ምዕራፍ 7 · 4 ደቂቃ ንባብ · 5 ደቂቃ ማዳመጥ
ለጸሎት ብዙ ጊዜ መሰጠት አለበት
በክርስቲያን ትምህርት ውስጥ የነበሩ ታላላቅ ሊቃውንትና መምህራን ከፍተኛውን የብርሃን ምንጫቸውን ሁልጊዜ በጸሎት ውስጥ አግኝተዋል። ከእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ወሰን ሳንወጣ እንኳ፣ ኤጲስ ቆጶስ አንድሩዝ በየቀኑ አምስት ሰዓት በጉልበቱ ተንበርክኮ ያሳልፍ እንደ ነበረ ተመዝግቧል። በክርስትና ዘመናት የሰውን ሕይወት ያበለጸጉና ያስዋቡ ታላላቅ ተግባራዊ ውሳኔዎች የተደረሰባቸው በጸሎት ውስጥ ነው።—ካኖን ሊደን
ብዙ የግል ጸሎቶች በነገሩ ባሕርይ አጭር መሆናቸው የግድ ቢሆንም፣ የሕዝብ ጸሎቶችም በአብዛኛው አጭርና የተጠቃለሉ ሊሆኑ ቢገባቸውም፣ በድንገት ከልብ ለሚወጣ አጭር ጸሎት ሰፊ ቦታና ዋጋ ቢኖረውም—በግል ከእግዚአብሔር ጋር በምናደርገው ኅብረት ግን ጊዜ ለዋጋው አስፈላጊ መለያ ነው። ከእግዚአብሔር ጋር ብዙ ጊዜ ማሳለፍ የተሳካ ጸሎት ሁሉ ምሥጢር ነው። እንደ ኃያል ኃይል የሚሰማ ጸሎት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከእግዚአብሔር ጋር የሚያሳልፉት ብዙ ጊዜ ፍሬ ነው። አጫጭር ጸሎቶቻችን ሹልነታቸውንና ውጤታማነታቸውን ያገኙት ቀድመዋቸው ከነበሩት ረጃጅም ጸሎቶች ነው። ለረጅም ጊዜ በቀጠለ ብርቱ ትግል በእግዚአብሔር ፊት ያላሸነፈ ሰው አጭሩን የሚያሸንፍ ጸሎት ሊጸልይ አይችልም። የያዕቆብ የእምነት ድል ያ ሌሊቱን ሙሉ የተደረገ ትግል ባይኖር ሊገኝ አይችልም ነበር። ከእግዚአብሔር ጋር መተዋወቅ ብቅ ብሎ በመውጣት አጭር ጉብኝት አይገኝም። እግዚአብሔር ስጦታዎቹን በአጋጣሚ ለሚመጡና በችኮላ ለሚመላለሱ አይሰጥም። ከእግዚአብሔር ጋር ብቻ ብዙ መቆየት እርሱን የማወቅና በእርሱ ዘንድ ተሰሚነት የማግኘት ምሥጢር ነው። እርሱን የሚያውቅ እምነት ለሚያሳየው ጽናት እሺ ይላል። ምርጥ ስጦታዎቹን የሚሰጠው ለእነዚያ ስጦታዎች ያላቸውን ምኞትና አድናቆት በልመናቸው ልባዊነት ብቻ ሳይሆን በዘላቂነቱም ለሚገልጡ ነው። በዚህም እንደ ሌሎች ነገሮች ሁሉ ምሳሌያችን የሆነው ክርስቶስ ብዙ ሌሊቶችን ሙሉ በጸሎት አሳልፏል። ልማዱ ብዙ መጸለይ ነበር። የሚጸልይበት የተለመደ ስፍራ ነበረው። ብዙ ረጃጅም የጸሎት ጊዜያት ታሪኩንና ባሕርዩን ይሠራሉ። ጳውሎስ ሌሊትና ቀን ጸለየ። ዳንኤል በቀን ሦስት ጊዜ ለመጸለይ እጅግ አስፈላጊ ከሆኑ ጉዳዮች ጊዜ መውሰድ ነበረበት። የዳዊት የጠዋት፣ የቀትርና የማታ ጸሎት በብዙ አጋጣሚዎች እጅግ ረጅም እንደ ነበረ አያጠራጥርም። እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅዱሳን በጸሎት ስላሳለፉት ጊዜ የተለየ ዘገባ ባይኖረንም፣ ምልክቶቹ እንደሚያሳዩት በጸሎት ብዙ ጊዜ አሳልፈዋል፤ በአንዳንድ አጋጣሚዎችም ረጃጅም የጸሎት ጊዜያት ልማዳቸው ነበሩ።
የጸሎታቸው ዋጋ በሰዓት የሚለካ እንደ ሆነ ማንም እንዲያስብ አንፈልግም፤ ዓላማችን ግን ከእግዚአብሔር ጋር ብቻ ብዙ መሆን የግድ አስፈላጊ መሆኑን በአእምሮአችን ማሳተም ነው፤ ይህ መለያ በእምነታችን ካልተገኘ ደግሞ እምነታችን ደካማና ላይ ላዩን የሆነ ዓይነት ነው።
ክርስቶስን በባሕርያቸው እጅግ በተሟላ ሁኔታ የገለጡና ዓለምን ለእርሱ እጅግ በብርቱ የነኩ ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር እጅግ ብዙ ጊዜ በማሳለፋቸው ይህ የሕይወታቸው ጎልቶ የሚታይ መለያ የሆነላቸው ሰዎች ናቸው። ቻርልስ ሲምዮን ከሌሊቱ አሥር ሰዓት እስከ ጠዋቱ ሁለት ሰዓት ያለውን ጊዜ ለእግዚአብሔር ሰጠ። ጆን ዌስሊ በየቀኑ ሁለት ሰዓት በጸሎት ያሳልፍ ነበር። የሚጀምረውም ከሌሊቱ አሥር ሰዓት ነበር። እርሱን በሚገባ የሚያውቅ አንድ ሰው ስለ እርሱ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ «ጸሎትን ከማንኛውም ነገር ይበልጥ የራሱ ሥራ አድርጎ ይቈጥረው ነበር፤ ከጸሎት እልፍኙም ሲወጣ ፊቱ ሊያበራ የቀረበ ጸጥታ ተላብሶ አይቼዋለሁ።» ጆን ፍሌቸር የጸሎቱ እስትንፋስ የክፍሉን ግድግዳዎች እስኪያጠቍራቸው ድረስ ጸለየ። አንዳንድ ጊዜ ሌሊቱን ሙሉ ይጸልይ ነበር፤ ሁልጊዜ፣ ደጋግሞና በታላቅ ልባዊነት። ሕይወቱ ሁሉ የጸሎት ሕይወት ነበር። «ልቤን ወደ እግዚአብሔር ሳላነሣ ከመቀመጫዬ አልነሣም» ይል ነበር። ወዳጁን ሲያገኝ ሁልጊዜ የሚለው ሰላምታ፦ «እየጸለይህ ነው ያገኘሁህ?» የሚል ነበር። ማርቲን ሉተር እንዲህ አለ፦ «በየጠዋቱ ሁለት ሰዓት በጸሎት ማሳለፍ ካቃተኝ ዲያብሎስ በቀኑ ሁሉ ድል ያገኛል። ብዙ ሥራ ስላለብኝ በየቀኑ ሦስት ሰዓት በጸሎት ሳላሳልፍ መዝለቅ አልችልም።» አንድ መሪ ቃልም ነበረው፦ «በሚገባ የጸለየ በሚገባ አጥንቷል።»
ሊቀ ጳጳስ ሌይተን ከእግዚአብሔር ጋር ብቻውን እጅግ ብዙ ይቆይ ስለ ነበረ ዘወትር በማሰላሰል ውስጥ ያለ ይመስል ነበር። የሕይወት ታሪኩን የጻፈው ሰው፦ «ጸሎትና ምስጋና ሥራውም ደስታውም ነበሩ» ይላል። ኤጲስ ቆጶስ ኬን ከእግዚአብሔር ጋር እጅግ ብዙ ይሆን ስለ ነበረ ነፍሱ በእግዚአብሔር ፍቅር የተማረከች ነበረች ይባል ነበር። በየማለዳው ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ከመሆኑ በፊት ከእግዚአብሔር ጋር ነበር። ኤጲስ ቆጶስ አዝበሪ እንዲህ አለ፦ «በተቻለኝ መጠን ብዙ ጊዜ ከሌሊቱ አሥር ሰዓት ተነሥቼ ሁለት ሰዓት በጸሎትና በማሰላሰል ለማሳለፍ አስባለሁ።» የእግዚአብሔርን መምሰሉ መዓዛ ዛሬም ድረስ የሚያውድ ሳሙኤል ራዘርፎርድ እግዚአብሔርን በጸሎት ለመገናኘት ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ይነሣ ነበር። ጆሴፍ አላይን የጸሎት ሥራውን ለማከናወን ከሌሊቱ አሥር ሰዓት ተነሥቶ እስከ ጠዋቱ ሁለት ሰዓት ይጸልይ ነበር። ሌሎች የእጅ ሙያተኞች እርሱ ከመነሣቱ በፊት ሥራቸውን ሲሠሩ ቢሰማ እንዲህ ብሎ ይጮኽ ነበር፦ «ኦ፣ ይህ እንዴት ያሳፍረኛል! ጌታዬ ከጌቶቻቸው የበለጠ አይገባውምን?» ይህን ሙያ በሚገባ የተማረ ሰው ከማይጐድለው ከሰማይ ባንክ እንደ ፈቀደ፣ ሲያቀርብ ወዲያውኑና በተቀባይነት ይወስዳል።
በስኮትላንድ ሰባኪዎች መካከል እጅግ ቅዱስና እጅግ ተሰጥኦ ካላቸው አንዱ እንዲህ ይላል፦ «የተሻሉትን ሰዓቶች ከእግዚአብሔር ጋር በኅብረት ማሳለፍ ይገባኛል። ይህ እጅግ የከበረውና እጅግ ፍሬያማው ሥራዬ ነው፤ ወደ ጥግም ሊገፋ አይገባውም። ከጠዋቱ አሥራ ሁለት ሰዓት እስከ ሁለት ሰዓት ያሉት የማለዳ ሰዓቶች ከሁሉ ይልቅ የማይቋረጡ ናቸው፤ ለዚህም ሊውሉ ይገባቸዋል። ከሻይ በኋላ ያለው ሰዓት የእኔ ምርጥ ሰዓት ነው፤ እርሱም በክብር ለእግዚአብሔር ሊቀደስ ይገባዋል። ከመተኛቴ በፊት የመጸለይን መልካሙን የቆየ ልማድ መተው አይገባኝም፤ ነገር ግን እንቅልፍን መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ሌሊት ስነቃ ተነሥቼ መጸለይ ይገባኛል። ከቁርስ በኋላ ጥቂት ጊዜ ለምልጃ ሊሰጥ ይችላል።» ይህ የሮበርት መሪ ማክሼን የጸሎት ዕቅድ ነበር። የሚታወሰው የሜቶዲስት ማኅበር በጸሎቱ ያሳፍረናል፦ «ከሌሊቱ አሥር እስከ አሥራ አንድ ሰዓት የግል ጸሎት፤ ከቀኑ አሥራ አንድ እስከ ምሽቱ አሥራ ሁለት ሰዓት የግል ጸሎት።»
ቅዱሱና ድንቁ የስኮትላንድ ሰባኪ ጆን ዌልሽ ስምንት ወይም አሥር ሰዓት በጸሎት ካላሳለፈ ቀኑን በከንቱ እንዳሳለፈ ይቈጥር ነበር። ሌሊት ለመጸለይ ሲነሣ የሚጠቀለልበት ወፍራም የሱፍ ልብስ ያስቀምጥ ነበር። ሚስቱ መሬት ላይ ተኝቶ ሲያለቅስ ስታገኘው ታማርር ነበር። እርሱም እንዲህ ይመልስላት ነበር፦ «አንቺ ሴት፣ ስለ ሦስት ሺህ ሰዎች ነፍስ መልስ መስጠት አለብኝ፤ ከብዙዎቹም ጋር ነገሩ እንዴት እንደ ሆነ አላውቅም!»
ምዕራፍ 7 ተጠናቋል
ለጸሎት ብዙ ጊዜ መሰጠት አለበት