ምዕራፍ 10 · 16 ደቂቃ ንባብ
ለእግዚአብሔር በስኬት እንዴት መሥራት ይቻላል
«ልጄ ሆይ፥ ዛሬ ሂድና በወይኔ አትክልት ሥራ።» ማቴዎስ 21:28 «ቤቴ እንዲሞላ ወደ መንገድና ወደ ቅጥር ውጣና ይገቡ ዘንድ ግድ በላቸው።» ሉቃስ 14:23 ለስኬታማ አገልግሎት ስለሚያስፈልጉ አንዳንድ ብቃቶች እናገራለሁ፤ እንዲህም እላለሁ፦ በመጀመሪያ፣ በተፈጥሮ መንግሥት እንዳሉ ሁሉ በጸጋ መንግሥትም ስኬትን የሚገዙ የተወሰኑ ሕጎች አሉ፤ እናንተም እነዚህን ሕጎች ማጥናትና ራሳችሁን ከእነርሱ ጋር ማስማማት ይገባችኋል። ገበሬ ዘሩን ባልታረሰ መሬት ወይም ሌላ ነገር በያዘው አፈር ላይ ቢበትን ከንቱ ድካም ነው። ማረስ፣ ማለስለስ፣ ዘሩንም በጥንቃቄ፣ በተገቢው መጠንና በትክክለኛው ጊዜ መዝራት አለባችሁ፤ ከዚያም ውኃ ማጠጣት፣ አረም መንቀልና መከሩን መጠበቅ ይኖርባችኋል። በመለኮታዊ ነገሮችም እንዲሁ ነው። ኦ! የመንፈሳዊው መንግሥት ሕጎች በአሠራራቸው ልክ እንደ ተፈጥሮው መንግሥት ሕጎች እርግጠኞችና የማይሳሳቱ እንደ ሆኑ፣ ምናልባትም ከእነርሱ እጅግ እንደሚበልጡ ውሎ አድሮ እናውቃለን፤ ነገር ግን ከልባችን ዕውርነት፣ ድንዛዜና አለማመን የተነሣ ልናውቃቸው አልቻልንም፣ ወይም አልፈለግንም። ሰዎች ተነሥተው ወዲያ ወዲህ ይሯሯጣሉ፤ ያለ ምንም አሳብ፣ ጥንቃቄ ወይም ድካም ለእግዚአብሔር መሥራት እንደሚችሉ ይጠብቃሉ። ምድራዊ ሙያን ለመማር የዓመታት ድካምና አሳብ ይሰጣሉ፤ ለእግዚአብሔር በሚሠሩት ሥራ ግን ማሰብና ማሰላሰል፣ ማቀድና መሞከር፣ መንገዶችን መፈተን፣ ጥበብን ለማግኘትም መጸለይና ከእግዚአብሔር ጋር መታገል ልፋቱ የሚገባው ነገር አይመስላቸውም። ኦ! አይደለም፤ ራሳቸውን ማድከም አይፈልጉም። ከዚያም ይወድቃሉ፣ ተስፋ ይቆርጣሉ፣ ትተውትም ይሄዳሉ።
እንግዲህ ወዳጆቼ ሆይ፥ ለእግዚአብሔር መሥራት የሚጀመረው በዚህ መንገድ አይደለም። የፈለጋችሁትን ያህል ቶሎ ጀምሩ—አሁኑኑ ጀምሩ—ነገር ግን በትክክለኛው መንገድ ጀምሩ። እንዴት እንደምትሠሩ እንዲያሳያችሁና ለሥራውም እንዲያስታጥቃችሁ አብዝታችሁ በመጸለይ ጀምሩ፤ በትሑት፣ በታዛዥና ለመማር በተዘጋጀ መንፈስም ጀምሩ።
አዲስ ኪዳንን ይህንኑ በማሰብ አጥኑት፤ እያንዳንዱ ገጹ የሚጨምርላችሁ ብርሃን ያስደንቃችኋል። እግዚአብሔር ለሰጣችሁ ለእያንዳንዱ ችሎታና ተጽዕኖ ፍጹም ተጠያቂዎች እንደሚያደርጋችሁ፣ እያንዳንዷን የጊዜያችሁን ቅጽበት፣ እያንዳንዱን የማንነታችሁን ችሎታ፣ እያንዳንዷን የተጽዕኖአችሁን ቅንጣት፣ እያንዳንዷንም የገንዘባችሁን ሳንቲም ለእርሱ እንድታበለጽጉ እንደሚጠብቅባችሁ ታያላችሁ።
ይህ ብርሃን አንድ ጊዜ ከበራላችሁ በቀሩት የሕይወታችሁ ጉዳዮችና ዘርፎች ሁሉ ድንቅ መሪ ይሆናችኋል። ዕቅዶቻችሁን አጥኑ። በምድራዊ ጦርነት ሰዎች የውጊያ ስልቶችን እንዴት ያጠናሉ! ጠላትንም በድንገት ይይዙት ዘንድ ልዩ ልዩ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ! ነገር ግን ወዮ! የእግዚአብሔር ሕዝብ ነፍሳትን ለመማረክ የሚሰጠው ጥንቃቄና ትኩረት ምንኛ ጥቂት ነው! ይሁን እንጂ ከተሞችን ከመያዝ ይልቅ ነፍሳትን መማረክ እጅግ የከበደ ሥራ ነው።
አንድን ሥራ ለመሥራት የተሻለው መንገድ የትኛው እንደ ሆነ ምናልባት በሕይወታቸው አንድ ሰዓት እንኳ ሳያቋርጡ አስበው የማያውቁ ሰዎች የሚያሳዩት ድፍረት ብዙ ጊዜ አስገርሞኛል፤ ከእግዚአብሔር ሠራተኞች እጅግ ስኬታማ በሆኑት አንዳንዶቹ ሕይወት ውስጥ ተሞክረው ፍሬያማ ስለ ሆኑ ዘዴዎችና መንገዶች ወዲያውኑ ፍርድ ይሰጣሉ። «ኦ! እኔ በዚህ አላምንም» ይላሉ። «ኦ! ይህ ሁሉ ከንቱ ነው፣ የሚያስቅ ነው፣ ስሕተት ነው!» ይላሉ፤ የሚኰንኗቸው ሰዎች ግን ምናልባት ለክርስቶስ ነፍሳትን የሚማርኩበትን የተሻለ መንገድ ለማግኘት ሲማልዱ፣ ሲያለቅሱ፣ ሲያጠኑ፣ ሲሞክሩና የልባቸውን ደም እስከ መሠዋት ሲደርሱ ቆይተው ይሆናል።
በአንድ ትልቅ የክርስቲያኖች ስብሰባ ላይ የደረሰብኝን ድንጋጤ ፈጽሞ አልረሳውም። በአንጻራዊነት ታዋቂ ቦታ የነበራቸው አንድ ጨዋ ሰው መዝሙር እያስጀመሩ ነበር፤ መዝሙሩም ከኢየሱስ ጋር አንድ ሰዓት ስለ መትጋት የሚናገር ስንኝ ነበረው። በመዝሙሩ መካከል ቆም ብለው እንዲህ የሚል ቃል ተናገሩ፦ «እዚህ ላይ በእውነት በደለኞች እንደ ሆንን እፈራለሁ። በሕይወቴ ከኢየሱስ ጋር አንድ ሰዓት ሳላቋርጥ ተግቼ እንደማውቅ ለመናገር እደፍራለሁ ብዬ አላስብም።» ፈጽሞ አልረሳውም። ጉንጮቼ በኀፍረት ነደዱ። «ኦ! አምላኬ ሆይ፥ መሪዎቹ እነዚህ ከሆኑ ሕዝቡ ቢሆን አያስደንቅም» አልሁ።
እንደዚያ ያለ ቦታ የያዘ ሰው ይህን ለመናገር ይደፍራል! ጌታ ይማረው። የጌታ ሥራ እንዲህ ባለ ዝብርቅርቅ መንገድ ቢሠራ አያስደንቅም! እላችኋለሁ፥ ነፍሳትን በመማረክ ስኬታማ መሆን የሚፈልጉ ቀናትን ብቻ ሳይሆን ሌሊቶችንም ጭምር መትጋት ያስፈልጋቸዋል። መንፈስ ቅዱስን አብዝተው ይሻሉ፤ ዛሬም ቢሆን «ይህ ወገን በጸሎትና በጦም ካልሆነ በምንም ሊወጣ አይችልም» የሚለው እውነት ነውና።
በዚህ ዘመን ከጌታችን ይልቅ ጠቢባን ሆነናል፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ መንገዱ ያው የጥንቱ መንገድ ነው፤ በአደባባይም ሆነ በግል በነፍሳት ላይ የሕይወትን ውኃ ማፍሰስ ከፈለጋችሁ እናንተ ራሳችሁ ከምንጩ አብዝታችሁ መጠጣትና ለማፍሰስ ዝግጁ ሆኖ እንዲገኝ ማድረግ ይኖርባችኋል! ይህ ከሌላችሁ ንግግራችሁ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሽዋሽዋ ጸናጽል ይሆናል። ኦ! በዚህችው የክርስቲያኖች ሰንበት የሚባክነውን የተሳሳተ አቅጣጫ የያዘ ጥረት ሳስብ ነፍሴ የደም እንባ ታነባለች። ድካሙ ብዙ ነው፤ ፍሬው ግን ምንኛ ጥቂት ነው?—ይህ ሁሉ የሆነው አሳብ፣ ጸሎትና ለነፍሳት መዳን ብቻ ያተኰረ ቅን ዓይን ስለ ጐደለው ስለ ታሰረ፣ ስለ ተበላሸና አቅጣጫ ስለ ሳተ ነው። እግዚአብሔር ለዚህ ያንቃን፤ ይህንንም እናደርግ ዘንድ ለማሰብ፣ ለመድከም፣ ለመማር፣ ለመታገልና ለመሠዋት ፈቃደኞች ያድርገን።
ቀጥሎም፣ ለስኬታማ አገልግሎት ሁለተኛው ብቃት እውነትን ወደ ልብ ዘልቆ እንዲገባ የማድረግ ኃይል ነው።
እውነትን ማድረስ አይደለም! ይህ ቃል ከክርስቲያናዊ ሥራ ጋር ተያይዞ ባይፈጠር ኖሮ ምንኛ ደስ ባለኝ።
«ማድረስ» ብሎ ነገር—ይህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የለም! የለም፣ የለም፤ ማድረስ አይደለም፤ ይልቁንም ወደ ውስጥ ሰንቅሩት—አስገቡት—እንዲሰማ አድርጉት። ሥራችሁ ይህ ነው፤—መናገር ብቻ አይደለም—በለሆሳስና በቀስታ በሕዝቡ ፊት ማኖርም አይደለም። ራሱን በሚበላ፣ ስለ ነፍሳት ሸክም በተሸከመ፣ በመንፈስ ቅዱስ በሚመራ ስኬታማ አገልግሎትና፣ እንደ ትምህርት ቤት ትምህርት ነገሩን አውርዶ ወደ ቤቱ በሚሄድና ለሚከተለው ውጤት በምንም መንገድ ራሱን ተጠያቂ በማያደርግ ግድ የለሽ፣ ነገሩን እንደ ዋዛ የሚያልፍ፣ ቀላል ዓይነት ነገር መካከል ያለው ልዩነት ይህ ነው። በአደባባይም ሆነ በግል ሥራ ልዩነቱ ሁሉ ይኸው ነው። እግዚአብሔር ተጠያቂ ያደረጋችሁ እውነትን ስለ ማድረስ ሳይሆን ወደ ውስጥ ስለ ማስገባት ነው—ልብ ድረስ ስለ ማድረስ፣ በሕሊና ውስጥ እንደ ግለት ብረት፣ ከዙፋኑ በቀጥታ እንደ ተወረወረ መብረቅ ስለ መትከል ነው፤ ይህንንም ለማድረግ የሚያስችለውን ኃይል በእጃችሁ አኑሯል፤ ባታደርጉት ግን ደም በልብሳችሁ ላይ ይሆናል! ኦ! ይህ የጨዋነት የሚመስል እውነትን የማቅረብ ዘዴ! እግዚአብሔር እንዴት ይጠላዋል! «ውድ ወዳጆች፥ ፈቃዳችሁ ቢሆን ታደምጣላችሁ? ፈቃዳችሁ ቢሆን ትለወጣላችሁ? ወደ ኢየሱስ ትመጣላችሁ? ወይስ ይህንንና ያንን ብቻ እናንብብ?»—ይህ ከሐዋርያት ስብከት ጋር ያለው መመሳሰል ጨለማ ከብርሃን ጋር ካለው መመሳሰል አይበልጥም።
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ «ሂዱና አድርጉት፤ ይገቡ ዘንድ ግድ በላቸው። ሥራችሁ ይህ ነው። ሕጋዊ እስከ ሆኑ ድረስ በምትጠቀሙባቸው ዘዴዎች ጉዳዬ አይደለም።»
«በማንኛውም ሰብዓዊ ዕቅድ ላይ ቆርጣችሁ ብትነሡ የምታሳዩትን ያንኑ ትጋት፣ ቅንዓትና ቁርጠኝነት አሳዩ፤ እስከ ዓለም ፍጻሜም ከእናንተ ጋር እንደ ምሆን ሁልጊዜ እርግጠኞች ሁኑ።
በሥራዬ ላይ ተሰማርታችሁ ሳላችሁ መገኘቴን ፈጽሞ አትጠራጠሩ። ከእናንተ ጋር እሆናለሁ፤ ሥራችሁንም አከናውናለሁ።» አድርጉት—ጌታ እውነትን ወደ ልብ እንድናደርስ ይርዳን!
የጳውሎስ መንገድ ይህ ነበር፤ የኢየሱስም መንገድ ይህ ነበር። ጳውሎስ፦ «እንግዲህ የጌታን ፍርሃት አውቀን ሰዎችን እናስረዳለን» ይላል። ኦ! ይህ ስለ አገልግሎት ምንኛ የሚያምር ማስተዋል ይሰጠናል!
ጳውሎስ ሆይ፥ ሰዎችን የምታስረዳው ለምንድን ነው? «እየመጣ ያለውን የጌታን ፍርሃት ስለማውቅ ነው፤ ደግሞም አንዱ ስለ ሁሉ ሞተ፤ እንግዲያስ ሁሉ ሞቱ ብለን ስለ ቆረጥን ነው። ስለዚህ ሰዎችን አስረዳለሁ።» በፊታቸው ነገሩን ካኖረ በኋላ ተስፋ ቆርጦ አልተወም።
በልቡ ተሸክሟቸው ነበር፤ «ሦስት ዓመት ሌሊትና ቀን በእንባ እያንዳንዳችሁን ከመገሠጽ እንዳላቋረጥሁ» ይላል። በአመክንዮው፣ በአንደበተ ርቱዕነቱና በውስጡ ባለው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ወደ ውስጥ እንደ ሰነቀረው ሁሉ በእንባውም አስገባው። ወደ ውስጥ እንዲገባ አድርጉት—ቃላችሁ እንዲሰማ አድርጉ፤ ምንም ስሜት በማይፈጥር በዚያ በደከመና በተዳከመ አነጋገር አታናግሯቸው—እንዲያውቁት አድርጉ። ለዚህ የሚበቃ መንፈስ ቅዱስ ከሌላችሁ እስኪኖራችሁ ድረስ ወደ እልፍኛችሁ ግቡ፤ ከዚያም መጥታችሁ ቃሉን ነፍስንና መንፈስን እስኪለይ ድረስ እንደሚወጋ ሁለት አፍ ያለው ሰይፍ ወደ ሕሊናቸው ሰንቅሩት።
ለስኬት የግድ አስፈላጊ የሆነው ሁለተኛው ነገር ቀላልነት ነው፤—እውነትን በተፈጥሮአዊ መንገድ ማቅረብ።
እውነትን ወደ ልብ ማድረስ ብቻ ሳይሆን ይህን ለማድረግ በቀላሉና በተፈጥሮአዊ መንገድ ልትሰጧቸው ይገባል። ከቅኖችና ከእውነተኞች ሰዎች አፍ በሚወጣበት ጊዜ እንኳ ለመለኮታዊው እውነት ስኬት ትልቁ እንቅፋት ነው የምለውን በአንድ ቃል እንዳስቀምጥ ብጠየቅ ድርቀት እላለሁ። ሰዎች ወደ ሃይማኖት በመጡበት ቅጽበት ልዩ የድምፅ ቃና፣ ልዩ ገጽታና ልዩ ጠባይ የሚይዙ ይመስላሉ—ባጭሩ ተፈጥሮአዊነታቸውን ያጣሉ።
አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ወደ እኔ መጥተው፦ «ኦ! ተፈጥሮአዊ ለመሆን ዓለምን ሁሉ በሰጠሁ ነበር፤ ነገር ግን ሰዎችን በዚህ መንገድ የማናገር ልማድ ውስጥ ገብቻለሁ። ተፈጥሮአዊ መሆን የማልችል ይመስለኛል። ልትረጂኝ ትችያለሽ?» ይሉኛል። እኔም፦ «አዎን፥ በዚህ ምክር ልረዳህ እችላለሁ—በእግዚአብሔር እርዳታ የዚህን ባርነት አንገት ለመስበር ቁረጥ። እንዴት እንደምትጀምር እነግርሃለሁ። በቤተ ሰብህ ጀምር። ስለ ምድራዊ ነገሮች በሚደረግ ጭውውት መካከል ድንገት አቋርጠህ ስለ ነፍሳቸው ወይም ስለ ራስህ ተሞክሮ መናገር ጀምር፤ ወይም በጉልበትህ ተንበርክከህ መጸለይ ጀምር» እላለሁ። «ኦ! ግን ይህ እንዴት ያለ መቋረጥ ይሆናል!» ከአባታችሁ ጋር መነጋገር መቋረጥ ሊሆን አይገባም። በዚያ መንፈስ ውስጥ ካላችሁ ምንም መቋረጥ አይኖርም። ይህ ከማንኛውም ነገር በላይ ይረዳችኋል። በዘመናችን ያለውን የብዙውን ሃይማኖት መርገም የሆነውን ይህን የማስመሰል ቅድስና ለማሸነፍ ቁረጡ።
የምንፈልገው የተቀደሰ ሰብዓዊነትን እንጂ የማስመሰል ቅድስናን አይደለም። ስለ ምድራዊ ነገሮች በምትናገሩበት መንገድ ስለ ሃይማኖትም ለወዳጆቻችሁ መናገር ያስፈልጋችኋል። አንድ ወዳጃችሁ ችግር ላይ ወድቆ ወደ እናንተ ቢመጣ ሰዎች ብልጽግናን ስለሚያገኙባቸው አጠቃላይ መርሆችና ብልጽግናን ስላላገኙት ሰዎች አሳዛኝ ስሕተቶች በዙሪያ ጥምጥም መናገር አትጀምሩም፤ በቀጥታ ወደ ጉዳዩ ትገባላችሁ፤ ከልባችሁ የምታዝኑለት ከሆነም የልብሱን ጫፍ ይዛችሁ ወይም እጃችሁን በእጁ አኑራችሁ፦ «ውድ ወዳጄ፥ በጣም አዝንልሃለሁ፤ ልረዳህ የምችልበት መንገድ አለን?» ትሉታላችሁ።
ገዳይ በሽታ የያዘው ወዳጅ ቢኖራችሁና እናንተ ብታዩት እርሱ ግን ባያውቀው፣ ስለ በሽታ ኃይልና ሰዎች ጤናቸውን ስለሚጠብቁበት መንገድ ትምህርት መስጠት አትጀምሩም፤ ይልቁንም፦ «ውድ ወዳጄ፥ ይህ የሚያስጨንቅህ ሳል ከምታስበው በላይ ከባድ እንዳይሆን እፈራለሁ፤ በጉንጭህም ላይ ያለው ያ መቅላት መጥፎ ምልክት ነው። ታመሃል ብዬ እፈራለሁ—ሐኪም እንድታማክር ልምከርህ» ትሉታላችሁ። ሰዎች ስለ ምድራዊ ነገሮች የሚናገሩት እንዲህ ነው። እንግዲህ ስለ መንፈሳዊ ነገሮችም ልክ እንዲሁ አድርጉ። ወዳጃችሁ በመንፈስ የከሰረ ከሆነ ንገሩት። ወዴት እንደሚሄድ፣ የሒሳብ ቀንም እየመጣ እንደ ሆነ፣ በቅርቡም በእግዚአብሔር ወኅኒ ቤት እንደሚገባ፣ ባለ ዕዳውም አንድ ጊዜ ይዞ ካሰረው የመጨረሻዋን ሳንቲም እስኪከፍል ድረስ ከቶ እንደማይወጣ ንገሩት። ወዳጃችሁ መንፈሳዊ በሽታ ካለበት ንገሩት፤ ስለ ሥጋው እንደምታደርጉት ሁሉ እንዲሁ ቀጥተኛና ልባዊ ሆናችሁ ያዙት። እንደምትጸልዩለት ንገሩት፤ በዓይኖቻችሁ ውስጥ የሚያነበው ያ ጭንቀት ራሱ ያነቃዋል፤ እርሱም ስለ ራሱ የሚጨነቅበት ጊዜ እንደ ደረሰ ማሰብ ይጀምራል። ሰዎችን ስለ ነፍሳቸው የምትማጸኑበትን ይህን ቀላል፣ ቀሊልና ተፈጥሮአዊ መንገድ ለማግኘት ጣሩ። እውነተኛ ክርስቲያኖች ሁሉ ይህን ቢያገኙትና በዚሁ ቢሠሩ ይህች አገር ከዳር እስከ ዳር በተናወጠች ነበር ብዬ አምናለሁ!
ሦስተኛ፣ ልባዊ መሆን አለባችሁ—ቆራጥ እስከ መጨረሻ ማለት እወዳለሁ።
በእርግጥም ወዳጆች ሆይ፥ እናንተ ራሳችሁ ከምትረዱት በላይ የዘላለምን ነገሮች እውነታ ሌላ ነፍስ እንድትረዳ ፈጽሞ ማድረግ እንደማትችሉ ይህን እንደ እውነት ያዙት። የእግዚአብሔር መንፈስ ለእናንተ የሚሰጣችሁን ያህል የመረዳት መጠን በሰሚያችሁ ነፍስ ውስጥ ትወልዳላችሁ እንጂ ከዚያ አይበልጥም፤ ስለዚህ በሕልም በሚመስል፣ በተመቻቸና በግማሽ እንቅልፍ ባለ ሁኔታ ውስጥ ብትሆኑ በሚሰሟችሁ ነፍሳት ውስጥ የምትወልዱት ያንኑ ዓይነት መረዳት ብቻ ነው። ነቅታችሁ፣ ፈጥናችሁ፣ ሕያዋን ሆናችሁ፣ ከምትናገሩት እውነት ጋር በጥልቅ ተስማምታችሁ ልትገኙ ይገባል፤ ያለዚያ ምንም ፍሬ አያፈራም።
ሞተው የተወለዱ፣ ጅማት የሌላቸው፣ በቍርጥማት የተጠቁና ኃይል የሌላቸው ይህን ያህል ብዙ መንፈሳዊ ልጆች ያሉን ለዚህ ነው። የተወለዱት ከግማሽ ሞተኞች ወላጆች ነው፤ ነፍስን ከማይዝ፣ የአፈር ጥልቀት ከሌለው፣ ጨበጥ ከሌለው፣ ኃይልም ከሌለው ስሜታዊ ከሆነ ሃይማኖት ነው፤ ውጤቱም የታመመ የስሜታዊ አማኞች መከር ነው። ኦ! ጌታ በዙሪያችን ከሚዘሉት ከእነዚህ ምስኪን ስሜታዊ ጥላዎች ይልቅ ሕይወትና ብርታት የሞላባቸው ሕያዋን፣ በሚገባ ያደጉ ልጆችን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የሚያመጣ በቅንዓትና በእምነት የተሞላ እውነተኛ፣ ብርቱ፣ ሕያውና ጠንካራ ክርስትና ይስጠን። ኦ!
ወዳጆች ሆይ፥ ይህ ሕያው መረዳት ለራሳችን ያስፈልገናል። ቢኖረን በሌሎች ውስጥ እንወልደዋለን። ኦ! እግዚአብሔርን ያዙት። «የቤቱ ቅናት እስኪበላችሁ ድረስ» በመንፈሱ እንዲያጠምቃችሁ ለምኑት።
ይህ መንፈስ የሥጋንና የደምን፣ የሥርዓትን፣ የጨዋነትንና የመከበርን—የሞትንና የልዩ ልዩ ዓይነት ብስባሽነትን—እንቅፋቶች ሁሉ እያቃጠለ መንገዱን ያበጃል! እያቃጠለ ያልፋል፤ በምትናገሯቸውም ሰዎች ልብ ውስጥ ሕያውና ኃይለኛ ውጤት ያስገኛል። ልባዊነት—እስከ ቁርጥ ውሳኔ የሚደርስ ልባዊነት—ሁሉን እንደ ጕድፍ እንደ ቈጠረው፣ አዎን፥ ነፍሱንም በእርሱ ዘንድ እንደማትከብር እንደ ቈጠረው እንደ ጳውሎስ ያለ ልባዊነት። ምሥጢሩ ያ ነበር። ሕይወቱንም ሆነ ሕይወትን የሚያካትተውን ማንኛውንም ነገር—ነጻነትን፣ ተድላን፣ ደስታን፣ ወዳጆችን፣ ስምን፣ ምቾትን፣ ወዘተ—ከቁም ነገር አልቈጠረም፤ ሁሉም በመሠዊያው ላይ ነበር፤ ሁሉም በሚዛኑ ላይ ነበር። በገዛ ነፍሱ ውስጥ የክርስቶስን ፍጹምነትና ሙላት፣ በዙሪያውም ያሉትን ሰዎች ነፍሳት መዳን ያገኝ ዘንድ ከእነዚያ አንዳቸውንም ውድ አድርጎ አልቈጠረም።
ኦ! ቀላል፣ ዋዘኛ፣ ምቾት ወዳድና ለብ ያለ ሃይማኖተኛ ነኝ ባይ ለሲኦል እንዴት ያለ መሳቂያ ነው! ኦ! በሰማይ ላሉ መላእክት እንዴት ያለ ኀፍረትና እንቆቅልሽ፣ ለእግዚአብሔርም እንዴት ያለ ታላቅ መጸየፊያ ነው!
«በራድ ወይም ትኩስ እንዳይደለህ ሥራህን አውቃለሁ። በራድ ወይም ትኩስ ብትሆንስ መልካም በሆነ ነበር።
እንዲሁ ለብ ስላልህ በራድም ወይም ትኩስ ስላልሆንህ ከአፌ ልተፋህ ነው።» — ራእይ 3:15-16 ኦ! ያ ምን ይሆን? ስለ ኀፍረት ታወራላችሁ? ያንን አስቡ! ኀፍረት! አንዳንዶቻችሁ ለእግዚአብሔር ወደ አደባባይ ስትወጡ ኀፍረት ይሰማችኋል። ጥቂት ሰዎች እዚህ ስትንበረከኩ ሲያዩአችሁ ኀፍረት ይሰማችኋል! በተሰበሰበው ፍጥረተ ዓለም ሁሉ ፊት ከእግዚአብሔር አፍ መተፋትን አስቡ። ያ ምን ይሆን? እግዚአብሔር ቢረዳኝ ያንን እሸሻለሁ። ያንን ኀፍረት ከምሸከም ይልቅ በሁለት ወንበዴዎች መካከል ከኢየሱስ ጋር በመስቀል ላይ መሰቀልን እመርጣለሁ። «በራድ ወይም ትኩስ ብትሆንስ መልካም በሆነ ነበር!»
አንዳንዶቻችሁ በደብዳቤዎቻችሁ ይህን በሙሉ ልብ መሰጠት እንደምትይዙ ትናገራላችሁ። ሁሉን እንደ ተዋችሁና ራሳችሁን ለድካም ሕይወት እየቀደሳችሁ እንደ ሆነ ትናገራላችሁ። እንግዲያውስ ትኩሳን ሁኑ። የፈሪሳውያንን ጣቶች እንደምታቃጥሉ አውቃለሁ። ግድ የለም። የሳምሶን ቀበሮዎች በእህሉ ላይ እንዳደረጉት ሁሉ እናንተም ሕሊናቸውን በእሳት እንደምትለኰሱ አውቃለሁ። ግድ የለም። ትኩሳን ሁኑ። እግዚአብሔር ትኩሳን ቅዱሳንን ይወዳል። ትኩሳን ለመሆን ቁረጡ። ሞኝ ይሉአችኋል፤ ጳውሎስንም እንዲሁ ብለውታል።
አክራሪ ይሉአችኋል፤ «ይህ ሰው እስራኤልን የሚያውክ ነው» ይላሉ፤ እናንተ ግን፦ «የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ስለ ተዋችሁ የምታውኩት እናንተና የአባታችሁ ቤት ናችሁ እንጂ እኔ አይደለሁም» ብላችሁ መመለስ አለባችሁ። ክሱን በእነርሱ ላይ መልሱት። ትኩሳን ሰዎች ትኩሳንን ሰዎች ፈጽሞ አያውኩም። ይበልጥ ትኩሳን በሆንን መጠን ይበልጥ እንቀራረባለን፤ እርስ በርሳችንም ይበልጥ እንዋደዳለን። በትኩሳኑ የሚታወኩት በራዶቹ ሰዎች ናቸው። ጌታ ትኩሳን እንድትሆኑ ይርዳችሁ—በእውነት ትኩሳን!
ሌላው የግድ አስፈላጊ ሁኔታ ደግሞ ኃይሎቻችንን ሁሉ መስጠት ነው።
ምንም ወደ ኋላ መያዝ የለበትም። «ሰይፉን ከደም የሚከለክል ርጉም ይሁን።» ያ መርገም ዛሬ በክርስትና ዓለም ላይ አርፎበታል። ኦ! ሰይፉን ጥቂት ወደ ውስጥ ይሰክሩታል እንጂ እስከ አንጀቱ ድረስ ዘልቀው አይገቡም። የዚህ ዘመን ወታደሮች ሕይወታቸውን ቢያጡ እንኳ ደምን ለማፍሰስ አይደፍሩም። እግዚአብሔር ስለ እነርሱ የሚለውን ሳይሆን ሰዎች ስለ እነርሱ የሚሉትን እያሰቡ ወደ ራሳቸው ስለሚመለከቱ፣ ወዮ! ሰውን እስከ ልቡ ድረስ ለመንካት አይደፍሩም። የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ተዋጊ መሆን ከፈለጋችሁ ደምን መፍራት የለባችሁም። አስፈላጊ ከሆነ «እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ ከሚመጣው ቍጣ እንድትሸሹ ማን አመለከታችሁ?» ለማለት መፍራት የለባችሁም። ይህን በማድረጋችሁ ከእነርሱ አንዳንዶቹን የምታድኑ ከሆነ፣ አስፈላጊ ሲሆን «የአባቴን ቤት የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት» ለማለት መፍራት የለባችሁም።
ኦ! ይህ የተረገመ ሽንገላ፤ ይህ የዓለምን ነቀፌታ ለመጋፈጥ የሚያስፈራ የተረገመ ፍርሃት፣ እግዚአብሔር ፈጽሞ እንደ እኛ እንደ ሆነ ሁሉ ክፉውን መልካም መልካሙንም ክፉ የማድረግ ይህ የተረገመ ልማድ ልል ነበር። እርሱ ይህን ርኩስ ማስመሰል አልፎ የሚያይ አይመስላችሁምን? ኦ! ወዳጆቼ ሆይ፥ በዚህ ረገድ ካልተሻሻልን ብዙም ሳይቆይ በፍርድ ይመጣል፤ ከዚያ በፊት ካላወቅን ያን ጊዜ ክቡሩንና ከንቱውን የሚለየውን ልዩነት እናውቃለን። ስኬታማ ሠራተኛ መሆን ከፈለጋችሁ ከመጀመሪያው ለመሰቀል ልባችሁን ማዘጋጀት አለባችሁ።
አንድ ውድ አገልጋይ በመድረክ ላይ እንዲህ ጨካኝ ስለ መሆኑ ከሚከራከረው ሰው ጋር ሲነጋገር፦ «ግድ የለኝም» አለው። ሌላውም፦ «ኦ!» አለ፤ «‹ግድ የለኝም› ባዩ ምን እንደ ደረሰበት አታውቅምን?»
እርሱም፦ «አዎን፥ ተሰቀለ፤ እኔም ከእርሱ ጋር ጎን ለጎን ለመሰቀል ዝግጁ ነኝ» አለ። ትክክል ስትሆኑ ግድ አይበላችሁ። ቢበዛ ልትሰቀሉ ትችላላችሁ፤ ቶሎም ያልፋል፤ ከዚያም መጽሐፍ ቅዱስ «ብንጸና፥ ከእርሱ ጋር ደግሞ እንነግሣለን»፤ «አብረንም ደግሞ እንድንከበር» ይላል። ብቻን መከበር ድንቅ ነገር በሆነ ነበር፤ ኦ፥ ግን አብሮ መከበርን አስቡ!
አንድ ጨዋ ሰው በቅርቡ እንዲህ አለ፦ «ስለ ክብሩ ብዙ እያሰብሁ ነበር። ድንቅ ነገር ነው—የሚከተለው ያ ክብር። ሰው እርሱን ለማግኘት ዕድሜውን ሙሉ በቆሻሻ ክምር ላይ ቢቀመጥ ይገባዋል።» ተመለከትሁትና አሰብሁ፦ ምናልባት ከምታስበው በላይ ቀርበህለት ይሆናል፤ ምናልባት እኔም እንዲሁ። አሃ! የሚከተለው ያ ክብር ድንቅ ነገር ነው። እንግዲያውስ ከእርሱ ጋርና ስለ እርሱ መከራን ለመቀበል ፈቃደኞች እንሁን። ከመጀመሪያው ለመሰቀል ልባችሁን አዘጋጁ፤ ከዚያም ቀላል ይሆናል።
በተጨማሪም፣ ራስን ፈጽሞ አሳልፎ መስጠት ለስኬታማ አገልግሎት ሁኔታ ነው።
በማንኛውም ነገር እንዲሁ ነው። ሁልጊዜ ምን ያህል እንደሚያስከፍለው፣ መቼ እንደሚመለስ፣ ወይም መሥዋዕቱ የሚገባው መሆን አለመሆኑን የሚያሰላ ወታደርን ምን ትሉታላችሁ? «ለሠራዊቱ ምንም አይጠቅምም። የምንፈልገው በማንኛውም ዋጋ ለማሸነፍ የሚገቡ ሰዎችን ነው» ትላላችሁ። እንግዲህ እግዚአብሔር ለማሸነፍ የሚገቡ፣ በማሸነፍ የሚያምኑ፣ የማሸነፍ ኃይል እንዳላቸው የሚያውቁ፣ ከማሸነፍ ጋር ሲነጻጸርም ሁሉን እንደ ጉዳት የሚቈጥሩ ወንዶችንና ሴቶችን ይፈልጋል። ስኬትን ትፈልጋላችሁ? በመጀመሪያ ወደዚህ ካልመጣችሁ ከቶ አታገኙትም።
አራተኛ—የሚያሰናክላችሁን ሁሉ መተው፣ ከመንገድ አሽቀንጥሮ መጣልና ከእግር በታች መርገጥ አለባችሁ።
መልካም ስም። ምናልባት እዚህ አንዳንድ አገልጋዮች ይኖሩ ይሆናል። ባለፈው እሑድ አንዳንዶች ነበሩ፤ ከዚያ በፊት ባለው እሑድም አንዳንዶች ነበሩ። ከእናንተ አንዳንዶቻችሁ ጽፋችሁልኛል፤ ሌሎቻችሁም አነጋግራችሁኛል። «ይህ ከራስ ክበብ ፈጽሞ መለየት ይሆናል» ትላላችሁ። ልክ ነው። አንዳንዶች፦ «አያችሁ፥ ይህን ከፍ ያለ መመዘኛ ማቆም የማይቀር ውጤቱ ሰይፍን ከምርጥ አድማጮቻችሁና ከምርጥ ወዳጆቻችሁ አንዳንዶቹ ውስጥ ዘወትር መስደድ ይሆናል» ይላሉ። ልክ ነው፤ ሰይፍን ለደም መስጠት ማለት ይኸው ነው።
የጠላትን ደም ማፍሰስ ብዙም አያስጨንቃችሁም—ፈተናው የወዳጆቻችሁ ደም ነው! ይህን ሁሉ አውቃለሁ፤ በዚያ አልፌአለሁ። አንድ ጊዜ ለረጅም ጊዜ እዚያ ነበርሁ። የራሴ የሚያመኝ ቍስል ነበር። ዲያብሎስ፦ «መስበክ ብትጀምሪ ዓይን አውጣ ሴት ይሉሻል» አለኝ፤ እኔም ይህ ስለ እኔ ከሚባል ወደ ሲኦል መሄድ ይሻላል እስኪመስለኝ ድረስ ተሰማኝ። «በጋዜጦች ላይ ያወጡሻል፤ ስለ አንቺም ልዩ ልዩ ባለጌና ጸያፍ ነገር ይናገራሉ» አለኝ፤ ያ በነፍሴ ላይ ምን እንደ ነበረ እግዚአብሔር ብቻ ያውቃል፤ ነገር ግን በመጨረሻ፦ «ጌታ ሆይ፥ ምንም ቢሉኝ ግድ የለኝም—ነፍሳትን እማርክ ዘንድ ራሴን ለአንተ እሰጣለሁ» እስክል ድረስ ለረጅም ጊዜ ታገልሁትና ተጋደልሁት። ተጸጽቼበት አውቃለሁ? ወደፊትስ እጸጸትበታለሁ? አይደለም፤ እርሱ ስምህን ይጠብቅልሃል። ወንድሜ ሆይ፥ ስምህን ለእርሱ አሳልፈህ ስጥ።
ጸሐፍትና ፈሪሳውያን በሥጋ ስለ መጣው ስለ ኢየሱስ አንድም መልካም ነገር ተናግረው አያውቁም። መልካም ስማችሁን ተዉ—ተከተሉት። የግድ ከሆነ ወደ ጌቴሴማኒ፣ ወደ ጎልጎታና ወደ መስቀሉ ልትከተሉት ቁረጡ። ግድ የለም—ተከተሉት። መልካም ስማችሁን ተዉ።
ከዚያም ልማዶቻችሁ። የማኅበረሰቡ ተራ የፋሽን ከንቱ ነገሮች ራሳችሁን ለክርስቶስ እንዳትቀድሱ እንቅፋት እንዲሆኑባችሁ የፈቀዳችሁ አንዳንዶቻችሁ ምንኛ ታፍሩ ይሆን! ይህን የሚያደርጉ ሰዎች ግን ክርስቲያኖች ነን ይላሉ። አላውቅም፤ ላምነው አልችልም። መጠጥ አለ፤ አንድ ብርጭቆ ወይን ይጠጣሉ። መልካም፥ ልትጠጡት ትችላላችሁ፤ ነገር ግን የመንግሥቱን ወይን አትጠጡም። ክርስቲያን ነን ባዮች እንደ ፓሪስ አመንዝሮች ይለብሳሉ። መልካም፤ ነገር ግን የበጉ ሙሽራ አይሆኑም። እርሱ ከእነርሱ ጋር በጎዳና አይሄድም፤ በአንድ ማዕድም አይቀመጥም።
ሃይማኖተኞች ብቻ ናቸው ወደሚባልባቸው ግብዣዎች መሄድ ትችላላችሁ፤ በዚያ ግን ጌታ ቢሰማው እጅግ የምታፍሩበት ልዩ ልዩ ሐሜትና ክርስቶስ የሌለበት ከንቱ ወሬ እንደሚካሄድ ታውቃላችሁ፤ ከዚያም ለጸሎት ምንም ፍላጎት ሳይኖራችሁ ትወጣላችሁ። ወደዚህ ሁሉ መሄድ ትችላላችሁ፤ ነገር ግን በዚያው ጊዜ መንፈስ ቅዱስ እንዲኖራችሁ እሞግታችኋለሁ። ልከራከርበት አልቆምም፤ የማውቀው ይህን ማድረግ እንደማትችሉ ብቻ ነው! ያ ሁሉ ወደ ጎን መደረግና መተው ይኖርበታል። «ይህ የሚያም ነጥብ ነው» ትላላችሁ። አዎን፤ ይህ ሰይፍን እስከ ደም መስደድ እንደ ሆነ አውቃለሁ።
አምስተኛ።—ገንዘባችሁን ለእግዚአብሔር አገልግሎት እንዲውል መቀደስ አለባችሁ።
አንድ ጊዜ አንድ በዕድሜ የገፉ አርበኛ ቅዱስ፦ «የገንዘብ አጠቃቀም የሰውን ጠባይ ከሁሉ ይበልጥ እርግጠኛ ፈተና ነው ብዬ እቈጥራለሁ» ሲሉ ሰማሁ፤ በዚያን ጊዜ ማጋነን መስሎኝ ነበር። በእርግጥ ሰው ሚስቱንና ልጆቹን የሚይዝበት መንገድ ከዚያ የበለጠ እርግጠኛ ፈተና ነው ብዬ አሰብሁ፤ ነገር ግን አመለካከታቸውን እስከማምን ድረስ ኖርሁ። ስለዚህ የሰው ተሞክሮ መለኮታዊውን ጥበብ እንዴት እንደሚያጸድቅ ታያላችሁ—«ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነው።» በአንድም በሌላም መልኩ እንዲሁ ነው። ገንዘቡን እስኪሰጥ ድረስ እግዚአብሔር ማንንም በጉልህ አይጠቀምበትም። እውነታን ብቻ እገልጣለሁ። ይህ እንዲህ እንደ ሆነ በተሞክሮና በእግዚአብሔር ሕዝብ ታሪክ እናውቃለን።
ገንዘባችሁን እንደ ግብ መተው አለባችሁ፤ ለራሱ ሲባል ማከማቸትን፣ ወይም የራሳችሁን ወይም የልጆቻችሁን የራስ ወዳድነት ፍላጎት ማርካትን ተዉ—ገንዘቡ ሁሉ ባለቤቱ ለሆነው ለእግዚአብሔር ተሰጥቶ ሙሉ በሙሉ ለአገልግሎቱ መዋል አለበት። ለነፍሳት ስኬታማ ሠራተኞች መሆን ከፈለጋችሁ ይህን በደጃፉ ላይ ማድረግ ይኖርባችኋል። ገንዘባችሁን ለጌታ ስጡ። ከፊሉን ማስቀመጥ ትክክል መስሎ ከታያችሁ እየሄዳችሁ ለእርሱ ልትጠቀሙበት አስቀምጡት፤ ጸሐፊያችሁ ወይም ሒሳብ ያዣችሁ ለእናንተ እንዲሆን የምትጠብቁትን ያህል በሰማይ አባታችሁ ፊት በራሳችሁ ላይ ጥብቅ ሁኑ፤ ያን ጊዜ ሁሉም መልካም ይሆናል።
ጠባብና አስቸጋሪ መንገድ ነው። ገንዘብ ላገኛችሁ ለእናንተ እንቀጠቀጣለሁ፤ ለእኔ ባለመኖሩም ደስ ይለኛል፤ ነገር ግን ስላገኛችሁት የማውቀውን የተሻለ ምክር እሰጣችኋለሁ። ገንዘብ መያዝ የሚያስፈራ ነገር ነው፤ ከዚያ ቀጥሎ ያለው የተሻለው ነገር ግን እርሱን መቀደስና ለክብሩ መጠቀም ነው፤ ይህን ባታደርጉ ግን እንደ ጭንቁር ነፍሳችሁን ይበላል። ነቀርሳ ለሥጋችሁ እንደ ሆነ ለመንፈሳዊ ተፈጥሮአችሁም እንዲሁ ይሆናል። ቃሉ የጳውሎስ ነው እንጂ የእኔ አይደለም።
ስለ ዋጋው አንድ ቃል መናገር አለብኝ።
ሁልጊዜ ወደ ተግባር የምገፋፋችሁ ይመስላችኋል። አዎን፥ ስለሚያስፈልጋችሁ ነው። እጅግ ብዙ ስትሠሩ እንደማላገኛችሁ ጌታ ያውቃል። ከእናንተ በአንዳንዶቻችሁ ከልቤ አፍራለሁ። አንዳንዶቻችሁ መገፋፋት እጅግ ስለሚያስፈልጋችሁ ስለ ተግሣጹ እግዚአብሔርን ልታመሰግኑ ይገባችኋል። ጳውሎስ፦ «ምን ትወዳላችሁ? በበትር ወይስ በፍቅርና በየውሃት መንፈስ ልምጣባችሁን?» ይላል። ከአንዳንድ ሰዎች ጋር እንዲህ ማድረግ ግድ ሆኖበት ነበር። የሚያስቀና ነገር አይደለም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ሥራ ሲሰጠን ልንሸሸው አንደፍርም፤ ይሁን እንጂ ብሩህ ገጽታም አለ—ዋጋው አለ።
«ምን!» ትላላችሁ፤ «ይከፍልሻል?» አዎን፥ መልካም ደመወዝ—የተጨቈነና የተነቀነቀ! እንዲህ ይላል፦ «ድሀውን የሚያስብ (ሥጋቸውን ብቻ ማለቱ ይመስላችኋል?)፣ እኔ አስበዋለሁ፤ በደዌውም ጊዜ መኝታውን አነጥፍለታለሁ (እንዴት ያለ ርኅሩኅ አነጋገር ነው!)።» ያራግፍለታል፤ ማንም ምድራዊ አስታማሚ፣ እጅግ ርኅሩኅ የሆነች ሚስትም እንኳ ልታደርገው በማትችለው ሁኔታ ላባዎቹን በትራሶቹ ላይ ያነጥፋል። «በደዌውም ጊዜ መኝታውን አነጥፍለታለሁ።» ወንድሜ ሆይ፥ ያን ጊዜ ትፈልገዋለህ! አንዳንዶቻችሁ አሁን እጅግ ራሳችሁን የቻላችሁ ናችሁ፤ ነገር ግን ያን ጊዜ ትፈልጉታላችሁ። «በደዌው ጊዜ መኝታውን አነጥፍለታለሁ። የዘላለም ክንዶቼን ከበታቹ አኖራለሁ።» በሞት ውኆች ውስጥ ድል እንድትነሡ ያደርጋችኋል። ያ ታላቅ ነገር ይሆናል፤ አይደለም እንዴ? ስለ ባልንጀሮቻችሁ ነፍሳት በፍቅራዊ ጭንቀትና በተጨነቀ ርኅራኄ ለመድከም ለወጣችሁ ለእናንተ ወደ መንግሥቱ የድል መግቢያ ይሰጣችኋል። በሙላት መግባትን ያዘጋጅላችኋል፤ ከዚያስ—ምን? ልጆችን ይሰጣችኋል፤ መካኒቱም ባል ካላት ይልቅ ብዙ ልጆች ይኖሯታል።
ኦ! በዚህ ረገድ ዓለሙ ሁሉ አንድ ነው። ወንድም ሴትም ሁሉ ልጆችን ይፈልጋሉ። በተለይም ከጌታ የተሰጡ ርስት ናቸው። የልጆችን ማጣት የሚተካ ምንም ነገር የለም። በትሑት ጎጆ የሚኖሩ እጅግ ድሆች ወላጆች ልጆቻቸውን አይሸጡላችሁም፤ በዓመት ሃያ ሺህ የሚያገኝ ባለጠጋም ወንድ ወይም ሴት ልጅ ማግኘት ካልቻለ ያንኑ ሰጥቶ ልጅ ለማግኘት ይሻል። የሰው ልጆች ሁሉ ልጆችን ይፈልጋሉ። እንግዲህ ጌታ ልጆችን ይሰጣችኋል። እናት—ቅድስት እናትም እንኳ ቢሆን—መልካም፣ ታዛዥና እግዚአብሔርን የሚፈሩ ልጆቿን ለወዳጆቿ ስታሳይ ደስ ከመሰኘት፣ ይልቁንም ከመደሰትና ከማመስገን ልትቆጠብ አትችልም ብዬ እገምታለሁ። እግዚአብሔር ይህን ከውስጣችን ሊያጠፋው ይፈልጋል ብዬ አላምንም።
አገልጋዩን ኢዮብን ለዲያብሎስ ለማሳየት ደስ እንዳለው ሁሉ እርሱ ራሱ በዚህ ደስ ይለዋል ብዬ አምናለሁ። «ባሪያዬን ኢዮብን ተመለከትኸውን?» አሃ! በእርሱ አልተመካበትምን?—ከዚያን ጊዜ ጀምሮም በእርሱ ሲመካ ኖሯል። እግዚአብሔር ይህን ስሜት በውስጣችን አኑሯል፤ ቅዱስ ሲሆንም ትክክለኛ ስሜት ነው። እግዚአብሔርን በሚፈሩና በታዛዥ ልጆች ከመኩራት አንቆጠብም፤ ነገር ግን መንፈሳዊ ልጆቻችሁን ለመላእክት ማሳየት ምን ይሆን? እግዚአብሔር የሰጣችሁን መንፈሳዊ ቤተ ሰብ በመድኃኒታችሁ ዙፋን ዙሪያ ሰብስባችሁ፦ «እነሆኝ፥ እኔና አንተ የሰጠኸኝ ልጆች» ስትሉ ምን ይሰማችሁ ይሆን?—እግዚአብሔር ብቻ በሚያውቀው ዓይነት ትግል፣ ፈተናና ግጭት የተማረኩ ልጆች፤ ጳውሎስ እንደሚለው «በእስራቴ የወለድኋቸው ልጆች»—በሰንሰለት—በመንፈሳዊ ግጭት፣ በድካምና በመከራ ዐውሎ ነፋስ መካከል የተወለዱ፣ በአእምሮ፣ በልብና በነፍስ ወሰን በሌለው ዋጋና ጫና በእቅፍ የተያዙ፣ የተወዘወዙ፣ የተመገቡ፣ የተንከባከቡና ያደጉ ልጆች፤ አሁን ግን፣ ጌታ ሆይ፥ እነሆ አለን። በዚያ ሁሉ አልፈን እዚህ ደርሰናል።
«እነሆኝ፥ እኔና አንተ የሰጠኸኝ ልጆች።» ምን ይሰማችሁ ይሆን? ስለ ድካሙ ታዝኑ ይሆን? ስለ መሥዋዕቱ ትጸጸቱ ይሆን? ስለ መራችሁ መንገድ ታጕረመርሙ ይሆን?
አሁን አንዳንድ ጊዜ እንደምትፈተኑት ትንሽ ቀለል ሊያደርገው ይችል ነበር ብላችሁ ታስቡ ይሆን?
ኦ! አይደለም፣ አይደለም!—ልጆቹ! ልጆቹ! ልጆች ይኖሩአችኋል! ይህ በቂ ዋጋ አይሆንምን?
ኦ! አንዳንድ ጊዜ፣ ከመጋረጃ በስተ ጀርባ ብዙ ትግል ከሚያመጣ ሥራ ጋር በተያያዘ በግጭትና በፈተና ውስጥ ሳልፍ፣ ራሴን በጌታ አበረታታለሁ፤ ወደ ቤታቸው የሄዱትንና ከወንዙ ዳር ሰላምታቸውን የላኩልኝን፣ እንደሚጠብቁኝና እንደሚጠባበቁኝ፣ እዚያ ስደርስም እኔን ለመድኃኒቱ የሚያቀርቡኝ የመጀመሪያዎቹ እንደሚሆኑ የነገሩኝን አስታውሳለሁ። ይህ በቂ ዋጋ አይሆንምን? አዎን፥ ጌታ ሆይ። አሜን።
ምዕራፍ 10 ተጠናቋል
ለእግዚአብሔር በስኬት እንዴት መሥራት ይቻላል