ምዕራፍ 10 · 10 ደቂቃ ንባብ
የቆሰለች ነፍስ
መጽሐፍ ቅዱስ የሰይጣንን ዘዴዎች በሚከተሉት ውስጥ በግልጽ ያሳየናል፦ ● ስሜቶቻችንን የሚነካው የሚያገሣው አንበሳ።
● አሳቦቻችንን የሚነኩት የውሸት ፍላጻዎች።
● ሰላማችንን የሚነኩት የቅያሜ «ጦጣዎች»።
ይሁን እንጂ ከዘዴዎቹ ሁሉ ይበልጥ ውጤታማ የሆነው በግልጽ አይታወቅም። ከመወለድህ በፊት ጀምሮ ዒላማ አድርጎሃል። እርሱ ሁሉን አዋቂ አይደለም፤ ስለዚህ አማኝና በውጊያው ተቃዋሚው እንደምትሆን አያውቅም፤ ስለሆነም ስለ ምንም ውጊያ ሳታውቅ በፊት ሊያቆስልህ ሞክሯል። ይህም በአብያተ ክርስቲያናታችን ውስጥ ባሉት በርካታ «ጤናማ ግንኙነትና አኗኗር የተዛባባቸው» ሰዎች ይታያል፤ ነገር ግን እየታገሉ ቍስላቸውን የማያውቁ ከእነዚህ እጅግ የሚበልጡ ብዙዎች እንዳሉ አምናለሁ።
አዲስ ፍጥረት
አማኝ በሆንሁ ጊዜ «ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል» ተብሎ ተማርሁ (2ኛ ቆሮንቶስ 5:17)። ይህ ቁጥር አሁንም በሕይወቴ ውስጥ ስለ ነበሩት የአሮጌው ባሕርይ ትናንሽ ነገሮች እኔን ለመገሠጽ ይጠቀሙበት ነበር። በተፈጥሮ በደለኛነት እንዲሰማኝ ተደረገ። የአሮጌ ልማዶቼ በሌሎች ላይ ካየኋቸው አንዳንዶቹ ያህል መጥፎ አይደሉም ብዬ በማሰብ የበደለኛነት ስሜቴን አቀለልሁ። እንደ እኛ አሮጌ ልማዶቻቸውን ማሸነፍ ያልቻሉትን ሰዎች ለመኰነን እጅግ ፈጣኖች ነበርን፤ በተለይም እንደ ማጨስና መጠጣት ያሉትን ግልጽ «ኃጢአቶች»፣ ዳንስንና ይህንን ከሚያደርጉ ጋር መወዳጀትን ሳንጠቅስ! ይህንን ቁጥር በተሻለ መረዳት፣ ስለ እግዚአብሔር ጸጋም የበለጠ ነገር መረዳት በመቻሌ ደስ ብሎኛል።
በክርስቶስ በአብ ዘንድ ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት ስላገኘንና ከእርሱ ጋር ስለ ታረቅን - ስለ ጸደቅን፣ ይቅር ስለ ተባልንና አዲስ ፍጥረት ስለ ተደረግን እግዚአብሔር ይመስገን። ይሁን እንጂ በዳንሁ ጊዜ ጥርሶቼ ሙሌታቸውን አራግፈው ወደ ወጣትነቴ ያልበሰበሰ ንጣት አልተመለሱም። እንዲያውም ሰውነቴ አዲስ ፍጥረት አልተደረገም፤ ይልቁንም ዕለት ዕለት እየሞተ ይቀጥላል።
