ምዕራፍ 4 · 16 ደቂቃ ንባብ · 20 ደቂቃ ማዳመጥ
በትርንጎ ዛፍ ሥር
በትርንጎ ዛፍ ሥር።
የታወቀ ክርስቶስ ልንጠቀምበት የሚገባ ክርስቶስ ነው። ሙሽራይቱ ውዴዋ ፍሬ እንደሚያፈራ ዛፍ መሆኑን አወቀች፤ ወዲያውም በጥላው ሥር ተቀመጠች፥ ፍሬውንም በላች። ስለ ክርስቶስ ይህን ያህል እያወቅን በእርሱ ግን ጥቂት ብቻ ደስ መሰኘታችን ያሳዝናል። ተሞክሮአችን ከእውቀታችን ጋር እኩል ይራመድ፤ ያም ተሞክሮ ጌታችንን በተግባር በመጠቀም የተሠራ ይሁን! ኢየሱስ ጥላ ይጥላል፤ በሥሩ እንቀመጥ። ኢየሱስ ፍሬ ይሰጣል፤ ጣፋጭነቱን እንቅመስ። አብልጦ ለመማር የሚያስችለው መንገድ የምታውቁትን መጠቀም እንደ ሆነ እርግጠኞች ሁኑ፤ ደግሞም አንድን እውነት በሚገባ ለመማር የሚቻለው በተሞክሮ በመማር ነው። አንድን ትምህርት በግል ፈትናችሁና ሞክራችሁ ስታረጋግጡት፥ ማንም ይቃወመኛል ብላችሁ ሳትፈሩ ታውቁታላችሁ። በመኃልዩ ውስጥ ያለችው ሙሽራ እንዲህ የምትል ያህል ናት፤ «ውዴ ጥላ እንደሚጥል እርግጠኛ ነኝ፥ በሥሩ ተቀምጬአለሁና፤ ጣፋጭ ፍሬም እንደሚያፈራ አምኛለሁ፥ ቀምሼዋለሁና።» የክርስቶስን የማዳን ኃይል ለማረጋገጥ ከሁሉ የተሻለው መንገድ በእርሱ ታምኖ ራስን መዳን ነው፤ የቅድስት እምነታችንን መለኮታዊነት እርግጠኛ ከሆኑት ሁሉ መካከል መለኮታዊ ኃይሏ በራሳቸው ላይ የሚሰማቸውን ያህል እርግጠኛ የሆነ የለም። በማመዛዘን ወንጌልን ወደ ማመን ልትደርሱ ትችላላችሁ፤ ተጨማሪ በማመዛዘንም በቀና ትምህርት ልትጸኑ ትችላላችሁ፤ ነገር ግን የግል ፈተናና እውነትን በውስጥ ማወቅ ወደር የሌላቸው ምርጥ ማስረጃዎች ናቸው። ኢየሱስ በዱር ዛፎች መካከል እንዳለ ትርንጎ ከሆነ ከእርሱ አትራቁ፤ ነገር ግን በጥላው ሥር ተቀመጡ፥ ፍሬውንም ቅመሱ። እርሱ መድኃኒት ነው፤ ይህን እውነት እያመናችሁ ሳትድኑ አትቅሩ። ክርስቶስን በምታውቁት መጠን በዚያው መጠን ተጠቀሙበት። ይህ ጤናማ አስተዋይነት አይደለምን?
ደግሞም ክርስቶስን በተቻለን መንገድ ሁሉ ለመጠቀም ነጻነት እንዳለን እንናገራለን። ጥላውንም ፍሬውንም ልንደሰትባቸው እንችላለን። ክርስቶስ ወሰን በሌለው ትሕትናው ለተቸገሩ ነፍሳት አለ። ኦ፥ ደግመን እንናገረው፤ ድፍረት ያለበት ቃል ነው፥ ግን እውነት ነው፤ ክርስቶስ ኢየሱስ ጌታችን ለሕዝቡ ጥቅም ይኖራል። መድኃኒት የሚኖረው ለማዳን ብቻ ነው። ሐኪም የሚኖረው ለመፈወስ ነው። መልካሙ እረኛ ስለ በጎቹ ይኖራል፤ አዎን፥ ይሞታልም። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በልቡ ጠቅልሎናል፤ ከሹመቶቹ ሁሉ፥ ከክብሩ ሁሉ፥ ከባሕርዩ መልክ ሁሉ፥ ካደረገውም ሁሉ፥ ገናም ከሚያደርገው ሁሉ ጋር በጥብቅ ተጋምደናል። የኃጢአተኞች ወዳጅ ለኃጢአተኞች ይኖራል፤ ኃጢአተኞችም እርሱን ሊያገኙትና እስከ መጨረሻ ሊጠቀሙበት ይችላሉ። እንደምንተነፍሰው አየር ለእኛ በነጻ የተሰጠ ነው። ምንጮች የተጠሙ እንዲጠጡ ካልሆነ ለምንድር ናቸው? ወደብስ በማዕበል የተንገላቱ መርከቦች መጠጊያ እንዲያገኙበት ካልሆነ ለምንድር ነው? ክርስቶስስ እንደ እኛ ያሉ ምስኪን በደለኞች ወደ እርሱ መጥተው እንዲመለከቱና በሕይወት እንዲኖሩ፥ ከዚያም በኋላ ፍላጎታችን ሁሉ ከሙላቱ እንዲሟላልን ካልሆነ ለምንድር ነው?
በዚህ መንገድ በሩ ተከፍቶልናል፤ ሙሉ በሙሉ እንድትደሰቱባቸው የምንጸልይላችሁን በጽሑፉ ውስጥ ያሉትን ሁለት ነገሮች ስንመለከት መንፈስ ቅዱስ እንድንገባ እንዲረዳን እንጸልያለን። መጀመሪያ፥ የልብ ዕረፍት በክርስቶስ፤ «በጥላው ሥር በታላቅ ደስታ ተቀመጥሁ።» ሁለተኛም፥ የልብ መታደስ በክርስቶስ፤ «ፍሬውም ለጕሮሮዬ ጣፋጭ ነበረ።»
1ኛ. ለመጀመር፥ እዚህ የልብ ዕረፍት በክርስቶስ አለን። ይህን ለማብራራት ይህን ቃል የተናገረችውን ሰው ጠባይ እንመልከት። «በጥላው ሥር በታላቅ ደስታ ተቀመጥሁ» ያለችው አድካሚ ጕዞ ምን እንደ ሆነ ቀድሞ የምታውቅ ነበረች፤ ስለዚህም ዕረፍትን ታከብር ነበር፤ ደክሞ የማያውቅ ሰው የዕረፍትን ጣዕም ምንም አያውቅምና። ያልደከመበትን እንጀራ የሚበላ፥ ከግንባሩም አንድ ጠብታ የታማኝ ላብ ፈስሶ የማያውቅ ሰነፍ ዕረፍት አይገባውም፥ ምን እንደ ሆነም አያውቅም። ዕረፍት የምትጣፍጠው ለሠራተኛ ሰው ነው፤ ብዙ ማይል አድካሚ መንገድ ተጕዘን ዝለን በመጨረሻ ተመችቶን የምንቀመጥበት ጥላ ወዳለበት ስፍራ ስንደርስ ያን ጊዜ በደስታ እንሞላለን።
ሙሽራይቱ ውዴዋን ስትፈልግ ነበር፤ ስትፈልገውም ልታገኘው የምትችልበትን ስፍራ ጠየቀች። «ነፍሴ የወደደችህ አንተ ሆይ፥ ወዴት እንደምታሰማራ፥ በቀትርም ጊዜ መንጋህን ወዴት እንደምታሳርፍ ንገረኝ» ትላለች። መልሱም «በመንጎቹ ፍለጋ ውጪ» ተብሎ ተሰጣት። መንገዷን ሄደች፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን እንዲህ ብላ ቈረጠች፤ «በጥላው ሥር እቀመጣለሁ።»
ብዙዎቻችሁ ሰላምን ለማግኘት መንገዳችሁን በመሄድ እጅግ ደክማችኋል። አንዳንዶቻችሁ ሥርዓተ አምልኮን ሞከራችሁ፥ ታመናችሁባቸውም፥ ካህኑም ሊረዳችሁ መጣ፤ እርሱ ግን በልባችሁ ጭንቀት አፌዘ። ሌሎቻችሁ በልዩ ልዩ የአስተሳሰብ ሥርዓቶች መልሕቅ የምትጥሉበትን ስፍራ ፈለጋችሁ፤ ነገር ግን ከማዕበል ወደ ማዕበል እየተወረወራችሁ በሚናወጠው የግምት ባሕር ላይ ዕረፍት አላገኛችሁም። ከእናንተም ብዙዎቹ ለሕሊናችሁ ዕረፍት ለማግኘት በመልካም ሥራችሁ ሞከራችሁ። ጸሎታችሁን አበዛችሁ፥ የእንባ ጐርፍ አፈሰሳችሁ፤ በምጽዋትና በመሳሰሉት አንዳች ብቃት እንዲቈጠርላችሁ፥ ልባችሁም በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን እንዲሰማው፥ በዚህም ዕረፍት እንዲያገኝ ተስፋ አደረጋችሁ። ከዮናስ ጋር በመርከብ የነበሩት ሰዎች መርከባቸውን ወደ የብስ ለመመለስ አጥብቀው እንደ ቀዘፉ፥ ነገር ግን ባሕሩ እየተናወጠና እየተነሣባቸው ስለ ሄደ እንዳልቻሉ፥ እናንተም ደከማችሁ፥ ደከማችሁ። በዚያ መንገድ ማምለጫ አልነበራችሁም፤ ስለዚህም ወደ ሌላ መንገድ፥ በኢየሱስ ወደ ማረፍ ተገፋችሁ። የኃጢአት ስሜት ተጭኖኝ፥ በፍጹም ነፍሴ ሰላምን ለማግኘት ስፈልግ፥ ከሰማይ በታች በየትኛውም ስፍራ ከፍ ብዬም ዝቅ ብዬም ላገኘው ያልቻልሁበትን ጊዜ ልቤ ወደ ኋላ ያስባል፤ ነገር ግን «በዛፍ ላይ የተሰቀለውን» ስለ ኃጢአት ምትክ ሆኖ ባየሁ ጊዜ ልቤ በጥላው ሥር በታላቅ ደስታ ተቀመጠ። ልቤም ከራሱ ጋር እንዲህ ብሎ አመዛዘነ፤ ኢየሱስ በእኔ ፋንታ መከራ ተቀበለን? እንግዲያስ እኔ መከራ አልቀበልም። ኃጢአቴን ተሸከመን? እንግዲያስ እኔ አልሸከመውም። እግዚአብሔር ልጁን በእኔ ፋንታ ምትክ አድርጎ ተቀበለውን? እንግዲያስ ከቶ አይመታኝም። ኢየሱስ መሥዋዕቴ ሆኖ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት አገኘን? እንግዲያስ ጌታን ያረካ እኔንም በሚገባ ሊያረካኝ ይገባል፤ ስለዚህ ከዚህ ወዲያ አልሄድም፥ ነገር ግን «በጥላው ሥር እቀመጣለሁ»፥ ደስ የሚያሰኝ ዕረፍትንም እደሰታለሁ።
«በጥላው ሥር በታላቅ ደስታ ተቀመጥሁ» ያለችው ጥላን ልታደንቅ ትችል ነበር፤ ፀሐይ አጥቍሯታልና። «ፀሐይ አጥቍሮኛልና፥ ጥቍር ስለ ሆንሁ አትመልከቱኝ» ብላ የጮኸችውን አሁን አላነበብንምን? ሙቀት ምን እንደ ሆነ፥ የሚያቃጥል ፀሐይ ምን እንደ ሆነ ታውቅ ነበር፤ ስለዚህ ጥላ ደስ አሰኛት። እጅግ ሞቃት በሆነ አገር እስክትጓዙ ድረስ የጥላን ጣፋጭነት ምንም አታውቁም፤ ያን ጊዜ ግን በእርሱ ደስ ትሰኛላችሁ። የመለኮትን ቍጣ ሙቀት ተሰምቷችሁ ያውቃልን? ታላቁ ፀሐይ—መለወጥም በመዞርም የተደረገ ጥላ የሌለበት ያ ፀሐይ—እጅግ የሚያቃጥሉ ጨረሮቹን፥ የቅድስናውንና የፍትሑን ጨረሮች፥ በእናንተ ላይ ወርውሮ ያውቃልን? በዚያ ታላቅ ብርሃን በሚለበልብ ጨረር ሥር ተሸማቅቃችሁ «በቍጣህ አልቀናል» ብላችሁ ታውቃላችሁን? ይህ ተሰምቷችሁ ከሆነ፥ ወደ ክርስቶስ የማስተስረያ መሥዋዕት ጥላ ሥር መምጣት እጅግ የተባረከ ነገር እንደ ሆነ አግኝታችኋል። ጥላ፥ እንደምታውቁት፥ በእኛና በብርሃኑና በሙቀቱ መካከል አንድ አካል ሲገባ ይጣላል፤ የጌታችንም እጅግ የተባረከ አካል በእኛና በሚያቃጥለው የመለኮት ፍትሕ ፀሐይ መካከል ገብቷል፤ ስለዚህ በምልጃው ጥላ ሥር በታላቅ ደስታ እንቀመጣለን።
አሁንም ሌላ ፀሐይ ሊያቃጥለን ቢጀምር ወደ ጌታችን እንሸሻለን። የቤት ችግር ወይም የሥራ ጭንቀት ወይም የሰይጣን ፈተና ወይም የውስጥ ርኵሰት ቢያስጨንቀን፥ በእርሱ ሥር ለመሸሸግ ወደ ኢየሱስ ጥላ እንቸኩላለን፤ በዚያም በቀዝቃዛው መታደስ በታላቅ ደስታ «እንቀመጣለን»። የተባረከው ጌታችን በመካከል መግባቱ የውስጣዊ ጸጥታችን ምክንያት ነው። ፀሐይ ሊያቃጥለኝ አይችልም፥ እርሱን አቃጥሎታልና። መከራዬ ሊያስጨንቀኝ አያስፈልግም፥ እርሱ መከራዬን ወስዶአልና፥ እኔም በእጁ ትቼዋለሁና። «በጥላው ሥር ተቀመጥሁ።»
ስለ ሙሽራይቱ እነዚህን ሁለት ነገሮች በሚገባ አስተውሉ። መድከም ምን እንደ ሆነ ታውቅ ነበር፥ በፀሐይ መጥቈርም ምን እንደ ሆነ ታውቅ ነበር፤ እናንተም እነዚህን ሁለት ነገሮች በምታውቁት መጠን ለክርስቶስ የምትሰጡት ግምት ከፍ ይላል። በእግዚአብሔር ቍጣ ሥር ተጨንቃችሁ የማታውቁ መድኃኒቱን አክብራችሁት አታውቁም። ጅረቶችና ወንዞች በበዙበት በዚህ አገር ውኃ ዋጋው ትንሽ ነው፤ ስለዚህም በተለምዶ መንገዶችን ትረጩበታላችሁ፤ ነገር ግን በሚያቃጥል አሸዋ ላይ የአንድ ቀን ጕዞ ብትጓዙ አንድ ጽዋ ቀዝቃዛ ውኃ የንጉሥ ቤዛ ያህል ዋጋ እንደሚኖረው አረጋግጥላችኋለሁ፤ እንዲሁም ክርስቶስ ለተጠሙ ነፍሳት ክቡር ነው፥ ለሌላ ለማንም ግን አይደለም።
አሁንም ሙሽራይቱ ዐርፋና ደስ ብሏት በተቀመጠች ጊዜ ጥላ ጋረዳት። «በጥላው ሥር ተቀመጥሁ» ትላለች። በተወደደው ጌታችን ሙሉ በሙሉ ተጋርዶ ከመሰማት የበለጠ ደስ የሚያሰኝ የአእምሮ ሁኔታ አላውቅም። ጥቍሩ ኃጢአቴ እዚህ አለ፤ ነገር ግን ክቡር ደሙ በዚያ ኃጢአቴን እየጋረደ ለዘላለም ይሰውረዋል። በተፈጥሮ ያለሁበት ሁኔታ እዚህ አለ፥ የእግዚአብሔር ጠላት ነኝ፤ ነገር ግን በደሙ ከእግዚአብሔር ጋር ያስታረቀኝ እርሱ ያንንም ጋርዶታል፤ ስለዚህ አሁን ወዳጅ በመሆኔ ደስታ አንድ ጊዜ ጠላት እንደ ነበርሁ እረሳለሁ። እኔ እጅግ ደካማ ነኝ፤ እርሱ ግን ብርቱ ነው፥ ብርታቱም ድካሜን ይጋርደዋል። እኔ እጅግ ድሀ ነኝ፤ እርሱ ግን ባለጠግነት ሁሉ አለው፥ ባለጠግነቱም ድህነቴን ይጋርደዋል። እኔ ፈጽሞ የማይገባኝ ነኝ፤ እርሱ ግን እጅግ የሚገባው ነው፤ ስሙንም ብጠቀም የሚገባኝ ብሆን የምቀበለውን ያህል እቀበላለሁ፤ የእርሱ ብቁነት የእኔን አለመብቃት ይጋርዳል። እውነቱን በሌላ በኩል አድርጎ እንዲህ ማለትም እጅግ ክቡር ነው፤ በእኔ ውስጥ መልካም ነገር ቢኖር ከእርሱ ጋር ራሴን ሳነጻጽር መልካም አይደለም፥ የእርሱ መልካምነት ፈጽሞ ያደበዝዘዋልና ይጋርደዋልምና። እወደዋለሁ ማለት እችላለሁን? አዎን እወደዋለሁ፤ ነገር ግን ፍቅሩ ስለሚጋርደው ፍቅር ብዬ ልጠራው አልደፍርም። አገለግለዋለሁ ብዬ አሰብሁን? ባገለግለው እወድ ነበር፤ ነገር ግን እርሱ ላደረገልኝ ሲነጻጸር የእኔ ምስኪን አገልግሎት ሊጠቀስ የሚገባው አይደለም። ጥቂት ቅድስና አለኝ ብዬ አሰብሁን? መንፈሱ በእኔ የሚሠራውን መካድ የለብኝም፤ ነገር ግን ነውር የሌለበትን ሕይወቱንና መለኮታዊ ፍጽምናዎቹን ሁሉ ሳስብ እኔ የት ነኝ? ምንስ ነኝ? ይህ አንዳንድ ጊዜ ተሰምቷችሁ አያውቅምን? እንደ ምንም እስክትሆኑ ድረስ በጌታችሁ ሥር ተጋርዳችሁና ተሰውራችሁ አታውቁምን? ጌታዬ እስከ ከበረ ድረስ በድሆች መጠለያ ብሞት ምንም እንደማይጎዳ መሰማት ምን እንደ ሆነ እኔ ራሴ አውቃለሁ። ሟች ሰዎች ቢወዱ ስሜን እንደ ክፉ ይጣሉት፤ የእርሱ ውድ ስም አንድ ቀን በሰማይ ላይ በከዋክብት የሚጻፍ ከሆነ ምን ይጎዳል? እርሱ ይጋርደኝ፤ እንዲህ በመሆኑ ደስ ይለኛል።
ሙሽራይቱ ሙሉ በሙሉ በተጋረደች ጊዜ ታላቅ ደስታ እንደ ተሰማት ትነግረናለች። ታላቁ «እኔ» ከራሱ የሚበልጥን ለመቀበል አይችልምና ታላቅ ደስታ ከቶ አያገኝም፤ ትሑቱ አማኝ ግን በጌታው በመጋረድ ደስታውን ያገኛል። ከራሳችን ከሚመስለን ብርሃን ይልቅ በኢየሱስ ጥላ ውስጥ የበለጠ ደስታ አለን። ሙሽራይቱ ታላቅ ደስታ ነበራት። እናንተ ክርስቲያኖች ታላቅ ደስታ እንዳላችሁ ተስፋ አደርጋለሁ፤ ከሌላችሁ ግን በእርግጥ የእግዚአብሔር ሕዝብ መሆናችሁን ራሳችሁን ልትጠይቁ ይገባችኋል። ደስ ያለው ፊት ማየት እወዳለሁ፤ አዎን፥ የእግዚአብሔር ቅዱሳን በሆኑት ልብ ውስጥ ስላለው ሐሤትም መስማት እወዳለሁ! ሃይማኖትና ትካዜ የተጋቡ፥ ከቶም ሊፋቱ የማይገባቸው የሚመስላቸው ሰዎች አሉ። በእሑድ መጋረጃዎችን አውርዱ፥ ክፍሎቹንም አጨልሙ፤ የአትክልት ቦታ ወይም ያበበች ጽጌረዳ ቢኖራችሁ እንዲህ ያሉ ውበቶች መኖራቸውን ለመርሳት ሞክሩ፤ እግዚአብሔርን በተቻላችሁ መጠን በሐዘን ልታገለግሉ አይገባችሁምን? መጽሐፋችሁን በብብታችሁ ይዛችሁ ወደ መገረፊያ ግንድ እንደሚነዱ ሰዎች በሐዘን ወደ አምልኮ ስፍራችሁ ተጐተቱ። ብትወዱ እንዲህ አድርጉ፤ ለእኔ ግን ልቤን ደስ የሚያሰኘውን፥ ነፍሴን የሚያቀጣጥለውን፥ በቅንዓትና በደስታ የሚሞላኝን ሃይማኖት ስጡኝ፤—ያ የሰማይ ሃይማኖት ሊሆን ይችላልና፥ በመንፈስ ከተጻፈው መኃልይ ተሞክሮም ጋር ይስማማልና።
ደስታ ምን ማለት እንደ ሆነ እንደምናውቅ ተስፋ ባደርግም፥ በእርሱ እየተደሰትን እንደ ተቀመጥን ራሳችንን ለመግለጽ የሚበቃ ያህል አለን ወይ ብዬ እጠራጠራለሁ። በኢየሱስ እግር ሥር ለመቀመጥ በቂ ጊዜ ትሰጣላችሁን? የደስታ ስፍራ በዚያ ነው፤ በእርሱ ትኖራላችሁን? በጥላው ሥር ተቀመጡ። አንዱ «ጊዜ የለኝም» ብሎ ይጮኻል። ትንሽ ለማግኘት ሞክር። በሌላ መንገድ ማግኘት ካልቻልህ ከእንቅልፍህ ስረቀው። ለልብህ ጊዜ ስጥ። አንድ ሰው ከሚስቱ ጋር አምስት ደቂቃ እንኳ ሳያሳልፍ ዘወትር በብርቱ ሥራ ለመሥራት ቢገደድ እጅግ ያሳዝን ነበር። ይህማ ባርነት ነው፥ አይደለምን? እንግዲያስ ከሁሉ ከሚበልጠው ውዳችን ጋር ለመነጋገር ጊዜ አይኖረንምን? በእርግጥ እንደ ምንም ብለን በጥላው ሥር በታላቅ ደስታ ከመቀመጥ በቀር ሌላ ምንም የማንሠራበትን ጥቂት ጊዜ ልናወጣ እንችላለን! መጽሐፍ ቅዱሴን ይዤ ለራሴ ልመገበው ስፈልግ፥ ብዙ ጊዜ በጥቅሱ ላይ ስለ መስበክና ከእርሱ ምን እንደምነግራችሁ ማሰብ እጀምራለሁ። ይህ አይሆንም፤ ከዚያ ርቄ በግሌ በኢየሱስ እግር ሥር እቀመጥ ዘንድ ታበርናክል የሚባል ጉባኤ መኖሩን መርሳት አለብኝ። ኦ፥ በእርሱ በመጋረድ ውስጥ ጥልቅ ደስታ አለ! እርሱ በአጠገባችሁ ነው፥ እናንተም ታውቃላችሁ። ተጽዕኖው ስለሚከብባችሁ ልታዩት እንደምትችሉ ያህል ውድ መገኘቱ በእርግጥ ከእናንተ ጋር ነው።
ብዙ ጊዜ ወዳጅ በትከሻዬ ላይ እንደሚመለከት ኢየሱስ በእኔ ላይ ያጐነበሰ ያህል ተሰምቶኛል። ቀዝቃዛ ጥላ በግንባራችሁ ላይ ባይወርድም፥ እንደ ወረደ ያህል ጥላው ሊሰማችሁ ይችላል፤ ልባችሁ ጸጥ ይላልና፤ በቤተሰብ ደክማችሁ ወይም በቤተ ክርስቲያን ተጨንቃችሁ ወይም በራሳችሁ ተበሳጭታችሁ ከሆነ፥ ጌታችሁን ካያችሁበት እልፍኝ ትወርዳላችሁ፤ ጌታን አይታችኋልና ለሕይወት ውጊያ እንደ ታጠቃችሁ፥ ለመከራዎቹና ለፈተናዎቹም እንደ ተዘጋጃችሁ ይሰማችኋል። «በጥላው ሥር» አለች «በታላቅ ደስታ ተቀመጥሁ።» ያ ደስታ ምን ያህል ታላቅ እንደ ነበረ ልትናገር አልቻለችም፤ ነገር ግን በእርሱ እንደ ተሸነፈች፥ በብፅዕና ሸክም ሥር ዝም ብላ መቀመጥ እንደሚያስፈልጋት ሆና ተቀመጠች። ስለ ክርስቲያኖች ስውር ደስታ ብዙ መናገር አልወድም፤ ሐሳባችንን የማይረዱ አንዳንዶች ሁልጊዜ በዙሪያችን አሉና፤ ነገር ግን ይህን ያህል ለመናገር እደፍራለሁ—የዓለም ሰዎች የአማኞች ስውር ደስታ ምን እንደ ሆነ እንኳ መገመት ቢችሉ፥ ከእኛ ጋር ለመካፈል ዓይናቸውን ይሰጡ ነበር። መከራ አለብን፥ እናምናለንም፥ እንዲኖረንም እንጠብቃለን፤ ነገር ግን ብዙ ጊዜ ከልክ የሚያልፍ ደስታ አለን። አንዳንድ ጊዜ ነፍሳችንን ወደ ደስታ ዐውሎ ነፋስ የሚወረውረውን ሐሤት ሌሎች እንዲመሰክሩ አንወድም። ምን ማለት እንደ ሆነ ታውቃላችሁ፥ አይደለምን? ከሰማያዊው ሙሽራ ጋር ብቻችሁን በነበራችሁ ጊዜ፥ ለእናንተ ለምስኪኑና ለማይገባው ስለ ክርስቶስ ጣፋጭ ፍቅር ለመላእክት ልትነግሩ ፈለጋችሁ። ሱራፌል የእግዚአብሔርን ጸጋ ከፍታና ጥልቀት እናንተ እንደምታውቁት አያውቁምና የወርቅ በገናዎችን አዲስ ዜማ ልታስተምሩ እንኳ ተመኛችሁ።
ሙሽራይቱ ታላቅ ደስታ ነበራት፤ ይህንም ያላረሳችው በመሆኑ በዚህ አንድ ምክንያት እናውቃለን። ይህ ቍጥርና መኃልዩ ሁሉ የተደሰተችበትን ነገር ማስታወሻ ነው። «በጥላው ሥር ተቀመጥሁ» ትላለች። ምናልባት ከአንድ ወር በፊት፥ ምናልባትም ከብዙ ዓመታት በፊት ሊሆን ይችላል፤ እርሷ ግን አልረሳችውም። ከእግዚአብሔር ጋር ያለ ኅብረት ደስታ በዕብነ በረድ ላይ ተጽፏል። ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር የነበረ የኅብረት ትዝታ «በዘላለም ናስ ላይ እንደ ተቀረጸ» ነው። ሐዋርያው «ከአሥራ አራት ዓመት በፊት» ይላል፥ «ሰውን በክርስቶስ አውቃለሁ።» አሃ፥ ያን ሁሉ ዓመት ሊያስታውሰው የሚገባ ነበር! ደስታውን አልተናገረም ነበር፤ ነገር ግን አከማችቶ ጠብቆት ነበር። «ከአሥራ አራት ዓመት በፊት ሰውን በክርስቶስ አውቃለሁ፥ በሥጋ እንደ ሆነ አላውቅም ወይም ከሥጋ ውጭ እንደ ሆነ አላውቅም» ይላል፤ ደስታው ይህን ያህል ታላቅ ነበርና። ወደ ኋላ ስንመለከት እንደ ሰው ልማድ ያሳለፍናቸውን የልደት ቀኖችን፥ በዓላትንና የችቦ ምሽቶችን እንረሳለን፤ ከውዱ ጋር የነበረንን የኅብረት ጊዜያት ግን በቀላሉ እናስታውሳለን። ታቦሮቻችንን፥ የመለወጥ ኅብረት ጊዜያችንን አውቀናል፤ እንደ ጴጥሮስም «በቅዱሱ ተራራ ከእርሱ ጋር» የነበርንበትን እናስታውሳለን። ራሳችን በመምህሩ ደረት ላይ ተደግፏል፤ ያንንም ጥልቅ ደስታ ከቶ ልንረሳው አንችልም፤ የተደሰትንበትንም ደስታ ለሌሎች ጥቅም በመዝገብ ከማስፈር ቸል አንልም።
አሁን የጉዳዩን የመጀመሪያ ክፍል እተዋለሁ፤ ምን ያህል በሚያምር ሁኔታ ተፈጥሯዊ እንደ ሆነ ብቻ አስተውላለሁ። ዛፍ ነበረ፥ እርሷም በጥላው ሥር ተቀመጠች፤ የተገደደ ነገር፥ የወግ ነገር አልነበረም። እንዲሁም እውነተኛ እግዚአብሔርን መምሰል ሁልጊዜ ከጤናማ አስተዋይነት ጋር፥ ከሁሉ ይልቅ ተገቢ፥ ያማረ፥ ጥበብ ያለበትና ተፈጥሯዊ ከሚመስለው ጋር የሚስማማ ሊሆን ይገባዋል። ክርስቶስ በዚያ አለ፤ በእርሱ ልንደሰት እንችላለን፤ ይህን መብት አንናቀው።
2ኛ. የጉዳያችን ሁለተኛው ክፍል የልብ መታደስ በክርስቶስ ነው። ፍሬውም ለጕሮሮዬ ጣፋጭ ነበረ። እዚህ አላስፋፋም፤ ነገር ግን በኋላ ልታብራሩአቸው የምትችሉትን ሐሳቦች በአጭሩ እሰጣችኋለሁ። ቀድሞ በጥላው ሥር እስክትሆን ድረስ የዛፉን ፍሬ አልተመገበችም። በክርስቶስ እስክትታመኑ ድረስ የክርስቶስን መልካም ነገሮች ማወቅ አይቻልም። ከጥላው ውጭ ላሉት አንድም ጣፋጭ ትርንጎ አይወድቅላቸውም። ኑ፥ በክርስቶስ ታመኑ፤ ያን ጊዜም በክርስቶስ ያለውን ሁሉ ትደሰቱበታላችሁ። እናንተ የማታምኑ ሆይ፥ የምታጡትን ብታውቁ! በጥላው ሥር ብቻ ብትቀመጡ ሁሉ ይሆንላችኋል፤ እምቢ ብትሉ ግን ከክርስቶስ መልካም ነገር አንዳች የእናንተ አይሆንም።
ነገር ግን ልክ በጥላው ሥር በሆነች ጊዜ ፍሬው ሁሉ የእርሷ ሆነ። «በጥላው ሥር ተቀመጥሁ» ትላለች፤ ከዚያም «ፍሬውም ለጕሮሮዬ ጣፋጭ ነበረ።» ወዳጄ ሆይ፥ በኢየሱስ ታምናለህን? እንግዲያስ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ የአንተ ነው፤ ዛፉ የአንተ ከሆነ ፍሬውን ልትበላ ይገባሃል። እርሱ ራሱ ፈጽሞ የአንተ ስለ ሆነ፥ ቤዛነቱና ከእርሱ የሚገኘው ይቅርታ፥ ሕያው ኃይሉ፥ ብርቱ ምልጃው፥ የዳግም ምጽአቱ ክብር፥ የእርሱ የሆነውም ሁሉ ለግልህና ለአሁኑ ጥቅምህና ደስታህ ተሰጥቶሃል። ክርስቶስ የእናንተ ስለ ሆነ ሁሉ የእናንተ ነው። ብቻ ሙሽራይቱን ምሰሏት፤ ፍሬው የእርሷ መሆኑን ባወቀች ጊዜ በላችው። በዚህ በጥብቅ ተከተሏት። ብዙ አማኞች ተስፋዎቹን የራሳቸው አድርገው የማይመገቡባቸው መሆናቸው ታላቅ ስሕተት ነው። እንደ እነርሱ አትሳቱ። በጥላው ሥር ፍሬውን ለመብላት መብት አላችሁ። ራሳችሁን ከቅዱሱ ግብዣ አትከልክሉ።
እንግዲህ ጽሑፉን ስናነብ ይህን ፍሬ ያለ ድካም ያገኘችው ይመስላል። ምሳሌው «ፍሬውን ሊያገኝ የሚወድ ዛፉን ይውጣ» ይላል። እርሷ ግን አልወጣችም፤ «በጥላው ሥር ተቀመጥሁ» ትላለችና። ፍሬው ወደ እርሷ ወደቀ ብዬ አስባለሁ። ከእኛም ጋር እንዲሁ እንደ ሆነ አውቃለሁ። ከእንግዲህ ገንዘባችንን እንጀራ ላልሆነ፥ ድካማችንንም ለማያጠግብ አናጠፋም፤ ነገር ግን በጌታችን ጥላ ሥር እንቀመጣለን፥ መልካሙንም እንበላለን፥ ነፍሳችንም በጣፋጭነት ደስ ትሰኛለች። ክርስቲያን ሆይ፥ ና፤ ከመስቀሉ በታች በመቀመጥ ወደ እምነት ጸጥ ያለ ዕረፍት ግባ፤ እስክትጠግብም ድረስ ትመገባለህ።
ሙሽራይቱ እየተመገበች ዐረፈች፤ ተቀመጠች፥ በላችም። እንዲሁ አንተ እውነተኛ አማኝ ሆይ፥ ክርስቶስን ስትመገብ ዕረፍ! ሙሽራይቱ «ተቀመጥሁ፥ በላሁም» ትላለች። በፊተኛው ምዕራፍ ንጉሡ በማዕዱ እንደ ተቀመጠ ነግራን አልነበረምን? ቤተ ክርስቲያን ጌታዋን፥ አማኙም መድኃኒቱን ምን ያህል እንደሚመስል እዩ! እኛም ደግሞ እንቀመጣለን፥ እንበላለንም፥ ንጉሡ እንደሚያደርግ። በንጉሣዊ ሁኔታ እንስተናገዳለን። ደስታው በእኛ ነው፥ ሰላሙም ልባችንንና አሳባችንን ይጠብቃል።
ደግሞም ሙሽራይቱ ይህን ፍሬ ስትመገብ እንደ ወደደችው አስተውሉ። ምላስ ሁሉ ፍሬን ሁሉ አይወድም። ስለ ማናቸውም ዓይነት ጣዕም ከሌሎች ሰዎች ጋር ከቶ አትከራከሩ፤ መስማማት አይቻልምና። ለአንዱ ሰው ከሁሉ የሚጣፍጥ ምግብ ለሌላው የሚያቅለሸልሽ ነው፤ ከሌሎቹ ሁሉ የሚመረጠው የትኛው ፍሬ ነው ብሎ ውድድር ቢደረግ፥ ምናልባት ፍሬዎች ያሉትን ያህል ሐሳቦች ይኖሩ ነበር። ነገር ግን ክርስቶስ ኢየሱስን የሚወድድ ብፁዕ ነው! ውድ ሰሚ ሆይ፥ እርሱ ይጣፍጥሃልን? እንግዲያስ የአንተ ነው። ክርስቶስን የወደደ ልብ ሆኖ ክርስቶስ የዚያ ልብ ያልሆነበት ከቶ የለም። እርሱን ስትመገብ ከነበርህና ቢጣፍጥህ፥ መመገብህን ቀጥል፤ ፍላጎት የሰጠህ እርሱ ምኞትህን ሊያረካ ራሱን ይሰጥሃልና።
ከክርስቶስ የሚመጡት ፍሬዎች ምንድር ናቸው? ከእግዚአብሔር ጋር ሰላም፥ የልብ መታደስ፥ በመንፈስ ቅዱስ ደስታ፥ ለወንድሞች ፍቅር አይደሉምን? ዳግመኛ መወለድ፥ መጽደቅ፥ መቀደስ፥ ልጅነት፥ የጸጋ ኪዳን በረከቶችም ሁሉ አይደሉምን? ሁሉስ እያንዳንዳቸውም ለጕሮሮአችን ጣፋጭ አይደሉምን? እነርሱን ስንመገብ «አዎን፥ እነዚህ ነገሮች በእውነት ደስ የሚያሰኙ ናቸው። እንደ እነርሱ ያለ የለም። ለዘላለም በእነርሱ እንኑር» አላልንምን? አሁንም ተቀመጡ፥ ተቀመጡና ተመገቡ። ሰዎችን ይህን እንዲያደርጉ ማግባባት ማስፈለጉ እንግዳ ነገር ይመስላል፤ ነገር ግን በመንፈሳዊው ዓለም ነገሮች በሥጋዊው ካሉት እጅግ ይለያሉ። ለአብዛኞቹ ሰዎች ሥጋና ቢላዋ ሹካም በፊታቸው ብታኖሩ ለመብላት እንዲነሡ ብዙ ማግባቢያ አያስፈልጋቸውም። ነገር ግን የማይበሉበትን ጊዜ እነግራችኋለሁ፤ ይኸውም ሲጠግቡ ነው፤ የሚበሉበትንም ጊዜ እነግራችኋለሁ፤ ይኸውም ሲራቡ ነው። እንዲሁም ነፍስህ መድኃኒቱን ክርስቶስን ብትናፍቅ እርሱን ትመገባለህ፤ ካልሆነ ግን ልሰብክልህ ወይም ና ብዬ ልጠራህ ጥቅም የለውም። ሆኖም በዚያ በጥላው ሥር የተቀመጥህ አንተ፥ «ወዳጆች ሆይ፥ ብሉ፤ ጠጡ፥ እጅግም ጠጡ» ሲል ልትሰማው ትችላለህ። ከእነዚህ መልካም ነገሮች ልታበዛ አትችልም፤ ክርስቶስ በበዛ መጠን ክርስቲያኑ ይሻላል።
ሙሽራይቱ ከሕይወት ዛፍ በሆነው በዚህ ምግብ በሙሉ ልብ እንደ ተመገበች እናውቃለን፤ በኋላ ዘመን ተጨማሪ ፈልጋለችና። እባካችሁ አራተኛውን ቍጥር አንብቡ። ጽሑፋችንን የያዘው ቍጥር ለጌታዋ የነበራትን የመጀመሪያ ፍቅሯን፥ የገጠር ፍቅሯን፥ የባላገር ፍቅሯን የሚገልጽ ያህል ነው። ወደ ዱር ሄደች፥ በዚያም እንደ ትርንጎ ዛፍ አገኘችው፤ በገጠር ሰው የበሰለ ትርንጎ እንደሚደሰትበት ተደሰተችበት። ነገር ግን በጸጋ አደገች፥ ስለ ጌታዋ አብልጣ ተማረች፤ ከሁሉ የሚበልጠው ውዷ ንጉሥ መሆኑን አገኘች። የዳግም ምጽአትን ትምህርት ተምራ ቢሆን አልደነቅም፤ ያን ጊዜ «ወደ የወይን ጠጅ ቤት አገባኝ» ብላ መዘመር ጀመረችና። እንዲህ ማለቷ ነው፤—በውርደቱ እንዳለው ክርስቶስ በሜዳ ብቻ እንዳውቀው አልተወኝም፤ ነገር ግን ወደ ንጉሣዊው ቤተ መንግሥት አገባኝ፤ ንጉሥም ስለ ሆነ የራሱ የጀግንነት ዓርማ ያለበትን ሰንደቅ አወጣ፥ በማዕዱም ተቀምጬ ሳለሁ በላዬ አውለበለበው፤ የዚያም ሰንደቅ መፈክር ፍቅር ነበረ።
በዚህ እጅግ ተሞላች። ታላቅ መድኃኒት፥ ድል አድራጊ መድኃኒት፥ ከፍ ከፍ ያለ መድኃኒት ማግኘት እንዴት ያለ ታላቅ ነገር ነበር! ነገር ግን ከአቅሟ በላይ ሆነባት፤ ከተማረችው ነገር እጅግ ብዙ ክብር የተነሣ ነፍሷ ታመመች፤ ልቧ የሚናፍቀውንስ ታያላችሁን? የመጀመሪያ ቀላል ደስታዎቿን፥ ያንን የገጠር ሐሤት ትናፍቃለች። «በትርንጎ አበረታቱኝ» ትላለች። ከአሮጌዎቹ ደስታዎች በቀር ምንም አያነቃቃትም። እንዲህ ተሰምቷችሁ ያውቃልን? ክርስቶስን በነጭ ፈረሱ ላይ ተቀምጦ ድል እየነሣ ድል ለመንሣት ሲወጣ ባየሁት ጊዜ፥ እንደ ክቡርና ከፍ ከፍ እንዳለ መድኃኒት በፍቅሩ ደስታ ጠግቤአለሁ፤ የመላእክትና የመላእክት አለቆች አንጸባራቂ ጉባኤ ሁሉ እየሰገዱለት በዙፋኑ መካከል ባየሁት ጊዜ ተዋጥሁ፤ አሳቤም በእግዚአብሔር ግርማ ሁሉ ወርዶ ነገሥታትንና መሳፍንትን ሁሉ በክብሩ ወሰን በሌለው ግርማ ፊት ወደ ምንምነት የሚያኮማትርበትን ቀን ወደ ፊት ተመለከተ። ያን ጊዜ እርሱን ሳይ እንደ ሞተ ሰው በእግሩ ሥር የምወድቅ ያህል ተሰማኝ፤ እድን ዘንድ እንዴት እንደ ሞተ «የቀድሞውን የጥንቱን ታሪክ» እንደ ገና የሚነግረኝን ሰው ፈለግሁ። ዙፋኑ ያሸንፈኛል፤ ከመስቀሉ ፍሬ ልልቀም። ከ«ዛፉ» እንደ ገና ትርንጎ አምጡልኝ። በቤተ መንግሥት ሳለሁ በፍርሃት ተውጫለሁ፤ እንደ ገና ወደ ዱር ልሂድ። ከዛፉ የተለቀመ ትርንጎ ስጡኝ፥ በቤተሰቡ ላሉ ወንዶችና ሴቶች ልጆች እንደ ሰጠሁት ያለ፥ እንደዚህ ያለ ትርንጎ፤ «እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ።» ወይም ይህን፤ «ይህስ ኃጢአተኞችን ይቀበላል።» ከኪዳኑ ቅርጫት አንድ ተስፋ ስጡኝ። የክርስቶስን ቅንነት ስጡኝ፤ ኢየሱስ የትርንጎ ዛፍ ከሆነ ሕፃን ሆኜ እንደ ገና ትርንጎ ልብላ። በእኔ ፋንታ በዛፍ ላይ ወደ ተሰቀለው ክርስቶስ፥ ወደሚጋርደኝ ክርስቶስ፥ ወደሚመግበኝ ክርስቶስ ልመለስ እወዳለሁ። ይህ ሊኖርበት ከሁሉ የሚበልጥ ደስተኛ ሁኔታ ነው። ጌታ ሆይ፥ ዘወትር እነዚህን ትርንጎዎች ስጠን! ከዓመታት በፊት የነገርናችሁን፥ እንዲህ ብሎ ይዘምር የነበረውን የቸርቻሪውን የጃክን አሮጌ ታሪክ ታስታውሳላችሁ፤—
«ምስኪን ኃጢአተኛ ነኝ፥ ምንምም አይደለሁም፥
ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ሁሉ በሁሉዬ ነው።»
የሚያውቁት ሰዎች በማያቋርጥ እርጋታው ተደነቁ። እነርሱ የጥርጣሬና የፍርሃት ዓለም ነበራቸው፤ ስለዚህ ለምን ከቶ እንደማይጠራጠር ጠየቁት። «እንግዲህ» አለ፥ «ምስኪን ኃጢአተኛ መሆኔንና ምንም አለመሆኔን ልጠራጠር አልችልም፤ ይህን አውቃለሁና፥ በየቀኑም ይሰማኛልና። ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉ በሁሉዬ መሆኑንስ ለምን እጠራጠራለሁ? እርሱ ነኝ ብሏልና።» ጠያቂውም «ኦ!» አለ፥ «እኔ ከፍታና ዝቅታ አለብኝ።» «እኔ የለብኝም» አለ ጃክ፤ «ከፍ ልል ከቶ አልችልም፥ ምስኪን ኃጢአተኛ ነኝና፥ ምንምም አይደለሁምና፤ ዝቅም ልል አልችልም፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉ በሁሉዬ ነውና።» ቤተ ክርስቲያንን ሊቀላቀል ፈለገ፤ እነርሱም ተሞክሮውን መናገር አለበት አሉ። እርሱም «ተሞክሮዬ ሁሉ ምስኪን ኃጢአተኛ መሆኔ፥ ምንምም አለመሆኔ፥ ኢየሱስ ክርስቶስም ሁሉ በሁሉዬ መሆኑ ነው» አለ። «እንግዲህ» አሉ፥ «በቤተ ክርስቲያን ጉባኤ ፊት ስትቀርብ አገልጋዩ ጥያቄዎች ሊጠይቅህ ይችላል።» «ይህን ልከለክል አልችልም» አለ ጃክ፥ «የማውቀውን ሁሉ እነግራችኋለሁ፤ የማውቀውም ይህ ብቻ ነው፤—
‹ምስኪን ኃጢአተኛ ነኝ፥ ምንምም አይደለሁም፥
ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ሁሉ በሁሉዬ ነው።›»
ወደ ቤተ ክርስቲያንም ተቀበለ፥ በቅድስና እየተመላለሰ ከወንድሞች ጋር ጸና፤ ነገር ግን ተሞክሮው ሁሉ ያው ነበር፥ ከዚያም ልታሳልፉት አትችሉም ነበር። አንድ ወንድም «አንዳንድ ጊዜ በጸጋ እንዲህ የተሞላሁ፥ በቅድስና እንዲህ ያደግሁ ሆኖ ይሰማኛል፤ ስለዚህም እጅግ ደስ ይለኝ ጀመር» አለ። «እኔ ከቶ እንዲህ አይሰማኝም» አለ ጃክ፤ «እኔ ምስኪን ኃጢአተኛ ነኝ፥ ምንምም አይደለሁም።» ሌላውም «ነገር ግን» አለ፥ «እንደ ገና ዝቅ እላለሁ፤ ቀድሞ እንደ ነበርሁ አልተቀደስሁምና አልዳንሁም ብዬ አስባለሁ።» ጃክም «እኔ ግን መዳኔን ከቶ አልጠራጠርም» አለ፥ «ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉ በሁሉዬ ነውና፥ እርሱም ከቶ አይለወጥምና።» ያ ቀላል ታሪክ እጅግ አስተማሪ ነው፤ የአንድ ተራ ሰው እምነት በቀላል መዳን ላይ እንዳለ ያሳያልና፤ በትርንጎ ዛፍ ሥር ያለች፥ በጥላው የምታርፍ፥ ፍሬውንም የምትመገብ ነፍስ ምስል ነው።
አሁንም በዚህ ጊዜ ኢየሱስን እንደ መስፍን ሳይሆን እንደ ትርንጎ ዛፍ እንድታስቡት እወዳለሁ፤ ይህም ሲሆን በጥላው ሥር እንድትቀመጡ እለምናችኋለሁ። ይህ ብዙ ሥራ አይደለም። ማንኛውም ሕፃን ሲሞቀው በጥላ ሥር ሊቀመጥ ይችላል። ቀጥሎም ኢየሱስን እንድትመገቡ እወዳለሁ፤ ማንኛውም የዋህ ሰው ትርንጎ በዛፉ ላይ ሲበስል ሊበላ ይችላል። እንግዲያስ ኑ፥ ክርስቶስን ውሰዱ። ከዚህ በፊት ከቶ ያልመጣችሁ አሁን ኑ። ኑ፥ እንኳን ደኅና መጣችሁ። ብዙ ጊዜ የመጣችሁ፥ ወደ ቤተ መንግሥቱም የገባችሁ፥ በግብዣው ማዕድ የተደገፋችሁ እናንተ የክርስትና ጌቶችና መኳንንት፥ ምስኪን ቅዱሳን ወደሚጋረዱበትና ወደሚመገቡበት ወደ ተራው ዱርና ወደ ተራው የትርንጎ ዛፍ ኑ። እንደ እኔ እንዳሉ ምስኪን ኃጢአተኞች ወደ ትርንጎ ዛፍ ሥር ብትመጡ፥ እንደ ገናም በቅርንጫፎች ብትጋረዱና በትርንጎ ብትበረታቱ ይሻላችኋል፤ አለዚያ በቤተ መንግሥቱ ክብር ሥር ልትዝሉ ትችላላችሁ። ከቅዱሳን የሚበልጡት የመጀመሪያ ምግባቸውን ሲበሉ፥ የመጀመሪያ የወንጌል ግብዣቸው በነበረው ትርንጎ ሲበረቱ ከዚያ ይልቅ የሚሻሉበት ጊዜ የለም።
ጌታ ራሱ የራሱን ጣፋጭ ፍሬ ያፍራላችሁ! አሜን።