በእጄ ያለው መክፈቻ
ሰማይ ተከፈተ

ምዕራፍ 13 · 8 ደቂቃ ንባብ

ሰማይ ተከፈተ

በዘመኔ በርካታ ተአምራትን አይቻለሁ — በሥጋ የተፈወሱ በርካታ ሰዎችንም ጨምሮ። ደንቆሮና ዲዳ የነበረች የ12 ዓመት ልጅ መስማት ስትችልና ለመጀመሪያ ጊዜ ስትናገር በቦታው ነበርሁ። ከተወለደች ጀምሮ ሽባ የነበረች አንዲት ሴት ከጸሎት በኋላ ስትራመድ አይቻለሁ። አንዲት ሴት እየተጸለየላት ሳለ በአንገቷ ላይ የነበረ ትልቅ እንቅርት ሲጠፋ አይቻለሁ።

ይሁን እንጂ እነዚህ ተአምራት የቱን ያህል ቢያስደስቱኝና ቢያበረታቱኝም፣ በቅርብ ዓመታት የቆሰሉ አማኞች የቆሰሏቸውን ሰዎች ለመልቀቅና ራሳቸውንም ለመፈታት «የመንግሥተ ሰማያትን መክፈቻ» ሲጠቀሙ ካየኋቸው የነፍስ ፈውስ ተአምራት የበለጠ አስደናቂ አልነበሩም።

ቀጥሎ ያሉት ታሪኮች በእውነተኛ ገጠመኞች ላይ የተመሠረቱ ናቸው፤ ምሥጢራዊነትን ለመጠበቅ ግን ስሞችና ቦታዎች ተቀይረዋል። ይሁን እንጂ ውጤቱን በምንም መንገድ አላጋነንሁም፤ የጌታንም ተአምራዊ ሥራ በታማኝነት ለመዘገብ ጥሬአለሁ።

ማሪ

ማሪን ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኘኋት የ28 ዓመት ወጣት ሳለች ነው። አማካሪዎቿ በሥነ አእምሮ ሕክምና ክትትል ሥር ሊያደርጓት እየሞከሩ ነበር፤ እርሷም በጥልቅ ድባቴ ውስጥ ሆና ራሷን ከሰው አግልላ ነበር። በካናዳ ምንም ዓይነት የልደት በዓልም ሆነ ገናን በማያከብር ጥብቅ የይሖዋ ምስክሮች ቤት ውስጥ ያደገችበትን አሳዛኝ የልጅነት ሕይወቷን ነገረችኝ። ከሁለቱም ወላጆቿ የፍቅር መግለጫ ትዝታ አልነበራትም፤ አባቷ እንደሚወዳት ሲነግራት ሰምታ አታውቅም፤ እቅፉንም ተሰምቷት፣ መሳሙንም አግኝታ አታውቅም።

ማሪ በ16 ዓመቷ ከቤት ኮበለለች። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ድንቅ የሆነውን የወንጌልን የምሥራች ሰማች፤ ወዲያውኑም ሕይወቷን ለክርስቶስ አሳልፋ ሰጠች፤ እርሱንም ለማገልገል ተመኘች።

በእነዚያ የመጀመሪያ ዓመታት ከማንነቷና ከስሜቷ ጋር ስትታገል አንዲት ትንሽ የአካባቢ ቤተ ክርስቲያን ተንከባከበቻት። አንድ ጊዜ ከቤተሰቧ ጋር ለመታረቅ ሙከራ ተደርጎ ነበር፤ ነገር ግን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ባላቸው የተለያየ ግንዛቤ ክርክር በመነሣቱ ገጠመኙ እጅግ የሚያሠቃይ ሆነ። መለያየታቸውም በምሬት የተሞላ ነበር፤ ማሪም ወላጆቿን ዳግመኛ ላለማየት ወሰነች። በመጀመሪያው ግንኙነታችን፦ «እጠላቸዋለሁ» አለችኝ።

በቀጣዮቹ ወራት ከማሪ ጋር ብዙ ሰዓታትን አሳለፍሁ። እንደ አባቷ ትመለከተኝ ነበር፤ እኔም በእርሷ ውስጥ ፈጽሞ ያላደገችውን ትንሽ ልጅ አየሁ። ምንም እንኳ በሚገባ የተማረችና ሁለት ቋንቋ እንኳ የምትናገር ብትሆንም፣ ብዙዎቹ ድርጊቶቿ የአፍላ ወጣት ድርጊቶች ነበሩ።

ታታሪ ሠራተኛ ነበረች፤ በተሰጣት ሥራም እጅግ ብቁ ነበረች፤ ስሜቷና ዝንባሌዋ ግን በራሱ የማይተማመን ጎረምሳ ዓይነት ነበር። ስለ ብዙ ነገሮች ተነጋገርን፤ ነገር ግን ወላጆቿ በተነሡ ቁጥር በመካከላችን ግድግዳ ይቆም ነበር።

በመጨረሻም እግዚአብሔር ከእናቷና ከአባቷ ፍቅርን እንድትቀበል ተደርጋ የተሠራች «የልብ ቅርጽ ያላት» ዕቃ አድርጎ እንደ ፈጠራት ላስረዳት ቻልሁ። እንዲህ ያለው ፍቅር የሚገለጠው ከረሜላና ስጦታ በመስጠት ሳይሆን፣ ምኞትንና ግብን በማበረታታት ዋስትናን፣ ለራስ ክብርን፣ ማንነትን፣ መጽናናትንና ተቀባይነትን በማሳደግ፣ እንዲሁም በሌሎች ብዙ ነገሮች ነው — እርሷ ፈጽሞ ያላገኘቻቸው ነገሮች።

ማሪ ወላጆቿ ይህን ፍቅር በውስጧ ባለማፍሰሳቸው በእርሷ ላይ ኃጢአት እንደ ሠሩ ለመስማማት ፈጣን ነበረች፤ ነገር ግን ወላጆቿ ከአብዛኞቻችን እንደማይለዩ ማስረዳቱ እጅግ ከባድ ነበር። እነርሱ በጨለማ እየተመላለሱ፣ የራሳቸውን ቁስል — የራሳቸውን የተናጋ ሕይወት — ተሸክመው የሚኖሩ የሰይጣን ጥቃት ሰለባዎች ናቸው። ማሪን የመጉዳት ፍላጎት አልነበራቸውም፤ የተሸከመቻቸውን ቁስሎችም ምናልባት አያውቁም ነበር።

«ለወላጆችሽ ደብዳቤ እንድትጽፊ እፈልጋለሁ» አልኋት። «አትጨነቂ! መላክ አይጠበቅብሽም፤ ነገር ግን በእንዲህ ያለ ደብዳቤ ምን እንደምትዪ እንድታስቢበት በእርግጥ እፈልጋለሁ። እንዴት እንደ ጎዱሽ በዝርዝር፣ ከምሳሌዎች ጋር ንገሪያቸው። ፍቅራቸውን ምን ያህል እንደምትናፍቂም ንገሪያቸው።»

ይህ ተመካሪው በንኡስ ሕሊናው ያለውን ወደ ንቁ ሕሊናው ገጽ እንዲያመጣ ስለሚረዳው በምክር አገልግሎቴ ብዙ ጊዜ የምጠቀምበት ልምምድ ነው።

ደብዳቤው አይላክም፤ ነገር ግን ትኩረታቸውን የሚያደርጉበት ተጨባጭ ነገር እንዲኖራቸው ያስችላቸዋል። ማሪ ደብዳቤውን ለመጨረስ በእንባ የተሞሉ ሦስት ሳምንታት ፈጀባት። ጌታ አሳቧን እንዲመራ ስንጸልይ፣ እርሱ ያስታወሳት ትዝታዎች አስደነቋት።

ደብዳቤው ሲያልቅ እንዳነበው ተጋበዝሁ። ይህ ለአማካሪው የግድ አስፈላጊ አይደለም፤ ለማማክራቸውም ሁሉ የጻፉትን ለእኔ ማሳየት እንደማይጠበቅባቸው በግልጽ አሳውቃለሁ። በዚህ ደብዳቤ ውስጥ እጅግ ብዙ ሕመም እንደ ነበረ ግልጽ ነበር፤ በሴት አካል ውስጥ ለተደበቀችው ለዚህች የጠፋች ትንሽ ልጅም ልቤ ተሰበረ።

ወረቀቱን አጥፌ ወደ ፖስታው መለስሁት። «ማሪ፣ አሁን ወላጆችሽን ይቅር ለማለትና ለመልቀቅ ትመርጫለሽ?»

ብዬ ጠየቅኋት። «አልችልም!» ብላ በእንባ ጮኸች። ከዚህ በላይ ምንም ማድረግ እንደማልችል ነገርኋት፤ የቁስሏ መድኃኒት አሁን በእጇ ነበር፤ ልትጠቀምበት ብትመርጥ «የመንግሥቱ መክፈቻ» የእርሷ ነበር።

ማሪ በቢሮዬ ተንበርክካ ብዙ እያለቀሰች ወላጆቿን ይቅር እንደምትል ለጌታ የነገረችውና ስለ እነርሱ፦ «ይህን ኃጢአት አትቍጠርባቸው» እንዲለው የፈለገችው ሦስት ተጨማሪ ሳምንታት ካለፉ በኋላ ነበር። ከዚያም በየዕለቱ በወላጆቿ ላይ በረከትን እንደምትጸልይ ቃል ገባችልኝ።

ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ማሪ በራስ መተማመኗ ሲያድግ ስመለከት፣ ለጥቂት ቀናት ወላጆቿን ለመጠየቅ ወደ ቤት እንድትሄድ እንደምፈልግ ነገርኋት። አጥብቃ ተቃወመች፤ በመጨረሻ ግን ይቀበሏት እንደ ሆነ ለማወቅ ልትጽፍላቸው ተስማማች።

ከሁለት ሳምንታት በኋላ በደስታ ተሞልታ እየሮጠች ወደ ቢሮዬ ገባች። ሁለት ደብዳቤዎች የያዘ ፖስታ ደርሷት ነበር፤ አንደኛው እንኳን ደህና መጣሽ የሚል ከእናቷ የተላከ አጭር ደብዳቤ ሲሆን፣ ሌላው ከአባቷ የተላከ ረዘም ያለ ደብዳቤ ነበር። የኋለኛው ደረቅና ቀዝቃዛ ነበር፤ ቤታቸውን እንደ ቀየሩና ብትመጣ አሁን ረጅም ጉዞ እንደሚሆንባት ይነግራታል። በቶሮንቶ ማልዶ የሚነሣ ባቡር መያዝ፣ በሞንትሪያል መቀየር እንደሚኖርባትና ከዚያም ሌሊት በጣም ዘግይታ ቤታቸው እንደምትደርስ ይገልጻል። ብዙ ሥራ ስላለበት ሊያያት ይችል እንደ ሆነ እርግጠኛ አልነበረም፤ ማሪን ከሁሉ በላይ ያስደሰታት ግን ደብዳቤውን፦ «ከብዙ እቅፍና መሳም ጋር፣ አባትሽ!» ብሎ መደምደሙ ነበር።

ማሪን በቶሮንቶ ባቡር ላይ ስሸኛት፣ እንደምጸልይላት ነገርኋት፤ ወደ ሃይማኖታዊ ክርክርም እንዳትገባ መከርኋት። «ከመመለስሽ በፊት» አልኋት፣ «አባትሽን ያንን ‹እቅፍና መሳም› መጠየቅሽን እንዳትረሺ።» ይህን ለማድረግ ድፍረት እንደሚኖራት ተጠራጠረች፤ እኔ ግን ለዚሁ ዓላማ እንደምጸልይላት አረጋገጥሁላት።

በዚያ ምሽት ዘግይቶ የስልክ ጥሪ ደረሰኝ። «ጋሬዝ፣ እኔ ነኝ፣ ማሪ።» የሆነውን ስትነግረኝ እጅግ የተደሰተች ትመስል ነበር፤ ራሷንም መቆጣጠር አቅቷት ነበር። በሞንትሪያል መድረክ እየቀየረች ሳለ፣ እናቷና አባቷ እዚያ ቆመው በድንገት አየቻቸው! ሊቀበሏት ረጅም መንገድ ተጉዘው መጥተው ነበር። ማሪ ወደ እነርሱ እየተራመደች ሳለች፣ ድንገት አባቷ ወደ ፊት ተራምዶ በእጆቹ አቀፋትና ሳማት! የሰማይ መላእክት እንዴት ደስ ብሏቸው ይሆን!

ግን ምን ሆኖ ነበር? ማሪ በመልቀቂያ ጸሎቷ ለአባቷ ሰማይን እንደ ከፈተችለት አምናለሁ። በዚያች ጠዋት የሰማዩ አባቷ በዚያ «በተከፈተው በር» በኩል ወደ ምድራዊ አባቷ ተናግሮ፣ ከሥራ አንድ ቀን ፈቃድ ወስዶ ሴት ልጃቸውን ለመቀበል ሚስቱን ይዞ እንዲጓዝ አነሣሥቶት ነበር። ከዚያም በልቡ ላይ ሠርቶ ማሪን ለመጀመሪያ ጊዜ በፍቅር እጁን ዘርግቶ እንዲስማት አደረገው። በርግጥ አባቷ ዕቅዱና ድርጊቱ በእግዚአብሔር እየተመራ መሆኑን አያውቅም ነበር።

ከሁለት ዓመት በኋላ ማሪ ጤናማና ውብ ወጣት ሴት ሆና አደገች። ከቤተሰቧ ጋር ሙሉ በሙሉ ታረቀች፤ ወደ ከተማቸውም እንኳ ተዛወረች። በወንጌላውያን ቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ ሆነች፤ ዲያቆኒት ሆና እንኳ ተሾመች። ብዙም ሳይቆይ ማሪ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ባል አገኘች፤ ሁለቱም ሚስዮናውያን ሆነው ጌታን ለማገልገል አቀዱ። እግዚአብሔር እንዴት መልካም ነው!

አንጄላ

አንጄላ በቢሮዬ ወንበር ላይ ከተቀመጠች በኋላ፦ «ጋሬዝ፣ ምን ሆኜ ነው?» ብላ ጮኸች። «ጆንን ባገባ ስሕተት የምሠራ መስሎኝ በየማለዳው በፍርሃት ተሞልቼ እነቃለሁ።»

በየማለዳው ግንኙነቱን ለማቋረጥ እንደምትወስን፣ ቀኑ እየገፋ ሲሄድ ግን ማቋረጥ እንደማትችል እንደምታውቅ አስረዳችኝ፤ ጆን ማንኛዋም ልጃገረድ ብታገባው የምትኮራበት መልካም ወጣት ነበርና። ራሱን ለክርስቶስ የሰጠ ክርስቲያን ነበር፤ በአክብሮትና በፍቅርም ይይዛት ነበር። ፍላጎቶቻቸው ተመሳሳይ ነበሩ፤ ሁለቱም በሚስዮናዊ አገልግሎት ጌታን የማገልገል ምኞት ነበራቸው።

አንጄላ እንዲህ ያለ ፍርሃት የተሰማት በዚህ ግንኙነት ብቻ ስላልነበረ ችግሩ የራሷ እንደ ሆነ ታውቅ ነበር። ሁለት ጊዜ መልካም ግንኙነቶችን አቋርጣ ከዚያ በኋላ ለምን «እንዲህ ያለ ሞኝነት» እንደ ሠራች እያሰበች ለሳምንታት አልቅሳ ነበር።

በምክር ጊዜያችን፣ ጤናማ በሆነ የወንጌላውያን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሽማግሌ ስለ ነበረው አባቷ ነገረችኝ። እጅግ ታከብረው ነበር፤ ነገር ግን ፈጽሞ ልታረካው እንደማትችል ይሰማት ነበር። የመጀመሪያ ልጁ ከሴት ይልቅ ወንድ እንዲሆን ይፈልግ እንደ ነበረ አሳውቆ ነበር። አንጄላ እያደገች ስትሄድ ከአባቷና ከታናናሽ ወንድሞቿ ጋር ክሪኬት ትጫወት ነበር። ጎበዝ ነበረች፤ ነገር ግን እንደ ወንድሞቿ ፈጽሞ ጎበዝ ስላልነበረች እነርሱ የሚያገኙትን አድናቆት አታገኝም ነበር። በትምህርት ቤት «ኤ» ውጤት ስታመጣ ለምን «ኤ ፕላስ» እንዳልሆነ ትጠየቅ ነበር። በባንክ የመጀመሪያ ሥራዋን ስትይዝ፣ ሌላ የተሻለ ባንክ ማመልከት ነበረባት ተባለች። እርሱን ለማስደሰት እጅግ ብትጥርም የአባቷን ምስጋና ወይም ማረጋገጫ ሰምታ አታውቅም ነበር።

አባቷ ማንነትንና ዋጋን ሊሰጣት እንዳልቻለ፣ በሕይወቷ ያሉትን ወንዶች ማርካት እንደማትችል ዘወትር ራሷን ስለምታይ በራስ መተማመኗ ዝቅተኛ እንደ ሆነ ጠቆምኋት።

ሰይጣን አባቷ እርሷን ባለመቀበሉ ምክንያት የተፈጠሩትን ቁስሎች ከጆን ጋር እግዚአብሔርን የሚያስከብር ግንኙነት እንዳትመሠርት ሊያደናቅፋት ይጠቀምባቸው ነበር። አንጄላ ሁኔታውን አየች፤ አባቷን በመልቀቅ ቁስሎቹን በማዳን እስራቱን እንዴት መስበር እንደምትችልም ተረዳች። ጌታን፦ «ይህን ኃጢአት በአባቴ ላይ አትቍጠርበት» ብላ ስትለምን አብረን ጸለይን።

ከጥቂት ሳምንታት በኋላ አንጄላ የኩላሊት ጠጠር ታመመች።

አብረን እንሠራበት የነበረውን አካባቢ ትታ ወደ ትውልድ ክፍለ ግዛቷ ተመለሰች፤ በዚያም ለቀዶ ጥገና ሆስፒታል ትገባ ነበር።

ከሁለት ወራት በኋላ ከቀዶ ጥገናው ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ስገናኛት፣ እየሮጠች መጥታ አቀፈችኝ፤ በታላቅ ደስታም አስደናቂ ታሪክ ነገረችኝ።

ቤት በደረሰች ጊዜ አባቷ ከሴት ልጁ ጋር ለማሳለፍ ከሥራ የአምስት ሳምንት ፈቃድ እንደሚወስድ አስታወቀ! ምግብ ቤት ይወስዳት ነበር፤ በአካባቢው ያሉ የሚጎበኙ ቦታዎችንም ያስጎበኛት ነበር። አብረው ተነጋገሩ፤ ከዚያ በፊት አንዳቸውም የማያውቋቸውን ስለ አንዳቸው ሌላውን ብዙ ነገሮች አወቁ። አባቷ ወደሚሠራባቸው ቦታዎች ብዙ ጊዜ ሄዱ፤ በየቦታውም ስለ ሴት ልጁና ስለምታደርጋቸው ድንቅ ነገሮች ይኮራ ስለ ነበር ታፍር ነበር። በእርሷ እጅግ ይኮራ ነበር!

«ጋሬዝ፣ ከአባቴ ጋር በፍቅር ወደቅሁ!» አለችኝ። ከዚያም፦ «ጆንን ለማየት ለመመለስም እጅግ ቸኩዬ ነበር» ብላ አከለች።

ጆንና አንጄላ በደስታ ተጋቡ፤ አብረውም ጌታን በደስታ አገለገሉ።

አባቷ ከሴት ልጁ ጋር ለማሳለፍ ከሥራ የአምስት ሳምንት ፈቃድ እንዲወስድ ያነሣሣው ምን ነበር? በአንጄላ የመልቀቂያ ጸሎት በተከፈተው በር በኩል ጌታ ተናግሮት ይሆን? እኔ በእርግጥ እንደዚያ አምናለሁ።

ቶኒ

ቶኒ እኔን ለማግኘት ድፍረት ለማሰባሰብ ብዙ ጥረት አስፈልጎት ነበር። በቁጣ ከተፈጸመ ፍቺ በኋላ በእናቱ ስላደገ ከማንኛውም ወንድ ጋር በሚገባ መግባባት አይችልም ነበር።

ትምህርት ቤት ከለቀቀ ወዲህ አንዱን ሥራ ከሌላው እየተከታተለ ቢይዝም አንዱንም ማቆየት አልቻለም ነበር። ምክንያቶቹን ሲነግረኝ አዳመጥሁት፤ ሁልጊዜም «የተቆጣጣሪዬ ጥፋት» እንደ ሆነ የሚያሳይ ተደጋጋሚ ሁኔታ ብዙም ሳይቆይ አየሁ።

ስለ ልጅነቱ፣ ስለ ብቸኝነቱና ትምህርት ቤትን ስለ መጥላቱ አብረን ተነጋገርን። ከአስተማሪዎቹ አንዱን እጅግ ይፈራ እንደ ነበረ ብዙም ሳይቆይ ታወቀ። ጎበዝ ተማሪ አልነበረም፤ ይህ አስተማሪ ደግሞ ባደረጋቸውና በተናገራቸው አንዳንድ ነገሮች እጅግ ጨካኝ ነበር። አስተማሪው ተማሪዎቹን በክፍል ውስጥ ምቾት በመንሣት የሚደሰት ይመስል ነበር፤ ስሱ የሆኑትንም በክፍሉ ፊት እያፌዘባቸው ያሳፍራቸው ነበር። ቶኒ ብዙ ጊዜ የንክሻ ቃላቱ ዒላማ ነበር።

ከዚያም ዛቻዎቹ ነበሩ። ሥራው «በሚፈለገው ደረጃ» ስላልሆነ ወደ ርእሰ መምህሩ እንደሚላክ ቶኒ ሳይዛትበት አንድም ሳምንት አያልፍም ነበር። ምንም እንኳ አብዝቶ ቢሠራም ይህን አስተማሪ ማርካት ፈጽሞ አልቻለም፤ ብዙ ጊዜም ተጨማሪ ሥራ ይሰጠው ነበር። ትምህርት ቤትን ለቅቆ ገንዘብ ለማግኘት የሚያስችል ዕድሜ ላይ ሲደርስ እጅግ ተደሰተ፤ ነገር ግን ቶኒ በሥልጣን ቦታ ካለ ማንኛውም ገዢ ባሕርይ ያለው ወንድ ጋር መግባባት ስላልቻለ ቁስሎቹ እንደ ቀሩ ብዙም ሳይቆይ ግልጽ ሆነ። ደስ የማይል ሥራ በተሰጠው ቁጥር፣ ይጠላኛል ብሎ ባሰበው ተቆጣጣሪ የተጣለበት ቅጣት አድርጎ ይወስደው ነበር። ያ ሥራ በዚያ ድርጅት ውስጥ ከማንኛውም ወጣት ሠራተኛ በተለምዶ የሚጠበቅ ሥራ መሆኑን ማየት አልቻለም።

ብዙ ጊዜ በሌሎች ሰዎች ድርጊት ወይም ቃል እንዴት እንደምንቆስልና እነዚያ ቁስሎች ኢየሱስ በመስቀል ላይ በገዛልን ነጻነት ተራምደን እንዳንኖር እንዴት እንደሚያደናቅፉን አስረዳሁት።

ቶኒ አስተማሪው ነፍሱን ለማቁሰል በሰይጣን እንዴት ጥቅም ላይ እንደ ዋለ ተረዳ። ያንን አስተማሪ ይቅር ለማለትና ጌታም ይቅር እንዲለው ለመለመን ሲመርጥ አብረን ጸለይን። ስለ አስተማሪው ቤተሰብ፣ በተለይም ወላጆቻቸውን እጅግ ያሳዝኑ ስለ ነበሩት ስለ ዓመፀኞቹ ወንዶች ልጆቹ ለመጸለይ ራሱን ሰጠ።

ብዙም ሳይቆይ ሌላ የሥራ ዕድል ተከፈተ፤ ቶኒም አመለከተ። ሥራውን አገኘ፤ በጥቂት ቀናትም ውስጥ ጀመረ።

ከአንድ ዓመት በኋላ ከሥራ ባልደረቦቹ ጋር እጅግ መልካም ግንኙነት ስለ መሠረተ የሠራተኞች ኃላፊ ሆኖ ተሾመ። የድርጅቱ ባለቤትም እንዳሉት፦ «ማንኛውንም ሥራ ልትሰጠው ትችላለህ፤ በሚገባ እንደሚሠራውም ታውቃለህ። የምተማመንበት ሰው ነው!» እግዚአብሔር መልካም ሥራ ሠርቶ ነበር።

ገጽ 1 / 1 · 8 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል