ምዕራፍ 22 · 14 ደቂቃ ንባብ · 19 ደቂቃ ማዳመጥ
መቶ ሠላሳ ዘጠነኛው መዝሙር
«ታላቁ እንግዳ ተቀባይነትህ እንደ ወሰን የለሽ ባሕር ይከብበናል። ሁሉ ቤት በሆነበት ልንጠፋ፣ ከአንተም ተንሳፍፈን ልንርቅ አንችልም።»
በማቴዎስ 1:23 ላይ ያሉት «እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ይሉታል» የሚሉት ቃላት የያዙትን ሙሉ ትርጕም የምንረዳ ከእኛ እጅግ ጥቂቶች ነን። ይህች አጭር ዓረፍተ ነገር የዓለምን ታላቅ እውነት ትገልጣለች። ሁሉን የሚችለው የሰማይና የምድር ፈጣሪ እግዚአብሔር በክብራማ ሰማይ ውስጥ የራቀ አምላክ አይደለም።
ደካማና ረዳት የለሽ በሆነው ሕይወታችን ውስጥ ለራሳችን ቅርብ እንደ ሆንን ያህል ቀርቦ ከእኛ ጋር ይኖራል። ይህ ለሰው ልብ እጅግ የማይታመን ስለሚመስል ለማመን እንዘገያለን። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ከመጀመሪያው ገጹ እስከ መጨረሻው እንደ ሐቅ ያስተምረዋል።
ማንኛውም ቅን አእምሮ ይህን ሊክድ አይችልም።
በዘፍጥረት መጀመሪያ ላይ «በገነት ዛፎች መካከል ስለ ነበረው የእግዚአብሔር አምላክ ሀልዎት» እናነባለን። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ዘወትር ይገለጥልናል። በየስፍራው ከሕዝቡ ጋር የዕለት ተዕለትና የቅርብ ግንኙነት አለው። በዘጸአት «በመካከላቸው ያድር ዘንድ መቅደስ» እንዲሠሩለት ሲጠይቃቸው እናገኘዋለን። በምድረ በዳ ከእነርሱ ጋር «እንደ ተመላለሰ»፣ በተስፋይቱ ምድርም በመካከላቸው «ማደሪያውን እንዳደረገ» ተመዝግቦአል። ሁልጊዜ እንደሚገኝ ወዳጅና ረዳት በእርሱ እንዲደገፉ አስተማራቸው።
በጕዳዮቻቸው ሁሉ እርሱን ሊያማክሩና ሕይወታቸውን ሊሰጡት ይገባቸው ነበር። በመጨረሻም በክርስቶስ በሥጋ መጣ። በሰዎች መካከል እንደ ሰው በዓለም ኖረ። ከአጥንታችን አጥንት፣ ከሥጋችንም ሥጋ ሆነ። ባሕርያችንን ለበሰ። ታላቅና የተባረከ እውነትን እጅግ እውን በሆነ መንገድ ገለጠልን፦ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእኛ ጋር ሊሆን አስቦአል።
ይህን እውነት የሚያምኑ የችግራቸውን መፍትሔ በእርሱ ያገኛሉ። የሕይወታቸውን ችግሮች ሁሉ ይፈታላቸዋል። ትንሽ ልጅ ሳለሁ፣ በችግር ውስጥ ስሆን የወላጆቼ መምጣት ሁልጊዜ ያሳርፈኝ እንደ ነበረ ትዝ ይለኛል። ከእነርሱ አንዱ «ልጄ፣ እኔ እዚህ ነኝ» ሲል በሰማሁ ጊዜ ሸክሙ ሁሉ ይወድቅ፣ ጭንቀቱም ሁሉ ጸጥ ይል ነበር። ይህን ያደረገው መገኘታቸው ብቻ ነበር። ሊያሳርፉኝ ቃል መግባት አላስፈለጋቸውም። ዕቅዳቸውን ሊነግሩኝም አላስፈለጋቸውም። የሚያስፈልገኝ ማረጋገጫ ሁሉ መገኘታቸው ነበር። ሁሉ ነገር እንደሚስተካከልና ሁሉም መልካም እንደሚሆንልኝ የሚያሳይ ነበር።
ከመጡ በኋላ ማየት የምፈልገው እንዴት እንደሚያደርጉት ብቻ ነበር።
ልዩ ወላጆች መሆን አለባቸው፤ ልጆቻቸው እጅግ ይተማመኑባቸዋልና። እኔም እንደዚያ እንደ ነበሩ አስባለሁ። አምላካችን ግን ከሁሉ የላቀ ነው። ስለዚህ ምሳሌው ፍጹም ይሠራል። የሚያስፈልገን ሀልዎቱ ብቻ ነው።
አንድም የተስፋ ቃል ወይም ስለ ዕቅዶቹ አንድም መገለጥ ባይኖረን እንኳ ለእኛ በቂ በሆነ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ «ከአንተ ጋር እሆናለሁ» ይላል። ይህም ጥያቄዎችንና ፍርሃቶችን ሁሉ ጸጥ አሰኝቶአል። ማን ሊጠራጠረው ይችላል? ወሰን የሌለው ጥበቡ፣ ፍቅሩና ኃይሉ ከእኛ ጋር እንደ ሆኑ ሊያረጋግጥልን ፈለገ። በልጅነቴ «ኦ፣ እናቴ መጣች!» የሚሉት አስማታዊ ቃላት ደጋግመው እፎይታንና መጽናናትን አምጥተውልኛል። በኋለኞቹ ዓመታቴ ደግሞ «ኦ፣ እግዚአብሔር እዚህ አለ!» የሚለውን ቃል በአክብሮት ሲነገር ሰምቻለሁ፤ ይህም እጅግ የተባረከ መዳን አምጥቶልኛል። እርሱ ባለበት ምን ልፈራ እችላለሁ? እንዲህ ብሎአልና፦ «አካሄዳችሁ ገንዘብን ያለ መውደድ ይሁን፥ ያላችሁም ይብቃችሁ፤ እርሱ ራሱ። አልለቅህም ከቶም አልተውህም ብሎአልና፤» (ዕብራውያን 13:5)። ስለዚህ በድፍረት «ጌታ ይረዳኛልና አልፈራም፤ ሰው ምን ያደርገኛል?» ልል እችላለሁ። በአባቴ መገኘት ይሰማኝ የነበረውን የሚያበረታ የደኅንነት ስሜት አሁንም አስታውሰዋለሁ። እርሱ በአጠገቤ ሳለ ምንም ነገር ፈርቼ አላውቅም። የሰማዩ አባቴ በአጠገቤ ሲሆንማ በእርግጥ ለፍርሃት ምንም ስፍራ ሊኖር አይችልም።
«አማኑኤል፣ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር» የሚለውን ሐቅ ግልጽና የተረጋገጠ ለማድረግ እሻለሁ። የሚሰጠው ተግባራዊ ርዳታና መጽናናት ያነሣሣኛል። ከእግዚአብሔር የገዛ ልጆች መካከል ይህን በእውነት የሚያምኑት ጥቂቶች እንደ ሆኑ እርግጠኛ ነኝ። እናምናለን ይሉ ይሆናል። በተመስጦ ድምፅ «ኦ፣ አዎን፣ እግዚአብሔር ሁልጊዜ ከእኛ ጋር እንዳለ እናውቃለን፤ ነገር ግን…» ብለው ሺህ ጊዜ ይደጋግሙ ይሆናል፤ ታሪኩም ሁሉ የሚነገረው በዚህ «ነገር ግን» ውስጥ ነው። ሀልዎቱን እንደ ቃል በቃል ሐቅ በምትቀበል ነፍስ መዝገበ ቃላት ውስጥ «ነገር ግን» የሚባል ነገር የለም። እንዲህ ያለች ነፍስ በማንኛውም የፍርሃት ወይም የጥርጣሬ ሐሳብ ላይ በደስታ ድል ትነሣለች። እግዚአብሔር አላት፤ ያም ይበቃታል። ሀልዎቱ ሁልጊዜና ለሁሉ ነገር የተረጋገጠ ዋስትናዋና ስንቋ ነው።
አንባቢዎቼ ከእኔ ጋር ወደ መዝሙር 139 እንዲመለሱ እለምናቸዋለሁ። በዚያ የዚህን እውነት የተባረከ መገለጥ እናገኛለን። የመዝሙሩ ማዕከላዊ ሐሳብ ከቍጥር 7 እስከ 12 ይገኛል፦ «ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ? ወደ ሰማይ ብወጣ፥ አንተ በዚያ ነህ፤ በሲኦልም ብተኛ፥ በዚያ አለህ። የንጋትን ክንፍ ብወስድ፥ በባሕርም መጨረሻ ብኖር፥ በዚያ ደግሞ እጅህ ትመራኛለች፥ ቀኝህም ትይዘኛለች። ‹በእውነት ጨለማ ይሸፍነኛል፥ በዙሪያዬ ያለውም ብርሃን ሌሊት ይሆናል› ብል፥ ጨለማ እንኳ በአንተ ዘንድ አይጨልምም፤ ሌሊትም እንደ ቀን ያበራል፤ ጨለማና ብርሃን በአንተ ዘንድ አንድ ናቸውና።»
ይህ ክፍል በየትም ብንሆን ምንም ብናደርግ ከእኛ ጋር ስላለው የማያቋርጥ ሀልዎቱ እጅግ ጠንካራ ማስረጃ ነው። ሰዎች በጌታ ፊት ለመሆን ይሻሉ። ነገር ግን ከፊቱ ሊያመልጡ አይችሉም። በዓለማት ሁሉ እርሱ የሌለበት ስፍራ የለም፤ በሰማይም፣ በሲኦልም፣ በባሕር መጨረሻም ቢሆን የለም። ምንም ጨለማ ለአንዲት ቅጽበት እንኳ ከእርሱ ሊሰውር አይችልም። ምክንያቱም እርሱ «ኵላሊታችንን ገንዘቡ አድርጎአልና» ነው። ይህም ከእኛ ጋር ብቻ ሳይሆን በውስጣችንም ነው ማለት ነው።
ስለዚህ ወደምንሄድበት ሁሉ አብሮን መሄዱ የግድ ነው።
ይህን እውነት አድርገን ልንቀበለው ይገባናል። ጌታችን «እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ» ያለው ቃል ውብ ስሜት ብቻ አልነበረም። የማይካድ ሐቅ ነው። እርሱ ከእኛ ጋር ነው፤ ከእርሱም ልንርቅ አንችልም።
በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ምንም ላናይ እንችላለን። እርሱ እንደማያየን ብዙ ጊዜ እናስብ ይሆናል። መዝሙራችን ግን ጨለማ ከእርሱ እንደማይሰውር ያረጋግጥልናል። እንዲያውም ጨለማና ብርሃን ለእርሱ አንድ ናቸው። በብሩሁ ብርሃናችን እንዳለን ሁሉ በጨለማው መንፈሳዊ ጥልቀታችንም በፊቱ እንገኛለን፤ በግልጥም እንታያለን። ጨለማው እርሱን ከእኛ ሊሰውረው ይችላል፤ እኛን ግን ከእርሱ አይሰውረንም። ማንኛውም መንፈሳዊ ርቀት ወይም መቅበዝበዝም ከፊቱ አያርቀንም። በመቅበዝበዛችን ወደ ኃጢአት ብንሰምጥ እንኳ አያርቀንም። በባሕር መጨረሻ ወይም በየትም ብንሆን ሊይዘንና ሊመራን ሁልጊዜ በዚያ አለ። ያለ እርሱ ጥበቃ የምንቀርበት አንድም ቅጽበት ወይም አንድም ስፍራ የለም።
አንዳንድ ጊዜ የአእምሮ መደናገር የሚያስታምሙንን ሰዎች ፍቅራዊ እንክብካቤ እንዳናስተውል ያደርገናል። የተደናገረ ሕፃን እናቱን ፈልጎ ሊጮኽ ይችላል፤ የሚያሳዝነውም ጩኸቱ ልቧን ይሰብረዋል። በዚያው ጊዜ እርሷ የሚያቃጥለውን እጁን ይዛ፣ በትኩሳት የጋለውን ራሱን እያቀዘቀዘች በእናት ፍቅር ትንከባከበዋለች። ሕመሙ እናቲቱን ከሕፃኑ ሊሰውራት ይችላል፤ ሕፃኑን ግን ከእናቲቱ አይሰውረውም።
ከአምላካችንና ከእኛም ጋር እንዲሁ ነው። ጥርጣሬዎቻችን፣ ፍርሃቶቻችን፣ ኀዘኖቻችንና ኃጢአቶቻችን እኛን ከእርሱ ሊሰውሩን አይችሉም።
ነገር ግን ብዙ ጊዜ እርሱን ከእኛ ይሰውሩታል። ጨለማና ብርሃን ለእርሱ አንድ እንደ ሆኑ ተናግሮአል። እምነታችን ይህን ከተቀበለ በጨለማ ጊዜያት ልንታመን እንችላለን። ልናየው ወይም ሊሰማን ባይችልም አምላካችን ይጠብቀናል። ከቶ አይተወንም።
ይሁን እንጂ ይህ የአምላካችን የማይለየን ሀልዎት ደስታ ወይም ኀዘን የሚሆንልን ስለ እርሱ በምናውቀው ላይ የተመካ ነው። ለገዛ ክብሩ ብቻ የሚጨነቅ ጨካኝ አምባገነን አድርገን ብናስበው፣ የማያቋርጥ ሀልዎቱን እንፈራለን። አፍቃሪ አባት አድርገን ብናየው ግን ደስ ይለናል። እርሱ የሚፈልገው ደስታችንን ብቻ ነው። ስለዚህ ሁልጊዜ ከእኛ ጋር በመሆኑ እናመሰግናለን። የፍቅር መገኘትና እንክብካቤ ለተወደደው ሰው ከመልካም በቀር ሌላ ትርጕም ሊኖረው አይችልምና።
የምናጠናው መዝሙር የእግዚአብሔር ሀልዎት ፍቅር እንደ ሆነ ያሳየናል። ወሰን የሌለው መጽናናትና ዕረፍት ያመጣልናል። ከቍጥር 1 እስከ 5 እንዲህ ይላል፦ «አቤቱ፥ መረመርኸኝ፥ አወቅኸኝም። አንተ አቀማመጤንና አነሣሤን አወቅህ፤ አሳቤን ሁሉ ከሩቅ አስተዋልህ። መንገዴንና መኝታዬን አንተ መረመርህ፥ አካሄዴንም ሁሉ አወቅህ። በአንደበቴ ቃል ሳይኖር፥ እነሆ፥ አቤቱ፥ አንተ ሁሉን አወቅህ። ኋላዬንና ፊቴን አንተ ከበብኸኝ፥ እጅህንም በላዬ አደረግህ።»
አምላካችን ያውቀናል፣ ይረዳናልም፤ መንገዳችንንም ሁሉ ያውቃል። በዓለም ሁሉ ሌላ የሚረዳን ማንም የለም። ሰዎች ተግባራችንን በተሳሳተ ሁኔታ ሊተረጕሙና ዓላማችንን በስሕተት ሊፈርዱ ይችላሉ። ተፈጥሮአዊ ባሕርያችን ግምት ውስጥ አይገባም፤ በውርስ ያገኘናቸው ዝንባሌዎችም አይታሰቡም። ስለ ደካማ ጤናችን ማንም ይቅርታ አያደርግልንም፤ ምን ያህል መታገል እንዳለብን ማንም አይገነዘብም። አባታችን ግን ሁሉን ያውቃል። ይረዳናል። ፍርዱ የምናውቀውንም የማናውቀውንም የባሕርያችንን ክፍል ሁሉ ያገናዝባል። ተግባራችንን የሚቈጣጠረውንም ያገናዝባል። ፍትሐዊ ሊሆን የሚችለው ሁሉን የሚረዳ ፍቅር ብቻ ነው፤ አምላካችንም ፍትሐዊ ነው። ፌበር እንዲህ ማለቱ አያስደንቅም፦ የምድር ኀዘኖች ከሰማይ ይበልጥ የሚሰሙበት ስፍራ የለም፤ የምድር ድካሞችም ከዚያ ይበልጥ በርኅራኄ የሚፈረዱበት ስፍራ የለም። ከእናንተ አንዳንዶቻችሁ ፍትሑ በእናንተ ላይ ይሆናል ብላችሁ ትፈሩት ይሆናል። ግን አታዩምን? የእናት ፍትሕ እንደ ሆነው ሁሉ ፍትሑ ሙሉ በሙሉ ከእናንተ ጋር ነው፤ ፍጥረታችንን ያውቃልና፥ አፈር መሆናችንንም ያስባልና። ማንም ሰብዓዊ ዳኛ ይህን ሊያደርግ አይችልም፤ ለእኔም ይህ የእግዚአብሔር ሁሉን መረዳት እጅግ ከተባረኩ መጽናናቶቼ አንዱ ነው። ብዙ ጊዜ ራሴን አልረዳም፤ በውስጤ ያለው ሁሉ የተደበላለቀና ተስፋ በሌለው ሁኔታ የተጠላለፈ ይመስላል። ነገር ግን እርሱ እንደ መረመረኝ አስታውሳለሁ። ያውቀኛል። ግራ የሚያጋቡ ሐሳቦቼን ይረዳል። ስለዚህ የተዘበራረቀውን ሁሉ እንዲፈታው ለእርሱ ልተወው እችላለሁ።
ነፍሴም ወዲያውኑ ለስላሳ ትራስ ላይ እንደምታርፍ እጅግ ደስ ወደሚያሰኝ የዕረፍት ስፍራ ትሰምጣለች። ደግሞም ስለ ፍላጎታችን ካለው ፍጹም እውቀቱ የተነሣ አቀማመጣችንንና አነሣሣችንን እንደሚያውቅ መነገሩ ምንኛ ያጽናናል! መንገዳችንን ይከብባል፤ መኝታችንንም ያስተውላል። አምላካችን እናት ሞኞች፣ ግድ የለሾችና የማያውቁ ነገር ግን እጅግ ለምትወዳቸው ትንንሽ ልጆቿ የምታደርገውን ለእኛ ያደርግልናል። እናት ከልጆቿ ጋር ስትሆን ሁልጊዜ ከራሷ ምቾትና ደኅንነት በፊት የእነርሱን ታስባለች። ምቹና ነፋስ የማይገባባቸው መቀመጫዎች ሊኖራቸው ይገባል። እርሷ ግን ማንኛውንም ምቾት ማጣት ትታገሣለች። የእርሷ ምንም ዓይነት ቢሆን የእነርሱ አልጋ ለስላሳ፣ ብርድ ልብሳቸውም ሞቃት ሊሆን ይገባዋል።
እርሷ በሻካራና አደገኛ መንገድ ለመሄድ ብትገደድም የእነርሱ መንገድ የተስተካከለና አስተማማኝ ሊሆን ይገባዋል።
በአፍቃሪ እናት ዓይን ከልጆቿ ምቾት ጋር ሲነጻጸር የራሷ ምቾት ምንም ዋጋ የለውም።
በእርግጥ አምላካችን በዚህ ዓለም ካሉ እናቶች ያነሰ ራሱን የሚሠዋ ፍቅር ሊኖረው አይችልም። በፍቅርና በራስ መሥዋዕትነት ረገድ ከፈጠራቸው እናቶች ሁሉ የሚሻልና የሚበልጥ ሊሆን ይገባዋል። አቀማመጣችንንና አነሣሣችንን እንደሚያውቅ አረጋግጦልናል። መንገዳችንንና መኝታችንን ይከብባል። ስለዚህ በሕይወታችን ትንንሽ ዝርዝሮች ሁሉ ፍቅሩ፣ ጥበቡና ኃይሉ ሊያቀርቡት የሚችሉትን እጅግ የተሻለውን እንደምናገኝ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። ይህን እጅግ ቃል በቃል ማለቴ ነው። ስለ መቀመጫዎቻችንና ስለ አልጋዎቻችን ግድ ይለዋል ማለቴ ነው። እያንዳንዳችን ለከፍተኛው ዕድገታችን የሚበጀውን ዓይነት እንድናገኝ ያደርጋል።
እናት ልትሆን ከምትችለው እጅግ የሚሻለው በዚህ በመጨረሻው ነጥብ ላይ ነው። ፍቅሩ የነገሮችን ፍጻሜ የሚያይና ከዝቅተኛው ይልቅ ለከፍተኛው ጥቅማችን የሚጨነቅ ጥበበኛ ፍቅር ነው። የእናት ደካማ ፍቅር ከልጁ ምቾት ባሻገር ማየት አይችልም። ምንም ዓይነት ምቾት ማጣት ሊያደርስበት አይችልም። የእግዚአብሔር ብርቱና ጥበበኛ ፍቅር ግን የተወሰነ ሕመም ሊፈቅድ ይችላል። ይህም ከእርሱ ለሚገኘው ለሚመጣው ክብር ሲል ነው።
በቤትም በውጭም በእግዚአብሔር እንታመን። ስለ ዕለት ተዕለት ኑሮአችን ሁሉን ያውቃል። ስለዚህ መቀመጫዎቻችንን፣ አልጋዎቻችንንና ሌሎች ትንንሽ ነገሮችን እርሱ ይምረጥልን።
በመዝሙራችን መንገዳችንን «እንደሚከብብ» ተነግሮናልና። ከእኛ አንዳንዶቻችን ባልተወደዱና ደስ በማያሰኙ ሰዎች ወይም ነገሮች «መከበብ» ምን እንደ ሆነ እናውቃለን። ነገር ግን ምናልባት በእግዚአብሔር እንደ ተከበብን ፈጽሞ አስበን አናውቅም። እርሱ እጅግ ስለሚወደን ብቻችንን ሊተወን አይችልም።
ምንም ዓይነት ቀዝቃዛነት ወይም ማግለል ሊያባርረው አይችልም። ሆኖም ይህ በክብር እውነት ነው! ከዚህም በላይ ከፊት ብቻ ሳይሆን «ከኋላም» ይከብበናል። ልክ እናት እንደምታደርገው። ልጆቿን ትከተላለች። የጣሉትን ሁሉ ታነሣለች፤ ያዝረከረኩትንም ታጸዳለች።
እኛ እናቶች ይህን በልጆች ክፍል ውስጥ በጡቦቹና በአሻንጉሊቶቹ እንጀምራለን። በሕይወታችን ሁሉ እናደርገዋለን። ልጆቻችን ያልፈጸሙትን ወይም በስሕተት ያደረጉትን ለማስተካከል እንሞክራለን። ብዙ ጥረትና ድካም ይጠይቃል፤ ፍቅራችን ግን ልጆቻችንን ከመንከባከብ ጋር ሲነጻጸር ያንን ጥረት ትንሽ ያስመስለዋል። የትኛዋ መልካም እናት የሚያዝንና የሚያለቅስ ልጅዋን ትመልሳለች? ወይስ ልጅዋ የተጠላለፈውን የካይቱን ገመድ እንዲፈታ ለመርዳት እምቢ ትላለች? ቋጠሮዎቹና መጠላለፎቹ በእርሱ ጥፋት የመጡ ቢሆኑ እንኳ ፍቅሯ እነዚያን ስሕተቶች ይረዳቸዋል፤ ያዝንላቸዋልም። ስለዚህ እነርሱን ለማስተካከል ለመርዳት ይበልጥ ትደክማለች።
አምላካችን ይህን ሁሉና ከዚህ የሚበልጥ ከሕፃንነታችን ጀምሮ ለእኛ ያደርጋል። ገና ሳናውቀው ጀምሮ እስከ ምድራዊ ሕይወታችን ፍጻሜ ድረስ ያደርገዋል። ምናልባት በፊታችን አይተነው ይሆናል፤ ከኋላችንም እንዳለ ግን ፈጽሞ አስበን አናውቅም። ሆኖም ይህ የተባረከ ሐቅ ነው። እርሱ ከኋላችን ነው። ጠማማውን ሊያቀና፣ ቋጠሮዎቻችንን ሊፈታና ስሕተቶቻችንን ሊክስ ይናፍቃል። ከእኛ ማንም የሚያስጨንቅ ያለፈ ታሪክ ቢኖረው ደስ ይበለው። ከኋላችን ያለው እግዚአብሔር ለእርሱ አደራ ብንሰጠው ሁሉን ያቀናዋል። ስሕተቶቻችንን እንኳ ለበጎ እንዲደረጉ ሊያደርጋቸው ይችላል። አሃ! በእግዚአብሔር መከበብ እንዴት ያለ ታላቅ ነገር ነው!
ደግሞም ከቍጥር 14 እስከ 16 ያለው ቃል ምንኛ ያጽናናል፦ «ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ።
ሥራህ ድንቅ ነው፤ ነፍሴም ፈጽማ ታውቀዋለች። በስውር በተሠራሁ ጊዜ፥ በምድር ጥልቅ ውስጥ በጥበብ በተሠራሁ ጊዜ፥ አካሌ ከአንተ አልተሰወረም። ዓይኖችህ ያልተሠራውን አካሌን አዩ፤ ገና አንዳቸውም ሳይኖሩ ለእኔ የተወሰኑት ቀኖች ሁሉ በመጽሐፍህ ተጻፉ።»
ብዙ ጊዜ ከምናምነው በላይ የተፈጠርንበትን መንገድ አንወደውም። የአእምሮአችን ወይም የሞራላችን «አሠራር» አይስማማንም። ከዚህ ያነሰ ወይም ከዚያ የበዛ ሆነን ብንፈጠር ይበልጥ እንሳካ ነበር ብለን እናስባለን። ያነሰ ቸኳይ ወይም ይበልጥ ቀናተኛ ብንሆን እግዚአብሔርን በተሻለ ልናገለግል እንችል ነበር። ለራሳችንና ለእርሱም ይበልጥ አጥጋቢ ልንሆን እንችል ነበር። እንደምናደንቀው ሰው ብንሆን ይህም ይረዳ ነበር ብለን እናምናለን። አንዳንድ ጊዜም በዚህ ምስኪን አሠራራችን እርሱን ደስ ለማሰኘት መጠበቅ ተስፋ ቢስ ነው ብለን ለማሰብ እንፈተናለን።
እግዚአብሔር እንደ ፈጠረን በእውነት ብንገነዘብ፣ የዚህ ሁሉ ሞኝነት ወዲያውኑ ይታየን ነበር። እኛ ግን በዚህ ጕዳይ ብዙም እጅ እንዳልነበረው ይሰማናል። ባሕርያችንን ለዕድል ትቶ በዘፈቀደ የተገጣጠምን ይመስለናል። ስለ ፍጥረት በጠቅላላው እናምናለን፤ ወደ ራሳችን ሲመጣ ግን በዝርዝሩ አናምንም። ይህ መዝሙር እግዚአብሔር ፍጥረታችንን በበላይነት እንደ ተቈጣጠረ ያሳያል። እጅግ ትንንሾቹን ዝርዝሮች እንኳ አስተዳደረ። በምሳሌያዊ አነጋገር፣ አንዳቸውም ገና ሳይኖሩ እያንዳንዱ «ብልት» ምን እንደሚሆን ጻፈ። ስለዚህ በተፈጥሮአችን እግዚአብሔር የሚፈልገውን ነን።
ልዩ ሥራ እንድንሠራ ፈጠረን። ይህን ስል በእርግጥ ተፈጥሮአዊ ባሕርያችንን ማለቴ ነው እንጂ በእኛ በኩል በኃጢአት መጣመማቸውን አይደለም።
እንዲህ ማየቱ ፈጣሪን እጅግ የሚያከብር ነገር አለው። ታላቅ የፈጠራ ተሰጥኦ ራሱን በብዙ መንገድ ለመግለጥ ሁልጊዜ ይሻል። እውነተኛ ሠዓሊ ራሱን አይደግምም። እያንዳንዱ ሥዕል ወይም ሐውልት የፈጠራ ኃይሉ አዲስ መግለጫ ነው። የሥዕል ትርኢት ሁለት አንድ ዓይነት ሥዕሎች ሊኖሩት አይገባም። ቢኖሩት የጥበቡን ዋጋ ያወርደዋል። «የእግዚአብሔር ፍጥረት» ለሆንነው ለእኛም እንዲሁ ነው። የፈጠራ ኃይሉ በእያንዳንዳችን በተለያየ መንገድ ይገለጣል።
አንዳንድ ጊዜ በሚያስጨንቀን በግል «አሠራራችን» ውስጥም ልዩ ኃይል አለ። ያ ባይኖር ለክብሩ ምስጋና የምንሆንበት የትርኢቱ ቀን ያልተሟላ ይሆን ነበር። እርሱ የሚጠይቀው ይህን ብቻ ነው፦ እርሱ ስለ ፈጠረን እርሱ ሊያስተዳድረን ይገባዋል። እርሱ ብቻ ይረዳናል፤ ስለዚህ ይህን ሊያደርግ የሚችለው እርሱ ብቻ ነው።
ውስብስብ ማሽንን የሠራ ሰው ለማስተዳደርና ለመጠገን ከሁሉ የተሻለ ብቃት አለው። ሌላ ማንም ጣልቃ የሚገባ ሊያበላሸው ይችላል። ውስብስብ አእምሮአችንንና በእርሱ ላይ ያለንን ደካማ ቍጥጥር ስናስብ፣ ለፈጣሪው አሳልፈን ሰጥተን በእጁ ልንተወው በማግኘታችን ልናመሰግን ይገባናል። ከእኛ የተሻለውን እንደሚያወጣ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። «ልዩ ጠባያችንና» ጕድለታችን እያለ እንኳ ለክብር የሚሆን ዕቃ ሆነን እንሠራለን።
የተቀደስንና ለጌታው የምንጠቅም፣ ለበጎም ሥራ ሁሉ የተዘጋጀን እንሆናለን።
አንድ የጥንት የኩዌከር ጸሐፊ የተናገረውና ከእኔ ጋር የቈየ አንድ አባባል አንድ ጊዜ አነበብሁ፦ «እግዚአብሔር እንደ ፈጠረህ በመሆንህ ብቻ ረክተህ ኑር።» ሐሳቤን እንድረዳ ረዳኝ። እግዚአብሔርን በእውነት ለመገዛት የዕለት ሁኔታዎቻችንን እንደምንቀበል ሁሉ እርሱ እንደ ፈጠረን ራሳችንንም ልንቀበል ይገባናል ብዬ አምናለሁ። እኛ ባንኖር የእግዚአብሔር ፍጥረት አንድ ክፍል ይጐድል ነበር። ሥራው ያልተሟላ ይሆን ነበር። ከዚህም በላይ ስለ ራሳችን ማጕረምረም በሠራን ላይ እንደ ማጕረምረም ነው፤ ይህም እርሱን ማሳዘኑ አይቀርም። እንግዲያስ እንርካ፤ መለኮታዊው ሸክላ ሠሪ እርሱ እንደሚሻል እንዲቀርጸን እንደ ወደደውም እንዲጠቀምብን እንታመንበት።
ቍጥር 17 እና 18 ሌላውን የእግዚአብሔርን የማያቋርጥ ሀልዎት ገጽታ ያወጣሉ፤ ይኸውም ሁልጊዜ ስለ እኛ እንደሚያስብ፣ ሐሳቡም የቸርነትና የፍቅር ሐሳብ እንደ ሆነ ነው፤ ዘማሪው የከበሩ ብሎ ይጠራቸዋልና። «አቤቱ፥ አሳብህ በእኔ ዘንድ እንዴት የከበረ ነው! ድምሩም እንዴት በዛ!
ብቈጥረው ከአሸዋ ይልቅ ይበዛል፤ ስነቃም ገና ከአንተ ጋር ነኝ።»
ብዙ ሰዎች እግዚአብሔር ለእነርሱ ምንም ትኵረት እንደማይሰጥ ለማሰብ ይፈተናሉ። ጕዳዮቻቸው እርሱ ሊመለከታቸው የማይገቡ ዝቅተኛ እንደ ሆኑ ያምናሉ። ትኵረቱን ተስፋ ለማድረግ እጅግ የማይገባቸው እንደ ሆኑ ይሰማቸዋል። ነገር ግን እንዲህ ባለው ሐሳብ እጅግ ይበድሉታል። እናት ለታላላቆቹ ልጆቿ እንደምትሰጠው ሁሉ ለትንሹ ሕፃኗ ትኵረት ትሰጣለች። ለእነርሱ ፍላጎትና ደስታ እንደምትጨነቅ ሁሉ ለትንንሽ ፍላጎቶቹና ደስታዎቹ ትጨነቃለች። እርግጠኛ አይደለሁም፤ ምናልባት ይበልጥ ትጨነቅ ይሆናል።
እጅግ ለሚያስፈልገው ታስባለች። የእናትን ልብ የሠራ እርሱ እጅግ ረዳት ለሌላቸው ፍጥረታቱ ይጠነቀቃል። የአንበሳ ግልገሎች ሲጮኹ ይሰማቸዋል። አንዲት ድንቢጥ እንኳ ያለ እርሱ በምድር ላይ አትወድቅም። እኛም «ከብዙ ድንቢጦች እናንተ ትበልጣላችሁ»። ስለዚህ ለአንዲት ቅጽበት እንኳ እንዳንዘነጋ መፍራት የለብንም።
ማንኛውንም ነገር መፍጠር ከፈጣሪው የማያቋርጥ ጥበቃን ይጠይቃል። የሁሉን ቻይነት ክብር ሁሉን በአንድ ጊዜ ሊያደርግ መቻሉ ነው። እጅግ ትንንሾቹን ዝርዝሮችና እጅግ ታላላቆቹን ሥራዎች ሊከታተል ይችላል። «ሁሉን ሊይዝ የሚችለው ወሰን የሌለው ታላቅነት ብቻ ነው። ከወሰን የለሽነት ያነሰ ታላቅነት ይጨፈልቀን ነበር።»
ታላላቅ ሥራዎችን ለመሥራት ብሎ ትንንሽ ዝርዝሮችን የሚዘነጋን ወንድ ወይም ሴት ለምን ደካማ አድርገን እንደምንቈጥር አላውቅም።
ሆኖም አምላካችንን ያንኑ ነገር እንደሚያደርግ እንከሰዋለን። ነገር ግን ከአንባቢዎቼ ማንም በዚህ ሞኝነት ተይዞ ከሆነ፣ ከአሁን ጀምሮ ይብቃ። «አቤቱ፥ አሳብህ በእኔ ዘንድ እንዴት የከበረ ነው! ድምሩም እንዴት በዛ!
ብቈጥረው ከአሸዋ ይልቅ ይበዛል፤ ስነቃም ገና ከአንተ ጋር ነኝ።»
የቀረው የመዝሙሩ ክፍል በነፍስና በእግዚአብሔር መካከል ያለውን ፍጹም ስምምነት ያሳያል። ይህ የቀላል እምነት ሕይወት የተጀመረበት ስፍራ ነው። ነፍስ እርሱ ሁልጊዜ እንደሚገኝና እንደሚጠነቀቅ አውቃ ከእግዚአብሔር ጋር አንድ ትሆናለች። እርሱ የሚወደውን ትወዳለች፤ እርሱ የሚጠላውንም ትጠላለች። ማንኛውም ክፍሏ ከእርሱ ጋር ሳይስማማ እንዳይቀር እንዲመረምራትና እንዲፈትናት በጕጕት ትለምነዋለች።
በሀልዎቱ ፊት ጨለማ ሊሸሽ ግድ ነው። ልብም ከብርሃኑ የተሰወረ ማንኛውንም ማዕዘን መታገሥ እንደማይችል ይሰማዋል። «የሕይወትን መንገድ አሳየኸኝ፤ በፊትህ የደስታ ጥጋብ አለ፥ በቀኝህም ለዘላለም ተድላ አለ።» (መዝሙር 16:11) በእንግሊዝ ገለልተኛ በሆነ አንድ ስፍራ የምትኖር አንዲት አሮጊት ብቸኛ በሆነው ጎጆዋ ለመንገደኞች የገብስ መጠጥና ቢራ እየሸጠች ብዙ ገንዘብ አገኘች። ነገር ግን ሕሊናዋ ስለዚህ ነገር ያስጨንቃት ነበር። ክርስቲያን ለመሆንና ስትሞት ወደ ሰማይ ለመሄድ ትፈልግ ነበር። ይህን ብታደርግ ግን ትርፋማ ንግዷን መተው እንዳለባት ተሰማት። ይህም ልትሸከመው የማትችል ከባድ ነገር መሰላት። ስለዚህ በሁለቱ መካከል ተወጠረች።
አንድ ሌሊት በተገኘችበት ስብሰባ ላይ አንድ ሰባኪ ስለ እግዚአብሔር የማያቋርጥ ሀልዎት ደስታ ተናገረ። ይህን እውነት ማወቅ ታላቅ ደስታ እንደሚያመጣ ተናገረ። ይህ ለእርሷም እውነት ሊሆን ይችላል በሚለው ሐሳብ ልቧ በደስታ ተሞላ። ስለ ቢራው ሁሉ ረስታ በቀላልና በቅንነት እንደ አስደናቂ እውነታ ተቀበለችው። ሰባኪው መናገሩን ሲቀጥል በልቧ እንዲህ ብላ ጮኸች፦ «ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ ሁልጊዜ ከእኔ ጋር እንደ ሆንህ አላውቅም ነበር! ጌታ ሆይ፥ ሁልጊዜ እዚህ ከእኔ ጋር ሆነህ እንደምትጠብቀኝ ማወቅ ምንኛ ያስደንቃል! ከእንግዲህ ወዲህ ብቸኝነት ፈጽሞ አይሰማኝም!»
ስብሰባው ሲያልቅ በእርሻዎቹ መካከል አቋርጣ ወደ ቤቷ ሄደች። ያ አስደሳች ሐሳብ በልቧ ውስጥ ይደጋገም ነበር፦ «አሃ፣ ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ ዛሬ ማታ ከእኔ ጋር ወደ ቤት ትመጣለህ።» እርሷም «ግድ የለም፣ ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ አሮጊቷ ቤቲ ከእንግዲህ ወዲህ ፈጽሞ አትለቅህም። እዚህ ከእኔ ጋር እንዳለህ አውቃለሁ» አለች።
በእግዚአብሔር ሀልዎት ያላት እምነት እየበረታ ሄደ፤ በእያንዳንዱ እርምጃም ይበልጥ ደስ ተሰኘች። ወደ ጎጆዋ በር በደረሰች ጊዜ ልቧ በደስታ ተሞልቶ ነበር። ስትገባም መጀመሪያ ያየችው ለሽያጭ ተዘጋጅቶ በጠረጴዛው ላይ የተቀመጠ ትልቅ የቢራ ማሰሮ ነበር። አንድ ሐሳብ መጣላት፦ «ጌታ ያንን የቢራ ማሰሮ አይወደውም።» ልቧም ፈጥኖ «እንግዲያስ መወገድ አለበት» ብሎ መለሰ። ማሰሮው ከባድ ነበር፤ ስለዚህ በአጠገቡ ተንበርክካ እንዲህ ብላ ጸለየች፦ «ጌታ ሆይ፥ ከእኔ ጋር ወደ ቤት መጥተሃል። በዚህ ጎጆ ውስጥ ትኖራለህ፤ ይህም ቢራ እዚህ እንዲሆን እንደማትፈልግ አውቃለሁ። እባክህ እንዳፈሰው ብርታትን ስጠኝ።» እግዚአብሔርም ብርታትን ሰጣት፤ ብዙም ሳይቆይ ቢራው በመንገዱ ላይ ይፈስስ ነበር። ከዚያም ወደ ውስጥ ተመልሳ ተንበረከከችና ስለ ረዳት ጌታን አመሰገነች። እንዲህም ብላ ጨመረች፦ «አሁንም ጌታ ሆይ፥ በዚህ ጎጆ ውስጥ የማትወደው ሌላ ነገር ቢኖር አሳየኝ፤ እርሱንም አስወግደዋለሁ።» ይህ በመዝሙራችን መጨረሻ ላይ ላለው መልእክት ፍጹም ምሳሌ አይደለምን?
