በእጄ ያለው መክፈቻ
የሰይጣን ዘዴዎች

ምዕራፍ 7 · 6 ደቂቃ ንባብ

የሰይጣን ዘዴዎች

ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሞቶ ከዚያም ከሙታን በተነሣ ጊዜ ሰይጣንንና የአጋንንት ሠራዊቱን ድል ነሥቶ ኃይላቸውን ሁሉ ገፈፋቸው፤ «አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ ድል በመንሣት በእርሱ እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው» (ቆላስይስ 2:15)። አሁን የሚዋጉት በውሸት፣ በማታለልና በፍርሃት ነው፤ እርሱም እነዚህን ወደ ሕይወታችን ክፍሎች ሁሉ ያሰርጻቸዋል፦ ወደ ዝንባሌዎቻችን፣ ወደ ስሜቶቻችን፣ ወደ አሳቦቻችን፣ እንዲያውም ወደ ሥጋችንም ጭምር።

ይሁን እንጂ በእነዚህ ክፍሎች ላይ ኃይል የሚኖራቸው እኛ ስንሰጣቸው ብቻ ነው! ሐዋርያው ጳውሎስ የእርሱን አሳብ እንደማንስት ተናግሯል (2ኛ ቆሮንቶስ 2:11)፤ የሚያሳዝነው ግን ይህ ዛሬ ለአብዛኞቹ አማኞች በፍጹም እውነት አለመሆኑ ነው!

የዲያብሎስ ፈንታ

ተቆጥተህ ታውቃለህ? እንዴታ ተቆጥተሃል። እኔም እንደዚሁ። ኢየሱስም በቤተ መቅደስ ውስጥ ገንዘብ ለዋጮችን ባየ ጊዜ ተቆጥቷል።

ሕዝቡን በከፋ ድህነትና በብዙ ደዌ ውስጥ ሆነው ባያቸው ጊዜም እንደ ተቆጣ እርግጠኛ ነኝ። የአዳም አለመታዘዝ ውጤት በሰው ልጆች ሁሉ ላይ ሲወድቅ ባየ ጊዜ ልቡ አዘነ። የቁጣ ስሜት በራሱ ኃጢአት አይደለም። ስሜቶች ሥነ ምግባራዊ ወይም ኢ-ሥነ ምግባራዊ አይደሉም - ከሥነ ምግባር ውጭ ናቸው። ይሁን እንጂ በስሜቶቻችን የምናደርገው ነገር እጅግ በጣም ያስፈልጋል። ጳውሎስ በተቆጣን ጊዜ ኃጢአት እንዳንሠራ ይመክረናል። ከዚያም በመቀጠል፣ «በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ» ይላል (ኤፌሶን 4:26)።

ሁኔታውን ወዲያውኑ መፍታት አለብን። በውስጣችን ያለው ቁጣ እንዲመግል ከፈቀድንለት፣ የእግዚአብሔርን ምርጥ ነገር የሚዘርፍብን ምሬት ይወልዳል። በዚህ ዓለም እስካለን ድረስ ሰዎች ይበድሉናል፤ መሰናክልም ይመጣል። ኢየሱስ ይህንን አስቀድሞ አስጠንቅቆናል (ሉቃስ 17:1)። ከቁጣችን በስተ ጀርባ «መልካም» ምክንያት ሊኖር ይችላል፤ እርሱ ግን በእንደዚህ ያሉ ጊዜያት ጸጋን እንድናውቅ የሚያስችለንን መንፈስ ቅዱሱን ሰጥቶናል።

«ከሰው ሁሉ ጋር ሰላምን ተከታተሉ ትቀደሱም ዘንድ ፈልጉ፥ ያለ እርሱ ጌታን ሊያይ የሚችል የለምና። የእግዚአብሔር ጸጋ ለማንም እንዳይጎድለው፥ ብዙዎቹም የሚረክሱበት አንድ መራራ ሥር ወደ ላይ በቅሎ እንዳያስጨንቅ» (ዕብራውያን 12:15)።

ቁጣውን በተገቢው መንገድ ካልፈታነው (ይህንንም ወደ ኋላ እንወያይበታለን)፣ ራሳችንን በቀጥታ በጠላት እጅ አሳልፈን እየሰጠን ነው! ጳውሎስ በመቀጠል «ለዲያብሎስም ፈንታ አትስጡት» ይላል (ኤፌሶን 4:27)። በዚያው የመጽሐፍ ክፍል ቆየት ብሎ እርስ በርሳችን ስለምንነጋገረው ነገር ሲያስተምር፣ መንፈስ ቅዱስን እያሳዘንን ሊሆን እንደሚችል ያስጠነቅቀናል (ኤፌሶን 4:30)።

ቁጣን (ወይም ሌሎች የተሳሳቱ ዝንባሌዎችን) ስንሸከም፣ ጠላት ወደ አሳቦቻችን መግቢያ ያገኛል፤ ውሸቱንና ማታለሉንም እየዘራ ሽብልቁን ይበልጥ ወደ ውስጥ ይነዳዋል። ብዙም ሳይቆይ እርቅ የማይቻል መስሎ ይታያል፤ እርሱም ያንን ውጊያ አሸንፏል።

ኢየሱስ ለራሳችን እንድንጠነቀቅ አስጠነቀቀን (ሉቃስ 17:3)፤ ጳውሎስም በሰይጣን እንዳንታለል እንድንጠነቀቅ አዘዘን (2ኛ ቆሮንቶስ 2:11)። ሁለቱም የተነገሩት እንደ በደሉን በምናስባቸው ሰዎች ላይ ይቅርታ ከማድረግ ጋር በተያያዘ ነው። ይቅር ያለማለት ዝንባሌ (እንደ ቁጣ) ለጠላት ብልጫን - ፈንታን - በሕይወታችን ውስጥ የእግር መርገጫን ይሰጠዋል። ተቃራኒዎቹ የይቅርታና የሰላም ዝንባሌዎች ግን ድል ያደርጉታል።

የሚያገሣው አንበሳ

አንበሳ የሚያድነውን እንስሳ አድብቶ ሲከተል አይተህ ታውቃለህ? እኔ አላየሁም፤ ነገር ግን ድመቴ በአትክልት ቦታችን ውስጥ ወፎችን ወይም አይጦችን አድብቶ ሲከተል ከማየው ብዙም የተለየ አይሆንም ብዬ እገምታለሁ። ሊይዘው ያሰበውን እንስሳ ስለ ዓላማው እንዳያስጠነቅቀው እጅግ ዝቅ ብሎ ያጎነብሳል፤ በጣም ቀስ ብሎም ይንቀሳቀሳል። በእርግጥም በከፍተኛ ድምፅ «ሚያው» ብሎ መምጣቱን አያሳውቃቸውም!

እንግዲያስ ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ «በመጠን ኑሩ ንቁም፥ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና» ብሎ ሲነግረን ምን ማለቱ ነው (1ኛ ጴጥሮስ 5:8)?

በጆን ባንየን «የመንገደኛው ጉዞ» (ፒልግሪምስ ፕሮግረስ) በተባለው መጽሐፍ ውስጥ፣ መንገደኛው ለአማኞች እረፍትና ደኅንነት ወደ ተሠራው ውቡ ቤተ መንግሥት እየቀረበ እንደ ነበር እናነባለን። ወደ ሰማያዊቷ ከተማ የሚጓዙት ሌሎቹ ፈሪው (ቲሞረስ) እና ተጠራጣሪው (ሚስትረስት) በታላቅ ፍርሃት አልፈውት ለምን እንደ ሸሹ አሁን ገባው፤ የመግቢያው በር በሁለት አንበሶች ይጠበቅ ነበርና።

ወዲያውኑ የመንገደኛው ልብ ከዳው፤ እርሱም ደግሞ ፈራ።

አንድ አንበሳ እየዘለለ ወደ ክፍልህ ገብቶ ቢያገሣብህ፣ አንተም እንደ እነርሱ - በፍርሃት ተሞልተህ - ምላሽ የምትሰጥ ይመስለኛል! እኔም እንደዚያ አደርግ ነበር!

የሚያገሡ አንበሶች በእኛ ላይ እንዲህ ያለ ተጽዕኖ አላቸው - እጅግ የሚያስፈሩ ናቸው።

ብዙም ሳይቆይ መንገደኛው ሁለቱም አንበሶች በሰንሰለት እንደ ታሰሩ፣ በመካከላቸው ባለው ጠባብ መንገድ እስከ ሄደ ድረስም ሁለቱም ሊደርሱበትና ሊጎዱት እንደማይችሉ አስተዋለ። አንበሳው ሰይጣን ጥርሶቹ እንደ ተነቀሉና በሰንሰለት እንደ ታሰረ መረዳት ያስፈልገናል።

በጠባቡ መንገድ እስከ ጸናን ድረስ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ሊጎዳ አይችልም። ከጠባቡ መንገድ ወጣ ብንል እንኳ ጠላት ሊያጠፋን ከመቻሉ በፊት የአብ ፍቅር ሊመልሰን ይዘረጋል። ይሁን እንጂ እርሱ ያገሣል፤ ብዙዎችም ስሜታቸው ለግሣቱ በሚሰጠው ምላሽ ይሸነፋሉ።

ግሣቱ ብዙ ጊዜ ኵነኔን የሚያመጣ የከሳሹ ድምፅ ነው።

ሜሪ በወጣቶች የመዘምራን ቡድን ውስጥ የብቻ ክፍሎችን ስትዘምር ይህ የመጀመሪያዋ ነበር። በዝማሬው አዝማች ውስጥ ካለው ከዚያ ከፍ ያለ ድምፅ በቀር፣ ሁሉም ነገር መልካም ሄደ፤ እዚያ ላይ ግን ድምፅዋ ትንሽ ደከም ብሎ ተንቀጠቀጠ። በጆሮዋ «ራስሽን አስገመትሽ» ብሎ የሾከሾከላት ጸጥ ያለ ድምፅ ብቻ ነበር፤ ነገር ግን እርሱ የአንበሳው ግሣት ነበር። ዳግመኛ በሕዝብ ፊት ላለመዘመር ተሳለች።

ፓስተር ጆን በቅዱስ ጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎቱን ሲጀምር ታላቅ ተስፋ ነበረው። አሁን ከሁለት ዓመት በኋላ ብቻ እየለቀቀ ነበር።

የወጣቶቹ ቡድን ዋናው ፓስተር እንደ ጠበቀው በቍጥር አላደገም ነበር፤ ስለዚህ ጆን እንዲለቅ ተጠየቀ። አንበሳው «እንደ ፓስተር ፈጽሞ አትሳካም። አንተ ውድቀት ነህ!» ብሎ አገሣ። ከአንድ ሳምንት በኋላ፣ እግዚአብሔር ለእረኝነት አገልግሎት እንደ ጠራው ለመጀመሪያ ጊዜ ባመነ ጊዜ ትቶት ለነበረው ዓለማዊ ሥራ እንደገና አመለከተ።

አሌክ እንደገና ወደቀ። ከዚህ ቆሻሻ የማጨስ ልማድ ነፃ ለመውጣት እጅግ ይናፍቅ ነበር፤ ነገር ግን ይህ ሲጋራ ሲቀርብለት ፈተናው በረታበት። አሁን የበደለኛነት ስሜት ተሰማው፤ አንበሳውም «እግዚአብሔር ሊጠቀምብህ አይችልም። ሁልጊዜ ታሳፍረዋለህ!» ብሎ አገሣ።

አንበሳው በእያንዳንዱ መንሸራተት ወይም ውድቀት ላይ ማግሣቱ ብቻ ሳይሆን፣ ከስሜቶቻችን መካከል በግሣቱ በቀላሉ ሊነኩ የሚችሉት የትኞቹ እንደ ሆኑም ያውቃል። ለአንዳንዶች የበደለኛነት ስሜት ነው፤ ለሌሎች ደግሞ ፍርሃት ነው። ብዙዎች ለግሣቱ ምላሽ የሚሰጡት ራስን ዝቅ አድርጎ በማየትና በመተማመን ማጣት ስሜት ነው። አንተ ምላሽ የምትሰጠው በየትኛው ነው?

የአንበሳው ግሣት በሌላ አማኝ ግድየለሽ አስተያየት በኩል ሲመጣ ምንኛ ያሳዝናል! በክርስቶስ አካል ውስጥ ውሸቶቹን - የዲያብሎስን ግሣት - ለመቃወም እርስ በርሳችን ማጽናትና ማበረታታት እጅግ አስፈላጊ ነው!

ቀስተኛው

አንድ ሰው ውጊያ ሊገጥም ሲል ከፍተኛውን ስፍራ መያዝ መልካም ነው። ይህም የጠላትን እንቅስቃሴ ለማየትና እነርሱን ለመቋቋም ተገቢውን እርምጃ ለመውሰድ ያስችልሃል። እንደ አማኞች «በክርስቶስ» የመሆንን ታላቅ መብት መረዳት ያስፈልገናል። ጳውሎስ እግዚአብሔር «ኢየሱስን ከአለቅነትና ከሥልጣን ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይ» ከፍ ከፍ እንዳደረገው ይናገራል (ኤፌሶን 1:21)።

ለአይሁድ እነዚህ የሰይጣን የአጋንንት ሠራዊት ማዕረጎች ስሞች ናቸው፤ ሁሉም ግን ከእግሩ በታች እጅግ ዝቅ ብለው ይገኛሉ። የአለቃቸውን ራስ ቀጥቅጧል፤ በእነርሱም ላይ ሥልጣን ሁሉ አለው። ድል ነሺዎች መሆንን እንድንማር ያንን ሥልጣን እንድንጠቀምበት ይፈልጋል። ከእርሱ ጋር የሚነግሡ አክሊልን ለመልበስ የተገባቸው መሆን አለባቸው፤ አክሊሎችም የሚሰጡት ለድል ነሺዎች ብቻ ነው።

