ምዕራፍ 4 · 4 ደቂቃ ንባብ · 5 ደቂቃ ማዳመጥ
ሊወገዱ የሚገባቸው ዝንባሌዎች
ብሬነርድ በአሜሪካ ጫካዎች ውስጥ፣ ካልዳኑ ምንም ነገር ደስ ሊያሰኘው ስለማይችል ስለሚጠፉት አሕዛብ ነፍሱን ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ሲያፈስስ ደጋግመን እንመልከተው። ጸሎት—በስውር የሚደረግ፣ የሚግለበለብና የሚያምን ጸሎት—የግል እግዚአብሔርን የመምሰል ሕይወት ሁሉ ሥር ነው። ሚስዮናዊው የሚኖርበትን አገር ቋንቋ በሚገባ ማወቅ፣ ገርና ልብን የሚማርክ ጠባይ፣ በእልፍኝ ውስጥ በሚደረግ የግል አምልኮ ለእግዚአብሔር የተሰጠ ልብ—እነዚህ፣ አዎን እነዚህ ናቸው ከዕውቀት ሁሉ ወይም ከሌሎች ስጦታዎች ሁሉ ይልቅ በሰው ልጆች ቤዛነት ታላቅ ሥራ ውስጥ የእግዚአብሔር መሣሪያዎች እንድንሆን የሚያበቁን።—የኬሪ ወንድማማች ማኅበር፣ ሴራምፖር
በአገልግሎት ውስጥ ሁለት ጽንፍ የወጡ ዝንባሌዎች አሉ። አንደኛው ከሕዝቡ ጋር ካለው ግንኙነት ራስን ዘግቶ መቀመጥ ነው። መነኩሴውና ባሕታዊው የዚህ ምሳሌዎች ነበሩ፤ ከእግዚአብሔር ጋር ይበልጥ ለመሆን ብለው ከሰዎች ራሳቸውን አገለሉ። እንደሚጠበቀውም አልተሳካላቸውም። ከእግዚአብሔር ጋር መሆናችን የሚጠቅመው በዋጋ የማይተመነውን በረከቱን ለሰዎች ስናውለው ብቻ ነው። ይህ ዘመን በሰባኪውም ሆነ በሕዝቡ ዘንድ እግዚአብሔርን አጥብቆ የሚሻ አይደለም። ናፍቆታችን ወደዚያ አያዘነብልም። ራሳችንን በጥናት ክፍላችን ውስጥ እንዘጋለን፤ ተማሪዎች፣ የመጻሕፍት ትሎች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ትሎች፣ ስብከት አዘጋጆች እንሆናለን፤ በሥነ ጽሑፍ፣ በአሳብና በስብከት እንታወቃለን፤ ሕዝቡና እግዚአብሔር ግን የት አሉ? ከልብ ርቀው ከአእምሮም ርቀዋል። ታላላቅ አሳቢዎችና ታላላቅ ምሁራን የሆኑ ሰባኪዎች ከጸሎተኞች ሁሉ የሚበልጡ ጸሎተኞች መሆን አለባቸው፤ አለዚያ ከኋላ ተመላሾች ሁሉ የከፉ ኋላ ተመላሾች፣ ልብ የሌላቸው ባለሙያዎች፣ በሰው ምክንያት ብቻ የሚመሩ፣ በእግዚአብሔርም ግምት ከሰባኪዎች ሁሉ ያነሱ ይሆናሉ።
ሌላው ዝንባሌ ደግሞ አገልግሎትን ፈጽሞ ሕዝባዊ ማድረግ ነው። ሰባኪው ከእንግዲህ የእግዚአብሔር ሰው ሳይሆን የጉዳይ ሰው፣ የሕዝብ ሰው ይሆናል። ተልእኮው ወደ ሕዝቡ ነው በማለት አይጸልይም። ሕዝቡን ማንቀሳቀስ፣ ፍላጎትን መቀስቀስ፣ ለሃይማኖት የሚያደላ ስሜትና ግርግር መፍጠር፣ ለቤተ ክርስቲያን ሥራም ፍላጎት ማነሣሣት ከቻለ—ይረካል። ከእግዚአብሔር ጋር ያለው የግል ግንኙነቱ በሥራው ውስጥ ምንም ድርሻ የለውም። በዕቅዶቹ ውስጥ ጸሎት ጥቂት ቦታ አለው፤ ወይም ጨርሶ ቦታ የለውም። የእንዲህ ዓይነቱ አገልግሎት ጥፋትና ውድቀት በምድራዊ ሒሳብ ሊሰላ አይችልም። ሰባኪው ለራሱና ለሕዝቡ በእግዚአብሔር ፊት በጸሎት ምን እንደ ሆነ፣ ለሰዎች እውነተኛ መልካም ነገር የማድረግ ኃይሉም፣ እውነተኛ ፍሬያማነቱም፣ ለእግዚአብሔርና ለሰው፣ ለዚህ ዘመንና ለዘላለም ያለው እውነተኛ ታማኝነቱም ልክ እንዲሁ ነው።
ሰባኪው ብዙ ሳይጸልይ መንፈሱን ከከፍተኛ ጥሪው መለኮታዊ ባሕርይ ጋር ተስማምቶ እንዲኖር ማድረግ አይቻለውም። ሰባኪው በግዴታ ብርታትና ለአገልግሎት ሥራና ልማድ በሚያሳየው አድካሚ ታማኝነት ብቻ ራሱን ብቁና ዝግጁ አድርጎ መጠበቅ ይችላል ብሎ ማሰብ ከባድ ስሕተት ነው። ስብከት ማዘጋጀት እንኳ—እንደ ጥበብ፣ እንደ ግዴታ፣ እንደ ሥራ ወይም እንደ ደስታ የማያቋርጥና አድካሚ ቢሆንም—ጸሎት ቸል ሲባል ልብን ይውጣል፣ ያደነድናል፣ ከእግዚአብሔርም ያርቀዋል። ሳይንቲስቱ እግዚአብሔርን በተፈጥሮ ውስጥ ያጣዋል። ሰባኪውም እግዚአብሔርን በስብከቱ ውስጥ ሊያጣው ይችላል።
ጸሎት የሰባኪውን ልብ ያለመልማል፤ ከእግዚአብሔር ጋር እንዲስማማና ለሕዝቡም እንዲራራ አድርጎ ይጠብቀዋል፤ አገልግሎቱን ከሙያ ቀዝቃዛ አየር ያወጣዋል፤ የዕለት ተዕለት ልማዱን ፍሬያማ ያደርጋል፤ እያንዳንዱንም መንኰራኵር በመለኮታዊ ቅባት ቅልጥፍናና ኃይል ያንቀሳቅሳል።
ቻርልስ ስፐርጀን እንዲህ ይላል፦ «በእርግጥም ሰባኪ ከሌሎች ሁሉ በላይ የጸሎት ሰው በመሆኑ ተለይቶ ይታወቃል። እንደ ማንኛውም ክርስቲያን ይጸልያል፤ አለዚያ ግብዝ በሆነ ነበር። ከተራ ክርስቲያኖችም አብልጦ ይጸልያል፤ አለዚያ ለተቀበለው ሹመት ብቁ ባልሆነ ነበር። እናንተ አገልጋዮች ሆናችሁ እጅግ ጸሎተኞች ካልሆናችሁ ሊታዘንላችሁ ይገባል። በቅዱስ አምልኮ ብትላሉ፣ ሊታዘንላቸው የሚገባ እናንተ ብቻ ሳትሆኑ ሕዝባችሁም ይሆናል፤ የምታፍሩበትና የምትዋረዱበትም ቀን ይመጣል። ቤተ መጻሕፍቶቻችንና የጥናት ክፍሎቻችን ሁሉ ከጸሎት እልፍኞቻችን ጋር ሲነጻጸሩ ባዶ ከንቱ ናቸው። በታበርናክል ያደረግናቸው የጾምና የጸሎት ጊዜያት በእውነትም ታላላቅ ቀናት ነበሩ፤ የሰማይ ደጅ ከዚያ ይበልጥ ተከፍቶ አያውቅም፤ ልቦቻችንም ወደ ማዕከላዊው ክብር ከዚያ ይበልጥ ቀርበው አያውቁም።»
ጸሎተኛ አገልግሎትን የሚያስገኘው ጸሎት፣ ደስ የሚል ጣዕም እንዲኖረው ቅመም እንደምንጨምር ጥቂት ተጨምሮ የሚገባ ጸሎት አይደለም፤ ጸሎቱ በአካሉ ውስጥ ሊኖር፣ ደሙንና አጥንቱንም ሊሠራ ይገባዋል። ጸሎት ወደ ጥግ የሚገፋ ትንሽ ግዴታ አይደለም፤ ከንግድና ከሌሎች የሕይወት ጉዳዮች ተነጥቀው ከቀሩ የጊዜ ቍርጥራጮች የሚሠራ ቍርጥራጭ ተግባርም አይደለም፤ ይልቁንም ከጊዜያችን የተሻለው፣ የጊዜያችንና የኃይላችን አንኳር ሊሰጠው ይገባል ማለት ነው። የጸሎት እልፍኝ በጥናት ክፍል ውስጥ ተውጦ ወይም በአገልግሎት