ምዕራፍ 6 · 2 ደቂቃ ንባብ · 2 ደቂቃ ማዳመጥ
መደምደሚያ
የመጽሐፉ መደምደሚያ
1. በሕይወቴ ካጋጠሙኝ ፈተናዎች ሁሉ የእግዚአብሔርን መኖርና የወንጌሉን እውነትነት መጠራጠር እጅግ የከፋውና ለመሸከምም እጅግ የከበደው ነው፤ ይህ ፈተና በመጣ ጊዜ መታጠቂያዬን ከእኔ ይወስዳል፤ መሠረቶቹንም ከበታቼ ያነሣል። ኦ! «ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁ» የሚለውን ቃል፣ ደግሞም «መሠረቶች በፈረሱ ጊዜ ጻድቅ ምን ያደርጋል?» የሚለውን ብዙ ጊዜ አስቤአለሁ።
2. አንዳንድ ጊዜ ኃጢአት ከሠራሁ በኋላ ከእግዚአብሔር እጅ ጽኑ ቅጣትን ስጠባበቅ፣ ከእርሱ ያገኘሁት ቀጣዩ ነገር የጸጋው መገለጥ ሆኖአል። አንዳንድ ጊዜ በተጽናናሁ ጊዜ በመከራ ውስጥ እንዲህ በመስጠሜ ራሴን ሞኝ ብዬ ጠርቻለሁ። ደግሞም በተዋረድሁ ጊዜ ለመጽናናት እንዲህ ያለ ስፍራ በመስጠቴ ጠቢብ እንዳልነበርሁ አሰብሁ። ሁለቱም በእንዲህ ያለ ኃይልና ክብደት በላዬ ነበሩ።
3. በዚህ በአንድ ነገር እጅግ ተደንቄአለሁ፤ እግዚአብሔር እጅግ በተባረከ የራሱ መገለጥ ነፍሴን ቢጐበኛትም፣ ከዚያ በኋላ እንደ ገና በመንፈሴ በጨለማ እጅግ ተሞልቼ ያደሰኝ ያ አምላክና ያ መጽናናት ምን እንደ ነበረ አንድ ጊዜ እንኳ ማሰብ እስከማልችል ድረስ እንዲህ ያሉ ሰዓታት እንደ ተከተሉኝ አግኝቻለሁ።
4. አንዳንድ ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ በአንዲት መስመር ውስጥ ልሸከመው ከምችለው በላይ አይቻለሁ፤ በሌላ ጊዜ ግን መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉ እንደ ደረቅ እንጨት ሆኖብኛል፤ ይልቁንም ሁሉንም ገልጬ ብመለከትም ከእርሱ ትንሽ ቅንጣት ያህል መታደስ እንኳ ማግኘት እስከማልችል ድረስ ልቤ ለእርሱ የሞተና የደረቀ ሆኖአል።
5. ከእንባዎች ሁሉ በክርስቶስ ደም የሚፈልቁት እጅግ የሚበልጡ ናቸው፤ ከደስታዎችም ሁሉ በክርስቶስ ላይ ከሚደረግ ልቅሶ ጋር የተደባለቀው እጅግ ጣፋጭ ነው። ኦ! ክርስቶስን በክንዳችን ይዘን በእግዚአብሔር ፊት መንበርከክ እንዴት ያለ መልካም ነገር ነው! ስለ እነዚህ ነገሮች አንዳች እንደማውቅ ተስፋ አደርጋለሁ።
6. እስከ ዛሬ ድረስ በልቤ ውስጥ ሰባት አስጸያፊ ነገሮችን አገኛለሁ፦ (1) ወደ አለማመን ማዘንበል። (2) ክርስቶስ የሚገልጠውን ፍቅርና ምሕረት ፈጥኖ መርሳት። (3) ወደ ሕግ ሥራ ማዘንበል። (4) በጸሎት መቅበዝበዝና መቀዝቀዝ። (5) የምጸልይለትን ነገር በትጋት መጠባበቅን መርሳት። (6) ተጨማሪ ስለሌለኝ ለማጕረምረም መቸኰል፣ ያለኝን ግን አላግባብ ለመጠቀም መዘጋጀት። (7) እግዚአብሔር ካዘዘኝ ነገሮች አንዱንም ሳደርግ ርኵሰቶቼ ራሳቸውን ጣልቃ ሳያስገቡ አይቀሩም፤ «መልካሙን አደርግ ዘንድ ስወድ በእኔ ክፉ እንዲያድርብኝ…»።
7. እነዚህን ነገሮች ዘወትር አያቸዋለሁ፤ ይሰማኛልም፤ በእነርሱም እጨነቃለሁ፤ እጨቈናለሁም፤ ቢሆንም የእግዚአብሔር ጥበብ ለበጎዬ ያዘጋጃቸዋል። (1) ራሴን እንድጸየፍ ያደርጉኛል። (2) በልቤ ከመታመን ይጠብቁኛል። (3) በውስጣችን ያለ ጽድቅ ሁሉ በቂ እንዳልሆነ ያሳምኑኛል። (4) ወደ ኢየሱስ መሸሽ አስፈላጊ እንደ ሆነ ያሳዩኛል። (5) ወደ እግዚአብሔር እንድጸልይ ያስገድዱኛል። (6) መትጋትና በመጠን መኖር እንደሚያስፈልገኝ ያሳዩኛል። (7) ደግሞም እንዲረዳኝና በዚህ ዓለም እንዲያሻግረኝ በክርስቶስ በኩል ወደ እግዚአብሔር እንድመለከት ያነሣሡኛል። አሜን።
ምዕራፍ 6 ተጠናቋል
መደምደሚያ