ምዕራፍ 4 · 5 ደቂቃ ንባብ
የቃል ኪዳን ሕዝብ
የአጋፔ ማዕድ
«ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ አመሰገነ፥ ቆርሶም ‹እንካችሁ ብሉ፤ ይህ ስለ እናንተ የሚሆን ሥጋዬ ነው› አለ»
(1ኛ ቆሮንቶስ 11:23-24)። ሁሉም እንዲሁ አደረጉ፤ ይህንንም በማድረጋቸው ራሳቸውን ከክርስቶስ አካል ጋር አንድ አደረጉ።
«እንደዚሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን ደግሞ አንሥቶ ‹ይህ ጽዋ በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው፤ በጠጣችሁት ጊዜ ሁሉ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት› አለ» (1ኛ ቆሮንቶስ 11:25-26)። ይህን በተናገረ ጊዜ በዚያ ከነበሩት አንዳቸውም ምን ማለቱ እንደ ሆነ አለመጠየቃቸው ያስደንቀኛል። ሁሉም እንደ ተረዱት ብቻ ነው መገመት የምችለው።
ቃል ኪዳን በሁለት ወገኖች መካከል የሚደረግ ስምምነት ነው። «ይህን ለእኔ አድርግልኝ፤ እኔም ያንን አደርግልሃለሁ!» ዛሬ ሰዎች ቃል ኪዳን ሲገቡ በጽሑፍ በሰፈረው ስምምነት ላይ የተፈረሙ ፊርማዎች ማስረጃ ሆነው መገኘታቸው የግድ ነው። የሚያሳዝነው፣ የጨዋ ሰው ቃል ከእንግዲህ ተቀባይነት የለውም። በኢየሱስ ዘመን ቃል ኪዳን የሚጸናው በጋራ በሚጠጣ መጠጥ ነበር። በቅርብ ዘመን በሰሜን አሜሪካ ቀደምት ነዋሪዎችና በአፍሪካ ነገዶች መካከል እንደ ነበረው ደም አልነበረም፤ ምንም እንኳ በብሉይ ኪዳን ዘመን የነበሩት ቃል ኪዳኖች ሁሉ የመሥዋዕት እንስሳ በማረድ ደም በማፍሰስ የሚገለጡ ቢሆኑም። በእርግጥም ሰው ቃል ኪዳን «ያደርጋል» ከማለት ይልቅ ቃል ኪዳን «ይቆርጣል» ይባል ነበር።
በአፍሪካ ፈር ቀዳጅ ስለ ነበረው ታላቁ ሚስዮናዊ ስለ ዶክተር ሊቪንግስተን አንድ አስደሳች ታሪክ ይነገራል። እርሱ ከመሪዎቹና ከተሸካሚዎቹ ጋር «በጨለማዋ አህጉር» ውስጥ ሲጓዙ ብዙ ጊዜ በጦረኛ ነገዶች ይማረኩ ነበር።
በአንድ ወቅት ምርኮኞቹ በጠላትነት በተነሣ አንድ አለቃ ፊት ቀረቡ፤ አለቃውም ግዛቱን ጥሰው ስለ ገቡ ይወቅሳቸው ጀመር። በሊቪንግስተን ዝምታ ቁጣው እየጨመረ ሲሄድ፣ ከመሪዎቹ አንዱ ወደ ሚስዮናዊው ዘንበል ብሎ «ቃል ኪዳን እንዲቆርጥ» አጥብቆ መከረው። ሊቪንግስተን የተጠየቀውን አልተረዳም ነበር፤ ነገር ግን ክርስቲያን አገልጋዩና ከጠላት ነገድ የተመረጠ አንድ ወጣት ለእርሱ አረማዊ ሥርዓት የሆነውን ነገር ሲፈጽሙ ሲመለከት ወዲያው በድንጋጤ ወደ ኋላ አፈገፈገ። በክንዳቸው ላይ ትንሽ ቆርጠው ደሙን በሳህን አጠራቀሙና አብረው ጠጡት!
ከዚያም አለቃው ወደ ፊት ቀርቦ ሊቪንግስተን የሚመራበትን፣ እጅግ የሚወደውን ወተት የሚያገኝበትን የፍየሉን ገመድ ያዘ። ሊቪንግስተን ደነገጠ፤ ከዚያም አለቃው ጥሰው የገቡትን ሰዎች ሊቀበል የወጣበትን ጫፉ በመዳብ የተለበጠ በትሩን በስጦታ በእጁ ሲያስይዘው ተገረመ። ከዚያም ከማራኪዎቻቸው ምግብ ከተቀበሉ በኋላ የሚያድሩበት ጎጆ ውስጥ ተወሰዱ።
ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሊቪንግስተን በሌላ የአፍሪካ ክፍል ሲጓዝ እንደገና ተማርኮ በጠላትነት በተነሣ በሌላ አለቃ ፊት ቀረበ። በዚህ ጊዜ ግን አለቃው በሚስዮናዊው ፊት በጉልበቱ ተንበረከከ። ማስተዋል የመጣው ያን ጊዜ ብቻ ነበር። ወጣቱ መሪ ስለ ሊቪንግስተን «ቃል ኪዳኑን በቆረጠ» ጊዜና ደሙን በመጠጣት ባጸናው ጊዜ፣ በእነርሱና በነገዱ መካከል፣ በተለይም በሊቪንግስተንና በአለቃው መካከል ስምምነት ተደርጎ ነበር።
አለቃው ለዚያ የቃል ኪዳን ስምምነት ምልክት እንዲሆን የቁርጠኝነቱና የድጋፉ ምልክት የሆነውን በትሩን ሰጥቶ ነበር። ሁለተኛው የጠላት አለቃ በትሩን አውቆት ነበር፤ ሊቪንግስተን የደም ወንድም እንዳለው ተረድቶ ለዚያ ለሚበልጥ ኃይልና ሥልጣን ተገዝቶ ነበር።
ኢየሱስ እንዲህ ያለውን ቃል ኪዳን ከእኛ ጋር አድርጓል! አሁን በዚህ ሽባ በሆነ ዓለም ውስጥ በእርሱ ሥልጣን ቀና ብለን መመላለስ እንችላለን! ደሙን ያፈሰሰ፣ ስለ እኛ ጽዋውን እስከ መራራው አተላ ድረስ የጠጣና የስሙን ሥልጣን የሰጠን የደም ወንድም አለን (የሐዋርያት ሥራ 3:16)!
ጠላታችን ሰይጣንና ተላላኪዎቹ ኃጢአትና ሞት በእኛ ላይ ሊገዙ አይገባም (ሮሜ 6:14)!
ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን «የቃል ኪዳኑን ጽዋ» እንዲጠጡ በጋበዛቸው ጊዜ፣ በአዲስ ቃል ኪዳን ውሎች መስማማታቸውን እየገለጡ እንደ ነበረ ያውቁ ነበር። በጌታ ማዕድ ምልክቶቹን በተቀበልን ቊጥር ሁሉ እንዲሁ ነው። እንጀራውን ስንበላ ራሳችንን የክርስቶስ አካል መሆናችንን እያወጅን ነው። ጽዋውን ስንጠጣ እርስ በርሳችን ልንገለገል፣ እርስ በርሳችን ልንዋደድና ለቃሉ ልንታዘዝ እንደገና ቃል ኪዳን እየገባን ነው።
ሳይገባው
ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው መልእክት እነዚህን ምልክቶች በመቀበል እጅግ እንድንጠነቀቅ ይመክረናል። የጌታን ጽዋ «ሳይገባው» ብንጠጣ የጌታን ሥጋ ባለመለየት ለራሳችን ፍርድ እንጠጣ ይሆናል። «ስለዚህ በእናንተ (በአማኞች) ዘንድ የደከሙና የታመሙ ብዙዎች አሉ» (1ኛ ቆሮንቶስ 11:30)።
በልቤ በሌላው ላይ ቂም ከያዝኩ፣ ወይም እንደ አገልጋይ፣ እንደሚወድ ወይም እየታዘዝኩ የማልኖር ከሆንኩ፣ እንጀራውንና ጽዋውን መቀበሌ ግብዝነት ነው። ሌላውን በክርስቶስ አካል ውስጥ ከእኔ ጋር አንድ እንደ ሆነ ማወቅ ተስኖኛል። ይህም ድካምና ሕመም እንዲመጣብኝ ሊያደርግ ይችላል። ይህ ከጌታ አይደለም፤ እርሱ የሕመም ምንጭ አይደለም፤ ነገር ግን ለዲያብሎስ መግቢያ ፈንታ ሰጥቼዋለሁ (2ኛ ቆሮንቶስ 2:11)፤ እርሱ ደግሞ እንዲህ ያለውን ፈንታ ለጥቅሙ እንዴት እንደሚጠቀምበት በሚገባ ያውቃል!
ለታመሙ መጸለይ
ያዕቆብ «ከእናንተ የታመመ ማንም ቢኖር የቤተ ክርስቲያንን ሽምግሌዎች ወደ እርሱ ይጥራ፤ በጌታም ስም እርሱን ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት። የእምነትም ጸሎት ድውዩን ያድናል ጌታም ያስነሣዋል፤ ኃጢአትንም ሠርቶ እንደ ሆነ ይሰረይለታል» (ያዕቆብ 5:14-15) ብሎ ሲጽፍ ምን ማለቱ እንደ ሆነ አሁን ይገባኛል።
ሽማግሌዎች ለምን መሳተፍ እንዳለባቸው ብዙ ጊዜ አስብ ነበር። ማንም ሰው መጸለይ አይችልም ነበርን? ሽማግሌዎች ከሚወዱ ወዳጆችና ከቤተሰብ የበለጠ የጸሎት ኃይል አላቸውን? አሁን ሽማግሌዎችን መጥራት ከጸሎት ኃይላቸው ጋር ሳይሆን ከሥልጣናቸው ጋር የተያያዘ ነው ብዬ አምናለሁ። ይህ ክፍል ከላይ ካየነው ከጳውሎስ ማስጠንቀቂያ ጋር መያያዝ አለበት፤ አማኞች የሚታመሙበትን ወይም የሚደክሙበትን ምክንያት የሚጠቁሙት እነዚህ ጥቅሶች ብቻ ናቸውና። በእርግጥ እኛም እንደ ማንኛውም የዓለም ሰው ለጀርሞች፣ ለበሽታዎችና ለሕመም ተጋላጮች ነን፤ ነገር ግን የጳውሎስ ማስጠንቀቂያ ለአማኞች አጥብቆ መነገር አለበት።
ሽማግሌዎቹ የአማኙ ሕመም በክርስቶስ አካል ውስጥ ላሉት ሌሎች ካለው የተሳሳተ አመለካከት ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ቢያስተውሉ፣ ያ ሰው እንዲታረቅ ለማዘዝ በቤተ ክርስቲያን ሽማግሌነታቸው ሥልጣናቸውን መጠቀም አለባቸው። ከዚያ በኋላ ብቻ ነው በጌታ ስም ዘይት (የመንፈስ ቅዱስ የበረከትና የጥበቃ ምልክት) ቀብተው ሊጸልዩለት የሚችሉት። የታመመው፣ በደለኛው፣ ይታደሳል፤ ይቅርም ይባላል።
የጌታ ጸሎት
ጌታችን የልቡን ቀዳሚ ነገሮች ለደቀ መዛሙርቱ ካስተማረ በኋላ ዓይኖቹን ወደ ሰማይ አንሥቶ አባቱን ተናገረ።
ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረችው ሌሊት የልቡን ጩኸት ለመስማት ዮሐንስ 17ን ለማንበብ ጊዜ መውሰድ ይገባል። አንድ ዋና ጭብጥ ላይ እያተኮርሁ በእነዚህ ድንቅ ቃላት ውስጥ ከአንተ ጋር ልመላለስ።
«አባት ሆይ፥ እኔ ላደርገው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ… ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን (ባሕርያትህን) ገለጥሁላቸው… ቃልህንም ጠብቀዋል። እኔ ስለ እነዚህ እለምናለሁ… የአንተ ናቸውና። እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉም። ወደ ዓለም