«አዲሱ ፍጥረት» የሚያመለክተው ቀድሞ ሞቶ የነበረውን የእኔን ክፍል - መንፈሴን ነው። በነፍስና በመንፈስ መካከል ስላለው ልዩነት ብዙ ግራ መጋባት እንዳለ አውቃለሁ፤ ነገር ግን ለዚህ መጽሐፍ ዓላማ መንፈስ ብዬ የምጠራው አሁን ለእግዚአብሔር ሕያው ሆኖ እኔን ካልዳነ ሰው የሚለየኝን የእኔን ክፍል ነው፤ ያልዳነው ሰው ምንም ያህል ክቡር ወይም ሃይማኖተኛ ቢሆን መንፈሱ የሞተ ነው። እነርሱም እንደ እኔ የተለያየ የጤንነት ደረጃ ያለው ሥጋ አላቸው፤ ጌታ ቀድሞ ካልመጣ በቀር ግን አንድ ቀን በእርግጥ ይሞታል።
እንዲሁም ነፍሳት አሉን - አእምሯችን፣ ፈቃዳችንና ስሜቶቻችን።
ክርስቲያን ያልሆነ ሰው እንኳ ሕያው ነፍስ አለው። በመዳን ጊዜ እነዚህ አዲስ ፍጥረት አይደረጉም፤ ከባለፈው ብዙ ቍስሎችን ይሸከማሉ፤ ለሰይጣንም ለም የጦር ሜዳ ይሆናሉ። እርሱ ቍስሎቹን ያውቃል - ለመሆኑ ቍስሎቹን በማድረስ ሠራዊቱ እጅግ ንቁ ነበሩ! ለረጅም ጊዜ ብዙ አዲስ (እና አንዳንድ የቆዩ) አማኞች የቆሰለች ነፍሳቸው ከፈቀደችላቸው በላይ የበሰሉ እንዲሆኑ በማዘዝ በውጊያው ብቃት እንደሌላቸው እንዲሰማቸው አድርገናል። ነፍሳቸው ሽባ ሆና ሳለ እንዲሮጡ - ጡንቻዎቻቸው ሟሽሸው ሳሉ እንዲዋጉ አጥብቀን አሳስበናቸዋል! ይልቁንም ጌታ የማስታረቅን አገልግሎት ስለ ሰጠን (2ኛ ቆሮንቶስ 5:18-19)፣ በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት ፈውስን በማምጣት ሕመማቸውንና ቍስላቸውን ማገልገል ይገባን ነበር።
የነፍስ ሰንበሮች
ብዙ ሰዎች በአብዛኛው ሕይወታቸው ምናልባትም ከወላጅ ወይም ከወንድሞችና እኅቶች የማያቋርጥ ትችትና የቃል ጥቃት ሲደርስባቸው ኖረዋል። ዓይን አፋር ባሕርያቸው ሌሎች ይህንን ጥቃት በትምህርት ቤት ወይም በሥራ ቦታ እንዲቀጥሉበት ይጋብዛል፤ ከዚያም በነፍሳቸው ላይ ታላላቅ «ሰንበሮች» ይዘው ወደ ጕልምስና ይገባሉ። ብዙ ጊዜ ከልክ በላይ ስሜታዊ ናችሁ ተብለው ይከሰሳሉ፤ በእርግጥም በደረሰባቸው ጥቃት ምክንያት እንደዚያ ናቸው። እንደገና እስኪተቹ ድረስ በበቂ ሁኔታ ይንቀሳቀሳሉ፤ ያን ጊዜ ግን ሕመሙን መቋቋም እንደማይችሉ ያገኙታል። አዳዲስ ሰንበሮች ይፈጠራሉ፤ እውነትም ይሁን የታሰበ እያንዳንዱ አዲስ ትችት በሰንበሩ ላይ እንደሚያርፍ ቡጢ ነው።
ፒተር ያደገው ክርስቲያናዊ ቢሆንም ፈገግታ በራቀው ቤት ውስጥ ነበር። ብቸኛ ልጅ ነበር፤ ጥቂት ወዳጆችም ነበሩት። ከትምህርት ቤት ወዳጆቹን ወደ ቤት እንዲያመጣ አይፈቀድለትም ነበር፤ ምክንያቱም «ዓለማውያን» ነበሩ፤ ቤተሰቡ በሚሄዱባት ትንሽ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ በእድሜው የሚገኙ ሌሎች ወጣቶች አልነበሩም። የአባቱን ጉጉትና ፍላጎት ፈጽሞ ማሟላት አልቻለም፤ አንድን ሥራ ለረጅም ጊዜ መያዝም አልቻለም። ተቀባይነት ለማግኘት በቂ እንደ ሆነ እንዲሰማው ፈጽሞ አልተደረገም። በሠላሳዎቹ አጋማሽ ላይ ከቤት ወጥቶ በአንድ የክርስቲያን ሚስዮን ውስጥ ለመሥራት ሄደ፤ በዚያም ሦስት ሌሎች ሰዎች ወዳጅ አደረጉት። በሥራውና በወዳጆቹ መደሰት ጀመረ፤ የዚያም አገልግሎት ተቀባይነት ያለው ክፍል ሆነ፤ በዚያ መሥራት ከጀመረ ከአንድ ዓመት ትንሽ በኋላ ግን ሦስቱም ወዳጆቹ እያንዳንዳቸው በቅርቡ ለቀው ሌላ ስፍራ ለመሥራት እንደሚሄዱ አስታወቁ።
ፒተር አንድ ሰው ይሰማዋል ተብሎ የሚጠበቀውን የተለመደ ሐዘን ከማሳየት ይልቅ እንግዳ በሆነ መንገድ መመላለስ ጀመረ። የሚሄዱት ወዳጆቹ እንዲጠሉት ሆን ብሎ ተነሣ። ለምሳሌ፣ ከአንዱ አንድ ነገር ተውሶ ሆን ብሎ ይሰብረውና በአጋጣሚ እንደ ሆነ ይናገር ነበር። እያንዳንዳቸው ወዳጆቹ በፒተር ቅር ተሰኝተው ሚስዮኑን ለቀው ሄዱ።
ታዲያ እንዲህ ያደረገው ለምን ነበር? ይህ የጀመረው ከእረፍት ጊዜው - ከቤቱ - ከተመለሰ በኋላ ወዲያውኑ እንደ ነበረ ነገረኝ። ያ መልካም ጊዜ አልነበረም፤ ወደ ሚስዮኑ በመመለሱም ደስ ብሎት ነበር። በቤቱ የደረሰበት ተጨማሪ ትችት በነፍሱ ላይ አዲስ ሰንበር እንዳስከተለ፣ የወዳጆቹ መሄድም በሰንበሩ ላይ እንደሚያርፍ ቡጢ እንደ ነበረ ስጠቁመው ፒተር ተሰበረና አለቀሰ። «የሚሰማኝ ልክ እንደዚያ ነው» አለ፤ «የእነርሱ መሄድ ለፍቅርና ለተቀባይነት የማልበቃ ነኝ የሚለውን ስሜቴን ብቻ አባባሰው።» ዛሬ ፒተር በክርስቶስ ያለውን ዋጋ አውቆ በአዲስ ነፃነት እየተመላለሰ ነው።
የስለት ቍስሎች
ለሌሎች ደግሞ ቍስሉ በአንድ ድርጊት የተፈጠረ ሊሆን ይችላል - በስለት ከመወጋት ጋር የሚመሳሰል ቍስል። የታወቀው ምሳሌ፣ በእርግጥ፣ በሚታመንና በሚወደድ ሰው የወሲብ ጥቃት የደረሰበት ልጅ ነው። በዚህ ምሳሌ ልጁ ተጠቂው እንጂ በደለኛው እርሱ እንዳልሆነ አይረዳም። ስለ ሁኔታው ለመናገር ይፈራል፤ ይልቁንም በትዝታው ውስጥ ቀብሮ ማቆየትን ይመርጣል።
ከጊዜ በኋላ ቍስሉ ይሸፈናል፤ በጕልምስና ዕድሜም እንኳ ለመጋፈጥ ወደ ላይ በቀላሉ አይወጣም።
ቍስሉ የተሸፈነበት «ማሰሪያ» የአዋቂውን ሰው ሌሎች የባሕርይ ክፍሎች የሚነካ እስራት ሆኗል። እንደዚህ ያለች ነፍስ ፈውስ ያስፈልጋታል!
አሌክን ማንበብና መጻፍ ለምን እንዳልቻለ በጠየቅሁት ጊዜ አንድ አሳዛኝ ታሪክ ነገረኝ። አባቱ ጥሏቸው ከሄደ በኋላ ለአራት ዓመታት እናቱ ብቸኛ ልጅዋን እጅግ አቀማጥላ ነበር። ከዚያም ሌላ አባት መጣ - አሌክን በአጠገቡ መኖሩን የማይወድና የማይፈልግ። ብዙም ሳይቆይ የመገፋትን ጥልቅ ሕመም አወቀ።
አሌክ በአምስት ዓመቱ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ገባ፤ በዚያም በክፍሉ ኋላ ተቀምጦ በሕልም ዓለም ይዋኝ ነበር። አንድ አሳቢነት የጎደለው መምህር የጮኸበትን ጊዜ በደንብ ያስታውሳል። «አሌክ፣ አንተ ከደደብ በቀር ሌላ ምንም አይደለህም!» የቆሰለችው ትንሽ ነፍስ ለራሷ «እንደዚያ የምታስበኝ ከሆነ እንደዚያው እሆናለሁ!» አለች። ገና ትንሽ ልጅ ሳለ ያንን መምህር ለማስደሰት ፈጽሞ ላለማጥናት ወሰነ… ስለዚህም ማንበብና መጻፍ የማይችል ጎረምሳ ሆኖ አደገ!
አሌክ ለመማር የሚያስችል በቂ ብልህነት ነበረውን? ከተነጋገርን ከአንድ ወር በኋላ ብቻ አሌክ በዕለታዊው ጋዜጣ ያሉትን የስፖርት ዜናዎች ሁሉ እያነበበ ነበር! በአንዲት ወጣት ሴት ላይ ፍላጎት አድሮበት ስለ ነበር ፈውሱን በተግባር ለመኖር ተነሣሥቶ ነበር። ስለ ስፖርተኞች ያለውን እውቀትና በጋዜጦች ያሉትን ፎቶግራፎቻቸውን ተጠቅሜ ሥዕሎቹን የሚያብራሩትን ቃላት እንዲያነብ አበረታታሁት።
ብዙም ሳይቆይ ሥዕሎች አላስፈለጉትም፤ በማስተዋል ማንበብ ሲጀምር ለራሱ ያለው ግምት ሲያድግ ተመለከትሁ። ብዙ መምህራን፣ ወላጆችና ሌሎች ሰዎች አሳቢነት የጎደላቸው ቃሎቻቸው በብዙ ወጣት ነፍሳት ላይ ያስከተሉትን የስለት ቍስል አሉታዊ ክብደት ፈጽሞ አያውቁም። ዛሬ ብዙ አዋቂዎች የእነዚያን ቍስሎች ቅርፊቶችና ጠባሳዎች አሁንም በነፍሳቸው ላይ ተሸክመው ይኖራሉ!
ጭረቶች
ከዚያም የጭረት ዓይነት ቍስሎች አሉ። ብዙውን ጊዜ ጠባሳ ወይም ዘላቂ እስራት አይተዉም፤ በተጎዱበት ጊዜ ግን በብዛት ሊደሙ ይችላሉ። በትክክል ካልታከሙ ግን ሊመግሉና ከዚያ የከፋ ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ። እንደዚህ ያሉ የነፍስ ቍስሎች አንድ ሰው ተስፋ ሲቆርጥ ወይም ታላቅ ብስጭት ሲገጥመው ሲከሰቱ አያለሁ። ይህም የብቃት ማነስና የብቸኝነት ስሜት አብሮት ይመጣል፤ መንፈሳዊ መከላከያዎችም ይወድቃሉ።
ይህ ለተጎዳው ሰው በርኅራኄ ድጋፍ በዙሪያው መቆም የሚያስፈልገን ጊዜ ነው። የመተሳሰብና የመረዳት ጊዜ ነው።
ሜሪ በዘጠናዎቹ ዓመታት በሰፊው የሚታወቀው በሽታ በነበረው በ«ኤፕስታይን ባር» ወይም «የዩፒ ጉንፋን» ታመመች። ሐኪሞቹ ዝግጁ መድኃኒት ስላልነበራቸው ለምን ያህል ጊዜ ታማ እንደምትቆይ አለማወቅ ከባድ ነበር። የቤተ ክርስቲያኗ አባላት ይጸልዩላት ነበር፤ እርሷ ግን አንድ ሰው መጥቶ ቢጠይቃት ትመኝ ነበር። ማንም አልመጣም፤ ምክንያታቸውም እንዲህ ያለው በሽታ ተላላፊ መሆን አለመሆኑን እርግጠኞች አለመሆናቸው ነበር። ይህንን መቀበል ከባድ ነበር፤ ሜሪ ግን በጸጋ ተቀበለችው። ከዚያም አንድ ቀን በነፍሷ ላይ ብዙ «መድማትን» ያስከተለ የስልክ ጥሪ ደረሳት። የቅርብ ወዳጇ ደውላ ሜሪ እምነትን እየተለማመደች እንዳልሆነች ግልጽ ስለ ሆነ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለሜሪ መጸለይን እንዳቆመች ነገረቻት። ምክንያታቸውም እንዲህ እያደረገች ቢሆን ኖሮ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ትድን ነበር የሚል ነበር።
ስብራቶች
በምሳሌዎቻችን እንቀጥል። በነፍስ ውስጥ እንደ ስብራት ያሉ ቍስሎች አሉን? አዎ፤ በአንድ አሰቃቂ ገጠመኝ ምክንያት በሕይወት ውስጥ እያነከሱ የሚሄዱ ብዙ አማኞች አሉ። የሚወዱት ሰው ሞት፣ የፈረሰ የጋብቻ ቃል መግባት ወይም አንድ የሕይወት አደጋ ሊሆን ይችላል። በገጠማቸው ነገር ሽባ ሆነዋል፤ እንደገና መራመድንም ፈጽሞ አልተማሩም።
ሜሊንዳ ከእናቷ ጋር ተከራክራ ነበር፤ በክርክሩ መካከልም በኃይል ገፍታት ነበር። ከጥቂት ወራት በኋላ እናቷ የጡት ካንሰር እንደ ያዛት ታወቀ፤ በአንድ ዓመት ውስጥም ሞተች። ምንም ዓይነት ክርክር ሜሊንዳ መግፋቷ በእናቷ ላይ ካንሰሩን እንዳላመጣ ሊያሳምናት አልቻለም። ራሷን ይቅር ማለት አልፈለገችም፤ የጌታንም ይቅርታ መቀበል አልቻለችም። ባገኘኋት ጊዜ የተሰበረች ሴት ነበረች፤ እስከ ዛሬም ድረስ ሽባ እንደ ሆነች ናት።
«ነፍሴን መለሳት»
ዛሬ ብዙ አማኞች የቆሰለች ነፍስ እንዳላቸው እርግጠኛ ነኝ። ጌታ እነዚያን ቍስሎች ሊፈውስ - ነፍስን ሊመልስ - እንደሚፈልግም እርግጠኛ ነኝ። መዝሙረኛው ዳዊት በዝሙትና በነፍስ ግድያ በደለኛ ነበረ፤ አስከፊ የነፍስ ቍስሎችን ተሸክሞ ነበር፤ ሆኖም አሁንም «እግዚአብሔር እረኛዬ ነው… ነፍሴን መለሳት» ማለት ይችል ነበር (መዝሙር 23:3)።
በራሳችን ሥራ የተፈጠሩ ቍስሎችም አሉ። ሆን ብለን ከግልጹ የእግዚአብሔር ቃል በተቃራኒ ስንመላለስ የራሳችንን ቍስሎች የምንፈጥር ይመስለኛል። ከጋብቻ ውጭ ያለ ወሲብና ፍቺ ሁልጊዜ በእግዚአብሔር ጸጋ መፈወስ የሚያስፈልጋቸውን የቆሰሉ ነፍሳት ይፈጥራሉ። እንዲህ ያለውን ፈውስ ማምጣት የእርሱ ፍላጎት እንደ ሆነ እጅግ እርግጠኛ ሁን። እንዲያውም ይህንን እንደ እውነተኛው የመቀደስ ሥራ - የመዳን ሁለተኛው ክፍል አድርጌ አየዋለሁ።
መጽደቅ አንድ ሰው ከኃጢአት ቅጣት ነፃ የወጣበት ነው፤ ለመንፈሱ መዳን ነው። መንፈስ ቅዱስ ይህንን ሥራ አስቀድሞ ፈጽሞታል።
መቀደስ አንድ ሰው ከኃጢአት ኃይል ነፃ የሚወጣበት ነው፤ ለነፍሱ መዳን ነው። ይህ የመንፈስ ቅዱስ የአሁኑ ሥራ ነው።
መክበር አንድ ሰው ከኃጢአት መገኘት ነፃ የሚወጣበት ነው፤ ለሥጋ መዳን ነው። ይህ መንፈስ ቅዱስ ገና የሚሠራው ሥራ ነው።
በእነዚህ ምክንያቶች አዳኝ ብለን እንጠራዋለን!
ዓሣ አጥማጁ
ሰይጣንን ከሚያገሣ አንበሳና ከቀስተኛ ጋር አመሳስለነዋል፤ ይሁን እንጂ ከጦር ዘዴዎቹ ሁሉ ይበልጥ ውጤታማው እንደ ዓሣ አጥማጅ መንጠቆና በትር ይመስለኛል - የነፍሳችን ቍስሎች የት እንዳሉ በትክክል ያውቃል። ለመሆኑ እነርሱን በመፍጠር ረገድ ተሳታፊ ነበረ። በሰማያዊ ስፍራ ወዳለው ውጊያ ለመግባት ስንዘጋጅ፣ ያን ጊዜ ገመዱን ይወረውራል፤ በቍስሉ ውስጥ ያጠምደዋል፤ ነፍስንም ውጤት አልባ እንድትሆን ያሽከረክራታል።
የግል ታሪክ
በ1990 መጀመሪያ ላይ በምዕራብ ካናዳ ተወላጅ ሕዝቦች መካከል በተጀመረ አዲስ የእግዚአብሔር ሥራ ውስጥ በቅርብ ተሳተፍሁ። መንፈሳዊው ውጊያ እጅግ ብርቱ ነበር። በዚያው ጊዜ እንቅልፍ ማጣትም ጀመርሁ። ሐኪሜ እንድተኛ ለማድረግ ብዙ የተለያዩ መድኃኒቶችን ሞከረ፤ ነገር ግን ሌሊቱን ሙሉ ነቅቼ እንዳላድር የሚያደርግ መንገድ እስኪገኝ ድረስ ብዙ ሳምንታት ፈጀ። ብዙዎች የሕንዳውያን (የአገሬው ተወላጆች) እርግማን ያረፈብኝ መስሏቸው ነበር፤ ከሰሜን ምዕራብ አሜሪካና ከካናዳ ሁሉ የማበረታቻ ደብዳቤዎችና የስልክ ጥሪዎች ይደርሱኝ ነበር። ሌላ ፓስተርና ባለቤቱ የሆኑትን ቻርልስንና ክላውዲያን እንዲጸልዩልኝ ጠየቅኋቸው፤ በዚያን ጊዜ እርሷ በላዬ ላይ «አስከፊ የመተው መንፈስ» እንዳለ እንደምትገነዘብ ነገረችኝ። ምን ማለቷ እንደ ሆነ ምንም አልገባኝም።
ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ለካህናትና ለሚስቶቻቸው በተዘጋጀ የአንግሊካን መንፈሳዊ ማረፊያ አንድ ሳምንት እንዳሳልፍ ተጋበዝሁ። በዚያም ከስሜቶቼ አንድ ክፍል እንደ ጎደለና ይህም ከእናቴ ሞት ጋር ብዙ ግንኙነት እንዳለው ተነገረኝ። እናቴ የሞተችው ጎረምሳ ሳለሁ ነበር፤ በዚያን ጊዜ እንደ ተለመደው ሐዘን ባላለቅስም፣ የእርሷን ሞት በሚገባ እንደ ተወጣሁት አስቤ ነበር። አሁን ይህ ከእንቅልፍ ማጣቴ ጋር አንድ ግንኙነት እንዳለው እየተነገረኝ ነበር? አሁንም አልገባኝም።
ከአራት ወራት በኋላ ከቤተ ክርስቲያኑ ኃላፊነቴ ለመልቀቅ ጠየቅሁ፤ ሽማግሌዎቹና አባላቱ ግን አልፈቀዱልኝም። ይልቁንም እነርሱና በከተማችን ያለው ሰፊው የቤተ ክርስቲያን አካል ብዙ ፍቅር አሳዩኝ።
ከስምንት ወራት በኋላ በቫንኩቨር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል የእንቅልፍ ክሊኒክ ታካሚ ሆኜ ገባሁ፤ በዚያም ሰውነቴ እንቅልፍ የሚያመጡትን የነርቭ ኬሚካሎች በማምረት ረገድ አካላዊ ብልሽት እንደ ደረሰበት ታወቀ። ስፔሻሊስቱ የዚህ ምክንያት ጭንቀት እንደ ሆነ ገለጸ። በሚቀጥለው ሳምንት ከቤተ ክርስቲያኑ መልቀቅ ቻልሁ፤ ቤተ ክርስቲያኑ አሁን በዓመቱ መጀመሪያ ከነበረው የምእመናን ተገኝነት ወደ ስድሳ በመቶ ዝቅ ብሎ ነበር።
በሚቀጥለው ማክሰኞ በየሳምንቱ ለጸሎት ከሚሰበሰቡ የቅርብ ወዳጆቼ፣ ከሌሎች ፓስተሮች ቡድን ጋር ነበርሁ። ቁርሳችንን እንደ ጨረስን ከእነርሱ አንዱ «ጋሬዝ፣ በላይህ ላይ አስከፊ የመተው መንፈስ እንዳለ ይሰማኛል!» አለኝ። እነዚህ ከዘጠኝ ወራት ገደማ በፊት የሰማኋቸው ቃላት ነበሩ። ወደ ቤት በተመለስሁ ጊዜ በአስተያየቷ ምን ማለቷ እንደ ነበረ እንድታብራራልኝ ለመጠየቅ ወደ ክላውዲያ ደወልሁ። በዚያ ምሽት ተቀምጬ ሕይወቴን መለስ ብዬ እንድቃኝ፣ በውስጤ ያለው ትንሹ ልጅ እንደ ተተወ የተሰማው ጊዜያትን እንድፈልግ ነገረችኝ።
እኔና ባለቤቴ አን የሕይወቴን የተለያዩ ወቅቶች ስናጤን ተደነቅን - የመተውን ሕመም የተሰማኝ እጅግ ብዙ ጊዜያት ነበሩ፤ ከእነርሱም ትንሽ ያልሆነው ገና የአሥራ አራት ዓመት ልጅ ሳለሁ የእናቴ ሞት ነበር። ያን ጊዜ አላለቀስሁም ነበር፤ ከዚያ በኋላ ግን ለተወሰነ ጊዜ አዝኜ ነበር። በዚያው ምሽት ቆየት ብዬ ስለ አሥራ ሦስተኛው ክፍለ ዘመን የመስቀል ጦርነቶች የሚተርክ ልብ ወለድ ለማንበብ ዘና አልሁ።
ሁለት ባላባቶች ሰዎቻቸውን እየመሩ በፈረንሳይ ሜዳዎች ላይ ወደ ውጊያ እየገቡ ነበር። ድንገት ፊት ለፊት ተገናኙ፤ ነገር ግን ሰር ሩፋስ ቆስሎ በኮርቻው ላይ ተዝለፍልፎ ነበር፤ ሰይፉም በጎኑ ተንጠልጥሎ ነበር። ጠላቱ ሰር ናይጄል ተቃዋሚውን ለመግደል ኃያል ሰይፉን ከፍ አድርጎ በፍጥነት ወደ እርሱ ጋለበ። ልክ የሞት ምቱን ሊመታ ሲል፣ ከሰር ሩፋስ ቀስተኞች ዘጠኝ ፍላጻዎች በአየር ላይ በርረው ዒላማቸውን በሰር ናይጄል ብብት ውስጥ አገኙ። በጦር ልብሱ ላይ ምንም ውጤት አልነበራቸውም፤ ምንም ጦር ልብስ ሊለበስበት በማይችልበት ደካማ ስፍራው ላይ ግን እጅግ ውጤታማ ነበሩ። የጌታ መንፈስ እየተናገረኝ እንደ ነበረ ተሰማኝ።
«ጋሬዝ፣ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር እየለበስህ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ከጠላት ጋር ወደ ውጊያ ስትገባ በጣም ደካማ ስፍራዎችህ የት እንዳሉ በትክክል እንደሚያውቅ ተገንዘብ - የአንተ ደካማ ስፍራ ደግሞ የመተው ስሜት ነው። በውጊያው ውጤታማ እንድትሆን ከፈለግህ መፈወስ አለባቸው!»
ሰዎች ባለፉት ሁለት ዓመታት ከቤተ ክርስቲያናችን ቀስ በቀስ ለምን እየራቁ እንደ ነበሩ አሁን መረዳት ጀመርሁ። ሦስት ሽማግሌዎች በሥራ ቦታ ለውጥ ምክንያት ለቀው ነበር፤ በሦስት ሌሎች መልካም ሰዎችም ተተክተው ነበር፤ ይሁን እንጂ አዲሱ የሽማግሌዎች ቦርድ የቀድሞዎቹ ሰዎች የጀመሯቸውን መርሐ ግብሮች ለማስቀጠል አስፈላጊ የሆኑ ስጦታዎች አልነበሩትም፤ ብዙም ሳይቆይ ከቤተ ክርስቲያኑ ቀስ ያለ ፍልሰት ተጀመረ። በመንገድ ላይ የማገኛቸው ሰዎች እየተጣደፉ ወደ እኔ መጥተው እንደሚወዱኝ፣ ነገር ግን «ልጆቻችን የወጣቶች አገልግሎታቸውን እጅግ ስለሚወዱት» ወደ ሌላ ቤተ ክርስቲያን መሄድ እንደ ጀመሩ ይነግሩኝ ነበር። ብዙ ምክንያቶች ነበሩ፤ ነገር ግን መጥተው አሳባቸውን ሊነግሩኝ የሚያስችል ጸጋ ያሳዩት ጥቂቶች ነበሩ። መዛወር እንደሚፈልጉ ባውቅ ኖሮ የመሸኛ ደብዳቤ በደስታ እሰጣቸው ነበር።
ከዚያም ይበልጥ እየደከምሁ ስሄድ፣ እንደ ለመዱት መንጋዬን እየመገብሁና እየመራሁ አልነበረም፤ ስለዚህ ተጨማሪ ሰዎች መልቀቅ ጀመሩ። እለምደው የነበረውን እርካታ በማግኘት ፋንታ፣ በየሳምንቱ ማለት ይቻላል ሌላ ባዶ ወንበር የማየት ሕመም ነበረብኝ። ለሕዝቤ እጅግ የተሰጠሁ ስለ ነበርሁ እያንዳንዱ መልቀቅ እንደ ትንሽ ፍቺ ነበር። ከእነዚያ ሰዎች ማንም ሆን ብሎ ሊጎዳኝ እንደማይፈልግ እርግጠኛ ነኝ፤ ጠላት ግን ድርጊታቸውን በመተው ቍስሎቼ ውስጥ እንደ መንጠቆ ተጠቀመበት። የቤተ ክርስቲያኔን ችግሮች ፈጽሞ ወደ ቤቴ አልወስድም ብዬ ብመካም ሐኪሙ ጭንቀት ብሎ መጥራቱ አያስደንቅም!
የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናቸውን ለመልቀቅ ሊያስቡ ለሚችሉ አንባቢዎች አንድ የግል ማሳሰቢያ፦ በትክክለኛውና በሥነ ምግባራዊው መንገድ አድርገው። ለፓስተርህ አሳብህን አሳውቀው፤ ምክንያቱም እርስ በርሳችን ምን ያህል በቀላሉ እንደምንቋሰል በትክክል ብታውቅ ትገረም ነበር።
ምዕራፍ 10 ተጠናቋል
የቆሰለች ነፍስ