በጸሎት የሚገኝ ኃይል
የጸሎት ሰዎች ምሳሌዎች

ምዕራፍ 8 · 3 ደቂቃ ንባብ · 4 ደቂቃ ማዳመጥ

የጸሎት ሰዎች ምሳሌዎች

የጸሎት ተግባር የሰው አእምሮ ሊያደርገው ከሚችለው ሁሉ እጅግ ከፍተኛው ብርታት ነው፤ ይህም ማለት ችሎታዎችን ሁሉ ፈጽሞ በአንድ ላይ አሰባስቦ መጸለይ ነው። አብዛኞቹ ዓለማውያን ሰዎችና ምሁራን ፈጽሞ መጸለይ አይችሉም።—ሳሙኤል ቴይለር ኮልሪጅ

ኤጲስ ቆጶስ ዊልሰን እንዲህ ይላል፦ «በሄንሪ ማርቲን የዕለት ማስታወሻ ውስጥ አስቀድመው ትኩረቴን የሚስቡት የጸሎቱ መንፈስ፣ ለዚህ ተግባር የሰጠው ጊዜና በእርሱም ውስጥ የነበረው ትጋት ናቸው።»

ፔይሰን ጉልበቶቹ ብዙ ጊዜና ለረጅም ሰዓት ያርፉበት የነበረውን የጠንካራ እንጨት ወለል እስኪጎደጉድ ድረስ ሸርሽሮታል። የሕይወት ታሪኩን የጻፈው ሰው እንዲህ ይላል፦ «ሁኔታው ምንም ዓይነት ቢሆን ሳያቋርጥ በጸሎት መጽናቱ በታሪኩ ውስጥ እጅግ ጎልቶ የሚታየው እውነታ ነው፤ ይህም እንደ እርሱ ታላቅ ለመሆን የሚሹትን ሁሉ ግዴታቸውን ያመለክታቸዋል። ለታዋቂውና ሳይቋረጥ ለዘለቀው ስኬቱ ዋናው ምክንያት ብርቱና ጽኑ ጸሎቱ እንደ ሆነ ጥርጥር የለውም።»

ክርስቶስ እጅግ የከበረለት ማርኲስ ደ ሬንቲ፣ ከግል አምልኮው ግማሽ ሰዓት ሲሞላ እንዲጠራው አገልጋዩን አዘዘው። አገልጋዩም በዚያን ጊዜ በአንድ ቀዳዳ በኩል ፊቱን አየ። ፊቱ በቅድስና እጅግ ስለ ተሞላ ሊቀሰቅሰው አልወደደም። ከንፈሮቹ ይንቀሳቀሱ ነበር፤ እርሱ ግን ፍጹም ዝም ብሎ ነበር። አገልጋዩ ሦስት ግማሽ ሰዓታት እስኪያልፉ ድረስ ጠበቀ፤ ከዚያም ጠራው፤ እርሱም ከተንበረከከበት ተነሥቶ ከክርስቶስ ጋር ኅብረት ሲያደርግ ግማሽ ሰዓቱ እጅግ አጭር እንደ ሆነበት ተናገረ።

ብሬነርድ እንዲህ አለ፦ «ብዙ ጊዜ በጸሎት ማሳለፍ በምችልበት በጎጆዬ ውስጥ ብቻዬን መሆን እወዳለሁ።»

ዊልያም ብራምዌል በግል ቅድስናው፣ በስብከቱ አስደናቂ ስኬትና ለጸሎቱ በተሰጡት ድንቅ መልሶች በሜቶዲስቶች ታሪክ ውስጥ ዝነኛ ነው። ለሰዓታት ያለማቋረጥ ይጸልይ ነበር። ኑሮው ሁሉ በጉልበቱ ተንበርክኮ ነበር ማለት ይቻላል። የአገልግሎት ወረዳዎቹን እንደ እሳት ነበልባል ያዳርስ ነበር። ያ እሳት የተቀጣጠለው በጸሎት ባሳለፈው ጊዜ ነበር። ብዙ ጊዜ ገለል ብሎ በአንድ የጸሎት ጊዜ እስከ አራት ሰዓት ያህል ያሳልፍ ነበር።

ኤጲስ ቆጶስ አንድሩስ በየዕለቱ ከአምስት ሰዓታት የሚበልጠውን ጊዜ በጸሎትና በአምልኮ ያሳልፍ ነበር።

ሰር ሄንሪ ሃቭሎክ የየዕለቱን የመጀመሪያዎቹን ሁለት ሰዓታት ሁልጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር ብቻውን ያሳልፍ ነበር። ሰፈሩ የሚነሣው ከጠዋቱ 12 ሰዓት ላይ ከሆነ፣ እርሱ ከሌሊቱ 10 ሰዓት ይነሣ ነበር።

ኧርል ኬርንስ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ሩብ ጉዳይ ላይ የቤተሰብ አምልኮን ከመምራቱ በፊት ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና ለጸሎት አንድ ሰዓት ተኩል ለማግኘት በየዕለቱ ከጠዋቱ 12 ሰዓት ይነሣ ነበር።

ዶክተር ጃድሰን በጸሎት ያገኘው ስኬት ለጸሎት ብዙ ጊዜ በመስጠቱ የመጣ ነው። በዚህ ጉዳይ እንዲህ ይላል፦ «ቢቻልህ በየዕለቱ ሁለት ወይም ሦስት ሰዓታትን በእርጋታ ለአምልኮ ሥርዓቶች ብቻ ሳይሆን በስውር ለመጸለይና ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት ለማድረግ ራሱ እንድትሰጥ ጉዳዮችህን አስተካክል። በቀን ሰባት ጊዜ ከሥራና ከሰዎች ተለይተህ ገለል ብለህ ነፍስህን ወደ እግዚአብሔር ለማንሣት ጣር። ቀኑን ከእኩለ ሌሊት በኋላ ተነሥተህ በሌሊቱ ጸጥታና ጨለማ መካከል ለዚህ ቅዱስ ሥራ ጥቂት ጊዜ በመስጠት ጀምር። ጎሕ ሲቀድም በዚያው ሥራ ላይ ያግኝህ። የጠዋቱ ሦስት ሰዓት፣ ስድስት ሰዓት፣ ዘጠኝ ሰዓት፣ አሥራ ሁለት ሰዓትና የምሽቱ ሦስት ሰዓትም ይህንኑ ይመስክሩ። ለእርሱ ጉዳይ ቁርጠኛ ሁን። ይህንንም ለመጠበቅ የሚቻልህን መሥዋዕት ሁሉ ክፈል። ጊዜህ አጭር እንደ ሆነ፣ ሥራና ሰዎችም አምላክህን እንዲቀሙህ መፍቀድ እንደሌለብህ አስብ።» እኛ ግን «የማይቻል ነው፤ የአክራሪ መመሪያ ነው!» እንላለን። ዶክተር ጃድሰን በአንድ ግዛት ላይ ለክርስቶስ ጥልቅ አሻራ አሳረፈ፤ በበርማም እምብርት የእግዚአብሔርን መንግሥት መሠረት በማይፈርስ ዓለት ጣለ። በዓለም ላይ ለክርስቶስ ብርቱ አሻራ ካሳረፉት ከጥቂቶቹ ሰዎች አንዱ፣ ውጤታማ ሰው ነበር። ከእርሱ የሚበልጥ ስጦታ፣ ተሰጥኦና ትምህርት የነበራቸው ብዙ ሰዎች እንዲህ ያለ አሻራ አላሳረፉም፤ ሃይማኖታዊ ሥራቸው በአሸዋ ላይ እንዳለ የእግር ዱካ ነው፤ እርሱ ግን ሥራውን በአልማዝ ድንጋይ ላይ ቀርጾታል። የሥራው ጥልቀትና ጽናት ምሥጢር ለጸሎት ጊዜ በመስጠቱ ውስጥ ይገኛል። ብረቱን በጸሎት እንደ ፍም ቀይ አድርጎ አቆየው፤ የእግዚአብሔርም ጥበብ በዘላቂ ኃይል ቀረጸው። የጸሎት ሰው ያልሆነ ማንም ሰው ለእግዚአብሔር ታላቅና ዘላቂ ሥራ ሊሠራ አይችልም፤ ለመጸለይም ብዙ ጊዜ የማይሰጥ ማንም ሰው የጸሎት ሰው ሊሆን አይችልም።

ጸሎት ደብዛዛና እንደ ማሽን ያለ የልማድ መፈጸሚያ ብቻ ነውን? ልዝብነት፣ አጭርነትና ላይ ላዩን መሆን ዋና መለያዎቹ እስኪሆኑ ድረስ የሠለጠንበት ተራ ሥርዓት ነውን? «ጸሎት እንደሚገመተው በቀላል የሕልም ዓለም ውስጥ ለደቂቃዎች ወይም ለሰዓታት በስንፍና የሚፈስስ ግማሽ ተገብሮ የሆነ የስሜት ጨዋታ ብቻ ነውን?» ካኖን ሊደን በመቀጠል እንዲህ ይላል፦ «በእውነት የጸለዩ ሰዎች መልስ ይስጡ። አንዳንድ ጊዜ ጸሎትን እንደ አባቶች አለቃ እንደ ያዕቆብ ከማይታይ ኃይል ጋር እንደ መታገል አድርገው ይገልጹታል፤ ይህም ትጋት በሞላበት ሕይወት ውስጥ ብዙ ጊዜ እስከ ሌሊቱ መጨረሻ ሰዓታት፣ እንዲያውም እስከ ንጋት ድረስ ሊዘልቅ ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ከቅዱስ ጳውሎስ ጋር የጋራ ምልጃን እንደ ኅብረት ተጋድሎ ይጠቅሱታል። ሲጸልዩም ዓይኖቻቸውን በጌቴሴማኒ ባለው በታላቁ አማላጅ ላይ፣ በዚያ የመገዛትና የመሥዋዕት ጭንቅ ውስጥ ወደ ምድር በሚወርዱት የደም ነጠብጣቦች ላይ ያደርጋሉ። ውትወታ የተሳካ ጸሎት ዋና ባሕርይ ነው። ውትወታ ማለት ሕልመኛነት ሳይሆን የማያቋርጥ ሥራ ማለት ነው። ‹መንግሥተ ሰማያት ትገፋለች፥ ግፈኞችም ይናጠቋታል› የሚለው ቃል የሚፈጸመው በተለይ በጸሎት በኩል ነው። የቀድሞው ኤጲስ ቆጶስ ሃሚልተን፦ ‹እጅግ የሚያስደስቱንና እጅግ አስፈላጊ ናቸው ብለን በምናስባቸው ጉዳዮች ላይ በምናውለው ትጋት ሁሉ የሚዘጋጁለትና የሚጸኑበት ሥራ አድርጎ በመመልከት የማይጀምር ማንም ሰው በጸሎት ብዙ መልካም ነገር ሊያደርግ አይችልም› ይል ነበር።»

ገጽ 1 / 1 · 3 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል
ቀዳሚ ቀጣይ