ምዕራፍ 7 · 6 ደቂቃ ንባብ
የክርስቶስ ፍቅር
የክርስቶስን ፍቅር ማወቅ
የእግዚአብሔር ሕዝብ መለያ ምልክት የክርስቶስን ፍቅር ማወቃቸው ነው። ከሞት ወደ ሕይወት የተሻገሩ ሁሉ ያለ አንዳች ልዩነት ሌላውን ምንም ባያውቁ ይህን ተምረዋል። ያልዳኑትም ሁሉ ያለ ልዩነት ሌላ ምንም ቢያውቁ ስለዚህ ምንም አያውቁም። የክርስቶስን ፍቅር ማወቅ፣ ጣፋጭነቱን መቅመስ፣ በመንፈስ ቅዱስ በልባችን እንደ ፈሰሰ በግል፣ በልምምድና በሕያውነት መረዳት የእግዚአብሔር ልጅ ብቻ መብት ነውና። ይህ እንግዳ ሊገባበት የማይችል የታጠረ ስፍራ ነው። ይህ የዱር እርያ እንዳይገባበት በቅጥርና በአጥር እጅግ የተጠበቀ የጌታ አትክልት ነው። በዚህ የሚመላለሱ ጌታ የተቤዣቸው ብቻ ናቸው። እነርሱ፣ እነርሱ ብቻ፣ ፍሬዎቹን ሊለቅሙና በደስታዎቹ ሊረኩ ይችላሉ።
እንግዲያስ ይህ ጥያቄ ምን ያህል አስፈላጊ ይሆናል፦ የክርስቶስን ፍቅር አውቃለሁን? ተሰምቶኛልን? ተረድቼዋለሁን? በልቤ ፈስሶአልን? ኢየሱስ እንደሚወደኝ አውቃለሁን? ክርስቶስ በእውነት እንደ ወደደኝ፣ እንደ መረጠኝና ልቡን በእኔ ላይ እንዳደረገ በሚገልጠው፣ ልቤ በሚያውቀውና ደስ በሚሰኝበት በዚህ ታላቅ እውነት አማካይነት ልቤ ሕያው ሆኖአልን? ተነቃቅቶአልን? ሞቆአልን? ወደ እርሱስ ተስቦአልን?
ነገር ግን እያንዳንዱ የእግዚአብሔር ልጅ የክርስቶስን ፍቅር እንደሚያውቅ እውነት ቢሆንም፣ የእግዚአብሔር ልጆች ሁሉ ይህን ፍቅር በእኩል መጠን እንደማያውቁትም እንዲሁ እውነት ነው።
በክርስቶስ ቤተሰብ ውስጥ ሕፃናት፣ ጎበዞች፣ ብርቱዎችና አባቶች አሉ። በሌላው ነገር ሁሉ እንደሚያድጉና እንደሚገፉ፣ በዚህም በእርግጥ ወደ ፊት ይገፋሉ። በእውነትም የፍቅር መጨመር፣ የክርስቶስን ፍቅር ይበልጥ ፍጹም በሆነ መንገድ መረዳት፣ በጸጋ አድገን እንደ ሆነ ወይም እንዳልሆነ ራሳችንን የምንፈትንበት እጅግ የተሻለና የማይስት መለኪያ ነው። በጸጋ አድገን ከሆነ፣ የክርስቶስን ፍቅር በማወቅና ያንኑ ፍቅር በመመለስ ወደ ፊት መግፋታችን ፍጹም እርግጥ ነው። ብዙዎች በኢየሱስ አምነዋል፤ ከፍቅሩም ጥቂት ያውቃሉ፤ ነገር ግን፣ ወይ! ወደ ውስጠኛው እልፍኝ ገብተው ከክርስቶስ ሮማን የተቀመመውን የወይን ጠጅ እንዲጠጡ ከተደረጉት ከሌሎች ጋር ሲነጻጸር የሚያውቁት በእርግጥ ጥቂት ነው። አንዳንዶች ተራራውን መውጣት ጀምረዋል፤ ከእግራቸው በታች የተዘረጋው ትእይንትም ያማረና እጅግ ውብ ነው፤ ነገር ግን የበሰሉ ቅዱሳን በቆሙበት ስፍራ ቢቆሙ፣ ወደ ምሥራቅና ወደ ምዕራብ፣ ወደ ሰሜንና ወደ ደቡብ ቢመለከቱ፣ ከመታወቅም የሚያልፈውን የክርስቶስን ፍቅር ርዝመቱንና ስፋቱን፣ ጥልቀቱንና ከፍታውን ሁሉ ቢያዩ ኖሮ ዓይኖቻቸው የሚያዩትን የሚያህል ትእይንት አይደለም።
ክርስቶስ ሁለንተናው ያማረ ነው
ቤተ ክርስቲያን ጌታ ኢየሱስን «ሁለንተናው ያማረ» ብላ ስትጠራው በእርሱ የማታደንቀው አንዳች ነገር እንደማታይ ታውጃለች። ዓለም መስቀሉን ሊሳደብና አሳፋሪ ብሎ ሊጠራው ይችላል፤ ለእርስዋ ግን እርሱ የክብር ማእከልና ነፍስ ነው። ትዕቢተኛና ፌዘኛ ሕዝብ ስለ ግርግም አልጋውና ስለ ገበሬ ልብሱ ንጉሡን ሊጥል ይችላል፤ በእርስዋ ዓይን ግን ልዑሉ በዚህ ምስኪን ልብስ ውስጥ የከበረ ነው። ለእርስዋ ከቶ ውበት አይጐድለውም፤ ፊቱ ከቶ አይጠወልግም፤ ክብሩም ከቶ አይጐድፍም። የተወጉትን እግሮቹን በደረትዋ ታቅፋለች፤ ቍስሎቻቸውንም እንደ ዕንቍ ትመለከታለች። ሰነፎች በመስቀሉ አጠገብ ቆመው ለቀልድና ለንቀት ብዙ ርእስ ያገኛሉ፤ እርስዋ ግን ለአክብሮት ስግደትና ወሰን ለሌለው ፍቅር የሚሆን ጽኑ ምክንያት እንጂ ሌላ አታገኝም። በየሹመቱ፣ በየስፍራውና በየዝምድናው ብትመለከተው አንዳች ጕድለት ልታገኝበት አትችልም፤ እንዲያውም የጕድለት ሐሳብ እንኳ ከእርስዋ እጅግ ርቆ ተሰዷል። ፍጹም አምላክነቱንና እንከን የሌለበትን ሰውነቱን ጠንቅቃ ስለምታውቅ፣ ነውር በሌለበት አካሉ ውስጥ ነቀፋ አለ ለሚል ሐሳብ ለአንዲት ቅጽበት እንኳ መጠጊያ አትሰጥም፤ እርሱን የሚያዋርድ ትምህርትን ሁሉ ትጸየፋለች፤ የሚያማምሩትን የፊቱን ገጽታዎች የሚሸፍነውን እጅግ ያጌጠ መጋረጃ እንኳ ትንቃለች፤ አዎን፣ ለክብሩ እጅግ ትቀናለችና ለምስጋናው የማይመሰክርን መንፈስ ሁሉ አትሰማም። ስለ ነውር የሌለበት ፅንሰቱ ወይም እድፍ ስለሌለበት ንጽሕናው የሚነገር አንዳች ፍንጭ ያለው ነቀፋ ነፍስዋን ወደ ቅዱስ ቍጣ ያነሣሣታል፤ ያንንም የስሕተት ትምህርት ፈጥና ትረግመዋለች፤ ያለ ርኅራኄም ታጠፋዋለች። በራስዋ በክርስቶስ ላይ እንደሚነገር ቃል የቤተ ክርስቲያንን ቍጣ ፈጽሞ ያነሣሣ ነገር የለም። ለእውነተኛ አማኞች ሁሉ ይህ ታላቅ ክህደት ነው፤ በቀላሉም ሊታይ የማይችል በደል ነው። ኢየሱስ አንዲት እድፍ ወይም ነውር የሌለበት፣ «ሁለንተናው ያማረ» ነው።
ሆኖም ይህ አሉታዊ ምስጋና፣ ይህ በድፍረት ጕድለትን መካድ፣ የቤተ ክርስቲያንን የፍቅር አድናቆት ሙላት ከመግለጥ እጅግ የራቀ ነው። ኢየሱስ በዓይኖችዋ ፊት በእውነት ያማረ ነው። መልከ መልካም ብቻ ወይም ውብ ብቻ አይደለም፤ ውበቶቹ የሚስቡ ውበቶች ናቸው፤ ክብሮቹም ልብን የሚማርኩ ናቸው። ፍቅር ከእነዚያ «በወተት ከታጠቡ፥ በሥርዓትም ከተቀመጡ የርግብ ዓይኖች» ይመለከታል፤ ከእነዚያ «የሚፈስስ ከርቤ ከሚያንጠባጥቡ እንደ አበባ ካሉ ከንፈሮች» ይፈስሳል፤ «በቢረሌ ፈርጥ በተለበጡ የወርቅ ቀለበቶች በተሞሉ» በእነዚያ እጆችም ላይ ያበራል።
ነገር ግን ይህ የቤተ ክርስቲያን ንግግር የምስጋና ቋንቋ ጫፍ ቢሆንም፣ የመግለጫም ሁሉ ከፍታ እንዲሆን ታስቦ እንደ ነበረ ጥርጥር ባይኖርም፣ ይህች አንዲት ዓረፍተ ነገር እጅግ በጥንቃቄ በሚደረግ ማሰላሰል ብትሰፋ እንኳ ከተሰማው አድናቆት ከትንሽ ቅንጣት የበለጠ ልትገልጥ አትችልም። ይህች ዓረፍተ ነገር እንደ ዔናቅ ልጅ ከሌሎች ሁሉ በላይ ከፍ ብላ ትታያለች፤ ቁመትዋ ግን ከሰማይ የተወለደው ፍቅር የደረሰበትን ታላቅ ከፍታ ሊደርስ አይችልም። የማይነገር ፍቅር ደካማ ምሳሌ ብቻ ናት፤ ከጥልቁ የፍቅር ባሕር ወደ ዳርቻ የተጣለች የተመረጠች ዕንቍ ናት።
የጌታ ዕንቍዎች
ወርቅ አንጥረኞች ከከበረ ነገር ግሩም ቅርጾችን ይሠራሉ፤ አምባርንና ቀለበትን ከወርቅ ያበጃሉ። እግዚአብሔር ግን የከበሩ ነገሮቹን ከተናቀ ነገር ይሠራል፤ ከሚያረክሱ ወንዞች ጥቁር ጠጠሮች መካከል ድንጋዮችን አንሥቶ በማይለወጠው ፍቅሩ የወርቅ ቀለበት ውስጥ ያኖራቸዋል፤ ለዘላለምም በጣቱ ላይ የሚያበሩ ዕንቍዎች ያደርጋቸዋል።
በክርስቶስ ያለ ውበት
የሰዎችን ልብ የሚማርክ ውበት የሚባል ነገር አለ። ጥቂት ያይደሉ ኃያላን ሰዎች በፊቱ ሰግደዋል፤ ክብርም ሰጥተውታል፤ እውነተኛ ውበት ብትፈልግ ግን የኢየሱስን ፊት ተመልከት፤ በዚያ የውበት ሁሉ ድምር አለህና። ከክርስቶስ በቀር በየትም ስፍራ ውበት የለም። አንተ ፀሐይ ሆይ፥ ከእርሱ ጋር ስትነጻጸር አታምርም። አንቺ ውብ ዓለም፣ የክቡር አምላክ ታላቅ ፍጥረት ሆይ፥ ከፊቱ ግርማ ጋር ስትነጻጸሪ ደብዛዛና ጨለምተኛ እድፍ ብቻ ነሽ። ክርስቶስን ስናይ ከዚያ በፊት ውበት ምን እንደ ሆነ ከቶ እንዳላወቅን ለማለት እንገደዳለን። ደመናዎች ሲገፈፉ፣ ከዓይናችን የሚሰውሩት መጋረጃዎች ሲገለጡ፣ በሰፊው ዓለም ውስጥ ካየነውና ከሰማነው ታላቅ ወይም ውብ ነገር አንዳች እንኳ ከእርሱ ጋር ለአንዲት ቅጽበት እንደማይነጻጸር እናገኛለን፤ እርሱ በአንድ ወቅት ከደረቅ መሬት እንደ ወጣ ሥር ታይቶ ነበር፤ ነገር ግን በቅርቡ ሰማይንና ምድርን በብርሃኑ ይሞላል፤ በክብሩም ልብን ሁሉ ደስ ያሰኛል።
ክርስቶስን መውደድ
በቤተ መንግሥት — በሰማይ ቤተ መንግሥት — ወዳጅ አለህን? ጌታ ኢየሱስ ወዳጅህ ነውን? እንደምትወደው ልትናገር ትችላለህን? እርሱስ በፍቅር መንገድ ራሱን ገልጦልህ ያውቃልን? አቤት! «ክርስቶስ ወዳጄ ነው» ማለት መቻል በዓለም ካሉት ነገሮች ሁሉ እጅግ ጣፋጭ ከሆኑት አንዱ ነው። የክርስቶስ ፍቅር የዘመዶችን ፍቅር አያስወጣም፤ ነገር ግን ለፍጡራን ያለንን ፍቅር ይቀድሰዋል፤ እጅግ የጣፈጠም ያደርገዋል። ምድራዊ ፍቅር ጣፋጭ ነው፤ ነገር ግን ማለፉ አይቀርም፤ ሞት በመጣ ጊዜ ከሚጠፋው ሀብት በቀር ሀብት፣ ከሚሞተው ፍቅር በቀር ፍቅር ባይኖርህ ምን ታደርጋለህ? አቤት፣ የክርስቶስ ፍቅር ቢኖርህ! ያንን ይዘህ የሞትን ወንዝ ልትሻገር ትችላለህ፤ በሰማይ እንደ ዕንቍህ ልትለብሰው፣ በእጅህም ላይ እንደ ማኅተም ልታኖረው ትችላለህ፤ ፍቅሩ «እንደ ሞት የበረታ፥ ከመቃብርም የበለጠ ኃያል» ነውና።
