ምዕራፍ 8 · 8 ደቂቃ ንባብ · 10 ደቂቃ ማዳመጥ
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉ አስቸጋሪ ነገሮች
ፈጥኖም ይሁን ዘግይቶ፣ እያንዳንዱ ወጣት ክርስቲያን ለመረዳት የሚከብዱና ለማመን የሚያስቸግሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ያጋጥሙታል። ለብዙ ወጣት ክርስቲያኖች እነዚህ አስቸጋሪ ነገሮች በክርስትና ሕይወታቸው እድገት ላይ ከባድ እንቅፋት ይሆኑባቸዋል። ብዙ ጊዜ ለቀናት፣ ለሳምንታትና ለወራት እምነታቸው በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ እንደ ግርዶሽ ይጨልማል። በትክክል በዚህ ነጥብ ላይ ጥበብ ያለበት ምክር ያስፈልጋል። እነዚህ አስቸጋሪ ነገሮች መኖራቸውን የመደበቅ ፍላጎት የለንም። ይልቁንም በግልጽ ልንጋፈጣቸውና ልንመረምራቸው እንወዳለን። እያንዳንዱ አስተዋይ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ፈጥኖም ይሁን ዘግይቶ ስለሚያጋጥሙት ስለ እነዚህ አስቸጋሪ ነገሮች ምን እናድርግ?
1. ስለ እነዚህ አስቸጋሪ ነገሮች በመጀመሪያ የምንለው፣ ከነገሩ ባሕርይ የተነሣ አስቸጋሪ ነገሮች መኖራቸው የሚጠበቅ መሆኑን ነው። አንዳንድ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አስቸጋሪ ነገሮች በመኖራቸው ይደነቃሉ፤ ይናወጣሉም። እኔ ግን አስቸጋሪ ነገሮች ባይኖሩበት ኖሮ ይበልጥ እደነቅና ይበልጥ እናወጥ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ምንድር ነው? ወሰን የሌለው ታላቅ፣ ፍጹም ጠቢብና ፍጹም ቅዱስ የሆነው የእግዚአብሔር አሳብ፣ ፈቃድ፣ ባሕርይና ማንነት መገለጥ ነው። ይህ መገለጥ የተሰጠው ግን ለማን ነው? እንደ እኔና እንደ አንተ ላሉ ወንዶችና ሴቶች፣ ውሱን ለሆኑ ፍጥረታት ነው። በአእምሮ እድገታቸው፣ ስለዚህም በእውቀታቸው፣ እንዲሁም በባሕርያቸው፣ ስለዚህም በመንፈሳዊ ማስተዋላቸው ፍጹማን ላልሆኑ ሰዎች ነው።
ከነገሩ የግድ አስፈላጊነት የተነሣ፣ እንደዚህ ላሉ ሰዎች በተሰጠ እንደዚህ ያለ መገለጥ ውስጥ አስቸጋሪ ነገሮች መኖራቸው አይቀርም። ውሱን የሆነው ወሰን የሌለውን ለመረዳት ሲሞክር ችግር መፈጠሩ የማይቀር ነው። አላዋቂዎች በእውቀቱ ፍጹም የሆነውን የእርሱን ቃል ሲያሰላስሉ፣ ለመረዳት የሚከብዱ ብዙ ነገሮች፣ ላልበሰለውና ትክክለኛነት ለጎደለው አእምሮአቸውም ሞኝነት የሚመስሉ አንዳንድ ነገሮች መኖራቸው የግድ ነው። ኃጢአተኛ ፍጥረታት ፍጹም ቅዱስ የሆነው አምላክ የሚጠይቃቸውን ነገሮች ሲሰሙ በአንዳንዶቹ ጥያቄዎቹ መናወጣቸው አይቀርም፤ አድራጎቱንም ሲመለከቱ በአንዳንዶቹ አድራጎቶቹ መናወጣቸው አይቀርም። እነዚህ አድራጎቶች እጅግ ጽኑ፣ ኮስታራ፣ ጨካኝና አስፈሪ መስለው መታየታቸው የግድ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ መሆኑ በተረጋገጠው ዓይነት መገለጥ ውስጥ ለእኛ አስቸጋሪ የሆኑ ነገሮች መኖራቸው የግድ እንደ ሆነ ግልጽ ነው። አንድ ሰው እንደ ማባዣ ሰንጠረዥ ቀላል የሆነ መጽሐፍ ሰጥቶኝ፦ «ይህ እግዚአብሔር ፈቃዱንና ጥበቡን ሁሉ የገለጠበት የእግዚአብሔር ቃል ነው» ቢለኝ፣ ራሴን እየነቀነቅሁ፦ «ይህን ማመን አልችልም። ወሰን የሌለው ጥበብ ፍጹም መገለጥ ለመሆን ይህ እጅግ ቀላል ነው» እለው ነበር። የእግዚአብሔርን አሳብ፣ ፈቃድ፣ ባሕርይና ማንነት በሚገልጥ በማንኛውም ሙሉ መገለጥ ውስጥ ለጀማሪ ለመረዳት የሚከብዱ ነገሮች መኖራቸው የግድ ነው፤ ከእኛም መካከል እጅግ ጠቢባንና እጅግ መልካሞች የሆኑት እንኳ ጀማሪዎች ብቻ ናቸው።
2. ስለ እነዚህ አስቸጋሪ ነገሮች ሁለተኛ የምንለው፣ በአንድ ትምህርት ውስጥ ያለ ችግር ወይም በአንድ ትምህርት ላይ የሚነሣ ከባድ ተቃውሞ ትምህርቱ ሐሰት መሆኑን በምንም መንገድ እንደማያረጋግጥ ነው። ብዙ የማያስተውሉ ሰዎች ያረጋግጣል ብለው ያስባሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ከእግዚአብሔር የመጣ መሆኑን፣ ፍጹም ከስሕተት የጸዳና የማይሳሳት መሆኑን ለማመን እንቅፋት የሚሆን አንዳች ችግር ቢያጋጥማቸው፣ ወዲያውኑ ትምህርቱ ፈርሷል ብለው ይደመድማሉ። ይህ ከአመክንዮ እጅግ የራቀ ነው። ለአፍታ ቆም ብለህ አስብ፤ ምክንያታዊና ሚዛናዊ መሆንንም ተማር። ዛሬ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ካገኙት የሳይንስ ትምህርቶች መካከል፣ ተቀባይነት እንዳያገኝ ታላቅ ችግር ያልገጠመው አንድም እንኳ የለም ማለት ይቻላል። ዛሬ በሁሉ ዘንድ ተቀባይነት ያገኘው የኮፐርኒከስ ንድፈ ሐሳብ በመጀመሪያ በታወጀ ጊዜ እጅግ ከባድ ችግር ገጥሞት ነበር። ይህ ንድፈ ሐሳብ እውነት ከሆነ ቬነስ የተባለችው ፕላኔት እንደ ጨረቃ እየሞላችና እየጎደለች መታየት ነበረባት። ነገር ግን በዚያን ጊዜ ከነበሩት ቴሌስኮፖች እጅግ በተሻለው እንኳ ይህ መሞላትና መጉደል ሊታይ አልቻለም። ሆኖም ንድፈ ሐሳቡን የሚደግፈው ቀጥተኛ ማስረጃ እጅግ ብርቱ ስለ ነበረ፣ መልስ የሌለው የሚመስለው ይህ ተቃውሞ እያለም ተቀባይነት አገኘ። ይበልጥ ኃይለኛ ቴሌስኮፕ በተሠራ ጊዜም፣ ቬነስ በእርግጥም እንደ ጨረቃ እንደምትሞላና እንደምትጎድል ታወቀ። ችግሩ ሁሉ የተነሣው፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ያሉት ችግሮች ሁሉ እንደሚነሡት፣ ሰው በጉዳዩ ውስጥ ያሉትን አንዳንድ እውነታዎች ካለማወቁ ነበር። በእያንዳንዱ የሳይንስ ዘርፍ ተቀባይነት ባለው የጤናማ አእምሮ አመክንዮ መሠረት፣ አንድን ንድፈ ሐሳብ የሚደግፈው ቀጥተኛ ማስረጃ አሳማኝ ከሆነ፣ በጥቃቅን ዝርዝሮች ውስጥ ምንም ያህል ችግሮች ቢኖሩ ምክንያታዊ ሰዎች ያምኑታል። እንግዲህ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን፣ ማለትም ስለ ራሱ፣ ስለ ዓላማዎቹና ስለ ፈቃዱ፣ ስለ ሰው ግዴታና ዕጣ ፈንታ፣ ስለ መንፈሳዊና ዘላለማዊ እውነታዎች እግዚአብሔር ራሱ የሰጠው ፍጹም የሚታመን መገለጥ መሆኑን የሚያሳየው ቀጥተኛ ማስረጃ ፍጹም አሳማኝ ነው። ስለዚህ በጥቃቅን ዝርዝሮች ውስጥ ምንም ያህል ችግሮች ቢኖሩ፣ ምክንያታዊ የሆነ ወንድ ሁሉና ሴት ሁሉ ሊያምነው ይገባል። ከአንድ እውነት ጋር ሊያስታርቃቸው ያልቻላቸው አንዳንድ እውነታዎች ስላሉ በሚገባ የተረጋገጠውን ያን እውነት የሚተው ሰው ጥልቀት የሌለው አሳቢ ነው። ከዚያ ትምህርት ጋር ሊያስታርቃቸው ያልቻላቸው እውነታ የሚመስሉ አንዳንድ ነገሮች ስላሉ የመጽሐፍ ቅዱስን መለኮታዊ ምንጭና ከስሕተት የጸዳ መሆኑን የሚተውም እጅግ ጥልቀት የሌለው የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር ነው።
3. ስለ መጽሐፍ ቅዱስ አስቸጋሪ ነገሮች ሦስተኛ የምንለው፣ መጽሐፍ ቅዱስ ከእግዚአብሔር የመጣ፣ ስለዚህም ሙሉ በሙሉ የሚታመን ነው በሚለው ትምህርት ላይ ካሉት ችግሮች ይልቅ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ከሰው የመጣ፣ ስለዚህም ሊሳሳት የሚችል ነው በሚለው ትምህርት ላይ እጅግ የበዙና እጅግ የከበዱ ችግሮች እንዳሉ ነው። አንድ ሰው አንዳች ችግር አቅርቦ፦ «መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ከሆነ ይህን እንዴት ታብራራዋለህ?» ሊልህ ይችላል፤ ምናልባትም አጥጋቢ መልስ ልትሰጠው አትችል ይሆናል። በዚያን ጊዜ ያሸነፈህ ይመስለዋል፤ ነገር ግን ፈጽሞ አላሸነፈህም። ወደ እርሱ ዞረህ እንዲህ ብለህ ጠይቀው፦ መጽሐፍ ቅዱስ ከሰው የመጣ ከሆነ በውስጡ የተፈጸሙትን ትንቢቶች እንዴት ታብራራቸዋለህ? የመጽሐፉን አስደናቂ አንድነት እንዴት ታብራራዋለህ? የማያልቀውን ጥልቀቱን እንዴት ታብራራዋለህ? ሰዎችን ወደ እግዚአብሔር ከፍ የሚያደርግበትን ልዩ ኃይሉን እንዴት ታብራራዋለህ? የመጽሐፉን ታሪክ፣ በሰዎች ጥቃት ሁሉ ላይ ያገኘውን ድል፣ ወዘተ፣ ወዘተ፣ ወዘተ እንዴት ታብራራዋለህ? እርሱ በአንተ አመለካከት ላይ ለሚያቀርበው ለእያንዳንዱ ኢምንት ተቃውሞ፣ አንተ በእርሱ አመለካከት ላይ እጅግ ጥልቅ ትርጉም ያላቸውን ብዙ ተቃውሞዎች ልታቀርብ ትችላለህ፤ ቅን የሆነ ማንኛውም ሰው በሁለቱ አመለካከቶች መካከል ለመወሰን አይቸገርም። መጽሐፍ ቅዱስ መለኮታዊ ምንጭና ሥልጣን እንዳለው የሚክደውን ሰው የሚገጥሙት ችግሮች፣ መለኮታዊ ምንጭና ሥልጣን እንዳለው የሚያምኑትን ከሚገጥሙት ችግሮች እጅግ የበዙና እጅግ የከበዱ ናቸው።
4. ስለ መጽሐፍ ቅዱስ አስቸጋሪ ነገሮች አራተኛ የምንለው፣ አንተ አንድን ችግር መፍታት አለመቻልህ ችግሩ ሊፈታ እንደማይችል አያረጋግጥም፤ አንተ ለአንድ ተቃውሞ መልስ መስጠት አለመቻልህም ለተቃውሞው መልስ ሊሰጥ እንደማይችል ፈጽሞ አያረጋግጥም። ይህን እጅግ ግልጽ የሆነ እውነታ ምን ያህል ጊዜ እንደምንዘነጋው እጅግ የሚገርም ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንድ ችግር ሲያጋጥማቸውና ጥቂት ካሰቡበት በኋላ ምንም መፍትሔ ሊያዩ ሳይችሉ ሲቀሩ፣ ማንም ሊፈታው አይችልም ወደሚል መደምደሚያ ወዲያውኑ የሚዘሉ፣ በዚህም በመጽሐፍ ቅዱስ ታማኝነትና በመለኮታዊ ምንጩ ላይ ያላቸውን እምነት የሚጥሉ ብዙዎች አሉ። ሁላችንም እንደ ሆንነው በእውቀት እጅግ ውሱን ለሆኑ ፍጥረታት የሚገባ ትንሽ ተጨማሪ ትሕትና ቢኖራቸው ኖሮ፦ «እኔ ለዚህ ችግር ምንም መፍትሔ ባላይም፣ ከእኔ ትንሽ የሚበልጥ ጠቢብ ሰው በቀላሉ ሊያገኝለት ይችላል» እንዲሉ ይመራቸው ነበር። ኦ! ሁሉን እንደማናውቅ፣ ትንሽ ተጨማሪ እውቀት ቢኖረን ኖሮ በቀላሉ ልንፈታቸው የምንችላቸው፣ አሁን ግን ልንፈታቸው የማንችላቸው እጅግ ብዙ ነገሮች እንዳሉ ብቻ ብናስታውስ! ከሁሉም በላይ፣ ለውሱን ጥበባችን—ወይም ለድንቁርናችን—ፈጽሞ የማይፈታ መስሎ ለሚታየው ነገር ወሰን ለሌለው ጥበብ እጅግ ቀላል መፍትሔ ሊኖረው እንደሚችል ፈጽሞ ልንዘነጋ አይገባም። አንድን አስቸጋሪ የአልጀብራ ጥያቄ ለመፍታት ለግማሽ ሰዓት በከንቱ ከሞከረ በኋላ፣ እርሱ ምንም መፍትሔ ስላላገኘ ለጥያቄው ምንም መፍትሔ የለውም ብሎ ስለሚናገር የአልጀብራ ጀማሪ ተማሪ ምን እናስባለን? ብዙ ልምድና ችሎታ የነበረው አንድ ሰው በአንድ ወቅት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ግልጽ ተቃርኖ የመሰለውን ነገር ስላገኘ፣ በታላቅ የመንፈስ ጭንቀት ሥራውን ትቶ እኔን ለማየት ከሩቅ መጣ። ነገሩን ለማስታረቅ ያደረገውን ሙከራ ሁሉ አክሽፎበት ነበር፤ ነገር ግን በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ለችግሩ እጅግ ቀላልና አጥጋቢ መፍትሔ ታየው።
5. ስለ መጽሐፍ ቅዱስ አስቸጋሪ ነገሮች አምስተኛ የምንለው፣ በመጽሐፉ ውስጥ ጉድለት የሚመስሉት ነገሮች ከብዙና ከአስደናቂ መልካምነቱ ጋር ሲነጻጸሩ እጅግ ኢምንት መሆናቸውን ነው። ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጉድለት ናቸው ብለው በሚያስቧቸው ኢምንት ነጥቦች ላይ በመዘብዘብ ይህን ያህል ጊዜ ማሳለፋቸው፣ ከሞላ ጎደል እያንዳንዱን ገጽ የሚያስጌጡትንና የሚያከብሩትን ተወዳዳሪ የሌላቸውን ውበቶችና ድንቆች ግን ፈጽሞ ሳያስተውሉ ማለፋቸው፣ በእርግጥ የአእምሮንም የልብንም ታላቅ ጠማማነት ያሳያል። አንድን ታላቅ የጥበብ ሥራ እያጠና ሳለ፣ በጥጉ ላይ የዝንብ ነጠብጣብ በመሰለው ነገር ላይ ብቻ ትኩረቱን ሁሉ ስለሚያደርግ ሰው ምን እናስባለን? «የመጽሐፍ ቅዱስ ሂሳዊ ጥናት» ተብሎ የሚወደሰው ነገር ትልቁ ክፍል የዝንብ ነጠብጣብ ናቸው ተብለው በሚታሰቡ ነገሮች ላይ የሚደረግ አድካሚና ምሁራዊ ምርመራ ሲሆን፣ የመጽሐፉን ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ክብሮች ግን ፈጽሞ ቸል ይላል።
6. ስለ መጽሐፍ ቅዱስ አስቸጋሪ ነገሮች ስድስተኛ የምንለው፣ የመጽሐፍ ቅዱስ አስቸጋሪ ነገሮች በጥልቀት ከሚያጠኑት ይልቅ ላይ ላዩን በሚያነቡት ዘንድ እጅግ የላቀ ክብደት እንዳላቸው ነው። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነተኛ ይዘትና ትርጉም ፈጽሞ የማያውቅና ኃይሉን ሁሉ በውስጡ ተቃርኖ የሚመስሉ ነገሮችን ለማግኘት የሚያውል ሰውን ውሰድ፤ ለእንደዚህ ያሉ ላይ ላዩን ለሚያጠኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች እነዚህ ችግሮች እጅግ ታላቅ ክብደት ያላቸው ይመስላሉ፤ የእግዚአብሔርን ቃል በቀንና በሌሊት ማሰላሰልን ለተማረ ሰው ግን ምንም ክብደት የላቸውም ማለት ይቻላል። መጽሐፍ ቅዱስን ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ከመቶ ጊዜ በላይ በጥንቃቄ ያጠናው ያ ኃያል የእግዚአብሔር ሰው ጆርጅ ሙለር ባጋጠሙት በማንኛውም ችግር አልታወከም። ነገር ግን ለመጀመሪያ ወይም ለሁለተኛ ጊዜ በጥንቃቄ ለሚያነበው ሰው ግራ የሚያጋቡና የሚያናውጡ ብዙ ነገሮች አሉ።
7. ስለ መጽሐፍ ቅዱስ አስቸጋሪ ነገሮች ሰባተኛ የምንለው፣ በጥንቃቄና በጸሎት ሲጠኑ በፍጥነት እንደሚጠፉ ነው። በአንድ ወቅት ግራ ያጋቡንና ያናወጡን፣ አሁን ግን ፍጹም ግልጽ የሆኑልንና ከእንግዲህ ምንም ችግር የማይፈጥሩብን ስንት ነገሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አሉ! እንግዲያስ ገና የቀሩት ችግሮችም ተጨማሪ ጥናት ሲደረግ ይጠፋሉ ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ አይደለምን?
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚያጋጥሙንን አስቸጋሪ ነገሮች እንዴት እንያዛቸው?
1. ከሁሉ በፊት፣ በቅንነት። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንድ ችግር ባገኘህ ቁጥር ችግሩ መኖሩን በግልጽ እመን። መልካምና ቅን ማብራሪያ መስጠት ካልቻልህ፣ ለጊዜው ምንም ማብራሪያ ለመስጠት አትሞክር።
2. በትሕትና። የአእምሮህንና የእውቀትህን ውሱንነት እወቅ፤ አንተ መፍትሔ ስላላገኘህ ብቻ መፍትሔ የለም ብለህ አታስብ። ምናልባትም እጅግ ቀላል መፍትሔ አለው። ዛሬ ምንም መፍትሔ ማግኘት ባትችልም አንድ ቀን ታገኘዋለህ።
3. በቁርጠኝነት። ምንም ያህል ጥናትና ብርቱ አስተሳሰብ ቢጠይቅብህ፣ ከተቻለ መፍትሔውን እንደምታገኝ ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉት አስቸጋሪ ነገሮች አእምሮህን ሥራ ላይ እንድታውል የሰማዩ አባትህ የሚያቀርብልህ ተግዳሮት ናቸው።
4. ያለ ፍርሃት። አንድ ችግር ስታገኝ፣ በመጀመሪያ እይታ ምንም ያህል መልስ የሌለው ቢመስልም አትደንግጥ። ከአንተ በፊት በሺህ የሚቈጠሩ ሰዎች እንደዚህ ያሉትን አግኝተዋል። ከመቶዎች ዓመታት በፊት ታይተዋል፤ ያም ሆኖ አሮጌው መጽሐፍ አሁንም ጸንቶ ቆሟል። ምንም እንኳ መፍትሔውን በትክክል የት እንደምታገኘው ባታውቅም፣ አንተ ከመወለድህ ብዙ ጊዜ በፊት ያልተገኘና ምናልባትም እልባት ያላገኘ ችግር ታገኛለህ ማለት አይመስልም። አሥራ ስምንት መቶ ዓመታት ጥብቅ ምርመራንና የማያቋርጥ አስፈሪ ጥቃትን ተቋቁሞ የቆመው መጽሐፍ ቅዱስ አንተ በምታገኛቸው በማንኛውም ግኝቶች ወይም በዘመናውያን ከሐዲዎች በማንኛውም ጥቃት ፊት አይወድቅም። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚሰነዘሩ የዘመናውያን ከሐዲዎች ጥቃቶች ሁሉ ባለፉት ዘመናት መቶ ጊዜ መልስ ያገኙ የቆዩ ተቃውሞዎች እንደገና ተቀባብተው መቅረባቸው ብቻ ናቸው። እነዚህ የቆዩ ተቃውሞዎች ባለፈው ዘመን አውልቀው በጣሏቸው ልብሶች ከነበራቸው ኃይል የበለጠ በአዲሶቹ ልብሶቻቸው ኃይል አይኖራቸውም።
5. በትዕግሥት። እያንዳንዱን ጥያቄ በአንድ ቀን ስላልፈታህ ተስፋ አትቍረጥ። አንድ ችግር የተቻለህን ሁሉ ጥረት ካከሸፈብህ ለጥቂት ጊዜ ወደ ጎን አቆየው። ምናልባት ወደ እርሱ ስትመለስ ችግሩ ጠፍቶ ይሆናል፤ በእርሱ እንዴት ግራ ተጋብተህ እንደ ነበርህም ትደነቃለህ። ይህን የሚጽፈው ሰው ዛሬ እንደ ቀን ብርሃን ግልጽ በሆኑ ጥያቄዎች ባለፈው ጊዜ ምን ያህል ክፉኛ ግራ ተጋብቶ እንደ ነበረ ሲያስብ ብዙ ጊዜ ፈገግ ይላል።
6. በመጽሐፍ ቅዱስ አማካይነት። በአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ ችግር ካገኘህ፣ በእርሱ ላይ ብርሃን የሚፈነጥቅና ችግሩን የሚያስወግድ ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ፈልግ። መጽሐፍ ቅዱስን እንደ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያብራራው የለም። ግልጽ ያልሆኑ የሚመስሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ከግልጽ ክፍሎች የሚመጣውን ብርሃን እንዲያጨልሙት ፈጽሞ አትፍቀድ፤ ይልቁንም ከግልጹ ክፍል የሚመጣው ብርሃን ግልጽ ያልሆነውን ክፍል የከበበው የሚመስለውን ጨለማ ያብራው።
7. በጸሎት። አንድ ሰው ችግሮችን በጕልበቱ ተንበርክኮ ሲመለከታቸው እንዴት እንደሚቀልጡ ድንቅ ነው። አንዳንድ ዘመናውያን ምሁራን አፍራሽ ተቺዎች ለመሆን ከተማሩባቸው ታላላቅ ምክንያቶች አንዱ መጸለይን መርሳታቸው ነው።
ምዕራፍ 8 ተጠናቋል
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉ አስቸጋሪ ነገሮች