እንደ ላክኸኝ እንዲሁ እኔ ወደ ዓለም ላክኋቸው። ስለ እነዚህም ብቻ አልለምንም፥ በቃላቸው ስለሚያምኑብኝ ደግሞ እንጂ (ይህ አንተንና እኔን ይጨምራል)። ሁሉ አንድ እንዲሆኑ… ዓለም ያምን ዘንድ። እኔም የሰጠኸኝን ክብር ሰጥቻቸዋለሁ… እኛ አንድ እንደ ሆንን አንድ ይሆኑ ዘንድ። በአንድነት ፍጹማን እንዲሆኑ፥ አንተ እንደ ላክኸኝ እኔንም እንደ ወደድኸኝ እነርሱን እንደ ወደድሃቸው ዓለም ያውቅ ዘንድ… ስምህን (ባሕርያትህን) አስታወቅኋቸው… እኔንም የወደድህባት ፍቅር በእነርሱ እንድትሆን እኔም በእነርሱ» (ዮሐንስ 17)።
የእግዚአብሔር ስም በሲና ተራራ ላይ በተገናኙ ጊዜ ለሙሴ ተገልጦ ነበር፤ ስለዚህ እርሱ «እግዚአብሔር፥ እግዚአብሔር፥ መሓሪና ሞገስ ያለው አምላክ፥ ቍጣው የዘገየ፥ ምሕረቱና እውነቱም የበዛ፥ ምሕረትን ለሺህ ትውልድ የሚጠብቅ፥ አበሳንና መተላለፍን ኃጢአትንም ይቅር የሚል» (ዘጸአት 34:6-7) መሆኑን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።
በእርግጥም ኢየሱስ እነዚህኑ ባሕርያት ላገኛቸው ሁሉ ገለጠ።
የእግዚአብሔር የወንጌል በራሪ ጽሑፍ
ከመጽሐፍ ቅዱስ አንዲት ገጽ እንኳ ወስጄ ለማያምን ወዳጄ የምሰጠው የወንጌል በራሪ ጽሑፍ አድርጌ ልጠቀምባት አልችልም። ከዮሐንስ 3 መጥቀስ ወይም የመዳንን መንገድ የሚያስረዳቸውን «የሮሜ መንገድ» መከተል እችላለሁ። «አራቱን ደረጃዎች» ወይም «የእግዚአብሔር ድንቅ የመዳን ዕቅድ»ን ልሰጣቸው እችላለሁ፤ ነገር ግን ከመጽሐፍ ቅዱስ አንዲት ገጽ ቀድጄ የወንጌል በራሪ ጽሑፍ አድርጌ ልሰጥ አልችልም።
ይሁን እንጂ የእግዚአብሔርን ቀዳሚ ነገሮች ማለትም የመዳን መንገዱን ለአማኙ ለማሳየት ሙሉ ምዕራፎችን አልፎ ተርፎም ሙሉ መጻሕፍትን መውሰድ እችላለሁ። ሕዝቡ እንደ አገልጋዮች፣ እንደሚዋደዱና እንደሚታዘዙ ሆነው በአንድነት ሲመላለሱ ዓለም እንደሚያውቅና እንደሚያምን አውጇል!
እኛ የእርሱ የወንጌል በራሪ ጽሑፍ ነን! ቅድሚያ የምንሰጣቸውን ነገሮች አስተካክለን ከእርሱ ቅድሚያዎች ጋር የምናስማማበት ጊዜ አሁን ነው! በአንዳችን ውስጥ የትምህርት ኑፋቄ ስናገኝ ለመናገር እንፈጥናለን፤ በአማኞች መካከል ያሉት ብዙ መከፋፈሎች ለዓለም ግልጥ ሆነው እየታዩ፣ የተግባር ኑፋቄን ለመቃወም እንዲሁ የምንፈጥንበት ጊዜ አሁን አይደለምን?
«የፍጥረት ናፍቆት የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ ይጠባበቃልና» (ሮሜ 8:19)።
ምዕራፍ 4 ተጠናቋል
የቃል ኪዳን ሕዝብ