በነዶዎች መካከል የተለቀመ
ጸጋና መዳን

ምዕራፍ 8 · 7 ደቂቃ ንባብ

ጸጋና መዳን

የጸጋ ድል

ሰዎች ሁሉ ክርስቶስን አለመውደዳቸው ከድንቆች ሁሉ ታላላቅ ከሆኑት አንዱ ነው። «የተናቀ ከሰውም የተጠላ ነበረ» ከሚለው እውነት ይበልጥ የዘራችንን ፍጹም መበላሸት በግልጥ የሚያሳይ ምንም ነገር የለም። ነገር ግን የሰውን ርኵሰት የታላቁን ቀላይ ምንጮች ተነድለው ያዩ ሰዎች መሲሑ የተደረገበትን ነገር ለማስረዳት አይቸገሩም። ጨለማ ከብርሃን ጋር፥ ክርስቶስም ከቤልሆር ጋር ኅብረት ሊኖረው አይቻልም ነበር። ሁለቱ አልተስማሙምና የወደቀው ሰው ከኢየሱስ ጋር ሊሄድ አልቻለም። በደለኛው ፍጡር ፍጹም የሆነውን መጥላቱ፥ እንዲህ ያሉ ሁለት ተቃራኒዎች ሲገናኙ የግድ የሚመጣ ውጤት ብቻ ነበር። «ስቀለው ስቀለው» የወደቀው ሰው ተፈጥሮአዊ ጩኸት ነው። የመጀመሪያው መደነቃችን ስፍራውን ይለቅቃል፥ ሌላም ድንቅ የሐሳባችንን ስፍራ ይሞላል። ሰዎች ሁሉ አለመውደዳቸው አስደንቆን ነበርን?—ከዚያ ይልቅ እጅግ የሚያስደንቀው ማንም ሰው ኢየሱስን መውደዱ ነው። በመጀመሪያው ሁኔታ የፀሐይን ብሩህነት ማየት የተሳነውን አስፈሪ ዕውርነት አየን—እየተንቀጠቀጥን አየነው፥ እጅግም ተደነቅን፤ በዚህኛው በሁለተኛው ሁኔታ ግን የናዝሬቱ ኢየሱስ አጥብቆ የተዘጋውን ዓይን ሲከፍት፥ የግብፅንም ጨለማ በሚያስደንቀው ብርሃኑ መለኮታዊ ጸዳል ሲበትነው እናያለን። ይህ ያነሰ ድንቅ ነውን? በመቃብሮች መካከል የነበረውን ጋኔን ያደረበትን ሰው አስፈሪ እብደት ማየት እንግዳ ነገር ከሆነ፥ ያንኑ ሰው ለብሶ ልቡም ተመልሶ በኢየሱስ እግር አጠገብ ተቀምጦ ማየት በእርግጥ እጅግ የሚበልጥ ተአምር ነው። የሰው ልብ ፍቅሩን ለኢየሱስ እንዲሰጥ ሲደረግ በእውነት የጸጋ ድል ነው፤ ይህ የሰይጣን ሥራ ሁሉ እንደ ፈረሰ፥ ሰውም ከወደቀበት ሁኔታ እንደ ተመለሰ ያረጋግጣልና።

የጽድቅ ልብስ

በሰማይ የምንለብሰው የክብር ልብሳችንም ሆነ ለዕለት ኑሮ የምንለብሰው የቅድስና ልብሳችን፥ ራሱን ዝቅ ያደረገው የክርስቶስ ፍቅር ስጦታዎች ናቸው።

ወንጌል

የምትፈልገው ሁሉ በወንጌል ውስጥ አለ። በመከራ ጊዜ የሚደግፍህ ነገር ትፈልጋለህን? በወንጌል ውስጥ አለ፦ «እንደ ዘመንህ ኃይልህ ይሁን»። ለተግባርህ የሚያበረታህ ነገር ያስፈልግሃልን? እግዚአብሔር እንድትታገሠው ወይም እንድትፈጽመው ለሚጠራህ ነገር ሁሉ ፍጹም የሚበቃ ጸጋ አለ። የተስፋህን ዓይን የሚያበራ ነገር ያስፈልግሃልን? ወይ! በወንጌል ውስጥ ዓይንህ የማይጠፋውን የብፅዕና እሳት መልሶ እንዲያንጸባርቅ የሚያደርጉ የደስታ ብልጭታዎች አሉ። በፈተና መካከል ጸንተህ እንድትቆም የሚያደርግህ ነገር ትፈልጋለህን? በወንጌል ውስጥ የማትነቃነቅ፥ የጌታም ሥራ ሁልጊዜ የሚበዛልህ ሊያደርግህ የሚችል ነገር አለ። ወንጌል እስከ አፉ ድረስ ያልሞላው ስሜት፥ ፍቅር፥ ሐሳብ፥ ምኞት ወይም ኃይል የለም። ወንጌል ለሰው ልጅ ሁለንተና እንደ ተዘጋጀ ግልጥ ነው፤ በየክፍሉ ሁሉ ለእርሱ ተስማሚ ነው። ለአእምሮ እውቀት አለ፤ ለልብ ፍቅር አለ፤ ለእግርም መምሪያ አለ።

የማይገባን ፍቅር

የእርሱን ፍቅር ማስተዋል ለዚያ ፍቅር የማንገባ መሆናችንን ከማስተዋል ጋር ሲመዛዘን እንደሚያደርገው፥ ክርስቶስን እጅግ እንድንወድ የሚያደርገን ሌላ ምንም ነገር የለም። ክርስቶስ እንደሚወደን ማሰብ ጣፋጭ ነው፤ ነገር ግን፥ ወይ፥ እንደ «የቄዳር ድንኳኖች» ጥቁሮች መሆናችንን ማስታወስ፥ እርሱ ግን ይወደናል! ይህ ከሌላው ነገር ሁሉ ልባችንን ሊያስጥል የሚገባው ሐሳብ ነው።

ጸጋ

ጸጋ ሁልጊዜ ጸጋ ነው፤ ነገር ግን ወደማይገባን ወደ እኛ ወደ ራሳችን ሲመጣ ስናየው የሚታየውን ያህል ቸርነቱ ጐልቶ የሚታይበት ጊዜ የለም።

የምሕረቱ ዕቃዎች

የእግዚአብሔር ምርጦች «የምሕረቱ ዕቃዎች» ተብለው ተጠርተዋል። ዕቃ ከተቀባይነት በቀር ሌላ ምንም እንዳልሆነ እናውቃለን። «ዕቃ» ምንጭ አይደለም፤ በውስጡ የሚፈስሰውን ነገር የሚይዝና የሚቀበል ብቻ ነው። እግዚአብሔር የተቤዣቸውም እንዲሁ ናቸው፤ በተፈጥሮአቸው መልካም ነገር የሚፈልቅባቸው ምንጮች አይደሉም፤ ተቀባዮች ብቻ ናቸው። በአንድ ወቅት በራሳቸው ተሞልተው ነበር፤ ጸጋ ግን ባዶ ያደርጋቸዋል፤ ከዚያም እንደ ባዶ ዕቃዎች በእግዚአብሔር ቸርነት መንገድ ላይ ይቀመጣሉ፤ እግዚአብሔርም በጽኑ ፍቅሩ እስከ አፋቸው ይሞላቸዋል፤ በዚህም የምሕረቱ ዕቃዎች መሆናቸው ይረጋገጣል። ከዚያ በኋላ እንደ «ዕቃዎች» ለሌሎች ሊያፈስሱ ይችላሉ፤ ነገር ግን ማፍሰስ የሚችሉት እግዚአብሔር በውስጣቸው ያኖረውን ብቻ ነው፤ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳቸውን መዳን ሊፈጽሙ ይችላሉ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ስለ በጎ ፈቃዱ መፈለግንም ማድረግንም በእነርሱ ካልሠራ በቀር ሊፈጽሙት አይችሉም። በምስጋና ሊትረፈረፉ ይችላሉ፤ ይህ ግን እግዚአብሔር በጸጋ ስለ ሞላቸው ብቻ ነው፤ ቅድስና ከእነርሱ እንደ ጅረት ሊፈስስ ይችላል፤ ይህ ግን ጌታ ምንጩ ሳይቋረጥ እንዲትረፈረፍ ስለሚያደርግ ብቻ ነው። ተቀባዮች ናቸው፤ ተቀባዮች ብቻ።

ወንጌል የሚጠይቀው

ወንጌል ለእግዚአብሔር የመስጠት ሥርዓት አይደለም፤ ከእግዚአብሔር የመቀበል ሥርዓት ነው እንጂ። ከሙላቱ መውሰድ፥ ከእርሱ «የመዳን ምንጮች» መጠጣት፥ ከግምጃ ቤቱ መቀበል ነው። ኃጢአተኛ ሆይ! ትድን ዘንድ እግዚአብሔር ከአንተ የሚጠይቀው ሁሉ ተቀባይ እንድትሆን ብቻ እንደ ሆነ አስታውስ፤ ይህንንም እርሱ ራሱ ይሰጥሃል፤ የመቀበልን ኃይል እንኳ። ምንም ነገር እንድታደርግ አይጠይቅህም፤ ባዶ እጅህን ዘርግተህ የምትሻውን ሁሉ እንድትወስድ ብቻ እንጂ። ጎተራዎችህን እንድትሞላና ባለ ጠጋ እንድትሆን አያዝዝህም፤ ድህነትህን ብቻ እንድትናዘዝ፥ እርሱም የምታኖርበት ስፍራ እንኳ የማታገኝለትን በረከት ያፈስስልህ ዘንድ የባዶ ክፍሎችህን ደጆች እንድትከፍት ያዝዝሃል እንጂ። ይህን እውነት ተምረሃልን? ከእግዚአብሔር እጅ እንደ ተቀባይ ለመኖር መጥተሃልን? በትሕትና መዳንን እየፈለግህ በምሕረት ደጅ ቆመሃልን? እንዲህ ካላደረግህ ግን—የራስህን ዋጋ ቢስ ሥራ ለእርሱ ከመስጠት ይልቅ የጸጋን ባለ ጠግነት ከእግዚአብሔር ለመቀበል ገና ፈቃደኛ ሆነህ የማታውቅ ከሆነ—በነጻ የሚሰጠውን ቸርነቱን ለመቀበል ፈቃደኛ ካልሆንህ—የክርስቶስን ወንጌል ለሚመስል ነገር ሁሉ ፈጽመህ እንግዳ ነህ።

ጸጋ ከመጠን ይልቅ በለጠ

ይህ ዓለም በታሪኩ ፈጽሞ ለኃጢአት አልፎ የተሰጠበት ዘመን ከቶ አልነበረም። እግዚአብሔር ሁልጊዜ በምድር ላይ አገልጋዮች ነበሩት፤ አንዳንድ ጊዜ በዋሻዎች ውስጥ ሃምሳ ሃምሳ ሆነው ተሸሽገው ይሆናል፤ ፈጽመው ግን ከቶ አልጠፉም። ጸጋ ሊያንስ ይችላል፤ ወንዙ እጅግ ጥልቀት የሌለው ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ፈጽሞ ደርቆ አያውቅም። ደመናዎች ቀኑን እስኪሰውሩ ድረስ ሁሉን የሸፈኑበት ጊዜ ከቶ አልነበረም። ነገር ግን ጸጋ በዓለማችን ሁሉ ላይ የሚዘረጋበት፥ «ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለች» የሚፈጸምበት ጊዜ በፍጥነት እየቀረበ ነው። «ጸጋ ከመጠን ይልቅ በለጠ»፤ ዓለም በኃጢአት ያጣው ሀብት ምንም ቢሆን፥ በጸጋ እጅግ የሚበልጥ አግኝቷል። ሰላም፥ ፍቅርና ደስታ የከበረ መኖሪያ ካገኙበት ከተድላ ገነት መባረራችን እውነት ነው፤ ነገር ግን በኢየሱስ በኩል ከእርሷ የተሻለ ርስት አለን። የሰማይ ሜዳዎች በሚሰጡት ሁልጊዜ አዲስ በሆነ ተድላ ከገነት እርሻዎች ይበልጣሉ፤ የሕይወት ዛፍና ከዙፋኑ የሚወጣው ወንዝም የሰማያዊውን ስፍራ ነዋሪዎች በገነት ከነበረው ደስታ በላይ ደስተኞች ያደርጓቸዋል። በኃጢአት ምክንያት ለሞት የተገዛን መሆናችን እውነት ነው፤ ነገር ግን ጸጋ ስለ እርሱ ስንል በደስታ የምንሞትለትን ዘላለማዊነት አልገለጠምን? በአዳም የጠፋው ሕይወት በክርስቶስ ከመመለስም አልፎ በብዙ ተመልሷል። የመጀመሪያው ልብሳችን በአዳም ተቀደደ፤ ኢየሱስ ግን ነውር ከሌለበት ከተፈጠርንበት ንጽሕና ልብስ እንኳ በዋጋ እጅግ በሚበልጥ መለኮታዊ ጽድቅ አልብሶናል። በኃጢአት ምክንያት ስለ ተዋረደውና ስለ ጐሰቈለው ሁኔታችን እናለቅሳለን፤ ነገር ግን ከመውደቃችን በፊት ከነበርነው ይልቅ አሁን ይበልጥ በደኅንነት እንዳለን፥ እንደ ፍጡራን የነበረን አቋም ሊመካበት ከሚችለው በላይ ከኢየሱስ ጋር ወደ ቅርብ ኅብረት እንደ ገባን ስናስብ ደስ ይለናል። ኢየሱስ ሆይ! አዳም ካጣው ይልቅ የሰፋ ርስት አተረፍህልን፤ ኃጢአታችን ካባከነው ይልቅ በሚበልጥ ባለ ጠግነት ሣጥናችንን ሞላህ፤ ተፈጥሮአዊ ብኵርናችን ሊያስገኝልን ከሚችለው እጅግ በሚበልጥ ክብር ጫንኸን፥ መብቶችንም አደልኸን። በእውነት፥ በእውነት፥ «ጸጋ ከመጠን ይልቅ በለጠ»።

ሁሉ በጸጋ ነው

የእግዚአብሔር ሕዝብ በጸጋ ከተጠሩ በኋላ በክርስቶስ ኢየሱስ ተጠብቀው ይኖራሉ፤ «ለመዳን በእምነት በእግዚአብሔር ኃይል የተጠበቁ» ናቸው፤ የዘላለም ርስታቸውን በኃጢአት እንዲያጡ አይፈቀድላቸውም፤ ፈተናዎች ሲነሡ ግን የሚቋቋሙበት ኃይል ይሰጣቸዋል፤ ኃጢአትም ሲያረክሳቸው እንደ ገና ይታጠባሉ፥ ደግሞም ይነጻሉ። ነገር ግን ልብ በል፤ እግዚአብሔር ሕዝቡን የሚጠብቅበት ምክንያት ሕዝቡ እንዲሆኑ ካደረጋቸው ምክንያት ጋር አንድ ነው—የራሱ ነጻና ሉዓላዊ ጸጋ። በፈተና ሰዓት ከተታደግህ፥ ቆም ብለህ ስለ ራስህ ብለህ እንዳልተታደግህ አስታውስ። መታደግን የሚያስገኝ ምንም ነገር በአንተ ዘንድ አልነበረም። በችግርህ ሰዓት ተመግበህ የሚያስፈልግህም ተሰጥቶህ ከሆነ፥ ይህ ታማኝ የእግዚአብሔር አገልጋይ ስለ ሆንህ ወይም ጸሎተኛ ክርስቲያን ስለ ሆንህ አይደለም፤ በእግዚአብሔር ምሕረት ምክንያት ብቻ፥ ያውም በዚያ ብቻ ነው። ለአንተ ምንም ነገር ሲያደርግ አንተ ለእርሱ በምታደርገው በማናቸውም ነገር አይነሣሣም፤ አንተን የሚባርክበት ምክንያቱ ፈጽሞና ሙሉ በሙሉ በራሱ እቅፍ ጥልቀት ውስጥ ነው። እግዚአብሔር ይባረክ፤ ሕዝቡ ይጠበቃሉ።

«ሞትም ገሃነምም ከቶ አይችሉም ወዳጆቹን ከደረቱ ሊለዩ፤ በፍቅሩ ውድ እቅፍ ውስጥ ለዘላለም ያርፋሉ።»

ግን ለምን? ቅዱሳን ስለ ሆኑ ነውን? ስለ ተቀደሱ ነውን? እግዚአብሔርን በመልካም ሥራ ስለሚያገለግሉ ነውን? አይደለም፤ ነገር ግን እርሱ በሉዓላዊ ጸጋው ስለ ወደዳቸው፥ ስለሚወዳቸውና እስከ መጨረሻም ስለሚወዳቸው ነው። ስለዚህ መዳን ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ሁሉ በጸጋ ነው። እንግዲያስ ክርስቲያን ምንኛ ትሑት ሊሆን ይገባዋል! ለመዳናችን እኛ ያደረግነው ምንም ነገር የለም፤ እግዚአብሔር ሁሉን አድርጎታል። የተቀበልነው የማይገባን ምሕረት ነው። እኛን እንዲያድን የመራው ወሰንና ጥልቀት የሌለው ፍቅሩ ነው፤ አሁንም የሚደግፈን ያው ፍቅርና ምሕረት ነው። ለእርሱ ክብር ይሁን!

ይህስ ኃጢአተኞችን ይቀበላል

«ይህስ ኃጢአተኞችን ይቀበላል»። በኃጢአት የታመምህ ምስኪን ኃጢአተኛ ሆይ፥ ይህ ቃል ለአንተ ምንኛ ጣፋጭ ነው! መልስ ስጥ፥ ለእርሱ መልስ ስጥ፥ እንዲህም በል፦ «እንግዲያስ በእርግጥ አይጥለኝም።» ታላቁን ማስተስሪያውን ትቀበል ዘንድ፥ ጽድቁንም ሁሉ ትለብስ ዘንድ ወደ ጌታዬ እንድትመጣ ላበረታታህ። ልብ በል፤ የምናገራቸው እውነተኛ፥ ትክክለኛ፥ በእርግጥም ኃጢአተኞች የሆኑትን ነው፤ በአጠቃላይ ኑዛዜ ኃጢአተኞች ነን የሚሉትን ብቻ ሳይሆን፥ የጠፋውን፥ የፈረሰውንና ተስፋ ቢስ የሆነውን ሁኔታቸውን የሚሰማቸውን ነው። እነዚህ ሁሉ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲመጡና በእርሱ እንዲድኑ በግልጥና በነጻ ተጋብዘዋል። ምስኪን ኃጢአተኛ ሆይ፥ ና፤ ና። እቀበላለሁ ብሎአልና ና። ፍርሃትህን አውቃለሁ፤ በልብህ እንዲህ እንደምትል አውቃለሁ፦ «ይጥለኛል። ጸሎቴን ባቀርብ አይሰማኝም፤ ወደ እርሱ ብጮኽ ምናልባት ሰማያት እንደ ናስ ይሆናሉ፤ እጅግ ታላቅ ኃጢአተኛ ስለ ሆንሁ ከእርሱ ጋር እኖር ዘንድ ከቶ ወደ ቤቱ አያስገባኝም።» ምስኪን ኃጢአተኛ ሆይ! እንዲህ አትበል፤ እርሱ ትእዛዙን አውጆአል። ይህ አይበቃምን? እርሱ፦ «ወደ እኔም የሚመጣውን ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም» ብሎአል። በዚያ የተስፋ ቃል ላይ አትደፍርምን? እርሱ ተናግሮታል በሚለው እንደዚህ ባለ ጽኑ መርከብ ወደ ባሕር አትወጣምን? ብዙ ጊዜ ለቅዱሳን ብቸኛው መጽናናት ይህ ነበር፤ በዚህ ኖሩ፥ በዚህም ሞቱ። እርሱ ተናግሮታል። ምን! ክርስቶስ እቀበልሃለሁ ብሎ ይነግርሃል፥ ነገር ግን አይቀበልህም ብለህ ታስባለህን? «ወደ እራት ኑ» ብሎ ደጁን ይዘጋባችኋልን? አይደለም፤ ወደ እርሱ ከሚመጡት አንዱንም እንደማያወጣ ከተናገረ፥ ሊያወጣህ እንደማይችል፥ እንደማያወጣህም እርግጠኛ ሁን። እንግዲያስ ና፤ ተናግሮአልና በዚህ መሠረት ፍቅሩን ፈትን። ና፥ አትፍራም፤ አስታውስ፥ ራስህን እንደ ኃጢአተኛ ከተሰማህ ያ ስሜት የእግዚአብሔር ስጦታ ነው፤ ስለዚህ አንተን ለመሳብ ብዙ ወዳደረገው ወደ እርሱ ያለ ሥጋት ልትመጣ ትችላለህ። አዳኝ እንደሚያስፈልግህ ከተሰማህ ክርስቶስ ነው እንዲሰማህ ያደረገው፤ ክርስቶስን ለመከተል ምኞት ካለህ ያን ምኞት የሰጠህ ክርስቶስ ነው፤ እግዚአብሔርን የምትናፍቅ ከሆንህ ያን ናፍቆት የሰጠህ እግዚአብሔር ነው፤ ስለ ክርስቶስ መቃተት ከቻልህ ያስቃተተህ ክርስቶስ ነው፤ ስለ ክርስቶስ ማልቀስ ከቻልህ ያስለቀሰህ ክርስቶስ ነው። አዎን፥ ከቶ ማግኘት እንደማይችል የሚፈራ ነገር ግን ምናልባት ያገኝ ይሆናል ብሎ ተስፋ የሚያደርግ ሰው በሚመኘው ብርቱ ምኞት ብቻ ልትመኘው ብትችል እንኳ—ተስፋ ልታደርገው ብቻ ብትችል እንኳ፥ ያን ተስፋ የሰጠህ እርሱ ነው። ወይ፥ ታዲያ ወደ እርሱ አትመጣምን? ከንጉሡ ስጦታዎች አንዳንዱ አሁን እንኳ በአንተ ላይ አለ፤ ና፥ ያደረገውንም አቅርበህ ተማጸን፤ ይህን አቅርበህ ስትማጸን በእግዚአብሔር ፊት ከቶ የማይሳካ ልመና የለም። ወደ እርሱ ና፤ «ይህስ ኃጢአተኞችን ይቀበላል» ተብሎ የተጻፈው እውነት እንደ ሆነ ታገኛለህ።

ገጽ 1 / 1 · 7 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል