ነገዎቼን እርሱ ይይዛል
ኖኅ

ምዕራፍ 9 · 3 ደቂቃ ንባብ

ኖኅ

«ኖኅ ገና ስለማይታየው ነገር ተረድቶ እግዚአብሔርን እየፈራ ቤተ ስዎቹን ለማዳን መርከብን በእምነት አዘጋጀ፥ በዚህም ዓለምን ኰነነ፥ በእምነትም የሚገኘውን ጽድቅ ወራሽ ሆነ» (ዕብራውያን 11:7)።

የኖኅና የመርከቡ ታሪክ በዘፍጥረት 6:5-7:24 ይገኛል። እዚህ በጌታ ፊት ጸጋን ያገኘ ሰው ምሳሌ አለን። እርሱ ጻድቅ፣ በትውልዱም ነቀፋ የሌለበት፣ ከእግዚአብሔርም ጋር የሚሄድ ሰው ነበር (ዘፍጥረት 6:9)።

በዘፍጥረት 6:13 እግዚአብሔር ኖኅን ተናገረው። ጌታ ሲናገርህ ከአንተ የሚፈልገውን ማወቅ አያስቸግርም።

እግዚአብሔርን ማመን አስቸጋሪ አልነበረም፤ ኖኅ ግን ከማመን ያለፈ ነገር አደረገ፤ ታዘዘ፤ እግዚአብሔር ያዘዘውንም ሁሉ አደረገ። እምነት ይህ ነው! በታዛዥ ተግባር የተገለጠ ማመን።

ለኖኅ የተሰጡት መመሪያዎች እጅግ እንግዳ ነበሩ፤ እርሱ ግን ሁሉንም ፈጸመ። የጥፋት ውኃንም ሆነ መርከብን ከዚያ በፊት አይቶ አያውቅም ነበር፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ትእዛዝ ሥራውን ጀመረ፤ ሥራውም እስኪፈጸም ድረስ አላረፈም። በዚህ ግዙፍ ሥራ ኖኅን ስለ ረዳ ስለ ማንም አናነብም፤ ልጆቹ እንኳ እንደ ረዱት አልተጻፈም፤ ነገር ግን እነርሱና ሚስቶቻቸው ከኖኅ መታዘዝ ተጠቃሚዎች ሊሆኑ ነበር። በጠቅላላው ስምንት ሰዎች ሕይወታቸውን ለእግዚአብሔር ጸጋና ለኖኅ መታዘዝ ባለ ዕዳ ይሆኑ ነበር።

ከዚህ የእምነት ምሳሌ ምን መጽሐፍ ቅዱሳዊ መርሕ ልንማር እንችላለን?

አንድ ግልጽ መልስ ራሱ ኢየሱስ በማቴዎስ 24:37-39 ይሰጠናል፤ በዚያም መሲሓዊ መንግሥቱን ለማቋቋም ስለሚመለስበት ጊዜ አይሁድን ያስተምራል።

የኖኅ ዘመን እንደ ነበረ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና። ከጥፋት ውኃ በፊት በነበሩት በእነዚያ ቀናት ኖኅ ወደ መርከብ እስከ ገባበት ቀን ድረስ ይበሉና ይጠጡ፣ ያገቡና ይጋቡ ነበር። የጥፋት ውኃ መጥቶ ሁሉን ጠርጎ እስኪወስዳቸው ድረስ ነገሩን አላስተዋሉም፤ የሰው ልጅ መምጣትም እንዲሁ ይሆናል።

ሰዎች የእግዚአብሔርን ነገር ከቁም ነገር አይቆጥሩም፤ ስለዚህ ታላቅ ፍርድ ይመጣባቸዋል። የሚድኑት ጥቂቶች ብቻ - ቅሬታዎች - ናቸው።

በዚህ ዓለም ላይ የሚመጣው ፍርድ እርግጠኛ ነው የሚለው መርሕ እዚህ አለ፤ ሆኖም ሌላም እውነት ይታያል፦ እግዚአብሔር በልጁ በኢየሱስ በኩል ለእኛ ያዘጋጀው መፍትሔ። ከእርሱ ጋር ለመመላለስ እንቢ በሚሉ ሁሉ ላይ ከሚመጣው ፍርድ የምንድንበትን መንገድ አዘጋጅቷል።

በኢየሱስ መርከብ ተዘጋጅቷል፤ ግብዣውም ሊገባ ለሚፈልግ ሁሉ ተሰጥቷል! ጌታ የጌቴሴማኒን ጭንቀትና በጎልጎታ ኮረብታ ላይ የቆመውን መስቀል ቢያስከፍለውም እንኳ ለአብ ፈቃድ ስለ ታዘዘ እናመሰግነዋለን። ከአብ ጸጋና ከወልድ መታዘዝ የተነሣ የሚገቡ ሁሉ መዳንን ያገኛሉ።

ስምንቱም ሰዎች ወደ ውስጥ በገቡ ጊዜ እግዚአብሔር የኖኅን መርከብ በር እንደ ዘጋ (ዘፍጥረት 7:16)፣ እንዲሁ በልጁ ውስጥ በመንፈስ ቅዱስ «አትሞናል» (ኤፌሶን 1:13)። መርከባችን በሆነው በኢየሱስ ውስጥ ዋስትና ብቻ ሳይሆን፣ በዚያ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ ተባርከናል (ኤፌሶን 1:3)። በእርግጥም ኤፌሶን 1 በሙሉ ስለ እንዲህ ያሉ በረከቶች ይናገራል።

በእርሱ ውስጥ፦ ● ቅዱሳንና ነውር የሌለብን ሆነናል (ቁ. 4)።

● የእግዚአብሔር ልጆች ሆነናል (ቁ. 5)።

● የእግዚአብሔርን የበዛ ጸጋ እንቀበላለን (ቁ. 6)።

● ቤዛነት (ከባርነት መዋጀት) አለን፤ የኃጢአታችንም ይቅርታ አለን (ቁ. 7)።

● እግዚአብሔር የፈቃዱን ምሥጢር ያሳየናል (ቁ. 9)።

● እግዚአብሔር ፍጥረትን ሁሉ አንድ ያደርጋል (ቁ. 10)።

● ለክብሩ ምስጋና እንድንኖር ተሹመናል (ቁ. 11)።

● በመንፈስ ቅዱሱ ታትመናል (ቁ. 13)።

ከዚያም በኤፌሶን 2:6 ጳውሎስ፣ እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባደረገው ቸርነት ወሰን የሌለውን የጸጋውን ባለጠግነት ያሳይ ዘንድ፣ በእርሱ ሆነን በሰማያዊ ስፍራ እንድንቀመጥ ከፍ ከፍ እንደ ተደረግን ይጽፋል።

ዋስትናችን የራሳችንን መርከብ በመሥራት ችሎታችን ወይም በመልካም ሥራዎቻችን ላይ አይደለም። የራሳችን ጽድቅ አይጠቅመንም። በራሳችን ፈጠራም ሆነ ብልሃት ማምለጥ አንችልም፤ ይልቁንም ሁሉ በጸጋ፣ በእምነት ነው። እግዚአብሔር የመዳንን መንገድ አቅዶ አዘጋጅቷል። እንድንገባም ይጋብዘናል። ልናምን እንችላለን፤ ነገር ግን ለግብዣው ካልታዘዝን አንድንም። የሚያድን እምነት የመታዘዝ ምላሽን ይጠይቃል።

በተጨማሪም በኖኅ አቅራቢያ የኖረ ሁሉ ስለሚሠራው ስለዚህ አስደናቂ መርከብ ያውቅ ነበር። ሁሉም የሚሰብከውን ያውቁ ነበር፤ ነገር ግን አንዳቸውም ለግብዣው ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አልነበሩም።

ሰዎቹ በዓይናቸው ፊት ግልጽ የነበረውን ለመቀበል እንቢ በማለታቸው ተኰነኑ። በተመሳሳይም በኢየሱስ የሚገኘው የመዳን የምሥራች ዛሬ ከዓለም የተሰወረ አይደለም፤ ነገር ግን ሰዎች ለግብዣው ምላሽ ላለመስጠት ይመርጣሉ፤ ስለዚህ የቤተ ክርስቲያን መኖር አሁንም ለዓለም ኵነኔ ነው።

ማጠቃለያ የኖኅ ታሪክ እንደ እምነት ምሳሌ የሚከተሉትን መርሖች ያስተምረናል፦ 1. በዓለም ላይ ፍርድ እየመጣ ነው።

2. እግዚአብሔር በጸጋው በልጁ በኢየሱስ የማምለጫ መንገድ አዘጋጅቷል፤ መዳንም በሌላ በማንም የለም።

3. ጸጋ የእግዚአብሔር መሠረታዊ ባሕርይ ነው።

4. መዳን ለእግዚአብሔር ግብዣ የመታዘዝ ምላሽን ይጠይቃል።

የሚያድን እምነት ይህ ነው።

ገጽ 1 / 1 · 3 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል