ምዕራፍ 20 · 3 ደቂቃ ንባብ · 4 ደቂቃ ማዳመጥ
የሚጸልይ መድረክ የሚጸልዩ ምእመናንን ይወልዳል
ጸሎቴ ከዲያብሎስ ራሱ እንደሚበልጥ እፈርዳለሁ፤ እንዲህ ባይሆን ኖሮ ሉተር ከዚህ ብዙ ቀደም ብሎ በሌላ ሁኔታ ላይ በተገኘ ነበር። ይሁን እንጂ ሰዎች እግዚአብሔር ለእኔ የሚያደርጋቸውን ታላላቅ ድንቆች ወይም ተአምራት አያዩም፤ አይቀበሉምም። ጸሎትን አንድ ቀን ብቻ እንኳ ቸል ብል፣ ከእምነት እሳት እጅግ ብዙውን አጣለሁ።—ማርቲን ሉተር
ሐዋርያት ከበዓለ ሃምሳ በፊት የጸሎትን ታላቅ አስፈላጊነት በጭላንጭል ብቻ ማየት ቻሉ። ነገር ግን በበዓለ ሃምሳ መንፈስ መጥቶ በሞላቸው ጊዜ ጸሎትን በክርስቶስ ወንጌል ውስጥ ወደ ወሳኝና ሁሉን ወደሚያዝ ስፍራው ከፍ አደረገው። አሁን ለእያንዳንዱ ቅዱስ የሚቀርበው የጸሎት ጥሪ የመንፈስ ከሁሉ የሚጮኽና ከሁሉ አጣዳፊ ጥሪ ነው። የቅዱሳን መንፈሳዊነት የሚሠራው፣ የሚጠራውና ፍጹም የሚሆነው በጸሎት ነው። ቅዱሳን በማለዳም በማታም ረጅም ጊዜ በጸሎታቸው ላይ ሳይገኙ ሲቀሩ ወንጌል በዝግታና በፍርሃት እርምጃ ይጓዛል።
ዘመናውያኑን ቅዱሳን እንዴት መጸለይ እንዳለባቸው ሊያስተምሩና በዚያ ላይ ሊያሰማሩ የሚችሉ ክርስቶስን የሚመስሉ መሪዎች ወዴት አሉ? የማይጸልዩ ቅዱሳንን ትውልድ እያሳደግን እንዳለን እናውቃለንን? የእግዚአብሔርን ሕዝብ ወደ ጸሎት ሊያስገቡ የሚችሉ ሐዋርያዊ መሪዎች ወዴት አሉ? ወደ ፊት ይምጡና ሥራውን ይሥሩ፤ ሊሠራ ከሚችለው ሥራ ሁሉ ታላቁ ይሆናልና። የትምህርት ተቋማት መብዛትና የገንዘብ ኃይል እጅግ መጨመር አሁን ከምንጸልየው በበዛና በተሻለ ጸሎት ካልተቀደሱ ለሃይማኖት ከሁሉ የከፋ እርግማን ይሆናሉ። የበዛ ጸሎት በራሱ አይመጣም። የሃያኛው ወይም የሠላሳኛው መቶ ክፍለ ዘመን የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዘመቻ ካልተጠነቀቅን ጸሎታችንን ከማገዝ ይልቅ ያደናቅፈዋል። ከሚጸልይ አመራር የሚመጣ የተለየ ጥረት እንጂ ሌላ ምንም አይጠቅምም። ዋነኞቹ የጸሎትን ወሳኝ አስፈላጊነትና ተግባር በቤተ ክርስቲያን ልብና ሕይወት ውስጥ ሥር ለማስያዝ በሚደረገው ሐዋርያዊ ጥረት ቀድመው መምራት አለባቸው። ከሚጸልዩ መሪዎች በቀር የሚጸልዩ ተከታዮች ሊኖሩት የሚችል የለም። የሚጸልዩ ሐዋርያት የሚጸልዩ ቅዱሳንን ይወልዳሉ። የሚጸልይ መድረክ የሚጸልዩ ምእመናንን ይወልዳል። ቅዱሳንን ወደዚህ የጸሎት ሥራ ሊያሰማራ የሚችል ሰው እጅግ ያስፈልገናል። እኛ የሚጸልዩ ቅዱሳን ትውልድ አይደለንም። የማይጸልዩ ቅዱሳን የቅዱሳን ግለትም ውበትም ኃይልም የሌላቸው የለማኝ ቅዱሳን ጭፍራ ናቸው። ይህን የፈረሰ ቅጥር ማን ይጠግናል? ቤተ ክርስቲያንን ወደ ጸሎት ሊያሰማራ የሚችል ከተሐድሶ አራማጆችና ከሐዋርያት ሁሉ ታላቅ ይሆናል።
በዚህም ሆነ በዘመናት ሁሉ የቤተ ክርስቲያን ታላቅ ፍላጎት እንዲህ ያለ ገዥ እምነት፣ እንዲህ ያለ እንከን የሌለበት ቅድስና፣ እንዲህ ያለ ጎልቶ የሚታይ መንፈሳዊ ብርታትና የሚያቃጥል ቅንዓት ያላቸው ሰዎች ናቸው ብለን ከሁሉ በላቀ ጥንቃቄ እንፈርዳለን፤ ጸሎታቸው፣ እምነታቸው፣ ሕይወታቸውና አገልግሎታቸውም በግለሰብና በቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ አዲስ ዘመናትን የሚከፍቱ መንፈሳዊ አብዮቶችን የሚያስነሣ ሥር ነቀልና ደፋር መልክ ያለው ይሆናል።
አዳዲስ ዘዴዎችን በመፍጠር ስሜት ቀስቃሽ ሁካታ የሚያስነሡትን ወይም ደስ በሚያሰኝ መዝናኛ የሚማርኩትን ማለታችን አይደለም፤ ይልቁንም በእግዚአብሔር ቃል ስብከትና በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ነገሮችን የሚያናውጡና አብዮቶችን የሚያመጡ ሰዎችን ነው—የነገሮችን አጠቃላይ አቅጣጫ የሚለውጡ አብዮቶችን።
በዚህ ጉዳይ ተፈጥሮአዊ ችሎታና የትምህርት ዕድል ወሳኝ ሚና የላቸውም፤ ይልቁንም የእምነት አቅም፣ የመጸለይ ችሎታ፣ ራስን ፈጽሞ ለእግዚአብሔር የመለየት ኃይል፣ ራስን የማሳነስ ችሎታ፣ በእግዚአብሔር ክብር ውስጥ ራስን ፈጽሞ ማጣት፣ የእግዚአብሔርንም ሙላት ሁሉ ዘወትር የሚናፍቅና የሚፈልግ የማይጠግብ ጥማት ናቸው—ቤተ ክርስቲያንን ለእግዚአብሔር በእሳት የሚያቀጣጥሉ ሰዎች፤ በጩኸትና በታይታ መንገድ ሳይሆን ሁሉን ለእግዚአብሔር በሚያቀልጥና በሚያንቀሳቅስ ጥልቅና ጸጥ ያለ ሙቀት።
እግዚአብሔር ተስማሚ ሰው ካገኘ ድንቅ ሊሠራ ይችላል። ሰዎችም እግዚአብሔር እንዲመራቸው ካደረጉ ድንቅ ሊሠሩ ይችላሉ። ዓለምን ያወከው ያ መንፈስ ሙሉ ስጦታ በእነዚህ በኋለኛው ዘመናት እጅግ ይጠቅማል። ለእግዚአብሔር ነገሮችን በኃይል የሚያናውጡ፣ መንፈሳዊ አብዮቶቻቸውም የነገሮችን ገጽታ ሁሉ የሚለውጡ ሰዎች የቤተ ክርስቲያን ሁሉ አቀፍ ፍላጎት ናቸው።
ቤተ ክርስቲያን ከእንዲህ ያሉ ሰዎች ፈጽሞ ተለይታ አታውቅም፤ ታሪኳን ያስውባሉ፤ የቤተ ክርስቲያን መለኮትነት ቋሚ ተአምራት ናቸው፤ ምሳሌነታቸውና ታሪካቸውም የማይጠፋ መነሣሣትና በረከት ነው። ቁጥራቸውና ኃይላቸው እንዲጨምር ጸሎታችን ሊሆን ይገባል።
በመንፈሳዊ ነገሮች የተደረገው እንደ ገና ሊደረግ፣ እንዲያውም በተሻለ ሊደረግ ይችላል። የክርስቶስ አመለካከት ይህ ነበር። እንዲህ አለ፦ «እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል፤ ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል፥ እኔ ወደ አብ እሄዳለሁና።» ያለፈው ዘመን ለእግዚአብሔር ታላላቅ ነገሮችን የማድረግን ዕድሎችም ሆነ ጥያቄዎች አላሟጠጠም። ለኃይልና ለጸጋ ተአምራቷ በቀደመው ታሪኳ ላይ የምትደገፍ ቤተ ክርስቲያን የወደቀች ቤተ ክርስቲያን ናት።
እግዚአብሔር የተመረጡ ሰዎችን ይፈልጋል—ራስና ዓለም በከባድ ስቅላት ከውስጣቸው የወጡ፣ ራስንና ዓለምን ፈጽሞ ባጠፋ ኪሣራ መመለስን ተስፋም ምኞትም የሌላቸው ሰዎችን፤ በዚህ ኪሣራና ስቅላት ፍጹም ልብን ወደ እግዚአብሔር ያዞሩ ሰዎችን።
የእግዚአብሔር ለጸሎት የሰጠው ተስፋ ከምንጠብቀው በላይ እንዲፈጸም በግለት እንጸልይ።
ምዕራፍ 20 ተጠናቋል
የሚጸልይ መድረክ የሚጸልዩ ምእመናንን ይወልዳል