ክርስቶስን መምሰል
በጕድለት በወደቁ ጊዜ ከልክ በላይ አለመተከዝ

ምዕራፍ 95 · 1 ደቂቃ ንባብ · 2 ደቂቃ ማዳመጥ

በጕድለት በወደቁ ጊዜ ከልክ በላይ አለመተከዝ

ክርስቶስ፦

ልጄ ሆይ፥ ነገሮች መልካም በሚሄዱበት ጊዜ ከሚገኝ ብዙ መጽናናትና የአምልኮ ትጋት ይልቅ በመከራ ጊዜ ያለ ትዕግሥትና ትሕትና በእኔ ዘንድ የበለጠ ደስ የሚያሰኙ ናቸው።

በአንተ ላይ በተነገረ በትንሽ ነገር ለምን ታዝናለህ? ከዚያ የበለጠ ቢሆን እንኳ ልትነካ አይገባህም ነበር። አሁን ግን ይለፍ። የመጀመሪያው አይደለም፤ አዲስ ነገርም አይደለም፤ ብዙ ዘመን ብትኖርም የመጨረሻው አይሆንም።

ተቃውሞ እስካልገጠመህ ድረስ በቂ ጀግንነት አለህ። ለሌሎች መልካም ምክር ትሰጣለህ፤ በቃልም እንዴት እንደምታበረታቸው ታውቃለህ፤ ያልተጠበቀ መከራ ደጃፍህን ሲያንኳኳ ግን በምክርም በብርታትም ትደክማለህ። እንግዲያስ በትንንሽ ነገሮች ብዙ ጊዜ የምታየውን ታላቅ ድካምህን አስብ። ይሁን እንጂ እነዚህና እንደ እነዚህ ያሉ ፈተናዎች ሲደርሱብህ ለበጎህ ይደርሳሉ።

በምታውቀው መጠን ከልብህ አውጣው፤ ቢነካህም እንኳ ለረጅም ጊዜ እንዲያወድቅህ ወይም እንዲያደናግርህ አትፍቀድለት። በደስታ ልትሸከመው ባትችል ቢያንስ በትዕግሥት ተሸከመው። ሳትወድ ብትሸከመውና ብትቈጣበትም እንኳ ራስህን ግታ፤ ደካሞች የሚሰናከሉበት ሥርዓት የሌለው ቃል ከከንፈሮችህ አይውጣ። አሁን የተነሣው ማዕበል ፈጥኖ ጸጥ ይላል፤ ውስጣዊ ኀዘንህም በሚመለሰው ጸጋ ይጣፍጣል። «እኔ ገና ሕያው ነኝ» ይላል ጌታ፤ «በእኔ ብትታመንና በአምልኮ ብትጠራኝ ልረዳህና ከፊት ይልቅ አብልጬ ላጽናናህ ዝግጁ ነኝ።»

ጸጥ ብለህ ኑር፤ ከዚህም የበለጠ ፈተና ለመሸከም ተዘጋጅ። ብዙ ጊዜ ብትታወክ ወይም በብርቱ ብትፈተን እንኳ ሁሉ ነገር አልጠፋም። አንተ ሰው ነህ እንጂ እግዚአብሔር አይደለህም። ሥጋ ነህ እንጂ መልአክ አይደለህም። በሰማይ ያሉ መላእክትና በገነት የነበረው ፊተኛው ሰው እንኳ ይህን ማድረግ ተስኗቸው ሳለ፣ አንተ ሁልጊዜ በአንድ ዓይነት የበጎ ምግባር ሁኔታ ልትኖር እንዴት ትጠብቃለህ? የተጨነቁትን የማድን፣ ድካማቸውን የሚያውቁትንም ወደ መለኮቴ የማመጣ እኔ ነኝ።

ደቀ መዝሙሩ፦

አቤቱ፣ ለአፌ ከማርና ከማር ወለላ ይልቅ የሚጣፍጡ ቃሎችህ የተባረኩ ይሁኑ። በቅዱስ ቃሎችህ ባታበረታኝ ኖሮ በእንደዚህ ያለ ታላቅ መከራና ጭንቀት ውስጥ ምን ባደረግሁ ነበር? የመዳንን ወደብ ብቻ ባገኝ ምንም ዓይነትና ምን ያህል መከራ ብቀበል ምን ይደንቃል? መልካም ፍጻሜን ስጠኝ። ከዚህ ዓለም ደስ የሚያሰኝ መሻገርን ስጠኝ። አምላኬ ሆይ፣ አስበኝ፤ በቀና መንገድም ወደ መንግሥትህ ምራኝ።

ገጽ 1 / 1 · 1 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል
ቀዳሚ ቀጣይ