በክርስትና ሕይወት እንዴት ስኬታማ መሆን እንደሚቻል
የቤተ ክርስቲያን አባልነት

ምዕራፍ 6 · 4 ደቂቃ ንባብ · 5 ደቂቃ ማዳመጥ

የቤተ ክርስቲያን አባልነት

ወጣትም ሆነ አረጋዊ፣ ማንም ክርስቲያን ከሌሎች አማኞች ጋር ኅብረት ሳይኖረው በክርስትና ሕይወት እውነተኛ ስኬት ሊያገኝ አይችልም። ቤተ ክርስቲያን በኢየሱስ ክርስቶስ በራሱ የተሠራች መለኮታዊ ተቋም ናት። ጸንቶ የሚኖር ብቸኛው ተቋም እርሷ ናት። ሌሎች ተቋማት ይመጣሉ ይሄዳሉ፤ በዘመናቸው ሥራቸውን ሠርተው ይጠፋሉ፤ ቤተ ክርስቲያን ግን እስከ ፍጻሜ ትኖራለች። «የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም» (ማቴዎስ 16:18)። ቤተ ክርስቲያን ከወንዶችና ከሴቶች፣ ፍጹማን ካልሆኑ ወንዶችና ሴቶች የተሠራች ናት፤ ስለዚህም ፍጹም ያልሆነች ተቋም ናት፤ ይህም ሆኖ ምንጭዋ መለኮታዊ ነው፤ እግዚአብሔርም ይወዳታል፤ እያንዳንዱ አማኝም የእርሷ አካል መሆኑን ተገንዝቦ በውስጧ ስፍራውን በግልጽ ሊይዝና በእርሷ ላይ ያለበትን ኃላፊነት ሊሸከም ይገባዋል።

እውነተኛይቱ ቤተ ክርስቲያን እውነተኛ አማኞችን ሁሉ፣ በእርሱ ላይ ባላቸው ሕያው እምነት ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የተባበሩትን ሁሉ ያቀፈች ናት። በአሁኑ ጊዜ በውጫዊ አደረጃጀቷ ቍጥር ወደሌላቸው ክፍልፋዮችና የአጥቢያ ጉባኤዎች ተከፋፍላለች፤ ይህ ሁሉ መከፋፈል ቢኖርም እውነተኛይቱ ቤተ ክርስቲያን አንዲት ናት። አንድ ጌታ አላት፤ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። አንድ እምነት አላት፤ ይኸውም አዳኝ፣ መለኮታዊ ጌታና ብቸኛ ንጉሥ እንደ ሆነ በእርሱ ማመን ነው፤ አንዲት ጥምቀትም አላት፤ ይኸውም በአንዱ መንፈስ ወደ አንዱ አካል መጠመቅ ነው (ኤፌሶን 4:4-5፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 12:13)። ነገር ግን እያንዳንዱ ክርስቲያን ከሌሎች አማኞች ጋር በግል የሚኖረው ኅብረት ያስፈልገዋል። የዚህ ኅብረት ውጫዊ መገለጫ በተደራጀ የአማኞች ጉባኤ ውስጥ አባል መሆን ነው። በዚህም የሁሉም አብያተ ክርስቲያናት አባላት ከሆኑ አማኞች ሁሉ ጋር ሰፊ ኅብረት ይኖረናል ብለን ተስፋ በማድረግ ከተደራጁ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ርቀን ብንቆም ራሳችንን እናታልላለን። ከአንዲት የአጥቢያ ጉባኤ ጋር በቅርብ ከመተባበር የሚገኘውን ጥቅም እናጣለን። ከየትኛውም የተደራጀ ጉባኤ አባልነት ርቀው የቆሙ ብዙ በጎ ሐሳብ ያላቸውን ሰዎች አውቃለሁ፤ ይህን አድርጎ መንፈሳዊ ሕይወቱ ያልተጐዳበትን አንድም ሰው ከቶ አላውቅም። በበዓለ ኀምሳ ቀን የተለወጡት ሦስት ሺህ ሰዎች ወዲያውኑ ተጠምቀው ወደ ቤተ ክርስቲያን ተጨመሩ (የሐዋርያት ሥራ 2:41፣ 47)፤ «በሐዋርያትም ትምህርትና በኅብረት እንጀራውንም በመቍረስ በየጸሎቱም ይተጉ ነበር።» ልንከተለው የሚገባን የእነርሱን ምሳሌ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስን በእውነት ተቀብለህ ከሆነ፣ ኢየሱስ ክርስቶስን የተቀበሉ ሌሎች ሰዎችን በተቻለ ፍጥነት ፈልገህ አግኝና ከእነርሱ ጋር ተባበር።

በብዙ ስፍራዎች የሚመረጥ ቤተ ክርስቲያን ላይኖር ይችላል፤ ያለችው አንዲት ብቻ ናትና። በሌሎች ስፍራዎች ደግሞ ሰው፦ «ከየትኛው የአማኞች ጉባኤ ጋር ልተባበር?» የሚለው ጥያቄ ይገጥመዋል። ፍጹም ቤተ ክርስቲያን በመፈለግ ጊዜህን አታባክን። ፍጹም ቤተ ክርስቲያን የለችም። ከማንኛዪቱም ጋር ከመተባበርህ በፊት ፍጹም ቤተ ክርስቲያን እስክታገኝ ድረስ ብትጠብቅ፣ ከአንዲቱም ጋር አትተባበርም፤ በዚህም አንተ ብቻ አባል የሆንክባት ቤተ ክርስቲያን አባል ትሆናለህ፤ ያቺም ከሁሉ ይልቅ ፍጹም ያልሆነች ቤተ ክርስቲያን ናት። ከቶ ምንም ቤተ ክርስቲያን አባል ከማልሆን ይልቅ ካወቅኋቸው አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እጅግ ፍጹም ያልሆነችው አባል ብሆን እመርጣለሁ። በጳውሎስ ዘመን የነበሩት የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት እጅግ ፍጹማን ያልሆኑ ተቋማት ነበሩ። ማንም ሰው ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች የተጻፉትን መልእክቶች ያንብብና በቆሮንቶስ የነበረችው ቤተ ክርስቲያን ምን ያህል ፍጹም ያልሆነች እንደ ነበረች፣ በውስጧም ምን ያህል ክፋት እንደ ነበረ ይመልከት፤ ይህም ሆኖ ጳውሎስ በቆሮንቶስ የነበረውን ማንኛውንም አማኝ ከዚህች ፍጹም ካልሆነች ቤተ ክርስቲያን እንዲወጣ ለመምከር ከቶ አላሰበም። ከአረማዊነት እንዲወጡ፣ ከማያምኑ ጋር ካለ ኅብረት እንዲለዩ ነግሮአቸዋል (2ኛ ቆሮንቶስ 6:14-18)፤ በቆሮንቶስ ካለችው ፍጹም ካልሆነች ቤተ ክርስቲያን ስለ መውጣት ግን አንዲት ቃል አልተናገረም። በቆሮንቶስ ያለችው ቤተ ክርስቲያን ሕይወታቸው የተበላሸባቸውን አንዳንድ ሰዎች ከአባልነቷ እንድትለይ ነግሮአታል (1ኛ ቆሮንቶስ 5:11-12)፤ ነገር ግን እነዚያ ሰዎች ገና ከኅብረታቸው ስላልተለዩ በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን የነበሩት አባላት እያንዳንዳቸው ከቤተ ክርስቲያኒቱ እንዲወጡ አልነገራቸውም።

ፍጹም ቤተ ክርስቲያን ልታገኝ ስለማትችል፣ ልታገኝ የምትችለውን እጅግ የተሻለውን ቤተ ክርስቲያን ፈልግ። በመጽሐፍ ቅዱስ ከሚያምኑበትና መጽሐፍ ቅዱስን ከሚሰብኩበት ቤተ ክርስቲያን ጋር ተባበር። መጽሐፍ ቅዱስ ከእግዚአብሔር በራሱ የመጣ የሚታመን መገለጥ፣ ለእምነትና ለኑሮ ሙሉ በሙሉ በቂ የሆነ መመሪያ መሆኑን የምታምንበትን እምነትህን ለመናድ የሚያዘነብሉ ቃላት በግልጽም ይሁን በስውር ከሚነገሩባቸው አብያተ ክርስቲያናት ራቅ። የጸሎት መንፈስ ካለባትና የጸሎት ስብሰባዎች በትጋት ከሚካሄዱባት ቤተ ክርስቲያን ጋር ተባበር። ለጠፉት ሰዎች መዳን እውነተኛና ሕያው ትኩረት ካላት፣ አዳዲስ ክርስቲያኖች ክትትልና እርዳታ ከሚያገኙባት፣ አገልጋዩም ሕዝቡም ለድሆችና ለተጣሉት ፍቅር ካላቸው፣ በዚህ ዓለም ያላት ተልእኮ «የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን» ከመጣው ከክርስቶስ ተልእኮ ጋር አንድ እንደ ሆነ ከምትቈጥር ቤተ ክርስቲያን ጋር ተባበር። በቤተ እምነቶች መካከል ስላለው ልዩነት ደግሞ፣ ሌሎች ነገሮች ሁሉ እኩል ከሆኑ፣ ስለ አስተምህሮ፣ ስለ አስተዳደርና ስለ ሥርዓቶች ያለው አመለካከቱ ለአንተ አመለካከት እጅግ ቅርብ ከሆነው ቤተ እምነት ጋር ተባበር። ነገር ግን ከራስህ ቤተ እምነት ሙት ቤተ ክርስቲያን ጋር ከመተባበር ይልቅ ከሌላ ቤተ እምነት ሕያው ቤተ ክርስቲያን ጋር መተባበር ይሻላል። የምንኖረው በቤተ እምነቶች መካከል ያለው ልዩነት እየቀነሰ በሚሄድበት ዘመን ነው፤ ብዙ ጊዜም ልዩነቶቹ በተግባር ምንም ፋይዳ የላቸውም፤ ሰውም በአቅራቢያው ከሚገኝ የራሱ ቤተ እምነት ቤተ ክርስቲያን ይልቅ በሌላ ቤተ እምነት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ይበልጥ እንደ ቤቱ ሆኖ ሊሰማው ይችላል። ቤተ እምነቶችን የሚለያዩአቸው ነገሮች አንድ ከሚያደርጓቸው ታላላቅና መሠረታውያን እውነቶች፣ ዓላማዎችና እምነት ጋር ሲነጻጸሩ ኢምንት ናቸው።

ከላይ ከተገለጸው ምሳሌ ጋር የምትስማማ ቤተ ክርስቲያን ማግኘት ካልቻልህ፣ ወደ እርሱ እጅግ የምትቀርበውን ቤተ ክርስቲያን ፈልግ። ወደዚያች ቤተ ክርስቲያን ግባ፤ በጸሎትና በሥራ ያቺን ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ልትሆን ይገባታል ብለህ ወደምታስበው ምሳሌ በተቻለህ መጠን ለማቅረብ ሞክር። ነገር ግን ቤተ ክርስቲያንንም ሆነ አገልጋዩን በመንቀፍ ኃይልህን አታባክን። በቤተ ክርስቲያኒቱና በአገልጋዩ ውስጥ መልካም የሆነውን ፈልግ፤ ያንንም ለማጠናከር የምትችለውን ሁሉ አድርግ። ስሕተት ከሆነው ነገር ጩኸት ሳታበዛ ግን በጽናት ራቅ፤ ለማስተካከልም ሞክር። በአንድ ቀን ወይም በአንድ ሳምንት ወይም በአንድ ወር ወይም በአንድ ዓመት ማስተካከል ባትችል ተስፋ አትቍረጥ። ትዕግሥት ያለው ፍቅር፣ ጸሎትና ጥረት ከጊዜ በኋላ ፍሬ ያፈራሉ። ለብቻ ገለል ብሎ መነጫነጭና ማጕረምረም ምንም አይጠቅምም። አንተንም ሆነ የቆምህላቸውን እውነቶች አስጠሊታ ከማድረግ በቀር ሌላ አያደርጉም።


ገጽ 1 / 1 · 4 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል
ቀዳሚ ቀጣይ