ተግባራት ግርግር ተዋጥቶ መቅረት ማለት አይደለም፤ ይልቁንም መጀመሪያ እልፍኙ፣ ጥናቱና እንቅስቃሴዎቹ ሁለተኛ ማለት ነው፤ ጥናቱም እንቅስቃሴዎቹም በእልፍኙ የሚታደሱና ውጤታማ የሚሆኑ ናቸው። በአገልግሎት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር ጸሎት ለሕይወትም መልክ ሊሰጥ ይገባዋል። ለባሕርይ ቀለምና አቅጣጫ የሚሰጥ ጸሎት ደስ የሚያሰኝ የችኮላ መዝናኛ አይደለም። ክርስቶስ «ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር» እንዳቀረበው ጸሎት በብርቱ ወደ ልብና ወደ ሕይወት ሊገባ ይገባዋል፤ እንደ ጳውሎስ ጸሎት ነፍስን ወደ ብርቱ ምኞት ጣር ሊስባት ይገባዋል፤ ያዕቆብ «የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች» ብሎ እንደ ገለጸው ጸሎት በውስጥ የተቀጣጠለ እሳትና ኃይል ሊሆን ይገባዋል፤ በወርቅ ጥና ውስጥ ገብቶ በእግዚአብሔር ፊት እንደ ዕጣን ሲጤስ ብርቱ መንፈሳዊ ምጥንና ለውጥን የሚያስከትል ዓይነት ሊሆን ይገባዋል።
ጸሎት ገና በእናታችን ቀሚስ ጫፍ ታስረን ሳለን የለመድነው ትንሽ ልማድ አይደለም፤ ለአንድ ሰዓት ማዕድ የሚደረግ የሩብ ደቂቃ ጨዋ የምስጋና ጸሎትም አይደለም፤ ይልቁንም እጅግ ቁም ነገር በሞላባቸው ዓመታችን ውስጥ የምንሠራው እጅግ ቁም ነገር ያለው ሥራ ነው። ከረጅሙ ማዕዳችንና ከበለጸገው ግብዣችን ይበልጥ ጊዜንና ፍላጎትን ይጠይቃል። ስብከታችንን ታላቅ የሚያደርገው ጸሎት ታላቅ ቦታ ሊሰጠው ይገባል። የጸሎታችን ዓይነት የስብከታችንን ዓይነት ይወስናል። ቀላል ጸሎት ቀላል ስብከትን ያስገኛል። ጸሎት ስብከትን ያበረታል፣ ቅባትን ይሰጠዋል፣ በልብም ውስጥ እንዲጣበቅ ያደርገዋል። ለመልካም ነገር ክብደት ባለው አገልግሎት ሁሉ ውስጥ ጸሎት ሁልጊዜ ቁም ነገር ያለው ሥራ ሆኖ ኖሯል።
ሰባኪ ከሁሉ በፊት የጸሎት ሰው መሆን አለበት። ልቡ በጸሎት ትምህርት ቤት ተምሮ መመረቅ አለበት። ልብ መስበክን ሊማር የሚችለው በጸሎት ትምህርት ቤት ብቻ ነው። ያለመጸለይን ጉድለት የትኛውም ዕውቀት ሊተካ አይችልም። የትኛውም ልባዊነት፣ የትኛውም ትጋት፣ የትኛውም ጥናት፣ የትኛውም ስጦታ ጉድለቱን አይሞላም።
ስለ እግዚአብሔር ብሎ ለሰዎች መናገር ታላቅ ነገር ነው፤ ስለ ሰዎች ብሎ ለእግዚአብሔር መናገር ግን ከዚያ የሚበልጥ ነው። ስለ ሰዎች ብሎ ለእግዚአብሔር በሚገባ መናገርን ያልተማረ ሰው ስለ እግዚአብሔር ብሎ ለሰዎች በሚገባና በእውነተኛ ስኬት ፈጽሞ አይናገርም። ከዚህም በላይ፣ በመድረክ ላይም ሆነ ከመድረክ ውጭ ያለ ጸሎት የሚነገሩ ቃላት የሚገድሉ ቃላት ናቸው።
ምዕራፍ 4 ተጠናቋል
ሊወገዱ የሚገባቸው ዝንባሌዎች