ምዕራፍ 6 · 6 ደቂቃ ንባብ
አሳዛኙ እውነት
የእግዚአብሔር ፍላጎትና በኢየሱስ ልብ ውስጥ ያለው ቀዳሚ ነገር፣ እርስ በርሳቸው ያላቸው ፍቅርና የአገልጋይነት መንፈሳቸው ለዚህ ዓለም እንዲህ ያለ ምስክር የሚሆን ሕዝብ እንዲኖረው ነው፤ ይኸውም ወንዶችና ሴቶች ጌታችንን ለማወቅ እስኪጮኹ ድረስ ነው። የሰላማችንን፣ የደስታችንንና የስምምነታችንን ምሥጢር ማወቅ ይፈልጋሉ። ትዳሮቻችንን፣ ቤቶቻችንን፣ ልጆቻችንንና የሥራ ቦታዎቻችንን የሚመለከቱት ለመንቀፍ ሳይሆን ምሥጢራችንን ለማወቅ ይሆናል።
ጳውሎስ አንባቢዎቹን «መንፈስ ይሙላባችሁ» ብሎ ከመከረና እንዲህ የመሞላትን አንዱን ማስረጃ «ለእያንዳንዳችሁ በክርስቶስ ፍርሃት የተገዛችሁ» መሆን እንደ ሆነ ከገለጸ በኋላ (ኤፌሶን 5:21)፣ ይህ በግንኙነቶቻችን ውስጥ እንዴት መሆን እንዳለበት ምሳሌዎችን ይሰጣል።
ክርስቲያናዊ ጋብቻ → ኤፌሶን 5:22-33
ክርስቲያናዊ ትዳሮች መሆን እንደሚገባቸው ቢሆኑ፣ ሁለቱም ወገኖች በመንፈስ ተሞልተው እርስ በርሳቸው ቢገዙ፣ ቢከባበሩና አንዱ ሌላውን ቢያስቀድም፣ ለሚመለከተው ዓለም የተገለጠ ምሥጢር በሆኑ ነበር። ሰዎች ኢየሱስ ከሙሽራው ከቤተ ክርስቲያን ጋር ያለውን ግንኙነት ባዩ ነበር፤ እርሱንም ለትዳራቸው ደግሞ መሠረት አድርገው ሊያውቁት በተሳቡ ነበር። አሁን እንደሚያደርጉት ወደ ፍቺ ፍርድ ቤቶች ከመሯሯጥ ይልቅ፣ የሚፈልጉ ሰዎች ወደ ቤታችን ወይም ወደ ቤተ ክርስቲያናችን በር የማያቋርጥ መንገድ በሠሩ ነበር!
ሴቶች ከሚቀበሉት ፍቅር የተነሣ ባሎቻቸውን ከሌሎች ወንዶች ሁሉ በላይ ሊያከብሩ ይወዳሉ፤ ወንዶችም ከሚቀበሉት ክብር የተነሣ ሚስቶቻቸውን ሊወዱ ይወዳሉ።
በዓለም ውስጥ እጅግ የተለመደው የመበደልና የብቀላ አስከፊ አዙሪት ፈንታ፣ በክርስቶስ እርስ በርስ የመባረክ አስደሳች አዙሪት በኖረ ነበር።
በክርስቲያን አማኞች መካከል ፍቺ እንዲህ የተለመደ መሆኑ እጅግ አሳዛኝ ነው። ይህ ምን ዓይነት ምስክርነት ነው?
ክርስቲያናዊ ቤት → ኤፌሶን 6:1-4
ወላጆች ከጌታና እርስ በርሳቸው ትክክለኛ ግንኙነት ባላቸው ቤት ውስጥ ልጆቻቸው አስተማማኝና ፍቅር በሞላበት ቤት ውስጥ ይጎለምሳሉ። እንደ ፓስተር ከማደርገው የምክር አገልግሎት አብዛኛው፣ በዚህ በጣም በተለየ ሁኔታ ውስጥ ባደጉ ልጆች ከደረሰባቸው ቊስል ጋር የተያያዘ ነው፤ ብዙውን ጊዜ ደግሞ «ክርስቲያን» የሆኑ አባቶች ልጆቻቸውን ደቀ መዛሙርት ማድረግ (ወይም መገሠጽ) ተስኗቸው ይልቁንም ያበሳጯቸዋል (ቆላስይስ 3:21)።
ዛሬ ክርስቲያን አማካሪዎች ስለ ተዛቡ ቤተሰቦች ይናገራሉ፤ በእነዚህ ቤተሰቦች ውስጥ የተዛቡት ወላጆች ያንን ፍቅር መስጠት ስለማይችሉ የልጁ «የፍቅር ማጠራቀሚያ» ሊቀበለው በተፈጠረበት ፍቅር አይሞላም። ልጁ ፍሬው ዋስትና፣ ማንነት፣ ለራስ ክብር መስጠት፣ ተቀባይነትና መበረታታት የሆነውን ፍቅር አይለማመድም። ልጁ ፍሬው ዋስትና፣ ማንነት፣ ለራስ ክብር መስጠት፣ ተቀባይነትና መበረታታት የሆነውን ፍቅር አይለማመድም።
በስሜትም በመንፈስም ጤናማ ሆነው ከማደግ ይልቅ ልክ እንደ ወላጆቻቸው የተዛቡ ይሆናሉ። ትከሻው በጎበጠና ልቡ በተሰበረ ዓለም ውስጥ ቀና ብለው መመላለስን ከቶ አይማሩም። በፍቅር ማጠራቀሚያቸው ውስጥ ያለው ባዶ ስፍራ በአንድ ነገር ይሞላል፤ ይኸውም በቁጣ ነው፤ ቁጣም በእግዚአብሔር ዓላማዎች ላይ የማመፅ ሕይወትን ያስከትላል። እንዲህ ያሉት ልጆች በጌታ ለወላጆቻቸው መታዘዝን ከቶ አይማሩም።
«አባቶች ሆይ፥ ልባቸው እንዳይዝል ልጆቻችሁን አታበሳጩአቸው» (ቆላስይስ 3:21)።
እጅግ ብዙ ዓመፀኛ ልጆች የ«ክርስቲያን» ቤቶች ውጤት መሆናቸው እጅግ አሳዛኝ ነው። ይህ ምን ዓይነት ምስክርነት ነው?
የሥራ ቦታ → ኤፌሶን 6:5-9
በመንፈስ የተሞላ አማኝ በሥራ ባልደረቦቹና በአሠሪዎቹ ፊት የአገልጋይን መንፈስ በማሳየት በሥራ ቦታው ምስክር እንዲሆን ተጠርቷል፤ ሥራውንም በሚገባ ለመሥራት የሚታመን ሊሆን ይገባዋል።
በአንድ ትልቅ መልሶ ማደራጀት ትምህርት ቤቱ ከሌሎች ሁለት ትምህርት ቤቶች ጋር ሊዋሃድ የነበረ አንድ መምህር አውቃለሁ። ከሦስቱ ትምህርት ቤቶች የመጡት መምህራን ሁሉ በመምህራኑ ስም ለትምህርት ቤቶቹ የአስተዳደር ቦርድ የሚናገር፣ ስለ አዲሶቹ የትምህርት ቤት ሕንጻዎች ንድፍና ስለ ቅጥር ውላቸው ፍላጎታቸውን የሚገልጽ የሠራተኞች ማኅበር ለማቋቋም ተሰበሰቡ።
ለዚህ አዲስ ማኅበር ፕሬዚዳንትነት አንድ ሰው በዕጩነት ቀረበ፤ ድጋፍም አገኘ። ሌላም ሰው በዕጩነት ቀርቦ ድጋፍ አገኘ። ከዚያም እጅግ በሚያስገርመው ሁኔታ ወዳጄ በዕጩነት ቀረበ። ወዲያውኑ በዕጩነት ቀርበው የነበሩት ሁለቱ ሰዎች የወዳጄን ዕጩነት ለመደገፍ ስማቸውን አነሡ። ሌላ ስም አልቀረበም፤ እርሱም ሠራተኞቹን ሁሉ እንዲወክል በሙሉ ድምፅ ተመረጠ። ከክፍሉ ሲወጣ ለአንድ የሥራ ባልደረባው መገረሙን ገለጸለት። «ለባለቤቴ እስክነግራት ድረስ ብቻ ቆይ» አለ፤ «ፈጽሞ አታምነኝም!» ባልደረባውም «ለምን አታምንህም?» ብሎ መለሰለት፤ «ሁልጊዜ እውነትን እንደሚናገር የምንተማመንበት አንተ ብቻ እንደ ሆንክ ሁላችንም እናውቃለን!»
ወዳጄ በእነዚያ ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ ሠራተኞች መካከል ብቸኛው ክርስቲያን ነበር።
የሚያሳዝነው፣ ከነጋዴዎች (ከእነርሱም መካከል ክርስቲያኖች አሉ) ጋር ለመነገድ ከሁሉ የከፉት ሰዎች ክርስቲያኖች እንደ ሆኑ ብዙ ጊዜ ይነግሩኛል።
በትንሹ ክፍያ ከአንተ ብዙውን ማግኘት ይፈልጋሉ። ጉርሻ በመስጠት ከሁሉ ደካሞች ናቸው፤ ብዙውን ጊዜም ዕዳ በመክፈል የመጨረሻዎቹ ናቸው! በእርግጥ ዓለም ከማያምኑ ሰዎች ይልቅ በእኛ ላይ አጥብቆ ይፈርድ ይሆናል፤ ይህ ግን የሚጠበቅ ነው!
የአገልጋዮች መንፈስ እንዲኖረን ተጠርተናል። ከዓለም በላቀ የቁርጠኝነትና የሥራ ጥራት ደረጃ ልንኖር ይገባናል! የሚያሳዝነው፣ በመንፈስ የተሞላ የሥራ ሥነ ምግባር ወይም ከባልደረቦቻቸው ጋር እንዲህ ያለ ግንኙነት የማያሳዩ ክርስቲያን አሠሪዎችንና ሠራተኞችን ሁላችንም እናውቃለን። ይህ ምን ዓይነት ምስክርነት ነው?
የአገልጋዮች መመናመን
አግባብነት ያላቸው ጥናቶች አብዛኞቹ እንደሚያሳዩት ሚስዮናውያን የአገልግሎት መስካቸውን ለቀው የሚሄዱበት ቀዳሚው ምክንያት በሰዎች መካከል ያለው ደካማ ግንኙነት ነው! በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤቶችና በቋንቋ ማሠልጠኛዎች ለብዙ ዓመታት ተምረዋል፣ በአገራቸው አብያተ ክርስቲያናት በልምምድ አገልግለዋል፣ ከሕይወታቸው ትልቁን ክፍል ለዝግጅት አውለዋል፤ ከአንድ የባሕር ማዶ የአገልግሎት ዘመን በኋላ ግን መራራ ሆነው፣ ተስፋ ቆርጠው፣ አፍረውና ቆስለው ወደ አገራቸው ተመልሰዋል። ይህ ሊሆን አይገባም!
በሰሜን አሜሪካ አንድ ፓስተር በአንዲት የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የሚያገለግልበት አማካይ ጊዜ ከአምስት ዓመት ያነሰ ነው። የመጀመሪያው ዓመት የጫጉላ ጊዜ ነው፤ ሁለተኛው የመላመድ። በሦስተኛው ዓመት በቅሬታ ጉርምርምታ የታጀበ ተስፋ መቁረጥ ይገባል፤ ፓስተሩም የቤተ ክርስቲያኑ አባላትም አንዳቸው ከሌላው ያልተፈጸሙ ተስፋዎች አሏቸው።
በአራተኛው ዓመት ቅሬታው ብዙውን ጊዜ በምሬትና በክስ ታጅቦ ወደ ላይ ይወጣል። ሰዎች ጎራ ይለያሉ፣ ብዙ ግለት ይፈጠራል፤ ፓስተሩም ብዙውን ጊዜ «ይህን መታገሥ የለብኝም!» እያለ ይሄዳል። ይህ ምን ዓይነት ምስክርነት ነው?
የቤተ ክርስቲያን ጠብ
በቤተ ክርስቲያን ጠብ ውስጥ ተሳትፈህ ታውቃለህ? ደስ የሚያሰኝ ነገር አይደለም! በአንድ ወቅት ከሦስት መቶ በላይ ሰዎች የነበሯት፣ አሁን ግን ፈጽሞ የሌለች አንዲት ቤተ ክርስቲያን አውቃለሁ። በዚያች ከተማ ያለ ሰው ሁሉ የታሪኩን አንዱን ገጽታ የሚያውቅ ይመስላል፤ በአንድ ወቅት በታማኝነት ይመላለሱ የነበሩ ብዙ ሰዎችም ዳግመኛ ወደ ቤተ ክርስቲያን እንደማይሄዱ ይናገራሉ!
ጠቡ መራራ ስለ ነበረ ቊስሎቹ እውነተኛ ናቸው። አማኞች እርስ በርሳቸው «ጥይት» እየተተኳኮሱ አንዱ ሌላውን ይገድሉ ነበር፤ ድምፁም በከተማይቱ ሁሉ አስተጋባ። ሰይጣን በደስታ ፈነጠዘ፤ ጌታ ግን አለቀሰ!
በእርግጥ አብዛኛው ጠባችን በቤት ውስጥ የተያዘ ነው ወይም ይበልጥ ስውር ነው። በቤተ ክርስቲያናቸው ወይም በቤተ ክርስቲያን ድርጅታቸው ላይ ቅሬታ ላላቸው ፓስተሮች የድጋፍ ቡድኖችን ስለሚያቋቁሙ የአገልጋዮች ቡድን የሚናገር አንድ የሚያስገርም የጋዜጣ ጽሑፍ አነበብሁ። ጽሑፉ በአንድ ቤተ እምነት ውስጥ «ብዙ ገንዘብ ለማግኘት ክስ ስለመሠረቱ» አገልጋዮች ተናገረ፤ ቀጥሎም ነጋዴዎች በሠራተኞቻቸው ላይ ከሚጨክኑት ይልቅ አብያተ ክርስቲያናት በፓስተሮቻቸው ላይ እጅግ እንደሚጨክኑ፣ ከሁሉም ይበልጥ ጨካኞቹ ደግሞ በወንጌላውያን ወግ ውስጥ ያሉት እንደ ሆኑ ጨመረ («ክሪስቺያን ዊክ» (ካናዳ)፣ ጁን 21 ቀን 94)።
እኛ ብዙ ሰዎችን ወደ ቤተ ክርስቲያናችን ለማምጣት በሚደረገው ፉክክር እንዴት እርስ በርሳችን እንደምንፎካከር ለማየት በአካባቢህ ጋዜጣ ላይ የቅዳሜ ምሽቱን የአብያተ ክርስቲያናት ማስታወቂያዎች ተመልከት፤ ብዙውን ጊዜ ሰዎቹ የሚመጡት ከሌላ ቤተ ክርስቲያን ነው! የአብያተ ክርስቲያናት እድገት አብዛኛው በመለወጥ የመጣ ሳይሆን ከሌላ ቤተ ክርስቲያን በመዛወር የመጣ እንደ ሆነ በሚገባ ተመዝግቧል። የግል ገጠመኞች የሚመከሩ አይደሉም፤ ነገር ግን በአንድ ወቅት ሊነገር የሚገባው አስደሳች ተሞክሮ አጋጥሞኝ ነበር።
የዩኒቨርሲቲው የትምህርት ዓመት ገና መጀመሩ ነበር፤ የአካባቢው ፓስተሮች ሁሉ ከተማሪዎቹ ጋር ተገናኝተው ስለ አብያተ ክርስቲያኖቻችን እንድንነግራቸው ተጋበዝን። እያንዳንዳችን ራሳችንን ለማስተዋወቅ ሁለት ሁለት ደቂቃ ተሰጠን።
ፓስተሮች አንዱ ከሌላው ተከትለው የአብያተ ክርስቲያኖቻቸውን መልካምነት ሲያወድሱ አዳመጥሁ። «ግሩም የሆነ ‹የኮሌጅና የሙያ ቡድን› አለን፤ እናንተንም የሚወስድ አውቶቡሳችንን ልንልክ እንችላለን።» «ሙዚቃችን በእርግጥ ያስደስታችኋል፤ ልክ ወጣቶች እንደሚወዱት ፈጣንና ሕያው ነው!»
«አብዛኞቹ አብረዋችሁ የሚማሩ ተማሪዎች ወደ ቤተ ክርስቲያናችን ይመጣሉ፤ ከግቢው አቅራቢያ እንገኛለንና።» በተራው ውስጥ እኔ በግምት 30ኛው ፓስተር ነበርሁ፤ የማገለግለውም ትንሽና እየታገለች ያለች አገልግሎትን ነበር። በቆምሁ ጊዜ ለተማሪዎቹ ምንም ልዩ ፕሮግራም የሌለን ትንሽ ቤተ ክርስቲያን እንደ ሆንን ነገርኋቸው። ሰፈራችንን ለክርስቶስ እንድንደርስ ሊረዱን ቢፈልጉ ከሥራ በቀር የምናቀርብላቸው ምንም ነገር አልነበረንም።
ተቀመጥሁ፤ ተማሪዎቹም አጨበጨቡ!
ቤተ ክርስቲያኗ እያደገች ስትሄድ ከምእመናኖቻችን ብዛት ያላቸው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሆኑ። ሁላችንም የምናገለግለው ያንኑ ታላቁን እረኛ ሆኖ ሳለ፣ ለበጎቹ እርስ በርሳችን ለምን እንፎካከራለን? ይህ ምን ዓይነት ምስክርነት ነው?
እርስ በርሳችን መከባበር፣ መዋደድና መገልገል ለምን እንዲህ ይከብደናል? ስለ መንፈስ ሙላት እየተናገርን በዚያው ጊዜ እንቅፋት የሚሆነን ትዕቢታችን ብቻ ነውን? ወይስ በውጊያ ውስጥ እንዳለንና ጠላትም እጅግ ተንኰለኛ እንደ ሆነ በቀላሉ አናውቅም?
ይህን እርግጠኛ ሁን! ለቃሉ በመታዘዝ እርስ በርሳቸው ትክክለኛ ግንኙነት ያላቸው ሕዝብ እንዲኖረው የጌታ ቀዳሚ ነገር ከሆነ፣ እንዲህ ያሉትን ግንኙነቶች ማበላሸት በእርግጥ የሰይጣን ቀዳሚ ነገር ነው! «ከፋፍለህ ግዛ» መፈክሩ ቢሆን አያስገርምም።
ምዕራፍ 6 ተጠናቋል
አሳዛኙ እውነት