የምልጃ አገልግሎት
የልመና መንፈስ

ምዕራፍ 12 · 9 ደቂቃ ንባብ

የልመና መንፈስ

«በዳዊት ቤት ላይ የጸጋንና የልመናን መንፈስ አፈስሳለሁ።»—ዘካርያስ 12:10።

«እንዲሁም ደግሞ መንፈስ ድካማችንን ያግዛል፤ እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና፥ ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል፤ ልብንም የሚመረምረው የመንፈስ አሳብ ምን እንደ ሆነ ያውቃል፥ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ቅዱሳን ይማልዳልና።»—ሮሜ 8:26, 27።

«በጸሎትና በልመናም ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ፤ በዚህም አሳብ ስለ ቅዱሳን ሁሉ እየለመናችሁ በመጽናት ሁሉ ትጉ።»—ኤፌሶን 6:18።

«በመንፈስ ቅዱስም እየጸለያችሁ።»—ይሁዳ 20።

መንፈስ ቅዱስ ሕይወቱ ይሆን ዘንድ ለእያንዳንዱ የእግዚአብሔር ልጅ ተሰጥቶአል። በእርሱ ውስጥ የሚኖረው በባሕርዩ በአንድ ክፍል እንዳለ የተለየ አካል ሆኖ ሳይሆን ራሱ ሕይወቱ ሆኖ ነው። ሕይወቱ የሚጠበቅበትና የሚበረታበት መለኮታዊ ኃይል ወይም ጉልበት እርሱ ነው። አማኝ ሊሆነው ወይም ሊያደርገው የተጠራውን ሁሉ መንፈስ ቅዱስ በእርሱ ውስጥ ሊሠራው ይችላል፥ ይሠራውማል። ቅዱሱን እንግዳ ባያውቀው ወይም ባይገዛለት ብፁዑ መንፈስ ሊሠራ አይችልም፤ ሕይወቱም ውድቀትና ኃጢአት የሞላበት በሽተኛ ሕይወት ይሆናል። ራሱን ሲሰጥ፥ ሲጠብቅና የመንፈስን አመራር ሲታዘዝ ግን እግዚአብሔር በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን ሁሉ በእርሱ ይሠራል።

ይህ መንፈስ ቅዱስ በመጀመሪያ ደረጃ የጸሎት መንፈስ ነው። «የጸጋንና የልመናን መንፈስ» ሆኖ ተስፋ ተሰጥቶበታል፤ ይህም ለልመና የሚሆን ጸጋ ነው። «አባ አባት ብለን የምንጮኽበትን የልጅነት መንፈስ» ሆኖ ወደ ልባችን ተላከ። በእውነተኛ እምነትና ትርጉሙን እያደገ በሚሄድ መረዳት፦ በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ ለማለት ያስችለናል። «እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ቅዱሳን ይማልዳልና።» በመንፈስ ስንጸልይም አምልኮአችን እግዚአብሔር እንደሚሻው፥ «በመንፈስና በእውነት» ይሆናል። ጸሎት በእኛ ውስጥ ያለው የመንፈስ እስትንፋስ ብቻ ነው፤ በጸሎት ያለ ኃይል የሚመጣው የምንጠብቀውና የምንታመንበት መንፈስ በእኛ ውስጥ ካለው ኃይል ነው። በጸሎት መውደቅ የሚመጣው የመንፈስ ሥራ በእኛ ውስጥ ከመድከሙ ነው። ጸሎታችን የመንፈስ ሥራ በእኛ ውስጥ ያለውን መጠን የሚያሳይ መለኪያ ነው። በትክክል ለመጸለይ የመንፈስ ሕይወት በእኛ ውስጥ ትክክል መሆን አለበት። በሥራዋ እጅግ ኃይል የምታደርገውን የጻድቅ ሰው ጸሎት ለመጸለይ ሁሉ ነገር የተመካው በመንፈስ በመሞላት ላይ ነው።

በጸሎት መንፈስ መጸለይን የመማርን በረከት ሊደሰትበት የሚወድ አማኝ ሊያውቃቸው የሚገቡ ሦስት እጅግ ቀላል ትምህርቶች አሉ። የመጀመሪያው፦ መንፈስ በአንተ እንደሚኖር እመን (ኤፌሶን 1:13)። በማንነቱ እጅግ ውስጣዊ በሆነው ጥልቅ ስፍራ፥ ተሰውሮና ሳይሰማው፥ እያንዳንዱ የእግዚአብሔር ልጅ ቅዱሱና ኃያሉ የእግዚአብሔር መንፈስ በእርሱ ውስጥ ይኖራል። ይህን የሚያውቀው በእምነት ነው፤ ይህም እምነት የእግዚአብሔርን ቃል ተቀብሎ ገና ምንም ምልክት የማያይበትን ነገር እውን አድርጎ የሚይዝ ነው። «የመንፈስን ተስፋ በእምነት እንድንቀበል።» በትክክልና በጽናት ለመጸለይ ያለንን ኃይል በሚሰማን ነገር ወይም ልንፈጽም እንችላለን ብለን በምናስበው እስከ ለካን ድረስ፥ ምን ያህል መጸለይ እንደሚገባን ስንሰማ ተስፋ እንቈርጣለን። ነገር ግን በሚሰማን ድካም ሁሉ መካከል መንፈስ ቅዱስ የልመና መንፈስ ሆኖ እግዚአብሔር በሚወደው ዓይነትና መጠን እንድንጸልይ ሊያስችለን ብሎ በውስጣችን እንደሚኖር በጸጥታ ስናምን ልባችን በተስፋ ይሞላል። ደስተኛና ፍሬያማ ለሆነ የክርስቲያን ሕይወት ሥር በሆነው እርግጠኝነት እንበረታለን፤ ይኸውም እርሱ እንድንሆን የሚፈልገውን እንድንሆን እግዚአብሔር የተትረፈረፈ ዝግጅት አድርጎአል የሚለው ነው። መንፈስ ቅዱስ ራሱ በእኛ ውስጥ እንደሚጸልይ፥ አሁንም እየጸለየ እንዳለ ስለምናይ፥ በበቂ ሁኔታ መቼም እንጸልያለን ወይ ብለን የሚሰማንን ሸክምና ፍርሃት ተስፋ መቍረጥም ማጣት እንጀምራለን።

ሁለተኛው ትምህርት፦ ከሁሉ በላይ መንፈስ ቅዱስን ከማሳዘን ተጠንቀቅ (ኤፌሶን 4:30)። ብታሳዝነው፥ ጸሎትህን በአብ ዘንድ ደስ የሚያሰኝ የሚያደርገውን ከክርስቶስ ጋር ያለውን የአንድነት ጸጥ ያለ፥ የሚታመንና ብፁዕ ስሜት እንዴት በአንተ ሊሠራ ይችላል? በኃጢአት፥ በአለማመን፥ በራስ ወዳድነት፥ በሕሊናህ ውስጥ ለሚናገረው ድምፁ ታማኝ ባለመሆን እንዳታሳዝነው ተጠንቀቅ። እርሱን ማሳዘን የግድ ነው ብለህ አታስብ፤ ይህ አሳብ የብርታትህን ጅማት ይቈርጣል። «ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ» የሚለውን ትእዛዝ መታዘዝ የማይቻል አድርገህ አትቍጠረው። እርሱ ራሱ እንድትታዘዝ የሚያደርግህ የእግዚአብሔር ኃይል ነው። ያለ ፈቃድህ በውስጥህ የሚነሣውን ኃጢአት፥ በሥጋ የሚነሣውን የስንፍና ወይም የትዕቢት ወይም የራስ ፈቃድ ወይም የቍጣ ዝንባሌ ፈቃድህ በመንፈስ ኃይል ወዲያውኑ ሊቃወመውና ወደ ክርስቶስና ወደ ደሙ ሊጥለው ይችላል፤ ከእግዚአብሔር ጋር ያለህ ኅብረትም ወዲያውኑ ይመለሳል። መንፈስ ቅዱስን በየዕለቱ መሪህ፥ ሕይወትህና ብርታትህ አድርገህ ተቀበለው፤ በልብህ ሊደረግ የሚገባውን ሁሉ እንዲያደርግ በእርሱ ልትታመን ትችላለህ። የማይታየውና የማይሰማው፥ ነገር ግን በእምነት የሚታወቀው እርሱ፥ የማይታየውን ክርስቶስን በእርግጥ ሕይወትህና ብርታትህ አድርጎ በውስጥህ ስለሚገልጠው፥ የሚያስፈልግህን ፍቅርና እምነት የመታዘዝንም ኃይል በዚያ ሳይታይና ሳይሰማ ይሰጣል። መገኘቱ በውስጥህ ስላልተሰማህ ባለመታመን መንፈስ ቅዱስን አታሳዝነው።

በተለይ በጸሎት ጉዳይ አታሳዝነው። ወደ አዲስና ጤናማ የጸሎት ሕይወት እንዲያመጣህ በክርስቶስ ስትታመን፥ እንደምትወደው በቀላልነት፥ በኃይልና በደስታ ወዲያውኑ መጸለይ እንደምትችል አትጠብቅ። አይደለም፤ ወዲያውኑ ላይመጣ ይችላል። ነገር ግን በአለማወቅህና በድካምህ በእግዚአብሔር ፊት በጸጥታ ብቻ ስገድ። ራስህን እንዳለህ በእግዚአብሔር ፊት ማቅረብና በተሰወረው፥ በአንተ ውስጥ በሚጸልየው መንፈስ መታመን ከሁሉ የሚሻልና እውነተኛው ጸሎት ነው። «እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና»፤ አለማወቅ፥ ችግርና ትግል ጸሎታችንን ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ያመለክቱታል። ነገር ግን «መንፈስ ድካማችንን ያግዛል»። እንዴት? «መንፈስ ራሱ»፥ ከአሳባችንና ከስሜታችን በታች በጥልቅ ሆኖ፥ «በማይነገር መቃተት ይማልድልናል»። ቃላት ባጣህ ጊዜ፥ ቃሎችህም ቀዝቃዛና ደካማ በመሰሉህ ጊዜ፥ ዝም ብለህ እመን፦ መንፈስ ቅዱስ በእኔ ውስጥ እየጸለየ ነው። በእግዚአብሔር ፊት ዝም በል፥ ጊዜና ዕድልም ስጠው፤ በጊዜው መጸለይን ትማራለህ። በአንተ ውስጥ ለሚያደርገው ምልጃ በትዕግሥትና በመታመን ራስህን በመስጠት ባለማክበርህ የጸሎትን መንፈስ እንዳታሳዝን ተጠንቀቅ።

ሦስተኛው ትምህርት፦ «መንፈስ ይሙላባችሁ» (ኤፌሶን 5:18)። የታላቁን እውነት ትርጉም ያየን ይመስለኛል፤ በትክክል ሊጸልይ የሚችለው ጤናማው መንፈሳዊ ሕይወት ብቻ ነው። ትእዛዙ ወደ እያንዳንዳችን ይመጣል፦ «መንፈስ ይሙላባችሁ»። ይህም አንዳንዶች በጅማሬው፥ በጥቂት የመንፈስ ሥራ መጠን ረክተው ሲያርፉ፥ መንፈስ እንዲሞላብን የእግዚአብሔር ፈቃድ እንደ ሆነ ያመለክታል። ይህ ከእኛ ወገን፥ መላ ማንነታችን በእርሱ ብቻ እንዲያዝና እንዲገዛ ለመንፈስ ቅዱስ ፈጽሞ መሰጠት አለበት ማለት ነው። ከእግዚአብሔር ወገን ደግሞ መንፈስ ቅዱስ እንዲይዘንና እንዲሞላን ልንታመንና ልንጠብቅ እንችላለን ማለት ነው። በጸሎት መውደቃችን የጸሎትን መንፈስ ሕይወታችን እንዲሆን ስላልተቀበልነው፥ አብ የልጁን ሕይወት በእኛ እንዲሠራ የልጁ መንፈስ አድርጎ ለሰጠው ለእርሱ ፈጽመን ስላልተገዛን እንደ ሆነ ግልጥ አይደለምን? ቢያንስ ቢያንስ እርሱን ለመቀበል፥ ራሳችንን ለእግዚአብሔር ለመስጠትና ስለዚህ በእርሱ ለመታመን ፈቃደኞች እንሁን። ራሱን ለእኛ ሊሰጥ በፈቀደው መጠን በሙላት እርሱን ለማግኘት ከመፈለግ እንቢ በማለት፥ ቸል በማለት፥ በማመንታት ዳግመኛ ሆን ብለን መንፈስ ቅዱስን አናሳዝን። ጸሎት የሥራችንና የቤተ ክርስቲያን ታላቅ ፍላጎት እንደ ሆነ በጥቂቱም ቢሆን አይተን ከሆነ፥ ይበልጥ ለመጸለይ በጥቂቱም ቢሆን ተመኝተን ወይም ቈርጠን ከሆነ፥ ወደ ኃይልና በረከት ሁሉ ምንጭ እንመለስ፤ የጸሎት መንፈስ በሙላቱ እንኳ ለእኛ እንደ ሆነ እንመን።

አብና ወልድ በጸሎታችን ያላቸውን ስፍራ ሁላችንም እንቀበላለን። የምንጸልየው ወደ አብ ነው፤ መልሱንም የምንጠብቀው ከእርሱ ነው። በእርሱ እየኖርን እርሱም በእኛ እየኖረ እንደምንሰማ የምንታመነው በወልድ ብቃት፥ ስምና ሕይወት ነው። ነገር ግን በቅድስት ሥላሴ ሦስቱም አካላት በጸሎት እኩል ስፍራ እንዳላቸው፥ በእኛ ውስጥ እንደሚጸልይ በምልጃ መንፈስ ቅዱስ ማመን በአብና በወልድ እንደ ማመን የግድ አስፈላጊ እንደ ሆነ ተረድተናልን? ይህን፦ «በእርሱ ሥራ ሁላችን በአንድ መንፈስ ወደ አብ መግባት አለንና» በሚለው ቃል ምንኛ ግልጥ አድርገን እናገኘዋለን! ጸሎት ወደ አብ፥ በወልድ በኩል መሆን እንዳለበት ሁሉ በመንፈስ መሆን አለበት። መንፈስም በእኛ ውስጥ ሊጸልይ የሚችለው በእኛ ውስጥ በሚኖርበት መጠን ብቻ ነው። በእኛ ውስጥ ለሚኖረውና ለሚጸልየው መንፈስ ራሳችንን ስንሰጥ ብቻ ጸሎትን የሚሰማው የእግዚአብሔር ክብርና ለዘላለም የተባረከውና እጅግ ኃይል የሚያደርገው የወልድ መካከለኛነት በኃይላቸው በእኛ ሊታወቁ ይችላሉ። (ማስታወሻ መ።)

የመጨረሻው ትምህርታችን፦ ስለ ቅዱሳን ሁሉ በመንፈስ ጸልይ (ኤፌሶን 6:18)። «የልመና መንፈስ» የተባለው መንፈስ ደግሞና በተለይም የምልጃ መንፈስ ነው። ስለ እርሱ፦ «መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል» ተብሎአል። «ስለ ቅዱሳን ይማልዳልና።» ስለ ክርስቶስ፦ «ደግሞ ስለ እኛ የሚማልደው» ተብሎ የተነገረው ያው ቃል ነው። አሳቡ በመሠረቱ የመካከለኛነት፥ አንዱ ስለ ሌላው የሚማጸንበት ነው። የምልጃ መንፈስ ፈጽሞ ሲይዘን፥ ስለ ሌሎች ከሚያደርገው ምልጃ ለይተን ለራሳችን ብቻ እንደምንፈልገው ያለ ራስ ወዳድነት ሁሉ ይወገዳል፤ ስለ ሰዎች የመማለድን አስደናቂ መብታችንን መጠቀም እንጀምራለን። ልባችን በዙሪያችን ላሉት የእግዚአብሔርን በረከት ለማግኘት ያለ ማቋረጥ ራሱን ለእግዚአብሔር ሲሰጥ፥ ስለ ሌሎች ራሱን የሚበላ መሥዋዕት የሆነውን የክርስቶስን ሕይወት ለመኖር እንናፍቃለን። ያን ጊዜ ምልጃ የጸሎታችን አጋጣሚ ወይም አልፎ አልፎ የሚመጣ ክፍል ሳይሆን ብቸኛው ታላቅ ዓላማው ይሆናል። ለራሳችን የምንጸልየው ጸሎትም ያን ጊዜ እውነተኛ ስፍራውን ይይዛል፤ ይኸውም የምልጃ አገልግሎታችንን ይበልጥ ኃይል ባለው መንገድ ለመፈጸም የተሻልን እንድንሆን የሚያዘጋጀን መንገድ ብቻ ነው።

ለእያንዳንዱ አንባቢዬ እጅግ የግል ቃል እንድናገር ይፈቀድልኝን? ለእነርሱ ልሰጣቸው የምችለውን እንዲሰጠኝ እግዚአብሔርን በትሕትና ለምኜዋለሁ፤ ይኸውም በጸሎት የመውደቅን ሕይወት በእውነት ለመተው፥ መንፈስ ቅዱስ እንዲኖሩት ሊያስችላቸው ወደሚችለው የምልጃ ሕይወት አሁኑኑ፥ ወዲያውም ለመግባት መለኮታዊ ብርሃንና ረድኤት ነው። ይህ የመንፈስን ሙላት በሚጠይቅ ቀላል የእምነት ድርጊት ሊሆን ይችላል፤ ሙላቱም በእግዚአብሔር ፊት ልትቀበለው የምትችለው፥ ስለዚህም እርሱ ሊሰጥ ፈቃደኛ የሆነው የመንፈስ ሙሉ መጠን ነው። አሁኑኑ ይህን በእምነት አትቀበለውምን?

በመለወጥ ጊዜ የሚሆነውን ላስታውስህ። አብዛኞቻችን፥ ምናልባት አንተም፥ ለጥቂት ጊዜ ኃጢአትን ለመተውና እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት በጥረትና በትግል ሰላምን ፈለግን። ነገር ግን በዚህ መንገድ አላገኘኸውም። የእግዚአብሔር የይቅርታ ሰላም የመጣው በእምነት፥ ስለ ክርስቶስና ስለ መዳኑ በሚናገረው በእግዚአብሔር ቃል በመታመን ነው። ክርስቶስ የፍቅሩ ስጦታ እንደ ሆነ ሰምተህ ነበር፤ ለአንተም ደግሞ እንደ ሆነ ታውቅ ነበር፤ የጸጋውንም እንቅስቃሴና መሳብ ተሰምቶህ ነበር፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ቃል በማመን ለአንተ የእግዚአብሔር ስጦታ አድርገህ እስክትቀበለው ድረስ እርሱ ሊሰጥ የሚችለውን ሰላምና ደስታ ከቶ አላወቅህም። በእርሱና በሚያድነው ፍቅሩ ማመን ልዩነቱን ሁሉ አመጣ፤ ሁልጊዜ ያሳዝነው ከነበረ ሰው ወደሚወደውና ወደሚያገለግለው ሰው ግንኙነትህን ለወጠ። ቢሆንም ከጊዜ በኋላ እርሱን እጅግ በደካማ ሁኔታ መውደድህንና ማገልገልህን አንድ ሺህ ጊዜ ተደንቀሃል።

በተለወጥህ ጊዜ ስለ መንፈስ ቅዱስ የምታውቀው ጥቂት ነበር። ከዚያ በኋላ በአንተ ውስጥ እንደሚኖር፥ አብ እንድትሆን ላሰበው ሁሉ በአንተ ውስጥ የእግዚአብሔር ኃይል እንደ ሆነ ሰማህ፤ ቢሆንም በአንተ መኖሩና በአንተ መሥራቱ ግልጥ ያልሆነና ያልተወሰነ፥ የደስታ ወይም የብርታት ምንጭም ሊባል የማይችል ነገር ሆኖአል። በተለወጥህ ጊዜ እርሱን እንደምትፈልገው ገና አላወቅህም ነበር፤ ከእርሱ ምን ልትጠብቅ እንደምትችልማ ይበልጥ አላወቅህም። ውድቀቶችህ ግን አስተማሩህ። አሁንም ባለመታመንህና ባለመከተልህ፥ የእግዚአብሔርን በጎ ፈቃድ ሁሉ በአንተ እንዲሠራ ባለመፍቀድህ እንዴት ስታሳዝነው እንደ ነበርህ ማየት ጀምረሃል።

ይህ ሁሉ ሊለወጥ ይችላል። ክርስቶስን ከፈለግህ፥ ወደ እርሱ ከጸለይህና እርሱን ለማገልገል ሞክረህ ካልተሳካልህ በኋላ በእምነት በመቀበል ዕረፍት እንዳገኘህ፥ ልክ እንዲሁ አሁንም ራስህን ለመንፈስ ቅዱስ ሙሉ አመራር ልትሰጥ፥ እግዚአብሔር የሚወደውን በአንተ ውስጥ እንዲሠራ ልትጠይቀውና ልትቀበለው ትችላለህ። አታደርገውምን? የሕይወትህ ሁሉ፥ የጸሎት ሕይወትህም ደግሞ መንፈስ ይሆን ዘንድ የክርስቶስ ስጦታ አድርገህ በእምነት ብቻ ተቀበለው፤ ኃላፊነቱን እንዲወስድም በእርሱ ልትታመን ትችላለህ። ከዚያም ምንም ያህል ደካማ ቢሰማህና በትክክል መጸለይ ባትችልም፥ መጸለይን እንደሚያስተምርህ በመተማመን በእግዚአብሔር ፊት በዝምታ መስገድ ልትጀምር ትችላለህ።

ውድ ወንድሜ ሆይ፥ ይቅር እንዲልህ ክርስቶስን እያወቅህ በእምነት እንደ ተቀበልኸው፥ አሁንም በዚያው እምነት ሥራውን በአንተ እንዲሠራ መንፈስ ቅዱስን የሚሰጠውን ክርስቶስን እያወቅህ ልትቀበል ትችላለህ። «ክርስቶስ ... ዋጀን፤ ... የመንፈስን ተስፋ በእምነት እንድንቀበል።» ተንበርከክ፥ በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቀው ጌታ ክርስቶስ ለእምነትህ ምላሽ በውስጥህ የሚኖረውን የመንፈስ ኃይል በሙላት የምትለማመድበትን ብፁዕ ሕይወት አሁን በአንተ እንደሚጀምር በቀላሉ እመን። ከስሜትና ከልምምድ ሁሉ ተለይተህ የልመናና የምልጃ መንፈስ ሆኖ ሥራውን እንዲሠራ በሙሉ መተማመን በእርሱ ተደገፍ። ያን የእምነት ድርጊት በየማለዳው፥ በጸለይህም ቍጥር አድስ፤ የሚታየው ሁሉ ቢቃወምም በአንተ ውስጥ እንዲሠራ ታመንበት፥—እየሠራ እንዳለ እርግጠኛ ሁን፥—የመንፈስ ቅዱስ ደስታ የሕይወትህ ኃይል ሆኖ ምን እንደ ሆነ እንድታውቅም ይሰጥሃል።

«የልመናን መንፈስ አፈስሳለሁ።» የጸሎት ምሥጢር የመለኮታዊ መኖር ምሥጢር እንደ ሆነ ማየት አትጀምርምን? በሰማይ ያለው እግዚአብሔር በእኛ ውስጥ የሚጸልይና ወደ አምላካችን ወደ ላይ የሚስበን መለኮታዊ ኃይል ሆኖ በዚያ እንዲኖር መንፈሱን በልባችን ይሰጣል። እግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ በውስጣችን ያለ ተመሳሳይ ሕይወትና መንፈስ እንጂ ሌላ ምንም ከእርሱ ጋር ኅብረት ሊያደርግ አይችልም። ሰው የተፈጠረው ለዚህ ነው፤ እግዚአብሔር በእርሱ እንዲኖርና እንዲሠራ፥ የሕይወቱም ሕይወት እንዲሆን። ኃጢአት ያጣው ይህን መለኮታዊ መኖር ነው። ክርስቶስ በሕይወቱ ሊያሳየው፥ በሞቱ መልሶ ሊያስገኝልን፥ ከዚያም በደቀ መዛሙርቱ ውስጥ ሊኖር በመንፈስ ከሰማይ ዳግመኛ በመምጣት ሊያካፍለን የመጣው ይህን ነው። ለጸሎት የተሰጡትን አስደናቂ ተስፋዎች ሊያስረዳና የራሳችን ልናደርጋቸው ሊያስችለን የሚችለው ይህ፥ በመንፈስ የሆነው የእግዚአብሔር መኖር ብቻ ነው። እግዚአብሔር ጸሎት ሁልጊዜ ወደ ላይ የሚወጣበት ሕይወት አድርጎ መለኮታዊ ሕይወቱን በውስጣችን እንዲጠብቅ መንፈስን የልመና መንፈስ አድርጎ ደግሞ ይሰጣል።

ያለ መንፈስ ቅዱስ ማንም ኢየሱስን ጌታ ብሎ ሊጠራ ወይም አባ አባት ብሎ ሊጮኽ አይችልም፤ ማንም በመንፈስና በእውነት ሊሰግድ ወይም ሳያቋርጥ ሊጸልይ አይችልም። መንፈስ ቅዱስ ለአማኝ የተሰጠው እግዚአብሔር እንዲሆንና እንዲያደርግ የሚፈልገውን ሁሉ በእርሱ ውስጥ እንዲሆንና እንዲያደርግ ነው። በተለይ የጸሎትና የልመና መንፈስ ሆኖ ተሰጥቶታል። በጸሎት ሁሉ ነገር የተመካው ሥራውን በእኛ ውስጥ እንዲሠራ በመንፈስ ቅዱስ በመታመናችን፥ ራሳችንን ለአመራሩ በመስጠትና በእርሱ ብቻና ፈጽመን በመደገፍ ላይ እንደ ሆነ ግልጥ አይደለምን?

«እምነትና መንፈስ ቅዱስም የሞላበት» ሰው ስለ ነበረው ስለ እስጢፋኖስ እናነባለን። ሁለቱ ሁልጊዜ አብረው ይሄዳሉ፥ እርስ በርሳቸውም በትክክለኛ መጠን ይመጣጠናሉ። እምነታችን በእኛ ውስጥ እንዲጸልይ መንፈስን አይቶ ሲታመንበትና ሲጠብቀው ሥራውን ይሠራል፤ አብ የሚፈልገውም የናፍቆት ምኞትን፥ የጋለ ልመናንና የተወሰነ እምነትን ነው። እንግዲህ እርሱን እንወቀው፤ እርሱን ያለ ማቋረጥ በሚሰጠው በክርስቶስ እምነት የተረጋገጠ መተማመንን እናሳድግ፤ አብ እንደሚወደው መጸለይን ልንማር እንችላለን።

ለተጨማሪ ጸሎት የቀረበ ልመና

ገጽ 1 / 1 · 9 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል