የመንፈስ ቅዱስ ማንነትና ሥራ
መንፈስ ቅዱስ ስለ ልጅነታችን መመስከሩ

ምዕራፍ 15 · 4 ደቂቃ ንባብ · 5 ደቂቃ ማዳመጥ

መንፈስ ቅዱስ ስለ ልጅነታችን መመስከሩ

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ መንፈስ ቅዱስ ሥራ ከሚናገሩት እጅግ ውድ ክፍሎች አንዱ በሮሜ 8:15-16 ይገኛል፦ «አባ አባት ብለን የምንጮኽበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና። የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል»። ለልጅነታችን ሁለት ምስክሮች አሉ፤ የመጀመሪያው የራሳችን መንፈስ ነው፤ እርሱ እግዚአብሔርን በቃሉ በማመን ስለ ልጅነታችን ይመሰክራል («ለተቀበሉት ሁሉ ግን … የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው» ዮሐንስ 1:12)።

መንፈሳችን እግዚአብሔር የሚናገረው እውነት እንደ ሆነ፣ እግዚአብሔር ስለ ተናገረም የእግዚአብሔር ልጆች እንደ ሆንን ያለ ማመንታት ያረጋግጣል። ነገር ግን ለልጅነታችን ሌላ ምስክርም አለ፤ እርሱም መንፈስ ቅዱስ ነው። እርሱ ከመንፈሳችን ጋር አብሮ ይመሰክራል። በዚህ ክፍል የተጠቀመው የግሪክ ቃል ትርጉም «አብሮ» የሚል ነው። ለመንፈሳችን ይመሰክራል አይልም፤ ከመንፈሳችን ጋር «አብሮ» ይመሰክራል እንጂ። ይህን እንዴት እንደሚያደርግ በገላትያ 4:6 ተገልጿል፦ «ልጆችም ስለ ሆናችሁ እግዚአብሔር አባ አባት ብሎ የሚጮኽ የልጁን መንፈስ በልባችሁ ውስጥ ላከ»። ኢየሱስ ክርስቶስን አዳኛችን አድርገን ስንቀበልና በእርሱ በኩል ልጆች እንደ ሆንን እግዚአብሔር ስለ ክርስቶስ የሰጠውን ምስክርነት ስንቀበል፣ የልጁ መንፈስ ወደ ልባችን ይመጣል፤ ልባችንን በታላቅና በሚያጥለቀልቅ የልጅነት ስሜት ይሞላዋል፤ በልባችንም ውስጥ «አባ አባት» እያለ ይጮኻል።

ልባችን በተፈጥሮው ለእግዚአብሔር ያለው አመለካከት የልጅ አመለካከት አይደለም። ለምሳሌ ኢየሱስ ያስተማረንን ጸሎት፦ «በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ» እያልን በልማድ ስንደግም በከንፈራችን አባት ብለን እንጠራው ይሆናል፤ ነገር ግን እርሱ አባታችን እንደ ሆነ እውነተኛ ስሜት የለንም። አባት ብለን መጥራታችን ቃል ብቻ ነው። አንታመንበትም። ወደ ፊቱ መቅረብን አንወድም፤ ከአባታችን ጋር እየተነጋገርን እንዳለን በማወቅ በሚገርም ደስታና መታመን ቀና ብለን ፊቱን ማየትን አንወድም።

እግዚአብሔርን እንፈራዋለን። በጸሎት ወደ እርሱ የምንቀርበው ማድረግ እንዳለብን ስለሚመስለን ነው፤ ምናልባትም ባናደርገው የሚደርስብንን ስለምንፈራ ይሆናል። ነገር ግን የልጁ መንፈስ ከመንፈሳችን ጋር አብሮ ስለ ልጅነታችን ሲመሰክር፣ ልጆች መሆናችንን በማወቅ እንሞላለን፤ ልባችንም በደስታ ይፈነድቃል። ምድራዊ አባታችንን እንኳ ታምነነው በማናውቀው መጠን እርሱን እንታመናለን። ምድራዊ አባታችንን እንፈራው ከነበረው ይልቅ እርሱን የምንፈራው እጅግ ያነሰ ነው።

አክብሮት አለ፤ ግርማውን መፍራትም አለ፤ ነገር ግን ኦ! እንዴት ያለ ድንቅ የሕፃን መታመን ነው!

መንፈስ ከመንፈሳችን ጋር የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን የሚመሰክረው መቼ እንደ ሆነ ልብ በል። በሮሜ 8 ያሉት ቍጥሮች በተደረደሩበት ቅደም ተከተል የተሞክሮውን ቅደም ተከተል እናገኛለን። በመጀመሪያ መንፈስ ቅዱስ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ አርነት ሲያወጣን፣ በዚህም ምክንያት እንደ ሕግ ሳይሆን እንደ መንፈስ በምንመላለስ በእኛ የሕጉ ጽድቅ ሲፈጸም እናያለን (ቍጥር 2-4)፤ ቀጥሎ አማኙ የሥጋን ነገር ሳይሆን የመንፈስን ነገር ሲያስብ እናያለን (ቍጥር 5)፤ ቀጥሎ አማኙ ዕለት ዕለት በመንፈስ የሰውነትን ሥራ ሲገድል እናያለን (ቍጥር 13)፤ ቀጥሎ አማኙ በእግዚአብሔር መንፈስ ሲመራ እናያለን፤ ከዚያም በኋላ፣ ከዚያም በኋላ ብቻ፣ መንፈስ ስለ ልጅነታችን ሲመሰክር እናያለን።

ብዙዎች የመንፈስን ምስክርነት ስለ ልጅነታቸው በተሳሳተ ስፍራ ይፈልጋሉ። ክርስቶስን መቀበላቸውን እንኳ ሳይመሰክሩ፣ ይልቁንም ሕይወታቸውን በውስጣቸው ለሚኖረው ለእግዚአብሔር መንፈስ ቍጥጥር ፈጽመው ሳይሰጡ፣ የመንፈስ ምስክርነት ስለ ልጅነታቸው እንዲሰጣቸው በተግባር ይጠይቃሉ። አይደለም፤ ነገሮችን በትክክለኛ ቅደም ተከተላቸው እንፈልግ። እግዚአብሔር ስላዘዘን ኢየሱስ ክርስቶስን አዳኛችን አድርገን እንቀበለው፤ ጌታችንና መምህራችን አድርገንም ራሳችንን ለእርሱ እንስጥ፤ እግዚአብሔር ስላዘዘ በዓለም ፊት እንመስክርለት (ማቴዎስ 10:32-33፤ ሮሜ 10:9-10)፤ እግዚአብሔር በቃሉ ስለ ተናገረና እርሱን በመጠራጠር ሐሰተኛ ልናደርገው ስለማንፈልግ፣ ኃጢአታችን ይቅር እንደ ተባለልን፣ የዘላለም ሕይወት እንዳለን፣ የእግዚአብሔር ልጆች እንደ ሆንን አጽንተን እንናገር (የሐዋርያት ሥራ 10:43፤ የሐዋርያት ሥራ 13:38-39፤ 1ኛ ዮሐንስ 5:10-13፤ ዮሐንስ 5:24፤ ዮሐንስ 1:12)፤ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ አርነት እንዲያወጣን ወደ እርሱ እየተመለከትን ሕይወታችንን ለሕይወት መንፈስ ቍጥጥር እንስጥ፤ አሳባችንን በሥጋ ነገር ላይ ሳይሆን በመንፈስ ነገር ላይ እናድርግ፤ ዕለት ዕለት በመንፈስ የሰውነትን ሥራ እንግደል፤ በነገር ሁሉ በእግዚአብሔር መንፈስ እንድንመራ ሕይወታችንን አሳልፈን እንስጥ፤ ከዚያም በኋላ ልባችንን በልጅነት ስሜት የሚሞላውንና «አባ አባት» እያለ የሚጮኸውን የልጁን መንፈስ ወደ ልባችን እንዲልክ በቀላሉ እግዚአብሔርን እንታመን፤ እርሱም ያደርገዋል።

አባታችን እግዚአብሔር ልጆቹ መሆናችንን እንድናውቅና እንድንገነዘብ ይናፍቃል። የሚናገሩትን ከሚገነዘቡና ያለ ፍርሃትና ያለ ጭንቀት ከሚታመኑት ልቦች አባት ብለን ስንጠራው መስማት ይናፍቃል። እርሱ አባታችን ነው። በዚያ ድንቅ ቃል፣ «አባት» በሚለው ቃል ውስጥ ያለውን የትርጉም ሙላት በመላው ፍጥረተ ዓለም ውስጥ የሚገነዘብ እርሱ ብቻ ነው፤ አባታችን እንደ ሆነ ስንገነዘብና አባት ብለን ስንጠራውም ደስ ይለዋል። ከጥቂት ዓመታት በፊት በኢሊኖይ ክፍለ ግዛት ከተወለደች ጀምሮ መስማትም መናገርም የማትችል ልጅ የነበረችው አንድ አባት ነበረ። ያቺ ትንሽ ልጅ መስማት እንደማትችልና ፈጽሞ እንደማትሰማ፣ እነርሱም እንዳሰቡት ፈጽሞ እንደማትናገር በተገነዘቡበት ቀን በዚያ ቤት ታላቅ ኀዘን ሆነ።

አባትየው መስማት የተሳናቸው ልጆች መናገር በሚማሩበት በኢሊኖይ ጃክሰንቪል ስላለ አንድ ተቋም ሰማ። ይህችንም ትንሽ ልጅ ወደዚያ ተቋም ወስዶ በበላይ ኃላፊው እጅ አስቀመጣት። ልጅቱ በዚያ ጥቂት ጊዜ ከቆየች በኋላ የበላይ ኃላፊው ለአባትየው መጥቶ ልጁን ቢጎበኝ እንደሚሻል ጻፈለት።

ቀን ተቀጠረ፤ ለልጅቱም አባቷ እንደሚመጣ ተነገራት። ሰዓቱ ሲቃረብ አባቷ በበሩ ሲገባ ለማየት በሩን እየተመለከተች በመስኮቱ ላይ ተቀመጠች። ልክ በሩን አልፎ እንደ ገባ አየችው፤ ደረጃውን ሮጣ ወረደች፤ ወደ ሣር ሜዳውም ሮጣ ወጥታ ተቀበለችው፤ ቀና ብላ ፊቱን አየች፤ እጆቿንም አንሥታ «አባዬ» አለች። ያ አባት የልጁ ዲዳ ከንፈሮች ለመጀመሪያ ጊዜ ሲናገሩና ያን ጣፋጭ ቃል «አባዬ» ብለው ሲያወጡ በሰማ ጊዜ፣ እንዲህ ያለ የደስታ ትርታ በልቡ ውስጥ ስላለፈ መሬት ላይ ወደቀ፤ በታላቅ ፍንደቃም በሣሩ ላይ ተንከባለለ። ነገር ግን ማንም ምድራዊ አባት በማይወድደው መጠን የሚወድድ፣ ልጆቹ ልጆች መሆናቸውን እንዲገነዘቡ የሚናፍቅ አባት አለ፤ ቀና ብለን ፊቱን አይተን መንፈስ ቅዱስ በልጅነት ስሜት ከሞላው ልብ «አባ» (አባዬ)፣ «አባት» ብለን ስንጠራው፣ የእግዚአብሔርን ደስታ ሊገልጽ የሚችል ምንም ቋንቋ የለም።

ገጽ 1 / 1 · 4 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል
ቀዳሚ ቀጣይ