ምዕራፍ 3 · 6 ደቂቃ ንባብ
በእውነት የሚሰግዱ
«በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል አሁንም ሆኖአል፤ አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና፤ እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል።»—ዮሐንስ 4:23-24።
ኢየሱስ ለሳምራዊቷ ሴት የተናገራቸው እነዚህ ቃላት፣ ስለ ጸሎት ጉዳይ ከሰጠው ትምህርት ተጽፎ የተገኘው የመጀመሪያው ነው። ወደ ጸሎት ዓለም አንዳንድ ድንቅ የመጀመሪያ ቅኝቶችን ይሰጡናል። አብ ሰጋጆችን ይሻል፤ አምልኮአችን አፍቃሪ ልቡን ያረካል፣ ለእርሱም ደስታ ነው። በእውነት የሚሰግዱትን ይሻል፤ ነገር ግን እርሱ እንደሚወዳቸው ያልሆኑ ብዙዎችን ያገኛል። እውነተኛ አምልኮ በመንፈስና በእውነት የሆነ ነው። ወልድ የመጣው ለዚህ በመንፈስና በእውነት ለሚሆን አምልኮ መንገድን ሊከፍትና ሊያስተምረን ነው። ስለዚህ በጸሎት ትምህርት ቤት ከምንማራቸው የመጀመሪያ ትምህርቶች አንዱ፣ በመንፈስና በእውነት መጸለይ ምን እንደ ሆነ መረዳትና ወደዚያ እንዴት መድረስ እንደምንችል ማወቅ መሆን አለበት።
ጌታችን ለሳምራዊቷ ሴት ስለ ሦስት ዓይነት አምልኮ ተናገረ። በመጀመሪያ የሳምራውያን አላዋቂ አምልኮ አለ፦ «እናንተስ ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ።» ሁለተኛው፣ እውነተኛ የእግዚአብሔር እውቀት ያለው የአይሁዳዊው አስተዋይ አምልኮ ነው፦ «እኛ መዳን ከአይሁድ ነውና ለምናውቀው እንሰግዳለን።» ሦስተኛውም እርሱ ራሱ ሊያስገባው የመጣው አዲሱ፣ መንፈሳዊው አምልኮ ነው፦ «በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል አሁንም ሆኖአል።» ከአገባቡ እንደምንረዳው፣ «በመንፈስና በእውነት» የሚሉት ቃላት ብዙ ጊዜ እንደሚታሰበው በትጋት፣ ከልብ፣ በቅንነት ማለት አይደሉም። ሳምራውያን አምስቱ የሙሴ መጻሕፍትና የእግዚአብሔር የተወሰነ እውቀት ነበራቸው፤ በመካከላቸውም እግዚአብሔርን በጸሎት በቅንነትና በትጋት የፈለጉ ከአንድ በላይ ሰዎች እንደ ነበሩ ጥርጥር የለውም። አይሁድ እስከዚያ ጊዜ ድረስ በተሰጠው ቃሉ ውስጥ የእግዚአብሔር እውነተኛና ሙሉ መገለጥ ነበራቸው፤ በመካከላቸውም እግዚአብሔርን በፍጹም ልባቸው የጠሩ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ነበሩ። ነገር ግን በቃላቱ ሙሉ ትርጕም «በመንፈስና በእውነት» አልነበረም። ኢየሱስ «ጊዜ ይመጣል አሁንም ሆኖአል፤» ይላል፤ የእግዚአብሔር አምልኮ በመንፈስና በእውነት የሚሆነው በእርሱና በእርሱ በኩል ብቻ ነው።
በክርስቲያኖች መካከል ዛሬም ሦስቱን ዓይነት ሰጋጆች እናገኛለን። አንዳንዶች ካለማወቃቸው የተነሣ የሚለምኑትን እንኳ በቅጡ አያውቁም፤ በትጋት ይጸልያሉ፣ ነገር ግን የሚቀበሉት እጅግ ጥቂት ነው። ሌሎች ደግሞ የበለጠ ትክክለኛ እውቀት ያላቸው፣ በሙሉ አእምሮአቸውና ልባቸው ለመጸለይ የሚጥሩ፣ ብዙ ጊዜም እጅግ በትጋት የሚጸልዩ አሉ፤ ነገር ግን በመንፈስና በእውነት ወደሚሆን የአምልኮ ሙሉ ብፅዕና አይደርሱም። ጌታችን ኢየሱስ ወደዚህ ወደ ሦስተኛው ክፍል እንዲያስገባን ልንለምነው ይገባል፤ በመንፈስና በእውነት እንዴት እንደምንሰግድ ከእርሱ መማር አለብን። መንፈሳዊ አምልኮ ይህ ብቻ ነው፤ አብ የሚሻቸውን የመሰሉ ሰጋጆች የሚያደርገንም ይህ ነው። በጸሎት ሁሉም ነገር በመንፈስና በእውነት የሚሆነውን አምልኮ በሚገባ በመረዳታችንና በመለማመዳችን ላይ የተመሠረተ ይሆናል።
«እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል።» መምህሩ በዚህ ያመለከተው የመጀመሪያው ሐሳብ፣ በእግዚአብሔርና በሰጋጆቹ መካከል ስምምነት መኖር እንዳለበት ነው፤ እግዚአብሔር እንደ ሆነ፣ አምልኮውም እንዲሁ መሆን አለበት። ይህም በፍጥረተ ዓለም ሁሉ በሚሠራ መርሕ መሠረት ነው፤ በአንድ ነገርና ያ ነገር ራሱን በሚገልጥለት ወይም በሚሰጥለት ብልት መካከል መጣጣምን እንጠብቃለን። ዓይን ለብርሃን፣ ጆሮም ለድምፅ ውስጣዊ ተስማሚነት አላቸው። እግዚአብሔርን በእውነት ሊያመልክ፣ እግዚአብሔርን ሊያገኝና ሊያውቅ፣ ሊወርስና ሊደሰትበት የሚወድ ሰው ከእርሱ ጋር መስማማት፣ እርሱንም የመቀበል ዐቅም ሊኖረው ይገባል። እግዚአብሔር መንፈስ ስለ ሆነ፣ በመንፈስ ልንሰግድ ይገባናል። እግዚአብሔር እንደ ሆነ፣ ሰጋጁም እንዲሁ ነው።
ይህስ ምን ማለት ነው? ሴቲቱ ትክክለኛው የአምልኮ ስፍራ ሰማርያ ወይስ ኢየሩሳሌም እንደ ሆነ ጌታችንን ጠይቃው ነበር። እርሱም ከእንግዲህ ወዲህ አምልኮ በአንድ ስፍራ እንደማይወሰን መለሰላት፦ «አንቺ ሴት፥ እመኚኝ፥ በዚህ ተራራ ወይም በኢየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ ይመጣል።» እግዚአብሔር መንፈስ እንደ መሆኑ፣ በቦታ ወይም በጊዜ ሳይታሰር፣ ወሰን በሌለው ፍጽምናው ሁልጊዜና በሁሉ ስፍራ ያው እንደ ሆነ፣ አምልኮውም እንዲሁ ከእንግዲህ ወዲህ በስፍራ ወይም በሥርዓት ሳይወሰን፣ እግዚአብሔር ራሱ መንፈሳዊ እንደ ሆነ መንፈሳዊ ይሆናል። ይህ እጅግ ጠቃሚ ትምህርት ነው። ክርስትናችን በተወሰኑ ጊዜያትና ስፍራዎች በመታጠሩ ምንኛ ይጐዳል! በቤተ ክርስቲያን ወይም በጓዳው በትጋት ለመጸለይ የሚሻ ሰው፣ የሳምንቱን ወይም የቀኑን አብዛኛውን ክፍል ሲጸልይ ከነበረበት መንፈስ ፈጽሞ በሚቃረን መንፈስ ያሳልፋል። አምልኮው የአንድ የተወሰነ ስፍራ ወይም ሰዓት ሥራ እንጂ የሁለንተናው አልነበረም። እግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ እርሱ የዘላለሙና የማይለወጠው ነው፤ እርሱ የሆነውን ሁልጊዜና በእውነት ነው። አምልኮአችንም እንዲሁ በመንፈስና በእውነት መሆን አለበት፤ እርሱን ማምለክ የሕይወታችን መንፈስ መሆን አለበት፤ እግዚአብሔር መንፈስ እንደ ሆነ ሕይወታችንም በመንፈስ የሆነ አምልኮ መሆን አለበት።
«እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል።» ወደ እኛ የሚመጣው ሁለተኛው ሐሳብ፣ በመንፈስ የሚሆነው አምልኮ ከእግዚአብሔር ራሱ መምጣት እንዳለበት ነው። እግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ የሚሰጠው መንፈስ ያለው እርሱ ብቻ ነው። መንፈስ ቅዱስን በመስጠት ለእንዲህ ያለ መንፈሳዊ አምልኮ ያበቃን ዘንድ ልጁን የላከው ለዚህ ነው። ኢየሱስ ሁለት ጊዜ «ጊዜ ይመጣል» ብሎ «አሁንም ሆኖአል» ብሎ ሲጨምር የሚናገረው ስለ ራሱ ሥራ ነው። በመንፈስ ቅዱስ ሊያጠምቅ መጣ፤ መንፈስም እርሱ እስኪከብር ድረስ ሊፈስ አልቻለም (ዮሐንስ 1:33፤ 7:37-38፤ 16:7)። ኃጢአትን ከጨረሰ በኋላ፣ በደሙም ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ገብቶ በዚያ ስለ እኛ መንፈስ ቅዱስን ከተቀበለ በኋላ (የሐዋርያት ሥራ 2:33) ነበር እንደ አብ መንፈስ ወደ እኛ ሊልከው የቻለው። ክርስቶስ ከዋጀን በኋላ፣ እኛም በእርሱ የልጆችን ስፍራ ካገኘን በኋላ ነበር አብ «አባ አባት» ብሎ የሚጮኽ የልጁን መንፈስ ወደ ልባችን የላከው። በመንፈስ የሚሆን አምልኮ፣ በክርስቶስ መንፈስ፣ በልጅነት መንፈስ የሚሆን የአብ አምልኮ ነው።
ኢየሱስ እዚህ የአብን ስም የሚጠቀመው ለዚህ ነው። ከብሉይ ኪዳን ቅዱሳን አንዱም እንኳ የልጅነትን ስም ለራሱ ሲወስድ ወይም እግዚአብሔርን አባቱ ብሎ ሲጠራ አናገኘውም። የአብ አምልኮ የሚቻለው የወልድ መንፈስ ለተሰጣቸው ብቻ ነው። በመንፈስ የሚሆን አምልኮ የሚቻለው ወልድ አብን ለገለጠላቸውና የልጅነትን መንፈስ ለተቀበሉ ብቻ ነው። መንገዱን የሚከፍትና በመንፈስ የሚሆነውን አምልኮ የሚያስተምር ክርስቶስ ብቻ ነው።
በእውነትም። ይህ በቅንነት ማለት ብቻ አይደለም። ደግሞም ከእግዚአብሔር ቃል እውነት ጋር በመስማማት ማለት ብቻ አይደለም። አገላለጡ ጥልቅና መለኮታዊ ትርጕም ያለው ነው። ኢየሱስ ከአባቱ ዘንድ ያለ አንድ ልጅ ሆኖ «ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ» በእኛ አደረ። «ሕግ በሙሴ ተሰጥቶ ነበርና፤ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ።» ኢየሱስ «እኔ … እውነት ሕይወትም ነኝ» ይላል። በብሉይ ኪዳን ሁሉ ጥላና ተስፋ ነበር፤ ኢየሱስ ግን እውነታውን፣ ተስፋ የምናደርገውን ነገር ተጨባጭ አካል አመጣ፣ ይሰጠናልም። በእርሱ የዘላለም ሕይወት በረከቶችና ኃይላት በእርግጥ ገንዘባችንና ልምምዳችን ናቸው። ኢየሱስ ጸጋንና እውነትን የተሞላ ነው፤ መንፈስ ቅዱስ የእውነት መንፈስ ነው፤ በእርሱ በኩል በኢየሱስ ያለው ጸጋ በተግባርና በእውነት የእኛ ይሆናል፤ ከመለኮታዊው ሕይወት የሚመጣ እውነተኛ ስጦታ ነው። ስለዚህ በመንፈስ የሚሆን አምልኮ በእውነት የሚሆን አምልኮ ነው፤ ከእግዚአብሔር ጋር ያለ ተጨባጭ ሕያው ኅብረት፣ መንፈስ በሆነው በአብና በመንፈስ በሚጸልየው ልጅ መካከል ያለ እውነተኛ መጣጣምና ስምምነት ነው።
ኢየሱስ ለሳምራዊቷ ሴት የተናገረውን ወዲያውኑ ልታስተውል አልቻለችም። ሙሉ ትርጕሙ እንዲገለጥ በዓለ ኀምሳ ያስፈልግ ነበር። ወደ ጸሎት ትምህርት ቤት ስንገባ በመጀመሪያው እንዲህ ያለውን ትምህርት ለመጨበጥ ገና አልተዘጋጀንም። ቆየት ብለን በተሻለ እንረዳዋለን። እርሱ እንደሚሰጠን ትምህርቱን ተቀብለን ብቻ እንጀምር። እኛ ሥጋውያን ነን፤ እግዚአብሔር የሚሻውን አምልኮ ልናቀርብለት አንችልም። ኢየሱስ ግን መንፈስን ሊሰጥ መጣ፤ ለእኛም ሰጥቶናል። ለመጸለይ የምንቀርብበት ዝንባሌ የክርስቶስ ቃላት ያስተማሩን ይሁን። ደስ የሚያሰኘውን አምልኮ ለእግዚአብሔር ማቅረብ እንደማንችል ጥልቅ ኑዛዜ፣ እርሱ እንዲያስተምረን የሚጠባበቅ የሕፃን የመማር ልብ፣ ራሱን ለመንፈስ እስትንፋስ የሚሰጥ ቀላል እምነት ይኑረን። ከሁሉ በላይ ይህን የተባረከ እውነት አጥብቀን እንያዝ—ጌታ ስለዚህ ብዙ የሚነግረን እንዳለው እናገኛለን—የእግዚአብሔርን አባትነት ማወቅ፣ ወሰን የሌለው አባትነቱ በልባችን መገለጡ፣ ልጆች ሊያደርገን ልጁንና መንፈሱን በሚሰጠን ወሰን በሌለው ፍቅር ማመን፣ በእርግጥ በመንፈስና በእውነት የመጸለይ ምሥጢር ነው። ክርስቶስ የከፈተልን አዲሱና ሕያው መንገድ ይህ ነው። ክርስቶስ ወልድና የወልድ መንፈስ በውስጣችን እየኖሩ አብን ሲገልጡልን፣ ይህ እውነተኛ፣ መንፈሳውያን ሰጋጆች ያደርገናል።
«ጌታ ሆይ፥ እንጸልይ ዘንድ አስተምረን።»
ብሩክ ጌታ ሆይ! አንድ ጽዋ ውኃ የከለከለችህን ሴት የእግዚአብሔር አምልኮ ምን መሆን እንዳለበት ያስተማርህበትን ፍቅር አመልካለሁ። በመንፈስና በእውነት ለመጸለይ በሚናፍቅ ልብ ወደ አንተ የሚመጣውን ደቀ መዝሙርህን አሁንም ከዚያ ባላነሰ እንደምታስተምረው በማረጋገጥ ደስ ይለኛል። ቅዱስ መምህሬ ሆይ! ይህን የተባረከ ምሥጢር እባክህ አስተምረኝ።
በመንፈስና በእውነት የሚሆነው አምልኮ ከሰው እንዳልሆነ፣ ነገር ግን ከአንተ ብቻ እንደሚመጣ፣ የጊዜያትና የወቅቶች ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በአንተ ያለ ሕይወት ፍሰት እንደ ሆነ አስተምረኝ። ባለማወቄና ለእርሱ የማቀርበው ምንም ነገር በራሴ እንደሌለኝ በጥልቅ እየተሰማኝ፣ በዚያው ጊዜም አዳኜ ሆይ፣ በሕፃን መንተባተቤ ውስጥ መንፈስ እንዲተነፍስ አንተ ያዘጋጀኸውን እያሰብሁ፣ በጸሎት ወደ እግዚአብሔር መቅረብን አስተምረኝ። በአንተ ልጅ እንደ ሆንሁ፣ የልጅም የመቅረብ ነፃነት እንዳለኝ፣ በአንተም የልጅነትና በእውነት የማምለክ መንፈስ እንዳለኝ እባርክሃለሁ። የአብ ብሩክ ልጅ ሆይ፣ ከሁሉ በላይ በጸሎት መተማመንን የሚሰጠው የአብ መገለጥ እንዴት እንደ ሆነ አስተምረኝ፤ የእግዚአብሔር ልብ ወሰን የሌለው አባትነትም ለጸሎትና ለአምልኮ ሕይወት ደስታዬና ብርታቴ ይሁን። አሜን።
ምዕራፍ 3 ተጠናቋል
በእውነት የሚሰግዱ