«[ክርስቶስ] ከእርሱ ጋር አስነሣን፥ በክርስቶስ ኢየሱስም ከእርሱ ጋር በሰማያዊ ስፍራ አስቀመጠን» (ኤፌሶን 2:6)።

ሰይጣን ሊደርስብን የሚችለው የሚንበለበሉ ፍላጻዎቹን በመወርወር ብቻ በሆነበት በዚያ ከፍተኛ ስፍራ ላይ መኖር አለብን። ጳውሎስ፣ «በሁሉም ላይ ጨምራችሁ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ» ብሎ በሚጽፍበት ጊዜ በእነዚያ በሚንበለበሉ ፍላጻዎች ላይ እርግጠኛ መከላከያም ተሰጥቶናል (ኤፌሶን 6:16)። ጠላት ውሸቶቹንና ክሶቹን በእኛ ላይ ሲወረውር፣ «እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው» የሚለውን በማስታወስ የእምነት ጋሻችንን ከፍ እናደርጋለን (ሮሜ 10:17)።

ማን እንደ ሆንንና «በክርስቶስ» የመሆንን መብቶች ማወቅ ያስፈልገናል።

እኔ… ● የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ (ዮሐንስ 1:12)።

● የኢየሱስ ወዳጅ ነኝ (ዮሐንስ 15:15)።

● ከክርስቶስ ጋር አብሮ ወራሽ ነኝ (ሮሜ 8:17)።

● ከጌታ ጋር ተጣብቄአለሁ (1ኛ ቆሮንቶስ 6:17)።

● የአካሉ ብልት ነኝ (ኤፌሶን 5:30)።

● ከእግዚአብሔር ጋር ታርቄአለሁ (2ኛ ቆሮንቶስ 5:18)።

● የእግዚአብሔር እጅ ሥራ ነኝ (ኤፌሶን 2:10)።

● የሰማይ ዜጋ ነኝ (ፊልጵስዩስ 3:20)።

● አዲስ ፍጥረት ነኝ (2ኛ ቆሮንቶስ 5:17)።

● በእግዚአብሔር የተመረጥሁ ነኝ (ቆላስይስ 3:12)።

● ቅዱስ ነኝ (ኤፌሶን 1:1)።

● በዚህ ዓለም እንግዳ ነኝ (1ኛ ጴጥሮስ 2:11)።

● በእግዚአብሔር ጸጋ የሆንሁትን ነኝ (1ኛ ቆሮንቶስ 15:10)።

● የሰይጣን ጠላት ነኝ (1ኛ ጴጥሮስ 5:8)።

● ጽድቅን ለብሻለሁ (ኤፌሶን 4:24)።

● የእግዚአብሔር ማደሪያ ነኝ (1ኛ ቆሮንቶስ 3:16)።

● የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ ቅዱስ ሕዝብና የእግዚአብሔር ርስት የሆነ ወገን አባል ነኝ (1ኛ ጴጥሮስ 2:9-10)።

በክርስቶስ እኔ… ● ሙሉ በሙሉ ይቅር ተብያለሁ (ሮሜ 5:1)።

● እጅግ ተባርኬአለሁ (ኤፌሶን 1:3)።

● ቅዱስ እንድሆን ተመርጬአለሁ (ኤፌሶን 1:4)።

● በመንፈሱ ታትሜአለሁ (ኤፌሶን 1:13)።

● ልጁ እንድሆን አስቀድሞ ተወስኜአለሁ (ኤፌሶን 1:5)።

● ክርስቶስ በውስጤ አለ (ቆላስይስ 1:27)።

● ሙሉ ሆኛለሁ (ቆላስይስ 2:10)።

● ከሰይጣን እጅ ተዋጅቻለሁ (ኤፌሶን 1:7)።

● በሰማያዊ ስፍራ ተቀምጬአለሁ (ኤፌሶን 2:6)።

● ከኵነኔ ነፃ ነኝ (ሮሜ 8:1)።

● ወደ እግዚአብሔር በቀጥታ መግባት አለኝ (ኤፌሶን 2:18)።

● በድፍረት ወደ እግዚአብሔር መቅረብ እችላለሁ (ኤፌሶን 3:12)።

የተሟላ ዝርዝር ለማግኘት መጽሐፍ ቅዱስህን አንብብ!

ቀደም ሲል ለአብዛኞቹ ቀላል ሕመሞች አንድ ቀላል መፍትሔ ነበር፦ «ሁለት አስፕሪን ውሰድና ተኛ!» ዛሬ እኔም ለአብዛኞቹ የጠላት ቀላል ጥቃቶች የማቀርበው ቀላል መፍትሔ አለኝ።

ከላይ ከተዘረዘሩት ጥቅሶች በየቀኑ ሁለቱን ውሰድና አሰላስላቸው። እምነትህ ብዙም ሳይቆይ ይበረታል፤ የሚንበለበሉትም ፍላጻዎች በአንተ ላይ ያላቸው ኃይል ይቀንሳል።

ገጽ 1 / 1 · 6 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል