ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች የተጻፈው የቀሌምንጦስ የመጀመሪያ መልእክት
የትሕትና ምሳሌ የሆነው ዳዊት

ምዕራፍ 18 · 1 ደቂቃ ንባብ · 1 ደቂቃ ማዳመጥ

የትሕትና ምሳሌ የሆነው ዳዊት

ነገር ግን እንዲህ ያለ ምስክርነት ስለ ተሰጠው፣ እግዚአብሔርም፦ «እንደ ልቤ የሆነውን ሰው፥ የእሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ፤ በዘላለም ምሕረትም ቀባሁት» ስላለለት ስለ ዳዊት ምን እንላለን? ይህ ሰው ራሱ ግን እግዚአብሔርን እንዲህ ይለዋል፦ «አቤቱ፥ እንደ ታላቅ ምሕረትህ ማረኝ፤ እንደ ርኅራኄህም ብዛት መተላለፌን ደምስስ። ከበደሌ አብዝተህ እጠበኝ፥ ከኃጢአቴም አንጻኝ። እኔ በደሌን አውቃለሁና፥ ኃጢአቴም ሁልጊዜ በፊቴ ነውና። አንተን ብቻ በደልሁ፥ በፊትህም ክፉ አደረግሁ፤ በቃልህ ትጸድቅ ዘንድ ወደ ፍርድ በገባህም ጊዜ ትረታ ዘንድ። እነሆ፥ በመተላለፍ ተፀነስሁ፥ እናቴም በኃጢአት ፀነሰችኝ። እነሆ፥ እውነትን ወደድህ፤ የተሰወረውንና የተሸሸገውን የጥበብ ነገር አሳየኸኝ። በሂሶጵ ትረጨኛለህ፥ እኔም እነጻለሁ፤ ታጥበኛለህ፥ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እሆናለሁ። ሐሤትንና ደስታን ታሰማኛለህ፤ የተዋረዱ አጥንቶቼ ሐሤት ያደርጋሉ። ፊትህን ከኃጢአቴ መልስ፥ በደሌንም ሁሉ ደምስስ። አምላክ ሆይ፥ ንጹሕ ልብን በውስጤ ፍጠር፥ የቀናውንም መንፈስ በውስጤ አድስ። ከፊትህ አትጣለኝ፥ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ አትውሰድ። የማዳንህን ደስታ መልስልኝ፥ በሚገዛ መንፈስህም አጽናኝ። ለዓመፀኞች መንገድህን አስተምራለሁ፥ ኃጢአተኞችም ወደ አንተ ይመለሳሉ። አምላክ ሆይ፥ የመድኃኒቴ አምላክ፥ ከደም አድነኝ፤ አንደበቴም በጽድቅህ ሐሤት ያደርጋል። አቤቱ፥ አፌን ትከፍታለህ፥ ከንፈሮቼም ምስጋናህን ያወራሉ። መሥዋዕትን ብትወድድስ በሰጠሁህ ነበር፤ በሚቃጠል መሥዋዕት ደስ አይልህም። ለእግዚአብሔር [የሚያስደስተው] መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፤ የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ እግዚአብሔር አይንቅም።»

ገጽ 1 / 1 · 1 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል
ቀዳሚ ቀጣይ