ምዕራፍ 8 · 14 ደቂቃ ንባብ
ኃይል የሚያደርግ ጸሎት ቅድመ ሁኔታዎች
«በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ የምትወዱትን ሁሉ ለምኑ ይሆንላችሁማል።» (ዮሐንስ 15:7) «ስለዚህ እላችኋለሁ፥ የጸለያችሁትን የለመናችሁትንም ሁሉ እንዳገኛችሁት እመኑ፥ ይሆንላችሁማል።» (ማርቆስ 11:24) «ከእናንተ ግን ማንም ጥበብ ቢጎድለው፥ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፥ ለእርሱም ይሰጠዋል። ነገር ግን በምንም ሳይጠራጠር በእምነት ይለምን፤ የሚጠራጠር ሰው በነፋስ የተገፋና የተነቃነቀ የባሕርን ማዕበል ይመስላልና። ያ ሰው ከጌታ ዘንድ አንዳች እንዲቀበል አይምሰለው።» (ያዕቆብ 1:5-7) «እንዲሁም ደግሞ መንፈስ ድካማችንን ያግዛል፤ እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና፥ ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል፤
ልብንም የሚመረምረው የመንፈስ አሳብ ምን እንደ ሆነ ያውቃል፥ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ቅዱሳን ይማልዳልና።» (ሮሜ 8:26-27) ጥቅሶቹን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተቀመጡበት ቅደም ተከተል አልወሰድኋቸውም፤ ይልቁንም አንዱ ሌላውን በሚከተልበትና ርዕሱንም በሚያብራሩበት አመክንዮአዊ ቅደም ተከተል ነው ያቀረብኋቸው።
አሁንም በምሰጠው በዚህ አጭር ንግግር ውስጥ በዚህ ጉዳይ ላይ ለደረሱኝ ደብዳቤዎች መልስ ለማካተት እሞክራለሁ። ምናልባት በዚህ ዘመን ከዚህ የበለጠ የተለመደ ተሞክሮ የለም፤ ክርስቲያን ነን ባዮች ዘወትር የሚነግሩኝም ከዚህ የበለጠ ነገር የለም፦ «እንግዲህ ለተወሰኑ ነገሮች ብዙ ጊዜ ጸልያለሁ፤ ነገር ግን ለጸሎቴ መልስ የማገኝ አይመስለኝም።» እንዲህ ያሉ ሰዎች ጸሎትን ፈጽሞ አለመተዋቸው ብዙ ጊዜ ይገርመኛል። እኔ ምንም መልስ ባላገኝ ኖሮ እተወው የነበረ ይመስለኛል።
እንግዲህ እላለሁ፤ ይህ እግዚአብሔርን እጅግ የሚያዋርድ ተሞክሮ ነው፤ ነገሩ እንዲህ ከሆነም አንድ ቦታ የተሳሳተ ነገር መኖር አለበት። ስሕተቱ ወይ በሚጸልዩት ሰዎች ወይ በሰጪው ላይ መሆን አለበት። ወይ! ክርስቲያኖች ብዙ ጊዜ እንደሚያደርጉት በመላው አገር ተሰብስበው ለመነቃቃት ሲጸልዩ፣ በአብያተ ክርስቲያናቸውና በቤተሰቦቻቸው ውስጥ ለአንድ ለተወሰነ ነገር ሲጸልዩ፣ ነገሩም ፈጽሞ ሳይመጣ ሲቀር፣ ይህ እግዚአብሔርን ምን ያህል እጅግ የሚያዋርድ ነገር እንደ ሆነ ብዙ ጊዜ ይሰማኛል።
ከጥቂት ዓመታት በፊት የመነቃቃት ማዕበል አየርላንድንና አሜሪካን በጠራረገ ጊዜ፣ በዚህ አገር ያሉ አብያተ ክርስቲያናት መነቃቃቱ ወደ እንግሊዝ እንዲመጣ ለመጸለይ የጋራ የጸሎት ስብሰባዎች እንዳደረጉ ታውቃላችሁ፤ ነገር ግን አልመጣም፤ ተጠራጣሪዎችም ራሳቸውን እየነቀነቁ በጋዜጦቻቸው እንዲህ ብለው ጻፉ፦ «እዩ፤ የክርስቲያኖች አምላክ ወይ ደንቁሯል ወይ አደን ሄዷል፤ ለመነቃቃት በአገሩ ሁሉ የጸሎት ስብሰባ አድርገዋል፤ መነቃቃቱ ግን አልመጣም።» ወይ! ይህን ሳስብ ጉንጮቼ በኀፍረት እንዴት ይግሉ ነበር! እንዴትስ አዘንሁበት! ይህ የሆነው አምላካችን ስለ ተኛ እንዳልሆነ አውቅ ነበር—ኃይሉ ውሱን ስለ ሆነ አይደለም—የርኅራኄ ልቡ ለኃጢአተኞች ስለማይናፍቅ አይደለም—መንፈሱን አፍስሶ በሌሎች ስፍራዎች የነበረውን ያን የከበረ የመታደስ ዘመን ሊሰጠን ስለማይችል አይደለም። ምክንያቱ ያ አልነበረም። ምክንያቱ አንድ ብቻ ነበር፤ እርሱም ሕዝቡ በክፉ መለመናቸው ነበር።