የፍቅር ዙሪያ
ክርስቲያን ወሰን የሌለው ፍቅር ያለውን አምላክ ያገለግላልና ርኅራኄው ሁልጊዜ እጅግ ሰፊ ሊሆን ይገባዋል። የፍቅር የከበረ ድንጋይ በጸጋ ወደ ታደሰ ልብ ጥሩ ኩሬ ሲጣል፣ ግልጽ የሆነውን የሕይወት ውኃ ዘወትር እየሰፉ ወደሚሄዱ የርኅራኄ ክበቦች ያንቀሳቅሰዋል፤ የመጀመሪያው ቀለበት ዙሪያው ብዙም ሰፊ አይደለም፤ ቤተ ሰዎቻችንን እንወዳለን፤ ስለ ቤተ ሰዎቹ የማያስብ ማንም ቢሆን ከማያምንም ሰው ይልቅ የሚከፋ ነውና። ነገር ግን የሚቀጥለውን ቀለበት ተመልከት፤ የእምነት ቤተ ሰዎችን እንወዳለን፤ «እኛ ወንድሞችን የምንወድ ስለ ሆንን ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተሻገርን እናውቃለን።» ደግሞም ተመልከት፤ ዘወትር እየሰፋ የሚሄደው ቀለበት እስከ ሐይቁ ዳርቻ ደርሶአል፤ ሁሉንም በክልሉ አጠቃሎአል፤ «ልመናና ጸሎት ምልጃም ምስጋናም ስለ ሰዎች ሁሉ» ሊደረግ ይገባልና። የኢየሱስ ተከታይ ማለት የሰው ወዳጅ ማለት ነው። ክርስቲያን በሙያው ሰውን ወዳጅ፣ በጸጋ ኃይልም ለጋስ ነው፤ የፍቅሩ ስፋት እንደ ሐዘን ግዛት ስፋት ነው፤ መርዳት በማይችልበትም ስፍራ አሁንም ይራራል።
የክርስቶስ ራስን ዝቅ ማድረግ
አዳኙ በሰዎች መካከል በተገለጠ ጊዜ ለራሱ ማዕረግ ለማግኘት ከሕዝቡ መካከል ከፍ ከፍ እንዳለ ሰው ሆኖ አልነበረም፤ ለሕዝቡ በረከትን ሊያመጣ ከሰማያት እንደ ወረደ ሆኖ እንጂ። ያልተማሩና ማንበብ መጻፍ የማይችሉ በእርሱ ውስጥ እጅግ የተሻለ ወዳጃቸውን ያገኛሉ። እርሱ በራሱ ቅንነት ተጠቅልሎ በደለኛውን በፍትሕ ዓይን የሚመለከት ጨካኝ ሕግ ሰጪ አይደለም፤ የቅጣትና የፍዳ ደፋር አዋጅ ነጋሪ ብቻ ወይም የወንጀልና የዓመፅ ርኅራኄ የሌለው ከሳሽም አይደለም። እርሱ የነፍሳችን የዋህ ወዳጅ ነው፤ ተኵላውን ከመግደል ይልቅ በጎቹን ለማዳን የሚወጣ መልካም እረኛ ነው። ሞግዚት ልጅዋን በርኅራኄ እንደምትጠብቅ፣ እርሱም የሰዎችን ነፍሳት ይጠብቃል፤ አባትም ለልጆቹ እንደሚራራ፣ እንዲሁ ኢየሱስ ለምስኪን ኃጢአተኞች ይራራል። ይህም ኃጢአተኞችን ወደ እርሱ ወደ ላይ ከመሳብ ይልቅ ወደ እነርሱ መውረድ ነው፤ በተራራው ራስ ላይ ቆሞ ውጡ ብሎ ማዘዝ ሳይሆን ከተራራው ወርዶ ከእነርሱ ጋር በወዳጅነት መቀላቀል ነው፤ ከፍ ካሉት መሰማሪያዎች በሸለቆዎችና በገደሎች ውስጥ ወዳሉት በጎቹ ወርዶ ይይዛቸው ዘንድ፣ በኃያላን ትከሻዎቹ ላይ ያነሣቸው ዘንድ፣ በንጽሕና ወደሚያጎርባቸው፣ በጸጋ ሁሉ ወደሚባርካቸውና ለሚመጣው ክብር ወደሚጠብቃቸው ስፍራ ይሸከማቸው ዘንድ ነው።
ምዕራፍ 7 ተጠናቋል
የክርስቶስ ፍቅር