በእጄ ያለው መክፈቻ
ቅድሚያ የሚሰጣቸው ነገሮች

ምዕራፍ 3 · 7 ደቂቃ ንባብ

ቅድሚያ የሚሰጣቸው ነገሮች

የቃል ኪዳኑ ማዕድ

የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ጴጥሮስና ዮሐንስ ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ የገቡት ሞቃትና አቧራማ በሆነ ቀን ነበር። የመጡት ፔሳኽን፣ ማለትም የፋሲካን በዓል ለማክበር ነበር፤ በዚያች ሰዓትም በዓሉ ወደሚዘጋጅበት ስፍራ የሚመራቸውን የውኃ ማሰሮ የተሸከመ አንድ ሰው እየተከተሉ ነበር።

ጌታ እንደ ነገራቸው መሪያቸውን ማግኘት አስቸጋሪ አልነበረም፤ የውኃ ማሰሮ የተሸከመ ወንድ ማየት የተለመደ አልነበረምና። ያ በአብዛኛው የሴቶች ሥራ ነበር።

ሰውየውም ባለ ሁለት ፎቅ ወደሆነ ደስ የሚል ቤት መራቸው፤ ባለቤቱም በሞቀ ሰላምታ ተቀበላቸው። የመጡበትን ጉዳይ በነገሩት ጊዜ፣ በላይኛው ፎቅ ወዳለ፣ ዕቃ ወደተሟላለት ሰፊ ክፍል አስገቧቸው።

ሁለቱም የበዓሉን ሥርዓት በሚገባ ያውቁ ስለ ነበር ዝቅተኛውን ማዕድ ለማዘጋጀት ብዙ ጊዜ አልወሰደባቸውም። የመራራ ቅጠላ ቅጠል ሳህኖች ከፖም፣ ከቀረፋና ከለውዝ ሳህኖች ጋር እየተፈራረቁ ተቀመጡ። የጨው ውኃ የያዘ ጠርሙስና ጥቂት የተቀቀሉ እንቁላሎች ከወይን ጠጅ ዕቃዎች አጠገብ ተቀመጡ፤ «ማጻ» ብለው የሚጠሩት ያልቦካ ቂጣም ብዙ ድርሻ ነበረ። ብዙም ሳይቆይ ሰዓቱ ደረሰ፤ ኢየሱስም ከቀሩት ደቀ መዛሙርት ጋር መጣ።

ወደ ሰገነቱ ሲገቡ የደስታ ጫጫታና የሞቀ ጨዋታ ይሰማ ነበር። ይህ የበዓል ጊዜ፣ ለአይሁድ ሁሉ በዓመቱ ውስጥ እጅግ አስደሳቹ ጊዜ ነበር፤ የይሖዋን ታላቅ ታማኝነት ደግመው የሚያስቡበት ጊዜ ነበርና። ከብዙ ዘመን በፊት ከግብፅ ባርነት አላዳናቸውምን? ከሮማውያን የአሁኑ ጭቆናስ ሊያድናቸው አይችልምን?

ለኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ይህ ጊዜ ምናልባት ከዚህም የበለጠ አጓጊ ነበር። ጌታቸው በጥንት ነቢያት እንደ ተተነበየው ነጻ ሊያወጣቸው የመጣው፣ ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የኖረው መሲሕ መሆኑን ለሕዝቡ የሚገልጥበት ቀን ቀርቦ እንደ ሆነ ያስቡ ነበር። በሕዝባቸው ታሪክ ውስጥ ወሳኝ በሆነ ጊዜ ላይ እንዳሉ ተሰምቷቸው ነበር። በእርግጥም ያለፈው ሳምንት ለየት ያለ ነበር፤ ነገሮችም ወደ መቋጫቸው እየደረሱ ነበር። የሃይማኖት መሪዎቹ በኢየሱስ ትምህርትም ሆነ በተወዳጅነቱ እጅግ እንደ ተናወጡ ግልጽ ነበር።

