ምዕራፍ 51 · 1 ደቂቃ ንባብ · 1 ደቂቃ ማዳመጥ
የኢየሱስ ክርስቶስን አርአያ ተከትሎ በትሕትና የሚገዛ ሰው መታዘዝ
ክርስቶስ፦
ልጄ ሆይ፥ ከመታዘዝ ለማምለጥ የሚሞክር ራሱን ከጸጋ ያርቃል። እንዲሁም ለራሱ የግል ጥቅምን የሚፈልግ ለሁሉ የጋራ የሆነውን ያጣል። ለአለቃው በነጻነትና በፈቃዱ የማይገዛ፣ ሥጋው ገና ፍጹም እንዳልታዘዘ፣ ነገር ግን ብዙ ጊዜ እንደሚያምፅበትና እንደሚያጕረመርምበት ያሳያል።
እንግዲህ የራስህን ሥጋ ልታሸንፍ ብትወድ ለአለቃህ መገዛትን ፈጥነህ ተማር። የውስጥ ሰው ካልፈረሰ የውጭው ጠላት ይበልጥ ፈጥኖ ይሸነፋልና። ከመንፈስ ጋር ካልተስማማህ ለነፍስ ከአንተ ከራስህ የበለጠ አስቸጋሪ፣ የከፋም ጠላት የለም። በሥጋና በደም ላይ ድል ልትነሣ ብትወድ ራስህን በእውነት መናቅን ፈጽሞ ልትይዝ ያስፈልግሃል።
ገና ራስህን ከልክ በላይ ስለምትወድ ራስህን ፈጽመህ ለሌሎች ፈቃድ አሳልፈህ ለመስጠት ትፈራለህ። ሁሉን የምችል፣ ልዑል፣ ሁሉን ከምንም የፈጠርሁ እኔ ስለ አንተ ብዬ ራሴን በትሕትና ለሰው ካስገዛሁ፣ ትቢያና ምንምነት ብቻ የሆንህ አንተ ስለ እግዚአብሔር ብለህ ለሰው ብትገዛ ታላቅ ነገር ነውን? ትዕቢትህን በትሕትናዬ ታሸንፍ ዘንድ ከሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑትና ዝቅተኛ ሆንሁ።
አንተ ትቢያ ብቻ የሆንህ፣ መታዘዝን ተማር! አንተ መሬትና ጭቃ ብቻ የሆንህ፣ ራስህን ማዋረድን ተማር፤ ከሰውም ሁሉ እግር በታች ተጐንበስ! የራስህን ፈቃድ መስበርን፣ ለመገዛትም ሁሉ ራስህን ማስገዛትን ተማር! ራስህን ለመቃወም ቅና! ትዕቢት በአንተ እንዲኖር አትፍቀድ፤ ነገር ግን ሁሉ በላይህ እንዲራመዱና በመንገድ እንዳለ ትቢያ እንዲረግጡህ እንዲህ ትሑትና ዝቅተኛ መሆንህን አሳይ!
አንተ ከንቱ ሰው፣ የምታማርረው ምን አለህ? አንተ ጐስቋላ ኃጢአተኛ፣ እግዚአብሔርን ብዙ ጊዜ የበደልህና ብዙ ጊዜ ሲኦል የተገባህ ሆነህ ሳለ ለሚከሱህ ምን መልስ ልትሰጥ ትችላለህ? ነገር ግን ፍቅሬን ታውቅ ዘንድ፣ ለቸርነቴም ሁልጊዜ አመስጋኝ ትሆን ዘንድ፣ ራስህንም ዘወትር ለእውነተኛ መገዛትና ትሕትና ትሰጥ ዘንድ፣ ንቀትንም በትዕግሥት ትታገሥ ዘንድ፣ ነፍስህ በፊቴ የከበረች ስለ ሆነች ዓይኔ ራራችልህ።
ምዕራፍ 51 ተጠናቋል
የኢየሱስ ክርስቶስን አርአያ ተከትሎ በትሕትና የሚገዛ ሰው መታዘዝ