወይም የዳኑ ቢሆኑ ግማሽ ብቻ የዳኑትን አይወክሉምን? ለጊዜው ከእግዚአብሔር ነገሮች ይልቅ ስለ ዚህ ዓለም ነገሮች የሚጨነቁትን? የራሳቸውን ጥቅም ማስፋፋት፣ የራሳቸውን ምቾት ማስጠበቅ በሁሉ ነገር ጌታን ደስ ከማሰኘት ይልቅ ያሳስባቸዋል። በራእይ 7:9-17 ከተነገረው፣ ከታላቁ መከራ ከሚወጣው ከዚያ ታላቅ ጉባኤ ክፍል ሊሆኑ ይችላሉ፤ ነገር ግን «ለእግዚአብሔርና ለበጉ በኵራት» ከሆኑት ከ144,000ዎቹ ክፍል አይሆኑም (ራእይ 14:1-5)። ጌታችን በሉቃስ 21:34-36 የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ረስተዋል፤ ስለዚህም «ሊመጣ ካለው ከዚህ ሁሉ ለማምለጥ፥ በሰው ልጅም ፊት ለመቆም» የተገባቸው ሆነው አይቈጠሩም። ከጳውሎስ ጋር «ስለ ጌታ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ እውቀት ብልጫ ሁሉን እንደ ጉዳት» አልቈጠሩም፤ ስለዚህም አይደርሱም፤ «መድረስ» የማይሆንላቸው ለዚያ ከሙታን መካከል ለሆነው ትንሣኤ ነው—ጳውሎስ ሊያመልጠኝ ይችላል ብሎ ለተሰማው፣ ነገር ግን ሊደርስበት ላለመው ትንሣኤ።

ክርስቲያኖች የሆኑ ወይም ክርስቲያኖች ነን ብለው የሚያስቡ ሁሉ ቅዱስ ጳውሎስ በፊልጵስዩስ 3:11 ወደሚናገርለት ወደዚያ ትንሣኤ እንደማይደርሱ፣ ወይም እንዲሁ ጌታን በአየር ለመቀበል እንደማይነጠቁ ያለንን ጽኑ እምነት በመዝገብ ልናሰፍር እንወዳለን። በመቀደስ ሕይወታቸው ከዓለም አይደሉም መሆናቸውን፣ ነገር ግን እርሱን እንደሚጠባበቁ ለሚገልጡ ግን «ያድናቸው ዘንድ ለሚጠባበቁት ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢአት ይታይላቸዋል»።

ገጽ 1 / 1 · 1 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል
ቀዳሚ