ምዕራፍ 90 · 1 ደቂቃ ንባብ · 2 ደቂቃ ማዳመጥ
ራስን ለመጽናናት ሳይሆን ለቅጣት የተገባ አድርጎ መቍጠር
ደቀ መዝሙሩ፦
ጌታ ሆይ፣ ለመጽናናትህም ሆነ ለማንኛውም መንፈሳዊ ጕብኝት የተገባሁ አይደለሁም። ስለዚህ ድሀና ብቸኛ አድርገህ ስትተወኝ በጽድቅ ታደርግብኛለህ። የእንባ ባሕር ባፈስስ እንኳ ለመጽናናትህ የተገባሁ አልሆንም። ስለዚህ ብዙ ጊዜና በጽኑ ስለ በደልሁህ፣ በብዙ ነገርም እጅግ ስለ ኃጢአትሁ ልገረፍና ልቀጣ ብቻ ይገባኛል። እንግዲህ በፍጹም ጽድቅ ለማንኛውም መጽናናት የተገባሁ አይደለሁም።
ነገር ግን ሥራዎችህ እንዲጠፉ የማትወድ ቸርና መሐሪ አምላክ ሆይ፣ አንተ የቸርነትህን ባለ ጠግነት ለምሕረት ዕቃዎች ታሳይ ዘንድ፣ ከሚገባው ሁሉ በላይና ከሰው ልክ በላይ ባሪያህን ለማጽናናት ዝቅ ትላለህ። መጽናናትህ እንደ ሰዎች ቃል አይደለምና።
ጌታ ሆይ፣ ማንኛውንም ሰማያዊ መጽናናት ትሰጠኝ ዘንድ ምን አደረግሁ? ምንም መልካም ነገር እንዳላደረግሁ፣ ነገር ግን ሁልጊዜ ለኃጢአት የፈጠንሁና ለመታረም የዘገየሁ እንደ ሆንሁ አስታውሳለሁ። ይህ እውነት ነው። ልክደው አልችልም። ሌላ ነገር ብናገር አንተ ትቃወመኛለህ፤ የሚከራከርልኝም አይኖርም። ስለ ኃጢአቴ ከሲኦልና ከዘላለም እሳት በቀር ምን ይገባኛል?
በእውነት ለንቀትና ለውርደት ሁሉ የተገባሁ መሆኔን እመሰክራለሁ። ለአንተ ከተሰጡ አገልጋዮችህ ጋር እታሰብ ዘንድም አይገባኝም። ይህን መስማት ቢከብደኝም፣ ምሕረትህን ለመለመን በቀላሉ እበቃ ዘንድ፣ ስለ እውነት ብዬ ኃጢአቴን በራሴ ላይ እመሰክራለሁ። በደለኛ የሆንሁና በኀፍረት ሁሉ የተሞላሁ እኔ ምን እላለሁ? አንደበቴ ከዚህ ብቻ በቀር ምንም ሊናገር አይችልም፦ «አቤቱ፥ በደልሁ፥ በደልሁ፤ ማረኝ፥ ይቅርም በለኝ። በጨለማና በሞት ጥላ ወደ ተሸፈነች ምድር ሳልሄድ ኀዘኔን አፈስስ ዘንድ ጥቂት ታገሠኝ።»
በደለኛና ጐስቋላ ከሆነ ኃጢአተኛ ስለ ኃጢአቱ እንዲጸጸትና ራሱን እንዲያዋርድ በቀር በተለይ ምን ትሻለህ? በእውነተኛ ኀዘንና በልብ ትሕትና የይቅርታ ተስፋ ይወለዳል፤ የታወከ ሕሊና ይታረቃል፤ ጸጋ ይገኛል፤ ሰው ከሚመጣው ቍጣ ይጠበቃል፤ እግዚአብሔርና ንስሐ የገባው ሰውም በቅዱስ አሳሳም ይገናኛሉ።
ጌታ ሆይ፣ ስለ ኃጢአት የሚሆን ትሑት ኀዘን በአንተ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሥዋዕት ነው፤ ከዕጣን መዓዛ እጅግ የሚጣፍጥ መሥዋዕት ነው። በተቀደሱ እግሮችህ ላይ እንዲፈስስ የወደድኸውም ደስ የሚያሰኘው ሽቱ ይህ ነው፤ የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ ከቶ አልናቅኸውምና። ከጠላት ቍጣ ኃይል የሚሸሸጉበት የመጠጊያ ስፍራ ይህ ነው። በሌላ ስፍራ የተገኘ ርኵሰት ሁሉ በዚህ ይታረማል፤ ይታጠባልም።
ምዕራፍ 90 ተጠናቋል
ራስን ለመጽናናት ሳይሆን ለቅጣት የተገባ አድርጎ መቍጠር