የመጽናናት ሁሉ አምላክ
እግዚአብሔር ቸር ነው

ምዕራፍ 7 · 13 ደቂቃ ንባብ · 17 ደቂቃ ማዳመጥ

እግዚአብሔር ቸር ነው

«እግዚአብሔር ቸር እንደ ሆነ ቅመሱ እዩም! በእርሱ የሚታመን ሰው ብፁዕ ነው!» (መዝሙር 34:8)።

በልብህ ጥልቅ ውስጥ ስለ እግዚአብሔር በእውነት ምን እንደምታስብ—ቸር አምላክ እንደ ሆነ ወይስ ክፉ አምላክ እንደ ሆነ እንደምታምን—ራስህን ጠይቀህ ታውቃለህን? ጥያቄው እንደሚያስደነግጥህ፣ እግዚአብሔርን ክፉ አምላክ አድርገህ በምንም መንገድ ልታስብ ትችላለህ የሚለውንም ሐሳብ ስትሰማ እንደምትደነግጥ እገምታለሁ። ነገር ግን ይህን ምዕራፍ አንብባችሁ ከመጨረሳችሁ በፊት፣ ከእናንተ አንዳንዶቻችሁ ምናልባት ሳታውቁት ቢሆንም በእውነት ግን፣ በጥርጣሬያችሁና በማጕረምረማችሁ፣ ለራሳችሁ ቢሰጥ የምትደነግጡበትን ባሕርይ ለእርሱ እንደ ሰጣችሁት ለማመን እንደምትገደዱ እጠረጥራለሁ።

እግዚአብሔር በእውነት ቸር መሆኑን መጀመሪያ ያወቅሁባትን ሰዓት ፈጽሞ አልረሳትም። መጽሐፍ ቅዱስ ቸር እንደ ሆነ እንደሚናገር እርግጥ ሁልጊዜ አውቅ ነበር፤ ነገር ግን ይህ ማለት በሃይማኖታዊ መንገድ ብቻ ቸር ነው ማለት እንደ ሆነ አስብ ነበር፤ እኛ እንዲኖረን ያዘዘውን ያንኑ ዓይነት በጎነት ይዞ በእውነትና በተግባር ቸር ነው ማለት እንደ ሆነ ፈጽሞ አልገባኝም ነበር። «የእግዚአብሔር ቸርነት» የሚለው አነጋገር ልረዳው የማይጠበቅብኝ አንድ ዓይነት ሰማያዊ አባባል ከመሆን የሚያልፍ ነገር አይመስለኝም ነበር። ከዚያም አንድ ቀን መጽሐፍ ቅዱሴን ሳነብ «እግዚአብሔር ቸር እንደ ሆነ ቅመሱ እዩም» የሚሉትን ቃላት አገኘሁ፤ ቃላቱም ድንገት ትርጕም ሰጡኝ።

እግዚአብሔር ቸር ነው፣ ብዬ ለራሴ ደገምሁ። ቸር መሆን—መልካም መሆን—ምን ማለት ነው? ከዚህ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል፦ ሰው ከሚያውቀው ሁሉ የሚበልጠውንና ከፍ ያለውን ጠብቆ መኖር። መልካም መሆን ክፉ ከመሆን ፍጹም ተቃራኒ ነው። ክፉ መሆን ትክክለኛውን ነገር እያወቁ አለማድረግ ነው፤ መልካም መሆን ግን የምናውቀውን የሚበልጠውን ማድረግ ነው። እግዚአብሔርም ሁሉን ስለሚያውቅ ከሁሉ የሚበልጠውንና ከፍ ያለውን መልካም ነገር ማወቁ የግድ እንደ ሆነ፣ ስለዚህም ቸርነቱ ከጥያቄ በላይ መሆኑ የግድ እንደ ሆነ አየሁ። ይህ ለእኔ ምን ማለት እንደ ነበር ፈጽሞ ልገልጸው አልችልም። የእግዚአብሔርን እውነተኛና ተጨባጭ ቸርነት እንዲህ ባለ ሁኔታ ከማየቴ የተነሣ በእርሱ ጥበቃ ሥር ምንም ነገር ሊበላሽ እንደማይችል አየሁ፤ ማንም ሰው ዳግመኛ ሊጨነቅ የማይችል መሰለኝ።

ደግሞም ሁኔታዎች በእርሱ ላይ በመሰከሩ ጊዜና ደግነት አጕድሎአል፣ ቸል ብሎአል ወይም ግድ የለሽ ሆኖአል ብዬ እንድጠራጠር በተፈተንሁ ጊዜ ሁሉ፣ «እግዚአብሔር ቸር ነው» የሚለው ቃል ደጋግሞ ባለሁበት አስቆመኝ፤ ቸር የሆነ አምላክ እኔ የገመትኋቸውን ክፉ ነገሮች ሊያደርግ ይችላል ብሎ ማሰብ ፈጽሞ የማይታሰብ መሆኑን አየሁ።

