በእጄ ያለው መክፈቻ
የማሰናከያ ዓለት

ምዕራፍ 9 · 6 ደቂቃ ንባብ

የማሰናከያ ዓለት

ኢየሱስ የብዙ ቅያሜ ምክንያት ነበር! ጴጥሮስም ጳውሎስም ብሉይ ኪዳንን በመጥቀስ «የማሰናከያ ዓለት» ብለው ጠርተውታል (ሮሜ 9:33 እና 1ኛ ጴጥሮስ 2:8)።

ፈሪሳውያን በእርሱ ተሰናከሉ፤ አጋንንት በእርሱ ተሰናከሉ፤ የገዛ ቤተሰቡም እንኳ በእርሱ ቅር ተሰኙ!

ነገር ግን እንደ ተናቁት ቀራጮች ያሉትን አንዳንዶችን ሆን ብሎ ከማሰናከል ተቆጠበ። «እንዳናሰናክላቸው» ጴጥሮስን ወደ ባሕር እንዲሄድ፣ የሚፈለገውንም ግብር በአንድ ዓሣ አፍ ውስጥ እንደሚያገኝ ነገረው (ማቴዎስ 17:24)። ሌሎችን ግን ሆን ብሎ የሚያሰናክል ይመስላል!

መጥምቁ ዮሐንስ - የኢየሱስ የአክስት ልጅ

መጥምቁ ዮሐንስ የኢየሱስ የሩቅ ዘመድ ነበር፤ ከእርሱም በጥቂት ወራት ቀድሞ ተወልዶ ነበር። በእናቱ ማኅፀን ሳለ እንኳ መንፈስ ቅዱስ የሞላበት ነበር፤ ለተስፋው መሲሕም ምላሽ የሰጠ የመጀመሪያው እርሱ ነበር። የኢየሱስ እናት ማርያም ስለ ልጅዋ መፀነስ ያለውን አስደናቂ ታሪክ ለመንገር ለመጀመሪያ ጊዜ በመጣች ጊዜ በኤልሳቤጥ ማኅፀን ውስጥ ዘልሎ ነበር።

ሁለቱ ልጆች በልጅነታቸው ብዙ ሰዓታትን አብረው አሳልፈው እንደሚሆን እርግጠኛ ነኝ። ምናልባት አብረው ተጫውተው አብረው ሠርተው፣ አብረው ሮጠው አብረው ተጣልተው፣ አብረው ተነጋግረው አብረውም ተከራክረው ይሆናል። ምናልባትም በእያንዳንዳቸው ልብ ውስጥ እያደገ ስለ ነበረው ሸክም አብረው ተነጋግረው ይሆናል።

በመጨረሻም ዮሐንስ አንድ እንግዳ ውስጣዊ ግፊትን ለመታዘዝ ከቤቱ ወጣ። «የጌታን መንገድ አዘጋጁ» ሲል ባወጀ ጊዜ የተረዳው ኢየሱስ ብቻ ሊሆን ይችላል (ማቴዎስ 3:3)፤ ከዚያም ወደ በረሃ ሄደ።

በዚያም ዮሐንስ ሊሰሙት ለሚፈልጉ ሁሉ መስበክ ጀመረ።

«መሲሑ በቅርቡ ይመጣል» እያለ ያውጅ ነበር፤ «እኛ ግን ዝግጁ አይደለንም! ንስሐ ግቡና ተጠመቁ። ወደ አምላካችሁ ተመለሱ!»

(ማቴዎስ 3:2-12) ሕዝቡም ምላሽ ሰጡ፤ ከይሖዋ ጋር ለመታረቅ ፈለጉ፤ አዲሱን ቁርጥ ውሳኔያቸውንም በአካባቢው ባለው ወንዝ በዮርዳኖስ በመጠመቅ አሳዩ። ጥምቀታቸው የንስሐ ጥምቀትና ወደ ትክክለኛው እምነት የመመለስ ጥምቀት ነበር።

አንድ ቀን ኢየሱስ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ መጣ፤ ዮሐንስም ለሕዝቡ «እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ!» ብሎ ጮኸ (ዮሐንስ 1:29)። ዮሐንስ ርግብ በኢየሱስ ላይ ስትወርድና በእርሱ ላይ ስትኖር እንዳየ መሰከረ።

ከዚህም በላይ መንፈስ ቅዱስ ይህ የሚመጣው መሲሕ ምልክት እንደሚሆን ለዮሐንስ አስቀድሞ ነግሮት ነበር፤ በዮሐንስ 1:34 ላይ «እኔም አይቻለሁ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ መስክሬአለሁ» ተብሎ ተጽፏል።

ዮሐንስ «የሰዎችን ጆሮ የሚያሳክክ» ተወዳጅ ሰባኪ አልነበረም።

እርሱን ለመስማትና ለማየት ከመጡት መካከል አብዛኞቹ አንድ እንግዳ ነገር ለማየት የመጡ ነበሩ፤ ራሳቸውን ጻድቅ አድርገው በሚቆጥሩት የምኵራብ መሪዎች ላይ የሚሰነዝረውን ወቀሳ ለመስማት በዚያ ለመገኘት ተስፋ ያደርጉ ነበር።

ለእንደዚህ ያሉ መሪዎች የሚናገራቸው የተመረጡ ቃላት ነበሩት፤ ሕዝቡም ይህንን ወደዱት፤ ሄሮድስ ግን አልወደደውም። እርሱ በዚያን ጊዜ የሮም መንግሥት ገዥ ነበር፤ ከወንድሙ ሚስት ጋር ዝሙት ይፈጽም የነበረ ክፉ ሰውም ነበር - ዮሐንስ ይህንን ዝሙት በግልጽ አወገዘ። ሄሮድስ ድምፁን ጸጥ ለማሰኘት ዮሐንስን ወደ ወኅኒ አስጣለው።

ዮሐንስ በዚያ ጨለማ እስር ቤት ውስጥ ሳለ ያስብ የነበረውን በዓይነ ሕሊናዬ መሳል እችላለሁ።

«ሄሮድስ፣ አንተ ሽማግሌ ሞኝ! ሁሉን የምትቆጣጠር መስሎህ እኔን ወኅኒ ማስገባትህ ድምፄን ጸጥ የሚያሰኝ ይመስልሃል። የአክስቴ ልጅ ግን መሲሑ ነው፤ ትንሿን መንግሥትህን ለመገልበጥና የራሱን መንግሥት ለመመሥረት መጥቷል! በቅርቡ ከዚህ እስር ቤት ያወጣኛል፤ የምትታሰረውም አንተ ትሆናለህ! የታሰሩትን ነፃ ለማውጣት እንደ መጣ አውጇል። ይህንን ሲያደርግ ፊትህን ለማየት ቸኩያለሁ!» በዚህም ዮሐንስ በክፍሉ ውስጥ ተደግፎ ይቀመጥና ይጠብቃል… ይጠብቃል… ይጠብቃል… በዚህ መካከል ኢየሱስ በአቅራቢያው ባሉት መንደሮች አገልግሎቱን ይቀጥላል፤ ዮሐንስን በእስር ቤት ለመጠየቅ ጊዜ እንኳ አያገኝም!

በእርግጥ ቢያንስ ሊጠይቀው ይመጣል! ነገር ግን ስለማይመጣ ዮሐንስ ቅር ይሰኛል፤ ከዚያም በኋላ አንገቱ ተቀላ! የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት አንድ ቀጥተኛ ጥያቄ እንዲጠይቁ ወደ ኢየሱስ ተላኩ። «የሚመጣው አንተ ነህን? ወይስ ሌላ እንጠብቅ?» (ማቴዎስ 11:3)። «የምንጠብቀውን ነገር እያደረግህ ስላልሆነ ከመስፈርታችን ጋር አትስማማም!»

ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ «ሄዳችሁ ያያችሁትን የሰማችሁትንም ለዮሐንስ አውሩለት፤ ዕውሮች ያያሉ፥ አንካሶችም ይሄዳሉ፥ ለምጻሞችም ይነጻሉ፥ ደንቆሮዎችም ይሰማሉ፥ ሙታንም ይነሣሉ፥ ለድሆችም ወንጌል ይሰበካል፤ በእኔም የማይሰናከለው ሁሉ ብፁዕ ነው» (ሉቃስ 7:22-23)።

የኢየሱስ ውድ ወዳጅ ማርያም

ኢየሱስ በትንሿ የቢታንያ ከተማ የሚኖሩ በጣም ልዩ ወዳጆች ነበሩት። ወዳጁ አልዓዛር እየሞተ እንደ ሆነና እኅቶቹ ማርያምና ማርታ ስለ እርሱ እያዘኑ እንደ ሆኑ ወሬ በደረሰው ጊዜ ከዚያ ጥቂት ማይሎች ብቻ ርቆ ነበር። «ኢየሱስም ማርታንና እኅትዋን አልዓዛርንም ይወድ ነበር። እንደ ታመመም በሰማ ጊዜ ያን ጊዜ በነበረበት ስፍራ ሁለት ቀን ዋለ» (ዮሐንስ 11:5-6)።

በእነዚያ ሁለት ቀናት ምንም ተአምር፣ ምንም ትምህርት ወይም ያደረገውን ምንም ነገር አናነብም! አልዓዛርም ሞተ! ኢየሱስ በመጨረሻ ወደ ቢታንያ በመጣ ጊዜ አልዓዛር በመቃብር አራት ቀን ቆይቶ ነበር፤ እኅቶቹም በጥልቅ ሐዘን ውስጥ ነበሩ። ሊቀበለው የወጣችው ማርታ ናት። ይህ የሚያስገርም ነው፤ ብዙ ጊዜ «ሥራ የምታበዛዋ» - በወጥ ቤት የታሰረችዋ - አድርገን የምናስባት እርሷ ናትና፤ እኅቷ ማርያም ግን ሁሉን ትታ በኢየሱስ እግር ሥር ትቀመጥ፣ እግሮቹን በውድ ሽቱ እያጠበች በፀጉሯ ታብሳቸው፣ የሚናገረውንም ሁሉ ትቀስም ነበር። ዛሬ ቢሆን ማርያም በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴ ታዋቂ ትሆን ነበር - የአካባቢው የሴቶች የአምልኮ ቡድን ሊቀ መንበር፤ እኅቷ ደግሞ ከበስተ ጀርባ ቡና እያፈላች ብስኩት ታቀርብ ነበር።

ማርታ ኢየሱስን «ጌታ ሆይ፥ አንተ በዚህ ኖረህ ብትሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር» አለችው (ዮሐንስ 11:21)። ኢየሱስ እርሱ ትንሣኤና ሕይወት ስለ ሆነ ወንድሟ ዳግመኛ በሕይወት እንደሚኖር አረጋገጠላት።

በማርታ ንግግር ውስጥ ምንም ወቀሳ አልሰማም፤ ሐዘን ብቻ ነው። ከዚያም ወደ ኢየሱስ እንድትመጣ ልትጠይቃት ወደ ማርያም ሄደች።

ነገር ግን ማርያም ለምን አስቀድማ በዚያ አልተገኘችም? እርሱ እየመጣ እንደ ሆነ በእርግጥ ታውቃለች አይደለም? ሁሉም ሰው ይህንን ያውቅ ነበር፤ ማርያም ግን በቤት ውስጥ ተቀምጣ ነበር። ለምን? ተኰራርፋ ነበር ብዬ ልጠቁም እችላለሁን!

ቅር ተሰኝታ ነበር ! ወደ ኢየሱስ በመጣች ጊዜ እያለቀሰች በፊቱ ወደቀች፤ ማርታ የተናገረችውንም ቃል ተናገረች። «ጌታ ሆይ፥ አንተ በዚህ ኖረህ ብትሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር» (ዮሐንስ 11:32)።

ኢየሱስ ለእኅቷ የተናገረውን የማጽናኛ ቃል ለማርያም እንዳልተናገረ አስተውል። ይህ በድምፅዋ ቃና ምክንያት ሊሆን ይችል ይሆን? ከሳሽ? ፈራጅ?

ኢየሱስ ማርያምን ከማጽናናት ይልቅ «ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ» (ዮሐንስ 11:35)፤ ይህ ግን አልዓዛር ስለ ሞተ አልነበረም - ይህንን ለተወሰነ ጊዜ ያውቅ ነበር፤ በጥቂት ጊዜ ውስጥም ሁሉም በትንሣኤው እንደሚደሰቱ ያውቅ ነበር። ያለቀሰው ማርያም፣ ማርታና ወዳጆቻቸው በሐዘን ውስጥ ስለ ነበሩም አልነበረም - የሚወዱት ሰው ሲሞት ይህ ተፈጥሯዊ ስለ ሆነ እንደሚያዝኑ ያውቅ ነበር።

ያለቀሰው ማርያም ቅር ስለ ተሰኘች ነው።

ኢየሱስ ስለ «በደሎቻችን» ይሞታል፤ እኛ ቅር ስንሰኝ ግን አሁንም ያዝናል።

ወደ ቢታንያ በሚሄድበት መንገድ ላይ ኢየሱስ ሰዎች ሊረዱት በማይችሉ ጊዜ ብዙ ጊዜ እንደሚሰናከሉ ለደቀ መዛሙርቱ ነግሯቸው ነበር። በጨለማ እየተመላለሱ ነው (ዮሐንስ 11:10)። ማርያም እንዴት ምላሽ እንደምትሰጥ ያውቅ ነበርን?

ቅያሜዎች ለምን ይመጣሉ?

ጌታ ቅያሜዎች እንዲመጡ የሚፈቅደው ለምንድን ነው? ዓላማው ስለ ራሳችን አንድ ነገር ሊገልጥልን ሊሆን ይችላልን? ዮሐንስ «እርሱ ሊልቅ እኔ ግን ላንስ ያስፈልጋል» ብሎ ቢያውጅም (ዮሐንስ 3:30)፣ የጊዜ ሰሌዳው የጌታ እንጂ የእርሱ እንዳልሆነ መገንዘብ ነበረበትን?

እግዚአብሔርን በእኛ መንገድ ነገሮችን እንዲያደርግ ለማሽከርከር በመሞከር ወጥመድ ውስጥ መውደቅ ቀላል ነው። ፈቃዱን በመፈጸምና የእኛን ፈቃድ በመፈጸም መካከል ያለውን መስመር ማለፍ እጅግ ቀላል ነው። ነገሮችን «በእኛ መንገድ» ሳያደርግ ሲቀር ቅር መሰኘት የለብንም፤ ምክንያቱም የምናልፍባቸውን ሸለቆዎች ምክንያት ማየት በማንችልበት ጊዜ እንኳ ለእኛ የሚበጀውን የሚያውቅ እርሱ ብቻ ነው።

ማርያም በጌታ «አገልግሎት» ውስጥም እንኳ መታዘዝና መታመን ከታዋቂነትና ከተወዳጅነት እጅግ እንደሚሻሉ መማር ያስፈልጋት ነበርን?

በመንግሥቱ ውስጥ ታላቅነት የሚመጣው እንደ አገልጋዮች እንኳ ታናሽ ለመሆን ለሚፈቅዱ ነው (ሉቃስ 9:48)።

በቅያሜዎች ምን እናድርግ?

በመጀመሪያ፣ የራስህ መሆኑን ተቀበል ! ቅያሜው የአንተ ነው! ሌላው አልበደለህም - «ጦጣውን» በራስህ ትከሻ ላይ የወሰድኸው አንተ ነህ፤ ስለዚህ አውርደህ ጣለው - አለዚያም ተሸከመው!

ቀጥሎ፣ መርምረው ! ጌታ እንዲመጣ የፈቀደው ስለ ራስህ አንድ ነገር እንዲያስተምርህ ነው።

እኔም አንዳንድ ከባድ ነገሮችን በዚህ መንገድ መማር ነበረብኝ፤ ለቅያሜዎች ምክንያት ከሆኑት አንዳንዶቹን ባለፈው ምዕራፍ ሰጥቼሃለሁ። የባሕርይ ዓይነቶችህን ማጥናትና በብርታቶችህ ላይ ማተኮርን መማር አለብህ። ለምሳሌ፣ አብዛኞቹ ፓስተሮች ሜላንኮሊክ (ጥልቅ አሳቢና ስሜታዊ) ባሕርይ ያላቸው ይሆናሉ። የሜላንኮሊክ ባሕርይ አንዱ ስጦታ ሌሎች ሳያዩ ብዙ ቀደም ብሎ ችግሮችን የማየት ችሎታ ነው። ይህ በሌሎች ላይ ነቃፊ እንዲሆኑ፣ ሌሎች «ግልጽ የሆነውን» ማየትና በዚያ ላይ አንድ ነገር ማድረግ ባለመቻላቸው ቅር እንዲሰኙ ሊያደርጋቸው ይችላል። ሁላችሁም እንደ እኔ ስላልሆናችሁ እግዚአብሔር ይመስገን!

የሁሉም ሰው ስጦታዎች የተለያዩ ናቸው። ለብዙ ዓመታት ሌሎች ማስተማሬን እንደ «ስጦታ» አለመቀበላቸው ቅር ያሰኘኝ ነበር። ሁሉም ሰው ማስተማር እንደሚችል ያስባል፤ ሰዎች እንደ ፓስተር ያለኝን ስጦታና ጥሪ ችላ ሲሉ «ወፍራም ቆዳ» እንዲኖረኝ መማር ነበረብኝ።

የራስህ መሆኑን ተቀብለህ ከመረመርኸው በኋላ ፣ አስወግደው !

በምርጫህ ስለ እርሱ ጸልይና ቅበረው! ያስቀየሙህን ባርካቸው፤ ቅያሜው እጅግ ከባድ መስሎ ከታየህ የመንፈስ ቅዱስን ማበርታት ፈልግ - እርሱ ለፈተናዎችህ ሁሉ በቂ እንደሚሆን ቃል ገብቷል።

«ከሰው ሁሉ ጋር ሰላምን ተከታተሉ ትቀደሱም ዘንድ ፈልጉ፥ ያለ እርሱ ጌታን ሊያይ የሚችል የለምና። የእግዚአብሔር ጸጋ ለማንም እንዳይጎድለው፥ ብዙዎቹም የሚረክሱበት አንድ መራራ ሥር ወደ ላይ በቅሎ እንዳያስጨንቅ» (ዕብራውያን 12:14-15)።

ከዚያም ጦጣዎቹ በትከሻህ ላይ ሲሆኑ የምትወስደው የመጨረሻው እርምጃ እርሳው ! የሚለው ነው። ቅያሜው ከእንግዲህ በልብህ ውስጥ እንዲኖር አትፍቀድለት። ለጌታ አሳልፈህ ስጠው፤ ከአእምሮህና ከልብህም እንዲወጣ ልቀቀው።

በመጨረሻም፣ ቅያሜን የምታመጣው አንተ አትሁን ፤ «መሰናክሉን ለሚያመጣው ወዮለት!» ተብሏልና (ሉቃስ 17:1)!

ገጽ 1 / 1 · 6 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል