ምዕራፍ 45 · 2 ደቂቃ ንባብ · 3 ደቂቃ ማዳመጥ
ጸጋን በትሕትና መጐናጸፊያ ሥር መሰወር
ክርስቶስ፦
የአምልኮን ጸጋ መሰወር፣ በእርሱ አለመታበይ፣ ስለ እርሱም አብዝቶ አለመናገርና አለማሰብ፣ ይልቁንም ራስህን አዋርደህ ለማይገባው ሰው ተሰጥቶ ይሆናል ብለህ መፍራት ይሻልሃል፤ ለአንተም ይበልጥ አስተማማኝ ነው። ፈጥኖ ወደ ተቃራኒው ሊለወጥ ይችላልና በዚህ ስሜት ላይ እጅግ አትጣበቅ። በጸጋ ውስጥ ሳለህ ያለ እርሱ ምን ያህል ጐስቋላና ችግረኛ እንደ ሆንህ አስብ። በመንፈሳዊ ሕይወት ማደግህ የመጽናናትን ጸጋ በማግኘት አይደለም፤ ነገር ግን ጸጋው ሲወሰድብህ በትሕትና፣ ለእግዚአብሔር ፈቃድ በመገዛትና በትዕግሥት በመታገሥ ነው፤ ይኸውም በጸሎት እንዳትሰለች፣ ሌላውንም ተግባርህን በጥቂቱ እንኳ ቸል እንዳትል ነው። ይልቁንም የምትችለውን በምታውቀው መጠን በሚገባ አድርግ፤ ስለ ደረቅነትህ ወይም ስለ አእምሮህ ጭንቀት ብለህ ራስህን ፈጽመህ ቸል አትበል።
ነገሮች እንደሚፈልጉት ባልሄዱላቸው ጊዜ ወዲያው ትዕግሥት የሚያጡና የሚሰንፉ ብዙዎች በእርግጥ አሉ። ነገር ግን የሰው መንገድ ሁልጊዜ በራሱ እጅ አይደለም። በሚፈልግበት ጊዜ፣ በሚፈልገው መጠንና ለሚፈልገው ሰው፣ እርሱን ደስ እንዳሰኘው እንጂ ከዚያ ሳይበልጥ፣ ጸጋን መስጠትና ማጽናናት የእግዚአብሔር ብቻ መብት ነው።
አንዳንድ ግድ የለሽ ሰዎች የአምልኮን ጸጋ አላግባብ በመጠቀም ከአቅማቸው በላይ ለማድረግ ስለ ፈለጉ ራሳቸውን አጥፍተዋል። የራሳቸውን ድካም አላስተዋሉም፤ ከአእምሮአቸው ፍርድ ይልቅ የልባቸውን ምኞት ተከተሉ። ከዚያም እግዚአብሔርን ደስ ከሚያሰኘው በላይ ለታላላቅ ነገሮች ስለ ደፈሩ ጸጋውን ፈጥነው አጡ። መኖሪያቸውን በሰማይ የሠሩት እነርሱ፣ በራሳቸው ክንፍ መብረርን ሳይሆን በእኔ ክንፍ መታመንን ይማሩ ዘንድ፣ የተዋረዱና የደኸዩ፣ ረዳት የሌላቸውና የተናቁ ስደተኞች ሆኑ።
በጌታ መንገድ ገና አዲሶችና ልምድ የሌላቸው በአስተዋዮች ምክር ራሳቸውን ካልመሩ በቀላሉ ሊታለሉና ሊወድቁ ይችላሉ። ልምድ ባላቸው ሌሎች ሰዎች ከመታመን ይልቅ የራሳቸውን አሳብ ሊከተሉ ቢወዱ ግን፣ ቢያንስ ከከንቱነታቸው ሊመለሱ ካልፈቀዱ፣ ለክፉ ፍጻሜ ይጋለጣሉ። በራሳቸው ዓይን ጠቢባን የሆኑ የሌሎችን ምሪት በትሕትና የሚቀበሉት እምብዛም ነው። ቢሆንም በከንቱ ራስን በማድነቅ ከሚፈለግ ታላቅ የእውቀት መዝገብ ይልቅ በትሕትናና በየዋህነት የሚፈለግ ጥቂት እውቀት ይሻላል። የትዕቢት ምንጭ ሊሆንብህ የሚችል ብዙ ነገር ከመያዝ ጥቂት ቢኖርህ ይሻልሃል።
ራሱን ፈጽሞ ለደስታ አሳልፎ የሚሰጥ ሰው የቀድሞ ረዳት ማጣቱን፣ የቀረበለትን ጸጋ እንዳያጣ የሚሰጋውን ያንን የተገራ የጌታን ፍርሃትም ይረሳልና እጅግ ያለ ጥበብ ያደርጋል። በመከራና በችግር ጊዜ እጅግ ተስፋ የሚቈርጥ፣ ስለ እኔም ሊያስብ ከሚገባው ያነሰ በመተማመን የሚያስብ ሰውም እጅግ ብርቱ ወይም ጠቢብ አይደለም። በሰላም ጊዜ እጅግ ተዘልሎ መኖር የሚወድ በፈተና ጊዜ ብዙ ጊዜ እጅግ ይተክዛል፤ ይፈራልም።
ሁልጊዜ ትሑትና በራስህ ዓይን ታናሽ ሆነህ ለመኖር፣ መንፈስህንም በመልካም ለመግታትና ለመግዛት ጥበብ ቢኖርህ ኖሮ በዚህ ፍጥነት ወደ አደጋና ወደ በደል ባልወደቅህ ነበር።
የትጋት መንፈስ በውስጥህ በተቀጣጠለ ጊዜ፣ ትጋቱ ሲለይህ ምን እንደሚሰማህ ብታሰላስል መልካም ነው። ይህም በሆነ ጊዜ፣ ለማስጠንቀቂያህና ለራሴ ክብር ለጊዜው የወሰድሁት ብርሃን እንደ ገና ሊመለስ እንደሚችል አስብ። እንደዚህ ያሉ ፈተናዎች ነገሮች ሁሉ ሁልጊዜ እንደ ፈቃድህ ቢሆኑልህ ከሚሆነው ይልቅ ብዙ ጊዜ ይጠቅማሉ። የሰው ዋጋ የሚለካው በብዙ ራእይ ወይም መጽናናት፣ ወይም በቅዱሳት መጻሕፍት እውቀት፣ ወይም ከሌሎች በላይ ከፍ ባለ ማዕረግ በመገኘቱ አይደለም፤ ነገር ግን በትሕትናው እውነተኛነት፣ ለመለኮታዊ ፍቅር ባለው ብቃት፣ የእግዚአብሔርን ክብር በንጽሕናና በሙላት ለመፈለግ ባለው ጽናት፣ ራሱን ከቁም ነገር ባለመቍጠሩና በእርግጥም በመናቁ፣ ከዚህም በላይ በሌሎች ከመከበር ይልቅ መናቅንና መዋረድን በመምረጡ ነው።
ምዕራፍ 45 ተጠናቋል
ጸጋን በትሕትና መጐናጸፊያ ሥር መሰወር