ምዕራፍ 5 · 5 ደቂቃ ንባብ
የክርስቶስ አካል
አንድ አካል
«እንዲሁ ብዙዎች ስንሆን በክርስቶስ አንድ አካል ነን፥ እርስ በርሳችንም እያንዳንዳችን የሌላው ብልቶች ነን» (ሮሜ 12:5)።
ሐዋርያው ጳውሎስ፣ እርስ በርስ በመገልገልና በመዋደድ የሚጠየቀው ግንኙነት ከሁሉ በተሻለ የሚታየው በሕያው አካል ምሳሌ መሆኑን ሊያስተምረን የጌታን የሰገነቱን ጸሎት ጭብጥ ያነሣል። ቤተ ክርስቲያንን በእግዚአብሔር የተመሠረተች ሕያው የክርስቶስ አካል አድርጎ ይመለከታታል። እርሷ ሰው ሠራሽ ድርጅት ሳትሆን እግዚአብሔር የሠራት ሕያው አካል ናት፤ ሕያውና ሕይወት ያለው እውነታ ናት። እርሷ የመገልገልና የመዋደድ ማሠልጠኛና መለማመጃ ሜዳ ናት። ክርስቲያናዊ ኅብረት እጅግ አስፈላጊ የሆነውም ስለዚህ ነው።
በአሥራ ስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረው የአንግሊካን ቄስ ጆን ደን እንዲህ ሲል ጻፈ፦ «ማንም ሰው ለብቻው ሙሉ የሆነ ደሴት አይደለም፤ እያንዳንዱ ሰው የአህጉሩ ቁራጭ፣ የዋናው ምድር ክፍል ነው። አንዲት የአፈር ጓል በባሕር ብትወሰድ፣ አንድ የባሕር ዳርቻ ጫፍ ወይም የወዳጅህ ወይም የራስህ ርስት ቢወሰድ እንደሚሆነው ሁሉ አውሮፓ ታንሳለች፤ የማንኛውም ሰው ሞት እኔን ያጎድለኛል፤ እኔ የሰው ልጆች ክፍል ነኝና፤ ስለዚህ ደወሉ ለማን እንደሚደወል ለማወቅ ከቶ አትላክ፤ የሚደወለው ለአንተ ነው።»
የእርሱ ስሜት ከዚያ አካል ሌሎች ክፍሎች ሁሉ ጋር እርስ በርስ መደጋገፉን የሚያውቅ የክርስቶስ አካል ብልት ስሜት ሊሆን ይችላል።
እስልምና መሐመድ ኢየሱስ ሊፈጽመው ያልቻለውን ለመፈጸም በእግዚአብሔር እንደ ተጠራ ያስተምራል! ሙስሊሞች ኢየሱስን ከመሐመድ ቀጥሎ ሁለተኛ የሆነ ታላቅ ነቢይ አድርገው ይቀበሉታል፤ ነገር ግን ሰዎችን ሁሉ አንድ ሕዝብ ማድረግ ስላልቻለ እንደ ወደቀ ያምናሉ። እስልምና የአሕዛብን ሁሉ ሕዝቦች እንደ ሙስሊሞች አንድ እንዲሆኑ ይጠራል። ኢየሱስ ሊያመጣው የመጣው አንድነት የዚህ ዓለም ሳይሆን የመንግሥቱ አባላት ለሆኑት መሆኑን አላስተዋሉም። በዚያ መንግሥት ውስጥ እንዲህ ያለ ግልጽ አለመስማማት መኖሩ እንዴት ያሳዝናል! እስልምና በፍጥነት ማደጉ ምንም አያስደንቅም!
በመለወጣችን፣ ማለትም ዳግመኛ በመወለዳችን ጊዜ፣ «ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናል» (1ኛ ቆሮንቶስ 12:13)። ይህ ባፕቲስቶችን፣ አንግሊካኖችን፣ ጴንጤቆስጤዎችንና አንተ የምትገኝበትን ማንኛውንም ቡድን ይጨምራል። ቤተ እምነቶቹን ሳይሆን፣ በእነዚህ ቡድኖች ሁሉ ውስጥ ያሉትን፣ ጌታን እንደ ግል አዳኛቸው የሚያውቁትንና ኃጢአታቸው በቀራንዮ በተፈጸመው ሥራ ይቅር እንደ ተባለ የሚያውቁትን ግለሰቦች ማለት ነው። ወደ አካሉ የሚደረገው ጥምቀት ደቀ መዛሙርቱ በበዓለ ኀምሳ ቀን፣ ከዚያም ቀን ወዲህ ብዙዎች ከተለማመዱት ወደ መንፈሱ ከሚደረገው ጥምቀት ጋር መምታታት የለበትም። የመጀመሪያው «በመንፈስ ወደ አካሉ» ሲሆን ሁለተኛው ግን «በጌታ ኢየሱስ ወደ መንፈሱ» ነው (ሉቃስ 3:16)። ለመጽደቅ «በክርስቶስ» መሆን አለብን፤ ለመቀደስ ደግሞ ክርስቶስ «በእኛ» መሆን አለበት።
የመንፈስ ሙላት
በአካሉ ውስጥ ካሉት ዋና ዋና መከፋፈሎች አንዱ ስለዚህ የመንፈስ ጥምቀት በሚነገሩት ልዩ ልዩ ትምህርቶች ምክንያት የመጣ ነው።
በልሳን መናገር በመንፈስ የመሞላት የመጀመሪያ ማስረጃ ነውን? ከቶ ማስረጃ ነውን? የትኛውንም አመለካከት ብንይዝ አለመስማማታችንን የመከፋፈል ምክንያት ልናደርገው አይገባም ከማለት በቀር ወደዚያ ክርክር አልገባም፤ እንዲያ ካደረግን በእርግጥ የትኛውንም የመንፈስ ቅዱስ ሙላት እውነታ እያሳየን አይደለንም!
እርሱ የሚመጣው የክርስቶስን ሕልውናና ፈቃዱን እውን ሊያደርግልን ነው። ወደ እውነት ይመራናል። ጳውሎስ «መንፈስ ይሙላባችሁ» (ኤፌሶን 5:18) ብሎ ሲመክረን፣ እንዲህ በመንፈስ የተሞላ ሕይወት ሦስት ማስረጃዎችን አከታትሎ መስጠቱ በጣም ያስገርመኛል፦ 1. የአምልኮ መንፈስ፤ በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ እርስ በርሳችሁ ተነጋገሩ፤ ለጌታ በልባችሁ ተቀኙና ዘምሩ፤ (ኤፌሶን 5:19)።
2. የምስጋና መንፈስ፤ ሁልጊዜ ስለ ሁሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አምላካችንንና አባታችንን ስለ ሁሉ አመስግኑ (ኤፌሶን 5:20)።
3. የአገልጋይነት መንፈስ፤ ለእያንዳንዳችሁ በክርስቶስ ፍርሃት የተገዛችሁ ሁኑ (ኤፌሶን 5:21)።
እነዚህ ሦስቱ በሕይወትህ ውስጥ ግልጽ ሆነው የማይታዩ ከሆነ በመንፈስ የተሞላህ ክርስቲያን እንደ ሆንክ አትንገረኝ!
ከዚያም ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች በጻፈው መልእክት ይህ ሦስተኛው ማስረጃ በግንኙነቶቻችን ውስጥ እንዴት እንደሚተገበር ያሳያል፤ በባልና በሚስት፣ በልጆችና በወላጆች፣ በሠራተኞችና በጌቶች መካከል (ኤፌሶን 5:22-6:9)።
የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን
ቤተ እምነቶችን በራሳቸው ክፉ አድርገው ከሚቆጥሩት ወገን አይደለሁም። ጌታ አብዛኞቹን ያቋቋማቸው በባሕርይና በእምነት አቋም እኛን ከሚመስሉ ሰዎች ጋር በአንድ ቡድን ውስጥ ሆነን እንደ አማኞች እንድንጎለምስ ለማስቻል እንደ ሆነ አምናለሁ፤ ነገር ግን ቡድኖቻችን በአምልኮ ስልት፣ በቅዱሳት መጻሕፍት አተረጓጎምና በሚያጐሉአቸው ነገሮች ሐሳባችንን ከማይጋሩት በክርስቶስ አካል ውስጥ ካሉ ሰዎች እንድንለያይ ሲያደርጉን፣ በራሳችን ላይ ፍርድ የማምጣት አደጋ ላይ ነን። እርስ በርሳችን ላንዋደድ እንችላለን፤ ነገር ግን እርስ በርሳችን እንድንዋደድ ታዝዘናል!
ሐዋርያው ስለ ክርስቶስ አካል ያለውን ማስተዋል የሚዘረዝርባቸው ሦስት ዋና ዋና የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍሎች አሉ።
1. ኤፌሶን 4:1-16 → ትሕትናን፣ የዋህነትን፣ ትዕግሥትንና ፍቅርን እያሳየን፣ በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅም እየተጋን ለጥሪያችን እንደሚገባ እንድንመላለስ እንመከራለን። «አንድ አካል» አለ ብሎ ያውጃልና (ኤፌሶን 4:4)። በመቀጠልም በቁጥር ሰባት ለዚያ አካል ስለ ተሰጡት ስለ አንዳንድ የጸጋ ስጦታዎች ይጽፋል። እነርሱም «ቅዱሳንን ለአገልግሎት ሥራ ፍጹማን ለማድረግ… ወደ ሙሉ ሰውነት» (ኤፌሶን 4:13) የተሰጡ የሐዋርያት፣ የነቢያት፣ የወንጌል ሰባኪዎች፣ የእረኞችና የአስተማሪዎች የአገልግሎት ስጦታዎች ናቸው።
2. ሮሜ 12:1-8 → አእምሯችን ታድሶ ራሳችንን ሕያው መሥዋዕት አድርገን እንድናቀርብ በድጋሚ እንመከራለን። የአካሉ ብልቶች ሁሉ አንድ ዓይነት ሥራ የላቸውም፤ ነገር ግን ሁላችንም እርስ በርሳችን እንደጋገፋለን። እርስ በርሳችን የምንገለገልባቸው ልዩ ልዩ የጸጋ ስጦታዎች አሉን (ሮሜ 12:6)።
ስለዚህ እንዲህ ልናደርግ ይገባናል፦ «ፍቅራችሁ ያለ ግብዝነት ይሁን። ክፉውን ነገር ተጸየፉት፤ ከበጎ ነገር ጋር ተባበሩ፤ በወንድማማች መዋደድ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ፤ እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ፤» (ሮሜ 12:9-10)።
3. 1ኛ ቆሮንቶስ 12-14 → ምዕራፍ 12ንና 14ን ከዚያ ታላቅ የፍቅር ምዕራፍ ከምዕራፍ 13 መለየት አንችልም! የመጀመሪያው ምዕራፍ ስለ አካሉ ትምህርትና ለዚያ አካል ስለ ተሰጡት «ካሪዝማታ» (የጸጋ ስጦታዎች) ይናገራል። እነዚህ የጸጋ ስጦታዎች የሚሰጡት ለግለሰቡ እንደ ሆነ ልብ በል፤ ለራሱ ጥቅም ሳይሆን ለመላው አካል ጥቅም ነው!
ከዚያም ጳውሎስ አንዱ የአካል ክፍል ሌሎቹን ክፍሎች እንደማያስፈልጉት መናገሩ ምን ያህል ሞኝነት እንደ ሆነ በማሳየት ስለ አካሉ ያለውን ትምህርት ያሰፋል! ዓይን እጅን «አታስፈልገኝም» ወይም ደግሞ ራስ እግሮችን «አታስፈልጉኝም» ሊል አይችልም (1ኛ ቆሮንቶስ 12:21)። እርስ በርሳችን እንፈላለጋለን!
በዚህ ምዕራፍ መጨረሻ በኤፌሶንና በሮሜ የመዘገባቸውን የጸጋ ስጦታዎች ዝርዝሮች አሰባስቦ ሁሉም በረጅሙ የካሪዝማታ ዝርዝሩ ውስጥ እንደሚገኙ ያሳያል።
እንዲህ ያሉት ስጦታዎች በፍቅር (1ኛ ቆሮንቶስ 13) እና በአግባቡ በሥርዓት (1ኛ ቆሮንቶስ 14) ካልተሠራባቸው በቀር ጥቅማቸው አነስተኛ ነው።
በክርስቶስ አካል ውስጥ ሙሉ በሙሉ ድርሻህን እየተወጣህ ነውን? ሌሎችን እያገለገልህ፣ ሌሎችን እየወደድህና ለቃሉ እየታዘዝህ በአንዲት የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሥር ሰድደሃልን? አገልግሎትህ ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የሰፋ ከሆነ፣ መሪዎችን ለመሾምና የዚያው የአካሉ የአጥቢያ መገለጫ አባል ሆነህ ለእነርሱ ተጠያቂ ለመሆን ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት አለህን?
አንዳንዶች ወደ ውጭ የሚዘረጋ ክንድ፣ ሌሎች ደግሞ ለዚህ ዓለም የሚናገር ድምፅ ለመሆን ይሹ ይሆናል፤ እኔ ግን ብዙ ጊዜ ራሴን ከትልቅ የእግር ጣት የበለጠ ምንም ማራኪነት እንደሌለው አድርጌ እመለከታለሁ! ቀድሞ ፓስተር እንደ መሆኔ ብዙ ጊዜ በጨለማና በሚሸቱ ስፍራዎች እሠራ ነበር፤ በጫና ውስጥ ሆኜ የሰዎችን ችግሮች እፈታ ነበር (በጣቶች መካከል ያለው አሸዋ)።
ይሁን እንጂ እንዳገለግል ስጠየቅ ለአካሉ ሚዛን የማምጣት ዕድል ስለማገኝ እንደ ተከበርሁ ይሰማኛል። በእርግጥም የትልቁ የእግር ጣት ዋና ሥራ ይኸው ነው!
ምዕራፍ 5 ተጠናቋል
የክርስቶስ አካል