የኃይለኛውንና የሚያሸንፈውን ጸሎት ቅድመ ሁኔታዎች አልተረዱም። አልፈጸሟቸውምም።
እስከ ዛሬ ድረስ ቢጸልዩና ያንኑ አቋም ይዘው ቢቀጥሉ ኖሮ እንኳ መልሱን ባላገኙ ነበር፤ ምክንያቱም እንደ ሌሎቹ ተስፋዎች ሁሉ ለእነዚህም ተስፋዎች ቅድመ ሁኔታዎች አሉ፤ ቅድመ ሁኔታዎቹን ካልፈጸምን ፊታችን እስኪጠቁር ድረስ ብንጸልይ እንኳ ከንቱ ነው። እግዚአብሔር እኛን ለመገናኘት አንዲት ስንዝር እንኳ አይንቀሳቀስም፤ ተስፋዎቹንም በሕይወታችን ፈጽሞ አይፈጽምም። እናንተ ስለሚጠፋው ዓለም ያለባችሁን ኃላፊነትና ግዴታ ለመገንዘብ የነቃችሁ ሆይ፣ ቃሌን አስተውሉ፤ የምለውንም ወደ ቤታችሁ ይዛችሁ ሂዱ—አስቡበት፣ ጸልዩበት፣ ለእናንተ የተላከ የጌታ መልእክት መሆኑን ለመገንዘብ ሞክሩ።
እነዚህ ስለ ጸሎት ከተሰጡት የከበሩ ተስፋዎች እጅግ ጥቂቱ ብቻ ናቸው። እግዚአብሔር የሕዝቡን የታመነ ጸሎት ለመመለስ ራሱን ያሰረባቸው እንደነዚህ ያሉ ብዙ ተስፋዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አሉ።
«የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች።» — ያዕቆብ 5:16 እንግዲህ አብዛኞቹ ክርስቲያን ነን ባዮች ለጸሎታቸው መልስ የማያገኙት ለምንድን ነው? በመጀመሪያ ደረጃ፣ እግዚአብሔር ተስፋዎቹን የሰጠው ለአንድ ዓይነት ባሕርይ ላላቸው ሰዎች ነው፤ እነርሱ ግን ያ ባሕርይ የላቸውም። እነዚህ ተስፋዎች የተሰጡት ለእግዚአብሔር ቅዱሳን ነው—ትእዛዛቱን ለሚጠብቁ፣ በብርሃን ለሚመላለሱና በመንፈስ ቅዱስ በኩል ከእርሱ ጋር ኅብረት ላላቸው ነው፤ ስለዚህም መንፈስ ስለ እነርሱ ሊማልድ ይችላል። መንፈስ በውስጡ በሌለበት ሰው፣ ስለዚያ ሰው እንዴት ሊማልድ ይችላል? በብርሃን የሚመላለሱ ሰዎች ምን ዓይነት ልመና እንደሚያቀርቡ፣ መቼ እንደሚያቀርቡትና እንዴት እንደሚያቀርቡት ማየት ይችላሉ፤ በብርሃን ውስጥ ስለ ሆኑ ሁሉንም ያያሉ። እንዲህ ያሉ ሰዎች ይለምናሉ፣ ይቀበላሉም። ነገር ግን ወዮ! የእግዚአብሔር ባሕርይ በየቀኑ የሚዛባው፣ ተጠራጣሪዎችም በእኛና በአምላካችን የሚሥቁት እንደነዚህ ያሉት ሰዎች እጅግ ጥቂቶች በመሆናቸው ነው።
እንግዲህ ይህን ቸል ለማለት ወይም ከእናንተ ለመግፋት አትሞክሩ። እነዚህ ተስፋዎች የተሰጡት ለማን ነው? ከዐውዱ ጋር ተያይዞ ሲታይ ከቅዱሳን በቀር ለሌላ የተሰጠ ተስፋ በዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ፈልጎ እንዲያሳየኝ ማንንም እሞግታለሁ (ንስሐ ከሚገቡ ኃጢአተኞች በቀር፤ እነርሱ ልዩ ወገን ናቸው፤ ልዩ ተስፋዎችም ተሰጥተዋቸዋል)።
ከእነዚህ ዓይነት ሰዎች በቀር ለሌላ ለጸሎት መልስ የሚሰጥ ተስፋ የለም። እነዚህ ተስፋዎች ለሰው ሁሉ የተሰጡ አይደሉም፤ አይደል? የኀጥኣን ጸሎት በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ነው፤ ከክፋታቸው ለመመለስ የሚጸልዩት ጸሎት ብቻ ሲቀር። ያን ጊዜ ያ ጸሎት አስጸያፊ አይደለም፤ ሌላው የኀጥኣን ጸሎት ሁሉ ግን አስጸያፊ ነው። እነዚህ ተስፋዎች የተሰጡት ለጻድቃን ነው—ማለትም፦ በመጀመሪያ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት ላላቸው ሰዎች። «በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ»—በሕያው እምነት ወደ ሕያው ኅብረት ከገቡ በኋላ ተስፋዎቹ የተሰጡት ያንን አንድነት ጠብቀው ለሚኖሩ ሰዎች ነው—በእርሱ ለሚመላለሱ፣ በእርሱ ለሚኖሩ፣ ኢየሱስ በዚያ አንድነት ምክንያት የሰጣቸውን ዕድሎችና መብቶች ለሚጠቀሙባቸው ነው።
እንግዲህ ወዳጆች ሆይ፣ ለጸሎታችሁ መልስ ለማግኘት በአንድ ወቅት ከኢየሱስ ጋር አንድ መሆናችሁ ብቻ በቂ እንዳልሆነ ታያላችሁ። ወደ ኋላ ያፈገፈጉ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች እንዳሉ እፈራለሁ። የእምነትን መያዣ ለቀዋል፤ በክርስቶስ አይኖሩም፤ ከእርሱ ውጭ ይኖራሉ፤ ሆኖም ሁልጊዜ ይጸልያሉ፤ እግዚአብሔር ጸሎታቸውን ለምን እንደማይመልስም ይገረማሉ። አታዩምን? የመጀመሪያው ቅድመ ሁኔታ ጐድሏል። ከወልድ በቀር ወደ አብ የሚቀርቡበት ምንም መንገድ የለም። በልጁ በኩልና በልጁ ውስጥ ሆነው ወደ እርሱ የማይወጡ ጸሎቶች ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ናቸው፤ ስለ ክርስቶስ ፈጽሞ ሰምቶ እንደማያውቀው እንደ ቆርኔሌዎስ ያሉት ብቻ ሲቀሩ፤ ነገር ግን ብርሃንን አግኝተው ልጁን ላወቁ ሰዎች ከልጁ ጋር ካለው ሕያው አንድነት ውጭ ሆነው የሚያቀርቡት ጸሎት ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም። ይህም ማለት «ስለ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ብለህ» ብሎ መናገር ብቻ አይደለም። ሰዎች በአፋቸው የሚሉት ብዙም ቁም ነገር አይደለም።
እግዚአብሔር የሰዎችን ቃል ከቶ አይመለከትም፤ እርሱ የሚመለከተው የሚያስቡትንና የሚሰማቸውን ነው፤ ሰዎች ጸሎታቸውን በእውነት ከልጁ ጋር በአንድነት ሆነው ሲያቀርቡም ያውቃል። እነዚህ ሰዎች ግን በአንድነቱ ውስጥ አይደሉም፤ ስለዚህም ጸሎታቸው ከሚጸልዩበት ክፍል በላይ ከፍ ብሎ አያውቅም።
ከአፋቸው እንኳ ለመውጣት ይቸገራሉ፤ እግዚአብሔር ፈጽሞ አይሰማቸውም። በገዛ ጉሮሯቸው ውስጥ ሰጥመው ይቀበራሉ።
ወይ! እናንተ አዲስ አማኞች፣ ከኢየሱስ ጋር ካላችሁ ሕያው አንድነት ፈጽሞ አትውጡ። በእርሱ ጽኑ—አጥብቃችሁ ያዙት—በእርሱ ተመላለሱ፤ በየቀኑም ለጸሎታችሁ መልስ ታገኛላችሁ። እግዚአብሔር የምትለምኑትን ሲያደርግ እንዳያችሁትና ሲናገራችሁ እንደ ሰማችሁት ያህል እርግጠኞች ትሆናላችሁ። «ሁልጊዜም እንድትሰማኝ አወቅሁ» ለማለት ትችላላችሁ። ስሙ ይባረክ! በእርሱ የሚኖሩ ሰዎች በልካቸው ይህን ማለት ይችላሉ።
የሚያሸንፍ ጸሎት ቀጣዩ ቅድመ ሁኔታ ለብርሃን መታዘዝ ነው። እንግዲህ በመታዘዝ መመላለስ ማለት ምን ማለት ነው? ከእግዚአብሔር ጸጋ ምን ያህል ትንሹ ወደ መንግሥተ ሰማያት እንደሚያስገባችሁ ለማወቅ ይህን አዲስ ኪዳን መመርመር ማለት አይደለም! ከጥቅሱ እውነተኛና ተግባራዊ ትርጉም ለማምለጥ ብቻ ይህ ሰው ስለ ጥቅሱ ምን ይላል፣ ያ ሰው ምን ይላል እያሉ መሯሯጥ አይደለም! እንዲህ ያሉ ሰዎች ማንም ይሁኑ ማን በልባቸው ግብዞች ናቸው—ቢያንስ ቅንነት የጐደላቸው ናቸው። የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማወቅ አይፈልጉም፤ ባያውቁት ይመርጣሉ። ከጥቅሱ ግልጽ፣ ተግባራዊና ቀላል ትርጉም ለመሸሽ ይፈልጋሉ፤ ከዚያም «የሚለውን ቃል በቃል ማለቱ አይደለም»፣ «እንዲህ ወይም እንዲያ ተብሎ መተርጎም አለበት» ይላሉ፤ በልባቸው ከዳተኞች ሆነው ሳሉ ራሳቸውን ያረጋጋሉ፣ ተመችቶ እንዲሰማቸውም ይጥራሉ። ይህ በብርሃን መመላለስ አይደለም።
በብርሃን መመላለስ በፀሐይ ብርሃን እንደ መሄድ ነው—ከብርሃኑ ለመሸሽ ወደዚያ ምሰሶ ጀርባ፣ ወደዚያኛውም ዛፍ ጀርባ መሮጥ አይደለም። በግልጽ ወጥቶ እንዲህ ማለት ነው፦ «አሁን ጌታ ኢየሱስ ሆይ፣ ፈቃድህን ማወቅ እፈልጋለሁ። ጌታ ሆይ፣ ብርሃንህን በእኔ ላይ አፍስስ። ወደ መግደያው ወይም በእሳት ወደ መቃጠል ቢመራኝ እንኳ ልከተለው ተዘጋጅቻለሁ።»
በመጀመሪያ ብርሃንን ለማግኘት ተመኙ። ወይ! እርሱን እንወደዋለን በሚሉ ሰዎች እርሱ እንዲህ መዛባቱና መሰደቡ—የሚሳሳቱት ብርሃን ስለ ጐደላቸው ነው ለማለት መሞከራቸው—ሳስበው ልቤን ያሳምመዋል፤ ለእግዚአብሔር ክብር በመቅናት በጽድቅ ቍጣ ይፈላል ልል ነበር። ከቶ እንዲህ አይደለም። እዚህ ብዙ ብርሃን አለ፤ ነገር ግን እንዲህ ማለት አለባችሁ፦ «አዎን ጌታ ሆይ፣ ቢፈርድብኝ እንኳ ብርሃኑን ለመቀበል ፈቃደኛ ነኝ። በልቤ፣ በአእምሮዬ ላይ ቢፈርድ፣ ጌታ ሆይ፣ በላዬ አፍስሰው።
በሕይወቴ ላይ ቢፈርድ፣ በላዬ አፍስሰው። በእነዚያ ባልንጀሮች፣ በእነዚያ ፈንጠዝያዎች ላይ ቢፈርድ፣ በላዬ አፍስሰው፤ እተዋቸዋለሁ። በንግዴ ላይ ቢፈርድ፣ በላዬ አፍስሰው፤ ያንን ንግድ እተወዋለሁ፤ በእርሱ ከመቀጠል ይልቅ በድኽነት መሞትን እመርጣለሁ። ከቤተሰቤ ጋር ባለኝ ግንኙነት ላይ ቢፈርድ፣ ከእነርሱ ተለይቼ እከተልሃለሁ።»
ጌታ እንደዚህ ላለች ነፍስ ሁልጊዜ ይመልሳል። ጣቱን በዚህኛውና በዚያኛው ቍስል ላይ ያኖራል፤ ምን ማድረግ እንዳለባችሁም ይነግራችኋል፤ በሚሰማ ድምፁ እንደ ሰማችሁት ያህል እርግጠኞች ትሆናላችሁ። በብርሃን መመላለስ ማለት ምን ማለት ነው? ድምፁን መታዘዝ ነው። ከሰው አመክንዮ ጋር ለመከራከር አትቁሙ፤ ነገር ግን ጳውሎስ እንዳደረገው ተነሥታችሁ ጌታችሁ ያዘዛችሁን ሩጫ ለመጀመር ተጓዙ። ጳውሎስ ከሥጋና ከደም ጋር ለመማከር አልቆመም። ምን እንደሚያስከፍለው ለማስላት አልቆመም፤ ነገር ግን ወደ ፊት ገፋ፤ እስከ መጨረሻውም እስኪደርስ ድረስ ከቶ አልቆመም። በብርሃን መመላለስ ይህ ነው—መታዘዝ ነው—በዚያ ቆሞ ስለ ነገሩ ከጌታ ጋር መከራከር አይደለም፤ «ወይ! ግን...» ማለት አይደለም—ይልቁንም ማድረግ ነው።
ወይ! ወዳጆች ሆይ፣ ማንም ሌላ ወንጌል ቢሰብክላችሁ፣ ማንም በሌላ ቅድመ ሁኔታ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ልታገኙ ወይም ቅዱሳን ልትሆኑ ትችላላችሁ የሚል ትምህርት ይዞ ቢመጣ—ስለ ክርስቶስ ብላችሁና ስለ ነፍሳችሁ ብላችሁ አትመኑት። ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ እንዳለ፦ «ማንም ወደ እናንተ ቢመጣ ይህንም ትምህርት ባያመጣ በቤታችሁ አትቀበሉት ሰላምም አትበሉት፤» — 2ኛ ዮሐንስ 1:10 «ነገር ግን ይህ እኮ እጅግ ውድ መሥዋዕት ነው» ትላላችሁ። በአንድ በኩል ልክ ነው፤ ነገር ግን ዋጋውን ከከፈላችሁ በኋላ፣ መሥዋዕቱን ካቀረባችሁ በኋላ፣ ወደ መንገዱም ከገባችሁ በኋላ፣ ደስታው፣ ብርሃኑ፣ ኃይሉና ክብሩ መቶ እጥፍ ይበልጣል። ዋጋዋ እጅግ የበዛውን ዕንቁ ያገኘ ማንም ሰው፣ ያለውን ሁሉ ቢሰጥ እንኳ፣ ለእርሷ ከመጠን በላይ እንደ ከፈለ የተሰማው አለን?
ከቶ የለም! ሰማዕታትና ምስክሮች በማሰቃያው መሣሪያ ላይና በእሳት ነበልባል ውስጥ እየተሠቃዩ እርሷን በመያዛቸው ተመኩ፤ ማንም የእግዚአብሔር ሰው—ወንድም ይሁን ሴት—ለእርሷ ከመጠን በላይ ዋጋ እንደ ከፈለ አስቦ ነበር የሚል አንድም ምስክርነት ሰምታችሁ አታውቁም። ከቶ አልሰማችሁም! ጸሎታችሁ እንዲመለስላችሁ ትፈልጋላችሁ? መንገዱ ይህ ነው። የገዛ ልባችሁ እንዳይፈርድባችሁ ሆናችሁ ተመላለሱ። ከወላጁ ጋር በፍቅርና በስምምነት የሚኖር የሚታዘዝ ልጅ ወደ ወላጁ ቀርቦ ውለታ ለመለመን አይፈራም። እንደሚያገኘው ያውቃል። የገዛ ልቡ አይፈርድበትም።
«ወዳጆች ሆይ፥ ልባችንስ ባይፈርድብን በእግዚአብሔር ዘንድ ድፍረት አለን፤» — 1ኛ ዮሐንስ 3:21 ድፍረትንና መታዘዝን ሊለያይ የሚችል ካለ ይሞክር ብዬ ማንንም እሞግታለሁ። ካልታዘዛችሁ ድፍረት ሊኖራችሁ አይችልም። የገዛ ልቡ እየፈረደበት ለማንኛውም በረከት በእምነት ወደ እግዚአብሔር ዙፋን መቅረብ እንደሚችል እንዲነግረኝ እዚህ ያለውን ማንኛውንም ክርስቲያን እሞግታለሁ። እንደማይችል ያውቃል። ለማንኛውም በረከት እምነትን ከመለማመዱ በፊት አስቀድሞ ያ የፍርድ ሁኔታ ከእርሱ መወገድ አለበት።
በብርሃን ተመላለሱ፤ ያን ጊዜ ከእርሱ ጋር ኅብረት ይኖራችኋል፤ ደሙም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻችኋል፤ መንፈስም እንዴት እንድትጸልዩና ስለ ምን እንድትጸልዩ ያስተምራችኋል፤ ይህንን ደግሞ አብዛኞቹ ክርስቲያን ነን ባዮች ፈጽሞ አያውቁትም።
በተጨማሪም የመንፈስ ቅዱስ መምራት፣ ማስተማርና ማነሣሣት ኃይል የሚያደርግ ጸሎት ቀጣዩ ቅድመ ሁኔታ ነው። እነዚህን ቅድመ ሁኔታዎች ነፍሳችንን ከራሱ ከእግዚአብሔር ልብ ጋር የሚያገናኙ አራት ቀለበቶች ያሉት ሰንሰለት ልንላቸው እንችላለን። አንደኛ፣ ከኢየሱስ ጋር ኅብረት፤ ሁለተኛ፣ ለትእዛዛቱ መታዘዝ፣ ማለትም በብርሃን መመላለስ፤ ሦስተኛ፣ በውስጥ የሚኖረው መንፈስ ምልጃ፤ አራተኛም፣ እምነትን መለማመድ። ከእነዚህ ቀለበቶች አንዱ ቢጐድላችሁ ጸሎታችሁ ይበላሻል። የቀሩት ሦስቱ ሁሉ ሊኖሯችሁ ይችላሉ፤ ነገር ግን አንዱ ቢጐድል መልስ አታገኙም። ግንኙነቱን ይቆርጣል፤ ምላሽም አይኖርም።
ብዙ ክርስቲያን ነን ባዮች የምልጃ መንፈስ ምን ማለት እንደ ሆነ አያውቁም ብዬ እፈራለሁ። መንፈስ በማይነገር መቃተት ስለ እነርሱ እንደሚማልድ ምንም አያውቁም። ይህ የምልጃ ጸሎት መንፈስ በወላጆች ውስጥ ሲበዛ ብዙ መንፈሳዊ ልጆች ሲወለዱ እናያለን። እንግዲህ መንፈስ ቅዱስ እዚህ ላይ መንፈስ ካላስተማረን በቀር እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን እንደማናውቅ ይናገራል፤ ስለዚህም ያዕቆብ እንደሚለው ሰዎች ዘወትር ይለምናሉ፣ አይቀበሉምም፤ በክፉ ይለምናሉና።
«ትለምናላችሁ፥ በምቾቶቻችሁም ትከፍሉ ዘንድ በክፉ ትለምናላችሁና አትቀበሉም።»
— ያዕቆብ 4:3 ይህም በምድር አድማስ የተወሰኑትን ምድራዊ ምኞቶቻችሁን፣ ፍቅራችሁንና ዓላማዎቻችሁን ማለት ነው።
እንግዲህ በሺህ የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች እየጸለዩ መልስ ፈጽሞ የማያገኙበት ዋናው ምክንያት ይህ ነው ብዬ አምናለሁ።
በጸሎታቸው ራስ ወዳዶች ናቸው፤ ምድራውያን ናቸው፤ ለምድራዊ ምኞታቸው፣ ፍቅራቸውና ለተፈጥሮ ዝንባሌያቸው ያውሉት ዘንድ በክፉ ይለምናሉ። እናቶች ለልጆቻቸው ለዓመታት እንደ ጸለዩና ከልጆቻቸው አንዱ እንኳ ወደ ጌታ እንዳልተመለሰ ይነግሩኛል።
እኔም «ይበልጥ የሚያሳዝን ነው፤ ይበልጥም ለእናንተ ኀፍረት ነው» እላለሁ። ለምን? ምክንያቱም ጸሎታቸው ራስ ወዳድነት ያለበትና በደመ ነፍስ ብቻ የሚቀርብ ጸሎት ነበርና፤ የጸለዩት ልጆቻቸው ስለ ሆኑ፣ ወይም በኃጢአት እንዳይወድቁና በቤተሰቡ ላይ ውርደት ወይም መከራ እንዳያመጡ ሃይማኖተኞች እንዲሆኑላቸው ስለ ፈለጉ፣ ወይም ሃይማኖተኞች ቢሆኑ ደስ የሚል ስለ ሆነ ነው። ነገር ግን እጅግ ጻድቃን እንዲሆኑ አይፈልጉም፤ የዚህን ዓለም ከንቱነትና ሞኝነት እስኪቆርጡና ራሳቸውን ፈጽመው ለክርስቶስ እስኪሰጡ ድረስ ለእግዚአብሔር ራሳቸውን እንዲሰጡ አይፈልጉም—ያ ከልክ ያለፈ ነው፤ ለራሳቸው መጽናኛ እንዲሆኑላቸው የሚበቃ ያህል ሃይማኖት ብቻ እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ። እናንተ እግዚአብሔር ብትሆኑ እንዲህ ያለውን ጸሎት ትመልሱ ነበርን? ዓላማቸው ቢመረመር፣ በየቀኑ ከሚቀርቡ ጸሎቶች በመቶዎችና በሺዎች የሚቆጠሩት ከዚህ ያልጠለቁና ከዚህ ከፍ ያላሉ ናቸው—መንፈስ ቅዱስም በእርግጥ ይመረምራቸዋል።
ብዙ ሚስቶችም ለባሎቻቸው በዚሁ መንገድ ይጸልያሉ ብዬ እፈራለሁ። ባሎቻቸው ለእግዚአብሔር ሳይታዘዙ እየኖሩ፣ ጊዜያቸውን፣ ችሎታቸውንና ገንዘባቸውን እያባከኑ፣ ለኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥት ሊያደርጉ የሚችሉትን ከእርሷ እየዘረፉ መሆናቸው አያስጨንቃቸውም። እጅግ የሚያሠቃያቸው ሐሳብ፣ ባሎቻቸው ሃይማኖተኞች ቢሆኑ በቤት ብዙ ጊዜ እንደሚያሳልፉ፣ አሁን ገንዘቡን ለልጆች ከማጠራቀም ይልቅ እንደሚያባክኑት፣ ሃይማኖተኞች ቢሆኑ ግን ይህ ሁሉ እንደሚስተካከል ነው። እንግዲህ እላለሁ፤ እግዚአብሔር የዚያችን ሚስት ለባሏ የምታቀርበውን ጸሎት ፈጽሞ አይመልስም! ባላችሁ ለእግዚአብሔር ምን ሊሆን እንደሚችል—ለእግዚአብሔር መንግሥት ምን ሊያደርግ እንደሚችል—ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እርሱ ደሙን እንዴት እንዳፈሰሰ—የኃጢአት ሕይወት እግዚአብሔርን ምን ያህል እንደሚያዋርድ ማሰብ አለባችሁ፤ ልባችሁ ሊሰበር እስኪደርስ ድረስ በዚህ ላይ ማሰላሰል አለባችሁ፤ ከጸሎታችሁም ጋር በጥበብ ብትሠሩ ባላችሁ በቅርቡ ወደ ጌታ ይመለሳል።
እግዚአብሔር ራስ ወዳድነትን ይጠላል—ራስ ወዳድነት ጠላቱ ነው፤ የዚያው ጠላት ሕያው መልክ ነው። ከራሳችሁ መውጣት አለባችሁ፤ ልጃችሁን ሁልጊዜ የእግዚአብሔር እንደ ሆነ፣ በኢየሱስ ክቡር ደም የተዋጀች ክብርት ነፍስ እንዳለችው፣ እርሱን የሚያከብርበትና መንግሥቱን የሚያስፋፋበት ችሎታና ብቃት እንዳለው አድርጋችሁ ማየት አለባችሁ፤ ጸሎታችሁንም በዚያ ላይ መሠረት አድርጋችሁ እንዲህ ማለት አለባችሁ፦ «አንተን እያዋረዱ ከሚያድጉ ይልቅ ሺህ ጊዜ በመቃብር ባኖራቸው—ድኾችና የተናቁ ቢሆኑ—እመርጣለሁ።» ያን ጊዜ ጸሎታችሁ ይመለስላችኋል!
ሰዎች ስለ ንግዳቸው ይጸልያሉ። እግዚአብሔር ግን ያንን ሰው ለማጥፋት መንገዱ እንዲሳካለት መፍቀድ እንደ ሆነ ያያል። ሥራውን ወደ ፊት ለማስኬድ ገንዘብ አያስፈልገውም። ብልጽግና ነፍሳቸውን እንደ በሽታ እንደሚበላ እግዚአብሔር ያያል፤ ስለዚህም እንዲሳካላቸው አይፈቅድም። የእግዚአብሔር መንፈስ ነፍስን ወደ ራስ ወዳድ ጸሎት ከቶ አይመራም። አይደለም፤ ሰዎች ሕጉን ስለማይጠብቁ እንድታለቅስ፣ ስለ ራሷ ጉዳይ ይልቅ ስለ እርሱ ጉዳይ አብልጣ እንድትጮኽ ይመራታል። የእግዚአብሔርን መንግሥት መስፋፋት የሚያግዝ ከሆነ የገዛ ቤቷ ባዶ ሆኖ እንዲቀር ፈቃደኛ ናት። በዚህም የእግዚአብሔርን መሠዊያ መሙላትና ማክበር ከቻለች፣ ድንቢጥ በገዛ መሠዊያዋ ላይ ቤትን እንድታገኝ ፈቃደኛ ናት።
ከዚያም የመጨረሻው ቀለበት ይመጣል—እምነት። ሌላም ምሥጢር ይኸውና። መንፈስ ቅዱስ ወዳልመራው ነገር ማንም አማኝ እምነትን ሊለማመድ አይችልም። ደጋግማችሁ ልትጸልዩ ትችላላችሁ፤ ነገር ግን መንፈስ በውስጣችሁ እስኪማልድ ድረስ እምነትን ፈጽሞ አትለማመዱም። ሦስቱን ቀዳሚ እርምጃዎች ለወሰዱ ሰዎች ማመን ብዙም አያስቸግርም።
ከኢየሱስ ጋር ኅብረት ያላቸው፣ በብርሃን የሚመላለሱ፣ መንፈስ ቅዱስ የሚማልድ መንፈስ ሆኖ በውስጣቸው ያለ—እነርሱ ስለ ምን እንደሚጸልዩ ያውቃሉ፤ የመንፈስ አሳብ ምን እንደ ሆነ ያውቃሉ፤ መንፈስ እንዴት እንደሚመራቸው ያውቃሉ፤ ወደ ዙፋኑም በድፍረት ቀርበው «ለምኑ ትቀበሉማላችሁ» እንደ ተባለው ሊለምኑና ሊቀበሉ ይችላሉ። ልመናቸው እንደ እግዚአብሔር አሳብ እንደ ሆነ ያውቃሉ፤ እምነታቸውን ሊፈትን ቢወድድ፣ አስፈላጊ ከሆነ እንደ ሲሮፊኒቃዊቱ ሴት ሊታገሉ ይችላሉ። እርሱ ሁልጊዜ ወዲያውኑ አይመልስም። በማይነገር መቃተት እንዲታገሉ ይተዋቸዋል፤ ነገር ግን መንፈስ ስለ እነርሱ እንደሚማልድ ያውቃሉ፤ አንዳንድ ጊዜም በታላቅ ተስፋ መቍረጥና ፈተና መካከል መልሱ እስኪመጣ ድረስ አጥብቀው ይይዛሉ። «አዎን፣ ይሆናል» የሚለውን የእምነት ማረጋገጫ ያገኛሉ። ሰዎች በመደነቅ ያዩዋቸዋል። ክርስቲያን ወዳጆቻቸው የሚጸልዩለት ነገር እንዳልመጣ ያውቃሉና «ነገሩን ያገኘኸው ያህል ደስ ብሎሃል» ይላሉ፤ «መያዣውን ተቀብያለሁ፤ እንደሚመጣ አውቃለሁ፤ እንደሚሆን ማረጋገጫ አለኝ።» አሁን እያንዳንዱ የሚጸልይ ወላጅ ለእያንዳንዱ ልጁ ይህ እስኪገኝ ድረስ ሊታገል ይገባዋል። እስከዚያ ድረስ ፈጽሞ ማቆም የለባችሁም፤ ከዚያም ከመጸለይ ጋር ደግሞ አሠልጥኑ—ከእግዚአብሔር ጋር አብራችሁ ሥሩ፤ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ የመንግሥቱ ሕግ ይህ ነው። እንዳገኛችሁት እመኑ፥ ይሆንላችሁማል።
ወይ! በዚያች ነጥብ ላይ ምስኪን ነፍሳትን በመርዳት ረገድ ምን ያህል መደናገርና መምታታት አለ! ሰዎች «እንደ ዳንህ እመን፤ ድነሃልም» ይላሉ። ክርስቲያኖች ይህን ምክር ለነፍሳት ሲሰጡ ብዙ ጊዜ ሰምቻለሁ። «እንደ ዳንህ እመን፤ ድነሃልም።» ውሸትን እመን፤ እውነትም ይሆናል ማለት ነው። ይህ የእግዚአብሔር ፍልስፍና ነውን? አንድን ሰው ገና ሳይድን እንደ ዳነ እንዲያምን መንገር ምን ጥቅም አለው?
ይህ ውሸትን እንዲያምን መንገር ነው። ሰዎች «እንደ ተቀደስህ እመን፤ ተቀድሰሃልም» ይላሉ።
እንዲያ ነው? መቼ ተቀደስህ? እግዚአብሔር አንድ ነገር ሳይሆን ሰውን እንዲያምነው ከቶ አይነግረውም። የስጦታውን መሰጠት ከእምነት መለማመድ ጋር በአንድ ጊዜ እንዲሆን አድርጎታል። እንዳገኛችሁት እመኑ፥ ይሆንላችሁማል—ይህም ከአንድ ሰዓት በፊት እንደ ተቀበላችሁ ማለት አይደለም፤ ያ እውነት አይሆንምና፤ ከአንድ ሰዓት በኋላ እንደምትቀበሉ ማለትም አይደለም፤ ያ መዳፈር ይሆናልና። እንዲህ ያለ ተስፋ የለም፤ ነገር ግን አሁን በዚህች ቅጽበት እንደምትቀበሉ እመኑ፤ ይሆንላችሁማል። «እስከዚህ ድረስ ሊታመንብኝ የሚደፍረውን ሰው ከቶ አላሳፍረውም።» ያገኙታል። የተአምራት ዘመን አልፏል ትላላችሁ።
አዎን፣ ምክንያቱም የዚያ ዓይነት እምነት ዘመን ስላለፈ ነው። ያ ዓይነት እምነት ሲመለስ ተአምራትም ይመለሳሉ። እግዚአብሔር ራሱን ከእውነተኛ ሕዝቡ እምነት ጋር አስሯል፤ የጸጋን ሕጎች ከሚሰብር ይልቅ የተፈጥሮን ሕጎች ሁሉ ቢሰብር ይመርጣል። የተፈጥሮን ሕግ በቀላሉ ወደ ጎን ሊያደርግ ይችላል፤ የጸጋን ሕግ ግን ከቶ ወደ ጎን አያደርግም። ራሱን ከእምነት ጋር አስሯል—በዓለም ሁሉ ራሱን ያሰረበት ብቸኛው ኃይል እርሱ ነው—እስከ ዛሬም በዚህ ዓለም ተነሥቶ «በእግዚአብሔር ታመንሁ፤ እርሱም አታለለኝ» ያለ ማንም የለም።
እምነት መታመን ማለት ነው—እምነት ራስን ፈጽሞ አሳልፎ መስጠት ማለት ነው—ልክ እየሞታችሁ እንዳላችሁና ከእግዚአብሔር ተስፋ ብቻ በቀር ምንም እንደ ሌላችሁ። «እየሞትሁ ነው፤ አሁን መታመን አለብኝ» ትላላችሁ፤ ያ ሰውም ራሱን በተስፋው ላይ ይጥላል። መሞከራቸውን ትተው በእውነት ይታመናሉ፤ በዓይኖቻቸውም ውስጥ ብርሃን ሲገባ አይታችኋል፤ የምስጋና መዝሙር ከከንፈሮቻቸው ሲፈነዳ ሰምታችኋል፤ እንደ ተቀበሉ አምነዋልና፤ ተቀብለዋልምና።
እንግዲህ ከጻፋችሁልኝ መካከል አንዳንዶቻችሁ ከኢየሱስ ጋር በኅብረት እንደምትኖሩ ታውቃላችሁ።
አንዳንዶቻችሁ በቅርቡ በብርሃን መመላለስ ጀምራችኋል። ጣዖታቱን ቆርጣችሁ አስወግዳችኋል፤ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር ፈቃድ ፈጽማችሁ ሰጥታችኋል፤ በጸጋውም እስከ መጨረሻ እንደምትከተሉት ቃል ገብታችኋል። መንፈስ ቅዱስ በውስጣችሁ እንዳለ በእርግጥ ይሰማችኋል። ወይ! ፈጽማችሁ እንድትታዘዙ፣ መንፈስ እንደ ፈቃዱ እንዲሠራ እንድትፈቅዱ እለምናችኋለሁ። አትከልክሉት። ሰውነታችሁን የሚጐዳ አይምሰላችሁ፤ ከልክ ያለፈ አይምሰላችሁ፤ አክራሪዎች እየሆናችሁ ያላችሁ አይምሰላችሁ፤ ለነገሩ እግዚአብሔር እንዲህ ያለውን ነገር አይፈልግም ብላችሁ አታስቡ—መንፈስን ተከተሉ። መንፈስ ይምራችሁ፤ በእናንተም ውስጥ ይቃትት፤ መንፈስ በእናንተ በኩል ከእግዚአብሔር ጋር ይታገል—ተከተሉት። በእነዚህ ስብሰባዎች ውስጥ ይህ ቢበዛልን ኖሮ ብዙ ፍሬ ባገኘን ነበር፤ ቤተ ክርስቲያንም ይህ ቢበዛላት ኖሮ ወደ መንግሥቱ የሚወለዱ ነፍሳት በበዙ ነበር።
በወጣትነቴ ዘመን የእግዚአብሔርን መንፈስ ካሳዘንሁባቸው ነገሮች አንዱ፣ እርሱ ሊያደርገኝ በሚወድደው መጠን የጸሎት ሴት እንዲያደርገኝ አለመፍቀዴ ነበር፤ ሆኖም ከብዙዎች ጋር ስነጻጸር ምናልባት የጸሎት ሴት ነበርሁ። ከመጸለይ ልቆጠብ እስከማልችል ድረስ የተወሰኑ ሰዎችንና ጉዳዮችን በልቤ ላይ ያኖር ነበር፤ ነገር ግን ወይ! በዚህ ረገድ መንገዱን ሁሉ በእኔ ላይ እንዲያደርግ ባለመፍቀዴ እንዴት መራራ ጸጸት ተጸጽቼ በጌታ ፊት አለቀስሁ! ተጠንቀቁ! እናንተም እርሱ መምራት የጀመረባችሁ ሰዎች፣ ይምራችሁ። ነፍሳችሁን ስለ ሌሎችና ከሌሎች ጋር አፍስሱ። ከንግግር ይልቅ በእውነተኛ ጸሎት ጊዜ ብዙ ነፍሳት ስለ ኃጢአታቸው እንደሚወቀሱ አምናለሁ።
ይህን ብዙ ጊዜ አስተውያለሁ። በአንድ ትልቅ አዳራሽ ወይም ቲያትር ቤት ጀርባ፣ ወይም በላይኛው ሰገነት ላይ፣ ሊታሰቡ ከሚችሉት እጅግ ሻካራ የሆኑ ብዙ ሰዎች እጅግ ባልተገባ ሁኔታ ሲረብሹ የጸሎት ኃይል ሲገታቸው አይቻለሁ። ምናልባት ሁከቱ ወደ ግልጽ ረብሻ ሊገነፍል በተቃረበ ጊዜ አንዲት ትንሽ ሴት እጆቿን በጉባኤው ላይ ዘርግታ «እንግዲህ እንጸልይ» ብላለች፤ እኔም የሰዎቹ ብዛት ሁሉ ጸጥታንና አክብሮትን ሲላበስ አይቻለሁ። የጉባኤውን ፊት ተመልክቻለሁ፤ ትልልቅ፣ ሻካራ፣ ፊታቸው በጥቀርሻ የጠቆረ ሰዎች ራሳቸውን ዝቅ ሲያደርጉ፣ አንዳንዴም ዓይናቸውን ሲጠርጉ አይቻለሁ፤ ለመዘመር በተነሣን ጊዜም ከዚያ በኋላ ምንም ሥርዓት የለሽ ድርጊት አልነበረም፤ ይልቁንም እንደ ሞት በሚያህል ጽሞና ተረጋግተው ለመስማት ተቀመጡ። በዚያ ጸሎት ጊዜ በመቶዎች የሚቆጠሩት ስለ ኃጢአታቸው ተወቀሱ። በወቀሳ የመታቸው በዚያች ሴት ልብ ውስጥ ስለ እነዚያ ነፍሳት የሚታገለው መንፈስ ቅዱስ ነበር።
ጸሎት የነፍስ ጭንቀት ነው—የመንፈስ ትግል ነው። ወንዶችና ሴቶች አንድ ነገር እንዲደረግ በጽኑ ቍርጠኝነት ሲፈልጉ እርስ በርሳቸው እንዴት እንደሚነጋገሩ ታውቃላችሁ። ለሰዎችም ይሁን ለእግዚአብሔር፣ ጸሎት ያ ነው፤ ልባችሁ ስለ ነፍሳት በመንፈስ ቅዱስ ሲነካ፣ ሲቀልጥ፣ ሲነሣሣና ሸክም ሲጫንበት ኃይል ይኖራችኋል፤ በጸለያችሁ ቍጥርም አንድ ሰው ስለ ኃጢአቱ ይወቀሳል—የአንዲት ምስኪን ነፍስ የጨለሙ ዓይኖች ይከፈታሉ፤ መንፈሳዊ ሕይወትም ይጀምራል።
ምዕራፍ 8 ተጠናቋል
ኃይል የሚያደርግ ጸሎት ቅድመ ሁኔታዎች