ምናልባት በማናቸውም ሁኔታ፣ በልብህ ስውር ጥልቀት ውስጥ እንኳ፣ ክፉ የሆነውን ነገር ለእግዚአብሔር ልትሰጥ ትችላለህ ከሚለው ሐሳብ በድንጋጤ ትሸሽ ይሆናል። ሆኖም ከወዳጆችህ አንዱ ቢያደርጋቸው እጅግ አሳፋሪና ደግነት የጐደላቸው አድርገህ የምትቈጥራቸውን ነገሮች አድርጎአል ብለህ እርሱን ለመክሰስ አታመነታም። ለምሳሌ ክርስቲያኖች ችግር ውስጥ ይገባሉ፤ ሁሉ ነገር ጨለማ ይመስላል፤ የጌታም መገኘት አይሰማቸውም። ጌታ ትቶአቸው እንደ ሆነ መጠራጠር ይጀምራሉ፤ አንዳንድ ጊዜም በግድ የለሽነትና በቸልተኝነት እስከ መክሰስ ይደርሳሉ። እነዚህ ክሶች ጌታ የተስፋ ቃሉን አይጠብቅም፣ ሰብዓዊ ወዳጆቻቸው ሁሉ እንዲያደርጉላቸው በሚጠብቁት ያህል በደግነትና በክብር አይይዛቸውም ከማለት ጋር አንድ እንደ ሆኑ ፈጽሞ አይገነዘቡም። ከሰብዓዊ ወዳጆቻችን አንዱ ችግር ስለ ደረሰብን ቢተወን፣ እንዲህ ያለውን ወዳጅ መልካም ከመሆን እጅግ የራቀ አድርገን እንቈጥረዋለን። ታዲያ ጌታችንን በእንዲህ ያለ ድርጊት ለአንድ አፍታ እንኳ እንዴት ልንከስሰው እንችላለን? አይደለም፣ ውድ ወዳጄ፤ ጌታ ቸር ከሆነ—በሃይማኖታዊ መንገድ ብቻ ሳይሆን በእውነት ቸር ከሆነ—ይህ የሆነው እርሱ ራሱ በጎነት ነው ብሎ ያስተማረንን ከፍተኛውን መለኪያ ሁልጊዜ፣ በሁኔታዎች ሁሉ ጠብቆ ስለሚመላለስ ነው። በእርሱ ዘንድ ቸርነት ልክ በእኛ ዘንድ እንደሚሆነው፣ ከሚያውቀው ሁሉ የሚበልጠውንና ከፍ ያለውን ጠብቆ መኖር ማለት መሆን አለበት።

እንግዲህ በተግባር ይህ ማለት ለእኛ ካለበት ኃላፊነት አንዱንም ቸል እንደማይል፣ ሁልጊዜም በተቻለ መጠን በሚበልጠው መንገድ እንደሚይዘን ነው። ይህ የተለመደ አነጋገር ሊመስል ይችላል፤ አንተም፦ «ሁላችንም የምናምነው ይህንኑ ስለ ሆነ ይህን ለምን ትነግሪናለሽ?» ብለህ ትጮኽ ይሆናል። ግን በእርግጥ ታምናለህን? ብታምን ኖሮ ቸልተኛ፣ ወይም ግድ የለሽ፣ ወይም ደግነት የጐደለው፣ ወይም ራሱን ብቻ የሚያስብ፣ ወይም ለሌሎች አሳቢነት የሌለው ነው ብለህ ማሰብ ይቻልህ ነበርን?

የጽድቅ መልክ አሳይታችሁ፦ «ኧረ፣ እኔ እንዲህ ባሉ ነገሮች ፈጽሞ አልከስሰውም፤ አልደፍርም» አትበሉ። በእርግጥ አትከስሱትምን? እናንተ ራሳችሁ ብታደርጉት የምታፍሩበትን ነገር አድርጎአል ብላችሁ ወቅሳችሁት አታውቁምን? ያ የመጨረሻው የሚያሠቃይ ተስፋ መክሸፍ በመጣ ጊዜ እንዴት ነበር? እርሱን ለማገልገል አጥብቃችሁ እየጣራችሁ ሳላችሁ እንዲህ ያለ ነገር እንዲደርስባችሁ በመፍቀዱ ጌታ ደግነት እንዳጐደለ አልተሰማችሁምን? ፈቃዱን እርግጥ ልትገዙለት የሚገባ፣ ነገር ግን በምንም መንገድ ሊወደድ የማይችል አምባገነንና ጨቋኝ ፈቃድ አድርጋችሁ አትመለከቱትምን? «ፈቃድህ ትሁን» ማለት አንዳንድ ጊዜ ከባድ ነገር አይመስላችሁምን? ነገር ግን ጌታ ቸር እንደ ሆነ፣ ሁልጊዜም በጎ የሆነውን እንደሚያደርግ በእውነት ብታምኑ ኖሮ ይህ ከባድ ሊመስል ይችል ነበርን?

ጌታ ኢየሱስ መልካም እረኛ እንደ ሆነ ሊነግረን እጅግ ተጠንቅቆአል፤ ሁኔታዎች ምን ያህል ጊዜ በእርሱ ላይ እንደሚመሰክሩ፣ እኛም ቸርነቱን ለመጠራጠር ምን ያህል እንደምንፈተን ያውቅ ነበርና። በአነጋገሩ ፍሬ ነገር እንዲህ ይላል፦ «መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ ክፉ እረኛ አይደለሁም። ክፉ እረኞች በጎቻቸውን ቸል ይላሉ፤ ይተዋቸውማል፤ እኔ ግን መልካም እረኛ ነኝ፤ በጎቼን ፈጽሞ ቸል አልልም፤ አልተዋቸውምም። ነፍሴን ስለ በጎቹ አኖራለሁ።» በእረኛ ዘንድ ያለው የበጎነት መለኪያው፣ እረኛው በእርሱ ጥበቃ ሥር የተሰጡትን በጎች በገዛ ነፍሱ ዋጋ እንኳ ቢሆን መጠበቅ እንዳለበት ነበር፤ እርሱም ራሱ ያስቀመጠውን መለኪያ ጠብቆ ኖረ። እንግዲህ እርሱ ቸር እንደ ሆነ—በሆነ ምሥጢራዊ፣ ሃይማኖታዊ መንገድ ሳይሆን በዚህ በተለመደው የጤናማ አእምሮ፣ ሰብዓዊ መንገድ—በእውነት ብናምን ወዲያውኑ ወደ ታላቅ ሰላምና መጽናናት ስፍራ እንደምንገባ አናይምን? እኔ በግ ከሆንሁና ጌታ በተለመደው፣ በጤናማ አእምሮ ትርጕም መልካም እረኛ ከሆነ፣ ምንኛ ፍጹም ተጠብቄአለሁ! በሁሉ ረገድ ከሁሉ የሚበልጠውን ጥበቃ እንደማገኝ ምንኛ እርግጠኛ መሆን እችላለሁ! ለዚህ ዘመንም ለዘላለምም ምንኛ ደኅና ነኝ!

ከራሳችን ጋር ሐቀኞች እንሁን። እግዚአብሔር በሕዝቅኤል መጽሐፍ የክፉ እረኛ ምልክቶች ናቸው ብሎ የነገረንን ጠባዮች በልባችን ስውር ውስጥ ለጌታ ሰጥተን አናውቅምን? ከእኛ ምቾት ይልቅ ለራሱ ምቾት ወይም ክብር ይበልጥ ያስባል ብለን አላሰብንምን? በደከምን ጊዜ እንዳላበረታን፣ የተሰበረውንም ልባችንን እንዳልጠገነ፣ በጠፋንም ጊዜ እንዳልፈለገን አላጕረመረምንምን?

እንዲያውም የታመመውን፣ ረዳት የሌለውንና የጠፋውን ሁኔታችንን ከእንግዲህ ወዲህ ከእኛ ጋር ምንም ጉዳይ የማይኖረው ስለ መሆኑ ምክንያት አድርገን አልተመለከትነውምን? ይህ ጌታ ክፉ እረኛ ነው፣ ለበጎቹም ያለበትን ኃላፊነት አይፈጽምም ብለን ፊት ለፊትና በግልጽ ከመናገር በምን ይለያል? ምናልባት ውስጣዊ ማጕረምረማችሁና ሮሮአችሁ በዚህ መልክ ሲተረጐም በድንጋጤ ትሸሹ ይሆናል፤ ነገር ግን በሐቅ ሲታይ ከዚህ ሌላ ምን ትርጕም ሊኖረው ይችላል? ብዬ እጠይቃችኋለሁ። ስለ ጌታ ያለን አመለካከት በእውነት ምን እንደ ሆነ እናይ ዘንድ፣ ስለ እርሱ ያሉንን ስውር አሳቦችና ስሜቶች አልፎ አልፎ ወደ መንፈስ ቅዱስ ሙሉ ብርሃን ጐትቶ ማውጣት እጅግ ወሳኝ ነው። ስለ እግዚአብሔር የተሳሳቱ አሳቦችን የማሰብ ልማድ ውስጥ መግባት እጅግ ቀላልና ገዳይ ነው፤ እነዚህም አሳቦች ሳናውቀው በሰፊ የጥርጣሬና የአለማመን ገደል ከእርሱ ይለዩናል።

ከምንም ነገር በላይ፣ ከኃጢአት እንኳ በላይ፣ ስለ እግዚአብሔር ያሉ የተሳሳቱ አሳቦች የመንፈሳዊ ሕይወታችንን መሠረት ይሸረሽራሉ፤ የፍቅሩንም ልብ ያሳዝናሉ። ይህን ከራሳችን መረዳት እንችላለን። ወዳጆቻችን በተሳሳተ መንገድ ሲፈርዱብንና ሳይረዱን ሲቀሩ፣ የምንንቀውንም ዓላማ ሲሰጡን የሚያሳዝነንን ያህል ሌላ ምንም አያሳዝነንም። ጌታንም ይህን ያህል የሚያሳዝነው ሌላ ነገር የለም ብዬ አምናለሁ። እንዲያውም ይህ ጣዖት ማምለክ ነው። ጣዖት ማምለክ የሐሰት አምላክ ፈጥሮ ማምለክ ካልሆነ ምንድር ነው? እኛስ በእርሱ ላይ በተሳሳተ መንገድ እንድንፈርድና ደግነት የጐደላቸውንና የማይታመኑ ድርጊቶችንና ስሜቶችን እንድንሰጠው ለራሳችን በፈቀድን ጊዜ የምናደርገው ይህንኑ ነገር ካልሆነ ምንድር ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ይህን በእግዚአብሔር ላይ መናገር ብሎ ይጠራዋል። «በእግዚአብሔር ላይ ተናገሩ፤ እንዲህም አሉ፦ ‹እግዚአብሔር በምድረ በዳ ማዕድ ሊያዘጋጅ ይችላልን?›» ይህ ለመጠየቅ እጅግ የዋህ ጥያቄ መስሎ ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔር በምድረ በዳ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ እንደሚያሟላ ተስፋ ሰጥቶ ነበር፤ ይህን ጥያቄ መጠየቅም እንደ ተናገረው ለማድረግ ባለው ችሎታ ላይ ስውር የመታመን ጕድለት እንዳለ የሚያመለክት ነበር፤ ስለዚህ የዋህ ቢመስልም በእውነት «በእርሱ ላይ መናገር» ነበር። ቸር አምላክ ሕዝቡን ወደ ምድረ በዳ መርቶ ከዚያ በኋላ «ማዕድ ማዘጋጀት» ሊያቅተው አይችልም ነበር፤ ይህን ማድረግ ይችል እንደ ሆነ መጠየቅም ቸር አይደለም ብሎ እንደ መናገር ነበር።

በተመሳሳይ መንገድ እኛም አንዳንድ ጊዜ ተመሳሳይ ጥያቄ ለመጠየቅ ክፉኛ እንፈተናለን። ሁኔታዎች እግዚአብሔር የሚያስፈልገንን ማሟላት የማይቻለው እስኪመስል ድረስ ብዙ ጊዜ ያደርጉታል፤ ስለዚህ ይችል እንደ ሆነ በመጠየቅ «በእርሱ ላይ ለመናገር» ደጋግመን እንፈተናለን። ከዚህ በፊት ብዙ ጊዜ ያደረገው ቢሆንም፣ እንደ ገና ሊያደርገው እንደሚችል ማመን ያቃተን ይመስላል፤ ቃሉን ስለማናምንና በቸርነቱ ስለማንታመን በልባችን «እንወስነዋለን»።

እምነታችን መሆን እንደሚገባው ቢሆን ኖሮ፣ የቱንም ያህል የማይመቹ ቢሆኑ ምንም ሁኔታዎች የሚያስፈልገንን ለማሟላት ያለውን የእግዚአብሔርን ኃይል «እንድንወስን» ሊያደርጉን አይችሉም ነበር። ሁኔታዎችን ሊፈጥር የሚችል አምላክ በእርግጥ ሁኔታዎችን ሊገዛ ይችላል፤ በምድረ በዳም እንኳ በእርሱ ለሚታመኑ ሁሉ «ማዕድ ሊያዘጋጅ» ይችላል።

በእግዚአብሔር ቸርነት ላይ ጥርጣሬ የሚጥሉ ብዙ ተመሳሳይ ጥያቄዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛሉ፤ እያንዳንዳቸውም ዛሬ የእግዚአብሔር ልጆች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች ቅጂ እንደ ሆኑ እፈራለሁ።

«እግዚአብሔር በመካከላችን አለን ወይስ የለም?»

«እግዚአብሔር ምሕረት ማድረግን ረሳን?»

«የእግዚአብሔር ምሕረት ለዘላለም ፈጽሞ ተቈረጠን?»

«እግዚአብሔር በቍጣው ርኅራኄውን ዘጋን?»

«የእግዚአብሔር የተስፋ ቃል ለዘላለም ይከሽፋልን?»

«አቤቱ፥ ለዘላለም ስለ ምን ጣልኸን?»

«ስለ ምን እንዲህ አድርገህ ሠራኸኝ?»

እስቲ እነዚህን ጥያቄዎች ለጥቂት እንመርምራቸው፤ በራሳችን ስውር ጥያቄዎች ውስጥ አምሳያዎቻቸውን እናገኝ እንደ ሆነም እንመልከት።

«እግዚአብሔር በመካከላችን አለን ወይስ የለም?»

ለእስራኤል ልጆች እንዳደረገው፣ ሁልጊዜ ከእኛ ጋር እንደ ሆነና ፈጽሞ እንደማይተወን በማያሻማ ቃል ነግሮናል፤ ሆኖም ችግር በመጣ ጊዜ እኛም እንደ እነርሱ ቃሉን መጠራጠርና በእውነት በዚያ ሊኖር ይችል እንደ ሆነ መጠየቅ እንጀምራለን። እስራኤላውያን ይህን ባደረጉ ጊዜ ሙሴ «እግዚአብሔርን መፈታተን» ብሎ ጠራው፤ እኛ ስናደርገውም ያንኑ ፍርድ ይገባዋል። በጌታ እውነተኛነትና ታማኝነት ላይ ጥርጣሬ ሳይጥል እንዲህ ያለውን ጥያቄ ሊጠይቅ የሚችል ማንም የለም፤ መጠየቁም፣ ብናውቀው ኖሮ፣ እርሱን መስደብና ስሙን ማጥፋት ነው። ወዮ! ይህ በእግዚአብሔር የገዛ ልጆች መካከል እንኳ የተለመደ ጥያቄ እንደ ሆነ አውቃለሁ፤ ደግሞም ብዙዎቹ ይህን መጠየቅ እውነተኛ ትሕትና ብቻ እንደ ሆነ፣ ራሳቸውን እንደሚቈጥሩት ላሉ የማይገባቸው ፍጥረታትም እርሱ ከእነርሱ ጋር መሆኑን እርግጠኞች መሆን የድፍረት ጥግ እንደ ሆነ እንደሚያስቡ አውቃለሁ።

ነገር ግን በዚህ ጉዳይ የእርሱ የገዛ ቃል ምን ይላል? ከእኛ ጋር እንደ ሆነ፣ ፈጽሞም እንደማይለቀንና ከቶም እንደማይተወን በተቻለው መንገድ ሁሉ ነግሮናል፤ ታዲያ የቃሉን እውነትነት በመጠራጠር እርሱን «ሐሰተኛ ልናደርገው» እንደፍራለንን? ቸር አምላክ ሊዋሽ አይችልም፤ እንዲህ ያለውን ጥያቄ መጠየቅ ለዘላለም መተው አለብን። እኛ ከራሳችን ጋር እንዳለን ያህል ጌታ በእውነት ከእኛ ጋር ነው፤ ሁኔታው ምንም ቢመስል ከእኛ ጋር እንደ ሆነ በቀላሉ ማመን ግድ ነው።

«እግዚአብሔር ምሕረት ማድረግን ረሳን?»

ይህን ጥያቄ መጠየቅ አንዲትን መልካም እናት ልጅሽን ረሳሽን? ብሎ እንደ መጠየቅ ያህል ክፉኛ «በእርሱ ላይ መናገር» ነው። ሆኖም ጌታ ራሱ እንዲህ ይላል፦ «በውኑ ሴት የምታጠባውን ሕፃንዋን ትረሳ ዘንድ ትችላለችን? አዎን፥ እነዚህ ይረሱ ይሆናል፥ እኔ ግን አልረሳሽም።» እናቶች የሆንን ሰዎች ልጆቻችንን ልንረሳ እንደምንችል አንድ ሰው ቢጠቁም ምን ያህል እንደምናዝንና እንደምንሰደብ በሚገባ እናውቃለን፤ ሌላ ማንም ባይረዳ እንኳ፣ ቢያንስ እኛ እናቶች እንዲህ ያለው ጥያቄ ጌታን እንዴት እንደሚያሳዝነው መረዳት መቻል አለብን።

«የእግዚአብሔር ምሕረት ለዘላለም ፈጽሞ ተቈረጠን?» «እግዚአብሔር በቍጣው ርኅራኄውን ዘጋን?»

እነዚህን ሁለት ጥያቄዎች ቸር የሆነውን አምላክ መጠየቅ እርሱን መስደብ ነው። የእናት ርኅራኄ ማለቁ የማይቻል እንደ ሆነ ሁሉ፣ ርኅራኄው በእኛ ላይ መዘጋቱ ወይም ምሕረቱ ለዘላለም ከእኛ መራቁ የማይቻል ነው። መዝሙረኛው እንዲህ ይላል፦ «እግዚአብሔር ለሁሉ ቸር ነው፥ ምሕረቱም በሥራው ሁሉ ላይ ነው።» እርሱ ቸር አምላክ ስለ ሆነና ሌላ ማድረግ ስለማይችል፣ በነገሮች ባሕርይ ራሱ ይህ እንዲሁ መሆኑ የግድ ነው።

«የእግዚአብሔር የተስፋ ቃል ለዘላለም ይከሽፋልን?»

በእያንዳንዱ ክርስቲያን ሕይወት ይህን ጥያቄ ለመጠየቅ የምንፈተንባቸው ጊዜያት ይመጣሉ። ሁሉ ነገር የተበላሸ ይመስላል፤ የእግዚአብሔርም የተስፋ ቃሎች ሁሉ የከሸፉ ይመስላሉ። ነገር ግን ጌታ ቸር እንደ ሆነ ብናስታውስ፣ እንዲህ ያለው ነገር ቢሆን ኖሮ ቸር መሆኑ እንደሚቀር እናያለን። የተስፋ ቃሉን የሚያፈርስ ሰው ክብር የሌለውና የማይታመን ሰው ተደርጎ ይቈጠራል፤ የገዛ ተስፋ ቃሉን ሊያፈርስ የሚችል አምላክም፣ ይህን ማሰብ ቢቻል እንኳ፣ ክብር የሌለውና የማይታመን ይሆን ነበር። እንዲህ ያለውንም ጥያቄ መጠየቅ «በእግዚአብሔር ላይ መናገር» ተብሎ ሊጠራ የሚገባውን ነቀፋ በቸርነቱ ላይ መጣል ነው። ጉዳዮች ምንም ቢመስሉ፣ እግዚአብሔር ቸር ስለ ሆነ ከተስፋ ቃሎቹ አንዱም ከቶ እንዳልከሸፈ፣ ሊከሽፍም እንደማይችል ይህን እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።

ሰማይና ምድር ያልፋሉ፥ ቃሉ ግን ከቶ አያልፍም።

«አቤቱ፥ ለዘላለም ስለ ምን ጣልኸን?»

መልካም እናት ልጅዋን መጣል እንደማይቻላት ሁሉ፣ ቸር አምላክ እኛን መጣል አይቻለውም። በችግርና በጨለማ ውስጥ ልንሆን፣ እንደ ተጣልንና እንደ ተተውን ሊሰማን ይችላል፤ ነገር ግን ስሜቶቻችን ከሐቆች ጋር ምንም ግንኙነት የላቸውም፤ ሐቁም እግዚአብሔር ቸር እንደ ሆነና ይህን ሊያደርግ እንደማይችል ነው። መልካሙ እረኛ የጠፋውን በግ ጥሎ ከዚያ በኋላ ግድ የለሽ አይሆንም፤ ይልቁንም ሊፈልገው ይወጣል፤ እስኪያገኘውም ድረስ ይፈልገዋል። ለዘላለም ጥሎናል ብሎ እርሱን መጠርጠር ታማኙን ፍቅሩን ማቍሰልና ማሳዘን ነው፤ ልክ አንዲት መልካም እናት ልጅዋ የቱንም ያህል ርቆ ቢባዝን ልትጥለው ትችላለች ተብላ ብትጠረጠር ልቧ እንደሚቈስል ማለት ነው። ነገሩ በሁለቱም ሁኔታ የማይቻል ነው፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ሁኔታ፣ ከኖሩት እናቶች ሁሉ በምትበልጠው እናት ሁኔታ እንኳ ከሚሆነው እጅግ ይበልጥ የማይቻል ነው።

«ስለ ምን እንዲህ አድርገህ ሠራኸኝ?»

ይህ ልንጠይቀው በጣም የምናዘነብልበት ጥያቄ ነው። በራሳችን የግል ተፈጥሮ ጉዳይ «ለእግዚአብሔር ለመመለስ» በአንድ ወቅት ወይም በሌላ ያልተፈተነ ከእኛ መካከል አንድ እንኳ የሚገኝ አይመስለኝም። ልዩ ጠባዮቻችንን ወይም የራሳችንን ልዩ መለያዎች አንወዳቸውም፤ በመልክ ወይም በችሎታ የሚበልጥ ስጦታ አለው ብለን የምናስበውን ሌላ ሰው ለመምሰል እንናፍቃለን። በውስጣዊም በውጫዊም ተፈጥሮአችን አንረካም፤ ውድቀቶቻችን ሁሉ የመጡት ባልታደለው ጠባያችን ምክንያት እንደ ሆነ እርግጠኞች እንሆናለን፤ ፈጣሪያችንንም «እንዲህ አድርጎ ስለ ሠራን» ለመውቀስ እናዘነብላለን።

በራሴ ተፈጥሮ ላይ እጅግ ለማመፅ የተፈተንሁበትን በሕይወቴ ያለውን አንድ ወቅት በግልጽ አስታውሳለሁ። ግልጽ ተናጋሪና ትጉ ዓይነት ሰው ነበርሁ፤ መልካም ክርስቲያን ለመሆን እጥር ነበር፤ ነገር ግን ምንም ልዩ የመንፈሳዊነት ገጽታ አልነበረኝም። ነገር ግን በመልኳ እንዲህ ቅድስት የምትመስል፣ እንዲህ ያለ መንፈሳዊ ጠባይም ያላት እኅት ነበረችኝ፤ የመንፈሳዊነት መገለጫ እስክትመስል ድረስ ነበረች፤ እኔም የእርሷን የቅድስና መልክና ጠባይ ብቻ ባገኝ እጅግ የተሻልሁ ክርስቲያን ልሆን እንደምችል እርግጠኛ ነበርሁ። ነገር ግን እነርሱን ለማግኘት ያደረግሁት ትግል ሁሉ ከንቱ ነበር።

የተፈጥሮ ጠባዬ ለማንኛውም የቅድስና ገጽታ እጅግ ትጉና ግልጽ ተናጋሪ ነበር፤ ብዙ ጊዜም በልቤ እግዚአብሔርን እየነቀፍሁ፦ «ስለ ምን እንዲህ አድርገህ ሠራኸኝ?» እል ነበር። ነገር ግን አንድ ቀን በአንድ የቆየ የምሥጢራዊ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ውስጥ ዓይኖቼን የከፈተ የሚመስል አንድ ዓረፍተ ነገር አገኘሁ። እንዲህ የሚል ነበር፦ «አምላክህ በሠራህ መልክ ሆነህ ለመኖር ረክተህ ኑር»፤ እግዚአብሔር እንደ ሠራኝ፣ እንድሆን የፈለገውንም ዓይነት ፍጥረት ማወቁ የግድ እንደ ሆነ በእውነት ሐቅ መሆኑ ድንገት ብልጭ አለልኝ፤ የድንች ተክል አድርጎ ሠርቶኝ ከሆነ ድንች በማብቀል መርካት እንዳለብኝ፣ የጽጌረዳ ቍጥቋጦ ሆኜ ጽጌረዳ ለማብቀል መመኘት እንደሌለብኝ፤ ለትሑት ሥራዎችም አዘጋጅቶኝ ከሆነ ታላቁን ሥራ ሌሎች እንዲሠሩ በመተው መርካት እንዳለብኝ ተረዳሁ። እኛ «ፍጥረቱ» ነን፤ እግዚአብሔርም ቸር ነው፤ ስለዚህ የእጁ ሥራ ደግሞ መልካም መሆኑ የግድ ነው፤ ገና ከዚህ እጅግ የራቅን ቢመስለንም፣ በእኛ ላይ ሥራውን ከመፈጸሙ በፊት ለክብሩ የሚሆን አንድ ነገር ከእኛ እንደሚሠራ ያለ ሥጋት ልንታመን እንችላለን።

መዝሙረኛው «እግዚአብሔር ቸር ነውና» የሚለውን ይህን የተባረከ አዝማች ደጋግሞ በመድገም ደስ የሚሰኝ ይመስላል። የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት ማውጫችሁን ወስዳችሁ ምን ያህል ጊዜ እንደሚለው ብትመለከቱ ይጠቅማችኋል። ሁሉም በዚህ አባባል ከእርሱ ጋር እንዲተባበሩም መከረ። «እግዚአብሔር የተቤዣቸው እንዲህ ይበሉ» የሚለው አጥብቆ የሚጮኸው ጩኸቱ ነበር። ድምፃችንን ከድምፁ ጋር ማዋሐድ አለብን—እግዚአብሔር ቸር ነው—እግዚአብሔር ቸር ነው። ነገር ግን በከንፈራችን ብቻ ብለነው ከዚያ በኋላ በድርጊታችን ቃላችንን ሐሰት ማድረግ የለብንም። ሰዎች ከልብ እንደምንለው እንዲያዩና ታላቅ ሐቅ መሆኑን እንዲያምኑ በአሳብ፣ በቃልና በድርጊት በመላ ሁለንተናችን «ልንለው» ይገባናል።

በእግዚአብሔር መለኮታዊ አሠራሮች ውስጥ ያሉ እጅግ ብዙ ነገሮች ለሥጋዊ ዓይን ቸርነት አይመስሉም፤ መዝሙራትንም ስናነብ መዝሙረኛው ከመዘገባቸው አንዳንድ ነገሮች በኋላ «ምሕረቱ ለዘላለም ነውና» እንዴት ሊል እንደ ቻለ ምናልባት እንገረም ይሆናል። እምነት ግን በእንደነዚህ ያሉ ምሥጢሮች ፊት ተቀምጦ፦ «እግዚአብሔር ቸር ነው፤ ስለዚህ የሚያደርገው ሁሉ፣ ምንም ቢመስል፣ መልካም መሆኑ የግድ ነው፤ እኔም ማብራሪያዎቹን መጠበቅ እችላለሁ» ይላል።

የቤት አስተዳደር ምሳሌ በዚህ ረገድ ብዙ ጊዜ ረድቶኛል። ቤቷን በሚገባ የምታስተዳድር መልካም የቤት እመቤት መሆኗን የማውቃት ወዳጅ ቢኖረኝ፣ በቤት ማጽጃ ጊዜ በቤቷ ያሉ ነገሮች ይብዛም ይነስም የተመሰቃቀሉ ቢመስሉ፣ ምንጣፎች ተነሥተው፣ የቤት ዕቃዎች በመሸፈኛ ተጠቅልለው፣ ምናልባትም የቀለም ቅብና የማስዋብ ሥራ አንዳንድ ክፍሎችን ለመኖሪያ የማይሆኑ አድርጓቸው ቢሆን እንኳ አልጨነቅም። ለራሴ፦ «ወዳጄ መልካም የቤት አስተዳዳሪ ናት፤ ምንም እንኳ አሁን ነገሮች ምቾት የሌላቸው ቢመስሉም፣ ይህ ሁሉ መመሰቃቀል የሆነው በመጨረሻ ከቀድሞው እጅግ ይበልጥ ምቹ ልታደርገው ስላሰበች ብቻ ነው» እላለሁ።

ይህ ዓለም የእግዚአብሔር የቤት አስተዳደር ነው፤ ምንም እንኳ አሁን ነገሮች እጅግ የተመሰቃቀሉ ቢመስሉም፣ እርሱ ቸር እንደ ሆነ፣ ስለዚህም መልካም የቤት አስተዳዳሪ መሆኑ የግድ እንደ ሆነ ስለምናውቅ፣ ይህ ሁሉ የአሁኑ መመሰቃቀል ያለ እርሱ ሊሆን ከሚችለው እጅግ የተሻለ ሁኔታ በመጨረሻ ለማምጣት ብቻ እንደ ሆነ ፍጹም እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። ሁላችንም የእግዚአብሔርን የቤት አስተዳደር ከእርሱ ይልቅ እኛ የተሻለ ልንሠራው እንደምንችል አንዳንድ ጊዜ ተሰምቶን ይሆናል፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ቸር እንደ ሆነ በተረዳን ጊዜ ከእንግዲህ ይህ ሊሰማን አይችልም። ዓለም ሁሉ የተበላሸ በሚመስለኝ ጊዜ ለራሴ፦ «ይህ የእኔ የቤት አስተዳደር አይደለም፤ የጌታ ነው እንጂ፤ ጌታም ቸር ነው፤ ስለዚህ የቤት አስተዳደሩ ደግሞ መልካም መሆኑ የግድ ነው፤ መጨነቄም ሞኝነት ነው» ማለት ብቻ እጅግ ያጽናናኛል።

ተስፋ የቈረጠ አንድ የእግዚአብሔር ልጅ ጥልቅ ትምህርት የተማረን አንድ ክርስቲያን፦ «ዓለም እንደ ፍርስራሽ አይመስልህምን?» ብሎ ጠየቀው።

«አዎን» አለ መላሹ በደስተኛ የመተማመን ድምፅ፤ «አዎን፣ እንደሚፈነዳ ዘር ፍርስራሽ።»

የኦክ ዛፍ ከሚበሰብስ የኦክ ፍሬ እምብርት ውስጥ መጀመሪያ ሲያቈጠቍጥ የተመለከተ ማንም ከእኛ ይህ ምን ማለት እንደ ሆነ ይረዳል። የኦክ ፍሬው የኦክን ዛፍ ከማብቀሉ በፊት ራሱ ፍርስራሽ መሆን አለበት። ከፈረሰ ዘር በቀር ከሌላ የበቀለ ተክል ከቶ የለም።

ጌታችን ከእኛ ጋር የሚያደርጋቸውን አሠራሮች ትርጕም ሊያስተምረን ይህን ሐቅ ይጠቀማል። «እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የስንዴ ቅንጣት በምድር ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች።» (ዮሐንስ 12:24)።

የዓለም በጠቅላላ ወይም በተለይ የራሳችን የግል ሕይወት የሚመስለው መፈራረስ ሙሉ ማብራሪያው እዚህ ተገልጦአል። በዚህ ብርሃንም ስናየው፣ ጌታ ቸር ሆኖ ሳለ በፈጠረው ዓለምና በሚወዳቸው ሰዎች ሕይወት ውስጥ ኀዘንና በደል እንዲኖር እንዴት ሊፈቅድ እንደሚችል መረዳት እንችላለን። እንዲፈቅደው የሚያስገድደው ቸርነቱ ራሱ ነው። ለእኛ ያለው የክብር ዓላማው ፍሬ ሊፈጸም የሚችለው በእንዲህ ያለ በሚመስል መፈራረስ ብቻ እንደ ሆነ ያውቃልና። ልባችን ደግሞ ያንን ፍሬ የሚናፍቅ እኛም መንገዶቹን ብንረዳ፣ ነገሮች እጅግ ከባድና እጅግ ምሥጢራዊ በሚመስሉበት ጊዜ እንኳ ስለ ቸርነቱ ሁሉ ልናመሰግነው እንችላለን።

ሐዋርያው የእግዚአብሔር ፈቃድ «በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም» እንደ ሆነ ይነግረናል። የቸር አምላክ ፈቃድ «በጎ» ከመሆን በቀር ሌላ ሊሆን አይችልም—እንዲያውም ፍጹም መሆኑ የግድ ነው፤ ይህንንም ባወቅን ጊዜ ሁልጊዜ «ደስ የሚያሰኝ» ሆኖ እናገኘዋለን፤ ይኸውም እንወደዋለን ማለት ነው። ፈቃዱ በጎ እንደ ሆነ አንድ ጊዜ በግልጽ ማየት ብንችል፣ ለእግዚአብሔር ፈቃድ ስለ መገዛት ያለብን ችግር ሁሉ እንደሚጠፋ እርግጠኛ ነኝ።

በጎ ነው ብለን ለማናምነው ፈቃድ ለመገዛት በከንቱ ደጋግመን እንታገላለን፤ በእውነት በጎ እንደ ሆነ ስናይ ግን በደስታ እንገዛለታለን። እንዲፈጸም እንፈልጋለን። ልባችን ሊቀበለው ዘልሎ ይወጣል።

ጣፋጭ የአምላክ ፈቃድ ሆይ፣ አመልክሃለሁ!

መንገዶችህንም ሁሉ አደንቃለሁ፤ በሕይወቴ ዘመን ቀን በቀን፣ አንተን ይበልጥ እወድሃለሁ።

የማይታዩ እግሮችህን ያሳረፍህበትን ዱካ ሁሉ መሳም እወዳለሁ፤ የተባረክህ ፈቃድ ሆይ፣ አንተን ልፈራ አልችልም!

ግዛትህ እጅግ ጣፋጭ ነውና።

ስለ ጌታ ወሰን የሌለው ቸርነት ልናገር የምችለውን ሁሉ ለመናገር ስፍራ ያንሰኛል። እያንዳንዱ ሰው ለራሱ «መቅመስና ማየት» አለበት። በሐቀኝነትና በታማኝነት ብቻ ቢያደርገው፣ የመዝሙረኛው ቃል በእርሱ ላይ እውነት ይሆናል፦ «የበዛውን የቸርነትህን ዝና ያወራሉ፥ ስለ ጽድቅህም በእልልታ ይዘምራሉ» (መዝሙር 145:7)።

ምዕራፍ 7 ተጠናቋል

እግዚአብሔር ቸር ነው

ገጽ 1 / 1 · 13 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል
ቀዳሚ ቀጣይ