ምዕራፍ 39 · 1 ደቂቃ ንባብ · 1 ደቂቃ ማዳመጥ
የደካሞችን ድካም መሸከሙና ለግብፅ ሁሉ ያደረገው ታላቅ በጎነት
87. እንግዲህ ጨካኞችን እንዲህ አስጠነቀቃቸው። ወደ እርሱ የመጡትን ሌሎቹን ግን ክርክራቸውን ወዲያው እስኪረሱና ከዓለም ተለይተው የሚኖሩትን ብፁዓን ብለው እስኪያመሰግኑ ድረስ አስተማራቸው። የተበደሉትንም እንዲህ አድርጎ ይከራከርላቸው ስለ ነበር፣ የተበደለው ሌሎቹ ሳይሆኑ እርሱ ራሱ ይመስልህ ነበር። ከዚህም በላይ ለሁሉ እጅግ ጠቃሚ ሊሆን ስለ ቻለ ብዙ ወታደሮችና ብዙ ሀብት የነበራቸው ሰዎች የኑሮን ሸክም አስቀምጠው በቀረው ዘመናቸው መነኮሳት ሆኑ። እግዚአብሔርም ለግብፅ ሐኪም እንደ ሰጠ ነበር። በኀዘን ሆኖ አባ እንጦንስን አግኝቶ ደስ ብሎት ያልተመለሰ ማን ነው? ስለ ሞተበት ሰው እያለቀሰ መጥቶ ኀዘኑን ወዲያው ያላራቀ ማን ነው? በቍጣ መጥቶ ወደ ወዳጅነት ያልተለወጠ ማን ነው? ድሃና ልቡ የተሰበረ የትኛው ሰው አግኝቶት፣ ሰምቶትና አይቶት ሀብትን ያልናቀና በድህነቱ ራሱን ያላጽናና? ቸልተኛ ሆኖ የነበረ የትኛው መነኩሴ ወደ እርሱ መጥቶ ይበልጥ ያልበረታ? የትኛው ወጣት ወደ ተራራው መጥቶ አባ እንጦንስን አይቶ ወዲያው ተድላን ያልካደና ራስን መግዛትን ያልወደደ? በጋኔን ተፈትኖ ወደ እርሱ መጥቶ ዕረፍትን ያላገኘ ማን ነው? በጥርጣሬስ ታውኮ መጥቶ የአእምሮ ጸጥታን ያላገኘ ማን ነው?
ምዕራፍ 39 ተጠናቋል
የደካሞችን ድካም መሸከሙና ለግብፅ ሁሉ ያደረገው ታላቅ በጎነት