«አቤቱ፥ የሚጠሉህን እኔ የጠላሁ አይደለሁምን? በሚቃወሙህስ የተሰቀቅሁ አይደለሁምን? ፈጽሜ ጠላኋቸው፤ እንደ ጠላቶቼም እቈጥራቸዋለሁ።
አቤቱ፥ መርምረኝ፥ ልቤንም እወቅ፤ ፈትነኝ፥ አሳቤንም እወቅ።
በእኔ ዘንድ የክፋት መንገድ ቢኖር እይ፥ ለዘላለምም በቀናው መንገድ ምራኝ።» ብርሃን ጨለማን እንደሚያባርር፣ እንዲሁ ተገንዝበን የምንኖርበት የእግዚአብሔር ሀልዎት ኃጢአትን ያባርራል። በእምነት በሀልዎቱ የምታድር ነፍስ እጅግ እውነተኛና አስደናቂ መዳንን ታውቃለች።
እንግዲህ አንዳንዶች «ይህ ሀልዎት ለእኔ እውን እንዲሆን እንዴት ላገኘው እችላለሁ?» ብለው እንደሚጠይቁ ተስፋ አደርጋለሁ። ስለዚህ በጥቂት ተግባራዊ ምክሮች እደመድማለሁ። በመጀመሪያ፣ ሐቅ መሆኑን ከቅዱሳት መጻሕፍት ራስህን አሳምን። ተሞክሮዎቻችን ሁልጊዜ በሐቆች ላይ ሊመሠረቱ ይገባቸዋል። ያለ እነርሱ ተሞክሮዎቹ ዋጋ ቢሶች ናቸው። ሐቁን የሚያስገኘው ስሜቱ አይደለም፤ ስሜቱን የሚያስገኘው ሐቁ ነው እንጂ። ከሁሉ አስቀድሞ እያንዳንዱ ነፍስ የሚያስፈልገው ይህ ነው።
የእግዚአብሔር የገዛ ቃላት ከጥርጥር በላይ ሊያሳምኗቸው ይገባል። ከእኛ ጋር ያለው ሀልዎቱ የማያቋርጥ እንደ ሆነ የማይለወጥ ሐቅ አድርገው ሊያውቁ ይገባቸዋል።
ከዚያም ይህ ነጥብ ከተረጋገጠ በኋላ እውን ልናደርገው ይገባናል። አንድ የጥንት ጸሐፊ እንዳለው፣ ሁልጊዜና በየስፍራው፣ በሁሉም ነገር «ሀልዎቱን ልንለማመድ» ይገባናል። የመጽሐፍ ቅዱስን ትእዛዝ ልትታዘዝ ይገባሃል። «በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ» ይላል። ስለዚህ በየሰዓቱና በየቅጽበቱ «ጌታ እዚህ አለ» በል። ሁሉን፣ መብላትና መጠጣትን እንኳ፣ በፊቱና ለእርሱ አድርግ። ቃል በቃል «የምትበሉ ወይም የምትጠጡ ብትሆኑ ወይም ማናቸውን ነገር ብታደርጉ ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት»። ይህን የማያቋርጥ «ሀልዎቱን የመለማመድ» ልማድ በመከተል ነፍስ የእምነት ልማድ ታገኛለች። በመጨረሻም መጀመሪያ ላይ ማመን አስቸጋሪ እንደ ነበረ ሁሉ ሀልዎቱን መጠራጠር አስቸጋሪ ይሆንባታል።
ይህ ታላቅ ጥረትን አይጠይቅም፤ የማይናወጥ እምነትን ብቻ ይጠይቃል። በዚህ ረገድ የሚረዳህ የተጠና ምክንያታዊነት ወይም የተራቀቀ ማሰላሰል አይደለም። ነፍስ በቀላል እምነት እግዚአብሔር እንደሚገኝ ልትገነዘብ ይገባታል። ከዚያም በነጻነትና በቅለት ስለ ሁሉ ነገር ሁልጊዜ ልታነጋግረው ይገባታል። እርሱ ከእኛ ታላላቅ ነገሮችን አይፈልግም። የሚጠይቀው እጅግ ጥቂት ነው። ሀልዎቱን ጥቂት ማስታወስ። ጥቂት የፍቅርና የመተማመን ቃላት። በዕለት ሥራዎቻችን መካከል ልብን ለአፍታ ወደ እርሱ ማንሣት። ቅርብና አፍቃሪ ወዳጅ ወደ ሆነው ወደ እርሱ ዘወትር መቅረብ። በሀልዎቱ ስሜት የመኖርና በዚህም ምክንያት ልባችን «ተዘልሎ እንዲቀመጥ» የመፍቀድ ምኞት። ትንሹ ማስታወስ እንኳ በእርሱ ዘንድ የተወደደ ነው። ሀልዎቱን ለእኛ እውን ለማድረግ ይረዳል።
በዚህ ልምምድ የሚጸና ማንም ቢሆን ብዙም ሳይቆይ የተባረከ መገንዘብን ያገኛል። በዚህ መጽሐፍ ልነግር ስለ ሞከርሁት ሁሉ፣ ልነግረውም ስለማልችለው ስለሚበልጠው ነገር ሁሉ፣ ስለ ጌታችን የተነገሩትን እነዚያን ድንቅ ቃላት ከቃላት በላይ እንድትረዳቸው ተስፋ አደርጋለሁ፦ «ስሙንም አማኑኤል ይሉታል፥ ትርጓሜውም። እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚል ነው።»
ፍጻሜ
ምዕራፍ 22 ተጠናቋል
መቶ ሠላሳ ዘጠነኛው መዝሙር