የደቀ መዛሙርቱ ጨዋታ በሙሉ ያለፈው ሳምንት በተፈጸሙት ነገሮች ላይና እነዚያ ነገሮች ምን ትርጉም እንዳላቸው በማሰብ ላይ ያተኮረ እንደ ነበር መገመት እችላለሁ። ከአምስት ቀን በፊት ብቻ ስለ ሆነው ወደ ኢየሩሳሌም የድል አድራጊነት አገባብ ጴጥሮስ ማውራቱን ማቆም እንዳልቻለ እርግጠኛ ነኝ፤ በዚያን ጊዜ ሕዝቡ ልብሳቸውን በአቧራማው መንገድ ላይ አንጥፈው፣ የዘንባባ ዛፍ ዝንጣፊዎችንም ቈርጠው እያውለበለቡ «በጌታ ስም የሚመጣ የእስራኤል ንጉሥ የተባረከ ነው» (ዮሐንስ 12:13) እያሉ ጮኹ።

ጌታው የተቀመጠበትን የአህያ ውርንጫ እየመራ፣ ራሱን ቀና አድርጎ ደረቱን ነፍቶ ሲሄድ ይታየኛል። ቀናተኞቹ (የነጐድጓድ ልጆች) ዮሐንስና ያዕቆብ ደግሞ ጌታቸው የገንዘብ ለዋጮችን ገበታዎች ገልብጦ ከመቅደስ ያባረራቸው መንገድ ይበልጥ ሳይማርካቸው አልቀረም። «የሊቀ ካህናቱን ፊት አያችሁት? ወንድሜ፣ እንዴት ተናዶ ነበር!»

ሁሉም ከማዕዱ አጠገብ በጎናቸው ተደገፉ፤ አሁንም በበዓሉ ደስታ ውስጥ ነበሩ፤ የፈንጠዝያ ጊዜ ነበር። ኢየሱስ ወዳጆቹ ሲደሰቱ በደስታ ይመለከታቸው ነበር፤ ነገር ግን እነርሱ ያላስተዋሉትን አንድ ነገር ያውቅ ነበር፤ ነገ ይሞታል።

ሐኪምህ በሕይወት የምትቆይበት ጊዜ አጭር እንደ ሆነ ቢነግርህ ምን ታደርጋለህ? በርግጥ የሌላ ሐኪም አስተያየት ትጠይቃለህ! ያም ደግሞ ይህን ዓለም፣ ዘወትር አብረውህ ያሉትን ሰዎችና ወዳጆችህን በቅርቡ እንደምትለይ ቢያረጋግጥስ? እኔ ምን እንደማደርግ አውቃለሁ። የያዝኩትን ሥራ ቶሎ ጨርሼ ለእኔ እጅግ ውድ ከሆኑት ጋር ለመሆን አመቻች ነበር፤ ከባለቤቴ፣ ከሴቶች ልጆቻችንና ከቤተሰቦቻቸው ጋር።

ምን ያህል እንደምወዳቸውና በእነርሱ ምን ያህል እንደምኮራ ልነግራቸው እወድ ነበር። ኢየሱስን እያገለገሉና ለክብሩ ምስጋና የሚሆን ሕይወት እየኖሩ ከእርሱ ጋር ወደ ፊት እንዲገፉ አበረታታቸው ነበር።

ይቅርታ ልጠይቃቸው የሚገባኝ ነገር፣ ያደረስኩባቸው ቊስል፣ የተናገርኩት ክፉ ቃል ወይም ግዴለሽነት ካለ እጠይቃቸው ነበር። እርስ በርሳችን ያለንን ግንኙነት ለማጽናት ሊደረግ የሚችልና ያልተደረገ ምንም ነገር እንዳይቀር እጅግ እርግጠኛ መሆን እፈልግ ነበር።

እንደ አዲሶቹ የስፖርት ውጤቶች ወይም እንደ ሐሜት ላሉት፣ በሌላ ጊዜ ብዙ ጊዜዬን ስለሚወስዱት ተራ ነገሮች ለማውራት ጊዜ አላገኝም ነበር። በእርግጥም የማደርገው ሁሉ ቅድሚያ በሚሰጣቸው ነገሮች ላይ ማተኮር ብቻ ይሆን ነበር። በዚያች ሌሊት፣ በፋሲካው ማዕድ ላይ፣ ጌታ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ሊያደርግ የነበረውም ይኸው ነው፤ ቅድሚያ በሚሰጣቸው ነገሮች ላይ ማተኮር!

የሚጠይቃቸው ነገሮች

እንደ ልማዳቸው ወደዚህ ሰገነት ሲገቡ ሁሉም ጫማቸውን አውልቀው ነበር። እግራቸው አቧራ ለብሶ ነበር፤ በጣቶቻቸው መካከል ያለው አሸዋም ምቾት ነሳቸው።

ብዙም ሳይቆይ የማጒረምረም ድምፅ መሰማት ጀመረ። የውኃ ሳህኖቹ ከበሩ አጠገብ ባለ ጠረጴዛ ላይ ነበሩ፤ ፎጣዎችም ተዘጋጅተው ነበር፤ ነገር ግን እግራቸውን አጥባ የምታሳርፋቸው አገልጋይዋ ልጅ የት ነበረች? እነርሱ ሲደርሱ እዚህ መገኘት ነበረባት!

ሁሉም የሚያስቡትን በመጀመሪያ አፍ አውጥቶ የተናገረው ጴጥሮስ እንደሚሆን መገመት እችላለሁ። እርሱ እኔን በጣም ይመስላል፤ ሁልጊዜ ሳያስብ ተናግሮ ራሱን የሚያስቸግር! «ልጅቱ የት አለች? እግሬ እያሳከከኝ ነው። አንድ ሰው ተሳስቶ ሊነግራት ረስቶ ይሆን? ይህን በዓል ያዘጋጀው ማነው? በኮሚቴው ውስጥ ያለው ማነው?» ሌሎቹ ዝም እንዲል ሊነግሩት ሲሞክሩ የኀፍረት ሹክሹክታ ይሰማ ነበር። ለነገሩ ዝግጅቱን ያደረገው ጌታ ራሱ ነበር! እርሱ ደግሞ አይሳሳትም፤ ዓላማዎቹን ልናስተውል በማንችልበት ጊዜ እንኳ።

ኢየሱስ ከማዕዱ ተነሥቶ ወደ ውኃ ሳህኖቹ ሄደ።

ጴጥሮስ «ጥሩ፣ ልጅቱን ሊጠራት ነው» ብሎ አሰበ።

ኢየሱስ መጎናጸፊያውን አውልቆ ፎጣ ታጠቀ፤ የውኃ ሳህን አንሥቶ ዞረ… ወደ ጴጥሮስ!

ጴጥሮስ «ወይ ጉድ፣ እኔ እንዳደርገው ሊጠይቀኝ ነው!» ብሎ አሰበ።

ይልቁንም ኢየሱስ የጴጥሮስን አቧራማ እግር ያጥባል፤ ከዚያም በዚያች ሌሊት ይጠብቀው የነበረውን መከራ የሚያመጣበትን፣ አሳልፎ የሚሰጠውን የአስቆሮቱ ይሁዳን ጨምሮ የሁሉንም እግር ያጥባል። ጌታ የይሁዳን እግር እያጠበ ቀና ብሎ ዓይኑን ሲመለከት መገመት ትችላለህ? በእነዚያ ዓይኖች ውስጥ ምን አየ?

ፍርሃት? ወይስ በደለኝነት? ይሁዳስ በጌታው ዓይኖች ውስጥ ምን አየ? ቀና ብሎ ማየት ችሎ ይሆን? እንዴት ያለ ፍቅር ነው!

ኢየሱስ ሳህኑንና ፎጣውን በበሩ አጠገብ ወዳለው ስፍራቸው መለሰ፤ መጎናጸፊያውንም ለብሶ ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዞረ።

«እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና» አላቸው (ዮሐንስ 13:1-20)።

የደቀ መዝሙርነት የመጀመሪያው ቅድሚያ አገልጋይነት ነው። ጌታ አገልጋዮች እንድንሆን አዝዞናል። ሊያገለግል እንጂ እንዲያገለግሉት ያልመጣውን እርሱን ልንመስል ብንፈልግ ይህ የግድ አስፈላጊ ነው (ማቴዎስ 20:28)። ይህ በመንግሥተ ሰማያት ታላቅ የመሆን ቅድመ ሁኔታና በመንፈስ የመሞላት ማስረጃ ነው (ኤፌሶን 5:18,21)።

ጌታ የአንዳችንን እግር አንዳችን በማጠብ ቃል በቃል እንድንከተለው ፈልጎ ነው ብዬ አላስብም (ምንም እንኳ ያንን መለማመድ ታላቅ በረከት ቢሆንም)፤ ይልቁንም በዚህ ዓለም ውስጥ ከመመላለስ ከሚመጣው አቧራና ቆሻሻ እርስ በርሳችን ለመታደስ እንድንጥር ነው። ከዚህ ዓለም ቆሻሻ ከፊሉ ሳይጣበቅብህ በዓለም ውስጥ መኖር አይቻልም። ጋዜጣ እያነበቡ፣ ቴሌቪዥን እየተመለከቱ ወይም ከጎረቤቶችና ከሥራ ባልደረቦች ጋር እየተጫወቱ በመርዙ ሳይለከፉ መቅረት ምን ያህል አልፎ አልፎ ነው? በአማኞች መካከል እንኳ እጅግ የተለመዱት ሐሜትና ማጒረምረም የክርስቲያናዊውን መንገድ የመመላለስ ደስታ ቶሎ ይሰርቁናል። የሌሎች አማኞችን የሚያነጹ ቃላት፣ ማደስና ማበረታታት ያስፈልገናል። እግራችንን መታጠብ ያስፈልገናል! የክርስቲያናዊ ኅብረት ዓላማ ይኸው ነው፤ ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ በዓለም ሰዎች መካከል የሚወረወረውን ያህል «ቆሻሻ» በአማኞች መካከልም ይወረወራል!

በክርስቶስ አካል ውስጥ እርስ በርሳችን እንድንገለገል የተጠራን ብቻ ሳይሆን፣ ጌታችንን አሳልፈው ለሚሰጡና ከተከታዮቹ አንዱ ለማይሆኑትም እንኳ አገልጋዮች እንድንሆን ተጠርተናል።

ኢየሱስ በልቡ ያለውን ሁሉ እያወቀ የይሁዳን እግር አጠበ። ጥርጣሬዎቹንና ብስጭቶቹን አየ፣ ሴራውንና ተንኰሉንም ያውቅ ነበር፤ ቢሆንም እግሩን ለማጠብ አላመነታም።

ይህን ሥራ በፈጸመ ጊዜ እርሱን ጌታ አድርገው የሚቀበሉትን ሁሉ እንዲሁ እንዲያደርጉ ጋበዘ።

ራሱን ብቻ በሚያስቀድም ዓለማችን ውስጥ የአገልጋይ መንፈስ መያዝ ቀላል አይደለም። ትሕትናን ይጠይቃል፤ ትሕትና ማለት ራስን እንዳለ በእውነት ማወቅና ራስን መቀበል ነው። ራሳችንን «በክርስቶስ» ሆነን ስናይ ሌሎች ስለ እኛ በሚያስቡት ነገር አንሸበርም። ጌታን ደስ እንደምናሰኝ ካወቅን ሌሎች የሚሉት ምን ያስጨንቀናል? መታመኛችን በእርሱና በተስፋዎቹ ላይ ነው።

ኢየሱስ ተልእኮው ምን እንደ ሆነ፣ ከየት እንደ መጣና ዕድል ፈንታው ምን እንደ ሆነ ያውቅ ነበር (ዮሐንስ 13:3)። ይህ እርግጠኝነት የአገልጋይነቱ መሠረት ነበር። አብ ሥልጣን ሰጥቶት ነበር፣ ወደ ዓለም ልኮት ነበር፣ ደግሞም መልሶ ይቀበለው ነበር።

እኛም ያው ተልእኮና ያው ዕድል ፈንታ አለን! ዓለም ደካሞች ወይም ወኔ ቢሶች ብሎ ሊጠራን፣ የአገልጋይነት መንፈሳችንን ለራሱ ጥቅም ሊጠቀምበት ይሞክር ይሆናል። ልብስህን ይወስዳሉ፣ አንድ ምዕራፍ አብረሃቸው እንድትሄድ ያስገድዱሃል፣ ባሪያቸውም ያደርጉሃል።

ኢየሱስ ይህ ቢደርስብን ሸሚዝህን ደግሞ እንድትሰጣቸውና ሁለተኛውን ምዕራፍ እንድትሄድ ነግሮናል! ይህን በማድረግህ ራስህን ከባርነታቸው እያወጣህ በፈቃድህ አገልጋይ እያደረግህ ነው (ማቴዎስ 5:40-41)።

ይሁዳ ክፉ ሥራውን ሊሠራ ከክፍሉ ከወጣ ብዙም ሳይቆይ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ሁለተኛውን መስፈርት አስተማራቸው። «እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ፥ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ። እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፥ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ» (ዮሐንስ 13:34-35)። ይህ ምርጫ ሳይሆን ትእዛዝ መሆኑን ልብ በል! እርሱ ምን ያህል እንደሚወድህ ለመለካት ሞክረህ ታውቃለህ? «እርስ በርሳችሁ» ምን ያህል እንደምትዋደዱ የሚለካበት ብቸኛው ሚዛን ያ ነው!

በጸጋውና በውስጣችን እንዲያድር በሚሰጠን በመንፈስ ቅዱስ ባይሆን ኖሮ ይህ የማይቻል ነበር።

«ከምወዳቸው ጋር በላይ መኖር፣ ኦ፣ ያ ክብር ይሆናል! ከማውቃቸው ጋር በታች መኖር ግን፣ እሱማ ሌላ ታሪክ ነው!»

(ደራሲው ያልታወቀ)።

እርስ በርሳችን ላንዋደድ እንችላለን፤ ነገር ግን እርስ በርሳችን እንድንዋደድ ታዝዘናል! ይህ ማለት ሐሜት የለም፣ ከጀርባ መውጋትም የለም ማለት ነው፤ ይልቁንም መከባበር፣ አንዱ ሌላውን ማስቀደም፣ አንዱ የሌላውን ሸክም መሸከምና ከዚህም የበለጠ ብዙ ነገር… ሦስተኛው መስፈርትም በደቀ መዛሙርቱ ፊት ቀረበ። «ብትወዱኝ ትእዛዛቴን ጠብቁ» (ዮሐንስ 14:15)። ለቃሉ እንድንታዘዝ ይጠራናል። የብሉይ ኪዳኑ ነቢይ ሳሙኤል የማይታዘዘውን ንጉሥ ሳኦልን እንዲህ ብሎ ገሠጸው፦ «በውኑ የእግዚአብሔርን ቃል ከመስማት ይልቅ የሚቃጠል መሥዋዕትና ሌላው መሥዋዕት እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋልን? እነሆ፥ መታዘዝ ከመሥዋዕት፥ መስማትም ከአውራ በግ ስብ ይበልጣል።

ዓመፀኝነት እንደ ምዋርተኛነት ኃጢአት ነው፥ እልከኝነትም እንደ በደልና እንደ ጣዖት አምልኮ ነው። አንተ የእግዚአብሔርን ቃል ስለ ናቅህ እርሱ ደግሞ ንጉሥ እንዳትሆን ናቀህ» (1ኛ ሳሙኤል 15:22-23)።

ሳኦል የጌታ የእግዚአብሔርን ቃል ስላልታዘዘ መንግሥቱንና ሥልጣኑን አጣ። ኢየሱስ ለሕዝቡ በተናገረ ጊዜ የሰሙት ሁሉ በመገረም ተሞሉ፤ እንደ ታላቅ ባለ ሥልጣን ይናገር ነበርና (ማቴዎስ 7:28-29)።

እርሱን አዳኝ አድርገን የምንቀበል እኛ ጌታ መሆኑንም ልናውቅ ይገባናል። እርሱ የሚናገረው ከሁሉ የላቀ ሥልጣን አለው።

ድምፁን ዕለት ዕለት ለመስማትና ለመለየት ስሱ መሆን ያስፈልገናል። እኛ በጎቹ ድምፁን ልንለይ እንደሚገባን ተናግሯል። ከሁሉ በላይ በቅዱሳት መጻሕፍት በኩል ሲናገረን ልንሰማውና የሚለውን ልንታዘዝ ይገባናል። አማኞች ሁሉ ለትእዛዛቱ እየታዘዙ የሚኖሩ የተጻፈው ቃል ተማሪዎች መሆን አለባቸው።

ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ የሚጠይቀው እርስ በርሳችን እንድንገለገል፣ እርስ በርሳችን እንድንዋደድና ቃሉን እንድንታዘዝ ነው።

የሰጣቸው ተስፋዎች

ኢየሱስ በደቀ መዛሙርቱ ፊት ካቀረባቸው ከሦስቱ መስፈርቶች በተጨማሪ የበለጸገ በረከትንም ተስፋ ሰጣቸው። እርሱ «በአባቴ ቤት» (ዮሐንስ 14:2) ብሎ በጠራው ስፍራ ቦታ አዘጋጅቶላቸው ዳግመኛ ይመጣል፤ ወደ ራሱም ይቀበላቸዋል። ሌላ አጽናኝ ስለሚልክላቸውና እንደ ፈቃዱ የሚለምኑትን ጸሎት ስለሚመልስላቸው እርሱ ካደረገው የሚበልጥ ሥራ ይሠራሉ። በክርስቶስ የመሆንን በረከት ሊያውቁና የአብን ፍቅር ሊለማመዱ ነበር።

አጽናኙ መንፈስ ቅዱስ በውስጣቸው ሊያድር ይመጣል፤ ወደ እውነትና ወደ እግዚአብሔር ፈቃድ እውቀትም ይመራቸዋል፤ ኢየሱስ ያስተማራቸውንም ሁሉ ያሳስባቸዋል።

«ልባችሁ አይታወክ፤ በእግዚአብሔር እመኑ፥ በእኔም ደግሞ እመኑ» (ዮሐንስ 14:1)።

«ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም። ልባችሁ አይታወክ አይፍራም» (ዮሐንስ 14:27)።

«ደስታዬም በእናንተ እንዲሆን ደስታችሁም እንዲፈጸም ይህን ነግሬአችኋለሁ» (ዮሐንስ 15:11)።

ለእነርሱ፣ ለእኛም፣ ዓለም ሊሰጠው ወይም ሊወስደው የማይችለውን ሰላም፣ መጠኑ ሙላት የሆነውን ደስታ፣ ከቶም የማይለየንና የማይተወንን፣ ከመንፈስ ራሱ በቀር ሌላ ያልሆነውን ሕልውና ተስፋ ሰጠ (ዘዳግም 31:6)።

እነዚህን ከጌታ ጋር ባለህ ጉዞ ተለማምደሃቸዋል? እኔ በእርግጥ ተለማምጃቸዋለሁ፤ ነገር ግን ከዚህ የበለጠ እናፍቃለሁ!

የእነዚህን ተስፋዎች ተሞክሮ የምናገኘው አገልጋዮች፣ የምንዋደድና ለቃሉ የምንታዘዝ ስንሆን ነው።

ገጽ 1 / 1 · 7 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል