የቄስ ቻርልስ ጂ. ፊኒ ማስታወሻዎች
የመጀመሪያው የእንግሊዝ ጉብኝት

ምዕራፍ 28 · 19 ደቂቃ ንባብ · 24 ደቂቃ ማዳመጥ

የመጀመሪያው የእንግሊዝ ጉብኝት

እንግሊዝን እንድጎበኝና በዚያች አገር መነቃቃትን ለማስፋፋት እንድሠራ ተደጋጋሚና አጣዳፊ ግብዣ ስለ ደረሰኝ፥ በ1849 መጸው ከባለቤቴ ጋር* በመርከብ ተሳፈርሁ፤ ማዕበል የበዛበትን ጉዞ ካለፍን በኋላም በኖቬምበር መጀመሪያ ሳውዝሃምፕተን ደረስን። በዚያም ሃንቲንግተንና ሴንት አይቭስ በሚባሉት ሁለት የገበያ ከተሞች መካከል በምትገኘው ሃውተን በምትባል መንደር ያለችውን ቤተ ክርስቲያን እረኛ አገኘን። ወደ ፊት ብዙ ጊዜ የምናገርለት እጅግ ቸር ሰው የሆነ አቶ ፖቶ ብራውን የተባለ ሰው እረኛውን አቶ ጄምስ ሃርኮርትን እኛን ሳውዝሃምፕተን ድረስ ሄዶ እንዲቀበለን ልኮት ነበር።

አቶ ፖቶ ብራውን በወላጆቹም ሆነ በአስተዳደጉ ኩዌከር ነበር። እርሱና አንድ ሸሪኩ በዱቄት ወፍጮ ሥራ ተሰማርተው ነበር፤ በሴንት አይቭስ የሚገኘው የኢንዲፔንደንቶች ጉባኤ አባላትም ነበሩ። በአካባቢያቸው የነበረውን ሁኔታ ሲመለከቱ እጅግ ተጨነቁ። በእንግሊዝ «ቤተ ክርስቲያን» ተብላ የምትጠራው ለነፍሳት መዳን የምታከናውነው እጅግ ጥቂት እንደ ሆነ ታያቸው። ለድሆች ትምህርት ከቤተ ክርስቲያኒቱ ትምህርት ቤቶች ሌላ ምንም ትምህርት ቤት አልነበረም፤ አብዛኛው ሕዝብም እጅግ ተዘንግቶ ነበር። ብዙ ከጸለዩና እርስ በርሳቸው ከተማከሩ በኋላ፥ በሚኖሩባት መንደርና በዙሪያቸው ባሉ መንደሮች የሚገኙትን ልጆች ለማስተማር እርምጃ ለመውሰድ፥ ይህንንም ተጽዕኖ በተቻላቸው መጠን ለማስፋፋት ተስማሙ። እንዲሁም ሀብታቸውን በተሻለው መንገድ በመጠቀም አምልኮን ለማቋቋምና ከመንግሥት ቤተ ክርስቲያን ነጻ የሆኑ አብያተ ክርስቲያናትን ለመገንባት ተስማሙ።

*ፊኒ ሁለተኛ ሚስቱ አድርጎ ያገባው የሮቼስተሯን ወይዘሮ ኤሊዛቤት ኤፍ. አትኪንሰንን ነበር።

ይህ ሥራ ከተጀመረ ብዙም ሳይቆይ የአቶ ብራውን ሸሪክ ሞተ። ሚስቱም ከእርሱ በፊት ሞታ እንደ ነበር አምናለሁ፤ ሸሪኩም ብዙ ወንዶችና ሴቶች ልጆች የነበሩበትን ቤተሰቡን ለአቶ ብራውን ወንድማዊ እንክብካቤ አደራ ሰጠ፤ አቶ ብራውንም ልጆቹን በአጎራባች መንደር ለምትኖር አስተዋይ ለሆነች አንዲት መበለት እንድታሳድጋቸው ሰጣቸው። የአቶ ብራውን ሸሪክ በሞቱ ጊዜ ያቀዱትን ሥራ ቸል እንዳይል፥ ነገር ግን በብርታትና በቅን ዓይን እንዲገፋበት ለመነው። የአቶ ብራውን ልብ በሥራው ላይ ነበር። ሸሪኩ ለልጆቹ ብዙ ሀብት ትቶላቸው ነበር። አቶ ብራውን ራሱ የነበሩት ሁለት ልጆች ብቻ ነበሩ፤ ሁለቱም ወንዶች ነበሩ። እርሱ ቀላል ኑሮ የሚኖር ሰው ነበር፤ ለራሱም ሆነ ለቤተሰቡ የሚያወጣው ገንዘብ እጅግ ጥቂት ነበር። በሚኖርባት መንደር አንድ መምህር ቀጠረ፤ ለሕዝብ አምልኮም በዚያ የጸሎት ቤት ሠራ። በዚያ እንደ አገልጋይ እንዲሠራ ጽንፈኛ የካልቪናዊነት አመለካከት የነበረውን አንድ ሰው ጠሩ፤ በዚህም ምክንያት ያ ሰው ዓመት ከዓመት ቢሠራም አቶ ብራውን የጠበቀውን የሚያሟላ ምንም ፍሬ አልታየም።

አቶ ብራውን ስለ መልካም ፍሬ መጥፋት ከአገልጋዩ ጋር ብዙ ጊዜ ይነጋገር ነበር። ደመወዙን ይከፍለው ነበር፤ በሰንበት ትምህርት ቤቶች፥ በመምህራንና በሠራተኞች አማካይነት ሃይማኖትን ለማስፋፋትም ገንዘቡን በልዩ ልዩ መንገድ ያወጣ ነበር፤ ነገር ግን የሚለወጡት ጥቂቶች ነበሩ፤ ወይም ማንም አይለወጥም ነበር። ይህንን ጉዳይ በአገልጋዩ ፊት ደጋግሞ ስላቀረበ፥ በመጨረሻ አገልጋዩ እንዲህ ሲል መለሰ፦ «አቶ ብራውን፥ ነፍሳትን እለውጥ ዘንድ እኔ እግዚአብሔር ነኝን? ወንጌልን እሰብክላቸዋለሁ፤ እግዚአብሔርም አይለውጣቸውም፤ ታዲያ ተጠያቂው እኔ ነኝን?» አቶ ብራውንም፦ «አንተ እግዚአብሔር ሁን ወይም አትሁን፥ እኛ ግን የሚለወጡ ሰዎች ሊኖሩን ይገባል። ሕዝቡ መለወጥ አለበት» ብሎ መለሰለት። ስለዚህ ይህ አገልጋይ ተሰናበተ። ቄስ ጄምስ ሃርኮርት ተቀጠረ። አቶ ሃርኮርት ክፍት ቁርባን የሚቀበል ባፕቲስት፥ ተሰጥዖ ያለው ሰው፥ ልብን የሚያነቃቃ ሰባኪና ለነፍሳት በትጋት የሚሠራ ሰው ነው። በእርሱ ስብከት ሰዎች መለወጥ ጀመሩ፤ ሥራውም ተስፋ ሰጪ በሆነ መንገድ ቀጠለ። ትንሿ ቤተ ክርስቲያናቸው በቍጥርም በእምነትም አደገች፤ እርሾውም ቀስ በቀስ ቢሆንም በግልጽ በሚታይ ሁኔታ በየአቅጣጫው እየተስፋፋ ነበር።

ብዙም ሳይቆዩ ሥራቸውን ወደ አጎራባች መንደሮች አስፋፉ፤ መልካም ውጤትም አገኙ። ነገር ግን አሁንም ቢሆን የሃይማኖት መነቃቃትን እንዴት እንደሚያስፋፉ አያውቁም ነበር። በእርሱ ኃላፊነት ሥር የተተዉት የሸሪኩ ልጆች አድገው ጎልማሶችና ቈነጃጅት ሆነው ነበር፤ ነገር ግን አልተለወጡም ነበር። ሦስት ሴቶችና ሦስት ወንዶች ልጆች ነበሩ፤ የተትረፈረፈ ሀብት ያለው መልካም ቤተሰብ ነበር፤ ነገር ግን ያልተለወጡ ነበሩ። አቶ ብራውን በዚያ ካውንቲ እጅግ የሚያስደስቱና ተሰሚነት ያላቸው ብዙ ወዳጆች ነበሩት፤ ለእነርሱም መዳን እጅግ ጥልቅ ጭንቀት ነበረው። የሟቹ ሸሪኩ ልጆች እንዲለወጡም እጅግ ይጨነቅ ነበር። ልጆቹን ለማስተማር በቤቱ መምህር ቀጥሮ ነበር፤ ከአጎራባች ከተሞችም የተከበሩ ቤተሰቦች ልጆች የሆኑ ቍጥራቸው ቀላል ያልሆነ ወጣቶች ከልጆቹ ጋር ተምረው ነበር። በካውንቲው ልዩ ልዩ ክፍሎች የሚኖሩ ወዳጆቹ ልጆች የሆኑት ወጣቶች የተጋበዙበት ይህ ትንሽ የቤተሰብ ትምህርት ቤት በአቶ ብራውንና በእነዚህ ቤተሰቦች መካከል ጠንካራ የመተሳሰብ ማሰሪያ ፈጥሮ ነበር። የአቶ ሃርኮርት ድካም በሆነ ምክንያት እነዚህን ቤተሰቦች አልደረሰም ነበር። በድሆችና በዝቅተኛ መደቦች መካከል ይሳካለት ነበር፤ ቀናተኛና ራሱን የሰጠ ነበር፤ ወንጌልንም ይሰብክ ነበር። አቶ ብራውን እንዳለው፦ «እርሱ የኢየሱስ ክርስቶስ ብርቱ አገልጋይ ነበር።» ነገር ግን አቶ ብራውን በተለይ በልቡ ይዟቸው የነበሩትን የዚያን ዓይነት ሰዎች ለመድረስ ልምድ ይጎድለው ነበር። እነዚህ ወንድሞች በጉዳዩ ላይ ብዙ ጊዜ ይነጋገሩ ነበር፤ እነዚያን ሰዎች እንዴት ሊደርሱአቸውና ወደ ክርስቶስ ሊስቡአቸው እንደሚችሉም ይጠያየቁ ነበር። አቶ ሃርኮርት የሚችለውን ሁሉ እንዳደረገ፥ ሌላ ነገር ካልተደረገ በቀር እነዚያ ሰዎች ጨርሶ ሊደረስባቸው እንደሚችሉ እንደማይታየው ተናገረ።

እርሱ የመነቃቃት ትምህርቶቼን አንብቦ ነበር፤ በመጨረሻም መጥቼ ከእነርሱ ጋር እሠራ እንደ ሆነ ለማየት ይጽፍልኝ ዘንድ ተገቢ መሆኑን ለአቶ ብራውን ሐሳብ አቀረበለት። ይህም ከአቶ ብራውን እንድጎበኛቸው እጅግ አጥብቆ የቀረበ ልመና እንዲደርሰኝ ምክንያት ሆነ። ከሌሎች ብዙ ሰዎችና ከአንዳንድ አገልጋዮችም ጋር ተነጋገረ፤ ይህም እንግሊዝን እንድጎበኝ አጥብቀው የሚጋብዙ ልዩ ልዩ ደብዳቤዎች እንዲደርሱኝ ምክንያት ሆነ።

መጀመሪያ ላይ እነዚህ ደብዳቤዎች ብዙም አልነኩኝም፤ ወደ እንግሊዝ እንዴት እንደምሄድ አይታየኝም ነበርና። ውሎ አድሮ ግን ቢያንስ ለተወሰነ ጊዜ ቤቴን ትቼ እንድሄድ መንገዱ የተከፈተልኝ መሰለ፤ ቀደም ብዬ እንደ ተናገርሁትም በ1849 መጸው እኔና ባለቤቴ ወደ እንግሊዝ ሄድን። እዚያ ደርሰን ጥቂት ቀናት ካረፍን በኋላ በመንደሩ የጸሎት ቤት ሥራዬን ጀመርሁ። አቶ ብራውን በሁሉም ረገድ አስደናቂ ሰው መሆኑን ብዙም ሳይቆይ ተረዳሁ። ኩዌከር ሆኖ ቢያድግም በአመለካከቱ ፍጹም ሁሉን አቀፍ ነበር፤ በገለልተኛ መንገድም በዙሪያው ላሉ ሰዎች መዳን በቀጥታ ይሠራ ነበር። ሀብት ነበረው፤ ንብረቱም ዘወትርና በፍጥነት እየጨመረ ነበር። የእርሱ ታሪክ ብዙ ጊዜ ይህንን ምሳሌ አሳስቦኛል፦ «የሚበትን አለ፥ ይጨመርለትማል፤ ከሚገባው በላይ የሚነፍግ አለ፥ ወደ ድህነትም ያዘነብላል።» ለሃይማኖታዊ ዓላማዎች ገንዘቡን እንደ ልዑል ያወጣ ነበር፤ ባወጣ መጠንም የሚያወጣው ይበዛለት ነበር።

እኛ እዚያ በነበርንበት ጊዜ ቤቱን ጠዋት፥ ቀትርና ማታ ክፍት አደረገ፤ በቅርብም በሩቅም ያሉ ወዳጆቹን መጥተው እንዲጠይቁት ጋበዘ። እጅግ ብዙ ሆነው መጡ፤ ስለዚህ ማእዱ በየምግቡ ማለት ይቻላል፥ እኔ ከእነርሱ ጋር እንድነጋገርና እነርሱም ስብሰባዎቻችንን እንዲካፈሉ በተጋበዙ ልዩ ልዩ ሰዎች ይከበብ ነበር።

ወዲያውኑ መነቃቃት ተጀመረ፤ በሕዝቡም መካከል ተስፋፋ። የሸሪኩ ልጆች ብዙም ሳይቆዩ በሃይማኖት ጉዳይ ተሳቡ፤ ወደ ክርስቶስም ተለወጡ። ሥራው ከአጎራባች መንደሮች በመጡት ሰዎች መካከልም ተስፋፋ። ቃሉን ሰሙ፤ በደስታም ተቀበሉ። አቶ ብራውን መለወጣቸውን ሲናፍቅና ሲጸልይላቸው በነበሩት በልዩ ወዳጆቹ መካከል ሥራው እጅግ ሰፊና ጥልቅ ከመሆኑ የተነሣ፥ እኔ ከዚያ ከመሄዴ በፊት፥ ሁሉም እንደ ተለወጡ፥ ይጨነቅላቸውና እንዲለወጡ ይጸልይላቸው ከነበሩት መካከል ጌታ አንዳቸውንም እንዳልተወ ተናገረ።

በአገሩ ሁሉ ተበትነው የሚኖሩት የእነዚህ በርካታ ሰዎች መለወጥ፥ በሚታወቁበት ስፍራ ሁሉ እጅግ መልካም ስሜት አሳደረ። በሃውተን የነበረው የአምልኮ ቤት ትንሽ ነበር፤ ነገር ግን በእያንዳንዱ ስብሰባ ጢም ብሎ ይሞላ ነበር፤ የአቶ ብራውንና የባለቤቱ ራስን መስጠትና ትጋት እጅግ የሚያስደስትና ልብን የሚነካ ነበር። እንግዳ ተቀባይነታቸው ወሰን ያለው አይመስልም ነበር። መምህራቸው ሃይማኖተኛ ሰው ነበር፤ በየቀኑና በየምግቡ ማለት ይቻላል ገብቶ ከእኛ ጋር ይቀመጥና በውይይቱ ይደሰት ነበር። ከአጎራባች ከተሞች፥ ብዙ ማይል ርቀው ከሚገኙ ስፍራዎች የሚመጡ የተከበሩ ሰዎች ለቁርስ እንዲደርሱ ማልደው ይገቡ ነበር። ከልጆቹ ጋር የተማሩት ወጣቶች ተጋበዙ፤ መጡም፤ እያንዳንዳቸውም እንደ ተለወጡ አምናለሁ። በዚህ ሁኔታ ስለ እነርሱ የነበረው ታላቅ ምኞቱ ተፈጸመ፤ በሰፊው ሕዝብ መካከልም ከጠበቀው እጅግ የበለጠ ሥራ ተሠራ። አቶ ሃርኮርት በዚያን ጊዜ ከሃውተን ሌላ በአጎራባች መንደሮች በርካታ የስብከት ቦታዎች ነበሩት። በሃውተን የተሠራው የዚህ ሥራ መዓዛ ለብዙ ዓመታት ቆየ። አቶ ሃርኮርት በሃውተን በቆየበት ጊዜ ሁሉ በጸሎት በተሞላ ከባቢ፥ በዙሪያውም ልብን የሚያቀልጥ ስሜት እያለ ይሰብክ እንደ ነበር ነገረኝ።

በዚያን ጊዜ በሃውተን ብዙ አልቆየሁም፤ ቢሆንም ለበርካታ ሳምንታት ቆየሁ። ወደ እንግሊዝ እንድመጣ አጥብቀው ከጻፉልኝ ወንድሞች መካከል የበርሚንግሃም ባፕቲስት አገልጋይ የሆነ አቶ ሮ የተባለ ሰው ነበር። እንግሊዝ መሆኔ እንደ ተነገረው ወደ ሃውተን መጣ፤ ስብሰባዎቹን እየተካፈለና ውጤቶቹን እየተመለከተም በርካታ ቀናት አሳለፈ።

በዲሴምበር አጋማሽ ገደማ ሃውተንን ትተን በአቶ ሮ ጉባኤ ውስጥ ለመሥራት ወደ በርሚንግሃም ሄድን። እዚህ እንደ ደረስን ብዙም ሳይቆይ በበርሚንግሃም ከእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ከተለዩት አገልጋዮች ዋናው ከነበረው ከቄስ ጆን ኤንጀል ጄምስ ጋር ተዋወቅን። እርሱ መልካምና ታላቅ ሰው ነበር፤ በዚያች ከተማ፥ እንዲያውም በመላው እንግሊዝ እጅግ ሰፊ ተሰሚነት ነበረው።

የመነቃቃት ትምህርቶቼ በእንግሊዝ ለመጀመሪያ ጊዜ በታተሙ ጊዜ፥ አቶ ጄምስ ትምህርቶቹን እጅግ የሚያመሰግን መግቢያ ጽፎላቸው ነበር። ነገር ግን በርሚንግሃም በደረስሁ ጊዜ፥ አቶ ጄምስ በአገልጋዮች ስብሰባዎችም ሆነ በብዕሩ በይፋ ካመሰገናቸው በኋላ፥ በዚህ በአትላንቲክ ማዶ በአንዳንድ ክበቦች ውስጥ ያሉ ሰዎች፥ በተለይ በእኔ አገልግሎት ሥር የተከሰቱት መነቃቃቶች እጅግ አሳዛኝ ፍጻሜ እንዳገኙ እንደ ነገሩት ተነገረኝ፤ ይህም ወሬ ለእርሱ እጅግ በብዛት ከመቅረቡ የተነሣ፥ ስለ እነዚያ የመነቃቃት ትምህርቶች በመደገፍ በይፋ የተናገረውን መልሶ እንደ ወሰደ ተነገረኝ።

ይሁን እንጂ በበርሚንግሃም ባየኝ ጊዜ የኢንዲፔንደንት አገልጋዮችን በቤቱ ለቁርስ ጠራ፤ እኔም እንድገኝ ጠየቀኝ። በእንግሊዝ ነገሮች የሚከናወኑበት የተለመደው መንገድ ይህ ነው። በቤቱ በተሰበሰብን ጊዜ ቁርሱ ካለቀ በኋላ ለአገልጋይ ወንድሞቹ እንዲህ አላቸው፤ የአገልግሎታቸውን ዓላማ ከመፈጸም እጅግ እየጎደሉ እንደ ሆነ ተሰምቶታል፤ ሕዝቡ ስብሰባ በመካፈሉ፥ የአገልጋዩን ደመወዝ በመክፈሉ፥ የሰንበት ትምህርት ቤቱን በማስቀጠሉና በውጫዊ ብልጽግና በመግፋቱ በጣም ረክተዋል፤ በአብዛኞቹ አብያተ ክርስቲያናት ግን የሚለወጡት እጅግ ጥቂቶች ናቸው፤ ከዚህ ሁሉ በኋላም ሕዝቡ ወደ ጥፋት እየሄደ ነው። በዚያን ጊዜ ሥራዬን ከእርሱ ጋር እየጀመርሁ የነበረው አቶ ሮ፥ በአቶ ጄምስ በራሱ ጉባኤ ውስጥ ከአንድ ሺህ አምስት መቶ ያላነሱ ንስሐ ያልገቡ ኃጢአተኞች እንደ ነበሩ ነገረኝ። በአቶ ጄምስ ቤት በተደረገው ቁርስ ላይ በታላቅ ግለት ተናገረ፤ አንድ ነገር መደረግ እንዳለበትም ገለጸ።

በመጨረሻም አገልጋዮቹ ጥያቄያቸውን ለመፈጸም እንደ ቻልሁ በልዩ ልዩ የኢንዲፔንደንት አብያተ ክርስቲያናት በተራ ስብሰባዎች ለማድረግ ተስማሙ። ነገር ግን ለተወሰኑ ሳምንታት ሥራዬን በአቶ ሮ ጉባኤ ብቻ ወሰንሁ፤ በዚያም ከዚያ በፊት አይተውት የማያውቁት ዓይነት እንቅስቃሴ፥ ብርቱ መነቃቃት ሆነ። መነቃቃቱ በታላቅ ኃይል በጉባኤው መካከል አለፈ፤ ንስሐ ካልገቡት እጅግ ብዙዎቹም ወደ ክርስቶስ ተመለሱ። አቶ ሮ በልቡም በነፍሱም ወደ ሥራው ገባ። መልካምና እውነተኛ ሰው ሆኖ አገኘሁት። በአመለካከቱ ፈጽሞ ቡድንተኛ ወይም ጭፍን አልነበረም፤ ነገር ግን ልቡን ለመለኮታዊ ተጽዕኖ ከፈተ፤ ከልቡ እንደሚሠራ ሰውም ራሱን ለነፍሳት በሚደረግ ድካም አፈሰሰ። ቀን ከቀን በቤተ ክርስቲያኑ የአገልጋዮች ክፍል (ቬስትሪ) ውስጥ ተቀምጦ ሊጠይቁት ከሚመጡት ጠያቂዎች ጋር ይነጋገርና ወደ ክርስቶስ ይመራቸው ነበር። ለብዙ ቀናት ጊዜው ሁሉ ማለት ይቻላል በዚህ ሥራ ተይዞ ነበር። በእንግሊዝ ያሉ ባፕቲስቶች በሙሉ ማለት ይቻላል ክፍት ቁርባንን የሚቀበሉ ስለ ሆኑ፥ የእርሱ ቤተ ክርስቲያን በዚያን ጊዜ በእንግሊዝ ዝግ ቁርባን ከሚከተሉት ጥቂት አብያተ ክርስቲያናት አንዷ ነበረች።

የተለወጡት ሰዎች ቍጥር ከበዛ በኋላ ቤተ ክርስቲያኒቱ አዲሶቹን አማኞች ለአባልነት ለመቀበል መመርመር ጀመረች። ብዙዎችን መረመሩ፤ ቁርባንም ሊያደርጉ ተዘጋጁ። እኔ ጠዋት ሰበክሁ፤ እነርሱም ቁርባናቸውን ከሰዓት በኋላ ሊያደርጉ ነበር። የጠዋቱ አገልግሎት ሲፈጸም አቶ ሮ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለጥቂት ደቂቃዎች እንድትቆይ ጠየቀ። እኔና ባለቤቴ ከጠዋቱ አገልግሎት በኋላ ወጥተን በእንግድነት ወደምናርፍበት ወደ አቶ ሮ ቤት ሄድን። ጥቂት ቆይቶ አቶ ሮ ወደ ቤት መጣ፤ ፊቱ በፈገግታ ተሞልቶ ወደ ክፍላችን ገባና፦ «ቤተ ክርስቲያናችን ምን ያደረገች ይመስላችኋል?» አለ። ልገምት አልቻልሁም፤ እንዲቆዩ በተጠየቁ ጊዜ ምን ሊያደርጉ እንደ ነበር የመጠየቅ ሐሳብ በእውነት ወደ አእምሮዬ አልመጣም ነበርና። እርሱም፦ «አንተንና ወይዘሮ ፊኒን ዛሬ ከሰዓት በኋላ ወደ ቁርባናችን ለመጋበዝ በሙሉ ድምፅ ወስነዋል» ብሎ መለሰ። እንዲህ ባለ አጋጣሚ ዝግ ቁርባናቸው ሊሸከሙት ከሚችሉት በላይ ሆኖባቸው ነበር። ይሁን እንጂ እንደገና ካሰብንበት በኋላ፥ ውሳኔውን በግፊት ውስጥ ሆነው አሳልፈውት ኋላ በመካከላቸው አንዳች ተቃራኒ ስሜትና ጸጸት እንዳያስከትል ብለን ግብዣቸውን ባንቀበል እንደሚሻል ወሰንን፤ በእውነትም ደክመን ስለ ነበር ይቅርታ ጠይቀን በቤት ቀረን።

ማታም እንደገና መስበክ ስለ ነበረብኝ ዕረፍት በማግኘቴ ደስ አለኝ። ብዙም ሳይቆይ በየመስበኪያ መድረኮቻቸው እንድሠራ የአገልጋዮቹን ግብዣ ተቀበልሁ። በየስፍራው ጉባኤዎቹ ጢም ብለው ይሞሉ ነበር፤ ታላቅ መነሣሣት ተቀሰቀሰ፤ ከስብከቱ በኋላ ጠያቂዎች እንዲመጡ በተጋበዙ ጊዜ ወደ ቬስትሪዎቹ የሚሰበሰቡት ሰዎች ቍጥርም ብዙ ነበር። ለትምህርት ወደዚያ እንዲሄዱ ጥሪ በቀረበ ቍጥር ትልልቆቹ ቬስትሪዎቻቸው በጠያቂዎች ጢም ብለው ይሞሉ ነበር። ስለ ዘዴዎች ቢሆን፥ በዚህ አገር የተጠቀምሁባቸውን እነዚያኑ በዚያም ተጠቀምሁ። ስብከት፥ ጸሎት፥ ውይይትና የጠያቂዎች ስብሰባዎች የተጠቀምንባቸው ዘዴዎች ነበሩ።

ነገር ግን አቶ ጄምስ በሥራዬ ተጽዕኖ ላይ የሚያስጠነቅቁ ደብዳቤዎች ከልዩ ልዩ አቅጣጫ እየደረሱት እንደ ነበር ብዙም ሳይቆይ ተረዳሁ። በዚህ በአትላንቲክ ማዶ የሚያውቃቸው ሰዎች ነበሩት፤ ከእነርሱም አንዳንዶቹ፥ እኔ እንደ ተረዳሁት፥ ስለ ተጽዕኖዬ የሚያስጠነቅቁ ደብዳቤዎች ጽፈውለት ነበር። ከዚህም በላይ ከራሱ ካውንቲ ልዩ ልዩ ክፍሎች ያው ግፊት ይደርስበት ነበር። እርሱ ለእኔ እጅግ ግልጽ ነበር፤ ጉዳዩ እንዴት እንደ ሆነም ነገረኝ፤ እኔም ለእርሱ እንዲሁ ግልጽ ሆንሁለት። እንዲህም አልሁት፦ «ወንድም ጄምስ፥ ኃላፊነትህ ታላቅ ነው። ተጽዕኖህ ታላቅ እንደ ሆነ አውቃለሁ፤ እነዚህ ደብዳቤዎችም ስለ እነዚህ ድካሞች ተጽዕኖህንም ኃላፊነትህንም ያሳያሉ። በአመለካከቴ መናፍቅ እንደ ሆንሁ እንድታስብ እየተገፋፋህ ነው። በሰበክሁ ቍጥር ስብከቴን ትሰማለህ፤ ወንጌልን እሰብክ ወይም አልሰብክ እንደ ሆነም ታውቃለህ።»

በሁለት ጥራዝ የታተመውን ሥርዓታዊ ሥነ መለኮቴን ይዤ ሄጄ ነበር። እንዲህም አልሁት፦ «ወንጌል ያልሆነ ነገር ስሰብክ ሰምተሃልን?» እርሱም፦ «አይ፥ ምንም ምንም አልሰማሁም» አለ። እኔም፦ «መልካም፤ እንግዲህ በቤት ላሉት ተማሪዎቼ የማስተምረውና በየስፍራው የምሰብከው ሥርዓታዊ ሥነ መለኮቴ አለኝ፤ እንድታነበውም እፈልጋለሁ» አልሁት። እርሱም ይህን ለማድረግ እጅግ ጓጓ። ብዙም ሳይቆይ እጅግ የተከበረ የሚመስል አንድ ሰው ከምሽት እስከ ምሽት ከእርሱ ጋር ወደ ስብሰባዎቻችን እንደሚመጣ አየሁ። አብረው ስብሰባ ይካፈሉ ነበር፤ ጠያቂዎችን በጠራሁ ጊዜም ወደ ውስጥ ገብተው ቦታ ባገኙበት ቆመው የሚነገረውን ሁሉ ይሰሙ ነበር። ይህ የተከበረ ሰው ማን እንደ ሆነ አላወቅሁም ነበር። ለብዙ ተከታታይ ምሽቶች በዚህ ሁኔታ መጡ፤ ነገር ግን አቶ ጄምስ ከእርሱ ጋር የነበረውን ሰው አላስተዋወቀኝም፤ በእነዚያም ስብሰባዎች ሊያነጋግረኝ ወደ እኔ አልቀረበም።

ነገሮች ለአንድ ወይም ለሁለት ሳምንት በዚህ ሁኔታ ከቀጠሉ በኋላ አቶ ጄምስና የተከበረው ወዳጁ ወደ ማረፊያችን መጡ። ከዶ/ር ሬድፎርድ ጋር አስተዋወቀኝ፤ በዚያው ጊዜም እርሱ ከታወቁት የሥነ መለኮት ሊቃውንታቸው ዋነኛው እንደ ሆነ፥ በራሱ የሥነ መለኮት ማስተዋል ይልቅ በዶ/ር ሬድፎርድ የሥነ መለኮት ማስተዋል የበለጠ እንደሚተማመን፥ ወደ በርሚንግሃም መጥቶ ስብሰባዎቹን እንዲካፈልና በተለይም ሥነ መለኮቴን ከእርሱ ጋር አብሮ እንዲያነብ እንደ ጠየቀው ነገረኝ። ከቀን ወደ ቀን ሲያነቡት እንደ ነበሩና ዶ/ር ሬድፎርድ በአንዳንድ የሥነ መለኮት ነጥቦች ላይ ከእኔ ጋር ሊነጋገር እንደሚወድ ተናገረ። ዶ/ር ሬድፎርድ ትኩረቴን ሊስብባቸው በፈለጋቸው ጥያቄዎች ሁሉ ላይ በሙሉ ነጻነት ተነጋገርን፤ ዶ/ር ሬድፎርድም በግልጽ እንዲህ አለ፦ «ወንድም ጄምስ፥ አቶ ፊኒን በማናቸውም ረገድ ጤናማ ያልሆነ ትምህርት ያለው አድርጌ የምቈጥርበት ምንም ምክንያት አይታየኝም። የሥነ መለኮት ሐሳቦችን የሚገልጽበት የራሱ መንገድ አለው፤ ነገር ግን በማናቸውም መሠረታዊ ነጥብ ከእኛ እንደሚለይ ማየት አልችልም።»

የእንግሊዝና የዌልስ ኮንግሪጌሽናል ኅብረት ያዘጋጀው አንድ ትንሽ መመሪያ መጽሐፍ ይዘው ነበር፤ በውስጡም የሥነ መለኮት አመለካከታቸው በአጭሩ ተገልጾ ይገኝ ነበር። ከዚህ መመሪያ አንዳንድ ክፍሎችን አነበቡልኝ፤ እኔም በተራዬ ጠየቅኋቸው። ማብራሪያቸውን ሰማሁ፤ በመካከላችንም መሠረታዊ ስምምነት እንዳለ ረካሁ።

ዶ/ር ሬድፎርድ በበርሚንግሃም ጥቂት ጊዜ ቈዩ። ከዚያም ወደ ቤታቸው ሄዱ፤ በእኔም ፈቃድ ሲስተማቲክ ቲኦሎጂ የተባለውን የሥነ መለኮት መጽሐፌን ይዘው ሄዱ፤ በጥንቃቄ ከዳር እስከ ዳር አንብበውትም ስለ እርሱ ያላቸውን አመለካከት እንደሚጽፉልኝ ነገሩኝ። በእርግጥም በሥነ መለኮት የተካኑ፥ ምሁርና ክርስቲያን፥ በሚገባ የተማሩ የሥነ መለኮት ሊቅ መሆናቸውን አስተዋልሁ። ስለዚህ የሚታረምና የሚሻሻል፥ ወይም መልሼ የምተወው ነገር ቢኖር እንዲጠቁሙኝ፥ ሥነ መለኮቴን እንዲተቹ ከመፍቀድ አልፌ እጅግ ፈቀድሁ። ይህንንም በጥልቀትና በግልጽነት እንዲያደርጉ ለመንሁአቸው። ወደ ቤታቸው ወስደው ራሳቸውን ለጥልቅ ምርመራው ሰጡ፤ ጥራዞቹንም በትዕግሥትና በትችት ዓይን ከዳር እስከ ዳር አነበቧቸው። ከዚያም በሥነ መለኮት አመለካከቴ እጅግ እንደሚስማሙ የሚገልጽ ደብዳቤ ከእርሳቸው ደረሰኝ፤ ሊጠይቁኝ የሚፈልጓቸው ጥቂት ነጥቦች እንዳሉም ጻፉ፤ ከበርሚንግሃም መውጣት እንደ ቻልሁም ወዲያው መጥቼ እንድሰብክላቸው ተመኙ።

በበርሚንግሃም ሦስት ወር ያህል የቈየሁ ይመስለኛል። በዚያች ከተማ እጅግ ብዙ አስደናቂ የመለወጥ ታሪኮች ነበሩ፤ ይሁን እንጂ አገልጋዮቹ መነቃቃቱን በከተማይቱ ሁሉ ለማስፋፋት አስፈላጊ የሆኑትን መንገዶች በሙሉ ልብ ለመጠቀም በዚያን ጊዜ ራሳቸውን ለማስገዛት አልተዘጋጁም ነበር።

እጅግ የሚያስደንቅ አንድ ታሪክ ስለ ነበረ ትኩረት ልሰጠው እወዳለሁ። በእንግሊዝ ዩኒቴሪያኒዝም መጀመሪያ ያቈጠቈጠውና የተስፋፋው በበርሚንግሃም እንደ ሆነ በዚህ አገር በአብዛኛው የታወቀ ይመስለኛል። በእንግሊዝ ከነበሩት ዋና ዋና የዩኒቴሪያን አገልጋዮች አንዱ፥ ምናልባትም ከመጀመሪያዎቹ አንዱ የነበሩት አረጋዊው ዶ/ር ፕሪስትሊ የኖሩት በዚያ ነበር። የእርሳቸው ጉባኤ እስከዚያን ጊዜ ድረስ በበርሚንግሃም እንዳለ አገኘሁ። ከበርሚንግሃም ከመውጣቴ በፊት አንድ ምሽት በዚህ ጥቅስ ላይ ሰበክሁ፦ «እናንተ አንገተ ደንዳኖች ልባችሁና ጆሮአችሁም ያልተገረዘ፥ እናንተ ሁልጊዜ መንፈስ ቅዱስን ትቃወማላችሁ።» በመጀመሪያ በመንፈስ ቅዱስ አምላክነትና አካልነት ላይ አተኰርሁ። ከዚያም ሰዎች መለኮታዊውን ትምህርት በስንት መንገድና በስንት ነጥብ እንደሚቃወሙ፥ በመንፈስ ቅዱስ ከተወቀሱ በኋላም የራሳቸውን መንገድ መከተላቸውን አጥብቀው እንደሚቀጥሉ፥ በእነዚህም ሁሉ መንፈስ ቅዱስን እየተቃወሙ እንደ ሆኑ ለማሳየት ጣርሁ። ጌታ በዚያች ምሽት እጅግ ልብን የሚመረምር ስብከት እንድሰብክ ነጻነትን ሰጠኝ። ዓላማዬ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ላይ መደገፋቸውን እንደ ምክንያት እያቀረቡ ሳሉ ሁልጊዜ እርሱን እንደሚቃወሙት ማሳየት ነበር።

በእንግሊዝ በሁሉም ስፍራ እንዳገኘሁት ሁሉ በበርሚንግሃምም ትልቁ ትኩረት በመንፈስ ቅዱስ አሠራር ላይ ይደረግ ነበር። ነገር ግን በነፍስ ላይ በቀጥታ በሚሠራው የመንፈስ ግዑዛዊ አሠራርና እርሱ በእርግጥ በሰዎች አእምሮ ላይ በሚያሳድረው ምግባራዊና አሳማኝ ተጽዕኖ መካከል ግልጽ ልዩነት የሚያደርግ የትም አላገኘሁም። ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ በእውነት የተሰማራበትን ሥራ ለሕዝቡ ማሳሰብ፥ ክርስቶስ በዚህ ጉዳይ ያስተማረውን ግልጽ ትምህርት ማብራራት፥ በዚህም ግዑዛዊ አሠራርን መጠበቅ ሳይሆን ራሳቸውን ለአሳማኝ ተጽዕኖው አሳልፈው መስጠትና ትምህርቱን መታዘዝ እንዳለባቸው እንዲያዩ መምራት ብዙ ጊዜ አስፈላጊ ሆኖ አገኘሁት። የዚያ ምሽት ስብከቴ ዓላማም ይኸው ነበር።

ወደ ማረፊያችን ከደረስሁ በኋላ በስብሰባው የነበሩና እንግድነት ወደ ተቀበለን ቤተሰብ የመጡ አንዲት ሴት በጉባኤው መካከል አንድ የዩኒቴሪያን አገልጋይ መኖሩን እንዳዩ ተናገሩ። ያ ለዩኒቴሪያን ሰው ጆሮ እንግዳ ሆኖ ሳይሰማ አልቀረም አልሁ። እርሳቸውም ይጠቅመዋል የሚል ተስፋ እንዳላቸው መለሱ። ከዚህ ብዙም ሳይቆይ፥ በለንደን እያገለገልሁ ሳለሁ፥ በዚያ ስብከት አማካይነት በሃይማኖታዊ ሕይወቱ ስለ ተደረገው ታላቅ ለውጥ የሚተርክ ደብዳቤ ከዚህ አገልጋይ ደረሰኝ። ደብዳቤውን እንደሚከተለው አቀርበዋለሁ፦

ኦገስት 16 ቀን 1850።

የተከበሩና የተወደዱ ጌታዬ ሆይ፦ — ከእንግሊዝ ልትሄዱ መሆኑን ከባነር ጋዜጣ ስለ ተረዳሁ፥ በበርሚንግሃም ስቲልሃውስ ሌን ከሰበካችሁት ስብከት ስላገኘሁት ጥቅም ባለ ዕዳችሁ መሆኔን እያወቅሁ ሳልገልጽላችሁ ብትሄዱ በተወሰነ ደረጃ ውለታ ቢስነት እንደሚሆንብኝ ይሰማኛል። የሰበካችሁት የመጨረሻው ስብከት ይመስለኛል፤ ስለ መንፈስ ቅዱስ መቃወም ነበር፤ ነገር ግን ጥቅሱን ፈጽሞ ላገኘው አልቻልሁም። እንዲያውም እኔን እጅግ ይመለከቱኝ በነበሩት ነጥቦች ተውጬ፥ ከዚያ በኋላ ለሁለት ወይም ለሦስት ቀናት ስለ ጥቅሱ ምንም አላሰብሁም ነበር። ከስብከቱ ያገኘሁትን ጥቅም ትረዱ ዘንድ በዚያን ጊዜ የነበርሁበትን ልዩ ሁኔታ በአጭሩ መተረክ ያስፈልገኛል።

የተማርሁት በኢንዲፔንደንቶች መካከል ለአገልግሎት በሚያዘጋጅ ከመንግሥት ቤተ ክርስቲያን ውጭ ካሉት ኮሌጆቻችን በአንዱ ነበር። ወደ አገልግሎት ገባሁ፤ ሰባት ዓመት ያህልም አገለገልሁ። በዚያ ጊዜ ውስጥ በሥነ መለኮት አመለካከቴ ቀስ በቀስ ታላቅ ለውጥ ደረሰብኝ። ለውጡ የመጣው በከፊል በፍልስፍናዊ ግምቶች፥ በከፊልም በመንፈሳዊ ሁኔታዬ ላይ በደረሰው ውድቀት ይመስለኛል። በጥልቅ ኀዘን እንዲህ ማለት እወዳለሁ፦ በኮሌጅ ቈይታዬ ያጣሁትን እግዚአብሔርን የመምሰል ሕይወቴን ይዞታ ዳግመኛ ፈጽሞ አላገኘሁትም። ለኀዘኖቼ ሁሉ በዋናነት ምክንያቱ ይህ እንደ ሆነ አምናለሁ። ግምቶቼ፥ ዶ/ር ዊልያምስ ስለ መለኮታዊ ሉዓላዊነትና ፍትሐዊነት የጻፉትን መጽሐፍ ገና ሳላነብ፥ በመሠረቱ የእርሳቸውን አመለካከት እንድቀበል መሩኝ። መጽሐፋቸውን ማንበቤም ሥርዓቴን ፍጹም አደረገው። ኃጢአት የእግዚአብሔር ጸጋ ያልተቸረው ፍጡር የግድ ሊጎድለው ከሚችልበት ባሕርይ የሚመነጭ ጉድለት ነው፤ ስለዚህ የሰው ውድቀት የሰውን ዘር የማይቀር የመጀመሪያ አለፍጽምና ከመግለጽ በቀር ሌላ ምንም ትርጉም የለውም። የእግዚአብሔር ምግባራዊ አስተዳደር ታላቁ ግብ ይህን አለፍጽምና በትምህርትና በመገለጥ ማረምና በመጨረሻም የሰውን ሁኔታ ፍጹም ማድረግ ነው። ስለ መንፈሳዊ አሠራር የዶ/ር ጄንኪንን አመለካከት ከዚያ ቀደም ብዬ ከብዙ ጊዜ በፊት ተቀብዬ ነበር።

በእንደዚህ ያሉ መርሆዎች እየተመራሁ፥ እንዴት እንደ ሆነ ማብራራት ሳያስፈልገኝ፥ ኃጢአት ለጊዜው የተፈቀደ ተራ መከራ ብቻ፥ ወይም ይልቁንም ወሰን በሌለው ጥበብና ቸርነት የሚፈወስ የግድ ያለ ክፋት እንደ ሆነብኝ፥ ዘላለማዊ ቅጣት በቸሩ አምላክ አሠራር ውስጥ ለአንዲት አፍታ እንኳ ሊታሰብ የማይገባ ጭካኔ እንደ ሆነብኝ፥ ማስተሰረያም ስለ ኃጢአት በፍልስፍና ባልተደገፈ አመለካከት ላይ የተመሠረተ ፍጹም ከንቱ ነገር እንደ ሆነብኝ ትረዳላችሁ። ሙሉ በሙሉ ዩኒቴሪያን ሆንሁ፤ በ1848 ዓመት መጀመሪያም ዩኒቴሪያንነቴን በይፋ መሰከርሁ፤ የአንድ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይም ሆንሁ። ይሁን እንጂ የአእምሮዬ ዝንባሌ፥ እንደ መታደል ሆኖ፥ በዩኒቴሪያኒዝም ውስጥ ለረጅም ጊዜ እንዳርፍ የማይፈቅድልኝ እጅግ በአመክንዮ የሚጓዝ ነበር። ድምዳሜዎቼን እስከ ተራ ዲዪዝም ድረስ ገፋኋቸው፤ ከዚያም ይበልጥ ወደ ፊት መሄድ እንዳለባቸው አገኘሁ። ለዚህ ግን አልተዘጋጀሁም ነበር። ነፍሴ ሁሉ በድንጋጤ ወደ ኋላ አፈገፈገች። መርሆዎቼን እንደ ገና መረመርሁ። በፍልስፍና ሥርዓቴ ሁሉ ላይ አብዮት ተካሄደ። የኃላፊነት ትምህርት በጣም ጥብቅና ቃል በቃል በሆነው ትርጉሙ ተመለሰልኝ፤ ከእርሱም ጋር ጥልቅ የኃጢአት ግንዛቤ መጣ። ስለ ትግሎቼና ስለ አእምሮ ሥቃዬ ዝርዝሩን ውስጥ መግባት አያስፈልገኝም።

እናንተን ከመስማቴ ሁለት ሳምንት ያህል ቀደም ብሎ፥ አንድ ቀን ወንጌላዊውን ሥርዓት መልሼ መቀበል እንዳለብኝ በግልጽ አየሁ። የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓት መሆኑን ፈጽሞ ተጠራጥሬ አላውቅም ነበር። ዩኒቴሪያን የሆንሁት በንጹሕ የምክንያታዊነት መሠረት ላይ ነበር። አሁን ግን መጽሐፍ ቅዱስን መቀበል ወይም በጨለማ መጥፋት እንዳለብኝ አገኘሁ። የታገሥሁትን የመንፈስ ጭንቀት መገመት ትችላላችሁ። በአንድ በኩል በየዕለቱ እየበረታ የሚሄድ ውስጣዊ እርግጠኝነት ነበር፤ የኃጢአት ስሜትና የክርስቶስ ፍላጎት በልቤ ላይ ይበልጥ ጸንቶ እየያዘ ነበር፤ ደግሞም የማውቀውን እውነት ትምህርት ለማግኘት ወደ እኔ ከሚመለከቱ ሰዎች መከልከል የሚያስከትለው አሳዛኝ ሁኔታ ነበር። በሌላ በኩል ራሴን ብገልጥ፥ በሁሉም ወገኖች ፊት፥ በተለይም ለእንደዚህ ያሉ ትግሎች ምንም ርኅራኄ በሌለው በዚያ ታላቅ አብዛኛው ሕዝብ ፊት፥ በሚታየው ወላዋይነቴ ስሜን ወዲያውኑ አጠፋ ነበር፤ ራሴንም፥ ሚስቴንና ልጆቼንም ወደ ዓለም እጥል ነበር። ይህን አማራጭ ለመቀበል ልቤን ማሳመን አልቻልሁም። መጠበቅን፥ የሕዝቡን አእምሮ ለለውጡ ቀስ በቀስ ማዘጋጀትን፥ ለጥቂት ወራትም ይበልጥ ጥብቅ ቍጠባ በማድረግ በሽግግሩ ወቅት ለምድራዊ ፍላጎቶቻችን መዘጋጀትን ወስኜ ነበር። በዚህ የአእምሮ ሁኔታ ሳለሁ ስብከታችሁን ሰማሁ። ታስታውሱታላችሁ፤ ያስከተለውንም ውጤት በቀላሉ ትረዳላችሁ። የመከራከሪያዎቻችሁ እውነትነት ተሰማኝ። ልመናዎቻችሁ ልቤን ሊቋቋሙት በማይቻል ኃይል ነኩት፤ በዚያችም ሌሊት ወደ ቤቴ ስመለስ በመንገድ ላይ፥ የሚመጣው ቢመጣ፥ ደሙን ማክበር በቅርቡ ለተማርሁትና ክብሩን ለማዋረድ ብዙ ላደረግሁት ለዚያ አዳኝ ራሴን ወዲያውኑ እንደ ገና ለመቀደስ በእግዚአብሔር ፊት ተሳልሁ።

ውጤቱም፥ በአቶ —— ደግ ድጋፍ፥ በቅርቡ በዚህ ከተማ ያለችው ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ሆኛለሁ። አሁን የማገኘው የአእምሮ ሰላም በእርግጥ አእምሮን ሁሉ ያልፋል። ከዚህ ቀደም በአገልግሎት ሥራ እንደዚህ ያለ ልብን የሚመስጥ ደስታ ፈጽሞ አግኝቼ አላውቅም። ጳውሎስ «ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው» ሲል የተናገረውን ትርጉም ሙሉ በሙሉ እረዳዋለሁ። ስለዚህ ስማችሁ በነፍሴ ውስጥ በምን ያህል የምስጋና ስሜት እንደሚታሰብ ልነግራችሁ አልችልም። እናንተን እንድሰማ ላመጣኝ ለደጉ መግቦት እግዚአብሔርን እባርካለሁ። አሁን ሳስበው፥ እናንተን ባልሰማ ኖሮ፥ አዲስ የነቃው ሃይማኖታዊ ሕይወቴ ጥልቅ የሆነውን የውስጥ ወቀሳዬን ያለማቋረጥ በመቃወሜ በቅርቡ ይጠፋ እንደ ነበር ከምናልባት የበለጠ እርግጥ ይመስለኛል። ሕሊናዬ እንደ ገና ይደነድን ነበር፤ እኔም በኃጢአቴ እሞት ነበር። በእግዚአብሔር ጸጋ፥ ወደ ፊት እግዚአብሔር ድካሜን በእርሱ ሊያጐናጽፍበት የሚችለውን ማናቸውንም ጠቃሚነት ምንጩ እናንተ እንደ ሆናችሁ እቈጥራለሁ፤ የድካማችሁን የዚህን ፍሬ ዕውቀት ከእናንተ መከልከልም ፍትሕ የጐደለው እንደሚሆን ይሰማኛል። እግዚአብሔር ወሰን በሌለው ምሕረቱና ጸጋው እስካሁን ከባረካችሁበት ይልቅ እንኳ የበለጠ ጠቃሚነት ያለበትን ረጅም ዕድሜ ይስጣችሁ፤ ይህ የማያቋርጥ ጸሎቴ ይሆናል። የተወደዱ ጌታዬ ሆይ፥ ከልብ የእናንተው፥ ይህን ደብዳቤ በተቀበልሁ ጊዜ በለንደን በዋይትፊልድ አሮጌው ታበርናክል ከቄስ ጆን ካምብል ጋር እያገለገልሁ ነበር። እንዲያነቡት ሰጠኋቸው። በግልጽ በሚታይ ጥልቅ ስሜት አነበቡት፤ ከዚያም «እነሆ፥ ለዚህ ብቻ እንኳ ወደ እንግሊዝ መምጣት ይገባ ነበር!» ብለው ጮኹ።

ከበርሚንግሃም ወደ ዉስተር ሄድሁ፤ በማርች አጋማሽ ገደማ ይመስለኛል፤ ከዶ/ር ሬድፎርድ ጋር ለማገልገል ነበር። ሲስተማቲክ ቲኦሎጂዬን እንዳነበቡና በአንዳንድ ነጥቦች ላይ ከእኔ ጋር መነጋገር እንደሚፈልጉ እንደ ጻፉልኝ ቀደም ብዬ ተናግሬአለሁ። ለታተሙት ልዩ ልዩ ትችቶች የሰጠኋቸውን መልሶች ይዤ ነበር፤ እነዚህንም ለዶ/ር ሬድፎርድ ሰጠኋቸው። ከዳር እስከ ዳር አነበቧቸው፤ ከዚያም መጥተው አዩኝና «እነዚህ መልሶች ልንነጋገርባቸው የፈለግኋቸውን ጥያቄዎች ሁሉ አጥርተዋቸዋል፤ ስለዚህ እናንተ ትክክል እንደ ሆናችሁ ሙሉ በሙሉ ረክቻለሁ» አሉኝ። ከዚያ በኋላ፥ እኔ እስከማስታውሰው ድረስ፥ በየትኛውም የሥነ መለኮት መጽሐፌ ክፍል ላይ አንድም ጊዜ ትችት አልሰነዘሩም። የዚያን መጽሐፍ የእንግሊዝ እትም ያዩ ሰዎች ለክርስቲያኑ ሕዝብ ያመሰገኑበትን መቅድም እንደ ጻፉለት ያውቃሉ።

በምጠቅሰው በዚያ ጊዜ፥ ማለትም ለእነዚያ ግምገማዎች የሰጠኋቸውን መልሶች አንብበው በጨረሱበት ጊዜ፥ መጽሐፉ በእንግሊዝ ወዲያውኑ እንዲታተም ጽኑ ፍላጎት ገለጹ፤ መጽሐፉ በዚያ እጅግ እንደሚያስፈልግና ታላቅ መልካም ነገር እንደሚያደርግ እንደሚያስቡም ተናገሩ። በእንግሊዝ በሥነ መለኮት ጥያቄዎች ላይ የእርሳቸው አስተያየት ታላቅ ክብደት ነበረው። ዶ/ር ሬድፎርድ በአውሮፓ ከሁሉ የላቁ የሥነ መለኮት ሊቅ እንደ ሆኑ ዶ/ር ካምብል በጋዜጣቸው አረጋግጠው እንደ ጻፉ አስታውሳለሁ። በዉስተር ብዙ ሳምንታት ቈየሁ፤ ለዶ/ር ሬድፎርድና በዚያች ከተማ ላለ አንድ የባፕቲስት ጉባኤም ሰበክሁ። እጅግ አስደናቂ የሆኑ ብዙ የመለወጥ ታሪኮች ነበሩ፤ ሥራውም በእርግጥ የሚያስደስት ነበር።

በዉስተር የነበሩ አንዳንድ ባለጸጋ ሰዎች እንደሚከተለው ያለ ሐሳብ አቀረቡልኝ። ተንቀሳቃሽ ታበርናክል፥ ማለትም የአምልኮ ቤት ለመሥራት አሰቡ፤ ፈርሶ በባቡር ሐዲድ ከቦታ ቦታ የሚጓጓዝና በጥቂት ወጪ ከወንበሮቹና ከአምልኮ ቤት ዕቃዎቹ ሁሉ ጋር እንደ ገና የሚተከል ነበር። በእያንዳንዱ ጎኑ መቶ ሃምሳ ጫማ የሆነ ካሬ አድርገው፥ ለአምስት ወይም ለስድስት ሺህ ሰዎች እንዲበቁ የተሠሩ ወንበሮች ያሉት አድርገው ሊሠሩት አሰቡ። እኔ ልጠቀምበትና ሁኔታዎች እንደሚጠይቁት ከቦታ ቦታ እየሄድሁ ለስድስት ወር በውስጡ ልሰብክ ብስማማ የሚሠራበትን ወጪ እነርሱ እንደሚሸፍኑ ተናገሩ። በዚያ ስፍራ የነበሩትን አገልጋዮች ባማከርሁ ጊዜ ግን እንዳላደርገው መከሩኝ። እነዚያ ሰዎች ባቀረቡት መንገድ ራሴን ችዬ በእንግሊዝ ሁሉ እየዞርሁ ከመስበክ ይልቅ፥ በልዩ ልዩ የእንግሊዝ ክፍሎች ቀድሞውኑ በተቋቋሙት ጉባኤዎች መስበኪያ መድረኮች ላይ ማገልገሌ የበለጠ ጠቃሚ እንደሚሆን አሰቡ።

አገልጋዮቹ በአጠቃላይ በዚያን ጊዜ እጅግ አዲስ የነበረውን እንዲህ ያለውን አካሄድ እንደማይደግፉ ለማመን ምክንያት ስለ ነበረኝ፥ ታበርናክሉን ለመጠቀም ቃል ከመግባት ተቈጠብሁ። ከዚያ ወዲህ ግን ምናልባት ስሕተት ሠርቼ እንደ ሆነ አስቤአለሁ፤ ምክንያቱም የኢንዲፔንደንት አብያተ ክርስቲያናትን ጉባኤዎችና የሕዝብ አምልኮ ስፍራዎች ባወቅኋቸው ጊዜ፥ በአብዛኛው እጅግ ትናንሽ፥ አየር በሚገባ የማይገባባቸው፥ በማይመች ሁኔታ የተቀመጡ፥ በቤተ ክርስቲያን — በእርግጥ የመንግሥት ቤተ ክርስቲያንን ማለቴ ነው — እጅግ የታጠሩና የተወሰኑ ሆነው አገኘኋቸው፤ ስለዚህም ትክክል መሆኔ ከዚያ ወዲህ አጠራጣሪ መስሎ ታይቶኛል፤ በአጠቃላይ ሲታይ፥ የራሴን የአምልኮ ስፍራ እንደ ተሸከምሁ ያህል ይዤ፥ ወደ ፈለግሁበት እየሄድሁ፥ የቤተ እምነት ልዩነት ሳይገድበኝ ብዙኃኑን ሕዝብ ለመሰብሰብ ዝግጅት ባደርግ ኖሮ በእንግሊዝ እጅግ የበለጠ መልካም ነገር ልፈጽም እችል ነበር የሚል አስተያየት ስላለኝ ነው። ኃይሌ አሁን በዚያን ጊዜ እንደ ነበረው ቢሆን ኖሮ፥ እንግሊዝን እንደ ገና ለመጎብኘትና እንደዚያ ያለውን ሙከራ ለማድረግ ጽኑ ዝንባሌ ይኖረኝ ነበር። ዶ/ር ሬድፎርድ በዉስተር በተደረገው ሥራ እጅግ ተነኩ፤ በለንደን በተደረጉት የሜይ ዓመታዊ ስብሰባዎችም ለእንግሊዝና ለዌልስ ኮንግሪጌሽናል ኅብረት ንግግር አደረጉ፤ ስለዚህም ሥራ እጅግ የሚማርክ ዘገባ ሰጡ። በለንደን ከዶ/ር ጆን ካምብል ጋር ማገልገል ልጀምር ስለ ነበርሁ በእነዚያ የሜይ ስብሰባዎች ተገኘሁ።

ዶ/ር ካምብል የዋይትፊልድ ተተኪ ነበሩ፤ በለንደን ፊንስበሪ በሚገኘው ታበርናክል ያለችው ቤተ ክርስቲያንና የቶተንሃም ኮርት ሮድ ቤተ ጸሎት እረኛ ነበሩ። እነዚህ ሁለቱም ቤተ ጸሎቶች በለንደን ውስጥ ሲሆኑ፥ በመካከላቸው ሦስት ማይል ያህል ርቀት አለ። የተሠሩት ለአቶ ዋይትፊልድ ሲሆን እርሱም ለብዙ ዓመታት አገልግሎባቸዋል። ዶ/ር ካምብል በዚያን ጊዜ የብሪቲሽ ባነር፥ የክርስቲያን ዊትነስና የአንድ ወይም የሁለት ሌሎች መጽሔቶችም አዘጋጅ ነበሩ። ድምፃቸው በሚገባ ስለማይፈቅድላቸው አይሰብኩም ነበር፤ ጊዜያቸውን ለእነዚያ ጋዜጦች ዝግጅት ሰጡ። ዋይትፊልድ በኖረበት የካህን መኖሪያ ቤት ይኖሩ ነበር፤ ዋይትፊልድ ይጠቀምበት የነበረውንም ቤተ መጻሕፍት ይጠቀሙ እንደ ነበር አምናለሁ። የዋይትፊልድ ሥዕል በታበርናክሉ በሚገኘው የጥናት ክፍላቸው ተሰቅሎ ነበር። የስሙ መዓዛ አሁንም በዚያ ነበር፤ ይሁን እንጂ በእርሱ ላይ የነበረው መንፈስ እኔ ወደዚያ በሄድሁበት ጊዜ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ብዙም አይታይም ነበር ማለት አለብኝ። ዶ/ር ካምብል አይሰብኩም ነበር ብያለሁ። አሁንም እረኝነቱን ይዘው፥ በካህኑ መኖሪያ ቤት እየኖሩ ደመወዙንም እየተቀበሉ ነበር፤ ነገር ግን ለሕዝባቸው እንዲሰብኩ ሊቀጠሩ ከሚችሉት እጅግ ተወዳጅ አገልጋዮች መካከል አንዳንዶቹን ለጥቂት ሳምንታት በየተራ በመቅጠር መስበኪያ መድረካቸውን ይሞሉ ነበር። እኔም ሥራዬን በዚያ የጀመርሁት በሜይ መጀመሪያ ላይ ነው። በታበርናክሉ እንደ ነበረው ያለ የማያቋርጥ የአገልጋዮች መለዋወጥ የሚያስከትለውን ውጤት የሚያውቁ ሰዎች በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ሃይማኖት የለመለመ ሁኔታ ላይ ይገኛል ብለው አይጠብቁም።

የዶ/ር ካምብል የአምልኮ ቤት ትልቅ ነበር። ወንበሮቹ ጥቅጥቅ ብለው የተደረደሩ ሲሆን፥ ሙሉ ሦስት ሺህ ሰዎችን ማስተናገድ ይችል ነበር። አንድ ወዳጄ በሙርፊልድስ ወይም በፊንስበሪ የሚገኘው ታበርናክልና ሁሉም ሰው የሰማው ታላቁ ኤክሰተር ሆል ከሁለቱ የትኛው ብዙ ሰዎችን እንደሚይዝ ለማረጋገጥ ልዩ ጥረት አደረገ። ታበርናክሉ ከኤክሰተር ሆል በብዙ መቶዎች የሚበልጡ ሰዎችን እንደሚያስቀምጥ ተረጋገጠ።

ቀዳሚ ቀጣይ