በነዶዎች መካከል የተለቀመ
በኀዘንና በመከራ ውስጥ

ምዕራፍ 3 · 11 ደቂቃ ንባብ

በኀዘንና በመከራ ውስጥ

የኀዘን ተግሣጽ

ጌታ ምርጥ ወታደሮቹን የሚያወጣው ከመከራ ደጋማ ቦታዎች ነው።

የፈተና መብቶች

በቀን ጊዜ ከተለመደው የምድር ከፍታ ከዋክብትን ማየት ባይቻልም፣ አንድ ሰው ወደ ጨለማ ጕድጓድ ቢወርድ ወዲያውኑ ይታዩታል ይባላል። በእርግጥም፣ ከእግዚአብሔር የተስፋ ቃሎች ምርጦቹን ቤተ ክርስቲያኑ ብዙውን ጊዜ የምታያቸው እጅግ በጨለመው ፈተናዋ ውስጥ ሳለች መሆኑ እውነት ነው። እግዚአብሔር ልጆቹን ወደ እቶን ባስገባ ቍጥር፣ እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር በእቶኑ ውስጥ እንደሚሆን እርግጥ ነው። ያዕቆብ መልአኩን እንዳየ የማነበው ሊታገል ግድ ወደ ሆነበት ስፍራ ከደረሰ በኋላ ነው፤ ያን ጊዜም ታጋዩ ያዕቆብ ታጋዩን መልአክ አየ። ኢያሱ የእግዚአብሔርን መልአክ ያየው በኢያሪኮ አጠገብ ከደረሰ በኋላ እንጂ ከዚያ በፊት እንደ ሆነ አላውቅም፤ ያን ጊዜም ኢያሱ መልአካዊውን ተዋጊ አየ። አብርሃም ጌታን ያየው በመምሬ ሜዳ እንግዳና ተቅበዝባዥ ከሆነ በኋላ እንጂ ከዚያ በፊት እንደ ሆነ አላውቅም፤ ያን ጊዜም ጌታ እንደ መንገደኛ ሰው ተገለጠለት። እጅግ ደስ የሚያሰኙ ልምምዶቻችንን የምናገኘው ተስፋ በሚያስቆርጡ ኀዘኖቻችን ውስጥ ነው። ራእዩን ለማየት ወደ ፍጥሞ መሄድ አለብህ። የሰማይን ብርሃን በምድር ጥላዎች ሳንዘናጋ የምንመለከትበትን ተገቢ ጨለማ ልናገኝ የምንችለው፣ ከዓለም ብርሃን ሁሉ ተገልሎ ማዕበል በከበበው ባዶ ዓለት ላይ ብቻ ነው።

በደመናው ውስጥ ያለ ብርሃን

«እግዚአብሔርም የኢዮብን ምርኮ መለሰ።» እንግዲህ ረጅሙ ኀዘናችን እንኳ ፍጻሜ አለው፤ ለጥልቁ የመከራችን ጥልቀትም ታች አለው። ክረምታችን ለዘላለም አይኮሳተርም፤ በጋ ፈጥኖ ፈገግ ይላል። ባሕሩ ለዘላለም ወደ ኋላ አይሸሽም፤ ውኆቹ ተመልሰው መምጣታቸው አይቀርም። ሌሊቱ ጨለማውን ለዘላለም በነፍሳችን ላይ አይዘረጋም፤ ፀሐይ ገና ትወጣለች፥ በክንፎቿም ሥር ፈውስ ይሆናል። «እግዚአብሔርም የኢዮብን ምርኮ መለሰ።» እንደዚሁም፣ እግዚአብሔር በኀዘኖቻችን ውስጥ ያሰበውን ዓላማ በፈጸመ ጊዜ ኀዘኖቻችን ፍጻሜ ያገኛሉ። በኢዮብ ጕዳይ ዓላማዎቹ እነዚህ ነበሩ፦ ሰይጣን ይሸነፍ ዘንድ፣ በገዛ መሣሪያው ይከሽፍ ዘንድ፣ ሁሉ ነገር እንደ ፈቀደው በሆነለት ጊዜ ተስፋው ይጨናገፍ ዘንድ። እግዚአብሔር በሰይጣን ግጥሚያ እጁን ዘርግቶ ኢዮብን በአጥንቱና በሥጋው ነክቶት ነበር፤ ነገር ግን ፈታኙ ሊያሸንፈው አልቻለም፤ ይልቁንም በእነዚያ አሸናፊ ቃላት ተገፍቶ ተመለሰ፦ «ቢገድለኝም እንኳ በእርሱ እታመናለሁ።» ሰይጣን በተሸነፈ ጊዜ ውጊያው ያቆማል። ጌታም ደግሞ የኢዮብን እምነት መፈተን አስቦ ነበር። በዚህ የዘንባባ ዛፍ ላይ ብዙ ሸክም ተንጠልጥሎ ነበር፤ እርሱ ግን አሁንም ቀጥ ብሎ አደገ። እሳቱ ብርቱ ነበር፤ ወርቁ ግን አልጐደለም፤ የተበላው ዝቃጩ ብቻ ነበር። ጌታ የነበረው ሌላው ዓላማ የራሱ ክብር ነበር። በእውነትም እጅግ ተከበረ። በሰው ዕጣ ላይ ከወደቀው ከከባዱ መከራ በታች ምስኪኑንና የተጨነቀውን ባሪያውን ባጸናበት ጸጋ አማካይነት፣ እግዚአብሔር ለታላቁ ስሙና ለጥበበኛ ምክሩ የዘላለም ዝና አተረፈ። እግዚአብሔር ሌላም ዓላማ ነበረው፤ እርሱም ደግሞ ተፈጸመ። ኢዮብ በመከራዎቹ ተቀድሶ ነበር። መንፈሱ ለዘበ፤ በውስጡ ተደብቆ የነበረ ራስን የማጽደቅ ዝንባሌ ሁሉ ፈጽሞ ተባረረ። አሁንም የእግዚአብሔር የጸጋ ዕቅዶች ስለ ተፈጸሙ በትሩን ያነሣል፤ የቀለጠውን ብር ከሚነድደው ፍም መካከል ያወጣዋል። እግዚአብሔር በፈቃዱ አያስጨንቅም፣ የሰውንም ልጆች በከንቱ አያሳዝንም፤ ይህንንም ከሚያስፈልገው በላይ ፈጽሞ ባለማስጨነቁ ያሳያል። የጥበቡንና የፍቅሩን ዓላማ ለማገልገል ፈጽሞ ከሚያስፈልገው በላይ ለአንዲት ቅጽበት እንኳ በእቶኑ ውስጥ እንዲቆዩ አይፈቅድም። «እግዚአብሔርም የኢዮብን ምርኮ መለሰ።» እንግዲያስ የተጨነቅህ አማኝ ሆይ፣ ተስፋ አትቍረጥ፤ የኢዮብን ምርኮ የመለሰ እርሱ ምርኮህን በደቡብ እንዳሉ ፈሳሾች ሊመልስ ይችላል። ወይንህን ዳግመኛ ያበቅላል፣ እርሻህም ፍሬዋን እንድትሰጥ ያደርጋል። ደስ ከሚላቸው ጋር ዳግመኛ ትወጣለህ፤ የደስታ መዝሙርም እንደ ገና በከንፈርህ ላይ ይሆናል። ተስፋ መቍረጥ ጨካኝ እግር ብረቱን በነፍስህ ላይ አያጥብቅ። ገና ተስፋ አድርግ፤ በዚህ ነገር ተስፋ አለና። አሁንም ታመን፤ የመተማመኛ ምክንያት አለና። እርሱ ደስ እያለህ ከምርኮ ዳግመኛ ያወጣሃል፤ አንተም ገና ለምስጋናው እንዲህ ብለህ ትዘምራለህ፦ «ልቅሶዬን ወደ ዘፈን ለወጥህልኝ፤ ማቄን ቀድደህ ደስታን አስታጠቅኸኝ።»

ከዝናብ በኋላ የሚያበራ ብርሃን

የክርስቶስ የንጉሥነት አገዛዝ፣ ዳዊት እንደ ገለጸው፣ ለጋውን ሣር ከምድር እንዲበቅል የሚያደርግ «ከዝናብ በኋላ እንደሚያበራ ብርሃን» ነው። ይህንንም ብዙ ጊዜ አይተናል። ከከባድ ዶፍ በኋላ ወይም ከረጅም የዝናብ ወቅት በኋላ ፀሐይ ስትወጣ፣ በሌላ ጊዜ እምብዛም የማናስተውለው ደስ የሚያሰኝ ጥራትና ትኩስነት በአየሩ ውስጥ ይኖራል። ምናልባትም እጅግ ብሩህ የአየር ጠባይ የሚሆነው ዝናቡ እንደ ቆመ፣ ነፋሱ ደመናዎቹን እንደ ጠራረገ፣ ፀሐይም በፈገግታዋ ምድርን ደስ ለማሰኘት ከእልፍኟ ብቅ ስትል ነው። በፈተና የተገራው የክርስቲያን ልብም እንዲሁ ነው። ኀዘን ለዘላለም አይኖርም። ከሚወርደው የመከራ ዶፍ በኋላ ጊዜ እየጠበቀ ጥርት ያለ ብርሃን ሁልጊዜ ይመጣል። የተፈተንህ አማኝ ሆይ፣ ይህን አስብ። ከመከራዎችህ ሁሉ በኋላ የሰንበት ዕረፍት ለእግዚአብሔር ሕዝብ ቀርቶላቸዋል። ይህ ሁሉ ዝናብ ካለፈ በኋላ ወደ ነፍስህ የሚመጣ ጥርት ያለ ብርሃን አለ። የተግሣጽህ ጊዜ አልፎ ሲሄድ፣ ማዕበሉ ተንሰቅስቆ እንቅልፍ እንደ ወሰደው፣ ደመናዎቹ ተቦጫጭቀው እንደ ተበጣጠሱ፣ ፀሐይም በክብር ልብሱ እንዳጌጠ ሙሽራ እንደ ገና ብቅ እንዳለችበት ምድር ይሆንልሃል። ለዚህም ፍጻሜ፣ ለጋውን ቡቃያ ያበቅል ዘንድ ኀዘን ከሚከተለው ደስታ ጋር እንደ ዝናብና እንደ ፀሐይ ብርሃን አብሮ ይሠራል። መከራውና መጽናናቱ በአንድነት ለበጎአችን ይሠራሉ። «የክርስቶስ ሥቃይ በእኛ ላይ እንደ በዛ፥ እንዲሁ መጽናናታችን ደግሞ በክርስቶስ በኩል ይበዛልናልና።» ከዝናብ በኋላ የሚያበራው ብርሃን ቅጠላ ቅጠሎችንና እህሎችን የሚያለመልም አየር ያስገኛል፤ ከኀዘን ወራትም በኋላ የሚመጣው የጌታ ደስታ ነፍስን ፍሬያማ ያደርጋል። በዚህም በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና እውቀት እናድጋለን።

የፈተና ጥቅም

ፈተናዎች ምን እንደ ሆንን ያስተምሩናል፤ አፈሩን ቆፍረው ከምን እንደ ተሠራን ያሳዩናል፤ አንዳንዶቹን ክፉ አረሞች ገለባብጠው ወደ ላይ ያወጧቸዋል።

መስቀል ተሸካሚዎች

የቀሬናው ስምዖን ለኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ተሸካሚ መሆኑ እንዴት ያለ የክብር ስፍራ ነበር! የክርስቶስን መስቀል ስለ እርሱ የመሸከም ክብር እናገኝ ዘንድ በዚያ ባለመገኘታችን ልናለቅስ ምንም አይቀረንም። ነገር ግን ማልቀስ አያስፈልገንም፤ የእርሱ ሕዝብ ከሆንን የምንሸከመው መስቀሉ ይኖረናልና። በዚህ በምድር ላይ መስቀል ተሸካሚዎች ያልነበሩ አክሊል ለባሾች በሰማይ የሉም። ከከበሩት ብዙ ሕዝብ መካከል በምድር ላይ መስቀል ያልነበረው አንድ እንኳ አይገኝም። አማኝ ሆይ፣ መስቀል አለህን? በወንድነት በትከሻህ ተሸከመው! አንሣው! ይህ የክርስቶስ መስቀል ስለ ሆነ መሸከሙ ክብር መሆኑ እንደማይቀር፣ ደግሞም በምትሸከመው ጊዜ እርሱን ስለምትከተል በተባረከ ኅብረት ውስጥ እንዳለህ እያወቅህ፣ በማያመነቱ እርምጃዎችና ደስ በሚለው ልብ መንገድህን ቀጥል።

የክርስቲያን የዕለት መስቀል

አማኝ ሆይ፣ ክርስቶስ ኢየሱስ መስቀሎችህን ይሰጥሃል፤ እነርሱም ተራ ስጦታዎች አይደሉም።

መጽናናት

መጽናናት ከሰማይ ወደ ታች፣ በምድረ በዳ ልቦች ላይ የሚንጠባጠብ ለስላሳ ጠል ነው፤ ከመለኮታዊ ምሕረት ምርጥ ስጦታዎች አንዱ ነው።

መራራት

መራራት በተለይ የክርስቲያን ግዴታ ነው። ክርስቲያን ምን እንደ ሆነ አስብ፤ ሌላው ሰው ሁሉ ራስ ወዳድ ቢሆን እንኳ እርሱ ከራስ ጥቅም ነጻ መሆን እንዳለበት፣ ለችግረኛ የሚራራ ልብ በሌላ በየትም ስፍራ ባይገኝ እንኳ በእያንዳንዱ ክርስቲያን ደረት ውስጥ አንድ ሊገኝ እንደሚገባ ትላለህ። ክርስቲያን «ንጉሥ» ነው፤ ንጉሥ በንፉግነት ለራሱ ብቻ መጨነቅ አይገባውም። እስክንድር፣ ወታደሮቹ በውኃ ጥም ሲሠቃዩ፣ አንድ ወታደር ያቀረበለትን ውድ ውኃ የሞላበትን ሳሕን ገፍቶ፣ ተገዢዎቹ ተጠምተው ሳሉ ንጉሥ መጠጣት አይገባውም፣ ይልቁንም ከእነርሱ ጋር መከራቸውን መካፈል ይመርጣል ካለበት ጊዜ ይበልጥ ንጉሣዊ የሆነበት ጊዜ ነበርን? እግዚአብሔር ነገሥታትና መሳፍንት ያደረጋችሁ እናንተ ሆይ፣ በገዛ ራስ ወዳድነታችሁ ላይ በንጉሣዊ ክብር ንገሡ፤ ለዓለሙ ንጉሣዊ ዘር የሚገባውንም የተከበረ ልግስና አድርጉ። ወደ ዓለም የተላካችሁት የሌሎች አዳኞች እንድትሆኑ ነው፤ ለራሳችሁ ብቻ የምትጨነቁ ከሆነ ግን እንዴት እንዲህ ልትሆኑ ትችላላችሁ? ብርሃናት መሆን የእናንተ ድርሻ ነው፤ ብርሃንስ ጨረሩን ወደ ድቅድቁ ጨለማ ሲበትን ራሱን አይጨርስምን? ስለ ጌታችሁ እንደ ተባለው፣ ስለ እናንተም፦ «ሌሎችን አዳነ፥ ራሱን ሊያድን አይችልም» ተብሎ እንዲነገር ማድረግ የእናንተ ሹመትና መብት አይደለምን?

ሕዝቤን አጽናኑ

እግዚአብሔር ለልጆቹ የሚፈጽሙበትን መንገድ ሳይሰጣቸው አንድም ግዴታ አይሰጣቸውም፤ ሕዝቡን «እንድናጽናና» ሲነግረን፣ የሚጽናኑበት መንገድ እንዳለ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። የእግዚአብሔር ልጅ ሆይ! የታመመውን ልብ የምታጽናናበት ርእስ ጠፍቶብሃልን? ስለ ቀደሙት ዘመናት ጥንታዊ ነገሮች ተናገር፤ በኀዘንተኛው ጆሮ የሚመርጠውን ጸጋ፣ የሚቤዠውን ምሕረትና መለኮታዊውን ፍቅር አንሾካሹክለት። የተጨነቀ ሰው ባገኘህ ጊዜ በነገር ሁሉ ስለ ተዘጋጀው ቃል ኪዳን ንገረው፤ ጌታ በቀደሙት ዘመናት ያደረገውን፣ ረዓብን እንዴት እንደ ቈረጠ ዘንዶውንም እንደ ወጋ ንገረው፤ እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር ያደረገውን ድንቅ ታሪክ ንገረው፤ ቀይ ባሕርን የከፈለ እግዚአብሔር በመከራ ጥልቅ ውኆች መካከል ለሕዝቡ ጐዳና ማበጀት እንደሚችል ንገረው—በማይቃጠለው በሚነድደው ቍጥቋጦ ውስጥ የተገለጠው እርሱ በመከራ እቶን ውስጥ እንደሚደግፈው ንገረው፤ እግዚአብሔር ለተመረጡት ሕዝቡ ያደረጋቸውን ድንቅ ነገሮች ንገረው፤ በዚያ ለማጽናናት የሚበቃ ነገር በእርግጥ አለ፤ ወርቅ አንጥረኛ የማቅለጫ ገንቦውን እንደሚመለከት እግዚአብሔርም እቶኑን እንደሚጠብቅ ንገረው። ያ ካልበቃ፣ ስለ አሁኑ ምሕረቶቹ ንገረው፤ ብዙ ቢሄድበትም ብዙ እንደ ቀረለት ንገረው፤ «በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኵነኔ የለባቸውም» ብለህ ንገረው፤ አሁን በውድ ልጁ ተቀባይነት እንዳገኘ ንገረው፤ አሁን ልጅ ሆኖ በጉዲፈቻ እንደ ተቀበለና አቋሙ አስተማማኝ እንደ ሆነ ንገረው፤ ኢየሱስ በላይ ሆኖ ስለ እርሱ እንደሚማልድ ንገረው፤ የምድር ምሰሶዎች ቢናወጡም እግዚአብሔር መጠጊያችን እንደ ሆነ ንገረው፤ የዘላለም አምላክ እንደማይደክም እንደማይታክትም ለኀዘንተኛው ንገረው። ይህም ካልበቃ ግን፣ ስለሚመጣው ንገረው፤ የዕንቍ በሮችና የወርቅ አደባባዮች ያሉት ሰማይ እንዳለ አንሾካሹክለት፤ እንዲህ ብለህ ንገረው፦

«ቢበዛ ጥቂት ፀሐዮች ቢዞሩ፣ ወደ ውቢቱ ከነዓን ዳርቻ ያደርሱታል፣»

ስለዚህም ኀዘኑን በሚገባ ሊታገሥ ይችላል፤ ክርስቶስ እንደሚመጣ፣ ምልክቱም በሰማያት እንደ ሆነ፣ መምጫውም እንደ ቀረበ፣ በምድር ላይ በቅንነት፣ በሕዝቡም ላይ በጽድቅ ሊፈርድ በቅርቡ እንደሚገለጥ ንገረው። ያም ካልበቃ፣ ስለ ኖረውና ስለ ሞተው ስለዚያ አዳኝ ሁሉን ንገረው፤ ወደ ቀራንዮ ውሰደው፤ የሚደሙትን እጆች፣ ጎንና እግሮች ሥልለት፤ የእሾህ አክሊል ስለ ደፋው የኀዘን ንጉሥ ንገረው፤ የፌዝ ቀይ ልብስ ስለ ለበሰው—ያም ደግሞ የኀዘን ግዛት ሐምራዊ ልብስ ነበረ—ስለ ኀያሉ የሥቃይና የደም ንጉሠ ነገሥት ንገረው፤ እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ እንደ ተሸከመ ንገረው። በዚህም፣ በእግዚአብሔር በረከት፣ ተልእኮህን ትፈጽማለህ፣ ከሕዝቡም አንዱን «ታጽናናለህ»። «ሕዝቤን አጽናኑ፥ ይላል አምላካችሁ።»

የአንጣሪው እሳት

በምድር ላይ በእቶን ውስጥ ያላለፈና ሰባት ጊዜ ያልነጠረ አንድም የብር ቅልጥ በሰማይ ግምጃ ቤት ውስጥ የለም፤ መለኮታዊው ዕንቍ ሠሪ ለልዩ ልዩ ፈተና ያላጋለጠው አንድም ዕንቍ የለም፤ ከቅይጡ ይጠራ ዘንድ እጅግ በሚፋጀው ፍም መካከል ያልቀለጠ አንዲትም የወርቅ ቅንጣት በቤዛው አክሊል ውስጥ የለም። ይህ ለእግዚአብሔር ልጅ ሁሉ የሚደርስ ነው። የጌታ ባሪያ ከሆንህ፣ «ወርቅ እንደሚፈተን» መፈተን አለብህ።

የቀለለ መከራ

ወደ ኢየሱስ አብልጠን ብንመለከት መከራዎቻችን ይህን ያህል ታላቅ ወይም ይህን ያህል አሳዛኝ ሆነው እንደማይታዩን ተረድቻለሁ። በጨለማው የፈተና ሌሊት ወደ ክርስቶስ መመልከት ጥቁሩን ሰማይ ያጠራዋል። ጨለማው እንደ ግብጽ ጨለማ፣ «የሚዳሰስ ጨለማ» ሆኖ ድቅድቅ በሚመስልበት ጊዜ እንኳ፣ ወደ ኢየሱስ መመልከት እንደ ብሩህ የመብረቅ ብልጭታ—እንደ እርሱ ደማቅ፣ ነገር ግን እንደ እርሱ ፈጥኖ የማያልፍ—ይሆናል። በመንገድ ላይ ሳለን ለድካማችን ሁሉ እርሱን አንድ ጊዜ ማየት በሚገባ ይበቃል። ወደ እርሱ መመልከት እጅግ አስጨናቂውን መንገድ ያበራል። በድምፁ ተበረታተን፣ በኃይሉ ጸንተን፣ እርሱ እንዳደረገው እስከ መጨረሻ ለማድረግና መከራ ለመቀበል ተዘጋጅተናል። እናንተ የደከማችሁና የተጨነቃችሁ ክርስቲያኖች ሆይ፣ «ወደ እርሱ ተመልከቱ፥ ብሩሃንም ሁኑ!»

በቅጣት ውስጥ ያለ ፍቅር

የእግዚአብሔር ሕዝብ ብዙ ጊዜ ይቀጣሉ፤ የጌታም እጅ በእነርሱ ላይ ትከብዳለች፤ ሆኖም በቅጣታቸው ውስጥ የአባት ቸርነት፣ በመከራቸውም ውስጥ ወሰን የሌለው ምሕረት አለ። ይህን ምሳሌ ሰምተህ ታውቃለህን? ወደ ሌላና ወደ ተሻለ መስክ ሊመራት የፈለጋት አንዲት በግ የነበረችው አንድ እረኛ ነበረ፤ ጠራት፣ አልመጣችም፤ መራት፣ አልተከተለችም፤ ነዳት፣ እርሷ ግን የገዛ ፈቃዷን ብቻ ተከተለች። በመጨረሻም በልቡ፦ «ይህን አደርጋለሁ» ብሎ አሰበ። ያቺ በግ አጠገቧ አንድ ትንሽ ጠቦት ነበራት፤ እረኛውም ጠቦቱን በእቅፉ አንሥቶ ወሰደው፤ ያን ጊዜ እናቲቱ በግ ደግሞ ተከትላ መጣች። ከአንተም ጋር እንዲሁ ነው፤ እግዚአብሔር አንተን ሲጠራ ቆየ፣ አንተ ግን አልመጣህም፤ ክርስቶስ «ና» አለ፣ አንተ ግን እንቢ አልህ፤ መከራ ላከ፣ አሁንም አልመጣህም፤ በመጨረሻም ልጅህን ወሰደ፣ አንተም ወዲያውኑ መጣህ፤ ያን ጊዜ አዳኙን ተከተልህ። አየህ፣ ይህ በእረኛው በኩል የፍቅር ሥራ ነበር። ያቺን በግ ለማዳን ብቻ ጠቦቱን ወሰደ፤ አዳኙም አንተንም ደግሞ ወደዚያ ያመጣህ ዘንድ ብቻ ልጅህን ወደ ሰማይ ወሰደ። ወደ መንፈሳዊ ሕይወት የሚያደርሱ የተባረኩ መከራዎች፣ የተባረኩ ኪሳራዎች፣ የተባረኩ ሞቶች! አንድ ሰው ከእርሻው መከር ሊሰበስብ ቢወድ በመጀመሪያ እንደሚያርሰው ታውቃለህ። እርሻውም እያጕረመረመ፦ «በፊቴ ላይ ይህ ጠባሳ ስለ ምንድር ነው? ይህ ሻካራ ግልበጣስ ስለ ምንድር ነው?» ሊል ይችላል። ምክንያቱም ሳይታረስ ዘር መዝራት አይቻልም፤ የተሳሉ ማረሻዎች ለመልካም ዘር ትልሞችን ያበጃሉ። ወይም ደግሞ ከተፈጥሮ ሌላ ምሳሌ ውሰድ፦ አንድ ሰው ከዛገ ብረት ቍራጭ ለታላቅ ተዋጊ የሚጠቅም ብሩህ ሰይፍ ሊሠራ ይፈልጋል። ምን ያደርጋል? ወደ እሳት ያስገባዋል፣ ያቀልጠዋልም፤ ዝቃጩን ሁሉ ያስወግዳል፣ ቆርቆሮውንም ሁሉ ያነሣል፤ ከዚያም በመዶሻው ይቀርጸዋል፤ በመስፍ ላይ ክፉኛ ይመታዋል፤ በውጊያ ቀን የማይሰበር መልካም ስለት ሆኖ እስኪወጣ ድረስ በአንዱ እሳት ከዚያም በሌላው ያለዝበዋል። እግዚአብሔር በአንተ ላይ የሚያደርገው ይህ ነው—እባክህ የእግዚአብሔርን የመግቦት መጽሐፍ በስሕተት አታንብበው፤ በትክክል ብታነብበው እንዲህ ይላልና፦ «ይህን ሰው እምረዋለሁ፤ ስለዚህም መታሁት፣ አቈሰልሁትም። እኔ የምወዳቸውን ሁሉ እገሥጻቸዋለሁ እቀጣቸውማለሁ።» እንግዲህ ኑ፥ ወደ ጌታ እንመለስ፤ እርሱ አቍስሎናል፥ እርሱም ይፈውሰናል፤ መትቶናል፥ እርሱም ቍስላችንን ይጠግናል።

መስቀልን መታገሥ

«በፊቱ ስላለው ደስታ በመስቀል ታገሠ።» ያ ደስታ ምን ነበር? ኦ፣ ዓለትን ሊያቀልጥ፣ የብረትንም ልብ ሊያነቃንቅ የሚገባ ሐሳብ ነው፦ በኢየሱስ ፊት የነበረው ደስታ በዋነኛነት እኛን የማዳን ደስታ ነበር። የአባቱን ፈቃድ የመፈጸም—በአባቱ ዙፋን ላይ የመቀመጥ—በመከራ በኩል ፍጹም የመሆን ደስታ እንደ ነበረ አውቃለሁ፤ ቢሆንም አዳኙ መስቀልን የታገሠበት ታላቁና ዋነኛው ምክንያት ይህ እንደ ሆነ አውቃለሁ—እኛን የማዳን ደስታ። ለሌሎች መልካም የማድረግ ደስታ ምን እንደ ሆነ ታውቃለህን? የማታውቅ ከሆነ አዝንልሃለሁ፤ እግዚአብሔር በዚህ ምስኪን ምድረ በዳ ከተዋቸው ደስታዎች ሁሉ ይህ እጅግ ጣፋጭ ከሆኑት አንዱ ነውና። ታውቀዋለህን? ወርቅህ ለድሆች በተሰጠ ጊዜ፣ ብርህም ለጌታ በተቀደሰ ጊዜ፣ ለተራቡት በሰጠኸው ጊዜ፣ ወደ ጎን ሄደህ፦ «የተራቡትን ማብላት፣ የተራቆቱትን ማልበስ፣ ለምስኪኖቹ ለሚሠቃዩ ወገኖቼም መልካም ማድረግ ለእርሱ ተብሎ ሊኖሩለት የሚገባ ደስታ እንደ ሆነ ይሰማኛል» ያልህበት ያ መለኮታዊ ደስታ ፈጽሞ ተሰምቶህ አያውቅምን? እንግዲህ ክርስቶስ የተሰማው ደስታ ይህ ነው፤ እኛን የሰማይ እንጀራ የማብላት ደስታ፣ ምስኪኖችንና የተራቆቱ ኃጢአተኞችን በራሱ ጽድቅ የማልበስ ደስታ፣ ቤት ለሌላቸው ነፍሳት ቤት የማዘጋጀት ደስታ፣ ከሲኦል ወህኒ እኛን የማዳንና የሰማይን የዘላለም ተድላ የመስጠት ደስታ ነበር። ኃጢአተኞችን ያድን ዘንድ እንዲህ መስቀልን እንዲታገሥና ነውርን እንዲንቅ የመራውን የፍቅሩን ታላቅነት ተመልከት። በእውነት የክርስቶስ ፍቅር «ከመታወቅ የሚያልፍ» ነው! ክርስቲያኖች ሆይ! ክርስቶስ እናንተን የማዳን ደስታ ብሎ ይህን ሁሉ ከታገሠ፣ እናንተ ስለ ክርስቶስ ማንኛውንም ነገር መሸከም ወይም መቀበል ታፍራላችሁን? በእርግጥ እንዲህ የወደደንን እርሱን መውደዳችን ስለ እርሱ ብለን ሁሉን ለመታገሥ ፈቃደኞች ሊያደርገን ይገባል። ክርስቶስን በመከተላችሁ ኪሳራ—ክብርን፣ ማዕርግን፣ ሀብትን ማጣት—እንደሚደርስባችሁ ይሰማችኋልን? ክርስቲያን በመሆናችሁ ፌዝና ነቀፋ እንደሚመጣባችሁ ይሰማችኋልን? እርሱ ፈቀቅ ሳይል መስቀልን ታግሦ ነውርን ናቀ፤ እናንተስ በእነዚህ ትናንሽ ነገሮች ምክንያት ፈቀቅ ትላላችሁን? አይደለም፤ በእግዚአብሔር ጸጋ እያንዳንዱ ክርስቲያን እንዲህ ይበል፦

«አሁን ለስሙ ባለኝ ፍቅር፣ ትርፌ የነበረውን ኪሳራ እቈጥራለሁ፤ የቀድሞ ትዕቢቴን ነውሬ እላለሁ፣ ክብሬንም በመስቀሉ ላይ እቸነክራለሁ።»

«ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነው።» በሕይወቴ የእርሱ እሆናለሁ፤ በሞቴም የእርሱ እሆናለሁ። ለክብሩ እኖራለሁ፣ በሙሉም አገለግለዋለሁ። ስለ ስሙ መከራ ልቀበል የተገባኝ ሆኜ ብቈጠር ደስ እያለኝ መስቀሌን አንሥቼ እከተለዋለሁ።

በኀዘን ውስጥ ያለ ጣፋጭነት

የመከራን ወራት መለስ ብለህ ስትመለከት፣ ፈተናዎቹ ቢኖሩም፣ በልብህ ውስጥ ያልተለመደ ሰላምና ደስታ ያገኘህባቸው ጊዜያት እንደ ነበሩ አይሰማህምን? በኀዘን በኩል ወደ እኛ የሚመጣ ጣፋጭ ደስታ አለ። የኀዘን መራራ የወይን ጠጅ በመላው ሰውነት ላይ እንደ ብርቱ መድኃኒት ይሠራል። የብልጽግና ጣፋጭ ጽዋ ብዙ ጊዜ በአፍ ውስጥ ምሬትን ይተዋል፤ የመከራ መራራ ጽዋ ግን በተቀደሰ ጊዜ ሁልጊዜ በአፍ ውስጥ ጣፋጭ ጣዕምን ይተዋል። በኀዘን ውስጥ ደስታ አለ። አውታሮቹ ሁሉ በላሉበትና በተበጠሱበት በዚህ በገና ውስጥ ዜማ አለ። ከድምፀ ብርቱው መለከት ፈጽሞ የማናገኛቸው፣ ከዚህ የኀዘን ክራር የምንሰማቸው ጥቂት ድምፆች አሉ። ከደስታ መዝሙር ፈጽሞ የማናገኘውን ልስላሴና ዜማ ከኀዘን ዋይታ እናገኛለን። ይህንንስ በመከራችን ውስጥ ወደ እግዚአብሔር ቀርበን የምንኖር በመሆናችን ልናብራራው አይገባንምን? ደስታችን በባሕሩ ዳርቻ ላይ እንደሚላተም ማዕበል ነው—ወደ ምድር ይወረውረናል። ኀዘኖቻችን ግን ወደ መለኮት ታላቅ ጥልቀት መልሶ እንደሚስበን እንደዚያ ወደ ኋላ እንደሚመለስ ማዕበል ናቸው። ያ ወደ ኋላ የሚመለስ ማዕበል፣ ያ የብልጽግናችን መጕደል፣ ወደ አባታችንና ወደ አምላካችን ዳግመኛ ባይመልሰን ኖሮ፣ በባሕሩ ዳርቻ ላይ ተጥለን በደረቅ መሬት ላይ በቀረን ነበር። የተባረከ መከራ! ወደ ምሕረት ዙፋን አመጣን፤ ለጸሎት ሕይወትን ሰጠ፤ ፍቅርን አቀጣጠለ፤ እምነትን አበረታ፤ ክርስቶስን ከእኛ ጋር ወደ እቶኑ አመጣ፤ ከዚያም ከቀድሞው ይልቅ በደስታ ከክርስቶስ ጋር እንድንኖር ከእቶኑ አወጣን።

ገጽ 1 / 1 · 11 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል