ምዕራፍ 1 · 3 ደቂቃ ንባብ · 4 ደቂቃ ማዳመጥ
መግቢያ
ቄስ ኤድዋርድ መኬንድሪ ባውንድስ ለሚወደው ጌታውና መድኃኒቱ ለኢየሱስ ክርስቶስ በፍጹም ፍቅር የተሰጠ ሰው ነበር። ከእንቅልፍ ሰዓታት በቀር ሁልጊዜ ይጸልይና ስለ እርሱ ይጽፍ ስለ ነበር መሰጠቱ ያልተለመደ ነበር።
እግዚአብሔር ለባውንድስ የልብ ስፋትንና እርሱን ለማገልገል የማይጠግብ ምኞትን ሰጠው። ለዚህም ዓላማ እኔ ከሁሉ የላቀ መነሣሣት ብዬ ልጠራው የምወደውን ጸጋ አግኝቶ ነበር፤ አለዚያማ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ካወቅነውና ካነበብነው ሁሉ እጅግ የሚልቁትን አዲሱንና አሮጌውን ነገሮች ከመዝገቡ ፈጽሞ ሊያወጣ ባልቻለ ነበር።
ባውንድስ በመንፈሳዊ ጽሑፎች ሰማይ ላይ ያለ ጥርጥር እንደ ቤቴልጊዝ ኮከብ ደምቆ የሚያበራ ነው። ከሐዋርያት ዘመን ወዲህ ከኖሩት ሰዎች መካከል የጸሎትን ሕይወት በመመርመር ረገድ በአስደናቂ ምርምሩ ጥልቀት የበለጠው አንድም ሰው የለም።
ጌታ «መልካም፥ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ፤ … ወደ ጌታህ ደስታ ግባ» ባለው ጊዜ ባውንድስ በእጅ ጽሑፎቹ ላይ በትጋት እየጻፈ ነበር። በ1911፣ በ1912 እና በ1913 በብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ ወደ እኔ ይልካቸው የነበሩት ደብዳቤዎቹ ብዙ ጊዜ «የእጅ ጽሑፎቹን እጨርስ ዘንድ እግዚአብሔር አዲስ ብርታትና አዲስ ራእይ እንዲሰጠኝ ጸልይልኝ» ይሉ ነበር።
ጆን ዌስሊ እጅግ ጣፋጭና ይቅር ባይ ጠባይ ነበረው፤ በተቈጣ ጊዜ ግን «እጅግ የሰላ ማስተዋልና እንደ ጅራፍ ምት የሚነድፍ የንግግር ስጦታ» የነበረው ሰው ነበር። ባውንድስ የዋህና ትሑት ነበር፤ ከጠላቶቹ አንዱንም ሲበቀል ፈጽሞ አላየነውም። ስለ እነርሱ አለቀሰ፤ በማለዳም በምሽትም ስለ እነርሱ እያነባ ይጸልይ ነበር።
ዌስሊ በቀላሉ ይታለል ነበር። ወንድሙ ቻርልስ ዌስሊ በአንድ ወቅት በምሬት ድምፅ «ወንድሜ» አለ፤ «የተወለደው ለአታላዮች ጥቅም ይመስለኛል።» ባውንድስን ግን ማንም ሊያታልለው አይችልም ነበር። ሰውን አንብቦ በመለየት ረገድ ብርቅ ችሎታ ነበረው። በስም ብቻ ሃይማኖተኛ ከሆኑ አስመሳዮች ሁሉ ይርቅ ነበር፤ በእነርሱም ላይ ጊዜውን አያባክንም ነበር።
ዌስሊ ቀኑን ሙሉ ይሰብክና በፈረስ ይጓዝ ነበር። ባውንድስ ቀንና ሌሊት ይጸልይና ይጽፍ ነበር።
ዌስሊ በኋለኞቹ ዓመታቱ የአስተምህሮ አቋሙ በምንም መንገድ እንዲዛባ አይፈቅድም ነበር። ባውንድስም በዚህ ረገድ እርሱን በጣም ይመስል ነበር።
ዌስሊ ገና በሕይወት ሳለ ዝናን አተረፈ። ሁልጊዜ በሕዝብ ዓይን ፊት ነበር። ባውንድስ ግን ለአሥራ ሁለት ዓመታት የክሪስቺያን አድቮኬት ጋዜጣ አርታኢ ሆኖ ሳለ እንኳ ከቤተ ክርስቲያኑ ውጭ ብዙም አይታወቅም ነበር።
ዌስሊ በሰማንያ ስድስት ዓመቱ እንኳ በጎዳናዎች ላይ ለሠላሳ ደቂቃ መስበክ ይችል ነበር። ባውንድስ በሰባ አምስት ዓመቱ በሌሊቱ አራተኛ ክፍል የመጀመሪያ ሰዓት ተነሥቶ በጉልበቱ ተንበርክኮ ለሦስት ሰዓት መጸለይ ይችል ነበር።
ዌስሊ በሞተበት ጊዜ ለሃምሳ ስድስት ዓመታት በክብርና በተቀባይነት ኖሮ ነበር። ስሙ በሰው ሁሉ አፍ ላይ ነበር። በብርቱ ስብከቱና በድርጅቱ ክርስትና በእንግሊዝ ዳግመኛ ተወለደ። ባውንድስ ለሃምሳ ዓመታት ያህል በአንጻሩ የማይታወቅ ነበር፤ በሚቀጥሉት ሃምሳ ዓመታት ግን «የጠፋውንና የተረሳውን የቤተ ክርስቲያን ምሥጢር» መልሶ ያስገኛል።
የዌስሊ መንፈሳዊነት፣ ተሰጥኦና ተወዳጅነት ገና ከወጣትነቱ ጀምሮ እንደ ግርማዊ ወንዝ ይፈስ ነበር። የባውንድስ ግን ተገድቦ ቆይቷል፤ አሁን ግን በማይገታ ኃይል መጥለቅለቅ ጀምሯል፤ ብዙም ሳይቆይ እርሱ የመንፈሳዊ ጽሑፎች ዓለም ታላቁ የአማዞን ወንዝ ይሆናል።
ሄንሪ ክራብ ሮቢንሰን ዌስሊ በኮልቼስተር ሲሰብክ በሰማ ጊዜ በማስታወሻ ደብተሩ እንዲህ ብሎ ጻፈ፦ «ሰፊ በሆነ መድረክ ላይ ቆሞ ነበር፤ በግራና በቀኙም አንድ አንድ አገልጋይ ቆመው ሁለቱ ደግፈው ያዙት። ድምፁ ደካማ ነበር፤ በጭንቅም ይሰማ ነበር፤ ነገር ግን የተከበረው ፊቱ፣ በተለይም ረጅሙ ነጭ ጸጉሩ፣ ፈጽሞ የማይረሳ ሥዕል ፈጠረ።» የእነዚህ መስመሮች ጸሐፊ በ1912፣ ባውንድስ ከመሞቱ ልክ ከአሥር ወር በፊት፣ በብሩክሊን የነበረውን መድረኩን ለቄስ ኢ. ኤም. ባውንድስ ለቀቀለት። ድምፁ ደካማ ነበር፤ ዓረፍተ ነገሮቹም ተሟልተው አይጠናቀቁም ነበር። ስብከቱ ሃያ ደቂቃ ብቻ ነበር፤ ከዚያም በጸጥታ ወደ መደምደሚያው ደርሶ የደከመ ይመስል ነበር።
ዌስሊ በአገልግሎት ዘመኑ ሁሉ የሚበቃውና የሚተርፈው ገንዘብ ነበረው። ባውንድስ ለገንዘብ ግድ አልነበረውም። አላናቀውም፤ ነገር ግን ከኃይል ዓይነቶች ሁሉ ዝቅተኛው እንደ ሆነ ይቈጥረው ነበር።
ዌስሊ «ዓይኑ እያበራና ከንፈሮቹ በምስጋና እየፈነዱ» ሞተ። «ከሁሉ የሚበልጠው እግዚአብሔር ከእኛ ጋር መሆኑ ነው» ብሎ ባውንድስ ለእነዚህ መስመሮች ጸሐፊ ጻፈ። «እርሱ ሲዘጋጅ እኔም ዝግጁ ነኝ፤ የሰማያዊውን ስፍራ ደስታ ለመቅመስ እናፍቃለሁ።»
ዌስሊ «ዓለም ደብሬ ናት» አለ። ባውንድስ ግን ጽንፈ ዓለሙ ሁሉ የእርሱ ክልል እንደ ሆነ አድርጎ ይጸልይ ነበር።
ዌስሊ ዓለማዊነትን የራቀ ሕያው ምሳሌ፣ የልበ ሰፊነትም መገለጫ ነበር። ባውንድስ ምድራዊነትን የራቀ፣ የትሕትናና ራስን የመካድ ሕያው ምሳሌ ነበር። ዌስሊ በቅዱሳን ልብ ውስጥ ለዘመናት ሁሉ ይኖራል። ባውንድስ ደግሞ ለዘላለም።
ዌስሊ በሲቲ ሮድ ቻፕል ቅጥር ግቢ ውስጥ በ«ውድ ሙታኑ» መካከል፣ ተገቢ የምስጋና ቃል በስድ ንባብ በተቀረጸበት እብነ በረድ ሥር ትንሣኤን እየጠበቀ አንቀላፍቷል። ባውንድስ በጆርጂያዋ ዋሽንግተን የመቃብር ስፍራ፣ ያለ እብነ በረድ መሸፈኛ፣ የሙሽራውን መምጣት እየጠበቀ አንቀላፍቷል።
እነዚህ ሁለት ሰዎች ሌሎች ሰዎች ሊደርሱባቸው ከማይችሉት በላይ የሆኑ ከፍ ያሉና ውድ ዓላማዎችን ይዘው ኖሩ። እነርሱ ስለ ሞቱ እንዲህ ያሉ ሰዎች ትውልድ ከዓለም ፈጽሞ ጠፍቶአልን? እንጸልይ።
ሆሜር ደብሊው ሆጅ
ብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ
ምዕራፍ 1 ተጠናቋል
መግቢያ