ምዕራፍ 13 · 5 ደቂቃ ንባብ
አብርሃም ተፈተነ
«አብርሃም በተፈተነ ጊዜ ይስሐቅን በእምነት አቀረበው፤ የተስፋን ቃል የተቀበለው እርሱ፦ ‹በይስሐቅ ዘር ይጠራልሃል› የተባለለትን አንድ ልጁን ሊያቀርብ ተዘጋጀ፤ እግዚአብሔር ከሙታን እንኳ ሊያስነሣው እንዲቻለው አስቦአልና፥ ከዚያም ደግሞ በምሳሌ አገኘው» (ዕብራውያን 11:17-19)።
በዚህ ጊዜ ምሳሌ የሆነው፣ በዘፍጥረት 22 እግዚአብሔር ልጁን ይስሐቅን እንዲሠዋ ባዘዘው ጊዜ አብርሃም ያሳየው መታዘዝ ነው። እግዚአብሔር ተናገረ፤ አብርሃምም ታዘዘ። ስለ ዘሩ የተሰጡትን የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃሎች ያውቅ ነበር፤ ይህም የተስፋ ቃል በይስሐቅ በኩል እንደሚፈጸም ይገምት ነበር፤ ነገር ግን ቃሉ መጣ፤ አብርሃምም ታዘዘ። እምነት ይህ ነው! እግዚአብሔር ይህን አስከፊ ነገር እንዲያደርግ ለምን እንደ ጠየቀው አልገባውም ነበር፤ ቢሆንም እርሱን አልጠየቀውም። ይልቁንም በቀላሉ ታዘዘ።
እግዚአብሔር የተናገረውን ተስፋ እግዚአብሔር ራሱ ሊፈጽመው እንደሚገባ ያውቅ ነበር። እንግዲህ እግዚአብሔር በተስፋው ልጅ በይስሐቅ በኩል የዓለምን አሕዛብ ሁሉ እንደሚባርክ ተስፋ ከሰጠ፣ እርሱም ይስሐቅን የሚገድለው ከሆነ፣ እግዚአብሔር የማይቻለውን ማድረግ — ከሞት ማስነሣት — ግድ ይሆንበታል።
ጳውሎስ በሮሜ 4:3 «አብርሃምም እግዚአብሔርን አመነ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት» ብሎ ያውጃል። ከዚያም ያዕቆብ በመጽሐፉ እንዲህ ሲል ይጽፋል፦ «አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን በመሠዊያው ባቀረበ ጊዜ በሥራ የጸደቀ አልነበረምን? እምነት ከሥራው ጋር አብሮ ያደርግ እንደ ነበረ፥ በሥራም እምነት እንደ ተፈጸመ ትመለከታለህን? መጽሐፍም። አብርሃምም እግዚአብሔርን አመነ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት ያለው ተፈጸመ፤ የእግዚአብሔርም ወዳጅ ተባለ» (ያዕቆብ 2:21-23)። ሐዋርያው በመቀጠል «ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው» ይላል (ያዕቆብ 2:14-16)። በሥራ ካልተገለጠ በቀር እምነት የሚባል ነገር የለም!
በዕብራውያን 11 እንዳሉት ሌሎች ምሳሌዎች ሁሉ፣ እዚህም ስለ እግዚአብሔርና በእኛ ውስጥ ስላለው ዓላማው እውነትን የሚያስተምረን ጥላ አለን። እዚህም እንደ ገና ስለ ትንሣኤና ስለ እግዚአብሔር ታማኝነት ግልጽ ትምህርት አለ። እግዚአብሔር የተስፋ ቃል ሰጥቷል፤ ሊፈጽመውም ይችላል፤ ሆኖም ከእነዚህ ቁጥሮች የምንቃርማቸው ሌሎች እውነቶችም አሉ።
እግዚአብሔር ሕዝቡን የሚፈትንባቸው ጊዜያት ይመጣሉ። ይህን የሚያደርገው ከውጤቱ አንዳች ነገር ለመማር አይደለም፤ ከፈተናው በፊት እንኳ ፍጻሜውን ያውቃልና፤ ደግሞም ወደ ኃጢአት የሚገፋፉ ፈተናዎች እንዲመጡ በመፍቀድ አይፈትነንም። ያ በገዛ ሥጋዊ ምኞታችን ተጠቅሞ ከመንገድ የሚያስተን የሰይጣን ሥራ ነው።
በእርግጥም ኢየሱስ ይህ ከቶ የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዳልሆነ እያወቀ ደቀ መዛሙርቱን «አባታችን ሆይ… ወደ ፈተና አታግባን» (ሉቃስ 11:4) ብለው እንዲጸልዩ አስተማራቸው። መፈተን ግን ፈቃዱ ነው። የሚያነጻን፣ የልጁን የኢየሱስን መልክ ይበልጥ እንድንመስል የሚያደርገንም በመፈተን ነውና።
ማዕድን ንጹሕ ብረት እንዲገኝበት ሲጣራ፣ በእቶንና በመጭመቂያ ወፍጮዎች ውስጥ ከባድ ፈተና ያልፋል። ማዕድኑ ሙሉ በሙሉ እስኪቀልጥ ድረስ ይጋላል፤ ዝገቱም ተገፍፎ ይወገዳል። ምንም ርኩሰት ሳይቀር፣ የቀለጠው ብረት በንጹሕ ብርሃን ያንጸባርቃል፤ ሲፈስስም ፊቱ ፍጹም ምስል ያሳያል። ጌታ የሚፈትነን ለዚህ ነው — ክብሩንና መልኩን እንድናንጸባርቅ።
ለብዙ ዓመታት ተማሪዎቹን በዓመታዊ ፈተናዎችና በየጊዜው በሚሰጡ ምዘናዎች በሚገመግም የትምህርት ሥርዓት ውስጥ መምህር ነበርሁ። እርግጥ ነው፣ ያንን ሥርዓት የወደዱት ተማሪዎች ጥቂቶች ነበሩ፤ ብዙ ወላጆችም ስላማረሩ ዛሬ በትምህርት ቤቶች የሚሰጠው ፈተና በአንጻራዊ ሁኔታ አነስተኛ ነው፤ ተማሪዎችም ያገኙት ዕውቀት ወይም ግንዛቤ ሳይመዘን ብዙ ጊዜ ሊመረቁ ይችላሉ። በፈተናዎች ላይ ከሚቀርቡት ዋና ዋና ቅሬታዎች አንዱ ሁልጊዜ የሚወድቁ ተማሪዎችን ማስከተላቸው ነው።
ከብዙዎች አስተሳሰብ በተቃራኒ፣ መውደቅ ወደ ስኬት የሚያደርስ ጠቃሚ መረማመጃ ድንጋይ ሊሆን ይችላል ብዬ አምናለሁ። ብርታታችን ምን እንደ ሆነ፣ የት የበለጠ ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልገን፣ ኃይላችንንም የት ይበልጥ በብቃት ልናውለው እንደምንችል እንድናውቅ ይረዳናል። በሌላ አነጋገር የፈተናው ውጤት በፊታችን ባለው ጎዳና ላይ ይበልጥ በዘዴ እንድናተኩር ሊረዳን ይችላል። በትምህርት ቤት ሳለሁ ከሕዝብ ፈተናዎቼ አንዳንዶቹን ወድቄ ነበር። ከዚያም ውጤታማ በሆንሁባቸው ትምህርቶች ላይ ለማተኮር መረጥሁ፤ በመጨረሻም በዩኒቨርሲቲ የክብር ዲግሪ ለማግኘት ደረስሁ። በሁለት ትምህርቶች የተወሰነውን የማለፊያ ነጥብ ማለፍ ስላልቻልሁ ብቻ ማንም ሰው ከቶ እንደ ወዳቂ አልቈጠረኝም!
አሁን ያለውን ፈተናውን ባናልፍ እግዚአብሔር ፈጽሞ እንደ ወዳቂ አይቈጥረንም።
በቀደመው ምዕራፍ እንደ ጻፍነው፣ ጌታ በአማኝ ሕይወት ውስጥ እንዲመጡ ከሚፈቅዳቸው ፈተናዎች አንዱ የመሰናከል ፈተና ነው።
ኢየሱስ እነዚህ ግድ እንደሚመጡ ተናገረ፤ ስለዚህ እንዴት መያዝ እንዳለብን ብንማር ይሻለናል (ሉቃስ 17:1)።
ሌላው ፈተና የተዘጋ በር ፈተና ነው። ወደ አንድ ድንቅና አዲስ ዕድል ዘልቄ እንደምገባ ስጠብቅ እግዚአብሔር በፊቴ በሩን ሲዘጋ ያለውን ቅሬታ ቀምሻለሁ። እግዚአብሔር በፊቴ ስላኖረው ስለዚህ ድንቅ ዕድል በነጻነት ተናግሬ ስለ ነበር፣ ጊዜው ሲደርስ እየመራ ከማሳለፍ ይልቅ በሩን መዝጋቱን ሳገኝ ኀፍረቱ እጅግ ጽኑ ነበር። ነገሩ ሳይፈጸም በቀረ ጊዜ እጅግ ሞኝ መስዬ ስለ ተሰማኝ፣ ያን ያህል በነጻነት ባልተናገርሁ ብዬ ምንኛ ተመኘሁ!
እግዚአብሔርን ስለ ምክንያቱ ጠየቅሁት፤ በዚህ ጉዳይ ለፈቃዱ ለመገዛት ጊዜ እንደ ወሰደብኝም መናዘዝ አለብኝ።
ያንን በር ለምን እንደ ዘጋው ለማየት ሌላ 10 ዓመት መጠበቅ ነበረብኝ። ይህን ያደረገው የበለጠ መልካም መንገድ ሊያዘጋጅልኝ ነበር። ይህን ታሪክ በሌላው መጽሐፌ፣ «ስቴፒንግ ስቶንስ» (የመረማመጃ ድንጋዮች) በተባለው፣ በዝርዝር እተርከዋለሁ።
ልንገጥመው የምንችለው ሦስተኛው ፈተና በጌታ እንዳንመራ ሊያሰናክሉን የሚችሉትን ነገሮች የሚመለከት ነው።
እነዚህም የግል ብርታታችንን፣ ግንኙነቶቻችንንና ንብረቶቻችንን ይጨምራሉ። እንደ አብርሃም፣ እጅግ የከበረብንን ነገር እንድንተው ልንጠየቅ እንችላለን። እግዚአብሔር ይህን የሚያደርገው ሊጎዳን አይደለም — ይህ ከቶ ሐሳቡ አይደለም። ይህን የሚያደርገው በገዛ ችሎታችን ላይ ሊኖረን ከሚችለው መታመን ሁሉ ነጻ ሊያወጣን ነው።
ብዙ ጊዜ ንብረቶቻችንን በፊቱ ስናኖር፣ እርሱን ለማገልገል እንድንጠቀምባቸው መልሰን እንድናነሣቸው ይጋብዘናል። ወደ ጌታ በመጣ ጊዜ የሮክ ኤንድ ሮል ባንድ ዋና ዘፋኝ የነበረውን ወዳጄን ሮብን አስባለሁ። መለወጡ እውነተኛ ነበር፤ ብዙም ሳይቆይ በምሽት ክበቦች መዝፈን እርካታ እንደማይሰጠው ተገነዘበ። የሚያውቀው ብቸኛ ሙዚቃ ሊዘምራቸው ለሚፈልጋቸው አዳዲስ መዝሙሮች የማይስማማ ስለ ነበር ጊታሩን አስቀመጠ። ጌታ መሣሪያውን እንደ ገና እንዲያነሣ እንደሚፈልግ ለማመን አራት ዓመት ፈጀበት፤ በዚያን ጊዜም አዳዲስ መዝሙሮችን መዘመር ጀመረ። ዛሬ ሮብ ለጌታ የሙሉ ጊዜ የሙዚቃ አገልግሎት ላይ ነው።
ሙሴ የሥራውና የሥልጣኑ ምልክት የሆነውን የእረኝነት በትሩን መጣል ነበረበት (ዘጸአት 4:3)፤ ከዚያም እንደ ገና እንዲያነሣው ታዘዘ፤ በዚህ ጊዜ ግን «የእግዚአብሔር በትር» ተባለ፤ በእርሱም በቀይ ባሕር መካከል መንገድ እንደ መክፈት ያሉ ታላላቅ ሥራዎችን ሊያደርግ ነበረው (ዘጸአት 4:17)።
እግዚአብሔር በምድያማውያን ላይ ታላቅ ድል እንዲያደርግ ጌዴዎን ሠራዊቱን መተው ነበረበት (መሳፍንት 7)።
ግንኙነቶችን፣ ቤተሰብን ወይም ቤታችንን እንድንተው ልንጠራ እንችላለን። የኢየሱስን የተስፋ ቃል ላስታውስህ፦ «እውነት እላችኋለሁ፥ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ቤትን ወይም ወላጆችን ወይም ወንድሞችን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን የተወ፥ በዚህ ዘመን ብዙ እጥፍ በሚመጣውም ዓለም የዘላለምን ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም» (ሉቃስ 18:29-30)።
የአብርሃምንና የይስሐቅን ታሪክ ባነበብሁ ቁጥር በአባቱ ልብ ውስጥ ከነበረው ሕመም አንዳች ይሰማኛል። በልቡ ያለውን ሐሳብ እያወቀ ልጁን ወደ ተራራው ሲመራው እንዴት ያለ የሥቃይ ጊዜ ሆኖበት ይሆን! እግዚአብሔር እንደ ምንም ፍጻሜውን ይለውጣል በሚለው ተስፋ ገና ተጣብቆ ነበር፤ እንዲያውም በትንቢት መንፈስ «እግዚአብሔር ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን በግ ራሱ ያዘጋጃል» ብሎ ተናገረ (ዘፍጥረት 22:8)።
ይህ ምን ያህል እውነት እንደሚሆን አላወቀም ነበር፤ ከብዙ ምዕተ ዓመታት በኋላ በዚያው ተራራ ላይ ሌላ አባት አንድያ ልጁ ለዓለም ኃጢአት እንደ ታረደ በግ ሆኖ ሲሞት ተመልክቷልና። የሰማዩ አባታችን ልብ እንዴት አዝኖ ይሆን! ቢሆንም ልጁ እንዲሞት ቈርጦ ነበር። ከኃጢአተኛና ከጠፋ ሁኔታችን እንድንቤዥ፣ ፍትሕ ከምሕረት ጋር የሚገናኝበት ብቸኛው መንገድ ይህ ነበር።
ማጠቃለያ እግዚአብሔር አብርሃምን አንድያ ልጁን — የተስፋውን ልጅ — እንዲሠዋ ሲጠይቀው ጨካኝ ወይም ለስሜቱ ግድ የለሽ አልነበረም። ለአገልጋዩ ታላቅ ዕድል ፈንታ ነበረው፤ ነገር ግን አስቀድሞ በእቶን ውስጥ መፈተን አስፈላጊ ነበር። በዚህ የዕብራውያን 11 ክፍል የሚከተሉት መርሖች ተገልጠዋል፦ 1. በፈተና ጊዜያችን እግዚአብሔር ታማኝ ነው።
2. እግዚአብሔር አንድን ነገር በመሥዋዕትነት እንድናኖር ሲጠራን፣ ይህ በኃይል መልሰን እንድናነሣው ነው።
3. እግዚአብሔር ፈተና በሕይወታችን እንዲመጣ የሚፈቅደው ሊያነጻን ብቻ ነው።
4. የቤዛነት ዕቅዱ «በግ ራሱ ማዘጋጀት» ነው።
ምዕራፍ 13 ተጠናቋል
አብርሃም ተፈተነ