ምዕራፍ 2 · 5 ደቂቃ ንባብ · 7 ደቂቃ ማዳመጥ
ንጽሕና ታዝዟል
ዕብራውያን 12:14 እንዲህ ይላል፦ «…ትቀደሱም ዘንድ ፈልጉ፥ ያለ እርሱ ጌታን ሊያይ የሚችል የለምና።»
ውድ ወዳጆቼ ሆይ፥ ባለፈው ደብዳቤዬ የጻፍሁበትን ርእስ እንደ ገና ላነሣ እወዳለሁ። በእውነትም የከበረ ርእስ ነው። በሃይማኖት ሕይወቴ ሁሉ ወድጄዋለሁ፤ ስለ እርሱም ተናግሬአለሁ፤ ዛሬም የንጹሕ ልብን በረከት መደሰትና ማወጅ ለራሴ ሰላም፣ ኃይልና ጠቃሚነት እጅግ አስፈላጊ እንደ ሆነ፣ ለሠራዊቱም እድገትና ብልጽግና እንደ ቀድሞው ሁሉ አስፈላጊ እንደ ሆነ እቈጥረዋለሁ።
ርእሱን በትክክል መረዳት ይህን በረከት ለራሳችሁ እንድታገኙ ይረዳችኋል፤ ለሌሎችም እንድታብራሩት ያስችላችኋል።
ባለፈው ደብዳቤዬ ስለ ንጽሕና በጠቅላላ ተናገርሁ፤ በዚህኛው ደግሞ ርእሱ በእናንተ ሕይወት በተግባር እንዴት እንደሚሠራ ጥቂት ልናገር እወዳለሁ። ውዱ ጌታችን ስለ «ልበ ንጹሖች» ሲናገርና ብፁዓን ሲላቸው ምን ማለቱ ነበር? ንጹሕ ልብ መያዝ ምን ማለት ነው? ለዚህ ጥያቄ መልስ ለመስጠት ሌላ ጥያቄ በመጠየቅ መጀመር አለብኝ፦ ልብ ሲባል ምን ማለት ነው? ለዚህም ጥያቄ እንዲህ ብዬ እመልሳለሁ፦ በደረታችሁ ውስጥ ሲመታ የሚሰማችሁን፣ የሰውነት ሥርዓት ማዕከላዊ ኃይል የሆነውን ያን ብልት ማለታችን አይደለም። ያ የሰው እጅግ አስፈላጊ ክፍል ነው፤ በጥሩ ሁኔታ መጠበቁም እጅግ አስፈላጊ ነው።
ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ክፍል የተናገረለትና እኔም ልነግራችሁ የምፈልገው በሰውነታችሁ ያለውን ልብ አይደለም፤ የነፍሳችሁ ማዕከላዊ ኃይል በመሆኑ ከእርሱ ጋር ይመሳሰላል ሊባል የሚችለውን ያን ኃይል ነው እንጂ። በደረታችሁ ውስጥ የሚመታው ልብ የተፈጥሮ ሰው ታላቅ አንቀሳቃሽ ኃይል እንደ ሆነ፥ እኛ የምንናገርለት ልብም የመንፈሳዊ ሰው ታላቅ አንቀሳቃሽ ኃይል ነው።
(ሀ) በዚህ ትርጉም ደስታን ወይም ኀዘንን የሚሰማው ልባችሁ ነው። «ያቺ ምስኪን ሴት ባሏ በሚያደርስባት በደል ልቧ ተሰብሮ ሞተች» ስትሉ፥ የገደላት የነፍሷ መራራ ጭንቀት ነው ማለታችሁ ነው።
(ለ) በትክክልና በስሕተት መካከል የሚመርጠው ልብ ነው። «የወንድሜ ልብ ከእግዚአብሔር፣ ከበጎነትና ከእውነት ጎን ነው» ስትሉ፥ እነዚህ ነገሮች የነፍሱ ታላቅ ምርጫ ናቸው ማለታችሁ ነው።
(ሐ) የሚከተለውን የአካሄድ መንገድ የሚወስነው ልብ ነው። «ይህ ወጣት ወደ ንስሐ መንበሩ ሄዶ ልቡን ለእግዚአብሔር ሰጠ» ስትሉ፥ መዳንን ለመቀበልና የክርስቶስ ወታደር ለመሆን በውስጠኛው ነፍሱ ወሰነ ማለታችሁ ነው።
(መ) ጽድቅን የሚወደውና ዓመፃን የሚጠላው ልብ ነው። እግዚአብሔር «ልጄ ሆይ፥ ልብህን ስጠኝ» ሲል፥ «አንተ ወጣት ወንድም ሆንክ ሴት፣ ና፤ ባለህ ኃይል ሁሉ እኔንና ቅድስናን ነፍሳትንም ውደድ፤ ዲያብሎስንና ኃጢአትንም ጥላ» ማለቱ ነው።
(ሠ) ጠባይን የሚቀርጸው፣ ምርጫን የሚመራውና የሰውን የሕይወት አካሄድና ምግባር ሁሉ የሚገዛው ልብ ነው። ልብ የመርከቡ አለቃ ነው። ሰው ምሕረትን ተቀብሎ፣ እግዚአብሔርን አገልግሎ፣ ጽድቅን ተከትሎ፣ ለባልንጀሮቹ መዳን ኖሮ በመጨረሻ በድል አድራጊነት ወደ ሰማያዊው ወደብ ይገባ እንደ ሆነ፥ ወይስ በዓመፅ ሕይወት ኖሮ፣ በኃጢአቱ ሞቶ፣ በዘላለም የተስፋ መቍረጥ ዓለቶች ላይ ተሰባብሮ ፍጻሜው ይሆን እንደ ሆነ የሚወስነው እርሱ ነው። ስለዚህ ለእያንዳንዳችን በጎ፣ ቅንና ንጹሕ ልብ መያዝ ምንኛ አስፈላጊ ነው!
እንግዲህ ጓዶቼ ሆይ፥ ልብ ሰውን እንዲህ ፈጽሞ የሚገዛ ከሆነ፥ ያ ልብ ንጹሕ መሆን እንዳለበት ከዚህ የበለጠ ግልጽ የሆነ ነገር ሊኖር ይችላልን? ነገር ግን ንጹሕ ልብ ምንድን ነው?
በኢየሱስ ክርስቶስ ደም አማካይነት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የነጻ ልብ መያዝ ምን ማለት ነው? ይህ እጅግ አስፈላጊ ጥያቄ ነው፤ ልመልሰው ስጥር ውድ ወታደሮቼ በጥንቃቄ እንደሚያዳምጡኝ እጅግ ተስፋ አደርጋለሁ።
1. በመጀመሪያ፥ ንጹሕ ልብ ክፉ ለማድረግ ፈጽሞ የማይፈተን ልብ አይደለም። ያልተፈተነ ልብ፥ ማለትም በአንድ ወይም በሌላ ዓይነት ኃጢአት ለመሥራት ለፈተና ፈጽሞ ያልተጋለጠ ወንድ ወይም ሴት፥ ምናልባት በዚህ ዓለም ውስጥ የለም፤ ከቶም ኖሮ አያውቅም። ብሩክ ጌታችን በምድረ በዳ በዲያብሎስ የተፈተነ ብቻ ሳይሆን በሕይወቱ ዘመን ሁሉ በክፉ መሳቢያዎች ተከብቦ ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ አዳኛችን በነገር ሁሉ እንደ እኛ እንደ ተፈተነ በግልጽ ይነግረናል፤ ነገር ግን ሃሌ ሉያ! ዓለምን፣ ሥጋንና ዲያብሎስን ተቋቋመ፤ ከዚያም አስጨናቂ ፈተና ያለ አንዳች እድፍ ወጣ። በሁሉም ላይ ድል ነሣ፤ ሐዋርያው በደስታ ተሞልቶ የተፈተነው «ከኃጢአት በቀር» እንደ ሆነ ያረጋግጥልናልና።
ጓዶቼ ሆይ፥ በምድራዊ ጕዞአችሁ ሁሉ፥ እስከ ሰማይ ደጆች ድረስ እንኳ ትፈተናላችሁ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ይመስገን፥ ፈተና ኃጢአት አይደለም፤ በምድር ማማለያዎችና በሲኦል ተንኰሎች ሁሉ ላይ ድል እንድትነሡ ጸጋ፥ የተትረፈረፈ ጸጋ ተዘጋጅቶላችኋል። ከአሸናፊዎች ልትበልጡ ትችላላችሁ። ነገር ግን አስታውሱ፥ ንጹሕ ልብ ቢኖራችሁም ከፈተና ጋር መዋጋት ይኖርባችኋል።
2. ንጹሕ ልብ መከራን ሊቀበል የማይችል ልብ አይደለም። ኢየሱስ ክርስቶስ ንጹሕ ልብ እንደ ነበረው አያጠራጥርም፤ ቅዱስና ነውር የሌለበት ነበረ፤ ቢሆንም «የሕማም ሰው» ነበረ። ጳውሎስ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ሁልጊዜ ነውር የሌለባት ሕሊና እንድትኖረው ቢተጋም፥ አንዳንድ ጊዜ «በልዩ ልዩ ፈተና ከማዘን» እንዳልዳነ ይነግረናል።
የጥንት ቅዱሳን ሁሉ የጨለማና የጭንቀት ሰዓታት ነበሩባቸው፤ ብዙዎቹም በመከራ ባሕር ውስጥ አልፈዋል። ከጥንቶቹ ቅዱሳን ጋር እንደ ነበረውም ከዘመናችን ቅዱሳን ጋር እንዲሁ ነው። በጭንቀታችን ውስጥ ለአለማመን፣ ለተስፋ መቍረጥና ለክፉ ሥራ እጅ ካልሰጠን ማልቀስና መተከዝ ኃጢአት አይደለም። ወንድሞችና እኅቶች ሆይ፥ አይዞአችሁ! «በጎርፍና በነበልባል ተከባችሁ» ሳላችሁ «መንገዳችሁን መቀጠል» አለባችሁ። ማመናችሁን ከቀጠላችሁ አታፍሩም፤ እግዚአብሔር ያድናችኋል።
3. ንጹሕ ልብ ስንል ኃጢአት ሊሠራ የማይችል ልብ ማለታችን አይደለም። ዲያብሎስ በአንድ ወቅት ውብና ኃጢአት የሌለበት ፍጡር ነበረ። ነገር ግን ለፈተና እጅ ሰጠ። የኃጢአት አልባነት አክሊል ከውቡ ግንባሩ ወደቀ፤ ከንጹሕ የመላእክት አለቃነት ወደ ርኩስ ጋኔንነት ተለወጠ፤ ከብሩሁና ኃጢአት ከሌለበት ሰማዩ እስከ ጨለማውና ጭጋጋማው ሲኦሉ ድረስ ተወረወረ። አዳም ከፈጣሪው እጅ በወጣ ጊዜ ንጹሕ ነበረ። እግዚአብሔር መልካም እንደ ሆነ ተናገረለት፤ ነገር ግን በሰይጣን ተታልሎ ንጽሕናውን አጣ፤ ከኤደንም ተባርሮ ወደ ኃጢአት፣ ወደ ኀዘንና ወደ ሞት ዓለም ተጣለ።
ቅዱሳንና ወታደሮች ከቅድስና ወደ ኃጢአት ሲወድቁ ብዙ ጊዜ ማየት ቃል የማይገልጸው ኀዘን ሆኖብናል። በዙሪያችን ካሉት ብዙ ምስኪን ወደ ኋላ የተመለሱ ሰዎች አንዳንዶቹ በአንድ ወቅት ከእግዚአብሔር ጋር በቅርበት ተመላልሰዋል፤ ልብሳቸውን ከዓለም እድፍ ጠብቀዋል፤ ንጹሕና መልካም ለሆነው ነገር ሁሉ ምሳሌ ነበሩ። ነገር ግን ወደ ደካማውና ወደሚናቀው የዓለም ነገር ተመልሰዋል፤ የታጠበች እርያ በጭቃ ለመንከባለል ትመለሳለች እንደሚባለው ዳግመኛ በጭቃ ውስጥ እየተንከባለሉ ነው። ስለዚህ ጓዶቼ ሆይ፥ የቱንም ያህል ንጹሖች ብትሆኑ ኃጢአት መሥራት ለእናንተ የሚቻል መሆኑን ታያላችሁ። ልብሳችሁን ነጭ አድርጋችሁ ብታጥቡ፣ ለተወሰነ ጊዜም በቅዱስ ኅብረት ከእግዚአብሔር ጋር ብትመላለሱ፣ ተራሮችን የሚያፈልስና ብዙዎችን የሚያድን እምነት ቢኖራችሁ እንኳ፥ በዚህ ሕይወት እስካላችሁ ድረስ ከጸጋ ልትወድቁ እንደምትችሉ ማስታወስ አለባችሁ።
ለራሳችሁ ካልተጠነቀቃችሁ፣ ካልተጋችሁና ካልጸለያችሁ በሚከብባችሁ ኃጢአት እንደምትያዙ፣ ሌሎችንም ካዳናችሁ በኋላ ራሳችሁ የተጣላችሁ እንደምትሆኑ እጅግ የሚመስል መሆኑን ማስታወስ አለባችሁ። ስለዚህ «እንደ ቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ።»
4. ንጹሕ ልብ ስንል የቱንም ያህል የተባረከ ቢሆን በደስታ፣ በጠቃሚነትና በኃይል ሊጨምር የማይችልን የንጽሕና ተሞክሮ ማለታችን አይደለም። ከአትክልት ቦታችሁ አረሙን ንቀሉ፤ አበቦቹ፣ ተክሎቹና ዛፎቹም ፈጥነው ያድጋሉ፣ በብዛት ያብባሉ፣ የበለጠም ፍሬያማ ይሆናሉ።
በዚህችው ቅጽበት ኢየሱስ ክርስቶስ የነፍሳችሁን የአትክልት ቦታ ከቅናትና ከትዕቢት ያጽዳ፤ የክፋትንና የራስ ወዳድነትን መርዛማ ተክሎች፣ ሌላውንም ክፉ ነገር ሁሉ ይንቀል፤ እምነት፣ ሰላም፣ ተስፋ፣ ፍቅር፣ ትሕትና፣ ድፍረትና ሌሎቹም የገነት ውብ አበቦች ሁሉ ይበልጥ በሚያስደንቅ ውበትና በተትረፈረፈ ፍሬያማነት ይለመልማሉ።
ወይ! አሁን በእግዚአብሔር ፊት ተንበርክካችሁ ራሳችሁን ፈጽማችሁ በከበረው አዳኛችሁ እጅ አትሰጡምን? ሊቀድሳችሁ እየጠበቀ ነው። የሚያሰናክላችሁን ሁሉ ከመርከቡ ወደ ባሕር ጣሉት። ልብን የሚያነጻ እግዚአብሔር ነው። ሥራውን እንዲሠራ ትፈቅዱለታላችሁን? አሁን በእምነት እንዲህ ብላችሁ ጩኹ፦ «ቍጣና ስንፍና፣ ምኞትና ትዕቢት፣ በዚህች ቅጽበት ተሸነፉ፤ ወደ ቤዛዬ ደም ቀይ ጎርፍ ተጣሉ።»
ነገር ግን ጓዶቼ ሆይ፥ ጥቂት ወደ ፊት መሄድ አለባችሁ፤ በድፍረትና በእምነትም ይህን የድል መዝሙር ዘምሩ፦ «ተፈጸመ፤ በዚህች ቅጽበት አድን፣ በሙሉ መዳንም ባርክ፤ በደምህ ቤዛነት አለኝ፤ ነውር የሌለበት ፍቅርና ሰላምም አለኝ።»
«መንፈስ ቅዱስ ሆይ፥ ቅዱስ እሳት ሆይ፥ ና፤ አሁን ምድራዊ መቅደሶችህን ና ሙላ፤ ከወራዳ ምኞት ሁሉ ባዶ ሆነዋልና አንተ ብቻ በውስጣቸው ንገሥ። ሉዓላዊ መብትህን፣ በአሳብ ሁሉና በኃይል ሁሉ ላይ ያለህን ቸር ባለቤትነትህን አውቀን፥ ሕይወታችን ስምህን እንዲያከብር በዚህች ቅዱስ ሰዓት ለአንተ እንሰጣለን። የነፍስን ክፍል ሁሉ ሙላ፤ አሳባችንን ሁሉ፣ ስሜታችንንም ሙላ፤ በላቀው ሥልጣንህ ሥር በደስታ ፈቃዳችንን እስክናስገዛ ድረስ። ተፈጸመ! በዚህች ቅጽበት ና፤ የምትናፍቀው ነፍሴ ፈጽማ የአንተ ናት፤ ልቤ የምትኖርበት ቤትህ ነው። ከእንግዲህ ለአንተ ብቻ እኖራለሁ።»
ምዕራፍ 2 ተጠናቋል
ንጽሕና ታዝዟል