ምዕራፍ 11 · 4 ደቂቃ ንባብ
የእኛ ምላሽ
የእግዚአብሔር ቅድሚያ የሰይጣንም ቅድሚያ ነው!
ይህንን እርግጠኞች መሆን እንችላለን! እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለው ዓላማ ምንም ይሁን ምን፣ ሰይጣን ያንን ሥራ ለማደናቀፍ የሚችለውን ሁሉ ያደርጋል። አማኞች በአንድነት እንዲኖሩ የጌታ ፍላጎት ከሆነ፣ ጠላት ያንን አንድነት ለማደናቀፍ እጅግ ተግቶ ይሠራል።
መጽሐፍ ቅዱስን ስናጠና ግንኙነቶች በእግዚአብሔር የቅድሚያ ዝርዝር ላይ ከፍ ያለ ስፍራ እንዳላቸው በጣም ግልጽ ነው። ለራሱና እርስ በርሳችን እንድንኖር ፈጥሮናል። መጽሐፍ ቅዱስ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ግንኙነትን ያጎላል፦ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር፣ ሰውም ከሰው ጋር።
በዘፍጥረት እግዚአብሔር ሰውን በመልኩ ፈጠረው - አብረው ኅብረት እንዲኖራቸው (1ኛ ዮሐንስ 1:3)። ከዚያም «ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም» ስለ ሆነ ለሰውየው ሴትን ፈጠረለት (ዘፍጥረት 2:18)።
በኋላም ልዩ ሕዝብ የሚወጣበትን አንድ ሰው መረጠ። ራሱን «የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክና የያዕቆብ አምላክ» ብሎ ጠራ፤ ለዘሮቻቸውም አባትና ባል ሆነ።
ሰይጣን ከሰዎች ራሳቸው ብዙ እርዳታ በማግኘት እነዚህን ግንኙነቶች ለማፍረስ የሚችለውን ሁሉ አደረገ! ዛሬም ሰዎችን ከእግዚአብሔር ለማራቅ፣ ቤተሰቦችን ለመበተንና አይሁድን ለማጥፋት አሁንም በብርቱ ትጋት እየሠራ እንደ ሆነ እወቅ።
ብሉይ ኪዳን ግንኙነቶችን በሚመለከት በአንድ ድንቅ ተስፋ ይደመደማል፦ «እኔ መጥቼ ምድርን በእርግማን እንዳልመታ፥ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች፥ የልጆችንም ልብ ወደ አባቶች ይመልሳል» (ሚልክያስ 4:6)።
የአዲስ ኪዳን አጽንዖትም እንደ ብሉይ ኪዳን ተመሳሳይ ነው፤ ለምስክርነታቸው መሠረት እንዲሆን በአንድነት የመኖር ተጨማሪ ኃላፊነት በአማኞች ላይ ተጨምሮበታል።
የአዲስ ኪዳን ዋና ዋና ክፍሎች ይህንን እውነት ያጎላሉ፤ በመጨረሻው ምዕራፍ ግብዣም ይደመደማሉ፦ «መንፈሱና ሙሽራይቱም። ና ይላሉ!» (ራእይ 22:17)። «ሙሽራ» እንደ «አካል» ሁሉ የግንኙነት ቃል ነው!
የተዛባ ቤተሰብ ቍስሎች
ጌታ አንድን ወንድ ወይም ሴት በክፉ ላይ በሚደረገው ውጊያ ውጤታማ የሆነ ኃያል ተዋጊ እንዲሆን ሊያበስል ቢፈልግ፣ ጠላት ያንን ወታደር ገና እንደ ምልምል ወደ ሠራዊቱ ሳይገባ በፊት «ሽባ» ሊያደርገው ይሞክራል።
ሰይጣን ሁሉን አዋቂ አይደለም፤ ስለዚህም የወደፊት ሕይወትህን አያውቅም። በየደቂቃው ከአንተ ጋር ለመታገል በሁሉ ስፍራ የሚገኝም አይደለም፤ ስለዚህ በውጊያው «የሽምቅ ውጊያ» ስልቶችን መጠቀም አለበት፤ ወታደሮቹም (አጋንንት) «ቢመታም ቢስትም» የሚል አሠራር ይከተላሉ። ግልጽ «ምቶች» ከ«ጤናማ ያልሆኑ» ቤተሰቦች እንደ መጡ ተደርገው በሚመደቡት ሰዎች ከፍተኛ ቍጥር ይታያሉ።
ዓለማዊና ክርስቲያን አማካሪዎች ሰዎች ቍስሎቻቸውን - የተዛባውን ሕይወታቸውን - እንዴት እንደሚይዙ ለማስተማር ብዙ ሰዓታትን ያጠፋሉ። ታካሚዎቻቸውን አማካሪዎቹ የሚሰጧቸውን «ምርኩዞች» በውጤታማነት መጠቀምን ወደሚማሩበት «የመቆያ» ደረጃ ለማድረስ ተስፋ ያደርጋሉ። ለምሳሌ፣ የአልኮሆሊክስ አኖኒመስ (የአልኮል ሱሰኞች ስም-አልባ ማኅበር) ግብ አባላቱን ወደ ፈውስ ከማምጣት ይልቅ ከመጠጥ ርቀው መቆየት እንዲችሉ ማድረግ ነው።
የሚያሳዝነው ብዙ ክርስቲያን አማካሪዎች እነዚህን ቍስሎች ለመያዝ ዓለማዊ ዘዴዎችንና መሣሪያዎችን ተቀብለዋል፤ ሰዎቻቸውን ኢየሱስ በመስቀል ላይ ወዳስገኘው የፈውስ ስፍራ እምብዛም አያደርሱም። «በእርሱ ቍስል እኛ ተፈወስን» (ኢሳይያስ 53:5)።
የሰይጣን ዘዴዎች በክርስቶስ የቀረበላቸውን መዳን ፈጽሞ ስለማይቀበሉ በእርሱ ላይ ወደሚዋጋው ሠራዊት ፈጽሞ የማይገቡትን ብዙዎችን ያቆስላሉ። ይሁን እንጂ አንድ ሰው በክርስቶስ አካል ውስጥ እንዳለ ሲታወቅ፣ ሰይጣን በተለይም ያ ሰው በእርሱ ላይ ማጥቃት ከጀመረ ጥረቱን በዚያ ሰው ላይ ያተኩራል።
የማስታረቅ አገልግሎት
ኢየሱስ በሰዎች ሕይወት ውስጥ ያለውን የሰይጣን ኃይል ድል ለማድረግ መጣ። በእርሱ አዲሱ ግንኙነታችን እንደ አማኞች በአንድነታችን - እንደ አንድ አካል - መገለጥ አለበት። ሰይጣን ይህንን አንድነት ወይም እነዚህን ግንኙነቶች የማጥፋት ኃይል የለውም፤ እኛ ግን ባለማወቅ፣ በሥጋዊነትና በነፍሳችን ጤናማ ባልሆኑ ቍስሎች ምሽጎችን ሰጥተነዋል።
ይህንን ሁኔታ ለማስተካከል ምን ማድረግ እንችላለን? በእርግጥ መጸለይ እንችላለን! ለመሆኑ ያለ መንፈስ ቅዱስ እርዳታና አመራር ምንም ማድረግ አንችልም! ይሁን እንጂ አብ ሥልጣኑንና ኃላፊነቱን አስቀድሞ ለእኛ በሰጠባቸው ጉዳዮች ጸሎትን እምብዛም እንደማይመልስ መገንዘብ አለብን። በሰዎች መካከል የማስታረቅ ኃላፊነት ከእንግዲህ የእርሱ አይደለም፤ የእኛ ነው። «ነገር ግን የሆነው ሁሉ፥ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን፥ ከእግዚአብሔር ነው፤ እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፥ በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ» (2ኛ ቆሮንቶስ 5:18-19)።
ቅያሜዎቻችንን መፍታት፣ «ቍስሎቻችንን» ለመረዳት መፈለግና ፈውስን፣ መታደስንና እርቅን ለማግኘት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መርሖችን መጠቀም ያስፈልገናል። ቆስለህ ከሆነ፣ ዳዊት እንዳወቀው «ነፍሴን መለሳት» (መዝሙር 23:3)፣ እንዲሁም «ልጁ አርነት ቢያወጣችሁ በእውነት አርነት ትወጣላችሁ» (ዮሐንስ 8:36) የሚለውን አውቀህ፣ ይህ የመጽሐፉ ክፍል በክርስቶስ ወደ ሙሉነት ስፍራ ለመድረስ አንዳች እርዳታ እንደሚሰጥህ እተማመናለሁ።
የተሰናከለው በግ
አማካሪዎች፣ ሽማግሌዎች ወይም ፓስተሮች ለሆናችሁ፣ ይህ አገልግሎታችሁ እንደ ሆነ አደራ እላችኋለሁ። እንደ ፓስተርና አማካሪ እጅግ የሚፈታተነኝ የመጽሐፍ ክፍል በማቴዎስ 18 ላይ ይገኛል። የዚህ ምዕራፍ አጠቃላይ ዐውድ ስለ ቅያሜ፣ ስለ መታደስ፣ ስለ እርቅና ስለ ይቅርታ የሚናገር ነው።
በተለይ እረኛውንና መቶዎቹን በጎች በሚመለከተው የማቴዎስ ምሳሌ እፈተናለሁ፤ እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፦ «ለአንድ ሰው መቶ በጎች ቢኖሩት ከእነርሱም አንዱ ቢባዝን፥ ዘጠና ዘጠኙን በተራራ ትቶ ሄዶም የባዘነውን አይፈልግምን? ቢያገኘውም፥ እውነት እላችኋለሁ፥ ካልባዘኑቱ ከዘጠና ዘጠኙ ይልቅ በእርሱ ደስ ይለዋል» (ማቴዎስ 18:12-14)።
ከበረቱ የወጣው በግ ነው እንጂ ፍየል አይደለም። በአዲስ ኪዳን አማኞች ብዙውን ጊዜ «በጎች» ተብለው ይጠራሉ፤ «ፍየል» የሚለው ቃል ግን ለማያምኑ ሰዎች ይውላል።
ይህ ሥዕል ቅር ተሰኝቶ ምናልባትም ለሚሰማው ሁሉ ለማሰራጨት የተዘጋጀ ትንሽ መርዝ ይዞ ከቤተ ክርስቲያን የወጣውን አማኝ ያሳያል። ሁላችንም ይህ በጉባኤዎቻችን ውስጥ ደርሶብናል፤ ብዙ ጊዜም እጆቻችንን እያሻሸን «እሰይ ተገላገልን! እንዴት ያለ አስቸጋሪ ሰው ነበር!» ለማለት እንፈተናለን። ይልቁንም ያንን በግ እንድንከተለው፣ ልንረዳውና ያለ ኵነኔ ልናገለግለው እንድንፈልግ፣ ጌታም እርቅንና መታደስን እንደሚያመጣ እንድንታመን እንመከራለን። ይህንን ብናደርግ ኖሮ ምናልባት በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ «አስቸጋሪ ሰዎች» እጅግ ጥቂት ይሆኑ ነበር!
አንዳንድ ጊዜ በጉ በጥልቅ ቆስሎ ይሄዳል። አንዲት ወጣት ሴት በጥልቅ ተጎድታ ወደ እኔ የመጣችበትን አስታውሳለሁ፤ የ«አገልግሎቷ» መሪዎች ስለ እርሷ አንዳንድ መጥፎ ሪፖርቶችን ተቀብለው ቀጥተዋት ነበር፤ ይሁን እንጂ ሪፖርቶቹ ምን እንደሚሉ ማንም ሊነግራት አልፈለገም። መሪዎቿን ለማየት ሄድሁ፤ ዋናው ፈራጇም «ትምህርት እንድታገኝ በገዛ ጦሷ እንድትብሰለሰል እየተውናት ነው» ብሎ ነገረኝ። ራሱን እንደ ፓስተር ለሚቆጥረው ለዚያ መሪ በጎቹን እንዲህ እንድናደርግ ፈቃድ እንደሌለን ነገርሁት።
«አንድ በግ በእሾህ ቍጥቋጦ ውስጥ ቢያዝ፣ በእሾህ ብቧጨርም የተጎዳውም በግ ሊነክሰኝ ቢችልም ነፃ ለማውጣት ተሳብቤ መግባት አለብኝ። ከዚያም ዘይትና ወይን አፍስሼ ቍስሎቹን እጠግናለሁ፤ ከዚያም ዳግመኛ ወደ እሾህ ቍጥቋጦ እንዳይገባ መክሬ በጉን እለቀዋለሁ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ እንደገና ሲጮህ ሰምቼ በጉን በሌላ ቍጥቋጦ ውስጥ ካየሁት፣ ያንኑ ሂደት እደግማለሁ። ይህም በተጨማሪ ምክርና ምናልባትም በገመድ በመጠቀም ይቀጥላል፤ ነገር ግን ከቍጥቋጦው ውጭ ቆሜ ጣቴን እየነቀነቅሁ ‹ይገባሃል!
በገዛ ጦስህ ተብሰልሰል!› ማለት ፈጽሞ አልችልም። ታላቁ እረኛ በሥሩ ያለ እረኛ ሆኜ እንዳገለግል በጠራኝ ጊዜ እንዲህ ያለ ፈቃድ አልሰጠኝም!»
ምንም እንኳ በእርሷ ላይ የቀረቡት ሪፖርቶች በውሸት ላይ የተመሠረቱ እንደ ነበሩ ለመሪዎቿ በግልጽ ያሳየኋቸው ቢሆንም፣ ያቺ ወጣት ሴት ከዚያ አገልግሎት ተሰናበተች! ይህን ያህል ክፉኛ መቍሰሏና ረጅም የባለሙያ ምክር ማስፈለጉ ምንም አያስደንቅም!
ምዕራፍ 11 ተጠናቋል
የእኛ ምላሽ