እውነተኛው የወይን ግንድ
በፍቅሬ ኑሩ

ምዕራፍ 21 · 2 ደቂቃ ንባብ

በፍቅሬ ኑሩ

አብ እንደ ወደደኝ እኔ ደግሞ ወደድኋችሁ፤ በፍቅሬ ኑሩ—ዮሐንስ 15:9

በፍቅሬ ኑሩ—የሰውን ቤት መኖሪያው እንለዋለን። የእኛ መኖሪያ፣ የነፍሳችን ቤት፣ የክርስቶስ ፍቅር ሊሆን ይገባዋል። ሕይወታችንን በዚያ ልንኖር፣ ቀኑን ሙሉ በዚያ እንደ ቤታችን ሆነን ልንቀመጥ ይገባናል፤ ክርስቶስ ሕይወታችን እንዲሆን የሚፈልገው ይህን ነው፤ በእርግጥም እንዲህ ሊያደርገው ይችላል። በወይኑ ግንድ ውስጥ ያለማቋረጥ መኖራችን በፍቅሩ ውስጥ መኖር ሊሆን ይገባዋል።

ምናልባት ከፍ ስላለው ወይም ጥልቅ ስለ ሆነው ሕይወት፣ ስለ በለጸገው ወይም ስለ ተሟላው ሕይወት፣ ስለ ተትረፈረፈው ሕይወት የሚነገረውን ሰምተህ ወይም አንብበህ ይሆናል። ደግሞም አንዳንዶች ያለማቋረጥ ይወድቁና ይሰናከሉ የነበረበት ሕይወታቸው ተለውጦ፣ እየተጠበቁና እየበረቱ እጅግም ደስ እየተሰኙ ወደሚኖሩበት የተባረከ ተሞክሮ ስለ ገቡበት አስደናቂ ለውጥ እንደ መሰከሩ ታውቅ ይሆናል። ይህ ታላቅ በረከት እንዴት እንደ መጣላቸው ብትጠይቃቸው ብዙዎቹ እንዲህ ይሉሃል፦ ይህ በክርስቶስ ፍቅር መኖር እውን እንዲሆን የታሰበ መሆኑን ወደ ማመን ተመሩ፤ ስለ እርሱም ሁሉን ለመተው ፈቃደኞች ሆኑ፤ ከዚያም ክርስቶስ ይህን በእነርሱ እውን እንደሚያደርገው እንዲታመኑት ተቻላቸው፤ ነገሩ ይህ ብቻ ነው።

አብ ለወልድ ያለው ፍቅር ስሜት ብቻ አይደለም—መለኮታዊ ሕይወት፣ ወሰን የሌለው ብርታት፣ የማይቋቋሙት ኃይል ነው። ክርስቶስን በሕይወትና በሞት በመቃብርም አሻግሮታል። አብ ወደደው፣ በእርሱም ኖረ፣ ሁሉንም አደረገለት። እንዲሁም ክርስቶስ ለእኛ ያለው ፍቅር ሊሰጠን ደስ የሚለውን ሁሉ በውስጣችን የሚሠራ ወሰን የሌለው ሕያው ኃይል ነው። የክርስትና ሕይወታችን ድካም፣ ይህ መለኮታዊ ፍቅር በእርግጥ በእኛ ደስ እንደሚሰኝ፣ እኛንም ገንዘቡ አድርጎ ሁሉን በእኛ እንደሚሠራ ለማመን ጊዜ አለመውሰዳችን ነው። የወይኑ ግንድ ቅርንጫፉን ፈጽሞ እንዴት እንደሚሸከመው፣ በውስጡም ሁሉን እንዴት ፍጹም አድርጎ እንደሚሠራ ለማየት ጊዜ አንወስድም። ክርስቶስ ብቻ ሊያደርገው የሚችለውን፣ ክርስቶስ፣ ኦ፣ በብዙ ፍቅር ሊያደርግልን የሚናፍቀውን ነገር ለራሳችን ለማድረግ እንጣጣራለን።

በፊት የተናገርነው ለውጥ ምሥጢርና የአዲስ ሕይወት መጀመሪያ ይህ ነው፦ ነፍስ ሁሉን ለማድረግ ፈቃደኛ የሆነውን ይህን ወሰን የሌለው ፍቅር ስታይና ራሷን ለእርሱ አሳልፋ ስትሰጥ ነው። «በፍቅሬ ኑሩ»። እንዲህ በየደቂቃው መኖር እንደሚቻል ማመን፤ ይህን አስቸጋሪ ወይም የማይቻል የሚያደርገው ሁሉ በክርስቶስ በራሱ እንደሚሸነፍ ማመን፤ ፍቅር በእርግጥ ራሱን ሙሉ በሙሉ ሊሰጠንና ፈጽሞ ላይተወን የሚናፍቅ ወሰን የሌለው ናፍቆት መሆኑን ማመን፤ በዚህም እምነት ይህን በእኛ እንዲሠራ ራሳችንን በክርስቶስ ላይ መጣል፤ የእውነተኛው የክርስትና ሕይወት ምሥጢር ይህ ነው።

ታዲያ ወደዚህ እምነት እንዴት መድረስ ይቻላል? የማይታየውን ልታይና ገንዘብህ ልታደርግ ብትወድ ከሚታየው ዘወር በል። ከኢየሱስ ጋር ብዙ ጊዜ ውሰድ፤ በአብ ፍቅር የሚኖርና አንተም በፍቅሩ እንድትኖር የሚፈልግ ሰማያዊ የወይን ግንድ አድርገህ ተመልከተው። ልብህ በእርሱና በፍቅሩ እርግጠኝነት እንዲሞላ ብትወድ፣ ከራስህ፣ ከጥረትህና ከእምነትህም ዘወር በል። መኖር ማለት አንድን ስፍራ ይዞ በዚያ ለመቆየት ከሌላው ነገር ሁሉ መውጣት ማለት ነው። ከሌላው ሁሉ ራቅ፤ ልብህንም በኢየሱስና በፍቅሩ ላይ አድርግ፤ ያ ፍቅር እምነትህን ያነቃዋል፣ ያጸናዋልም። በዚያ ፍቅር ተጠመድ፤ በአምልኮ ተመልከተው፤ ተጠባበቀው። እርሱ ወደ አንተ እንደሚዘረጋ፣ በኃይሉም ወደ ራሱ አንሥቶ መኖሪያህና ቤትህ እንደሚሆን እርግጠኛ ልትሆን ትችላለህ።

በፍቅሬ ኑሩ። ጌታ ኢየሱስ ሆይ፣ አያለሁ፤ በመለኮታዊ የፍቅርና የበረከት ሙላትህ ለእኛ እውነተኛው የወይን ግንድ ያደረገህ በአባትህ ፍቅር መኖርህ ነበር። ኦ፣ እኔም እንዲሁ እንደ ቅርንጫፍ በፍቅርህ ልኑር፤ ሙላቱ እንዲሞላኝና በዙሪያዬ ባሉት ሁሉ ላይ እንዲትረፈረፍ።

ገጽ 1 / 1 · 2 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል