በነዶዎች መካከል የተለቀመ
መንፈስ ቅዱስ

ምዕራፍ 19 · 2 ደቂቃ ንባብ

መንፈስ ቅዱስ

መለኮታዊ ትምህርት

በመከራ ጥልቀት ውስጥ የጸጋን በቂነት እንማራለን። በመከራ ውስጥ እጅግ ጠቃሚ የሆኑትን የጸጋ ትምህርቶች የተማሩ፣ የጸጋ ስንቅ ምን ያህል የበዛ እንደ ሆነ በዚያው የፈተኑ፣ የጸጋም ድል እርግጠኛ መሆኑን በዚያው የተገነዘቡ ሰዎች «በመከራችን ደግሞ እንመካለን» ቢሉ ተገቢ ነው። ወታደሮች ሁሉ የጦርነትን ሐሳብ ይወዱ እንደ ሆነ አላውቅም፤ አንዳንዶች ይወዳሉ፤ ለዘመቻ የሚናፍቁ ብዙዎች አሉ። ዝቅተኛ ማዕረግ ያለው መኮንን ስንት ጊዜ እንዲህ እያለ አጕረምርሟል፦ «ዕድገት የለም፤ ከፍ የማለት ተስፋ የለም፤ ክብር የለም፤ ጦርነት ቢኖር ኖሮ እንደሚገኘው ያለ የምርኮ ገንዘብ የለም። ወደ መድፉ አፍ መሮጥ ብንችል ኖሮ፣ በማዕረግ ከፍ የማለት ተስፋ በፊታችን በኖረ ነበር።» የባሩድን ሽታ ፈጽሞ የማያውቁ ሰዎች በደረታቸው ላይ የሚሰቅሉት ሜዳሊያ ጥቂት ነው። ሰዎች የጀግንነት ዘመን ብለው የሚጠሩት የኔልሰንና የትራፋልጋር ዘመን አልፏል፤ ስለዚህም እግዚአብሔርን እናመሰግናለን። ቢሆንም ከቀድሞ ዘመቻዎቻችን የቀሩ ቅሪቶች ሆነው አሁንም በሆስፒታሎቻችን ውስጥ እንደሚገኙት ያሉ ጀግኖች አሮጌ አርበኞች ከዚህ ዘመን ይወጣሉ ብለን አንጠብቅም። አይደለም፣ ወንድሞች ሆይ፣ ወደ ፊት መግፋት ከፈለግን መከራ ሊደርስብን ግድ ነው። ወጣቶች በግሪንዊች ትምህርት ቤት በመማርና በደረቅ ምድር ላይ ምሰሶ በመውጣት ብቻ የባሕር ኃይል ዕጩ መኮንኖች አይሆኑም፤ ወደ ባሕር መውጣት አለባቸው። እኛም በብዙ ውኃ ላይ ሥራችንን መሥራት አለብን፤ የእግዚአብሔርን ሥራና በጥልቁ ያለውን ተአምራቱን ማየት ከፈለግን በማዕበል ጊዜ በእውነት በመርከቡ ወለል ላይ መቆም አለብን። የእግዚአብሔርን ቀኝ እጅ የማዳን ኃይል ማወቅ ከፈለግን ከንጉሥ ዳዊት ጋር ጎን ለጎን ቆመን መሆን አለብን፤ አንበሳውን ለመግደል ወደ ጕድጓዱ ወርደን፣ ወይም በስምንት መቶዎቹ ላይ ጦር አንሥተን መሆን አለብን። ተጋድሎ ልምድን ያመጣል፤ ልምድም በሌላ በምንም መንገድ ሊገኝ የማይችለውን በጸጋ ማደግን ያመጣል።

የመንፈስ ሥራ

በውስጣችን ካለው መንፈስ ቅዱስ ተለይቶ በመስቀል ላይ ያለው ክርስቶስ ለእኛ ምንም ጥቅም እንደሌለው ሁልጊዜ እናስታውስ። የመንፈስ ጣት ደሙን በሕሊናችን ላይ ካልቀባው ያ ደም የሚፈሰው በከንቱ ነው፤ መንፈስ ቅዱስ በዙሪያችን ካልጠቀለለውና ውድ በሆኑ እጥፋቶቹ ካላለበሰን ያ የጽድቅ ልብስ የተሠራው በከንቱ ነው። መንፈስ ጽዋውን አቅርቦ ወደ ከንፈራችን እስኪያደርሰው ድረስ የሕይወት ውኃ ወንዝ ጥማችንን ሊያረካ አይችልም። ሙታን ነፍሳት ሆነን እስካለን ድረስ በእግዚአብሔር ገነት ውስጥ ያሉት ነገሮች ሁሉ ፈጽሞ ደስታ ሊሰጡን አይችሉም፤ ያ ሰማያዊ ነፋስ መጥቶ በሕይወት እንድንኖር እፍ እስኪልብን ድረስ ደግሞ ሙታን ነን። ለእግዚአብሔር ወልድ ያለብንን ያህል ለእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም ባለ ዕዳዎች ነን ለማለት አናመነታም። በእርግጥም ከመለኮታዊው ሥላሴ አንዱን አካል ከሌላው ማስቀደም መሞከር ታላቅ ኃጢአትና በደል ነው። አንተ አብ ሆይ፣ ለእኛ ያለው ጸጋ ሁሉ፣ ፍቅርና ምሕረት ሁሉ ምንጭ ነህ። አንተ ወልድ ሆይ፣ የአባትህ ምሕረት የሚፈስበት መስመር ነህ፤ ያለ አንተም የአባትህ ፍቅር ወደ እኛ ፈጽሞ ሊፈስ ባልቻለ ነበር። አንተም መንፈስ ሆይ፣ ከምንጩ ራስ ከአብ በመስመሩ በክርስቶስ በኩል የሚፈሰውን መለኮታዊ በረከት እንድንቀበል የምታስችለን አንተ ነህ፤ ይህም በረከት በአንተ አማካይነት ወደ ልባችን ይገባል፣ በዚያም ይኖራል፣ የከበረ ፍሬውንም ያፈራል። እንግዲህ መንፈስን ከፍ ከፍ አድርጉት። በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ ሰማያዊ ሐሳብ፣ የተቀደሰ ሥራ ወይም ለእግዚአብሔር የተለየ ተግባር በመንፈስ ቅዱስ በእኛ ውስጥ ያልተሠራ ከቶ ኖሮ አያውቅም።

ገጽ 1 / 1 · 2 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል