የእንጦንስ ሕይወት
አባ እንጦንስ እስከ ዕለተ ሞቱ ጤናማ እንደ ኖረና ዝናው ዓለምን ሁሉ እንደ ሞላ

ምዕራፍ 44 · 1 ደቂቃ ንባብ · 1 ደቂቃ ማዳመጥ

አባ እንጦንስ እስከ ዕለተ ሞቱ ጤናማ እንደ ኖረና ዝናው ዓለምን ሁሉ እንደ ሞላ

93. የአባ እንጦንስ የሥጋ ሕይወት ፍጻሜ ይህ ነው፤ ከላይ የተነገረውም የተጋድሎው ጅማሬ ነበር። ይህ ትረካ ከበጎነቱ ጋር ሲነጻጸር ጥቂት ቢሆንም፣ ከዚህ ተነሥታችሁ የእግዚአብሔር ሰው አባ እንጦንስ ምን ያህል ታላቅ እንደ ነበረ አስቡ። እርሱ ከወጣትነቱ ጀምሮ እስከዚህ ታላቅ ዕድሜ ድረስ ለተጋድሎ የነበረውን ቅንዓት ሳይለዋወጥ ጠበቀ፤ በእርጅናም ምክንያት የተንደላቀቀ ምግብ ምኞት አላሸነፈውም፤ በሥጋውም ድካም ምክንያት የአለባበሱን ሁኔታ አልለወጠም፤ እግሮቹንም እንኳ በውኃ አልታጠበም፤ ሆኖም ምንም ጕዳት ሳይደርስበት ፈጽሞ ጤናማ ሆኖ ኖረ። ዓይኖቹ አልፈዘዙም ነበር፤ ፍጹም ጤናማ ነበሩ፤ አጥርቶም ያይ ነበር። ከጥርሶቹም አንዱ እንኳ አልወደቀም ነበር፤ ነገር ግን ከሽማግሌው ዕድሜ ብዛት የተነሣ እስከ ድዱ ድረስ ተሸርሽረው ነበር። በእጆቹም በእግሮቹም ብርቱ ሆኖ ኖረ፤ ሰዎች ሁሉ ልዩ ልዩ ምግብ፣ ገላ መታጠብና ልዩ ልዩ ልብስ ሲጠቀሙ፣ እርሱ ይበልጥ ደስተኛና ብርቱ ሆኖ ይታይ ነበር። ዝናው በየስፍራው መሰማቱ፣ ሁሉም በአድናቆት ማየታቸው፣ አይተውት የማያውቁትም መናፈቃቸው የበጎነቱና እግዚአብሔር ለነፍሱ ያለው ፍቅር ግልጥ ማስረጃ ነው። አባ እንጦንስ የታወቀው በመጻሕፍት ወይም በዓለማዊ ጥበብ ወይም በማናቸውም ሙያ አይደለም፤ እግዚአብሔርን በመፍራቱ ብቻ ነው እንጂ። ይህ የእግዚአብሔር ስጦታ እንደ ሆነ ማንም አይክድም። የራሱን ሰዎች በየስፍራው የሚያስታውቅ፣ ይህንንም ለአባ እንጦንስ ከመጀመሪያው ተስፋ የሰጠው እግዚአብሔር ባይሆን ኖሮ፣ በተራራ ውስጥ ተሰውሮ ይኖር የነበረው ይህ ሰው ከወዴት እስከ እስጳንያና እስከ ጋሊያ፣ እንዴትስ እስከ ሮሜና እስከ አፍሪካ ድረስ ሊሰማ ይችል ነበር? እነርሱ በስውር ቢሠሩም፣ ተሰውረው ሊኖሩ ቢፈልጉም፣ ጌታ ግን የሚሰሙ ሁሉ የእግዚአብሔር ትእዛዛት ሰዎችን ሊያከናውኑ እንደሚችሉ አውቀው በበጎነት መንገድ በቅንዓት እንዲጓዙ፣ ለሁሉ የሚያበሩ መብራቶች አድርጎ ይገልጣቸዋል።

ምዕራፍ 44 ተጠናቋል

አባ እንጦንስ እስከ ዕለተ ሞቱ ጤናማ እንደ ኖረና ዝናው ዓለምን ሁሉ እንደ ሞላ

ገጽ 1 / 1 · 1 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል
ቀዳሚ ቀጣይ